በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕሊናህን ጠብቅ

ሕሊናህን ጠብቅ

ሕሊናህን ጠብቅ

የተዛባ የኮምፒውተር ፕሮግራም እንዳለው በሚታወቅ አውሮፕላን ተሳፍሮ ለመሄድ የሚደፍር ሰው እንደማይኖር የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው የአውሮፕላኑን የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ቢያዛባ ወይም መረጃዎቹን ሆን ብሎ በሐሰት መረጃዎች ቢቀይርስ! ይህ ሁኔታ አንድ አካል በሕሊናህ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እያደረገ ካለው ሙከራ ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል። የምትመራበትን የሥነ ምግባር ደንብ ለማበላሸት ቆርጦ ተነስቷል። ዓላማው ከአምላክ ጋር የሚያጋጭህን ጎዳና እንድትከተል ማድረግ ነው!​—⁠ኢዮብ 2:​2-5፤ ዮሐንስ 8:​44

ለመሆኑ ይህ ክፉ ጠላት ማን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን . . . እርሱም የቀደመው እባብ” ተብሎ ተጠርቷል። (ራእይ 12:​9 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) በኤደን የአትክልት ሥፍራ የሐሰት ምክንያት በማቅረብ ሔዋን ትክክል እንደሆነ የምታውቀውን ነገር ችላ እንድትልና በአምላክ ላይ እንድታምፅ ባግባባት ጊዜ በድርጊት ታይቷል። (ዘፍጥረት 3:​1-6, 16-19) ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሰይጣን ሰዎች በጅምላ የአምላክ ጠላት እንዲሆኑ ለማድረግ የሚገለገልባቸውን የማሳሳቻ ድርጅቶች በሙሉ ሲያቋቁምና ሲመራ ቆይቷል። ከእነዚህ የማሳሳቻ ድርጅቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የሐሰት ሃይማኖት ነው።​—⁠2 ቆሮንቶስ 11:​14, 15

የሐሰት ሃይማኖት ሕሊናን ያበላሻል

የሐሰት ሃይማኖት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ታላቂቱ ባቢሎን ተብላ በምትጠራ ምሳሌያዊ ጋለሞታ ተመስላለች። ትምህርቶቿ የብዙ ሰዎችን የሥነ ምግባር ስሜት በማዛባት ከእነርሱ የተለየ እምነት ያላቸውን ሰዎች እንዲጠሉ አልፎ ተርፎም የጭካኔ ድርጊት እንዲፈጽሙባቸው አድርገዋል። እንዲያውም የራእይ መጽሐፍ እንደሚናገረው አምላክ የራሱን አምላኪዎች ደም ጨምሮ ‘በምድርም ለታረዱ ሁሉ ደም’ በግንባር ቀደምትነት ተጠያቂ የሚያደርገው የሐሰት ሃይማኖትን ነው።​—⁠ራእይ 17:​1-6፤ 18:​3, 24

ኢየሱስ የሐሰት ሃይማኖት የአንዳንዶችን የሥነ ምግባር አቋም ምን ያህል ሊያዛባ እንደሚችል ለደቀ መዛሙርቱ ሲነግራቸው “የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል” ብሏል። እንደነዚህ ያሉት ዓመፀኛ ግለሰቦች በሥነ ምግባር ምንኛ የታወሩ ናቸው! ኢየሱስ “አብንና እኔን ስላላወቁ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 16:​2, 3 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ኢየሱስ እነዚህን ቃላት ተናግሮ ብዙም ሳይቆይ ለሠሩት ወንጀል ሕሊናቸው እንዳይቆረቁራቸው ራሳቸውን ማሳመን በቻሉ አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ገፋፊነት ተገደለ። (ዮሐንስ 11:​47-50) ከዚህ በተቃራኒ ኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮቹ በመካከላቸው ባለው ፍቅር ተለይተው እንደሚታወቁ ተናግሯል። ያም ሆኖ ፍቅራቸው ጠላቶቻቸውን ሳይቀር እስከመውደድ ሰፊ መሆን ነበረበት።​—⁠ማቴዎስ 5:​44-48፤ ዮሐንስ 13:​35

የሐሰት ሃይማኖት የብዙዎችን ሕሊና ያበላሸበት ሌላው መንገድ ብዙሃኑ የሚፈልገውን ዓይነት ሥነ ምግባር በማስተማር ነው። ለዚያውም ሥነ ምግባር የሚባል ነገር ካላቸው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን በተመለከተ ትንቢት ሲናገር “ሕይወት የሚገኝበትን [“ጤናማ፣” NW ] ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፣ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ” ብሏል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 4:​3

በዛሬው ጊዜ የሃይማኖት መሪዎች አምላክ ከጋብቻ ውጪ የሚደረግን የጾታ ግንኙነት አይቃወምም ብለው በማስተማር የሰዎችን ጆሮ ያክካሉ። ሌሎች ደግሞ ግብረሰዶምን በዝምታ ይመለከታሉ። እንዲያውም አንዳንድ ቀሳውስት ራሳቸው ግብረሰዶም የሚፈጽሙ ናቸው። ዘ ታይምስ በተባለ የብሪታኒያ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ርዕስ “ግብረ ሰዶም እንደሚፈጽሙ በግልፅ የሚታወቁ አሥራ ሦስት ቀሳውስት” ለእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ሲኖድ እንደተመረጡ ዘግቧል። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ሥነ ምግባር ችላ ካሉና ቤተ ክርስቲያናቸውም ከዚያ ያለፈ ነገር ካላደረገ ተከታዮቻቸው ምን ዓይነት የአቋም ደረጃ ይከተላሉ ብለን ልንጠብቅ እንችላለን? በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጨርሶ ግራ ቢጋቡ ምንም አያስደንቅም።

በመብራት ምልክቶች በተመሰሉት የሥነ ምግባር ደንቦችና መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረው መንፈሳዊ እውነቶች መመራት ምንኛ የተሻለ ነው! (መዝሙር 43:​3፤ ዮሐንስ 17:​17) ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ አመንዝሮችም ሆኑ ዝሙት የሚሠሩ ሰዎች ‘የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ’ ያስተምራል። (1 ቆሮንቶስ 6:​9, 10) ‘ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው የለወጡ’ ወንዶችና ሴቶች ሥራቸው በአምላክ ፊት “ነውር” እንደሆነ ይነግረናል። (ሮሜ 1:​26, 27, 32) ይህ ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች የፈጠሩት የሥነ ምግባር እውነት አይደለም፤ አምላክ ፈጽሞ የማይሽረው በመንፈስ አነሳሽነት ያስጻፈው የአቋም ደረጃ ነው። (ገላትያ 1:​8፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​16) ሆኖም ሰይጣን ሕሊናን የሚያበላሽበት ሌሎች መንገዶችም አሉት።

በመዝናኛ ረገድ መራጮች ሁኑ

አንድ ሰው መጥፎ ድርጊት እንዲፈጽም ማስገደድ አንድ ነገር ነው፤ መጥፎ ድርጊት የመፈጸም ፍላጎት እንዲያድርበት ማድረግ ግን ከዚያ የከፋ ነው። “የዚህ ዓለም ገዥ” የሆነው የሰይጣን ግብም ይኸው ነው። የረከሰ አስተሳሰቡን ሞኞች በሆኑ ወይም ባልጠረጠሩ ሰዎች በተለይ ደግሞ ይበልጥ ለጥቃት በተጋለጡት ወጣቶች አእምሮና ልብ ውስጥ ለመቅረጽ አጠያያቂ የሆኑ ጽሑፎችን፣ ፊልሞችን፣ ሙዚቃዎችን፣ የኮምፒውተር ጨዋታዎችን እንዲሁም በኢንተርኔት የሚተላለፉ ወሲባዊ ሥዕሎችን በመሰሉ መንገዶች ይጠቀማል።​—⁠ዮሐንስ 14:​30፤ ኤፌሶን 2:​1, 2

ፔዲያትሪክስ በተባለ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ሪፖርት “[በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ] ወጣቶች በየዓመቱ 10, 000 የሚያክሉ የዓመፅ ድርጊቶችን የሚመለከቱ ሲሆን ለልጆች የሚተላለፉ ፕሮግራሞች ደግሞ የበለጠ በጭከና ድርጊቶች የተሞሉ ናቸው” በማለት ይገልጻል። በተጨማሪም ሪፖርቱ “በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች በየዓመቱ 15, 000 የብልግና ፊልሞች፣ የሽሙጥ አነጋገሮችንና ቀልዶችን ይመለከታሉ” በማለት ገልጿል። ብዙ ተመልካች በሚኖርበት ምሽት ላይ የሚተላለፉ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች እንኳን “በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ ከ8 የሚበልጡ የጾታ ግንኙነት ድርጊቶችን የሚያሳዩ ሲሆን ይህም በ1976 ከነበረው በአራት እጥፍ ይበልጣል” በማለት ጠቅሷል። ጥናቱ የሚተላለፉት “ጸያፍ ንግግሮችም በሚያስደንቅ መጠን ጨምረዋል” ብሎ መናገሩ ብዙም የሚያስገርም አይደለም። ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ብዛት ያላቸው ሳይንሳዊ ጥናቶች እነዚህን ፕሮግራሞች አዘውትሮ መመልከት ሰዎችን ይበልጥ እንደሚያበላሿቸው ያስጠነቅቃሉ። ስለዚህ አምላክን ማስደሰትና ራስህን መጥቀም የምትፈልግ ከሆነ “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፣ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና” የሚለውን በምሳሌ 4:​23 ላይ የሚገኘውን ምክር ተከተል።​—⁠ኢሳይያስ 48:​17

በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉ በርካታ ሙዚቃዎችም ሕሊናን ያበላሻሉ። ዘፈኖቹ በብዙ የምዕራባውያን አገሮች የሙዚቃ ሰንጠረዥ የመጀመሪያውን ቦታ አግኝቶ የነበረ አንድ ዘፋኝ “አስደንጋጭ ስሜት ለመፍጠር ልዩ ጥረት” ማድረጉን ዘ ሳንዴይ ሜይል በተባለ የአውስትራሊያ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ሪፖርት አስታውቋል። ጽሑፉ እንደገለጸው “ዘፈኖቹ ዕፅ መውሰድን፣ በሥጋ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸምን የጾታ ግንኙነትና አስገድዶ መድፈርን” የሚያወድሱ ሲሆን “ሚስቱን ገድሎ በድኗን ሐይቅ ውስጥ ስለመጣልም ይዘፍናል።” ጋዜጣው የጠቀሳቸውን ሌሎቹን ግጥሞቹን እዚህ ላይ ለመግለጽ የሚቀፍፉ ናቸው። ሆኖም ዘፈኑ ከፍተኛ የክብር ሽልማት አስገኝቶለታል። ከላይ እንደተጠቀሱ ያሉትን በሙዚቃ ጣፍጠው የቀረቡ መርዛማ ሐሳቦችን በአእምሮህና በልብህ ውስጥ መዝራት ትፈልጋለህ? በዚህ መንገድ የሚመላለሱ ሰዎች ሕሊናቸውን ስለሚያበላሹና ውሎ አድሮ የአምላክ ጠላቶች የሚያደርጋቸው ‘ክፉ ልብ’ በውስጣቸው እንዲፈጠር ስለሚፈቅዱ እንዲህ ማድረግ እንደማትፈልግ የታወቀ ነው።​—⁠ዕብራውያን 3:​12፤ ማቴዎስ 12:​33-35

ስለዚህ መዝናኛን በመምረጥ ረገድ ጠንቃቃ ሁን። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት በጥብቅ ያሳስበናል:- “በቀረውስ፣ ወንድሞች ሆይ፣ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፣ እነዚህን አስቡ።”​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​8

አብረሃቸው የምትውላቸው ሰዎች በሕሊናህ ላይ ተጽእኖ ያሳድራሉ

ኒል እና ፍራንዝ ልጆች ሳሉ ጥሩ ጠባይ ካላቸው ክርስቲያኖች ጋር ቅርርብ ነበራቸው። a ሆኖም ከጊዜ በኋላ “ከመጥፎ ጓደኞች ጋር መዋል ጀመርኩ” በማለት ኒል ይናገራል። ይህም ለወንጀል ድርጊትና ለወኅኒ እንደዳረገው በቁጭት ይናገራል። የፍራንዝ ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም። “በዓለም ካሉ ወጣቶች ጋር ብውል ምንም አልሆንም የሚል አስተሳሰብ አድሮብኝ ነበር” በማለት በሐዘን ይናገራል። “ሆኖም ገላትያ 6:​7 እንደሚናገረው ‘እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳል።’ እኔ መሳሳቴንና ይሖዋ ትክክል መሆኑን የተረዳሁት ከባድ ችግር ውስጥ ከገባሁ በኋላ ነው። በፈጸምኩት ወንጀል ምክንያት የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደብኝ።”

ኒልንና ፍራንዝን የመሰሉ ሰዎች በአንድ ጀንበር ወንጀል እንደማይፈጽሙ የታወቀ ነው። በአንድ ወቅት እንዲህ ያለውን ወንጀል መፈጸም ፈጽሞ የማይታሰብ ነበር። እዚያ ደረጃ ላይ የደረሱት ቀስ በቀስ ሲሆን ብዙውን ጊዜ የመጀመሪያው እርምጃ መጥፎ ጓደኝነት ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:​33) ከዚያም አደገኛ ዕፆችን መውሰድ ወይም ከልክ በላይ አልኮል መጠጣት ሊከተል ይችላል። እንዲያውም ሕሊና “በአልኮል ታጥቦ ሊወሰድ የሚችል የሰው ስብዕና ክፍል ነው” ተብሎ መገለጹ የተገባ ነው። ከዚያ በኋላ ወንጀል ወይም የሥነ ምግባር ብልግና መፈጸም ቀላል ነው።

ታዲያ ለምን የመጀመሪያውን እርምጃ ትወስዳለህ? ከዚህ ይልቅ አምላክን ከልብ ከሚወድዱ አስተዋይ ሰዎች ጋር ተቀራረብ። በትክክል የሚመራህና ከብዙ ሥቃይ የሚታደግ ጠንካራ ሕሊና እንዲኖርህ ይረዱሃል። (ምሳሌ 13:​20) አሁንም በእሥር ላይ የሚገኙት ኒልና ፍራንዝ ሕሊናቸው በደንብ መሰልጠን እንዲያውም ሊንከባከቡት የሚገባ መለኮታዊ ስጦታ መሆኑን ተገንዝበዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከአምላካቸው ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት ብርቱ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። አንተም ጠቢብ በመሆን ከእነርሱ ስህተት ተማር።​—⁠ምሳሌ 22:​3

ሕሊናህን ጠብቅ

ጤናማ ፍርሃትን ጨምሮ ለአምላክ ፍቅርና እምነት ስናዳብር ሕሊናችንን የመጠበቅ ፍላጎት እንዳለን እናሳያለን። (ምሳሌ 8:​13፤ 1 ዮሐንስ 5:​3) እነዚህ ባሕርያት የጎደሉት ሕሊና ሥነ ምግባራዊ ጥንካሬ እንደማይኖረው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል መዝሙር 14:​1 በልባቸው “አምላክ የለም” ስለሚሉ ሰዎች ይናገራል። እንዲህ ያለው የእምነት ማጣት ጠባያቸውን የሚነካው እንዴት ነው? ጥቅሱ በመቀጠል “በሥራቸው ረከሱ፣ ጎሰቈሉ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም” ይላል።

በአምላክ ላይ እውነተኛ እምነት የሌላቸው ሰዎች ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ የጸና ተስፋ አይኖራቸውም። ስለሆነም ሥጋዊ ምኞቶቻቸውን በማርካት ለዛሬ ብቻ መኖር ይፈልጋሉ። ፍልስፍናቸው “ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ” የሚል ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:​32) በሌላ በኩል ግን ትኩረታቸውን በዘላለም ሕይወት ሽልማት ላይ ያደረጉ ሰዎች ብልጭ ብሎ በሚጠፋ የዓለም ደስታ አይዘናጉም። የሰለጠነው ሕሊናቸው በትክክል እንደሚሠራ የበረራ ኮምፒውተር ከአምላክ የታማኝነት ጎዳና ዝንፍ ሳይሉ መጓዛቸውን እንዲቀጥሉ ይረዳቸዋል።​—⁠ፊልጵስዩስ 3:​8

ሕሊናህ በሙሉ ኃይሉ በትክክል መሥራቱን እንዲቀጥል ከተፈለገ ከአምላክ ቃል ዘወትር መመሪያ ማግኘት ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ መመሪያ የሚገኝበትን መንገድ በሥዕላዊ ሁኔታ ሲገልጽ “ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ:- መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ” በማለት ይናገራል። (ኢሳይያስ 30:​21) ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ለማንበብ ጊዜ መድብ። ይህም ትክክል የሆነውን ለማድረግ ትግል በምታደርግበት ወይም ስጋት በሚሰማህና በጭንቀት በምትዋጥበት ጊዜ ጥንካሬና ብርታት እንድታገኝ ይረዳሃል። ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ የምትተማመን ከሆነ በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ እንደሚመራህ እርግጠኛ ሁን። አዎን “ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ፤ በቀኜ ነውና አልታወክም” በማለት የጻፈውን መዝሙራዊ ምሳሌ ኮርጅ።​—⁠መዝሙር 16:​8፤ 55:​22

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሞቹ ተቀይረዋል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ታላቂቱ ባቢሎን” ተብላ የተገለጸችው የሐሰት ሃይማኖት ለብዙ ሰዎች ሕሊና መደነዝ ተጠያቂ ናት

[ምንጭ]

ቄሱ ወታደሮችን ሲባርኩ:- U.S. Army photo

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዓመፅ ድርጊትንና የሥነ ምግባር ብልግናን መመልከት ሕሊናህን ይጎዳዋል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአምላክ ቃል ዘወትር መመሪያ ማግኘት ሕሊናህን ይጠብቅልሃል