በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወርቃማው ሕግ—በስፋት የሚታወቅ ትምህርት

ወርቃማው ሕግ—በስፋት የሚታወቅ ትምህርት

ወርቃማው ሕግ—በስፋት የሚታወቅ ትምህርት

“እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው።”​ማቴዎስ 7:⁠12

እነዚህ ቃላት ኢየሱስ ክርስቶስ የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ በዝነኛ የተራራ ስብከቱ ላይ የተናገራቸው ናቸው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ባሉት ብዙ መቶ ዘመናት ይህንን ቀላል አነጋገር አስመልክቶ ብዙ ተብሏል፣ ብዙ ተጽፏል። እንደ አብነት ለመጥቀስ ያህል “የቅዱስ ጽሑፉ መሠረት፣” “አንድ ክርስቲያን ለባልንጀራው ማድረግ የሚጠበቅበትን ነገር ጠቅለል አድርጎ የሚገልጽ ሐሳብ፣” እና “መሠረታዊ የግብረገብ መመሪያ” ተብሎ ተወድሷል። በጣም የታወቀ ከመሆኑ የተነሣ ብዙውን ጊዜ ወርቃማው ሕግ እየተባለ ይጠራል።

ይሁን እንጂ ስለ ወርቃማው ሕግ የሚነገረው ነገር ክርስቲያን ተብለው በሚጠሩት ሰዎች ዙሪያ ብቻ የተወሰነ አይደለም። የአይሁድ እምነት፣ የቡድሃ እምነትና የግሪክ ፍልስፍና ይህን መሠረታዊ የግብረገብ እውነት በተለያዩ መንገዶች አብራርተውታል። በተለይ ግን በሩቅ ምሥራቅ ሕዝብ ዘንድ በስፋት የሚታወቀው አባባል፣ በምሥራቁ ዓለም እንደ ታላቅ የሃይማኖት ጠቢብና አስተማሪ የሚታየው ኮንፊሽየስ የተናገረው ነው። ኮንፊሽየስ ከጻፋቸው አራት መጽሐፎች መካከል አናሌክትስ በተባለው ሦስተኛ መጽሐፍ ውስጥ ይህ ሐሳብ ሦስት ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። ሁለቱ፣ ኮንፊሽየስ ተማሪዎቹ ለጠየቁት ጥያቄ “እንዲደረግባችሁ የማትፈልጉትን ነገር በሌሎች ላይ አታድርጉ” በማለት መልስ የሰጠባቸው አጋጣሚዎች ናቸው። በሌላ ወቅት ደግሞ ደዝጎንግ የተባለ ተማሪው “ሌሎች እንዲያደርጉብኝ የማልፈልገውን ነገር እኔም በእነርሱ ላይ ማድረግ አልፈልግም” ብሎ በኩራት ሲናገር አስተማሪው በጉዳዩ ላይ እንዲያስብበት በሚያደርግ መንገድ “ጥሩ ብለሃል፤ ሆኖም እስከ አሁን እንዲህ ማድረግ አልቻልክም” በማለት መልሶለታል።

አንድ ሰው እነዚህን ቃላት ሲያነብ ኮንፊሽየስ ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት ከአሉታዊ ድርጊት አኳያ እንደገለጻቸው መረዳት አያዳግተውም። በሁለቱ አነጋገሮች መካከል ያለው ግልጽ ልዩነት ኢየሱስ የተናገረው ወርቃማው ሕግ ለሌሎች መልካም በማድረግ አዎንታዊ እርምጃ መውሰድን የሚጠይቅ መሆኑ ነው። ሰዎች ለሌሎች አሳቢነት በማሳየት፣ ሌሎችን ለመርዳት አንዳንድ ነገር በማድረግና በየዕለቱ በዚህ ደንብ በመመራት ኢየሱስ ከተናገረው አዎንታዊ ተግባር የሚጠይቅ አባባል ጋር በሚስማማ መንገድ ቢኖሩ ኖሮ ይህ ዓለም ከአሁኑ የተሻለ የሚሆን አይመስልህም? እንደዚያ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።

ሕጉ የተጠቀሰው በአዎንታዊ ጎኑም ይሁን በአሉታዊ ወይም በሌላ በማንኛውም መንገድ ዋናው ቁም ነገር በተለያዩ ዘመናትና አካባቢዎች የኖሩና የተለያየ ሁኔታ ያላቸው ሰዎች ወርቃማው ሕግ በሚያስተላልፈው መልእክት ላይ ከፍተኛ እምነት መገንባታቸው ነው። ይህ ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ የጠቀሰው ሐሳብ በየትኛውም ቦታና በማንኛውም ዘመን የኖሩ ሰዎችን ሕይወት የሚነካ ዓለም በሰፊው የሚታወቅ ትምህርት መሆኑን የሚያሳይ ነው።

እስቲ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ሰዎች እንዲያከብሩኝ፣ አድሎ እንዳይፈጽሙብኝ፣ እንዳይሸነግሉኝ እፈልጋለሁ? የዘር መድሎ፣ ወንጀልና ጦርነት በሌለበት ዓለም ውስጥ መኖር እፈልጋለሁ? እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ለሌላው ስሜትና ደህንነት በሚያስብበት ቤተሰብ ውስጥ መኖር እፈልጋለሁ?’ እንደ እውነቱ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ አልፈልግም የሚል ማን ይኖራል? የሚያሳዝነው ግን ይህን ሁኔታ ያገኙ ሰዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው። እንዲያውም ለአብዛኞቹ እንዲህ ያሉትን ነገሮች ተስፋ ማድረግ ሕልም ሆኖ ይታያቸዋል።

እየደበዘዘ የመጣው ወርቃማው ሕግ

በታሪክ ውስጥ የሰዎች መብት ሙሉ በሙሉ ተረግጦ በሰብዓዊው ፍጥረት ላይ ወንጀል የተፈጸመባቸው የተለያዩ አጋጣሚዎች ተከስተዋል። ከእነዚህ መካከል በአፍሪካ የተካሄደው የባሪያ ንግድ፣ የናዚ የመግደያ ካምፖች፣ በኃይል የሚፈጸም የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛና በየቦታው የተከሰቱት አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋዎች ይገኙበታል። የተፈጸሙት አሰቃቂ ድርጊቶች ለቁጥር የሚያታክቱ ናቸው።

ዛሬ ያለው በቴክኖሎጂ የመጠቀ ዓለም ራስ ወዳድነት የተጠናወተው ነው። አብዛኞቹ ሰዎች ስለ ሌሎች የሚያስቡት የራሳቸው ጥቅም ወይም መብቴ ነው የሚሉት ነገር እስካልተነካ ድረስ ብቻ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5) ብዙዎች ይህን ያህል ራስ ወዳድ፣ ጨካኝ፣ ስለሌላው ስሜት የማያስቡና የራሳቸው ጥቅም ብቻ የሚታያቸው የሆኑት ለምንድን ነው? ብዙዎች ወርቃማውን ሕግ የሚያውቁት ቢሆንም ከእውነታው የራቀና ጊዜ ያለፈበት አባባል እንደሆነ ተሰምቷቸው ችላ ስለሚሉት አይደለምን? የሚያሳዝነው ደግሞ በአምላክ እናምናለን የሚሉ ብዙ ሰዎች ያላቸው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አለመሆኑ ነው። ደግሞም ዛሬ ካለው አዝማሚያ አንጻር ሲታይ የሰዎች ራስ ወዳድነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንደሚሄድ መገመት አያዳግትም።

ስለሆነም የሚከተሉትን በጣም ወሳኝ ጥያቄዎች መመርመሩ ተገቢ ነው:- በወርቃማው ሕግ መመራት ምን ይጠይቃል? ዛሬም በዚህ ሕግ የሚመሩ ሰዎች አሉ? መላው የሰው ዘር ከወርቃማው ሕግ ጋር በሚስማማ መንገድ የሚኖርበት ጊዜስ ይመጣ ይሆን? ለእነዚህ ጥያቄዎች እውነተኛ መልስ ለማግኘት የሚከተለውን ርዕስ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኮንፊሽየስና ሌሎች ሰዎች ወርቃማውን ሕግ በተለያዩ መንገዶች አስተምረዋል