በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሠለጠነ ሕሊና ያስፈልግሃል

የሠለጠነ ሕሊና ያስፈልግሃል

የሠለጠነ ሕሊና ያስፈልግሃል

በኒው ዚላንድ አየር መንገድ አውሮፕላን በበረራ ቁጥር 901 ተሳፍረው ወደ አንታርክቲካ የሚጓዙ መንገደኞችና ሠራተኞች የማይረሳ ዕለት ያሳልፋሉ ተብሎ ታስቦ ነበር። አስደናቂ ውበት የተላበሰውን ነጭ አሕጉር ግሩም ዕይታ ለማግኘት DC-10 አውሮፕላን ዝቅ ብሎ መብረር ሲጀምር ሁሉም መንገደኞች በደስታ ተውጠው ፎቶ ግራፍ ማንሻቸውን ማስተካከል ጀመሩ።

የ15 ዓመታት የሥራ ልምድ ያለው የአውሮፕላኑ አብራሪ 11, 000 የበረራ ሰዓት አስመዝግቧል። አብራሪው በረራ ከመጀመሩ በፊት የበረራ መረጃውን በአውሮፕላኑ ኮምፒውተር ውስጥ መዘገበ። ይህንን ሲያደርግ ግን የተሰጠው አቅጣጫ መጠቆሚያ መረጃ የተሳሳተ መሆኑን አላወቀም ነበር። ይህ DC-10 አውሮፕላን ከ2, 000 ጫማ ከፍታ በታች ደመናውን እየሰነጠቀ በመብረር ላይ እያለ ከኢረበስ ተራራ ግርጌ ጋር ተጋጭቶ በውስጡ የነበሩት 257 ሰዎች በሙሉ አለቁ።

አውሮፕላኖች በሰማይ ላይ ለመብረር ኮምፒውተሮች በሚሰጧቸው መመሪያዎች ላይ እንደሚታመኑ ሁሉ ሰዎችም በሕይወት መንገድ በሚያደርጉት ጉዞ እንዲመራቸው ሕሊና ተሰጥቷቸዋል። በበረራ ቁጥር 901 ላይ የደረሰው አሰቃቂ አደጋ ስለ ሕሊናችን ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል ለአስተማማኝ በረራ በትክክል የሚሠሩ የበረራ መሣሪያዎችና ቋሚ ምልክቶች እንደሚያስፈልጉ ሁሉ የእኛም መንፈሳዊ፣ ሥነ ምግባራዊ ሌላው ቀርቶ አካላዊ ደህንነታችን ቋሚና ትክክለኛ በሆኑ የሥነ ምግባር ደንቦች በሚመራ ሕሊና ላይ የተመካ ነው።

የሚያሳዝነው ግን ዛሬ ባለው ዓለም ውስጥ እንደነዚህ ያሉት የሥነ ምግባር ደንቦች እየጠፉ ወይም ችላ እየተባሉ ነው። አንዲት አሜሪካዊት አስተማሪ እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “በዛሬው ጊዜ ማሙሽ ማንበብ ስለ አለመቻሉ፣ መጻፍ ስለ አለመቻሉ እንዲሁም በካርታ ላይ ፈረንሳይ የምትገኝበትን ቦታ ለይቶ ለማሳየት ስላለበት ችግር ሲነገር በየጊዜው እንሰማለን። በተጨማሪም ማሙሽ ትክክልና ስህተት የሆነውን ለመለየት የሚቸገር መሆኑም እውነት ነው። ማንበብና መጻፍ አለመቻሉ እና ሒሳብ መሥራት የማይችል መሆኑ ብቻ ሳይሆን በሥነ ምግባር ረገድ ግራ የሚጋባ መሆኑም ካለበት ትምህርት ነክ ከሆኑት ችግሮቹ መካከል መደመር ይኖርበታል።” አክለው ሲናገሩ “የዛሬ ወጣቶች የሥነ ምግባር ትርጉም በጠፋበት ዓለም ውስጥ ይኖራሉ። እስቲ አንዱን የትኛው ‘ትክክል’ የትኛው ደግሞ ‘ስህተት’ እንደሆነ እንዲነግራችሁ ጠይቁት፤ ወዲያውኑ ግራ ሲገባው፣ የሚለው ጠፍቶት ምላሱ ሲተሳሰር፣ ሲደነግጥና ስጋት ሲያድርበት ትመለከታላችሁ። . . . ይህ ግራ መጋባት ኮሌጅ ከገባ በኋላም ከመሻሻል ይልቅ ይበልጥ እየተባባሰ ይሄዳል” ብለዋል።

የዚህ ግራ መጋባት መንሥዔ ጥሩ ሥነ ምግባር እንደየሰዉ ወይም እንደየባሕሉ ሁኔታ ይለያያል የሚለው በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው ሥነ ምግባር አንጻራዊ ነው የሚለው አመለካከት ነው። የአውሮፕላን አብራሪዎች ቋሚ በሆኑ ምልክቶች ሳይሆን በሚወዛወዙ አልፎ ተርፎም አንዳንድ ጊዜ ከቦታቸው እልም ብለው በሚጠፉ ምልክቶች እየተመሩ የሚያበርሩ ቢሆን ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስብ! በኢረበስ ተራራ ላይ እንደደረሰው ዓይነት አሰቃቂ አደጋዎች በተደጋጋሚ እንደሚከሰቱ ምንም ጥርጥር የለውም። በተመሳሳይም ዓለም የማይለዋወጡ የሥነ ምግባር የአቋም ደረጃዎችን ሳይከተል በመቅረቱ ምክንያት ዘግናኝ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ መከራና ሞትን እያጨደ ነው። ለትዳር ጓደኛ ታማኝ ባለመሆን ምክንያት ቤተሰቦች ይፈርሳሉ፤ እንዲሁም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በኤድስ ወይም በጾታ ግንኙነት በሚተላለፍ ሌላ በሽታ የሥቃይ ኑሮ ይገፋሉ።

ሥነ ምግባር አንጻራዊ ነው የሚለው አመለካከት እንደ ስልጣኔ ይታይ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እንዲህ ያለውን አመለካከት የሚያራምዱ ሰዎች “ቀኛቸውንና ግራቸውን” መለየት እንዳልቻሉት በጥንቷ ነነዌ እንደነበሩት ሰዎች ናቸው። ይህን አመለካከት የሚከተሉ ሁሉ “ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ” ይሉ ከነበሩት ከሃዲ እስራኤላውያን በምንም አይለዩም።​—⁠ዮናስ 4:​11፤ ኢሳይያስ 5:​20

ታዲያ አስተማማኝ መምሪያ ይሆንልን ዘንድ ሕሊናችንን የሚያሠለጥንልን ግልጽና የማያሻማ ሕግ እንዲሁም መሠረታዊ ሥርዓት ለማግኘት ወደየት ዞር ልንል እንችላለን? በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ፍላጎት አጥጋቢ በሆነ መንገድ የሚያሟላ ሆኖ አግኝተውታል። መጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ምግባርን፣ ለሥራ ሊኖረን የሚገባንን አመለካከት፣ ልጆችን ስለ ማሠልጠንና አምላክን እንዴት ማምለክ እንዳለብን ጨምሮ የማይዳስሰው ርዕስ የለም። (2 ጢሞቴዎስ 3:​16) ባለፉት ብዙ ዘመናት ሁሉ ፍጹም እምነት የሚጣልበት መጽሐፍ መሆኑ ተረጋግጧል። የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር የአቋም ደረጃዎች ያወጣው በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ ከፍተኛ ባለ ሥልጣን የሆነው ፈጣሪያችን ስለሆነ ለሁሉም የሰው ዘር የሚሠሩ ናቸው። ስለሆነም ሥነ ምግባርን በተመለከተ ግራ በተጋባ ሁኔታ የምንኖርበት ምክንያት የለም።

ይሁን እንጂ ሕሊናህ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ጥቃት እየተሰነዘረበት ነው። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ሕሊናህን መጠበቅ የምትችለውስ እንዴት ነው? በመጀመሪያ ጥቃቱን እየሰነዘረ ያለው ማን እንደሆነና የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች ማወቁ ከሁሉ የተሻለ ነው። እነዚህም በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ይብራራሉ።