በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ግብዝነትን እንዴት ልትመለከተው ይገባል?

ግብዝነትን እንዴት ልትመለከተው ይገባል?

ግብዝነትን እንዴት ልትመለከተው ይገባል?

በጌተሰማኒ የአትክልት ሥፍራ የአስቆሮቱ ይሁዳ ወደ ኢየሱስ ቀረበና “ሳመው።” ይህ የተለመደ ሞቅ ያለ የፍቅር መግለጫ ነበር። ይሁን እንጂ ይሁዳ ይህን ያደረገው በዚያ ምሽት ኢየሱስን ሊይዙት ለመጡት ሰዎች የቱ እንደሆነ ለመጠቆም ነበር። (ማቴዎስ 26:48, 49) ይሁዳ የቅንነት ጭምብል በማጥለቅ በውስጡ ያለውን መጥፎ ፍላጎት የሚደብቅና ያልሆነውን ሆኖ ለመታየት የሚሞክር ግብዝ ሰው ነበር። “ግብዝ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “መልስ የሚሰጥ” ማለት ሲሆን አንድን የመድረክ ተዋናይም ለማመልከት ያገለግል ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ይህ ቃል አስመሳይ በመሆን ሌሎችን ለማታለል የሚጥርን ሰው ለማመልከት ይሠራበት ጀመር።

የግብዝነት ድርጊት ስታይ ምን ይሰማሃል? ለምሳሌ የሲጋራ አምራቾች ምርታቸው ለጤና ጎጂ እንደሆነ የሚያሳይ የህክምና ማስረጃ እያለ ሲጋራ ማጨስን ሲያበረታቱ ስትመለከት ትናደዳለህ? እንከባከባቸዋለን ብለው በአደራ የተቀበሏቸውን ሰዎች የሚያንገላቱ ሞግዚቶች ግብዝነት ያበሳጭሃል? እውነተኛ ነው ብለህ የተማመንክበት ወዳጅህ አታላይ ሆኖ ሲገኝ ታዝናለህ? ሃይማኖታዊ ግብዝነትስ እንዴት ይነካሃል?

“እናንተ ግብዞች . . . ወዮላችሁ”

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የነበረውን ሃይማኖታዊ ሁኔታ ተመልከት። ጻፎችና ፈሪሳውያን ታማኝ የአምላክ ሕግ አስተማሪዎች እንደ ሆኑ አድርገው ራሳቸውን ቢያቀርቡም የሚያስተምሩት የሰዎችን ትኩረት ከአምላክ የሚያርቁ ሰብዓዊ ትምህርቶችን ነበር። ጻፎችና ፈሪሳውያን የሕጉን ፊደል ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ ቢያደርጉም በፍቅርና በርኅራኄ ላይ የተመሠረቱትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ግን ችላ ብለው ነበር። በሰው ፊት ሲታዩ ለአምላክ ያደሩ ይመስላሉ፤ በውስጣቸው ግን ክፋትን ተሞልተዋል። ቃላቸውና ድርጊታቸው ፈጽሞ አይጣጣምም። ማንኛውንም ነገር የሚያደርጉት ‘በሰዎች ዘንድ ለመታየት’ ነበር። “በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጥ ግን የሙታን አጥንት ርኲሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን” ይመስላሉ። ኢየሱስ በተደጋጋሚ “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን . . . ወዮላችሁ” በማለት በድፍረት ግብዝነታቸውን አጋልጧል።​—⁠ማቴዎስ 23:5, 13-31

በዚያን ዘመን በሕይወት ኖረህ ቢሆን እንደሌሎች ልበ ቅን ሰዎች ሁሉ አንተም በዚህ ሃይማኖታዊ ግብዝነት እንደምትንገሸገሽ መገመት አያዳግትም። (ሮሜ 2:21-24፤ 2 ጴጥሮስ 2:​1-3) ይሁን እንጂ ጻፎችና ፈሪሳውያን በሚያሳዩት ግብዝነት ሳቢያ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ያስተምሩትና ይከተሉት የነበረውን ጨምሮ የትኛውንም ሃይማኖት አልቀበልም እስክትል ድረስ ትመረር ነበርን? እንዲህ ማድረግህ በራስህ ላይ ጉዳት አያስከትልም?

ሃይማኖታዊ ነን የሚሉ ሰዎች የሚያሳዩት ግብዝነት ጨርሶ ሃይማኖት የተባለ ነገር እንድንጠላ ሊያደርገን ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ አቋማችን የእውነተኛ አምላኪዎችን ግብዝነት የሌለበት አኗኗር እንዳናስተውል ይጋርደናል። ከግብዝነት ለመሸሽ የምንወስደው እርምጃ ከእውነተኛ ወዳጆችም ጭምር ሊያርቀን ስለሚችል ግብዝነትን በተመለከተ ያለን አቋም ምክንያታዊና ሚዛናዊ መሆኑ ተገቢ ነው።

“ተጠንቀቁ”

በመጀመሪያ ግብዞች የሚባሉት እነማን እንደሆኑ መለየት መቻል አለብን። ይህ ሁልጊዜ ቀላል ነው ማለት አይደለም። የአንድ ቤተሰብ አባላት ይህን የተገነዘቡት በራሳቸው ላይ ከደረሰው አሳዛኝ ሁኔታ ነው። እናት በሕመም ምክንያት ለረጅም ጊዜ ራስዋን አታውቅም ነበር። በፈጸመው የሕክምና ስሕተት ምክንያት እናታቸው እንዲህ እንድትሆን ባደረገው ሆስፒታል ላይ ቤተሰቡ ክስ ለመመሥረት በአቅራቢያው በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ሰባኪ የሆነ አንድ ጠበቃ ቀጠረ። ምንም እንኳ ሆስፒታሉ 3.4 ሚልዮን ዶላር ካሳ ቢከፍልም እናታቸው በበጎ አድራጊዎች እርዳታ ስትታከም ቆይታ ስትሞት ለቀብሯ የሚከፈል ገንዘብ መታጣቱ የቤተሰቡን ሐዘን ይበልጥ መሪር አደረገው። ለምን? ምክንያቱም ጠበቃው አብዛኛውን ገንዘብ ወደ ኪሱ ብሎት ነበር። ይህን ጠበቃ አስመልክቶ አንድ የሕግ መጽሔት ሲናገር:- “ስብከቱም እንደ ድርጊቱ ከሆነ . . . ‘እንጸልይ’ ሳይሆን ‘እናጭበርብር’ ነው የሚለው ማለት ነው” ብሏል። ከእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ራሳችንን ልንጠብቅ የምንችለው እንዴት ነው?

ኢየሱስ በዘመኑ በሃይማኖታዊ ግብዝነት ተከበው ይኖሩ ለነበሩት ሰዎች “ተጠንቀቁ” የሚል ምክር ሰጥቷቸው ነበር። (ማቴዎስ 16:6፤ ሉቃስ 12:1) አዎን፣ መጠንቀቅ አለብን። ሰዎች በጎ ዓላማ ይዘው የተነሱ ወይም ቅን አስተሳሰብ ያላቸው መስለው ሊታዩ ይችላሉ። ሆኖም በዚህ ብቻ በእነርሱ ላይ እምነት በመጣል ፋንታ የማስተዋል ችሎታችንን መጠቀም ያስፈልገናል። ሐሰተኛ የብር ኖት በዝውውር ላይ እንዳለ ብናውቅ የያዝነው ገንዘብ እውነተኛ መሆኑን አናረጋግጥም?

በእውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሳይቀር ግብዞች ነበሩ። ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ እነርሱን በተመለከተ “እነዚህ በፍቅር ግብዣችሁ ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ ከውኃ በታች እንደ ተሰወሩ ዓለቶች ናቸው፤ ያለፍርሃት ራሳቸውን የሚመግቡ እረኞች፣ በነፋስ ወዲያና ወዲህ የሚገፉ ዝናብ አልባ ደመናዎች፣ በመከር መጨረሻ ፍሬ የማይገኝባቸው ዛፎች” ናቸው በማለት አስጠንቅቋል።​—⁠ይሁዳ 12 NW 

‘መጠንቀቅ’ ማለት ራስ ወዳድና በአምላክ ቃል ላይ ያልተመሠረቱ ሐሳቦችን የሚያስፋፋ ሆኖ ሳለ አፍቃሪ መስሎ በሚቀርብ ሰው አለመታለል ማለት ነው። እንደዚህ ዓይነት ሰው ጸጥ ባለ ውኃ ውስጥ እንዳለ ሹል ዓለት ጥንቁቅ ባልሆነ ሰው መንፈሳዊ መርከብ ላይ የመሰበር አደጋ ሊያደርስበት ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 1:​19) ይህ ግብዝ ሰው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ነገር እንደሚሰጥ ቢናገርም ‘ዝናብ አልባ እንደሆነ ደመና’ ጠብ የሚ​ለው ነገር አይኖርም። ልክ ምንም እንደማያፈራ ዛፍ እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍሬ አያፈራም። (ማቴዎስ 7:​15-​20፤ ገላትያ 5:​19-21) አዎን፣ ከእንደነዚህ ዓይነት አሳሳቾች ራሳችንን መጠበቅ አለብን። ይህ ሲባል ግን የማንኛውንም ሰው ውስጣዊ ዝንባሌ መጠራጠር እንጀምራለን ማለት አይደለም።

“አትፍረዱ”

ፍጽምና የሌላቸው የሰው ልጆች የራሳቸውን ጉድለት ችላ ብለው የሌሎችን እንከን መለቃቀም ይቀናቸዋል! ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ ደግሞ ለግብዝነት ባሕርይ የተጋለጥን ያደርገናል። ኢየሱስ “አንተ ግብዝ፣ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፣ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጕድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ” ብሏል። “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፣ . . . በወንድምህም ዓይን ያለውን ጕድፍ ስለ ምን ታያለህ፣ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም?” በማለት የሰጠውን ምክር መስማታችን ተገቢ ነው።​—⁠ማቴዎስ 7:1-5

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ግብዞች ሊያስመስላቸው የሚችል ድርጊት ሲፈጽሙ ብንመለከት ቸኩለን ከግብዞች ጎራ እንዳንመድባቸው መጠንቀቅ አለብን። ለምሳሌ ሐዋርያው ጴጥሮስ ከኢየሩሳሌም የመጡ ከአይሁድ ወገን የሆኑ ክርስቲያኖችን ለማስደሰት በአንጾኪያ ከነበሩ መሰል አሕዛብ አማኞች ‘አፈግፍጎና ተለይቶ’ ነበር። በርናባስም ‘በጴጥሮስና በሌሎች አይሁዳውያን ግብዝነት’ እስከመሳብ ደርሶ ነበር። ጴጥሮስ አሕዛብ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ እንዲቀላቀሉ መንገድ የመክፈት ልዩ መብት አግኝቶ የነበረ ቢሆንም እንዲህ ዓይነት የግብዝነት ባሕርይ አሳይቷል። (ገላትያ 2:11-14፤ ሥራ 10:24-28, 34, 35) ነገር ግን ይህ የጴጥሮስና የበርናባስ ትንሽ ስህተት ከአስቆሮቱ ይሁዳ ወይም ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጎራ እንዲመደቡ አላደረጋቸውም።

“ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን”

ኢየሱስ “ለሰዎች መልካም ስታደርግ፣ በምኩራብና በጎዳና በሰዎች ዘንድ ሊደነቁ እንደሚፈልጉ ተዋንያን በፊትህ መለከት አታስነፋ” በማለት ምክር ሰጥቷል። (ማቴዎስ 6:​2 ፊሊፕስ) ሐዋርያው ጳውሎስም “ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 12:​9) ወጣቱ ጢሞቴዎስንም “ከንጹሕ ልብና . . . ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር” እንዲኖረው አበረታቶታል። (1 ጢሞቴዎስ 1:​5) ከራስ ወዳድነትና ከአስመሳይነት ነፃ የሆነ እውነተኛ ፍቅርና እምነት ካለን ሰዎች ያምኑናል። አብረውን ለሚሆኑ ሁሉ የጥንካሬና የብርታት ምንጭ እንሆናለን። (ፊልጵስዩስ 2:4፤ 1 ዮሐንስ 3:17, 18፤ 4:20, 21) ከሁሉም በላይ ደግሞ የይሖዋን ሞገስ እናገኛለን።

በአንጻሩ ደግሞ የግብዝነት ባሕርይ የተጠናወታቸው ሰዎች ውሎ አድሮ ጥፋት ይጠብቃቸዋል። ግብዝነት በመጨረሻ መጋለጡ አይቀርም። ኢየሱስ “የማይገለጥ የተከደነ፣ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለም” ብሏል። (ማቴዎስ 10:26፤ ሉቃስ 12:2) ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞንም “እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፣ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፣ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና” በማለት ተናግሯል።​—⁠መክብብ 12:14

እስከዚያ ግን የሌሎች ግብዝነት የእውነተኛ ወዳጆቻችንን ከልብ የመነጨ ፍቅር እንድናጣ እስኪያደርገን ድረስ ተጽዕኖ እንዲያሳድርብን ለምን እንፈቅዳለን? እጅግም ተጠራጣሪ ሳንሆን መጠንቀቅ እንችላለን። በተቻለን መጠን ግብዝነት የሌለበት ፍቅርና እምነት እንዲኖረን እንጣር።​—⁠ያዕቆብ 3:17፤ 1 ጴጥሮስ 1:​22

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጻፎችና ፈሪሳውያን ግብዝነት ኢየሱስንና ደቀ መዛሙርቱን ከመከተል እንዲያግድህ ትፈቅድ ነበር?