በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋን ግብዣዎች መቀበል በረከት ያስገኛል

የይሖዋን ግብዣዎች መቀበል በረከት ያስገኛል

የሕይወት ታሪክ

የይሖዋን ግብዣዎች መቀበል በረከት ያስገኛል

ማሪያ ዶ ሴዉ ዛናርዲ እንደተናገረችው

“ይሖዋ የሚያደርገውን ያውቃል። ግብዣ ካቀረበልሽ ግብዣውን በትህትና መቀበል አለብሽ።” አባቴ ከ45 ዓመታት በፊት የተናገራቸው እነዚህ ቃላት የይሖዋ ድርጅት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድጀምር ያቀረበልኝን የመጀመሪያ ግብዣ እንድቀበል ረድተውኛል። ዛሬም ቢሆን አባቴ ለሰጠኝ ምክር በጣም አመስጋኝ ነኝ። እንዲህ ያሉትን ግብዣዎች መቀበሌ ታላላቅ በረከቶች አስገኝቶልኛል።

አባቴ በ1928 የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ኮንትራት ከገባ በኋላ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር አደረበት። እርሱ የሚኖረው በመካከለኛው ፖርቱጋል ስለነበር ከአምላክ ጉባኤ ጋር የሚያደርገው ግንኙነት በፖስታ በሚያገኛቸው ጽሑፎችና ከአያቶቼ በወረሰው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የተወሰነ ነበር። በ1949 ማለትም የ13 ዓመት ልጅ ሳለሁ ቤተሰባችን የእናቴ የትውልድ አገር ወደሆነው ወደ ብራዚል በመሰደድ በሪዮ ዲ ጃኔሮ ከተማ ዳርቻ መኖር ጀመረ።

አዳዲሶቹ ጎረቤቶቻችን ቤተ ክርስቲያናቸውን እንድንጎበኝ ስለጋበዙን ለተወሰኑ ጊዜያት አብረናቸው ሄድን። አባቴ ስለ ሲኦል እሳት፣ ስለ ነፍስና ስለ ምድር የወደፊት እጣ እያነሳ እነርሱን መጠየቅ ቢያስደስተውም እነርሱ ግን የሚሰጡት መልስ አልነበራቸውም። አባቴ “እውነተኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መጠበቅ ይኖርብናል” ማለትን ያዘወትር ነበር።

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ማየት የተሳነው ሰው ቤታችንን አንኳኩቶ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ቅጂዎችን አበረከተልን። አባቴ እነዚያኑ ተመሳሳይ ጥያቄዎች ሲጠይቀው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ትክክለኛ መልሶች ሰጠው። በቀጣዩ ሳምንት አንዲት ሌላ የይሖዋ ምሥክር መጥታ ተጨማሪ ጥያቄዎ​ቻችንን ከመለሰችልን በኋላ ወደ “መስክ” መውጣት እንዳለባት በመግለጽ ይቅርታ እንድናደርግላት ጠየቀች። አባቴ ለማለት የፈለገችው ነገር እንዳልገባው ሲነግራት ማቴዎስ 13:​38ን በማንበብ የስብከቱ ሥራ በመላው ዓለም መሠራት ያለበት ሥራ እንደሆነ ገለጸችለት። ከዚያም አባቴ “እኔም መሄድ እችላለሁ?” በማለት ሲጠይቃት “እንዴታ” በማለት መለሰች። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንደገና በማግኘታችን እጅግ ተደሰትን! አባቴ በቀጣዩ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተጠመቀ ሲሆን እኔ ደግሞ ከዚህ ብዙም ሳይቆይ ኅዳር 1955 ተጠመቅሁ።

የመጀመሪያውን ግብዣ መቀበል

ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ሪዮ ዲ ጃኔሮ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በሙሉ ጊዜ የስብከቱ ሥራ እንድካፈል የሚያበረታታ መልእክት የያዘ አንድ ትልቅ ቡናማ ፖስታ ደረሰኝ። በወቅቱ እናቴ ጤንነቷ ጥሩ ስላልነበረ አባቴን ምክር ጠየቅኩት። ፈርጠም ብሎ “ይሖዋ የሚያደርገውን ያውቃል” ሲል መለሰልኝ። “ግብዣ ካቀረበልሽ ግብዣውን በትህትና መቀበል አለብሽ።” በእነዚህ ቃላት በመበረታታት ማመልከቻ ቅጹን ሞልቼ ሐምሌ 1, 1957 የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ። በመጀመሪያ የተመደብኩት በሪዮ ዲ ጃኔሮ ግዛት በምትገኘው ትሬስ ሪዮስ ከተማ ነበር።

መጀመሪያ አካባቢ የካቶሊኮችን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ስለማንጠቀም የከተማዋ ነዋሪዎች እኛን ለመስማት ፈቃደኞች አልነበሩም። ይሁን እንጂ ቀናተኛ ካቶሊክ ከነበረው ከዠራልዶ ራማልዮ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስንጀምር ሁኔታዎች ተለወጡ። በእርሱ እርዳታ የከተማው ቄስ ፊርማ የሰፈረበትን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ያገኘሁ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ወዲህ ተቃውሞ የሚያስነሳ ሰው ሲያጋጥመኝ የቄሱን ፊርማ ስለማሳየው ዝም ይላል። ብዙም ሳይቆይ ዠራልዶ ተጠመቀ።

በ1959 በትሬስ ሪዮስ ከተማ እምብርት ላይ የወረዳ ስብሰባ ሲደረግ ከመጠን በላይ ተደስቼ ነበር። በጊዜው መጽሐፍ ቅዱስ ያጠና የነበረው የፖሊስ አዛዥ እንኳ ሳይቀር ፕሮግራሙን የሚያስተዋውቁ ጨርቆች በከተማው ውስጥ እንዲሰቀሉ ዝግጅት አድርጓል። በትሬስ ሪዮስ ለሦስት ዓመታት ካገለገልኩ በኋላ ከሳኦ ፓውሎ ከተማ በስተ ምዕራብ 110 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በኢቱ አዲስ ምድብ ተሰጠኝ።

ቀይ፣ ሰማያዊና ቢጫ መጻሕፍት

እኔና የአገልግሎት ጓደኛዬ ትንሽ ዞር ዞር ካልን በኋላ በከተማው መሃል አንድ ማረፊያ አገኘን። የቤቱ ባለቤት ማሪያ የምትባል ባሏ የሞተባት ደግ ሴት ስትሆን ልክ እንደ ልጆችዋ አድርጋ ተንከባክባናለች። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ በኢቱ የሚገኘው የሮማ ካቶሊክ ቄስ ቤቷ ድረስ በመምጣት እንድታስወጣን ነገራት። ሆኖም ፈርጠም ብላ “እናንተ ባሌ ሲሞት እኔን ለማጽናናት ምንም ነገር አላደረጋችሁም። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ግን የእምነታቸው ተከታይ ባልሆንም እንኳ ረድተውኛል” በማለት መለሰች።

በዚህ ጊዜ ገደማ አንዲት ሴት በኢቱ የሚገኙት የካቶሊክ ቄሶች የቤተ ክርስቲያን አባሎቻቸውን “ስለ ሰይጣን የሚናገረውን ቀይ መጽሐፍ” ከይሖዋ ምሥክሮች እንዳይቀበሉ እንዳስጠነቀቋቸው ገለጸችልን። በዚያ ሳምንት ስናበረክተው የነበረውን “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” የተባለውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መጽሐፍ ማመልከታቸው ነበር። ቀሳውስቱ ቀዩን መጽሐፍ “በማገዳቸው” ሰማያዊውን መጽሐፍ (“አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር”) ለማበርከት የሚያስችል አቀራረብ አዘጋጀን። በኋላ ግን ቄሶቹ የተደረገውን ለውጥ በመስማታቸው ቢጫውን መጽሐፍ (ሃይማኖት ለሰው ልጆች ምን አድርጎላቸዋል?) የሚለውን መጠቀም ጀመርን። እነዚህን የመሳሰሉ ለውጦች እያደረግን እናገለግል ነበር። የተለያየ ዓይነት ቀለም ያላቸውን ልዩ ልዩ መጻሕፍት ማግኘታችን ምንኛ ጠቅሞናል!

በኢቱ አንድ ዓመት ገደማ ካገለገልኩ በኋላ ለአገር አቀፍ ስብሰባ አንዳንድ ዝግጅቶች ለማድረግ ሪዮ ዲ ጃኔሮ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ማለትም በቤቴል በጊዜያዊነት እንዳገለግል የቀረበልኝን ግብዣ በደስታ ተቀበልኩ።

ተጨማሪ መብቶችና ተፈታታኝ ሁኔታዎች

በቤቴል የሚሠራ ነገር ፈጽሞ ጠፍቶ አያውቅም። በሚያስፈልግበት ቦታ ሁሉ ማገልገል በመቻሌ ተደስቼ ነበር። ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት በሚደረገው የዕለት ጥቅስ ውይይትና ዘወትር ሰኞ ማታ በሚደረገው የቤተሰብ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ መገኘት በመንፈሳዊ ያበለጽጋል! ኦቶ ኤስቴልማንና ሌሎች ተሞክሮ ያካበቱ የቤተሰቡ አባላት የሚያቀርቧቸው ከልብ የመነጩ ጸሎቶች በጥልቅ ነክተውኛል።

ስብሰባው እንዳለቀ ወደ ኢቱ ለመመለስ ሻንጣዎቼን አዘጋጀሁ። ይሁን እንጂ የቅርንጫፍ አገልጋዩ ግራንት ሚለር ቋሚ የቤቴል ቤተሰብ አባል እንድሆን የሚጋብዝ ደብዳቤ ሲሰጠኝ በጣም ተገረምኩ። በቤቴል ሆዛ ያዜድጂያን ከተባለች እህት ጋር አንድ ክፍል ውስጥ እናድር ነበር። እህት ሆዛ አሁን ድረስ በብራዚል ቤቴል በማገልገል ላይ ትገኛለች። በእነዚያ ጊዜያት የቤቴል ቤተሰብ ቁጥር በጣም አነስተኛ ነበር። ሃያ ስምንት ብቻ የነበርን ሲሆን ሁላችንም የቅርብ ጓደኛሞች ነበርን።

በ1964 ዣኦ ዛናርዲ የተባለ አንድ ወጣት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሥልጠና ለማግኘት ወደ ቤቴል መጣ። ከዚያም የወረዳ አገልጋይ ወይም ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ በአቅራቢያው እንዲያገለግል ተመደበ። ሪፖርቱን ቤቴል ሊያደርስ ሲመጣ አንዳንድ ጊዜ እንገናኝ ነበር። የቅርንጫፍ አገልጋዩ ወንድም፣ ዣኦ ሰኞ ሰኞ ማታ በምናደርገው የቤተሰብ ጥናት ላይ እንዲገኝ ፈቅዶለት ስለነበር አብረን ተጨማሪ ጊዜ ማሳለፍ ቻልን። ዣኦና እኔ ነሐሴ 1965 ከተጋባን በኋላ ከእርሱ ጋር በወረዳ ሥራ እንድካፈል የቀረበልኝን ግብዣ በደስታ ተቀበልኩ።

በእነዚያ ጊዜያት ራቅ ብለው በሚገኙ የብራዚል ክልሎች የወረዳ ሥራ መሥራት ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መወጣት ይጠይቅ ነበር። በሚና ዠራይስ ግዛት አራንሃ ከተማ የሚገኘውን አንድ የአስፋፊዎች ቡድን እንጎበኝባቸው የነበሩትን ጊዜያት ፈጽሞ አልረሳቸውም። የተወሰነ መንገድ ድረስ በባቡር ከሄድን በኋላ ሻንጣዎቻችንን፣ የጽሕፈት መኪናችንን፣ የስላይድ ፊልም ለማሳየት የምንጠቀምበትን መሣሪያ፣ የአገልግሎት ቦርሳችንንና ጽሑፎቻችንን ይዘን ቀሪውን መንገድ በእግር መጓዝ ነበረብን። ሉሪቫል ሻንታል የተባለ አንድ በዕድሜ የገፋ ወንድም ሁልጊዜ እኛን ለመርዳት በባቡር ጣቢያው ቆሞ ሲጠባበቀን ማየቱ በጣም ያስደስተን ነበር።

በአራንሃ የሚደረጉት ስብሰባዎች በኪራይ ቤት ውስጥ የሚከናወኑ ነበሩ። ከቤቱ ጀርባ በሚገኝ አንድ ትንሽ ክፍል ውስጥ የምናድር ሲሆን በአንደኛው የክፍሉ ጠርዝ በማገዶ እንጨት ምግብ የምናበስልበትና ወንድሞች በባልዲ የሚያመጡልንን ውኃ የምናሞቅበት አንድ ምድጃ ይገኛል። አቅራቢያችን በሚገኘው የሸንበቆ እርሻ መሃል የተቆፈረው ጉድጓድ ለመጸዳጃነት ያገለግለን ነበር። ቻጋስ የተባለውን በሽታ የሚያስተላልፉት ባርበር ቢትልስ የተባሉ ነፍሳት እንዳይነድፉን ስንል ማታ ማታ ኩራዝ ለኩሰን እናድር ነበር። ጠዋት ስንነሳ አፍንጫችን በጭሱ ጠቁሮ እናገኘው ነበር። በጣም ለየት ያለ ተሞክሮ ነው!

በፓራና ግዛት በወረዳ ሥራ በማገልገል ላይ እንዳለን እንደገና ቡናማ ቀለም ያለው ትልቅ ፖስታ ከቅርንጫፍ ቢሮው ደረሰን። በዚህ ጊዜ ግን ግብዣው በፖርቱጋል እንድናገለግል ነበር! ደብዳቤው በፖርቱጋል ክርስቲያናዊው ሥራችን በእገዳ ሥር በመሆኑና መንግሥት ብዙ ወንድሞችን በማሰሩ ግብዣውን ከመቀበላችን በፊት በሉቃስ 14:​28 ላይ የሰፈረውን መሠረታዊ ሥርዓት በጥንቃቄ እንድናስብበትና ኪሳራውን እንድናሰላ የሚያበረታታ ነበር።

እንዲህ ዓይነት ስደት ወዳለበት አገር ለመሄድ ፈቃደኞች እንሆን ይሆን? ዣኦ “ፖርቱጋላውያን ወንድሞቻችን እዚያ መኖርና ይሖዋን በታማኝነት ማገልገል ከቻሉ እኛ የማንችለው ለምንድን ነው?” በማለት ተናገረ። እኔም የአባቴን የማበረታቻ ቃላት በማስታወስ “ግብዣውን ያቀረበው ይሖዋ ከሆነ እሺ ማለትና በእርሱ መታመን ይኖርብናል” በማለት ስምምነቴን ገለጽኩ። ብዙም ሳንቆይ ለጉዞው የሚያስፈልጉንን ሰነዶች ለማዘጋጀትና ተጨማሪ መመሪያዎች ለመቀበል ሳኦ ፓውሎ ወደተዛወረው ቤቴል ተጓዝን።

ዣኦ ማሪያና ማሪያ ዣኦ

መስከረም 6, 1969 ኤዉዤንዮ ሲ የተባለችው መርከባችን ሳኦ ፓውሎ ከሚገኘው ሳንቶስ ወደብ ተነስታ ጉዞዋን ተያያዘችው። ከዘጠኝ ቀናት የባሕር ላይ ጉዞ በኋላ ፖርቱጋል ደረስን። በመጀመሪያ ቀድሞ የሊዝበን ግዛት በነበሩት በአልፋማና በሙራሪያ ጠባብ መንገዶች ተሞክሮ ካላቸው ወንድሞች ጋር በመሥራት የተወሰኑ ወራት አሳለፍን። ወንድሞች በቀላሉ ፖሊሶች ዓይን ውስጥ እንዳንገባ አስተዋዮች መሆን እንደሚኖርብን አስተምረውናል።

የጉባኤ ስብሰባዎች የሚካሄዱት በምሥክሮች ቤት ውስጥ ሲሆን ጎረቤቶቻችን ጥርጣሬ እንዳደረባቸው ሆኖ ከተሰማን ቤቱ ከመከበቡና ወንድሞች ከመታሠራቸው በፊት ቶሎ ብለን የስብሰባውን ቦታ እንቀይር ነበር። ሽርሽሮች ብለን የምንጠራቸውን ትልልቅ ስብሰባዎቻችንን ከሊዝበን ወጣ ብሎ በሚገኘው ሞንሳንቶ መናፈሻና በባሕር ጠረፍ ላይ በሚገኘው ኮስታ ዳ ካፓሪካ ጫካ ውስጥ እናካሂድ ነበር። ወደ እነዚህ ልዩ ስብሰባዎች ስንሄድ የአዘቦት ልብስ እንለብስ የነበረ ሲሆን ንቁ ሆነው መጠበቅ የሚችሉ የተወሰኑ ወንድሞች ምቹ ቦታዎች ላይ ቆመው ሁኔታውን ይከታተሉ ነበር። ጥርጣሬ ያደረበት አንድ ሰው ቢመጣ ጨዋታ ለመፍጠር፣ ሽርሽር ለማስመሰል ወይም ባሕላዊ ዘፈን ለመዝፈን ጊዜ ይኖረናል።

የደህንነት ፖሊሶች እንዳያውቁን ስንል በእውነተኛ ስማችን መጠራት አቆምን። ወንድሞች የሚያውቁን ዣኦ ማሪያ እና ማሪያ ዣኦ በሚለው ስማችን ነበር። ስማችንን በየትኛውም ደብዳቤም ሆነ መዝገብ ላይ አናሰፍርም ነበር። ከዚህ ይልቅ ቁጥር ተሰጠን። ምናልባት ብታሰር ወንድሞችን አሳልፌ እንዳልሰጥ ስል አድራሻቸውን በቃሌ ላለመያዝ ከፍተኛ ጥረት አደርግ ነበር።

እገዳዎች ቢኖሩም እኔና ዣኦ ይህንን ነጻነታችንን አንድ ቀን ልናጣው እንደምንችል በመገንዘባችን ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች በሙሉ ለመጠቀም ቁርጥ ውሳኔ አድርገን ነበር። በሰማያዊው አባታችን በይሖዋ ላይ መታመንን ተምረናል። ይሖዋ መላእክቱን ተጠቅሞ ‘የማናየውን የምናየው’ ያክል ሆኖ እንዲሰማን በሚያደርግ መንገድ ጠብቆናል።​—⁠ዕብራውያን 11:​27

በአንድ ወቅት ፖርቶ ውስጥ ከቤት ወደ ቤት በማገልገል ላይ ሳለን አንድ የቤት ባለቤት ወደ ውስጥ ካልገባችሁ አለን። አብራኝ የነበረችው እህት ያለምንም ማወላወል ወደ ቤት ስትገባ ምንም ምርጫ ስላልነበረኝ አብሬአት ገባሁ። ይባስ ብሎ ኮሪደሩ ላይ የወታደር ልብስ የለበሰ ሰው ፎቶግራፍ ተሰቅሎ ሳይ ደነገጥኩ። አሁን ምን ማድረግ እንችላለን? ሰውዬው ቁጭ እንድንል ከጋበዘን በኋላ “ልጅሽ ለውትድርና ቢመለመል በጦር ኃይል ውስጥ እንዲያገለግል ትፈቅጂለታለሽ” በማለት ጠየቀኝ። ትንሽ ማሰብን የሚጠይቅ ሁኔታ ነበር። በልቤ ከጸለይኩ በኋላ ረጋ ብዬ “ልጆች የሉኝም። አንተም በእኔ ቦታ ብትሆን ተመሳሳይ መልስ እንደምትሰጥ እርግጠኛ ነኝ” በማለት ስመልስለት ዝም አለ። ስለዚህ በመቀጠል “ወንድምን ወይም አባትን በሞት ማጣት ምን እንደሚመስል ብትጠይቀኝ ግን ልመልስልህ እችላለሁ። ምክንያቱም ታናሽ ወንድሜንና አባቴን አጥቻለሁ።” በምናገርበት ወቅት ዓይኔ እንባ አቅርሮ ነበር። ሰውዬውም ለማልቀስ ዳድቶት እንደነበረ ተመልክቻለሁ። ሚስቱ በቅርቡ እንደሞተችበት ገለጸልን። የትንሣኤን ተስፋ ሳብራራለት በጥሞና አዳመጠኝ። ከዚያም ጉዳዩን በይሖዋ እጅ በመተው በትህትና ተሰናብተነው ሄድን።

እገዳ ቢኖርም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የእውነትን እውቀት እንዲያገኙ እገዛ ተደርጎላቸዋል። ባለቤቴ ኦራሲኦ ከተባለ ፈጣን እድገት ካደረገ ነጋዴ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመረው ፖርቶ ውስጥ ነበር። በኋላ ስመ ጥር ዶክተር የሆነው ልጁ ኤሚልዮም ከይሖዋ ጎን የቆመ ሲሆን ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ተጠምቋል። በእርግጥም የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ ሊያስቆመው የሚችል አንዳችም ነገር የለም።

“ይሖዋ ምን እንደሚያደርግ አታውቁም

በ1973 ዣኦና እኔ ቤልጂየም ብራስልስ ውስጥ በሚደረገው “መለኮታዊ ድል” በተሰኘ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ እንድንገኝ ተጋበዝን። በስብሰባው ላይ ከሞዛምቢክ፣ ከአንጎላ፣ ከኬፕ ቨርዴ፣ ከማዴይራና ከኤዞርዝ የመጡ ልኡካንን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ የስፔይንና የቤልጅየም ወንድሞች ተገኝተው ነበር። ኒው ዮርክ ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት የመጣው ወንድም ኖር በመዝጊያ ንግግሩ ላይ “ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችሁን ቀጥሉ” ሲል አሳሰበ። “ይሖዋ ምን እንደሚያደርግ አታውቁም። ማን ያውቃል፣ ቀጣዩ ብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ በፖርቱጋል ይደረግ ይሆናል!”

በቀጣዩ ዓመት የስብከቱ ሥራ በፖርቱጋል እውቅና አገኘ። በ1978 በሊዝበን የመጀመሪያውን ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ስናደርግ ወንድም ኖር የተናገራቸው ቃላት ፍጻሜያቸውን አገኙ። በደረትና በጀርባ ላይ የሚነገቱ ማስታወቂያዎችን፣ መጽሔቶችንና የሕዝብ ንግግር መጋበዣ ወረቀቶችን በመጠቀም በሊዝበን አውራ ጎዳናዎች ምሥክርነት መስጠት ምንኛ ያስደስታል! ሕልማችን እውን የሆነ ያህል ነበር።

ለፖርቱጋላውያን ወንድሞቻችን ያለን ፍቅር እያደገ ሄዷል። ከእነዚህ ወንድሞች መካከል ብዙዎቹ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸውን በመጠበቃቸው የተነሣ እስርና ድብደባ ደርሶባቸዋል። ፍላጎታችን በፖርቱጋል ማገልገላችንን መቀጠል ቢሆንም እዚያ መቆየት ግን አልቻልንም። በ1982 ዣኦ ከባድ የልብ ሕመም ስላጋጠመው ቅርንጫፍ ቢሮው ወደ ብራዚል እንድንመለስ ሐሳብ አቀረበልን።

የፈተና ጊዜ

በብራዚል ቅርንጫፍ ቢሮ የሚገኙ ወንድሞች ከፍተኛ ድጋፍ ያደረጉልን ሲሆን በሳኦ ፓውሎ ግዛት ታውባቴ ከተማ በሚገኘው ኪሪሪም ጉባኤ እንድናገለግል ተመደብን። የዣኦ ጤንነት እያሽቆለቆለ በመምጣቱ ብዙም ሳይቆይ ከቤት መውጣት የማይችልበት ደረጃ ላይ ደረሰ። ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ቤታችን ድረስ ይመጡ ነበር። በቤታችን ሳምንታዊውን የመጽሐፍ ጥናት ስብሰባ ጨምሮ በየቀኑ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ይደረግ ነበር። እነዚህ ዝግጅቶች መንፈሳዊነታችንን እንድንጠብቅ ረድተውናል።

ዣኦ ጥቅምት 1, 1985 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ በይሖዋ አገልግሎት የተቻለውን ሁሉ ማድረጉን ቀጥሎ ነበር። ሐዘንና ጭንቀት ላይ ወድቄ የነበረ ቢሆንም አገልግሎቴን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። ሌላው መሰናክል የገጠመኝ ሚያዝያ 1986 ሌቦች ቤቴን ሰብረው ሁሉንም ነገር ለማለት ይቻላል በሰረቁ ጊዜ ነበር። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቸኝነትና ፍርሃት ተሰማኝ። አንድ ባልና ሚስት ለተወሰነ ጊዜ እነርሱ ጋር እንድቀመጥ ያደረጉ ሲሆን ለዚህም በጣም አመስጋኝ ነኝ።

የዣኦ ሞትና የደረሰብኝ ዝርፊያ ለይሖዋ የማቀርበውን አገልግሎትም ነክቶብኛል። ለአገልግሎት የነበረኝ ድፍረት ጠፋ። ችግሩን ግልጥልጥ አድርጌ ለቅርንጫፍ ቢሮው ስጽፍ ስሜታዊ ሚዛኔን መልሼ እስካገኝ ድረስ ለተወሰነ ጊዜ በቤቴል እንዳሳልፍ ተጋበዝኩ። ያ ጊዜ ምንኛ አበረታች ነበር!

ትንሽ ደህና ስሆን በሳኦ ፓውሎ ግዛት በምትገኘው ኢፑዋ ከተማ ውስጥ እንዳገለግል የቀረበልኝን ግብዣ ተቀበልኩ። የስብከቱ ሥራ አብዛኛውን ጊዜዬን ይዞት የነበረ ቢሆንም ተስፋ የምቆርጥባቸው ጊዜያት ነበሩ። የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሲሰማኝ ወደ ኪሪሪም ጉባኤ ወንድሞች እደውላለሁ። በአንድ ወቅት አንድ ቤተሰብ ሊጠይቀኝ መጥቶ እኔ ጋር ጥቂት ቀናት አሳልፏል። እንዲህ የመሳሰሉት ጉብኝቶች በእርግጥም አበረታች ነበሩ! በኢፑዋ ባሳለፍኩት የመጀመሪያ ዓመት 38 የተለያዩ ወንድሞችና እህቶች እኔን ለመጠየቅ ሲሉ ረዥም ጉዞ አድርገዋል።

በ1992 ማለትም ዣኦ ከሞተ ከስድስት ዓመታት በኋላ ከይሖዋ ድርጅት ሌላ ግብዣ ቀረበልኝ። በዚህ ጊዜ ግብዣው በሳኦ ፓውሎ ግዛት በምትገኘው ፍራንካ ከተማ ተዛውሬ እንዳገለግል ነበር። እስካሁን እዚሁ በማገልገል ላይ ስሆን ክልሉ በጣም ፍሬያማ ነው። በ1994 የከተማውን ከንቲባ መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመርኩ። በዚህ ወቅት ይህ ሰው በብራዚል የመንግሥት ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ ለማግኘት ዘመቻ እያካሄደ ነበር። ጊዜው በጣም የተጣበበ ቢሆንም ሁሌ ሰኞ ሰኞ ከሰዓት በኋላ እናጠና ነበር። ጥናታችን እንዳይስተጓጎል ሲል ስልኩን ይነቅለው ነበር። በመጨረሻም ፖለቲካን እርግፍ አድርጎ በመተው ከመጽሐፍ ቅዱስ በተማረው እውነት እርዳታ ትዳሩ እንደገና እንዲያንሰራራ ሲያደርግ ማየት ምንኛ ያስደስታል! በ1998 እርሱና ሚስቱ ተጠመቁ።

ወደ ኋላ መለስ ብዬ ስመለከት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በመሆን ያሳለፍኩት ሕይወት ብዙ በረከቶችና መብቶች ያስገኘልኝ ነው ብዬ መናገር እችላለሁ። ይሖዋ በድርጅቱ በኩል ያቀረበልኝን ግብዣ መቀበሌ በእርግጥም የተትረፈረፉ በረከቶች አስገኝቶልኛል። ወደፊትም ቢሆን ምንም ዓይነት ግብዣ ይምጣልኝ ግብዣውን ለመቀበል ከምንጊዜውም ይበልጥ ፈቃደኛ ነኝ።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1957 የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ስጀምርና በዛሬው ጊዜ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1963 ከብራዚል ቤቴል ቤተሰብ ጋር

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ነሐሴ 1965 በሠርጋችን ዕለት

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሥራው እገዳ ሥር በነበረበት ጊዜ በፖርቱጋል የተደረገ ትልቅ ስብሰባ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1978 በተደረገውና “ድል አድራጊ እምነት” በተሰኘው ብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ወቅት የመንገድ ላይ ምሥክርነት ስንሰጥ