በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ትዕግሥትን ልበሱ”

“ትዕግሥትን ልበሱ”

“ትዕግሥትን ልበሱ”

“ርኅራኄን፣ . . . ትዕግሥትን ልበሱ።”​—⁠ቆላስይስ 3:12

1. ትዕግሥት በማሳየት ረገድ አንድ ግሩም ምሳሌ ጥቀስ።

 በደቡባዊ ምዕራብ ፈረንሳይ የሚኖረው ሬዢ በ1952 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። ባለቤቱ ይሖዋን ማገልገሉን ለማስቆም ለበርካታ ዓመታት ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች። የሞተር ብስክሌቱን ጎማ በማስተንፈስ ከስብሰባ ለማስቀረት ሞክራለች፤ እንዲያውም በአንድ ወቅት ከቤት ወደ ቤት እየሄደ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በሚሰብክበት ጊዜ እየተከተለች የመንግሥቱን ምሥራች ለቤት ባለቤቶች ሲናገር ታፌዝበት ነበር። ሬዢ እንዲህ ያለ የማያቋርጥ ተቃውሞ ቢደርስበትም ትዕግሥት ማሳየቱን አላቆመም። ይሖዋ ሁሉም አገልጋዮቹ ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ትዕግሥት እንዲያሳዩ ስለሚጠብቅባቸው ሬዢ ለሁሉም ክርስቲያኖች ግሩም ምሳሌ ይሆናል።

2. “ትዕግሥት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ ምንድን ነው? ቃሉስ ምን ያመለክታል?

2 “ትዕግሥት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “የመንፈስ ርዝማኔ” ማለት ነው። በእንግሊዝኛ የተዘጋጀው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ይህን ቃል አሥር ጊዜ “መቻል፣” ሦስት ጊዜ “ትዕግሥት፣” አንድ ጊዜ ደግሞ “ትዕግሥት ማሳየት” በማለት ተርጉሞታል። “ትዕግሥት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡም ሆነ የግሪክኛው ቃል ታጋሽ፣ ቻይና ለቁጣ የዘገዩ መሆን የሚል ሐሳብም ያስተላልፋል።

3. ክርስቲያኖች ለትዕግሥት ያላቸው አመለካከት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ግሪካውያን ከነበራቸው አመለካከት የሚለየው እንዴት ነው?

3 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ግሪካውያን ትዕግሥት ማሳየትን እንደ መልካም ምግባር አድርገው አይመለከቱትም ነበር። የኢስጦይክ ፈላስፎች ጭራሽ ቃሉን እንኳ አይጠቀሙም ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ዊሊያም ባርክሌይ እንደተናገሩት ትዕግሥት ማሳየት “ከግሪካውያን የሥነ ምግባር ደንብ ፈጽሞ የሚቃረን” ሲሆን “ማንኛውንም ዓይነት ስድብ ወይም ጥቃት ታግሠው የሚያልፉ አለመሆናቸው” ያኮራቸው ነበር። ጨምረውም “ለግሪካውያን ትልቅ ሰው የሚባለው የተቻለውን ሁሉ አድርጎ የሚበቀልን ሰው ሲሆን በክርስቲያኖች ዘንድ ግን ትልቅ ሰው የሚባለው ሁኔታው የሚፈቅድለት እንኳ ቢሆን ከመበቀል የሚቆጠብ ሰው ነው።” ግሪካውያን ትዕግሥት ማሳየትን የድክመት ምልክት እንደሆነ አድርገው ሊመለከቱት የሚችሉ ቢሆንም ሌሎች ጉዳዮችን ጨምሮ እዚህም ላይ “ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፣ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 1:25

ትዕግሥተኛ በመሆን ረገድ ክርስቶስ ያሳየው ምሳሌ

4, 5. ኢየሱስ ምን ድንቅ የትዕግሥት ምሳሌ አሳይቷል?

4 ትዕግሥት በማሳየት ረገድ ከይሖዋ ቀጥሎ ክርስቶስ ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ኢየሱስ በከባድ ተጽዕኖ ሥር በነበረ ጊዜ በሚያስደንቅ መንገድ ስሜቱን ተቆጣጥሯል። ስለ እርሱ እንዲህ ተብሎ ተተንብዮአል:- “ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፣ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።”​—⁠ኢሳይያስ 53:7

5 ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ ያሳየው የትዕግሥት ባሕርይ ምንኛ የሚያስደንቅ ነው! የጠላቶቹን መሠሪ ጥያቄዎችና የተቃዋሚዎቹን ስድብ በጽናት ተቋቁሟል። (ማቴዎስ 22:15-46፤ 1 ጴጥሮስ 2:23) ደቀ መዛሙርቱ ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሆነ አለማቋረጥ ይጨቃጨቁ በነበረበት ጊዜ ሁሉ ትዕግሥት አሳይቷቸዋል። (ማርቆስ 9:33-37፤ 10:35-45፤ ሉቃስ 22:24-27) ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት ምሽት ‘እንዲተጉ’ ከነገራቸው በኋላ ጴጥሮስና ዮሐንስ ተኝተው ባገኛቸው ጊዜ ያሳየው ራስን የመግዛት መንፈስ ምንኛ የሚደነቅ ነው!​—⁠ማቴዎስ 26:36-41

6. ጳውሎስ ከኢየሱስ ትዕግሥት የተጠቀመው እንዴት ነው? ከዚህ ምን እንማራለን?

6 ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላም ትዕግሥት ከማሳየት አልተቆጠበም። ቀደም ሲል ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ጉዳይ ከማንም በበለጠ ያውቀዋል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ፤ ስለዚህ ግን፣ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግሥቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ፣ ምሕረትን አገኘሁ።” (1 ጢሞቴዎስ 1:15, 16) ቀደም ሲል እንከተለው የነበረው አኗኗር ምንም ይሁን ምን በኢየሱስ እስካመንን ድረስ ለእኛም ትዕግሥቱን የሚያሳየን ቢሆንም እንኳ “ለንስሐ የሚገባ ፍሬ” እንድናፈራ ይጠብቅብናል። (ሥራ 26:20፤ ሮሜ 2:4) ክርስቶስ በትንሿ እስያ ይገኙ ለነበሩ ሰባት ጉባኤዎች የላከው መልእክት ታጋሽ መሆኑን ብቻ ሳይሆን የባሕርይ ለውጥ እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸው እንደነበረም ያሳያል።​—⁠ራእይ ምዕራፍ 2 እና 3

የመንፈስ ፍሬ

7. በትዕግሥትና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው?

7 ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ 5ኛ ምዕራፍ ላይ የሥጋ ሥራን ከመንፈስ ፍሬ ጋር አነጻጽሯል። (ገላትያ 5:19-23) ከይሖዋ ባሕርያት መካከል አንዱ ትዕግሥት እንደመሆኑ መጠን የዚህ ባሕርይ ምንጭ እርሱ ሲሆን የመንፈሱ ፍሬ ነው። (ዘጸአት 34:6, 7) ጳውሎስ “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ . . . ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት” በማለት ባሰፈረው የመንፈስ ፍሬ ዝርዝር ውስጥ ትዕ​ግሥትን በአራተኛ ቦታ አስቀምጦታል። (ገላትያ 5:22, 23) ስለዚህ የአምላክ አገልጋዮች መለኮታዊውን ትዕግሥት እንዲያንጸባርቁ የሚገፋፋቸው መንፈስ ቅዱስ ነው።

8. ትዕግሥትን ጨምሮ በጠቅላላ የመንፈስ ፍሬዎችን እንድናፈራ የሚያስችለን ምንድን ነው?

8 ይህ ሲባል ግን ይሖዋ መንፈሱን አስገድዶ ይሰጣል ማለት አይደለም። መንፈስ ቅዱስ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን አለብን። (2 ቆሮንቶስ 3:17፤ ኤፌሶን 4:30) በምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ፍሬዎቹን በማፍራት መንፈሱ በሕይወታችን ላይ እንዲሠራ እንፈቅዳለን። ጳውሎስ የሥጋ ሥራዎችንና የመንፈስ ፍሬን ከዘረዘረ በኋላ “በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ። አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፣ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል” በማለት ጨምሮ ተናግሯል። (ገላትያ 5:25፤ 6:7, 8) ትዕግሥትን በማዳበር ረገድ እንዲሳካልን ከፈለግን ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የሚያፈሯቸውን የተቀሩትን የመንፈስ ፍሬዎች ማፍራት አለብን።

“ፍቅር ይታገሣል”

9. ጳውሎስ “ፍቅር ይታገሣል” በማለት ለክርስቲያኖች የተናገረው ለምን ሊሆን ይችላል?

9 ጳውሎስ “ፍቅር ይታገሣል” ብሎ ሲናገር ፍቅርና ትዕግሥት እርስ በርስ የተሳሰሩ ባሕርያት መሆናቸውን አመልክቷል። (1 ቆሮንቶስ 13:4) አልበርት ባርንዝ የተባሉ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንደተናገሩት ጳውሎስ ይህን ጠበቅ አድርጎ እንዲገልጽ ያስገደደው ምክንያት ቆሮንቶስ በሚገኘው ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ንትርክና ጭቅጭቅ ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:11, 12) ባርንዝ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “እዚህ ላይ [ትዕግሥትን ለማመልከት] የገባው ቃል ቸኩሎ እርምጃ ከመውሰድ፣ በስሜት ገንፍሎ ከመናገርና አስተያየት ከመስጠት እንዲሁም ከግልፍተኝነት የሚቃረን ነው። የሚያስጨንቅ ወይም የሚያበሳጭ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ለረዥም ጊዜ ችሎ የመኖርን ሐሳብ የሚያስተላልፍ ነው።” ፍቅርና ትዕግሥት የክርስቲያን ጉባኤን ሰላም በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።

10. (ሀ) ፍቅር ታጋሽ እንድንሆን የሚረዳን በምን መንገድ ነው? ይህን በተመለከተ ጳውሎስ ምን ምክር ሰጥቷል? (ለ) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የአምላክን ትዕግሥትና ደግነት በማስመልከት ምን ሐሳብ ሰጥተዋል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

10 “ፍቅር ይታገሣል፣ ቸርነትንም [“ደግነትም፣” NW ] ያደርጋል፤ ፍቅር . . . የራሱንም አይፈልግም፣ አይበሳጭም።” ስለዚህ ፍቅር በብዙ መንገዶች ታጋሽ እንድንሆን ይረዳናል። a (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5) ፍቅር እርስ በርስ በትዕግሥት ተቻችለን እንድንኖር፣ ሁላችንም ፍጹማን አለመሆናችንንና ስህተት ልንሠራ እንደምንችል እንድናስታውስ ይረዳናል። ለሌሎች አሳቢና ይቅር ባይ እንድንሆን ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ” በማለት ያበረታታናል።​—⁠ኤፌሶን 4:1-3

11. በተለይ ክርስቲያኖች አንድ ላይ በሚኖሩበት ወይም በሚሠሩበት ቦታ ትዕግሥት ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

11 እንደ ጉባኤ፣ ቤቴል ቤቶች፣ ሚስዮናውያን ቤቶች፣ የግንባታ ቡድን ወይም ኮርስ የሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች ባሉ ክርስቲያኖች በሕብረት በሚኖሩባቸውና በሚሠሩባቸው ቦታዎች ሁሉ አንዱ ለሌላው ትዕግሥት ማሳየቱ ሰላምና ደስታ እንዲሰፍን ያደርጋል። የጠባይ፣ የምርጫ፣ የአስተዳደግ፣ የግብረ ገብ ደንቦችና ሌላው ቀርቶ በንጽሕና አጠባበቅ ረገድ ያሉት ልዩነቶች አልፎ አልፎ የሚያበሳጩ ሁኔታዎችን ሊፈጥሩ ይችላሉ። በቤተሰብ ውስጥም እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ለቁጣ የዘገዩ መሆን እጅግ አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 14:29፤ 15:18፤ 19:11) የተሻለ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ተስፋ በማድረግ ሁሉም ትዕግሥት ማሳየታቸው አስፈላጊ ነው።​—⁠ሮሜ 15:1-6

ትዕግሥት እንድንጸና ይረዳናል

12. አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ ትዕግሥት ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

12 ትዕግሥት፣ መጨረሻ ወይም መፍትሔ ያላቸው የማይመስሉ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ እንድንጸና ይረዳናል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው የሬዢ ሁኔታ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነበር። ባለቤቱ ይሖዋን እንዳያገለግል ለዓመታት ስትቃወመው ኖራለች። የሆነ ሆኖ አንድ ቀን እያለቀሰች ወደ እርሱ መጣችና “ይህ እውነት መሆኑን አውቃለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እፈልጋለሁ፤ እባክህ እርዳኝ” አለችው። ከጊዜ በኋላ እርሷም ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆናለች። ሬዢ “ይሖዋ በትግል፣ በትዕግሥትና በጽናት የተሞሉትን እነዚያን ዓመታት እንደባረካቸው ይህ ማስረጃ ይሆናል” ብሏል። ትዕግሥት ማሳየቱ ክሶታል።

13. ጳውሎስ እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? እኛም መጽናት እንችል ዘንድ የእርሱ ምሳሌ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

13 ወደ መጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ መለስ ስንል ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ ትዕግሥት በማሳየት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ነው። (2 ቆሮንቶስ 6:3-10፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:16) ሊሞት ተቃርቦ ሳለ ለወጣት ጓደኛው ለጢሞቴዎስ ምክር በለገሰው ጊዜ ሁሉም ክርስቲያኖች መከራ እንደሚደርስባቸው አስጠንቅቆታል። ጳውሎስ የራሱን ምሳሌ በመጥቀስ ለጽናት አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ የሆኑ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ዘርዝሮለታል። እንዲህ ሲል ጻፈ:- “አንተ ግን ትምህርቴንና አካሄዴን አሳቤንም እምነቴንም ትዕግሥቴንም ፍቅሬንም መጽናቴንም ስደቴንም መከራዬንም ተከተልህ፤ በአንጾኪያና በኢቆንዮን በልስጥራንም የሆነብኝን የታገሥሁትንም ስደት ታውቃለህ፤ ጌታም ከሁሉ አዳነኝ። በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:10-12፤ ሥራ 13:49-51፤ 14:19-22) ለመጽናት ሁላችንም እምነት፣ ፍቅርና ትዕግሥት ሊኖረን ይገባል።

ትዕግሥትን ልበሱ

14. ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ ትዕግሥት ያሉትን አምላካዊ ባሕርያት ከምን ጋር አመሳስሏቸዋል? ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ምን ምክር ሰጣቸው?

14 ሐዋርያው ጳውሎስ ትዕግሥትንና ሌሎች አምላካዊ ባሕርያትን ክርስቲያኖች ‘የአሮጌው ሰው’ መለያ የሆኑትን ድርጊቶች አውልቀው ካስወገዱ በኋላ ሊለብሱት ከሚገባቸው ልብስ ጋር አመሳስሏቸዋል። (ቆላስይስ 3:5-10) እንዲህ በማለት ጻፈ:- “እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፣ ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።”​—⁠ቆላስይስ 3:12-14

15. ክርስቲያኖች ትዕግሥትንና ሌሎች አምላካዊ ባሕርያትን እንደ ልብስ ‘መልበሳቸው’ ምን ውጤት ያስገኛል?

15 የጉባኤ አባላት ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትንና ፍቅርን እንደ ልብስ ‘ሲለብሱ’ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላቸዋል እንዲሁም በይሖዋ አገልግሎት ወደፊት እንዲገፉ ይረዳቸዋል። በተለይ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ትዕግሥተኞች መሆን ይኖርባቸዋል። አልፎ አልፎ ለክርስቲያኖች ምክር እንዲለግሱ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ሆኖም ይህን ለማድረግ የተለያዩ መንገዶችን ሊጠቀሙ ይችላሉ። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ “እየታገሥህና እያስተማርህ፣ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም” በማለት ከሁሉ የተሻለውን ባሕርይ ጠቅሷል። (2 ጢሞቴዎስ 4:2) አዎን፣ የይሖዋ በጎች ሁልጊዜ በትዕግሥት፣ በአክብሮትና በርኅራኄ መያዝ ይኖርባቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 7:12፤ 11:28፤ ሥራ 20:28, 29፤ ሮሜ 12:10

“ሰውን ሁሉ ታገሡ”

16. ‘ሰውን ሁሉ መታገሣችን’ ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?

16 አምላክ ለሰው ዘር ትዕግሥት ማሳየቱ እኛም ‘ሰውን ሁሉ እንድንታገሥ’ ግድ ይለናል። (1 ተሰሎንቄ 5:14) ይህም የይሖዋ ምሥክር ላልሆኑ የቤተሰብ አባላት፣ ለጎረቤቶች፣ ለሥራ ባልደረቦችና በትምህርት ቤት አብረውን ለሚማሩ ታጋሽ መሆን ማለት ነው። ብዙ ምሥክሮች አብረዋቸው ከሚሠሩት ወይም ከሚማሩት የሚደርስባቸውን ትችት ወይም ቀጥተኛ ተቃውሞ አንዳንድ ጊዜም ለበርካታ ዓመታት ችለው በመኖር በእነርሱ ላይ የሚሰነዘረውን መሠረተ ቢስ ጥላቻ ለማርገብ ችለዋል። (ቆላስይስ 4:5, 6) ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፣ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፣ በሚጐበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን።”​—⁠1 ጴጥሮስ 2:12

17. ይሖዋን በፍቅሩና በትዕግሥቱ ልንመስለው የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረግ ያለብንስ ለምንድን ነው?

17 የይሖዋ ትዕግሥት በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች መዳንን ያስገኛል። (2 ጴጥሮስ 3:9, 15) ይሖዋን በፍቅሩና በትዕግሥቱ የምንመስለው ከሆነ የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩና ለክርስቶስ ንጉሣዊ አገዛዝ ራሳቸውን ማስገዛት ይችሉ ዘንድ ሰዎችን በማስተማሩ ሥራ መካፈላችንን እንቀጥላለን። (ማቴዎስ 28:18-20፤ ማርቆስ 13:10) መስበካችንን አቆምን ማለት የይሖዋን ትዕግሥት እንደመገደብ ሊቆጠር የሚችል ከመሆኑም በላይ ሰዎችን ወደ ንስሐ ለማድረስ ያለውን ዓላማ መገንዘብ እንደተሳነን ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።​—⁠ሮሜ 2:4

18. ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች የሚጸልየው ምን ነበር?

18 ጳውሎስ በትንሿ እስያ በቆላስይስ ይኖሩ ለነበሩ ክርስቲያኖች በላከው ደብዳቤ ላይ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ስለዚሁ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን የፈቃዱ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን፣ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም፤ በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጋችሁ፣ ከደስታም ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ እንደ ክብሩ ጒልበት መጠን በኃይል ሁሉ እየበረታችሁ፣ በቅዱሳንም ርስት በብርሃን እንድንካፈል ያበቃንን አብን እያመሰገናችሁ፣ በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን።”​—⁠ቆላስይስ 1:9-12

19, 20. (ሀ) ይሖዋ የሚያሳየውን ትዕግሥት እንደ ፈተና አድርገን ከመመልከት መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ትዕግሥተኞች መሆናችን ምን ጥቅሞች ያስገኛል?

19 “ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ” የይሖዋ ፈቃድ ሲሆን እኛም በዚህ ‘የፈቃዱ ትክክለኛ እውቀት ከተሞላን’ ይሖዋ የሚያሳየው ትዕግሥት ፈተና አይሆንብንም። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) በተለይ ‘የመንግሥቱን ወንጌል በመስበክ’ ‘በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እናፈራለን።’ (ማቴዎስ 24:14) ይህን በታማኝነት ማድረጋችንን ከቀጠልን “ከደስታም ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ” እንችል ዘንድ ‘በኃይል ሁሉ ያበረታናል።’ እንዲህ ስናደርግ ‘እንደሚገባ እንመላለሳለን’ እንዲሁም ‘በነገር ሁሉ እርሱን ደስ እያሰኘን’ እንዳለን ማወቃችን ሰላም ያስገኝልናል።

20 ይሖዋ በትዕግሥቱ አማካኝነት ባሳየው ጥበብ ሙሉ በሙሉ የምናምን እንሁን። ለእኛም ሆነ ለስብከታችን እንዲሁም ለትምህርታችን ጆሯቸውን ለሚሰጡ ሰዎች መዳንን ያመጣል። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) እንደ ፍቅር፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ የዋህነትና ራስን መግዛት የመሰሉትን የመንፈስ ፍሬዎች ማፍራታችን በትዕግሥት እንድንደሰት ያደርጉናል። ከቤተሰብ አባሎቻችን ጋርም ሆነ ጉባኤ ካሉት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በተሻለ መንገድ በሰላም እንድንኖር ያስችለናል። ቻይ መሆናችን አብረውን ለሚሠሩ ወይም አብረውን ለሚማሩ ትዕግሥት እንድናሳያቸው ይረዳናል። በተጨማሪም የምናሳየው ትዕግሥት ዓላማ ያለው ማለትም መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙትን የሚያድንና ታጋሽ የሆነውን አምላክ ይሖዋን የሚያስከብር ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ጎርደን ዲ ፌ የተባሉ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር “ፍቅር ይታገሣል ቸርነትንም ያደርጋል” በማለት ጳውሎስ በሰጠው ሐሳብ ላይ አስተያየታቸውን ሲገልጹ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “በጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት መሠረት እነዚህ ባሕርያት [ትዕግሥትና ደግነት] አምላክ የሰው ልጆችን የሚመለከትባቸው ሁለት ገጽታዎች ናቸው። (ከሮሜ 2:​4 ጋር አወዳድር።) አምላክ ዓመፀኛ በሆኑት ሰዎች ላይ ቁጣውን ከማውረድ በታቀበ ጊዜ በአንድ በኩል ፍቅራዊ ትዕግሥቱ ታይቷል። በሌላ በኩል ደግሞ ምሕረቱ በተገለጠባቸው በሺህ በሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ ደግ መሆኑ ታይቷል። በዚህም የተነሳ ጳውሎስ ስለ ፍቅር ማብራሪያ ሲሰጥ ስለ አምላክ ሁለት መግለጫዎችን ሰጥቷል። አንደኛው በክርስቶስ አማካኝነት ትዕግሥት ማሳየቱንና በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መለኮታዊ የፍርድ ቅጣት ሊቀበሉ ለሚገባቸው ሰዎች ደግ መሆኑን አሳይቷል።”

ልታብራራ ትችላለህ?

• ክርስቶስ ትዕግሥትን በማሳየት ረገድ ድንቅ ምሳሌ የሚሆነው በምን መንገዶች ነው?

• ትዕግሥትን ለማዳበር ምን ይረዳናል?

• ትዕግሥት ቤተሰብን፣ ክርስቲያኖችንና ሽማግሌዎችን የሚረዳው እንዴት ነው?

• ትዕግሥተኞች መሆናችን ለእኛም ሆነ ለሌሎች ጥቅም የሚያመጣው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በከባድ ተጽእኖ ሥር እያለም እንኳ ደቀ መዛሙርቱን በትዕግሥት ይዟቸዋል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ከወንድሞች ጋር ባላቸው ግንኙነት ትዕግሥት በማሳየት ረገድ ጥሩ ምሳሌ እንዲሆኑ ተመክረዋል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋን በፍቅሩና በትዕግሥቱ የምንመስለው ከሆነ ምሥራቹን መስበካችንን እንቀጥላለን

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ ክርስቲያኖች ‘በደስታ የሚታገሡ’ እንዲሆኑ ጸልዮአል