በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ከእኔ ተማሩ’

‘ከእኔ ተማሩ’

‘ከእኔ ተማሩ’

“ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ።”​—⁠ማቴዎስ 11:29

1. ከኢየሱስ መማር አስደሳች የሚሆንልንና ሕይወታችንን ይበልጥ ትርጉም ያለው የሚያደርገው ለምንድን ነው?

 ኢየሱስ ክርስቶስ አሳቡ፣ ትምህርቱና ድርጊቱ በጠቅላላ ሁልጊዜ ቀና ነበር። በምድር ላይ የቆየባቸው ጊዜያት አጭር ቢሆኑም እንኳ አርኪ የሆነ ሥራ ከማከናወኑም በላይ ምንጊዜም ደስተኛ ነበር። ደቀ መዛሙርትን ሰብስቦ አምላክን እንዴት ማምለክ እንደሚችሉ፣ የሰውን ዘር እንዴት እንደሚወድዱና ዓለምን እንዴት ማሸነፍ እንደሚችሉ አስተምሯቸዋል። (ዮሐንስ 16:33) ልባቸው በተስፋ እንዲሞላ ከማድረጉም በላይ “በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል።” (2 ጢሞቴዎስ 1:10) አንተም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ከሆንክ ደቀ መዝሙርነት ለአንተ ምን ትርጉም አለው? ኢየሱስ ስለ ደቀ መዝሙርነት የተናገራቸውን ቃላት በመመርመር ሕይወታችንን ይበልጥ ትርጉም ያለው ማድረግ ስለምንችልበት መንገድ ልንማር እንችላለን። ይህም የእርሱ ዓይነት አመለካከት ማዳበርንና አንዳንድ ዋና ዋና መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ ማዋልን ይጨምራል።​—⁠ማቴዎስ 10:24, 25፤ ሉቃስ 14:26, 27፤ ዮሐንስ 8:31, 32፤ 13:35፤ 15:8

2, 3. (ሀ) የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ማለት ምን ማለት ነው? (ለ) ‘እኔ የማን ደቀ መዝሙር ነኝ’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

2 በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ደቀ መዝሙር” ተብሎ የተተረጎመው ቃል አንድን ነገር በትኩረት የሚከታተል ወይም የሚማር የሚል መሠረታዊ ትርጉም አለው። የጭብጡ ጥቅሳችን በሆነው በማቴዎስ 11:​29 ላይ ከዚህ ጋር የሚዛመድ አንድ ቃል አለ። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አዎን፣ ደቀ መዝሙር ተማሪ ነው። ብዙውን ጊዜ ወንጌሎች “ደቀ መዝሙር” የሚለውን ቃል ከኢየሱስ ጋር ይሰብኩና የእርሱን መመሪያ ይከተሉ የነበሩትን የኢየሱስን የቅርብ ተከታዮች ለማመልከት ይጠቀሙበታል። የኢየሱስን ትምህርቶች በምሥጢር የተቀበሉ ሰዎችም ነበሩ። (ሉቃስ 6:17፤ ዮሐንስ 19:38) የወንጌል ጸሐፊዎችም “የዮሐንስ [መጥምቁ] እና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት” በማለት ዘግበዋል። (ማርቆስ 2:18) ኢየሱስ ተከታዮቹን “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት” እንዲጠበቁ አስጠንቅቋቸው ስለነበረ ‘እኔ የማን ደቀ መዝሙር ነኝ?’ ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን።​—⁠ማቴዎስ 16:12

3 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ማለትም ከእርሱ የተማርን ከሆንን ሌሎች ከእኛ ጋር በሚሆኑበት ጊዜ መንፈሳዊ እረፍት ያገኛሉ። የዋሆችና በልባችን ትሑታን እንደሆንን መመልከት መቻል ይኖርባቸዋል። በሥራ ቦታ አስተዳደራዊ ኃላፊነት ካለን፣ ወላጅ ከሆንን ወይም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የእረኝነት ኃላፊነት የተጣለብን ከሆንን በሥራችን ያሉ ሰዎች ኢየሱስ በእርሱ ሥር የነበሩትን ሰዎች በያዘበት መንገድ እንደምንይዛቸው ይሰማቸዋል?

ኢየሱስ ሰዎችን ይይዝ የነበረበት መንገድ

4, 5. (ሀ) ኢየሱስ ችግር የነበረባቸውን ሰዎች እንዴት ይይዝ እንደነበረ ማወቁ አስቸጋሪ የማይሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በአንድ ፈሪሳዊ ቤት ተጋብዞ ሳለ ምን አጋጠመው?

4 ኢየሱስ ሰዎችን በተለይ ደግሞ ሥር የሰደደ ችግር የነበረባቸውን ሰዎች እንዴት ይይዝ እንደነበረ ማወቅ ይኖርብናል። ይህን መማር አስቸጋሪ ሊሆንብን አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ መከራ የደረሰባቸውን አንዳንድ ሰዎች ጨምሮ ኢየሱስ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ስለነበረው ግንኙነት የሚገልጹ በርካታ ዘገባዎችን ይዟል። ከዚያም የሃይማኖት መሪዎች በተለይ ደግሞ ፈሪሳውያን ተመሳሳይ ችግር ለገጠማቸው ሰዎች ያንጸባርቁ የነበረውን አመለካከት እናያለን። ሁለቱን ማነጻጸሩ እውቀታችንን የሚጨምርልን ሆኖ እናገኘዋለን።

5 በ31 እዘአ ኢየሱስ በገሊላ ምድር እየተዘዋወረ ይሰብክ በነበረበት ጊዜ “ከፈሪሳውያንም አንድ ከእርሱ ጋር ይበላ ዘንድ [ኢየሱስን] ለመነው።” ኢየሱስም ግብዣውን ሳያመነታ ተቀበለ። “በፈሪሳዊው ቤትም ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ። እነሆም በዚያች ከተማ ኃጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት፤ በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደ ተቀመጠ ባወቀች ጊዜ፣ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ አመጣች። በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፣ በራስ ጠጒርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበረች።”​—⁠ሉቃስ 7:36-38

6. አንዲት “ኃጢአተኛ” ሴት በአንድ ፈሪሳዊ ቤት የተገኘችው ለምን ሊሆን ይችላል?

6 ይህን ትዕይንት በዓይነ ሕሊናህ መመልከት ትችላለህ? አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ በማለት ሁኔታውን ገልጿል:- “ችግረኞች ጥቂት ፍርፋሪ ለማግኘት ግብዣ ወዳለበት ቦታ ይሄዱ ስለነበር ይህችም ሴት (ቁ.37) የአካባቢውን ልማድ ተከትላ ወደዚያው ሄዳለች።” አንድ ሰው ሳይጋበዝ እንዲህ ባለ ግብዣ ላይ ሊገኝ የሚችለው በዚህ ምክንያት መሆን አለበት። ግብዣው ካለቀ በኋላ የተራረፉ ምግቦችን ለማግኘት የተኮለኮሉ ሌሎች ሰዎችም ሳይኖሩ አይቀርም። ሆኖም ይህች ሴት ያሳየችው ጠባይ ፈጽሞ የተለየ ነበር። ግብዣው እስኪያልቅ ድረስ ጥግ ተቀምጣ አልጠበቀችም። “ኃጢአተኛ” የሚል መጥፎ ስም አትርፋ የነበረ ሲሆን ኢየሱስም ‘ብዙ ኃጢአት’ ያለባት መሆኗን እንደሚያውቅ ተናግሯል።​—⁠ሉቃስ 7:47

7, 8. (ሀ) በሉቃስ 7:​36-38 ላይ ሰፍሮ እንደሚገኘው ዓይነት ሁኔታ ቢገጥመን ምን ምላሽ ልንሰጥ እንችላለን? (ለ) ስምዖን ምን ተሰማው?

7 በዚያን ዘመን ትኖር እንደነበርና ራስህን በኢየሱስ ቦታ እንዳለህ አድርገህ አስብ። ምን ታደርግ ነበር? ይህች ሴት ወደ አንተ ስትቀርብ ስትመለከት ትሸማቀቅ ነበር? እንዲህ ያለው ሁኔታ ምን ዓይነት ስሜት ያሳድርብህ ይሆን? (ሉቃስ 7:45) ትጸየፋት ነበር?

8 ከሌሎቹ እንግዶች አንዱ ብትሆን ኖሮ አንተም በተወሰነ መጠን ፈሪሳዊው ስምዖን የነበረው ዓይነት አመለካከት ይኖርህ ነበር? “[ኢየሱስን] የጠራው ፈሪሳዊም አይቶ:- ይህስ ነቢይ ቢሆን፣ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፣ ኃጢአተኛ ናትና ብሎ በልቡ አሰበ።” (ሉቃስ 7:39) በተቃራኒው ግን ኢየሱስ ከአንጀቱ የሚራራ ሰው ነበር። ሴትዮዋ ያለችበትን ሁኔታና ጭንቀት ተረድቷል። በኃጢአተኝነት ኑሮ ውስጥ እንዴት ልትገባ እንደቻለች አናውቅም። በእርግጥ ዝሙት አዳሪ ከነበረች በከተማው የሚኖሩ ቀናተኛ አይሁዳውያን ያደረጉላት እርዳታ አልነበረም ለማለት ይቻላል።

9. ኢየሱስ ምን ብሎ መለሰ? ምንስ ውጤት ተገኝቶ ሊሆን ይችላል?

9 ሆኖም ኢየሱስ ሊረዳት ፈለገ። “ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል” አላት። ከዚያም “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ” በማለት ጨምሮ ተናገረ። (ሉቃስ 7:48-50) ዘገባው እዚህ ላይ ያበቃል። አንድ ሰው ኢየሱስ ብዙም ያደረገላት ነገር የለም ብሎ ያስብ ይሆናል። በመሠረቱ ኢየሱስ ያሰናበታት ባርኮ ነው። ይህች ሴት ወደ ቀድሞ አሳዛኝ አኗኗሯ ተመልሳለች ብለህ ታስባለህ? በእርግጠኝነት መናገር ባንችልም ሉቃስ ቀጥሎ የተናገረውን ልብ በል። ኢየሱስ “እየሰበከና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች እየተናገረ በየከተማይቱ በየመንደሩም ያልፍ” እንደነበር የተናገረ ሲሆን ‘በገንዘባቸው የሚያገለግሉ’ ‘ብዙ ሌሎች ሴቶች’ ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደነበሩም ዘግቧል። ንስሐ የገባችውና አመስጋኝ የነበረችው ይህች ሴት በንጹሕ ሕሊና፣ በአዲስ ዓላማና ለአምላክ የበለጠ ጥልቅ ፍቅር በማዳበር እርሱን በሚያስከብር አኗኗር ከእነዚህ ሴቶች ጎን ተሰልፋ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው።​—⁠ሉቃስ 8:1-3

በኢየሱስና በፈሪሳውያን መካከል የነበረው ልዩነት

10. ስለ ኢየሱስና በስምዖን ቤት ስለነበረችው ሴት የሚናገረውን ዘገባ መመርመሩ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

10 ከዚህ ሕያው ዘገባ ምን ልንማር እንችላለን? ይህ ታሪክ ስሜታችንን በጥልቅ እንደሚነካው የተረጋገጠ ነው፣ አይደለም እንዴ? በስምዖን ቤት እንዳለህ አድርገህ አስብ። ምን ዓይነት ስሜት ያድርብህ ነበር? እንደ ኢየሱስ ታደርግ ነበር ወይስ ትንሽም ቢሆን እንደጋባዡ ፈሪሳዊ ይሰማህ ነበር? ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደ መሆኑ መጠን ልክ እንደ እርሱ ማሰብና ማድረግ እንደማንችል የታወቀ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የፈሪሳዊው ስምዖን ዓይነት ስሜት ማንጸባረቅ እንደማንፈልግ ግልጽ ነው። እንደ ፈሪሳውያን መሆን የሚያስደስታቸው ጥቂት ሰዎች ይኖሩ ይሆናል።

11. ከፈሪሳውያን ወገን መመደብ የማንፈልገው ለምንድን ነው?

11 መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው መግለጫና ከምሁራን አስተያየት በመነሣት ፈሪሳውያን ለማኅበረሰቡ ብልጽግናና ብሔራዊ ደህንነት ካለ እነርሱ ተቆርቋሪ እንደሌለ አድርገው ያስቡ እንደነበር ማወቅ እንችላለን። የአምላክ ቃል ግልጽና ለመረዳት የማያስቸግር መሆኑ ደስ አያሰኛቸውም ነበር። ሕጉ በግልጽ በማይናገርበት ጊዜ ጉዳዩን ለሕሊና ከመተው ይልቅ ሕጉን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል የሚያብራሩ ተጨማሪ ሐሳቦችን ያካትቱ ነበር። እነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች ጥቃቅን በሆኑ ጉዳዮች እንኳን ሳይቀር ለሁሉም ዓይነት የኑሮ ዘርፍ መመሪያ የሚሆኑ ደንቦችን ያወጡ ነበር። a

12. ፈሪሳውያን ስለ ራሳቸው ምን ዓይነት አመለካከት ነበራቸው?

12 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ ፈሪሳውያን ራሳቸውን ደጎች፣ ጨዋዎች፣ የማያዳሉና የተሰጣቸውን ሥራ በብቃት የሚወጡ እንደሆኑ አድርገው ይመለከቱ እንደነበር ገልጿል። አንዳንዶቹ እነዚህ ባሕርያት እንደነበሯቸው አይካድም። ምናልባት ኒቆዲሞስ ወደ አእምሮህ ይመጣ ይሆናል። (ዮሐንስ 3:1, 2፤ 7:​50, 51) ከጊዜ በኋላ አንዳንዶቹ የክርስትናን መንገድ ተቀብለዋል። (ሥራ 15:5) ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ ፈሪሳውያንን ስለመሳሰሉ አንዳንድ የአይሁድ ሰዎች ሲጽፍ “በእውቀት አይቅኑ እንጂ ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ እመሰክርላቸዋለሁና” ብሏል። (ሮሜ 10:2) ይሁን እንጂ ተራው ሕዝብ የሚመለከታቸው ኩራተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተመጻዳቂዎች፣ ስህተት ለቃቃሚዎች፣ ኮናኞችና ሌሎችን የሚንቁ እንደሆኑ አድርጎ እንደነበር የወንጌል ዘገባዎች ይገልጻሉ።

ኢየሱስ የነበረው አመለካከት

13. ኢየሱስ ስለ ፈሪሳውያን ምን ብሎ ለመናገር ተገድዷል?

13 ኢየሱስ ጻፎችና ፈሪሳውያን ግብዞች እንደሆኑ በመግለጽ ክፉኛ ነቅፏቸዋል። “ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፣ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም።” አዎን፣ ሸክሙ ከባድ ነበር፤ በሕዝቡ ላይ የተጫነው ቀንበርም የሚያሠቃይ ነበር። ኢየሱስ ጻፎችንና ፈሪሳውያንን “ደንቆሮዎች [“ሰነፎች፣” NW ]” በማለት ጠርቷቸዋል። ሰነፍ ሰው የኅብረተሰብ ጠንቅ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ ጻፎችንና ፈሪሳውያንን “ዕውሮች መሪዎች” በማለት የጠራቸው ሲሆን ‘ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፣ በሕግ ያለውን ዋና ነገር የምትተዉ’ በማለት አስረግጦ ተናግሯል። ኢየሱስ እንደ ፈሪሳውያን አድርጎ እንዲመለከተው የሚፈልግ ማን አለ?​—⁠ማቴዎስ 23:1-4, 16, 17, 23

14, 15. (ሀ) ኢየሱስ ከማቴዎስ ሌዊ ጋር ካደረገው ውይይት ስለ ፈሪሳውያን ምን ነገር ያስገነዝበናል? (ለ) ከዚህ ዘገባ ምን ጠቃሚ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

14 የወንጌል ዘገባዎችን የሚያነብ ማንኛውም ሰው ለማለት ይቻላል ብዙዎቹ ፈሪሳውያን የነበረባቸውን ጉልህ ችግር ማየት ይችላል። ኢየሱስ ቀረጥ ሰብሳቢ የነበረውን ማቴዎስ ሌዊን ደቀ መዝሙሩ እንዲሆን ከጋበዘው በኋላ ሌዊ ትልቅ ግብዣ አደረገለት። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ፈሪሳውያንና ጻፎቻቸውም በደቀ መዛሙርቱ ላይ:- ስለ ምን ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ትበላላችሁ ትጠጡማላችሁ? ብለው አንጐራጐሩ። ኢየሱስም መልሶ:- . . . ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው።”​—⁠ሉቃስ 5:27-32

15 በዚያን ወቅት ሌዊ ከኢየሱስ አነጋገር የተገነዘበው ሌላም ነገር ነበር። ኢየሱስ “ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደ ሆነ ተማሩ” በማለት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 9:​13) ፈሪሳውያን ዕብራውያን ነቢያት የጻፏቸውን ጽሑፎች እንደሚያምኑባቸው ቢናገሩም በሆሴዕ 6:​6 ላይ የተነገረውን ይህን ቃል ግን አይቀበሉም ነበር። ያወጡትን ወግ እስካልተላለፉ ድረስ ምንም ዓይነት ስህተት እንደፈጸሙ ሆኖ አይሰማቸውም ነበር። ስለዚህ እያንዳንዳችን ራሳችንን እንዲህ እያልን ልንጠይቅ እንችላለን:- ‘ሌሎች የሚመለከቱኝ የግል አመለካከትን በሚጠይቁ ወይም ማንኛውም ሰው ሊገምት በሚችላቸው ጉዳዮች ረገድ የሚወጡ ደንቦችን በተመለከተ ድርቅ ያለ አቋም እንዳለኝ አድርገው ነው? ወይስ ይበልጥ ጎልቶ የሚታያቸው መሐሪና ደግ መሆኔ ነው?’

16. የፈሪሳውያን መንገድ ምን ነበር? እንደ እነርሱ ከመሆን መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?

16 ፈሪሳውያን ስህተት መለቃቀም ይወድዱ ነበር። ተፈጽሟል ብለው የሚያስቡትም ይሁን በእውነት የተፈጸመ ምንም የሚያልፉት ስህተት አልነበረም። ፈሪሳውያን ሰዎች ተሸማቅቀውና ዘወትር ድክመቶቻቸውን እያሰቡ እንዲኖሩ አድርገዋል። ፈሪሳውያን እንደ አዝሙድ፣ እንስላልና ከሙን ያሉ ትናንሽ ተክሎችን አሥራት አድርገው ማውጣታቸው በጣም ያኩራራቸው ነበር። በአለባበሳቸው ሃይማኖተኛ መስለው ለመታየት ይሞክሩ የነበረ ሲሆን ሕዝቡንም ለመምራት ይፈልጉ ነበር። በእርግጥም ድርጊታችን ኢየሱስ ከተወልን ምሳሌ ጋር የሚስማማ እንዲሆን ከፈለግን በሰዎች ላይ ስህተት ከመለቃቀምና የሌሎችን እንከን ከማጋነን መታቀብ ይገባናል።

ኢየሱስ ችግሮችን ይፈታ የነበረው እንዴት ነው?

17-19. (ሀ) ኢየሱስ ከባድ ችግር ሊፈጥር ይችል ለነበረ አንድ ሁኔታ እንዴት መፍትሔ እንዳስገኘ ግለጽ። (ለ) ሁኔታውን የሚያስጨንቅና የማያስደስት ያደረገው ምንድን ነው? (ሐ) ሴትዮዋ ወደ ኢየሱስ ስትቀርብ አንተ እዚያ ኖረህ ቢሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?

17 ኢየሱስ ችግሮችን ይፈታ የነበረበት መንገድ ከፈሪሳውያን ፈጽሞ የተለየ ነበር። ኢየሱስ ከባድ ችግር ሊፈጥር ይችል የነበረን አንድ ሁኔታ እንዴት እንደያዘ ተመልከት። ጉዳዩ ለ12 ዓመታት ደም ይፈሳት የነበረችን አንዲት ሴት የሚመለከት ነው። ታሪኩን በሉቃስ 8:​42-48 ላይ ማንበብ ትችላለህ።

18 የማርቆስ ዘገባ ሴትዮዋ ‘በፍርሃት ትንቀጠቀጥ’ እንደነበር ይገልጻል። (ማርቆስ 5:33) ለምን? ምክንያቱም የአምላክን ሕግ እንደጣሰች ታውቅ ስለነበር ነው። በዘሌዋውያን 15:​25-28 መሠረት ከተፈጥሮ ውጭ ደም የሚፈስሳት አንዲት ሴት ደሙ መፍሰሱን እስኪያቆም ብሎም ከዚያ በኋላ አንድ ሳምንት እስኪያልፍ ድረስ ርኩስ ትሆናለች። የነካችው ማንኛውም ዕቃ ሆነ ሰው ርኩስ ይሆናል። ይህች ሴት ወደ ኢየሱስ ለመቅረብ በሕዝቡ መካከል ተሹለክሉካ ማለፍ ነበረባት። ከ2, 000 ዓመት በፊት የተጻፈውን ይህ ታሪክ ስናነብ ሴትዮዋ የነበረችበትን ሁኔታ በማሰብ ከልብ እንደምናዝን የታወቀ ነው።

19 በዚያን ዕለት ኖረህ ቢሆን ኖሮ ሁኔታውን እንዴት ትመለከተው ነበር? ምንስ ትናገር ነበር? ኢየሱስ ችግር እንደፈጠረች አድርጎ ከመናገር ይልቅ ሴትዮዋን በደግነት፣ በፍቅርና በአሳቢነት እንደያዛት ልብ በል።​—⁠ማርቆስ 5:34

20. ዘሌዋውያን 15:​25-28 በጊዜያችን የሚሠራ ሕግ ቢሆን ኖሮ ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ከፊታችን ይጋረጥብን ነበር?

20 ከዚህ ክስተት ልንማር የምንችለው ነገር ይኖር ይሆን? በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆነህ የምታገለግል ነህ እንበል። እንዲሁም በዘሌዋውያን 15:​25-28 ላይ የሚገኘው ሕግ በክርስቲያኖች ላይ እንደሚሠራና አንዲት ክርስቲያን ሴት ይህን ሕግ በመተላለፏ ምክንያት ከፍተኛ ጭንቀትና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት እንዳደረባት አድርገህ አስብ። ምን ታደርግ ነበር? በሕዝብ ፊት በመገሠጽ ታዋርዳት ነበር? “ኧረ በጭራሽ፣ እንዴት እንዲህ አደርጋለሁ! የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ደግ፣ አፍቃሪ፣ አስተዋይና አሳቢ ለመሆን የተቻለኝን ሁሉ እጥራለሁ” ብለህ ታስብ ይሆናል። በጣም ጥሩ ነው! ችግሩ ግን የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ተግባራዊ ማድረጉ ላይ ነው።

21. ሕጉን በሚመለከት ኢየሱስ ለሰዎች ያስተማረው ምንድን ነው?

21 ሰዎች ከኢየሱስ መነቃቃትን፣ መበረታታትንና እፎይታን አግኝተዋል። የአምላክ ሕግ የሚለው ነገር ቁርጥ ያለ ትእዛዝ በሚሆንበት ጊዜ ሕጉ የሚለውን መፈጸም ይገባ ነበር። ብዙ ነገሮችን የሚያካትት በሚሆንበት ጊዜ ግን በሕሊናቸው ተጠቅመው ውሳኔ በማድረግ ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር ማሳየት ይችሉ ነበር። ሕጉ እንደ አስፈላጊነቱ የሚለዋወጥ እንጂ መፈናፈኛ የሚያሳጣ አልነበረም። (ማርቆስ 2:27, 28) አምላክ ሕዝቡን ይወድዳል፣ ሁልጊዜ የሚጠቅማቸውን ያደርግላቸዋል፣ በሚሳሳቱበት ጊዜም ይምራቸዋል። ኢየሱስም እንደዚህ ነበር።​—⁠ዮሐንስ 14:9

የኢየሱስ ትምህርት ያስገኘው ውጤት

22. ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሱስ ያገኙት ትምህርት ምን ዓይነት አመለካከት እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል?

22 የኢየሱስን ትምህርት አድምጠው የእርሱ ደቀ መዛሙርት የሆኑ “ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነው” በማለት የተናገራቸውን ቃላት እውነተኝነት አረጋግጠዋል። (ማቴዎስ 11:30) ኢየሱስ ሸክም እንደጫነባቸው፣ እንደጨቀጨቃቸው ወይም በኃይለ ቃል እንደተናገራቸው ሆኖ ፈጽሞ አልተሰማቸውም። እንዳይሸማቀቁና ደስተኛ እንዲሆኑ እንዲሁም ከአምላክም ሆነ ከሰዎች ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል። (ማቴዎስ 7:1-5፤ ሉቃስ 9:49, 50) አንድ መንፈሳዊ መሪ የዋህና በልቡም ትሑት በመሆን ለሌሎች የእረፍት ምንጭ መሆን እንዳለበት ከእርሱ ተምረዋል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 16:17, 18፤ ፊልጵስዩስ 2:3

23. ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሱስ ጋር መሆናቸው ምን አስፈላጊ ትምህርት አስተምሯቸዋል? ምን መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱስ ረድቷቸዋል?

23 ከዚህም በላይ ብዙዎች ከኢየሱስ ጋር መሆንና እርሱ ያሳየው ዓይነት መንፈስ ማሳየት አስፈላጊ መሆኑን በእጅጉ ተረድተዋል። ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው:- “አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፣ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ።” (ዮሐንስ 15:9, 10) የአምላክ አገልጋይ በመሆን በሚያከናውኑት ሥራ ውጤታማ መሆን ከፈለጉ ስለ አምላክ ድንቅ ሥራዎች የሚናገረውን ምሥራች ለሕዝብ በመስበክና በማስተማር እንዲሁም ቤተሰባቸውንና ወዳጆቻቸውን በጥሩ መንገድ በመያዝ ከኢየሱስ የተማሩትን ሁሉ በሥራ ላይ ማዋል ነበረባቸው። ጉባኤ ውስጥ ባለው የወንድማማች ማኅበር ውስጥም የኢየሱስ መንገድ ትክክለኛ መንገድ መሆኑን በተደጋጋሚ ማስታወስ ይኖርባቸዋል። ያስተማራቸው ትምህርቶች እውነት ናቸው፤ በእርሱ ላይ የተመለከቱት ባሕርያትም በእርግጥ ልናዳብራቸው የሚገቡን ባሕርያት ናቸው።​—⁠ዮሐንስ 14:6፤ ኤፌሶን 4:20, 21

24. ኢየሱስ ከተወልን ምሳሌ በትኩረት ልናስብባቸው የሚገቡን ምን ነገሮች አሉ?

24 እስከ አሁን ያየናቸውን ነጥቦች በምትመረምርበት ጊዜ ማሻሻያ ልታደርግ የምትችልባቸው መንገዶች እንዳሉ ይሰማሃል? ኢየሱስ አሳቡ፣ ትምህርቱና ድርጊቱ ሁሉ ሁልጊዜ ቀና ነበር ብትባል አትስማማም? እንግዲያው አይዞህ። “ይህን ብታውቁ፣ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ” በማለት አበረታትቶናል።​—⁠ዮሐንስ 13:17

[የግርጌ ማስታወሻ]

a “[በኢየሱስና በፈሪሳውያን መካከል] መሠረታዊ ልዩነት እንዲኖር ያደረገው ስለ አምላክ የነበራቸው ፈጽሞ ተቃራኒ የሆነ አመለካከት ነው። ፈሪሳውያን አምላክ ከሰዎች ብዙ ነገር እንደሚጠይቅ አድርገው ሲመለከቱት ኢየሱስ ደግሞ ደግና ሩኅሩኅ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተው ነበር። አንድ ፈሪሳዊ አምላክ ጥሩና አፍቃሪ መሆኑን ባይክድም ፍቅሩና ጥሩነቱ ተገልጿል ብሎ የሚያስበው ቶራህን [ሕጉን] በመስጠቱና አንድ ሰው ሕጉ የሚጠይቀውን ነገር መፈጸም በመቻሉ እንደሆነ አድርጎ ነው። እነዚህ ባሕርያት እንደተንጸባረቁና ሕጉን በመፈጸም እነዚህን ባሕርያት ማንጸባረቅ እንደሚችሉ አድርገው ያስቡ ነበር። . . . በፈሪሳውያን አመለካከት ሕጉን ለማብራራት ተብለው የወጡ መመሪያዎችን ጨምሮ በቃል የተላለፉ ወጎችን መጠበቅ ቶራህን እንደ መፈጸም ተደርጎ ይታይ ነበር። . . . ኢየሱስ በፍቅር ላይ የተመሠረተው ጥንድ ትእዛዝ (ማቴ. 22:34-40) ለጠቅላላው ሕግ መሠረት እንደሆነ አድርጎ መመልከቱና ውልፍት የማያደርገውን የቃል ወግ ማውገዙ . . . ከፈሪሳውያን ጋር አጋጭቶታል።”​—⁠ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሺነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ቲኦሎጂ

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

• ኢየሱስ ሰዎችን የያዘው እንዴት ነበር?

• ኢየሱስ ካስተማረበት መንገድ ምን ልንማር እንችላለን?

• ፈሪሳውያንና ኢየሱስ የሚለያዩት እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ለሰዎች የነበረው አመለካከት ከፈሪሳውያን ምንኛ የተለየ ነበር!