ይሖዋ ዕድሜያችንን እንዴት እንደምንቆጥር ያስተምረናል
ይሖዋ ዕድሜያችንን እንዴት እንደምንቆጥር ያስተምረናል
“ጥበብን የተሞላ ልብ ይኖረን ዘንድ፣ ዕድሜያችንን መቁጠር አስተምረን።”—መዝሙር 90:12 አ.መ.ት
1. ይሖዋ “ዕድሜያችንን” እንዴት “መቁጠር” እንደምንችል እንዲያስተምረን መጠየቃችን ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
ይሖዋ አምላክ ፈጣሪያችንና ሕይወት ሰጪያችን ነው። (መዝሙር 36:9፤ ራእይ 4:11) ስለሆነም የሕይወት ዘመናችንን እንዴት በጥበብ ልንጠቀምበት እንደምንችል ከይሖዋ የተሻለ ሊያስተምረን የሚችል ማንም የለም። ስለዚህ መዝሙራዊው “ጥበብን የተሞላ ልብ ይኖረን ዘንድ፣ ዕድሜያችንን መቁጠር አስተምረን” በማለት አምላክን መማጸኑ የተገባ ነው። (መዝሙር 90:12 አ.መ.ት) ይህን ልመና የያዘውን 90ኛውን መዝሙር በጥንቃቄ ልንመረምረው ይገባናል። በመጀመሪያ ግን ይህን በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መዝሙር በአጭሩ እንከልስ።
2. (ሀ) መዝሙር 90ን እንዳቀናበረ የተገለጸው ማን ነው? የተጻፈውስ መቼ ሊሆን ይችላል? (ለ) መዝሙር 90 ለሕይወት ያለንን አመለካከት ሊነካ የሚገባው እንዴት ነው?
2 መዝሙር 90 አናት ላይ የሠፈረው ጽሑፍ መዝሙሩ “የእግዚአብሔር ሰው የሙሴ ጸሎት” እንደሆነ ይናገራል። ይህ መዝሙር የሰው ልጅ ሕይወት አላፊ መሆኑን ጠበቅ አድርጎ ስለሚገልጽ የተቀነባበረው በሺህ የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ታማኝ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ምክንያት በሞት በተቀጡበት ማለትም ከግብፅ የባርነት ቀንበር ነፃ ወጥተው ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ በተጓዙበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። (ዘኁልቊ 32:9-13) ያም ሆነ ይህ መዝሙር 90 ፍጽምና የሌላቸው የሰው ልጆች ዕድሜ አጭር መሆኑን ያሳያል። ስለሆነም ውድ የሆነውን ዕድሜያችንን በጥበብ ልንጠቀምበት ይገባናል።
3. የመዝሙር 90 ጠቅለል ያለ ይዘት ምንድን ነው?
3 መዝሙር 90 ከቁጥር 1 እስከ 6 ይሖዋ ዘላለማዊ መጠጊያችን እንደሆነ ይገልጻል። ከቁጥር 7 እስከ 12 ደግሞ እንደ ጥላ ቶሎ የሚያልፈውን የሕይወት ዘመናችንን በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ባለው መንገድ መጠቀም እንችል ዘንድ ምን እንደሚያስፈልገን ይጠቁመናል። ከቁጥር 13 እስከ 17 ላይ እንደተገለጸው ደግሞ የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነትና በረከት ለማግኘት በጥልቅ እንመኛለን። እርግጥ ነው ይህ መዝሙር በግለሰብ ደረጃ በይሖዋ አገልግሎት ስለሚያጋጥመን ሁኔታ ይተነብያል ማለት አይደለም። የሆነ ሆኖ በጸሎት መልክ የቀረበውን በዚህ መዝሙር ውስጥ የሠፈረውን መግለጫ ልብ ልንለው ይገባናል። እንግዲያው ራሳቸውን ለአምላክ ከወሰኑ ሰዎች አንጻር መዝሙር 90ን በጥልቅ እንመርምር።
ይሖዋ “መጠጊያችን” ነው
4-6. ይሖዋ እውነተኛ ‘መጠጊያ’ የሆነልን እንዴት ነው?
4 መዝሙራዊው በሚከተሉት ቃላት ይከፍታል:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ከትውልድ እስከ ትውልድ መጠጊያችን ሆንህልን። ገና ተራሮች ሳይወለዱ፣ ምድርንና ዓለምን ከመፍጠርህ በፊት፣ አንተ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላክ ነህ።”—መዝሙር 90:1, 2 አ.መ.ት
5 ‘ዘላለማዊው አምላክ’ ይሖዋ እውነተኛ “መጠጊያችን” ማለትም መንፈሳዊ መሸሸጊያችን ነው። (ሮሜ 16:25 አ.መ.ት) ‘ጸሎት ሰሚ’ እንደመሆኑ መጠን እኛን ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ ስለሆነ ደህንነት ይሰማናል። (መዝሙር 65:2) ጭንቀቶቻችንን ሁሉ በውድ ልጁ በኩል በሰማያዊ አባታችን ላይ ስለምንጥል ‘አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችንንና አሳባችንን ይጠብቅልናል።’—ፊልጵስዩስ 4:6, 7፤ ማቴዎስ 6:9፤ ዮሐንስ 14:6, 14
6 በምሳሌያዊ አባባል ይሖዋ እውነተኛ “መጠጊያችን” ስለሆነልን መንፈሳዊ ደህንነት አግኝተናል። በተጨማሪም ‘ቤት’ (ማለትም ሕዝቦቹ የሚገኙበትን ጉባኤ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል) ያዘጋጀ ሲሆን እዚያም አፍቃሪ የሆኑ እረኞች ከፍተኛ የደህንነት ስሜት እንዲሰማን ያደርጉናል። (ኢሳይያስ 26:20፤ 32:1, 2፤ ሥራ 20:28, 29) ከዚህም በላይ አንዳንዶቻችን በአምላክ አገልግሎት ረዥም ዓመት በቆየ ቤተሰብ ውስጥ እንኖር ይሆናል፤ ይህም በግለሰብ ደረጃ ‘ከትውልድ እስከ ትውልድ እውነተኛ መጠጊያ’ ሆኖልናል ሊባል ይችላል።
7. ተራሮች ‘የተወለዱት’ ምድርም ‘በምጥ’ የተገኘችው እንዴት ነው?
7 ይሖዋ “ተራሮች ሳይወለዱ” ወይም ምድር “በምጥ” [NW ] ከመገኘቷ በፊት ይኖር ነበር። በሰው ዓይን ሲታይ ከተለያዩ ገጽታዎቿ፣ ኬሚካላዊ ዑደቶቿና እጅግ ውስብስብ ከሆኑት አሠራሯ ጋር ምድርን መፍጠር ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ነው። መዝሙራዊው ተራሮች እንደ ‘ተወለዱ’ ምድርም ‘በምጥ’ እንደተገኘች አድርጎ መናገሩ ይሖዋ እነዚህን ነገሮች ሲፈጥር ምን ያህል ሥራ እንደጠየቀበት በመገንዘብ ለዚህ የፍጥረት ሥራ ያለውን ታላቅ አክብሮት መግለጹ ነበር። እኛስ ለፈጣሪ የእጅ ሥራዎች ተመሳሳይ የአክብሮትና የአድናቆት ስሜት ሊኖረን አይገባንም?
ይሖዋ ምንጊዜም እኛን ለመርዳት ዝግጁ ነው
8. ይሖዋ ‘ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላክ ነው’ የሚለው አባባል ምን ትርጉም አለው?
8 መዝሙራዊው “አንተ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላክ ነህ” በማለት ዘምሯል። “ዘላለም” የሚለው ቃል መጨረሻ ያላቸውን ሆኖም የሚቆዩበት የጊዜ ርዝመት በግልጽ ያልተቀመጠላቸውን ነገሮች ሊያመለክት ይችላል። (ዘጸአት 31:16, 17፤ ዕብራውያን 9:15) ሆኖም በመዝሙር 90:2 እና በሌሎች የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የሚገኘው ‘ዘላለም’ የሚለው አገላለጽ “መጨረሻ የሌለው” የሚል ትርጉም አለው። (መክብብ 1:4) አምላክ ለዘላለም የሚኖር ነው የሚለው አባባል ለአእምሯችን የሚከብድ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይሖዋ መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ የለውም። (ዕንባቆም 1:12 NW ) ምንጊዜም ሕያውና እኛን ለመርዳት ዝግጁ ነው።
9. መዝሙራዊው የሰው ልጆችን የአንድ ሺህ ዓመት ዕድሜ ከምን ጋር አወዳድሮታል?
9 በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው መዝሙራዊ የሰው ልጆችን የአንድ ሺህ ዓመት ዕድሜ ዘላለማዊ በሆነው ፈጣሪ ፊት በጣም አጭር ከሆነ የጊዜ ርዝማኔ ጋር አወዳድሮታል። አምላክን በማስመልከት እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ሰዎችን ወደ ዐፈር [“ትቢያ፣” NW ] ትመልሳለህ፤ ‘የሰው ልጆች ሆይ፤ ወደ ቦታችሁ ተመለሱ’ ትላለህ፤ ሺህ ዓመት በፊትህ፣ እንዳለፈችው እንደ ትናንት ቀን፣ እንደ ሌሊትም እርቦ ነውና።”—መዝሙር 90:3, 4 አ.መ.ት
10. አምላክ ሰውን ‘ወደ ትቢያ እንዲመለስ’ የሚያደርገው እንዴት ነው?
10 አምላክ ሟች የሆነውን የሰው ልጅ ‘ወደ ትቢያ ይመልሰዋል።’ ይህም ማለት ሰው እንደተፈጨ ወይም እንደተደቆሰ አፈር ወደ ‘ትቢያ’ ይመለሳል ማለት ነው። ይሖዋ የሰውን ልጅ ‘ወደ ወጣህበት መሬት ተመለስ’ ያለው ያህል ነው። (ዘፍጥረት 2:7፤ 3:19) የትኛውም ፍጹም ያልሆነ ሰው ‘ወንድሙ እንኳ ለዘላለም ይኖር ዘንድ ሊያድነው ወይም ቤዛውን ለእግዚአብሔር ሊሰጥለት’ ስለማይችል ይህ አባባል ብርቱ ደካማ፣ ሀብታም ድሃ ሳይል ለሁሉም የሚሠራ ነው። (መዝሙር 49:6-9) ይሁን እንጂ ‘በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት ይኖረው ዘንድ አምላክ አንድያ ልጁን በመስጠቱ’ ምንኛ አመስጋኞች ነን!—ዮሐንስ 3:16፤ ሮሜ 6:23
11. ለእኛ ረዥም መስሎ የሚታየን ጊዜ በአምላክ ዘንድ በጣም አጭር የሆነው ለምንድን ነው?
11 ከይሖዋ አንጻር ሲታይ 969 ዓመት የኖረው ማቱሳላ እንኳ የኖረው ከአንድ ቀን ያነሰ ጊዜ ነው። (ዘፍጥረት 5:27) በአምላክ ዘንድ አንድ ሺህ ዓመት ሲያልፍ የ24 ሰዓት ርዝማኔ ያለው አንድ ቀን ያለፈ ያህል ነው። በተጨማሪም መዝሙራዊው አንድ ሺህ ዓመት በአምላክ ፊት አንድ ጠባቂ በጥበቃ ሥራ ከሚቆይበት ከአንድ ሌሊት እርቦ ጋር እኩል እንደሆነ ተናግሯል። (መሳፍንት 7:19) ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው ለእኛ ረዥም መስሎ የሚታየን ጊዜ ዘላለማዊ በሆነው አምላክ በይሖዋ ዘንድ በጣም አጭር መሆኑን ነው።
12. ሰዎች በአምላክ ‘ተጠርገው የተወሰዱት’ እንዴት ነው?
12 ከአምላክ ዘላለማዊነት ጋር ሲነፃፀር በአሁኑ ጊዜ ያለው የሰው ልጅ እድሜ በእርግጥም በጣም አጭር ነው። መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል:- “እንደ ጎርፍ ጠርገህ ስትወስዳቸው፣ እንደ ሕልም ይበናሉ፤ እንደ ማለዳ ሣር ታድሰው ይበቅላሉ፤ ሣሩም ንጋት ላይ አቆጥቁጦ ይለመልማል፤ ምሽት ላይ ጠውልጎ ይደርቃል።” (መዝሙር 90:5, 6 አ.መ.ት) ሙሴ በሺህ የሚቆጠሩ እስራኤላውያን አምላክ ‘እንደ ጎርፍ ጠርጎ’ በምድረ በዳ ሲገድላቸው ተመልክቷል። የዚህ መዝሙር ክፍል “ሰዎችን በሞት እንቅልፍ ጠርገህ ትወስዳቸዋለህ” ተብሎ ተተርጉሟል። (ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን) በሌላ በኩል ደግሞ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች የሚቆዩበት የሕይወት ዘመን በአንድ ሌሊት እንቅልፍ እንደሚታይ ‘ሕልም’ አጭር ነው።
13. ‘እንደ ለምለም ሣር’ የሆንነው እንዴት ነው? ይህስ አመለካከታችንን እንዴት ሊነካው ይገባል?
13 እኛ ‘ማለዳ ላይ እንደሚለመልም’ ሆኖም ከፀሐዩ ትኩሳት የተነሳ ምሽት ላይ እንደሚጠወልግ “ሣር” ነን። አዎን፣ በአንዲት ቀን ጠውልጎ እንደሚደርቅ ሣር ሕይወታችን አላፊ ነው። ስለዚህ ይህን ውድ ንብረት ፈጽሞ አናባክን። ከዚያ ይልቅ የቀረውን የሕይወት ዘመናችንን በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ እንዴት ልንጠቀምበት እንደሚገባ ለማወቅ አምላክ የሚሰጠውን መመሪያ መፈለግ ይኖርብናል።
ይሖዋ ‘ዕድሜያችንን መቁጠር’ ያስተምረናል
14, 15. መዝሙር 90:7-9 በእስራኤላውያን ላይ የተፈጸመው እንዴት ነው?
14 መዝሙራዊው አምላክን በሚመለከት እንዲህ ብሏል:- “በቁጣህ አልቀናልና፤ በመዓትህም ደንግጠናል። በደላችንን በፊትህ፣ የተሰወረ ኃጢአታችንንም በገጽህ ብርሃን ፊት አኖርህ። ዘመናችን ሁሉ በቁጣህ ዐልፎአልና፤ ዕድሜአችንንም በመቃተት እንጨርሳለን።”—መዝሙር 90:7-9 አ.መ.ት
15 እምነተ ቢስ የነበሩት እስራኤላውያን ‘በአምላክ ቁጣ አልቀዋል።’ ‘በመዓቱ ደንግጠዋል’ ወይም ‘በንዴቱ ተሸብረዋል።’ (ኒው ኢንተርናሽናል ባይብል) አንዳንዶች መለኮታዊ ፍርድ ተበይኖባቸው “በምድረ በዳ ወድቀዋል።” (1 ቆሮንቶስ 10:5) ይሖዋ ‘በደላቸውን በፊቱ አኑሮ’ ነበር። በገሃድ ለፈጸሙት ስህተት ተጠያቂ አድርጓቸው የነበረ ሲሆን “የተሰወረ” ወይም በድብቅ የፈጸሙት ኃጢአትም ቢሆን ‘በገጹ ብርሃን ፊት’ ነበር። (ምሳሌ 15:3) ንስሐ ያልገቡት እስራኤላውያን በአምላክ ቁጣ ‘ዕድሜያቸውን በመቃተት ጨርሰዋል።’ እንዲያውም ለአጭር ጊዜ የሚቆየው ዕድሜያችን ከአፋችን እንደሚወጣው ትንፋሽ ብን ብሎ የሚጠፋ ነው።
16. አንዳንዶች በድብቅ ኃጢአት እየፈጸሙ ከሆኑ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?
16 ማናችንም በድብቅ ኃጢአት ብንፈጽም እንዲህ ያለውን ድርጊት ለተወሰነ ጊዜ ከሰው ዓይን መሠወር እንችል ይሆናል። ይሁን እንጂ በድብቅ የምንሠራው ኃጢአት ‘በይሖዋ ገጽ ብርሃን ፊት’ የተገለጠ ሲሆን የምንፈጽመውም ድርጊት ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ያበላሽብናል። ከይሖዋ ጋር የነበረንን የቀረበ ዝምድና እንደገና ማግኘት ከፈለግን ይቅር እንዲለን መጸለይና ኃጢአት መሥራታችንን ማቆም እንዲሁም ክርስቲያን ሽማግሌዎች የሚሰጡንን መንፈሳዊ እርዳታ በአመስጋኝነት መቀበል ይኖርብናል። (ምሳሌ 28:13፤ ያዕቆብ 5:14, 15) የዘላለም ሕይወት ተስፋችንን አደጋ ላይ ጥለን ‘ዕድሜያችንን በመቃተት ከመጨረስ’ ይልቅ እንዲህ ማድረጋችን ምንኛ የተሻለ ነው!
17. አማካይ የሰዎች እድሜ ምን ያህል ነው? ዕድሜያችን በምን የተሞላ ነው?
17 ፍጽምና የሌላቸውን የሰው ልጆች ዕድሜ ርዝመት በማስመልከት መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል:- “የዕድሜአችን ዘመን ሰባ ዓመት፣ ቢበዛም ሰማንያ ነው፤ ከዚያ በላይ ከሆነም ድካምና መከራ ብቻ ነው፤ ቶሎ ያልፋልና፤ እኛም ወዲያው እንነጉዳለን።” (መዝሙር 90:10 አ.መ.ት ) በአጠቃላይ ሲታይ የሰው እድሜ 70 ዓመት ገደማ ነው፤ ይሁንና ካሌብ በ85 ዓመቱ አስገራሚ ጥንካሬ እንደነበረው ተናግሯል። እንደ አሮን (123)፣ ሙሴ (120) እና ኢያሱ (110) ያሉ አንዳንድ ሰዎች ከተለመደው የዕድሜ ጣሪያ በላይ ኖረዋል። (ዘኁልቊ 33:39፤ ዘዳግም 34:7፤ ኢያሱ 14:6, 10, 11፤ 24:29) ይሁን እንጂ ከግብፅ ከወጣው እምነት የለሽ ትውልድ መካከል 20 እና ከዚያ በላይ እድሜ ያላቸው በ40 ዓመት ጊዜ ውስጥ ሞተው አልቀዋል። (ዘኁልቊ 14:29-34) በዛሬው ጊዜ በብዙ አገሮች የሰዎች አማካይ እድሜ መዝሙራዊው ከተናገረው ክልል አያልፍም። ዕድሜያችን ‘በድካምና በመከራ’ የተሞላ ነው። ቶሎ ያልፋል “እኛም ወዲያው እንነጉዳለን።”—ኢዮብ 14:1, 2
18, 19. (ሀ) “ጥበብን የተሞላ ልብ ይኖረን ዘንድ ዕድሜያችንን መቁጠር አስተምረን” የሚለው አባባል ምን ትርጉም አለው? (ለ) ጥበብን ማግኘታችን ምን እንድናደርግ ያንቀሳቅሰናል?
18 በመቀጠልም መዝሙራዊው እንዲህ በማለት ዘምሯል:- “የቁጣህን ኃይል ማን ያውቃል? መዓትህም የመፈራትህን ያህል ታላቅ ነው። ጥበብን የተሞላ ልብ ይኖረን ዘንድ፣ ዕድሜያችንን መቁጠር አስተምረን።” (መዝሙር 90:11, 12 አ.መ.ት) ከመካከላችን የአምላክን ቁጣ ኃይል ወይም የመዓቱን መጠን በትክክል የሚያውቅ የለም። ይህም ለይሖዋ ያለንን አክብሮታዊ ፍርሃት ሊያሳድገው ይገባል። እንዲያውም “ጥበብን የተሞላ ልብ ይኖረን ዘንድ፣ ዕድሜያችንን መቁጠር አስተምረን” ብለን እንድንጠይቅ ሊያነሳሳን ይገባል።
19 መዝሙራዊው የተናገራቸው ቃላት ሕዝቡ የቀረውን ዕድሜያቸውን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ባለው መንገድ በጥበብ መመዘንና መጠቀም እንዲችሉ ይሖዋ እንዲያስተምራቸው የቀረበ ጸሎት ነው። ሰባ ዓመት አማካይ እድሜ 25, 500 ቀናት ገደማ አሉት። ምንም ያህል ዓመት እንኑር ‘ነገ የሚሆነውን አናውቅም። ሕይወታችን ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋሎት ነው።’ (ያዕቆብ 4:13-15) ‘ጊዜና ያልታሰበ አጋጣሚ በሁላችንም ላይ ሊደርስ’ የሚችል በመሆኑ ከአሁን በኋላ ለምን ያህል ጊዜ እንደምንኖር አናውቅም። ስለዚህ መከራዎችን ለመቋቋም፣ ሌሎችን ተገቢ በሆነ መንገድ ለመያዝና አሁኑኑ በይሖዋ አገልግሎት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ እንችል ዘንድ ጥበብን እንድናገኝ እንጸልይ! (መክብብ 9:11፤ ያዕቆብ 1:5-8) ይሖዋ በቃሉ፣ በመንፈሱና በድርጅቱ አማካኝነት ይመራናል። (ማቴዎስ 24:45-47፤ 1 ቆሮንቶስ 2:10፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ጥበበኞች መሆናችን ‘የአምላክን መንግሥት መፈለጋችንን’ እንድንቀጥልና ዕድሜያችንን ለይሖዋ ክብር በሚያመጣና ልቡን ደስ በሚያሰኝ መንገድ እንድንጠቀምበት ያንቀሳቅሰናል። (ማቴዎስ 6:25-33፤ ምሳሌ 27:11) እርግጥ ነው ይሖዋን በሙሉ ልብ ማምለካችን ሙሉ በሙሉ ከችግር ነፃ ያደርገናል ማለት ባይሆንም ከፍተኛ ደስታ ያስገኝልናል።
የይሖዋ በረከት ደስታ ያስገኝልናል
20. (ሀ) አምላክ ‘የሚጸጸተው’ በምን መንገድ ነው? (ለ) ከባድ ስህተት ብንሠራም እንኳ ከልብ ንስሐ ከገባን ይሖዋ ምን ያደርጋል?
20 በቀሪው የሕይወት ዘመናችን ሁሉ ደስተኞች ሆነን ብንኖር ምንኛ ግሩም ነው! በዚህ ረገድ ሙሴ እንዲህ በማለት ተማጽኗል:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ ተመለስ፤ ይህ እስከ መቼ ይሆናል? ለአገልጋዮችህም ራራላቸው [“ተጸጸት፣” NW ]። በዘመናችን ሁሉ ደስ እንዲለን ሐሤትም እንድናደርግ፤ ምሕረትህን [ወይም “ታማኝ ፍቅርህን” የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ] በማለዳ አጥግበን።” (መዝሙር 90:13, 14 አ.መ.ት) አምላክ ፈጽሞ አይሳሳትም። ሆኖም ይሖዋ የቅጣት ፍርድ እንደሚያስፈጽም የተናገረውን ማስጠንቀቂያ ሰምተው ኃጢአተኞች ንሥሐ ቢገቡና በጠባያቸውና በአኗኗራቸው ላይ ለውጥ ቢያደርጉ ከቁጣው ‘ሊመለስ’ እንዲሁም ‘ተጸጽቶ’ ሊወስድ ያሰበውን ቅጣት ሊተው ይችላል። (ዘዳግም 13:17) ስለሆነም ከባድ ስህተት ብንሠራም እንኳ ከልብ ንስሐ ከገባን ይሖዋ ‘በምሕረቱ ያጠግበናል’፤ በዚህም የተነሳ ‘ሐሤት ልናደርግ’ እንችላለን። (መዝሙር 32:1-5) የጽድቅ ጎዳና በመከተል አምላክ ለእኛ ያለውን ታማኝ ፍቅር እንቀምሳለን እንዲሁም “በዘመናችን ሁሉ” ማለትም በቀሪው የሕይወት ዘመናችን በሙሉ “ደስ እንዲለን” ማድረግ እንችላለን።
21. መዝሙር 90:15, 16 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ሙሴ እየለመነ ያለው ስለምን ነገር ሊሆን ይችላል?
21 መዝሙራዊው እንደሚከተለው በማለት ተማጽኗል:- “መከራ ባሳየኸን ዘመን መጠን፣ ክፉም ባየንባቸው ዓመታት ልክ ደስ አሰኘን። ሥራህ ለአገልጋዮችህ፣ ክብርህም ለልጆቻቸው ይገለጥ።” (መዝሙር 90:15, 16 አ.መ.ት) ሙሴ መከራ ባዩበትና ሥቃይ በተቀበሉበት ዘመን ልክ ወይም ከዚያ በሚበልጥ ዘመን እስራኤልን በደስታ እንዲባርክ አምላክን መጠየቁ ሊሆን ይችላል። አምላክ እስራኤላውያንን ለመባረክ የሚያከናውነው ‘ሥራ’ ለአገልጋዮቹ ግልጥ ሆኖ እንዲታይና ክብሩም ለልጆቻቸው ወይም ለዘሮቻቸው እንዲገለጥ ጠይቋል። እኛም አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ ለታዛዥ የሰው ልጆች በረከት እንዲዘንብ ልንጸልይ እንችላለን።—2 ጴጥሮስ 3:13
22. በመዝሙር 90:17 መሠረት ስለምን ነገር መጸለይ እንችላለን?
22 መዝሙር 90 በሚከተሉት ልመናዎች ይደመደማል:- “የጌታ የአምላካችን ሞገስ በላያችን ይሁን፤ የእጆቻችንን ሥራ ፍሬያማ አድርግልን፤ አዎን፣ ፍሬያማ አድርግልን።” (መዝሙር 90:17 አ.መ.ት) እነዚህ ቃላት አምላክ በእርሱ አገልግሎት የምናከናውነውን ጥረት እንዲባርክልን ልንጸልይ እንደምንችል ያሳያሉ። ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆን ጓደኞቻቸው የሆኑት “ሌሎች በጎች” “የጌታ የአምላካችን ሞገስ በላያችን” በመሆኑ እንደሰታለን። (ዮሐንስ 10:16) የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመሆንም ሆነ በሌሎች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች አምላክ ‘የእጆቻችንን ሥራ ፍሬያማ በማድረጉ’ ምንኛ ደስተኞች ነን!
ዕድሜያችንን መቁጠራችንን እንቀጥል
23, 24. በ90ኛው መዝሙር ላይ ማሰላሰላችን ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው?
23 በ90ኛው መዝሙር ላይ ማሰላሰላችን እውነተኛ ‘መጠጊያችን በሆነው’ በይሖዋ ላይ ያለንን ትምክህት ያጠናክርልናል። ሕይወት አጭር ስለመሆኑ በተናገራቸው ቃላት ላይ በማሰላሰል ዕድሜያችንን በመቁጠር ረገድ መለኮታዊ መመሪያ እንደሚያስፈልገን ይበልጥ መገንዘብ ይኖርብናል። አምላካዊ ጥበብ ለማግኘትና ለማንጸባረቅ ሳናሰልስ የምንጥር ከሆነ የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነትና በረከት እንደምናገኝ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
24 ይሖዋ ዕድሜያችንን እንዴት መቁጠር እንደምንችል ማስተማሩን ይቀጥላል። እኛም መመሪያውን እሺ ብለን የምንከተል ከሆነ ዕድሜያችንን ለዘላለም ልንቆጥር እንችላለን። (ዮሐንስ 17:3) በእርግጥ ለዘላለም መኖር የምንፈልግ ከሆነ ይሖዋን መጠጊያችን ማድረግ ይገባናል። (ይሁዳ 20, 21 NW ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው ይህ ጉዳይ አበረታች በሆኑት በ91ኛው የመዝሙር ቃላት ውስጥ በጥሩ መንገድ ተብራርተዋል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ይሖዋ እውነተኛ ‘መጠጊያ’ የሆነልን እንዴት ነው?
• ይሖዋ ምንጊዜም እኛን ለመርዳት ዝግጁ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
• ይሖዋ ‘ዕድሜያችንን በመቁጠር’ ረገድ የሚረዳን እንዴት ነው?
• ‘በዘመናችን ሁሉ ደስተኞች’ እንድንሆን የሚያስችለን ምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ “ገና ተራሮች ሳይወለዱ” አምላክ ነው
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከይሖዋ አንጻር የ969 ዓመቱ ማቱሳላ እንኳ የኖረው ከአንድ ቀን ለሚያንስ ጊዜ ነው
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ‘የእጆቻችንን ሥራ ፍሬያማ አድርጎልናል’