በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመዳን ተስፋ ይኖር ይሆን?

የመዳን ተስፋ ይኖር ይሆን?

የመዳን ተስፋ ይኖር ይሆን?

ሃያኛው መቶ ዘመን የሰው ልጅ ከኖረባቸው ዘመናት ሁሉ የከፋ ደም መፋሰስ የታየበት ዘመን ተብሎ ሲጠራ ቆይቷል። በተለይ ደግሞ ካለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ወዲህ ወንጀል፣ ጦርነት፣ የጎሳ ብጥብጥ፣ አደገኛ ዕፆችን መውሰድ፣ እምነት አጉዳይነት፣ ጭቆናና ዓመፅ በጣም ተስፋፍተው ይገኛሉ። ከዚህም በተጨማሪ በሽታ፣ እርጅናና ሞት የሚያስከትሉትን ሕመምና ሥቃይ አስብ። በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ተንሰራፍተው ከሚገኙት ትላልቅ ችግሮች መገላገል የማይናፍቅ ማን አለ? የወደፊቱን ጊዜ ስንመለከት የመዳን ተስፋ ይኖር ይሆን?

ከዛሬ 2, 000 ዓመት ገደማ በፊት ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲያይ ተደርጎ የነበረውን ራእይ ልብ በል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።” (ራእይ 21:​3, 4) ነቢዩ ኢሳይያስም በተመሳሳይ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፣ የሕዝቡንም ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።”​—⁠ኢሳይያስ 25:​8

አምላክ የገባቸው ተስፋዎች ፍጻሜ ምን ማለት እንደሚሆን አስብ! የሰው ዘር ከጭቆናና ከዓመፅ ብሎም መከራና ስቃይ ከሚያስከትሉ ነገሮች በሙሉ ይላቀቃል ወይም ነጻ ይወጣል። እንዲያውም ሕመም፣ የዕድሜ መግፋትም ሆነ ሞት ከሚያስከትሉት ሥቃይ እንገላገላለን! የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ፍጹም ሁኔታዎች በሰፈኑበት ምድር ላይ ስለሚገኝ የዘላለም ሕይወት ይናገራል። (ሉቃስ 23:​43፤ ዮሐንስ 17:​3) ይህን ተስፋ ለማግኘት የሚመኙ ሁሉ ሊያገኙት ይችላሉ። ‘የአምላክ ፈቃድ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ ነው።’​—⁠1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4

ይሁን እንጂ አምላክ ከገባቸው ተስፋዎች ጥቅም ማግኘት ከፈለግን በመዳናችን ረገድ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚጫወተውን ሚና መገንዘብና በእርሱ ላይ እምነት ማሳደር ይኖርብናል። ኢየሱስ ራሱ እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐንስ 3:​16) ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ረገድ የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና ጎላ አድርጎ ሲገልጽ “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” በማለት ተናግሯል። (ሥራ 4:​12) ሐዋርያው ጳውሎስና ጓደኛው ሲላስ ከቅን ልቦና ተነሳስቶ ጥያቄ ላቀረበላቸው ሰው “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን፣ አንተና ቤተ ሰዎችህም ትድናላችሁ” በማለት መልሰውለታል።​—⁠ሥራ 16:​30, 31

አዎን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ “የሕይወት መገኛ” ሲሆን መዳን የሚቻለው በእርሱ በኩል ብቻ ነው። (ሥራ 3:​15 አ.መ.ት) ይሁን እንጂ እኛን በማዳን ረገድ አንድ ሰው ይሄን ያህል ቁልፍ ሚና ሊጫወት የሚችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ በዚህ ረገድ የሚጫወተውን ሚና በግልጽ መገንዘባችን የመዳን ተስፋችንን ሊያጠነክርልን ይገባል።

[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ገጽ 3:- ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች:- USAF photo; ረሃብ ያጠቃቸው ልጆች:- UNITED NATIONS/J. FRAND; በእሳት የሚጋየው የጦር መርከብ:- U.S. Navy photo