በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኖኅ እምነት ዓለምን ይኮንናል

የኖኅ እምነት ዓለምን ይኮንናል

የኖኅ እምነት ዓለምን ይኮንናል

ምድር አቀፍ የውኃ መጥለቅለቅ በመጣ ጊዜ የሰዎችን ሕይወት ለማትረፍ መርከብ ስለሠራ ኖኅ የሚባል ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው ሰምተህ ታውቃለህ? ታሪኩ ጥንታዊ ቢሆንም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያውቁታል። ሆኖም የኖኅ የሕይወት ታሪክ ለሁላችንም ትርጉም እንዳለው ብዙዎች አይረዱም።

ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ስለተፈጸመ ታሪክ የምናስብበት ምን ምክንያት ይኖራል? የኖኅንና የእኛን ሁኔታ የሚያመሳስለው ነገር ይኖር ይሆን? ከሆነስ ከኖኅ ታሪክ ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

በኖኅ ዘመን የነበረው ዓለም

በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት ስሌት መሠረት ኖኅ የተወለደው በ2970 ከዘአበ ማለትም አዳም ከሞተ ከ126 ዓመታት በኋላ ነው። በኖኅ ዘመን ምድር በዓመፅ ተሞልታ የነበረ ሲሆን አብዛኞቹ የአዳም ዝርያዎችም የዓመፀኛ ቅድመ አያቶቻቸውን ምሳሌ ለመከተል መርጠው ነበር። “እግዚአብሔርም የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደ በዛ፣ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ አየ።”​—⁠ዘፍጥረት 6:5, 11, 12

ይሖዋን ያሳዘነው የሰው ልጆች ዓመፅ ብቻ አልነበረም። የዘፍጥረት ዘገባ እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ፤ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ። . . . በእነዚያ ወራት ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ፤ ደግሞም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ልጆች ባገቡ ጊዜ ልጆችን ወለዱላቸው፤ እነርሱም በዱሮ ዘመን ስማቸው የታወቀ ኃያላን ሆኑ።” (ዘፍጥረት 6:2-4) እነዚህን ቃላት ሐዋርያው ጴጥሮስ ከጻፈው ዘገባ ጋር ስናወዳድር “የእግዚአብሔር ልጆች” የተባሉት ያልታዘዙ መላእክት እንደሆኑ እንገነዘባለን። ኔፍሊሞቹ ደግሞ የሰው ሴቶች ልጆችና ሥጋ የለበሱ ከዳተኛ መላእክት በፈጸሙት ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ግንኙነት የተወለዱ ዲቃሎች ናቸው።​—⁠1 ጴጥሮስ 3:19, 20

“የሚዘርሩ” የሚል ትርጉም ያለው “ኔፍሊም” የሚለው ስማቸው ሌሎችን አንስተው የሚያፈርጡ ግለሰቦችን ያመለክታል። ጨካኝ ጉልበተኞች ነበሩ። የሴሰኛ አባቶቻቸው ኃጢያትም የሰዶምና ጎሞራ ነዋሪዎች ከፈጸሙት ልቅ የሆነ የጾታ ድርጊት ጋር ተመሳስሏል። (ይሁዳ 6, 7) አንድ ላይ ተባብረው ምድርን በከፍተኛ ዓመፅ አናውጠዋት ነበር።

በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ከበደል የራቀ’

ክፋት በጣም ከመስፋፋቱ የተነሳ አምላክ የሰውን ዘር ለማጥፋት ወስኖ ነበር። ሆኖም በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን አገኘ። . . . ኖኅ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ጻድቅና ከበደል የራቀ ሰው ነበር፤ አካሄዱንም ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ።” (ዘፍጥረት 6:8, 9 አ.መ.ት) ጥፋት በተፈረደበት አምላካዊ አክብሮት የሌለው ዓለም ውስጥ እየኖሩ ‘አካሄድን ከእግዚአብሔር ጋር ማድረግ’ እንዴት ይቻላል?

ኖኅ የእምነት ሰው ከነበረውና በአዳም የሕይወት ዘመን ከኖረው አባቱ ከላሜህ ብዙ እንደተማረ ምንም ጥርጥር የለውም። ላሜህ ለልጁ (“እረፍት” ወይም “መጽናናት” ማለት እንደሆነ የሚገመተውን) ኖኅ የሚለውን ስም ሲያወጣ “እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከተግባራችንና ከእጅ ሥራችን ይህ ያሳርፈናል” ሲል ተንብዮ ነበር። አምላክ የምድርን እርግማን ሲያስወግድ ይህ ትንቢት ተፈጽሞአል።​—⁠ዘፍጥረት 5:29፤ 8:21

ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና መመስረት የሚገባው እያንዳንዱ ግለሰብ በመሆኑ ፈሪሀ አምላክ ያላቸው ወላጆች መኖር ለልጆች መንፈሳዊነት ዋስትና አይሆንም። ኖኅ መለኮታዊ ተቀባይነት ያለው ጎዳና በመከተል ‘አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አድርጓል።’ ስለ አምላክ የተማረው ነገር እርሱን እንዲያገለግል ገፋፍቶታል። አምላክ ‘ሥጋን ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃ እንደሚያመጣ’ ሲነግረው የኖኅ እምነት አልተናወጠም።​—⁠ዘፍጥረት 6:13, 17

ኖኅ ከዚያ ቀደም ሆኖ የማያውቀው ይህ የጥፋት ውኃ እንደሚመጣ እርግጠኛ በመሆን አምላክ እንደሚከተለው በማለት የሰጠውን ትእዛዝ ፈጽሟል:- “ከጎፈር እንጨት መርከብን ለአንተ ሥራ፤ በመርከቢቱም ጉርጆችን አድርግ፣ በውስጥም በውጭም በቅጥራን ለቅልቃት።” (ዘፍጥረት 6:14) አምላክ ስለመርከቧ አሠራር የሰጠውን ዝርዝር መመሪያ ተከትሎ መሥራቱ ቀላል አልነበረም። ኖኅ ግን “እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።” (ዘፍጥረት 6:22) ኖኅ ሥራውን ሲያከናውን ሚስቱ፣ ወንዶች ልጆቻቸው ሴም፣ ካምና ያፌት እንዲሁም የልጆቹ ሚስቶች አግዘውት ነበር። ይሖዋም እምነታቸውን ባርኮላቸዋል። ዛሬ ላሉ ቤተሰቦች እንዴት ግሩም ምሳሌ ናቸው!

ይህችን መርከብ መሥራት ምን ይጠይቅ ነበር? ይሖዋ ርዝመትዋ 133 ሜትር፣ ወርድዋ 22 ሜትርና ከፍታዋ 13 ሜትር ገደማ የሆነች ውኃ የማታስገባ ባለ ሦስት ደርብ ግዙፍ የእንጨት ሳጥን እንዲሠራ ኖኅን አዞት ነበር። (ዘፍጥረት 6:15, 16) እንዲህ ዓይነቷ መርከብ ከብዙዎቹ ዘመናዊ የጭነት መርከቦች ጋር የሚመጣጠን የመሸከም አቅም ይኖራታል። ሆኖም የኖኅ መርከብ ሕይወት አድን ነበረች።

እንዴት ያለ ግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክት ነበር! ሥራው በሺዎች የሚቆጠሩ ዛፎችን መቁረጥ፣ ወደ ግንባታው ስፍራ ማጓጓዝ ከዚያም ቆራርጦ ሳንቃና ጣውላ ማዘጋጀት ይጠይቅ እንደነበር እሙን ነው። ከዚህም በላይ በሕንጻ ዙሪያ እንደሚሠራው ያለ መወጣጫ እንጨት መሥራት፣ ችንካር ማዘጋጀት፣ መርከቡ ውኃ እንዳያስገባ የሚረዳውን ቅጥራን ማግኘት፣ የእቃ ማስቀመጫዎች፣ መገልገያ መሣሪያዎች እና የመሳሰሉትን ማሰባሰብን ይጨምራል። ሥራው ከነጋዴዎች ጋር መደራደር እንዲሁም ለሸቀጦቹና ላገኘው ግልጋሎት ክፍያ መስጠትም ጠይቆበት ሊሆን ይችላል። ሳንቃዎቹንና ጣውላዎቹን አስተካክሎ መግጠምና በቂ ጥንካሬ ያለው ነገር መሥራት የአናጺነት ሞያ እንደጠየቀባቸው ግልጽ ነው። ደግሞም ግንባታው ራሱ 50 ወይም 60 ዓመታት ገደማ ፈጅቶ ሊሆን እንደሚችል አስበው!

ቀጣዩ የኖኅ ተግባር ደግሞ በቂ ምግብና የከብቶች ድርቆሽ ማዘጋጀት ይሆናል። (ዘፍጥረት 6:21) ብዛት ያላቸው እንስሳትን ማሰባሰብና በሥርዓት መርከብ ውስጥ ማስገባት ሊኖርበት ነው። ኖኅ አምላክ ያዘዘውን ሁሉ አከናወነ፤ ሥራውም ተጠናቀቀ። (ዘፍጥረት 6:22) የይሖዋ በረከት ስለተጨመረበት ሥራው በተሳካ መንገድ ዳር ሊደርስ ችሏል።

‘የጽድቅ ሰባኪ’

ኖኅ መርከብ ከመሥራት በተጨማሪ ‘የጽድቅ ሰባኪ’ ሆኖ የማስጠንቀቂያ መልእክት በማሰማት አምላክን በታማኝነት አገልግሏል። ሕዝቡ ግን ‘የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ አላወቁም [“አላስተዋሉም፣” NW ]’ ነበር።​—⁠2 ጴጥሮስ 2:5፤ ማቴዎስ 24:38, 39

በወቅቱ ከነበረው መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ውድቀት አንጻር ኖኅና ቤተሰቡ የተጠራጣሪ ጎረቤቶቻቸው ማላገጫና መዘባበቻ ሆነው እንደነበር መገመት አያዳግትም። ሰዎቹ እንደ እብድ ቆጥረዋቸው መሆን አለበት። ያም ሆኖ ግን የኖኅ ቤተሰብ በወቅቱ የነበሩትን አምላካዊ አክብሮት የሌላቸው ሰዎች ዓመፀኝነት፣ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነና የዕብሪተኝነት ዝንባሌ አለመከተላቸው ኖኅ ለቤተሰቡ መንፈሳዊ ማበረታቻና ድጋፍ በመስጠት ረገድ ተሳክቶለት እንደነበር ያሳያል። ኖኅ እምነቱን በሚያንጸባርቅ ንግግርና ድርጊት በወቅቱ የነበረውን ዓለም ኰንኗል።​—⁠ዕብራውያን 11:7

ከጥፋቱ በሕይወት መትረፍ

አምላክ የጥፋት ውኃው ከመምጣቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ሥራው ወደ ተጠናቀቀው መርከብ እንዲገባ ለኖኅ ነገረው። የኖኅ ቤተሰብና እንስሳቱ ከገቡ በኋላ ይሖዋ ዘባቾቹ ሁሉ በውጭ እንዳሉ በሩን ‘በስተ ኋላው ዘጋው።’ ያልታዘዙት መላእክት ጥፋቱ ሲመጣ ሥጋዊ አካላቸውን በመተው ያመለጡ ይመስላል። ሌሎቹስ? ኔፍሊሞቹን ጨምሮ ከመርከቡ ውጪ በምድር ላይ የነበረ ሕይወት ያለው ፍጥረት በሙሉ ጠፋ። የተረፉት ኖኅና ቤተሰቡ ብቻ ነበሩ።​—⁠ዘፍጥረት 7:1-23

ኖኅና ቤተሰቡ በመርከቧ ውስጥ አንድ ሙሉ የጨረቃ ዓመት ከአሥር ቀናት አሳልፈዋል። እንስሳቱን በመመገብና ውኃ በማጠጣት፣ ቆሻሻውን በማጽዳት እንዲሁም ጊዜውን በማስላት በሥራ ተጠምደው ነበር። የዘፍጥረት መጽሐፍ እያንዳንዱን የጥፋት ውኃውን ምዕራፍ ልክ እንደ መርከብ የዕለት ሁኔታ መመዝገቢያ አስፍሯል። ይህም የዘገባውን ትክክለኝነት የሚያረጋግጥ ነው።​—⁠ዘፍጥረት 7:11, 17, 24፤ 8:3-14

መርከቧ ውስጥ እያሉ ቤተሰቡ በሚያደርገው መንፈሳዊ ውይይትና ለአምላክ በሚያቀርበው ምስጋና ረገድ ኖኅ ግንባር ቀደም እንደነበር ምንም አያጠራጥርም። ምናልባትም ከጥፋት ውኃ በፊት የነበረውን ታሪክ ጠብቀው ያቆዩት ኖኅና ቤተሰቡ ሳይሆኑ አይቀሩም። በቃል ሲተላለፉ የኖሩ አስተማማኝ መረጃዎች ወይም በእጃቸው የነበሩ በጽሑፍ የተቀመጡ ታሪካዊ መዛግብት በጥፋት ውኃው ወቅት ጠቃሚ ውይይት ለማድረግ ረድተዋቸው ሊሆን ይችላል።

ኖኅና ቤተሰቡ እንደገና ደረቅ መሬት ሲረግጡ ምን ያህል ተደስተው ይሆን! ኖኅ መጀመሪያ ያደረገው ነገር ቢኖር መሠዊያ መሥራትና ሕይወታቸውን ላተረፈላቸው አምላክ መሥዋዕት ማቅረብ ነበር። በዚህ ጊዜ ለቤተሰቡ እንደ ካህን ሆኗል ማለት ይቻላል።​—⁠ዘፍጥረት 8:18-20

“የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ”

ኢየሱስ ክርስቶስ “የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና” ብሏል። (ማቴዎስ 24:37) ዛሬም ክርስትያኖች፣ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ የሚያሳስቡ የጽድቅ ሰባኪዎች ናቸው። (2 ጴጥሮስ 3:5-9) ይህ ንጽጽር እንዳለ ሆኖ ከጥፋት ውኃው በፊት በኖኅ አእምሮ ውስጥ ይመላለስ የነበረው ነገር ምን ይሆን ብለን እናስብ ይሆናል። የስብከት እንቅስቃሴው ከንቱ እንደሆነ ተሰምቶት ያውቅ ይሆን? የተሰላቸበትስ ጊዜ ይኖር ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ምንም የሚለው ነገር የለም። የምናውቀው ነገር ቢኖር ኖኅ አምላክን መታዘዙን ነው።

የኖኅ ታሪክ ለእኛ ያለውን ተግባራዊ ጠቀሜታ አስተዋልክ? ተቃውሞና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም ይሖዋን ታዝዟል። ይሖዋ እንደ ጻድቅ የቆጠረውም ለዚህ ነው። የኖኅ ቤተሰብ አምላክ ጥፋት የሚያመጣበትን ትክክለኛ ጊዜ ባያውቅም ጥፋቱ እንደሚመጣ ያውቅ ነበር። ኖኅ በአምላክ ቃል ላይ የነበረው እምነት ለዓመታት ባከናወነው ከባድ ሥራና ፍሬ ቢስ ይመስል በነበረው የስብከት እንቅስቃሴው ያለመታከት እንዲቀጥል ረድቶታል። “ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፣ በዚህም ዓለምን ኰነነ፣ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ” ተብሎ መነገሩ በእርግጥም ትክክል ነው።​—⁠ዕብራውያን 11:7

ኖኅ እንዲህ ያለ እምነት ሊገነባ የቻለው እንዴት ነው? ከሁኔታዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ስለ ይሖዋ በሚያውቀው በእያንዳንዱ ነገር ላይ ጊዜ ወስዶ ያሰላስልና ባገኘውም እውቀት ሕይወቱን ይመራ የነበረ ይመስላል። ኖኅ ከአምላክ ጋር በጸሎት ይነጋገር እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲያውም ከይሖዋ ጋር በጣም ከመቀራረቡ የተነሳ “አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ” ተብሎለታል። የቤት ራስ እንደመሆኑ መጠን ለቤተሰቡ ጊዜ ይመድብና ፍቅራዊ እንክብካቤ ያደርግ ነበር። ይህም የሚስቱን፣ የልጆቹን እና የልጆቹን ሚስቶች መንፈሳዊነት መንከባከብን ይጨምራል።

ልክ እንደ ኖኅ ሁሉ ዛሬ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም በቅርቡ ይሖዋ ይህን አምላካዊ አክብሮት የሌለው የነገሮች ሥርዓት እንደሚያጠፋው ያውቃሉ። ጥፋቱ የሚመጣበትን ቀንና ሰዓት አናውቀውም፤ ቢሆንም የዚህን ‘የጽድቅ ሰባኪ’ እምነትና ታዛዥነት መኮረጃችን ‘ነፍሳችንን ለማዳን’ ያስችለናል።​—⁠ዕብራውያን 10:36-39

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በእርግጥ ተፈጽሟልን?

የስነ ሰብአት ተመራማሪዎች (Anthropologists) ከሁሉም ነገዶችና ብሔሮች ማለት ይቻላል፣ የተሰበሰቡ ወደ 270 የሚጠጉ ስለ ውኃ መጥለቅለቅ የሚናገሩ አፈ ታሪኮች አግኝተዋል። ክላውስ ዌስተርማን የተባሉ ምሁር “የጥፋት ውኃው ታሪክ በመላው ዓለም ይገኛል” ብለዋል። “እንደ ፍጥረት ዘገባ ሁሉ ይህም ቢሆን ከዋናዎቹ ባህላዊ ቅርሶቻችን አንዱ ነው። በየትኛውም የምድር ክፍል ጥንት ስለተፈጸመ ታላቅ የጥፋት ውኃ የሚናገር ታሪክ መገኘቱ እጅግ የሚያስገርም ነው! ።” ለዚህ ሊሰጠው የሚችለው ማብራሪያ ምንድን ነው? ኤንሪኮ ጋልቢያቲ የተባሉ ተንታኝ እንዲህ ይላሉ:- “በተለያዩና በጣም ተራርቀው በሚገኙ ሕዝቦች መካከል ስለ ጥፋት ውኃ የሚናገር ተመሳሳይ አፈ ታሪክ መኖሩ ለነዚህ አፈ ታሪኮች መሠረት የሆነ ታሪካዊ እውነታ እንዳለ ያረጋግጣል።” ይሁን እንጂ ከምሁራን አስተያየቶች ይበልጥ ለክርስቲያኖች ትልቅ ዋጋ ያለው ኢየሱስ ራሱ የጥፋት ውኃውን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እንደተፈጸመ እውነተኛ ክንውን አድርጎ መናገሩን ማወቃቸው ነው።​—⁠ሉቃስ 17:26, 27

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አፈ ታሪክ ስለ ኔፍሊሞች የሚለው ነገር ይኖር ይሆን?

በአማልክት እና በሰዎች መካከል ስለተፈጸሙ የጾታ ድርጊቶች እና በዚህ መሃል ስለተወለዱት “ጀግኖች” ወይም “አምላክ አከል ሰዎች” የሚናገሩ ታሪኮች በግሪካውያን፣ በግብጻውያን፣ በኡጋሪያውያን፣ በሁሪያንና፣ እና በሜሶጶጣሚያ ሰዎች መንፈሳዊ ትምህርቶች ውስጥ የተለመዱ ነበሩ። የግሪካውያኑ አፈ ታሪካዊ አማልክት ሰብዓዊ ቁመና ያላቸውና ውብ ነበሩ። ይበሉና ይጠጡ፣ ይተኙ፣ የጾታ ግንኙነት ይፈጽሙ፣ ይጣሉ፣ ይደባደቡ፣ ሴቶችን አታልለውና አስገድደው ወሲብ ይፈጽሙ ነበር። ቅዱስ ናቸው ቢባልም የማታለልና የወንጀል ድርጊት የመፈጸም ችሎታ ነበራቸው። እንደ አኪሊዝ ያሉ ጀግኖች ሰብዓዊም መለኮታዊም ዝርያ እንዳላቸው እንዲሁም ከአለመሞት ባሕርይ በስተቀር ከሰው በላይ የሆነ ችሎታ የተላበሱ እንደሆኑ ይነገርላቸው ነበር። ስለዚህ የዘፍጥረት መጽሐፍ ስለ ኔፍሊም የሚናገረው ሐሳብ የእነዚህ አፈ ታሪኮች ምንጭ ምን ሊሆን እንደሚችል ወይም ምን እንደሆነ እንድናውቅ ይረዳናል።