“በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን”
“በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን”
ድንገት መብራት ጠፍቶ አካባቢያችን በጨለማ እስካልተዋጠ ድረስ የብርሃንን መኖር እምብዛም አናደንቅም። የሚያስደስተው ግን የሰማይዋ “የኃይል ማመንጫ ጣቢያ፣” ፀሐይ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ናት። ከፀሐይ ለምናገኘው ብርሃን ምስጋና ይግባውና ማየት፣ መብላት፣ መተንፈስ እንዲሁም መኖር ችለናል።
ብርሃን ለሕይወት የግድ አስፈላጊ በመሆኑ በመጀመሪያው የፍጥረት ቀን እንደታየ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ መጠቀሱ ሊያስገርመን አይገባም። “እግዚአብሔርም:- ብርሃን ይሁን አለ፤ ብርሃንም ሆነ።” (ዘፍጥረት 1:3) እንደ ንጉሥ ዳዊት ያሉ አምላካዊ ፍርሃት ያላቸው ሰዎች ይሖዋ የሕይወትና የብርሃን ምንጭ መሆኑን ተገንዝበው ነበር። ዳዊት “የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና፤ በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን” ሲል ጽፏል።—መዝሙር 36:9
የዳዊት ቃላት ቃል በቃልም ሆነ በምሳሌያዊ አባባል ይሠራሉ። ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዳስቀመጠው “ለማየት ብርሃን አስፈላጊ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም።” አክሎም እንዲህ ይላል:- “የዓይንን ያክል ለሰው አንጎል ብዙ መረጃ የሚያቀብል የስሜት ሕዋስ የለም።” ብዙ ነገሮችን መማራችን በማየት ችሎታችን ላይ የተመካ በመሆኑና ይህን ችሎታ በተገቢ መንገድ ለመጠቀም ደግሞ ብርሃን ስለሚያስፈልግ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ብርሃን በምሳሌያዊ ሁኔታም ተሠርቶበታል።
በመሆኑም ኢየሱስ ለተከታዮቹ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 8:12) ኢየሱስ በምሳሌያዊ ሁኔታ የተናገረለት ብርሃን በአዳማጮቹ አእምሮና ልብ ውስጥ መንፈሳዊ የእውቀት ብርሃን ሊፈነጥቅ የሚችለውና እሱ የሰበከው የእውነት መልእክት ነው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለዓመታት በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ከቆዩ በኋላ አምላክ ለሰው ልጅ ያለውን ዓላማና የመንግሥቲቱን ተስፋ መረዳት ችለዋል። ይህ እውቀት ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ በመሆኑ በእርግጥም “የሕይወት ብርሃን” ነው። ኢየሱስ ለሰማያዊ አባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ እንዲህ ብሏል:- “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” (ዮሐንስ 17:3) ይህንን መንፈሳዊ ብርሃን ፈጽሞ አቅልለን መመልከት የለብንም!