በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ያድናል—እንዴት?

ኢየሱስ ያድናል—እንዴት?

ኢየሱስ ያድናል​—⁠እንዴት?

“ኢየሱስ ያድናል!” “ኢየሱስ አዳኛችን ነው!” በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ብዙ አገሮች ውስጥ እንዲህ ያሉት መልእክቶች በሕንፃ ግድግዳዎችና ሕዝብ በሚበዛባቸው ሌሎች ቦታዎች ተጽፈው ይታያሉ። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ኢየሱስ አዳኛቸው እንደሆነ ከልባቸው ያምናሉ። “ኢየሱስ የሚያድነን እንዴት ነው?” ብለህ ብትጠይቃቸው ምናልባት “ኢየሱስ ለእኛ ሲል ሞቷል” ወይም “ኢየሱስ ለኃጢአታችን ሲል ሞቷል” በማለት ይመልሱልህ ይሆናል። አዎን፣ የኢየሱስ ሞት መዳን የምንችልበትን መንገድ ከፍቶልናል። ይሁን እንጂ የአንድ ሰው ሞት እንዴት የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸፍን ይችላል? “የኢየሱስ ሞት ሊያድነን የሚችለው እንዴት ነው?” ተብለህ ብትጠየቅ ምን ብለህ ትመልሳለህ?

መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ በጣም ቀላል ሆኖም ግልጽና ብዙ ትርጉም ያዘለ ነው። ይሁን እንጂ ትርጉሙን ለመረዳት በመጀመሪያ የኢየሱስ ሕይወትና ሞት ለአንድ ከባድ ችግር መፍትሔ ያስገኘው እንዴት እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል። የኢየሱስ ሞት ስላለው ከፍተኛ ዋጋ በቂ ግንዛቤ ማግኘት የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው።

አምላክ፣ ኢየሱስ ሕይወቱን እንዲሰጥ ሲያደርግ በአዳም ኃጢአት ምክንያት የተነሳው ችግር መፍትሄ የሚያገኝበትን መንገድ ማበጀቱ ነው። አዳም የሠራው ኃጢአት ያስከተለው ጥፋት ምንኛ ከባድ ነበር! የመጀመሪያው ሰውና ሚስቱ ሔዋን ፍጹማን ነበሩ። የሚኖሩት ውብ በሆነ የኤደን የአትክልት ስፍራ ነበር። አምላክ መኖሪያቸውን የመንከባከብ ትርጉም ያለው ሥራ ሰጥቷቸው ነበር። በምድር ላይ የሚገኙ ሌሎች ሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ የመግዛት ሥልጣን ተሰጥቷቸው ነበር። እንዲሁም ሰዎች ተባዝተው ምድር በሚልዮን በሚቆጠሩ መሰሎቻቸው ስትሞላ ገነትን እስከ ምድር ዳር ድረስ ማስፋት ይችሉ ነበር። (ዘፍጥረት 1:​28) የተሰጣቸው ሥራ ምንኛ አስደሳችና አስደናቂ ነበር! ከዚህም በተጨማሪ እርስ በርሳቸው ሞቅ ያለ ወዳጃዊ ቅርርብ ነበራቸው። (ዘፍጥረት 2:​18) የጎደለባቸው ምንም ነገር አልነበረም። ደስታ የሞላበት የዘላለም ሕይወት ከፊታቸው ተዘርግቶላቸው ነበር።

አዳም ወይም ሔዋን ኃጢአት ይሠራሉ ብሎ ማሰብ በጣም ይከብድ ነበር። ሆኖም የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ፈጣሪያቸው በሆነው በይሖዋ አምላክ ላይ ዓመፁ። መንፈሳዊ ፍጡር የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን በማታለል የይሖዋን ትእዛዝ እንድትጥስ አደረጋት። አዳምም የእርሷን ፈለግ ተከተለ።​—⁠ዘፍጥረት 3:​1-6

ፈጣሪ በአዳምና በሔዋን ላይ ስለሚወስደው እርምጃ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የሚፈጥር ነገር አልነበረም። ቀድሞውኑም ቢሆን አለመታዘዝ የሚያስከትለውን መዘዝ ግልጽ አድርጓል። “ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና” በማለት ተናግሯል። (ዘፍጥረት 2:16, 17) አሁን አንድ አንገብጋቢ ጥያቄ መልስ ማግኘት ይኖርበታል።

የሰው ዘር ከባድ ችግር ውስጥ ገባ

የመጀመሪያው ኃጢአት የሰውን ዘር ከባድ አዘቅት ውስጥ ከቶታል። አዳም ሲፈጠር ፍጹም ሰው ነበር። ስለዚህም ልጆቹ በፍጽምና ለዘላለም መኖር ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ አዳም ልጅ ከመውለዱ በፊት ኃጢአት ሠራ። አዳም “ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፣ ወደ አፈርም ትመለሳለህ” የሚል ፍርድ በተበየነበት ጊዜ መላው የሰው ዘር በአብራኩ ውስጥ ነበር። (ዘፍጥረት 3:​19) ስለዚህ አዳም ኃጢአት ሠርቶ ልክ አምላክ እንደተናገረው መሞት ሲጀምር እርሱን ጨምሮ መላው የሰው ዘር የሞት ፍርድ ተበይኖበት ነበር።

ሐዋርያው ጳውሎስ ቆየት ብሎ እንደሚከተለው ሲል መጻፉ የተገባ ነበር:- “ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።” (ሮሜ 5:​12) አዎን፣ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይዘው በፍጽምና መወለድ የነበረባቸው ልጆች በመጀመሪያው ኃጢአት ምክንያት የሚታመሙ፣ የሚያረጁና የሚሞቱ ሆነው ተወለዱ።

አንድ ሰው “ይህ ግን ፍትኃዊ አይደለም” ሊል ይችላል። “አምላክን ላለመታዘዝ የመረጠው አዳም እንጂ እኛ አይደለንም። ታዲያ ለዘላለም በደስታ የመኖር ተስፋችንን የምናጣው ለምንድን ነው?” አንድ የሕግ ችሎት መኪና የሰረቀው አባትዬው ሆኖ ሳለ ልጁን እስር ቤት ቢያስገባ ልጁ “ይህ ፍትኃዊ አይደለም! እኔ ምንም አላጠፋሁም” በማለት አቤቱታውን በትክክል ማቅረብ እንደሚችል እናውቃለን።​—⁠ዘዳግም 24:​16

ሰይጣን የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ኃጢአት እንዲሠሩ በማድረግ አምላክን አጣብቂኝ ውስጥ መክተት እንደሚችል ሆኖ ተሰምቶት ይሆናል። ሰይጣን በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ማለትም አንድም ልጅ ከመወለዱ በፊት ጥቃት ሰነዘረ። አዳም ኃጢአት በሠራበት ቅጽበት የተነሳው አንገብጋቢ ጥያቄ “ይሖዋ አዳምና ሔዋን ለሚወልዷቸው ልጆች ምን ያደርጋል?” የሚል ነበር።

ይሖዋ አምላክ ፍትኃዊና ተገቢ የሆነ እርምጃ ወስዷል። ጻድቁ ኤሊሁ “ክፋትን ያደርግ ዘንድ ከእግዚአብሔር፣ በደልንም ይሠራ ዘንድ ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 34:​10) እንዲሁም ነቢዩ ሙሴ ይሖዋን አስመልክቶ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና [“ፍትህ ያለበት፣” NW ] ነው፤ የታመነ አምላክ፣ ክፋትም የሌለበት፣ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው።” (ዘዳግም 32:​4) እውነተኛው አምላክ በአዳም ኃጢአት ምክንያት ለተፈጠረው ችግር ያዘጋጀው መፍትሔ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋችንን የሚያሳጣ አይደለም።

አምላክ ፍጹም መፍትሔ አዘጋጀ

አምላክ በሰይጣን ላይ ፍርድ ሲበይን በተናገራቸው ቃላት ውስጥ የተካተተውን መፍትሔ ተመልከት። ይሖዋ ለሰይጣን እንዲህ አለው:- “በአንተና በሴቲቱ [በአምላክ ሰማያዊ ድርጅት] መካከል፣ በዘርህና [በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው ዓለም] በዘርዋም [በኢየሱስ ክርስቶስ] መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን [ሰይጣንን] ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ [የኢየሱስ ሞት]።” (ዘፍጥረት 3:​15) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው በዚህ የመጀመሪያ ትንቢት መሠረት ይሖዋ መንፈሳዊ ልጁ ወደ ምድር በመምጣት ፍጹም ሰው ሆኖ እንዲኖርና በኋላም እንዲሞት ማለትም ሰኮናው እንዲቀጠቀጥ ዓላማ እንደነበረው አሳይቷል።

አምላክ አንድ ፍጹም ሰው እንዲሞት የፈለገው ለምንድን ነው? አዳም ኃጢአት ከሠራ የሚደርስበትን ቅጣት በተመለከተ ይሖዋ አምላክ ምን ብሎት ነበር? ትሞታለህ ብሎት አልነበረምን? (ዘፍጥረት 2:​16, 17) ሐዋርያው ጳውሎስ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው” በማለት ጽፏል። (ሮሜ 6:​23) አዳም የሠራው ኃጢአት የገዛ ራሱን ሕይወት አስከፍሎታል። ሕይወት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ኃጢአት ለመሥራት መረጠ። ስለዚህም አዳም ለሠራው ኃጢአት በሞት ተቀጥቷል። (ዘፍጥረት 3:​19) ታዲያ በአዳም ኃጢአት ምክንያት በመላው የሰው ዘር ላይ ስለተበየነው የሞት ኩነኔስ ምን ለማለት ይቻላል? ከኃጢአታቸው እንዲላቀቁ ለማድረግ አንድ ሰው መሞት ነበረበት። ታዲያ የመላውን የሰው ዘር ኃጢአት በትክክል ሊሸፍን የሚችለው የማን ሞት ብቻ ነው?

አምላክ ለጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ የሰጠው ሕግ “ሕይወት በሕይወት” እንዲከፈል ይጠይቅ ነበር። (ዘጸአት 21:​23) በዚህ ሕጋዊ መሠረታዊ ሥርዓት መሠረት የሰውን ዘር ኃጢአት ለመሸፈን የሚከፈለው ዋጋ አዳም ካጣው ጋር ተመጣጣኝ መሆን ይኖርበታል። የኃጢአትን ደመወዝ ሊከፍል የሚችለው የአንድ ሌላ ፍጹም ሰው ሞት ብቻ ነው። ኢየሱስ ደግሞ ይህን ማድረግ የሚችል ሰው ነበር። በእርግጥም ኢየሱስ ሊዋጅ የሚችለውን ሁሉንም የአዳም ዘር ለማዳን የተከፈለ “ተመጣጣኝ ቤዛ” ነው።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 2:​6 NW፤ ሮሜ 5:16, 17

የኢየሱስ ሞት ከፍተኛ ዋጋ አለው

የአዳም ሞት ምንም ዋጋ አልነበረውም። ለሠራው ኃጢአት መሞት ይገባው ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የሞተው ኃጢአት ሳይኖርበት በመሆኑ የእርሱ ሞት ከፍተኛ ዋጋ አለው። ስለዚህ ይሖዋ አምላክ ታዛዥ ለሆነው ለኃጢአተኛው የአዳም ዘር ቤዛ ሆኖ የተከፈለው የኢየሱስ ፍጹም ሕይወት ያለውን ዋጋ መቀበል ይችላል። እንዲሁም የኢየሱስ መሥዋዕት ዋጋ ላለፉ ኃጢአቶች ይቅርታ በማስገኘት ብቻ የተወሰነ አይደለም። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ምንም ዓይነት የወደፊት ተስፋ አይኖረንም ነበር። በኃጢአት የተወለድን በመሆናችን እንደገና ኃጢአት መሥራታችን አይቀርም። (መዝሙር 51:​5) የኢየሱስ ሞት ይሖዋ አምላክ በመጀመሪያ ለአዳምና ለሔዋን ልጆች አስቦት ወደነበረው ፍጽምና የመድረስ አጋጣሚ ስለሚሰጠን ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን ይገባል!

አዳም ፈጽሞ ልንከፍለው በማንችለው ከፍተኛ ዕዳ (ኃጢአት) ውስጥ ከትቶን ከሞተ አባት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በሌላው በኩል ግን ኢየሱስ፣ ከተዘፈቅንበት ዕዳ ነፃ የሚያወጣንን ብቻ ሳይሆን ለዘላለም ለመኖር የሚያስችለንን በቂ ሃብት አውርሶን እንደሞተ አባት ነው። የኢየሱስ ሞት ያለፈ ኃጢአታችንን የሚያስተሰርይ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ ሕይወታችን የተደረገ አስደናቂ ዝግጅት ጭምር ነው።

ኢየሱስ ለእኛ ብሎ የሞተ በመሆኑ ያድነናል። የኢየሱስ ሞት ምንኛ ዋጋ ያለው ዝግጅት ነው! ይህ ዝግጅት የአዳም ኃጢአት ያስከተለውን የተወሳሰበ ችግር ለመፍታት አምላክ ከተጠቀመባቸው ዘዴዎች መካከል አንዱ እንደሆነ አድርገን ከተመለከትነው በይሖዋና ነገሮችን በሚያከናውንባቸው መንገዶች ላይ ያለን እምነት ይጠነክራል። አዎን፣ የኢየሱስ ሞት “በእርሱ የሚያምን ሁሉ” ከኃጢአት፣ ከህመም፣ ከእርጅና እና ከሞት ጭምር መዳን የሚችልበትን አጋጣሚ ከፍቷል። (ዮሐንስ 3:​16) አምላክ እኛን ለማዳን እንዲህ ያለ ፍቅራዊ ዝግጅት በማድረጉ አመ​ስጋኝ አይደለህም?

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዳም በመላው የሰው ዘር ላይ ኃጢአትንና ሞትን አምጥቷል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ለችግሩ ትክክለኛ መፍትሔ አዘጋጅቷል