በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

በኤደን ገነት ውስጥ አምላክ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውን ዛፍ በተመለከተ የሰጠውን ሕግ እንድትተላለፍ እባብ ሔዋንን ያነጋገራት እንዴት ነው?

ዘፍጥረት 3:​1 እንዲህ ይላል:- “እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነበረ። ሴቲቱንም:- በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት።” እባብ ሔዋንን እንዴት እንዳነጋገራት የሚገልጹ የተለያዩ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል። የተሰጠው አንደኛው ሐሳብ የተነጋገሩት በሰውነት እንቅስቃሴ አማካኝነት ነው የሚል ነው። ለምሳሌ ያህል ጆሴፍ ቤንሰን የተባሉ እንግሊዛዊ ቄስ “በአንድ ዓይነት ምልክት ተነጋግረዋል የሚለው ሐሳብ ሚዛን የሚደፋ ይመስላል። እንዲያውም በዚያ ዘመን የማሰብ ችሎታ እና ንግግር የእባቦች መለያ ባሕርያት እንደነበሩ በአንዳንዶች ዘንድ ይታመናል። . . . ሆኖም ለዚህ ማረጋገጫ ማግኘት አይቻልም” የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል።

ይሁን እንጂ እባብ የሰውነት እንቅስቃሴ ብቻ በመጠቀም ሔዋን ከተከለከለው ፍሬ ብትበላ እንደ አምላክ እንደምትሆንና ይህም መልካምና ክፉ የሆነውን ለማወቅ እንደሚያስችላት እንዴት ሊገልጽላት ይችላል? ከዚህም በላይ ሔዋን እባብ ላነሳው ጥያቄ መልስ በመስጠት በውይይቱ ተካፋይ ሆናለች። (ዘፍጥረት 3:​2-5) እባብ በምልክት ወይም በሰውነት እንቅስቃሴ ተጠቅሞ አነጋግሯታል የሚለው ሐሳብ ሔዋንም መልስ የሰጠችው የሰውነት እንቅስቃሴ ተጠቅማ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ያደርሰናል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን መናገሯን ይገልጻል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ክስተት በመጥቀስ “እባብ በተንኰሉ ሔዋንን እንዳሳታት፣ አሳባችሁ ተበላሽቶ . . . እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ” በማለት ክርስቲያን ወንድሞቹን አስጠንቅቋል። ጳውሎስ “ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኰለኞች ሠራተኞች” እንዳያሳስቷቸው ማስጠንቀቁ ነበር። ‘ዋነኛ ሐዋርያት’ የተባሉት እነዚህ ሰዎች ስጋት የፈጠሩት የሰውነት እንቅስቃሴና ምልክት በመጠቀም ብቻ አልነበረም። ንግግርን ይኸውም ሌሎችን ለማሳሳት ብለው የሚጠቀሙባቸውን ተንኮል ያዘሉ ቃላትንም ይጨምራል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 11:​3-5, 13

በኤደን ገነት ውስጥ ሔዋን እንድትሳሳት ያደረጋት የተነገራት ቃል ቢሆንም እባቡ ለመናገር የሚያስችል የድምፅ አውታር ነበረው ማለት ግን አይደለም። እባቦች የድምፅ አውታር አያስፈልጋቸውም። የአምላክ መልአክ በአህያ አማካኝነት በለዓምን ባነጋገረው ጊዜ አህያዋ እንደሰው ያለ የተወሳሰበ የድምፅ አውታር አላስፈለጋትም። (ዘኁልቊ 22:​26-31) በግልጽ እንደሚታየው ‘ቃል የሌለው አህያ በሰው ቃል ለመናገር’ የሚያስችለውን ኃይል ያገኘው ከመንፈሳዊው ዓለም ነው።​—⁠2 ጴጥሮስ 2:​16

ሔዋንን ካነጋገራት እባብ በስተጀርባ የነበረው መንፈሳዊ ፍጡር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን” ተብሎ ተገልጿል። (ራእይ 12:​9) ሔዋን ሰምታ መልስ የሰጠችባቸው ቃላት የፈለቁት ‘የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ከሚለውጠው’ ከሰይጣን ነው።​—⁠2 ቆሮንቶስ 11:​14

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘እንደ እግዚአብሔር መልካምንና ክፉን የምታውቁ ትሆናላችሁ’