ወርቃማው ሕግ ዛሬም ይሠራል
ወርቃማው ሕግ ዛሬም ይሠራል
አብዛኛዎቹ ሰዎች ወርቃማውን ሕግ ኢየሱስ ያመነጨው የሥነ ምግባር ትምህርት እንደሆነ አድርገው ቢያስቡም ኢየሱስ ራሱ “ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 7:16
አዎን፣ ወርቃማው ሕግ የሚል ስያሜ ያገኘውን ጨምሮ ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች በአጠቃላይ የመነጩት ኢየሱስን ወደ ምድር ከላከው ፈጣሪ ከይሖዋ አምላክ ነው።
ከመጀመሪያም ቢሆን አምላክ ሰዎችን ሲፈጥር ዓላማው እነርሱ ራሳቸው መያዝ በሚፈልጉበት መንገድ ሌሎችን እንዲይዙ ነበር። “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” በሚለው ጥቅስ ላይ እንደተንጸባረቀው ሰዎችን የፈጠረበት መንገድ ለሌሎች ደህንነት አሳቢ በመሆን ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ነው። (ዘፍጥረት 1:27) ይህም ማለት ሰዎች በሰላም፣ በደስታና በስምምነት ለዘላለም እንዲኖሩ አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ በተወሰነ መጠን ግሩም የሆኑ ባሕርያቱን አካፍሏቸዋል ማለት ነው። ከአምላክ ያገኙት ሕሊና ተገቢውን ሥልጠና ካገኘ እነርሱ ራሳቸው መያዝ በሚፈልጉበት መንገድ ሌሎችን እንዲይዙ ይመራቸዋል።
ራስ ወዳድነት ነገሠ
ታዲያ የሰው ልጅ ሕይወት ጅምሩ እንዲህ ያማረ ከነበረ ችግር የተፈጠረው ምኑ ላይ ነው? በአጭሩ መጥፎ የሆነ የራስ ወዳድነት ባሕርይ ብቅ በማለቱ ነው። ብዙ ሰዎች በዘፍጥረት ምዕራፍ 3 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ምን እንዳደረጉ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ያውቃሉ። አዳምና ሔዋን የአምላክን መሠረታዊ የጽድቅ መስፈርቶች በሙሉ በሚቃወመው በሰይጣን ተገፋፍተው በራሳቸው ለመመራት ሲሉ በራስ ወዳድነት የአምላክን አገዛዝ አንቀበልም አሉ። ይህ የራስ ወዳድነትና የዓመፅ እርምጃቸው በእነርሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በዘሮቻቸው ሁሉ ላይ አሳዛኝ ውጤት አስከትሏል። ይህ ደግሞ ወርቃማው ሕግ ተብሎ የተጠራውን ትምህርት ችላ ማለት የሚያስከትለውን አስከፊ ውጤት በግልጽ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። በዚህ ምክንያት “ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።”—ሮሜ 5:12
በጥቅሉ ሲታይ ሰዎች ለይሖዋ አምላክ ፍቅራዊ መንገዶች ጀርባቸውን ይስጡ እንጂ እሱ አልተዋቸውም። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ለእስራኤል ሕዝብ የሚመሩበትን ሕግ ሰጥቷቸው ነበር። ሕጉ እነርሱ ራሳቸው መያዝ በሚፈልጉበት መንገድ ሌሎችን እንዲይዙ አስተምሯቸዋል። ሕጉ ባሪያዎች፣ አባት የሌላቸው ልጆችና መበለቶች እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የሚገልጽ መመሪያ ሰጥቷል። ድብደባ፣ አፈናና ስርቆት የፈጸሙ ሰዎች እንዴት መዳኘት እንዳለባቸው ይናገራል። ስለ ንጽሕና አጠባበቅ የተሰጡት ሕጎች ለሌሎች ጤንነት አሳቢነት ማሳየትን የሚያንጸባርቁ ነበሩ። ሌላው ቀርቶ ወሲባዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ሕጎችም ተሰጥተዋል። ይሖዋ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ብሎ ለሕዝቡ በመናገር የሕጉን ፍሬ ነገር ጠቅለል አድርጎ ያስቀመጠ ሲሆን ኢየሱስም ከጊዜ በኋላ ይህን ሐሳብ ጠቅሶታል። (ዘሌዋውያን 19:18፤ ማቴዎስ 22:39, 40) ከዚህም በተጨማሪ ሕጉ በእስራኤላውያን መካከል የሚኖሩ ስደተኞች እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የሚገልጽ መመሪያ ይዞ ነበር። “በስደተኛው ግፍ አታድርጉ፤ እናንተ በግብፅ ምድር ስደተኞች ስለ ነበራችሁ የስደተኛ ነፍስ እንዴት እንደ ሆነች አውቃችኋልና” የሚል ትእዛዝ ነበረው። በሌላ አነጋገር እስራኤላውያን ችግር ለደረሰባቸው ሰዎች ከልብ አሳቢነት እንዲያሳዩ ይጠበቅባቸው ነበር።—ዘጸአት 23:9፤ ዘሌዋውያን 19:34፤ ዘዳግም 10:19
እስራኤላውያን ሕጉን በታማኝነት እስከተከተሉ ድረስ ይሖዋ ሕዝቡን ባርኳል። በዳዊትና በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ብሔሩ በልጽጎ የነበረ ሲሆን ሕዝቡም ተደስቶና ረክቶ ይኖር ነበር። ታሪካዊው ዘገባ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሎአቸው ነበር። ይሁዳና እስራኤል . . . እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር።”—1 ነገሥት 4:20, 25
የሚያሳዝነው ግን የብሔሩ ሰላምና መረጋጋት ለረጅም ጊዜ አልዘለቀም። እስራኤላውያን አምላክ ሕግ ቢሰጣቸውም አልጠበቁትም። ከዚህ ይልቅ ራስ ወዳድነት ለሌሎች አሳቢነት እንዳያሳዩ እንቅፋት እንዲሆንባቸው ፈቀዱ። በዚህ ላይ የክህደት ጎዳናቸው ተጨምሮበት በግለሰብም ሆነ በብሔር ደረጃ ችግር ላይ ጥሏቸዋል። በመጨረሻም ይሖዋ በ607 ከዘአበ ባቢሎናውያን የይሁዳን መንግሥት፣ ኢየሩሳሌምን እንዲሁም ዕጹብ ድንቅ ውበት የነበረውን ቤተ መቅደስ ሳይቀር እንዲያጠፉ ፈቀደላቸው። ለምን? “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ቃሌን አልሰማችሁምና እነሆ፣ ልኬ የሰሜንን ወገኖች ሁሉ ባሪያዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እወስዳለሁ፣ በዚህችም ምድር በሚቀመጡባትም ሰዎች በዙሪያዋም ባሉ በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ላይ አመጣቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፣ ለመደነቂያና ለማፍዋጫም ለዘላለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ።” (ኤርምያስ 25:8, 9) የይሖዋን ንጹሕ አምልኮ መተዋቸው እንዴት ያለ ጉዳት አስከትሎባቸዋል!
ሊኮረጅ የሚገባው ምሳሌ
በሌላ በኩል ኢየሱስ ክርስቶስ ወርቃማውን ሕግ በማስተማር ብቻ ሳይወሰን በዚያ በመመራት ረገድ ግሩም ምሳሌ ሆኗል። ለሌሎች ደህንነት ከልብ ያስብ ነበር። (ማቴዎስ 9:36፤ 14:14፤ ሉቃስ 5:12, 13) አንድ ቀን ኢየሱስ ናይን በምትባል ከተማ አቅራቢያ ለቀብር ከሚሄዱ ሰዎች መካከል ልጅዋን በሞት በማጣትዋ ምክንያት ቅስሟ የተሰበረ አንዲት መበለት ተመለከተ። መጽሐፍ ቅዱስ ሁኔታውን ሲገልጽ “ጌታም ባያት ጊዜ አዘነላት” ይላል። (ሉቃስ 7:11-15) ቫይንስ ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ የተባለው መዝገበ ቃላት “አዘነ” ተብሎ የተተረጎመው ሐረግ “አንጀቱ ተላወሰ” ማለት እንደሆነ ጠቅሷል። የልቧ ኃዘን ተሰምቶት ነበር። ይህ ደግሞ ኃዘኗን ለማቅለል አዎንታዊ እርምጃ እንዲወስድ አነሳስቶታል። ኢየሱስ ልጁን ከሞት አስነስቶ ‘ለእናቱ በሰጣት’ ጊዜ መበለቷ ምን ያህል ተደስታ ይሆን!
በመጨረሻም ኢየሱስ ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ የሰው ዘር ከኃጢአትና ከሞት ባርነት እንዲላቀቅ ሥቃይ ለመቀበልና ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኗል። በወርቃማው ሕግ በመመራት ረገድ ከዚህ የላቀ ምን ምሳሌ ሊኖር ይችላል?—ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 15:13፤ ዕብራውያን 4:15
በወርቃማው ሕግ የሚመሩ ሰዎች
በዘመናችንስ በወርቃማው ሕግ የሚመሩ ሰዎች አሉ? አዎን፣ አሉ። ደግሞም እንዲህ የሚያደርጉት በሚመቻቸው ጊዜ ብቻ አይደለም። ለምሳሌ ያህል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በናዚ ጀርመን ሥር የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች በአምላክ ላይ ያላቸውን እምነትና ለባልንጀሮቻቸው ያላቸውን ፍቅር አጽንተው በመያዝ ወርቃማውን ሕግ ለመጣስ ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል። ሕዝቡ አይሁዳውያንን እንዲጠላቸውና አድልዎ እንዲፈጸምባቸው መንግሥት ቅስቀሳ ቢያካሂድም የይሖዋ ምሥክሮች ወርቃማውን ሕግ ከመከተል ወደኋላ አላሉም። ሌላው ቀርቶ በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ያለቻቸውን ምግብ በረሃብ ለሚሠቃዩ አይሁዳውያንና አይሁዳውያን ላልሆኑ እስረኞች በማካፈል አሳቢነት ማሳየታቸውን ቀጥለዋል። ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት መሣሪያ አንስተው ሌሎችን እንዲገድሉ ቢያዝዛቸውም ሌሎች እንዲገድሏቸው እንደማይፈልጉ ሁሉ እነርሱም ከመግደል ተቆጥበዋል። ደግሞስ እንደ ራሳቸው አድርገው የሚወድዷቸውን ሰዎች የሚገድሉበት ምን እጅ ይኖራቸዋል? ብዙዎቹ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ወደ ማጎሪያ ካምፖች ከመላካቸውም ባሻገር ተገድለዋል።—ማቴዎስ 5:43-48
አሁን ይህን ርዕስ በምታነብበት ጊዜ እንኳን ወርቃማው ሕግ ተግባራዊ በመሆኑ ምክንያት በተደረገ ዝግጅት በኢሳይያስ 2:2-4 ላይ በትንቢት እንደተነገረው “ብዙዎች አሕዛብ” እንዲያውም አሁን ቁጥራቸው በዓለም ዙሪያ ከስድስት ሚልዮን በላይ የሆነ ሰዎች ‘የይሖዋን መንገድ ተምረዋል፣ በጎዳናውም ይሄዳሉ።’ በምሳሌያዊ መንገድ “ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውን ማጭድ ለማድረግ” እንዴት እንደሚቀጠቅጡ ተምረዋል። በእነዚህ አስጨናቂ ቀናት ውስጥ ሰላምና ደህንነት አግኝተዋል።
እየተጠቀምህ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ዛሬ ብዙ ሰዎች በተስፋ መቁረጥና ከአቅም በላይ በሆኑ ችግሮቻቸው ምክንያት እንደሚሠቃዩ ይገነዘባሉ። ስለዚህ ሌሎች ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘው ተስፋና ተግባራዊ ሊሆን ስለሚችለው መመሪያ እንዲማሩ ለመርዳት በፈቃደኝነት በጎ ሥራ እየሠሩ ነው። ይህ ሁሉ ከዚህ በፊት ተደርጎ በማያውቅ መጠን በመከናወን ላይ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የማስተማር ሥራ አካል ነው። ምን ውጤት አስገኝቷል?አንተስ?
እስቲ ለአንድ አፍታ በሰይጣን ዲያብሎስ ገፋፊነት በኤደን ገነት ውስጥ ከተፈጸመው ዓመፅ ወዲህ የሰው ልጅ ወርቃማውን ሕግ ገሸሽ በማድረጉ ምክንያት የደረሰበትን መከራና ሥቃይ አስብ። ይሖዋ በቅርቡ ሁኔታውን የመለወጥ ዓላማ አለው። እንዴት? “ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ።” (1 ዮሐንስ 3:8) የዲያብሎስ ሥራ የሚፈርሰው በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ማለትም ጥበቡና ችሎታው ባለውና ወርቃማውን ሕግ ባስተማረው እንዲሁም በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ ባደረገው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ነው።—መዝሙር 37:9-11፤ ዳንኤል 2:44
የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት “ጐለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም። ሁልጊዜ ይራራል ያበድርማል፣ ዘሩም በበረከት ይኖራል” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 37:25, 26) ዛሬ አብዛኛው ሰው ለሌላው ‘ከመራራትና ከማበደር’ ይልቅ መቀበልና መንጠቅ የሚቀናው ሆኗል ቢባል አትስማማም? በግልጽ እንደሚታየው ወርቃማውን ሕግ መከተል አንድ ሰው አሁንም ሆነ በመጪው የአምላክ መንግሥት ሥር በረከት እንዲያገኝ ስለሚያስችለው ወደ እውነተኛ ሰላምና ደህንነት ይመራል ለማለት ይቻላል። የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ የሚታየውን የራስ ወዳድነትና የክፋት ርዝራዥ ሙሉ በሙሉ ጠራርጎ በማስወገድ ብልሹ የሆነውን የአሁኑን ሰብዓዊ አገዛዝ አምላክ በሚያቋቁመው አዲስ ሥርዓት ይተካዋል። በዚያን ጊዜ ሰዎች ሁሉ በወርቃማው ሕግ መመራት የሚያስገኘውን ደስታ ያጣጥማሉ።—መዝሙር 29:11፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ወርቃማውን ሕግ በማስተማር ብቻ ሳይወሰን ተግባራዊ በማድረግም ግሩም ምሳሌ ትቷል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወርቃማውን ሕግ መከተል ወደ እውነተኛ ሰላምና ደህንነት ይመራል