በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከውጥረት እፎይታ ለማግኘት የሚረዳ ተግባራዊ መፍትሔ

ከውጥረት እፎይታ ለማግኘት የሚረዳ ተግባራዊ መፍትሔ

ከውጥረት እፎይታ ለማግኘት የሚረዳ ተግባራዊ መፍትሔ

“እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ።”​—⁠ማቴዎስ 11:28

1, 2. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ከመጠን ያለፈ ውጥረትን ለማስታገስ የሚረዳ ምን ነገር ይዟል? (ለ) የኢየሱስ ትምህርቶች ምን ያህል ውጤታማ ነበሩ?

 ውጥረት ሲበዛ ጎጂ እንደሆነና አልፎ ተርፎም ለጭንቀት ሊዳርግ እንደሚችል ሳትስማማ አትቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ መላው ሰብዓዊ ፍጡር በከባድ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኝና ብዙዎችም ከዚህ በውጥረት የተሞላ ሕይወት የሚገላገሉበትን ጊዜ በናፍቆት እንደሚጠባበቁ ያመለክታል። (ሮሜ 8:20-22) ይሁን እንጂ ቅዱሳን ጽሑፎች በአሁኑ ጊዜም እንኳ ሳይቀር በተወሰነ መጠን ከውጥረት እፎይታ ማግኘት የምንችልበትንም መንገድ ይጠቁማሉ። እንዲህ ያለውን እፎይታ ማግኘት የሚቻለው ከዛሬ 2, 000 ዓመት በፊት በሕይወት የኖረ አንድ ወጣት የሰጠውን ምክርና የተወውን ምሳሌ በመከተል ነው። ይህ ሰው አናጢ የነበረ ቢሆንም ከሙያው ይበልጥ ለሰዎች ፍቅር ነበረው። በንግግሩ የሰዎችን ልብ ነክቷል፣ ፍላጎታቸውን አርክቷል፣ ደካሞችን ረድቷል እንዲሁም የተጨነቁትን አጽናንቷል። ከዚህም በላይ ብዙዎች አቅማቸው የፈቀደውን ያህል በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። በዚህም የተነሳ ከነበረባቸው ከመጠን ያለፈ ውጥረት እፎይታ አግኝተዋል፤ አንተም ተመሳሳይ እፎይታ ልታገኝ ትችላለህ።​—⁠ሉቃስ 4:16-21፤ 19:47, 48፤ ዮሐንስ 7:46

2 ይህ ሰው ማለትም የናዝሬቱ ኢየሱስ በጥንቷ ሮም፣ አቴንስ ወይም እስክንድርያ ይኖሩ እንደነበሩት አንዳንድ ሰዎች በዓለማዊ እውቀት የሚመራ አልነበረም። ሆኖም ትምህርቶቹ በሰፊው የታወቁ ነበሩ። አምላክ ምድራችንን በተሳካ ሁኔታ ስለሚገዛበት መስተዳድር የሚገልጸው መልእክት የትምህርቱ ጭብጥ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ በጊዜያችን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ኑሮን ለመምራት የሚረዱ ቁልፍ መሠረታዊ ሥርዓቶችን አስተምሯል። ኢየሱስ ያስተማራቸውን ትምህርቶች አውቀው በሥራ ላይ የሚያውሉ ሁሉ ካለባቸው ከመጠን ያለፈ ውጥረት እፎይታ ማግኘትን ጨምሮ ሌሎች ተግባራዊ ጥቅሞችን ያገኛሉ። አንተስ እንዲህ ያለውን ጥቅም ማግኘት አትፈልግም?

3. ኢየሱስ ምን ትልቅ ግብዣ አቅርቧል?

3 ‘ከዚህን ያህል ዓመት በፊት ይኖር የነበረ አንድ ሰው በዛሬ ጊዜ በእኔ ሕይወት ላይ ትርጉም ያለው ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላልን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። እስቲ ኢየሱስ ያቀረበውን ስሜት ቀስቃሽ ግብዣ ልብ በል:- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።” (ማቴዎስ 11:28-30) ኢየሱስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር? እነዚህን ቃላት በመጠኑም ቢሆን በጥልቀት እንመርምርና ካለብህ ከባድ ውጥረት እፎይታ ማግኘት ትችል ዘንድ እንዴት ሊረዱህ እንደሚችሉ እንመልከት።

4. ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው ለእነማን ነው? አድማጮቹ የሚጠየቅባቸውን ማድረግን አስቸጋሪ ሆኖ ያገኙትስ ለምን ሊሆን ይችላል?

4 ኢየሱስ ሕጉ የሚጠይቅባቸውን ለማድረግ ይፍጨረጨሩ ለነበሩ ሆኖም በአይሁድ መሪዎች ምክንያት ሃይማኖት ላንገፈገፋቸውና ‘ሸክማቸው ለከበዳቸው’ በርካታ ሰዎች እየተናገረ ነበር። (ማቴዎስ 23:4) በሁሉም የሕይወት ዘርፍ ለማለት ይቻላል መቋጫ የሌላቸው ሕጎችን አውጥተው ነበር። ሁልጊዜ ይህን ወይም ያን “አታድርግ” የሚል ትእዛዝ የምትሰማ ብትሆን ለውጥረት አይዳርግህም? በተቃራኒው ደግሞ ኢየሱስ ያቀረበው ግብዣ ሰዎችን ወደ እውነት፣ ወደ ጽድቅና ወደ ተሻለ ሕይወት የሚመራ ነበር። አዎን፣ እውነተኛውን አምላክ ማወቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገውን ነገር በትኩረት መከታተልን ያጠቃልላል፤ ምክንያቱም ሰዎች ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ማየት የቻሉትና የሚችሉትም በእሱ አማካኝነት ነው። ኢየሱስ “እኔን ያየ አብን አይቶአል” በማለት ተናግሯል።​—⁠ዮሐንስ 14:9

ሕይወትህ በከፍተኛ ውጥረት የተሞላ ነው?

5, 6. በኢየሱስ ዘመን የነበረው የሥራ ሁኔታና የሚከፈለው ደሞዝ ከጊዜያችን ጋር የሚወዳደረው እንዴት ነው?

5 ሥራህ ወይም የቤተሰብህ ሁኔታ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ከትቶህ ከሆነ ይህ ጉዳይ ትኩረትህን እንደሚስበው የታወቀ ነው። ወይም ጭንቀት የሚፈጥሩብህ ሌሎች ኃላፊነቶች ይኖሩ ይሆናል። እንደዚያ ከሆነ ያለህበት ሁኔታ ኢየሱስ የረዳቸው ቅን ሰዎች ከነበሩበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነው። ለምሳሌ ያህል የዕለት ጉርስ ማግኘት ምን ያህል አድካሚ እንደሆነ ተመልከት። በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙዎች ከባድ የኑሮ ትግል እንዳለባቸው ሁሉ በኢየሱስ ዘመን የነበሩ በርካታ ሰዎችም ተመሳሳይ ትግል ነበረባቸው።

6 በዚያን ዘመን አንድ የቀን ሠራተኛ በቀን 12 ሰዓት በሳምንት ደግሞ 6 ቀናት ይሠራ የነበረ ሲሆን ብዙውን ጊዜ በቀን የሚከፈለው አንድ ዲናር ብቻ ነበር። (ማቴዎስ 20:2-10) አንተ ወይም ጓደኞችህ ከሚያገኙት ደሞዝ ጋር ሲወዳደር ይህ ምን ያህል ነው? በጥንት ጊዜ ይከፈል የነበረውን ደሞዝ ከዘመናችን ጋር ማወዳደሩ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ማወዳደር የሚቻልበት አንደኛው መንገድ የገንዘቡን የመግዛት አቅም መመርመር ነው። አንድ ሃይማኖታዊ ምሁር በኢየሱስ ዘመን ከአራት ኩባያ የስንዴ ዱቄት የተጋገረ አንድ ዳቦ ለአንድ ሰዓት ሥራ ከሚከፈል ደሞዝ ጋር እንደሚመጣጠን ተናግረዋል። አንድ ሌላ ምሁር ደግሞ አንድ ጽዋ ጥሩ ወይን ጠጅ ለሁለት ሰዓት ሥራ ከሚከፈል ደሞዝ ጋር እኩል እንደነበር ተናግረዋል። በዚያን ዘመን የነበሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ለማቆየት በየቀኑ ምን ያህል ይለፉና ይደክሙ እንደነበር ከእነዚህ መግለጫዎች መመልከት አያዳግትም። እንደ እኛ ሁሉ እነርሱም እረፍትና እፎይታ ማግኘት ይፈልጉ ነበር። ተቀጥረህ የምትሠራ ከሆንክ በየጊዜው ይበልጥ እንድትሠራ ግፊት እንደሚደረግብህ ይሰማህ ይሆናል። ብዙውን ጊዜ በሚገባ የታሰበበት ውሳኔ ለማድረግ ጊዜ አናገኝም። ከዚህ ሁሉ እፎይ የምትልበት መንገድ እንደምትፈልግ የታወቀ ነው።

7. የኢየሱስ መልእክት ምን ውጤት አስገኝቶ ነበር?

7 ኢየሱስ ‘ለደካሞችና ሸክማቸው ለከበደባቸው’ ሰዎች ያቀረበው ግብዣ በዚያን ጊዜ የነበሩ የብዙ አድማጮችን ስሜት በእጅጉ ማርኮ እንደነበር ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 4:25፤ ማርቆስ 3:7, 8) እንዲሁም ኢየሱስ “እኔም አሳርፋችኋለሁ” በማለት ተስፋ እንደሰጠ አስታውስ። ይህ ተስፋ ለጊዜያችንም ይሠራል። እኛም ‘የደከምንና ሸክማችን የከበደን’ ከሆንን ይህ ተስፋ ለእኛም ሊሠራ ይችላል። እንዲሁም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ወዳጅ ዘመዶቻችንም ሊሠራ ይችላል።

8. ልጅ ማሳደግና የዕድሜ መግፋት ተጨማሪ ውጥረት የሚፈጥሩት እንዴት ነው?

8 በሰዎች ላይ ጫና የሚፈጥሩ ሌሎች ነገሮችም አሉ። ልጆችን ማሳደግ አንድ ፈታኝ ሁኔታ ነው። ልጅ መሆን ራሱም ፈታኝ ሊሆን ይችላል። በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ በርካታ ሰዎች አእምሯዊና አካላዊ የጤና መታወክ ይገጥማቸዋል። በሕክምናው መስክ ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ በመደረሱ ሰዎች ረዥም ዕድሜ መኖር ቢችሉም እንኳ አረጋውያን ለየት ካሉ ችግሮች ጋር ይታገላሉ።​—⁠መክብብ 12:1

ቀንበሩን መሸከም

9, 10. በጥንት ጊዜ ቀንበር ምንን ለማመልከት ያገለግል ነበር? ኢየሱስ ቀንበሩን በላያቸው እንዲሸከሙ ለሰዎች ግብዣ ያቀረበው ለምን ነበር?

9 በማቴዎስ 11:​28, 29 ላይ በሚገኙት ቃላት ውስጥ ኢየሱስ “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ” እንዳለ አስተውለሃል? በዚያ ዘመን ይኖር የነበረ አንድ ተራ ሰው ቀንበር ተሸክሞ የሚሠራ ያህል ሊሰማው ይችላል። ከጥንት ጊዜ አንስቶ ሰዎች ቀንበር የሚለውን ቃል ባርነትን ወይም ጭቆናን ለማመልከት ሲጠቀሙበት ኖረዋል። (ዘፍጥረት 27:40፤ ዘሌዋውያን 26:13፤ ዘዳግም 28:48) ኢየሱስ ያገኛቸው ብዙዎቹ የቀን ሠራተኞች ቃል በቃል በትከሻቸው ላይ ቀንበር ተሸክመው ከባድ ዕቃዎችን ያጓጉዙ ነበር። እንደ ቀንበሩ ቅርጽ አንዳንዱ የሚመች ሌላው ደግሞ አንገትና ትከሻን እየፈገፈገ የሚያሳምም ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ አናጢ የነበረ እንደመሆኑ መጠን ቀንበር ሠርቶ ሊሆን ይችላል። ከሆነ ደግሞ “ልዝብ” የሆነ የሚመች ቀንበር እንዴት መሥራት እንደሚቻል ያውቃል። ቀንበሩ የሚመችና የማይቆረቁር እንዲሆን አንገትና ትከሻ ላይ የሚያርፈውን ክፍል በቆዳ ወይም በጨርቅ ይጠቀልለው ይሆናል።

10 ኢየሱስ “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ” ብሎ ሲናገር ራሱን ለአንድ ሠራተኛ አንገትና ትከሻ የሚመች ‘ልዝብ’ ቀንበር ከሚሠራ ሰው ጋር አመሳስሎ መናገሩ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ኢየሱስ “ሸክሜም ቀሊል ነውና” በማለት ተናግሯል። ይህም ቀንበሩ ለሸክም የማይቆረቁርና ሥራውም ቢሆን አድካሚ አለመሆኑን ያመለክታል። እርግጥ ነው ኢየሱስ ቀንበሩን እንዲሸከሙ አድማጮቹን ሲጋብዝ በዚያን ጊዜ ይደርስባቸው ከነበረው ጭቆና በሙሉ ወዲያው እንደሚገላገሉ መናገሩ አልነበረም። ያም ሆኖ ግን ነገሮችን ከተለየ አቅጣጫ እንዲያዩ ማድረጉ ራሱ ትልቅ እረፍት ያስገኝላቸዋል። በአኗኗራቸውና ነገሮችን በሚያከናውኑበት መንገድ ላይ የሚያደርጉት ማስተካከያም እፎይታ ያመጣላቸዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ብሩህና ጠንካራ የሆነ ተስፋ ማግኘታቸው ያለባቸውን ውጥረት ያቃልልላቸዋል።

አንተም እረፍት ማግኘት ትችላለህ

11. ኢየሱስ አንድን ቀንበር በሌላ ቀንበር ስለ መቀየር ያልተናገረው ለምንድን ነው?

11 ኢየሱስ ሕዝቡ በላያቸው ላይ ያለውን ቀንበር በሌላ ቀንበር እንዲቀይሩት እንዳልተናገረ ልብ በል። በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች የሚኖሩበትን አገር የሚያስተዳድሩ መንግሥታት እንዳሉ ሁሉ በዚያን ጊዜም የሮም መንግሥት አገሪቱን ይገዛ ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሮማውያን ከሚያስከፍሉት ቀረጥ ነፃ መሆን አይቻልም። የጤናና የኢኮኖሚ ችግሮች አልተወገዱም። አለፍጽምና እና ኃጢአት በሰዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ቀጥለው ነበር። ቢሆንም ዛሬ እኛ እፎይታ ማግኘት እንደምንችለው ሁሉ የኢየሱስን ትምህርት ተቀብለው በሥራ ላይ በማዋል እረፍት ማግኘት ይችሉ ነበር።

12, 13. እረፍት ያመጣል በማለት ኢየሱስ ጎላ አድርጎ የገለጸው ምንድን ነው? አንዳንዶችስ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው?

12 ኢየሱስ ስለ ቀንበር የተናገረው ምሳሌ ይበልጥ የሚሠራው ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በተመለከተ ነው። የኢየሱስ ዋነኛ ሥራ በአምላክ መንግሥት ላይ ይበልጥ በማተኮር ሰዎችን ማስተማር እንደነበር የተረጋገጠ ነው። (ማቴዎስ 4:23) ስለዚህ ኢየሱስ “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ” ብሎ ሲናገር የእሱን ፈለግ በመከተል በዚህ ሥራ መካፈልን እንደሚጨምር ግልጽ ነው። ሥራ ማግኘት ብዙ ሰዎችን የሚያሳስብ ጉዳይ ቢሆንም እንኳ ኢየሱስ ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች ይተዳደሩበት የነበረውን ሥራ እንዲቀይሩ እንዳነሳሳቸው የወንጌል ዘገባዎች ያሳያሉ። ኢየሱስ “በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ” በማለት ለጴጥሮስ፣ ለእንድርያስ፣ ለያዕቆብ እና ለዮሐንስ ያቀረበላቸውን ጥሪ አስታውስ። (ማርቆስ 1:16-20) እነዚህ ዓሣ አጥማጆች እሱ በሚሰጣቸው መመሪያና እርዳታ በመታገዝ እርሱ በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ ሰጥቶ እያከናወነ ያለውን ሥራ ቢያከናውኑ ከፍተኛ እርካታ እንደሚያገኙ ገለጸላቸው።

13 አንዳንድ አይሁድ አድማጮቹ መልእክቱ ገብቷቸው በሕይወታቸው ተግባራዊ አድርገውታል። በሉቃስ 5:​1-11 ላይ የምናነበውን በባሕር ዳርቻ የተከናወነ ትዕይንት በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። አራት ዓሣ አጥማጆች ሌሊቱን ሙሉ ሲለፉ ቢያድሩም አንድም ዓሣ አልያዙም ነበር። በድንገት ግን መረባቸው በዓሦች ተሞላ! ይህ እንዲሁ በአጋጣሚ የተከሰተ አልነበረም፤ የኢየሱስ እጅ ነበረበት። ዓይናቸውን አቅንተው ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሲመለከቱ የኢየሱስን ትምህርቶች ለማዳመጥ ጓጉተው የተሰበሰቡ እጅግ ብዙ ሰዎች ተመለከቱ። ይህም ኢየሱስ ለእነዚህ ለአራቱ ‘ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምዱ ትሆናላችሁ’ በማለት የነገራቸው ምን እንደሆነ ማስተዋል አስችሏል። እነርሱስ የሰጡት ምላሽ ምን ነበር? “ታንኳዎችንም ወደ ምድር አድርሰው ሁሉን ትተው ተከተሉት።”

14. (ሀ) በዛሬው ጊዜ እረፍት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ያወጀው እረፍት የሚያስገኝ ምሥራች ምንድን ነው?

14 አንተም ተመሳሳይ ምላሽ መስጠት ትችላለህ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች የማስተማሩ ሥራ አሁንም በመከናወን ላይ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ስድስት ሚልዮን የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ‘ቀንበሩን በላያቸው እንዲሸከሙ’ ኢየሱስ ያቀረበውን ግብዣ በመቀበል “ሰዎችን አጥማጆች” ሆነዋል። (ማቴዎስ 4:19) አንዳንዶች ይህንን የሙሉ ጊዜ ሥራቸው አድርገው የያዙት ሲሆን ሌሎች ደግሞ የተቻላቸውን ያህል ጊዜያቸውን ለዚህ ሥራ ያውላሉ። ይህ ሥራ ለሁሉም እረፍት ያስገኘላቸው ሲሆን በሕይወታቸው ውስጥ ያለባቸውን ውጥረት ቀንሶላቸዋል። ይህም ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ ምሥራች ለሌሎች መንገር ማለትም የሚያስደስት ሥራ መሥራትንም ይጨምራል። (ማቴዎስ 4:23) ምሥራች መናገር በተለይ ደግሞ ይህን ምሥራች መናገር ምንጊዜም ቢሆን የሚያስደስት ነው። ብዙዎች ያለባቸውን ውጥረት ማቃለል እንደሚችሉ ለማሳመን የሚረዱን መሠረታዊ ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው እናገኛለን።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

15. ኢየሱስ ሕይወታችንን ስለምንመራበት መንገድ ከሰጠው ትምህርት ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

15 ስለ አምላክ መንግሥት ገና መማር የጀመሩ ሰዎችም እንኳ ሕይወታቸውን እንዴት መምራት እንደሚችሉ ከኢየሱስ ትምህርቶች የተወሰነ ጥቅም አግኝተዋል። የኢየሱስ ትምህርቶች እረፍት እንደሰጣቸውና ሕይወታቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲለውጡ እንደረዳቸው ብዙዎች በእርግጠኝነት ሊናገሩ ይችላሉ። በተለይ ማቴዎስ፣ ማርቆስ እና ሉቃስ የጻፏቸውን በወንጌሎች ውስጥ የሚገኙትን ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚገልጹትን አንዳንዶቹን መሠረታዊ ሥርዓቶች በመመርመር ይህንን በራስህ ሕይወት ልታረጋግጥ ትችላለህ።

እረፍት የሚገኝበት መንገድ

16, 17. (ሀ) ኢየሱስ ያስተማራቸውን አንዳንዶቹን ቁልፍ ትምህርቶች የት ልታገኛቸው ትችላለህ? (ለ) የኢየሱስን ትምህርቶች በሥራ ላይ በማዋል እረፍት ለማግኘት ምን ማድረግ ያስፈልጋል?

16 በ31 እዘአ የጸደይ ወራት ኢየሱስ እስከ ዛሬ ድረስ በሰዎች ዘንድ ሰፊ እውቅና ያተረፈ አንድ ንግግር አቀረበ። አብዛኛውን ጊዜ የተራራው ስብከት በመባል ይታወቃል። ይህ ስብከት ከማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ ምዕራፍ 7 እና በሉቃስ ምዕራፍ 6 ላይ ሰፍሮ የሚገኝ ሲሆን አብዛኞቹን የኢየሱስ ትምህርቶች ጠቅለል አድርጎ ይዟል። ኢየሱስ ያስተማራቸውን ሌሎች ትምህርቶች በወንጌሎች ውስጥ በሌሎች ቦታዎችም ላይ ማግኘት ትችላለህ። አብዛኞቹ ትምህርቶች በጣም ግልጽ ቢሆኑም በሥራ ማዋሉ ግን እንደመናገሩ ቀላል አይደለም። እነዚህን ምዕራፎች ለምን ጊዜ ወስደህ በጥንቃቄ አታነብባቸውም? ትምህርቶቹ ያላቸው ኃይል አስተሳሰብህንና ዝንባሌህን እንዲቀርጹ ፍቀድ።

17 እርግጥ ነው የኢየሱስን ትምህርቶች በተለያዩ መንገዶች መከፋፈል ይቻላል። በወር ውስጥ በየቀኑ ቁልፍ በሆነ አንድ ትምህርት ላይ ለመሥራት ግብ ማውጣት ትችል ዘንድ እነዚህን ትምህርቶች እንከፋፍላቸው። እንዴት? ትምህርቶቹን እንዲሁ ገረፍ ገረፍ አድርገህ ብቻ አትለፋቸው። “የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” በማለት ኢየሱስ ክርስቶስን የጠየቀውን ባለጠጋ አለቃ አስታውስ። ኢየሱስ የአምላክ ሕግ የሚጠይቃቸውን በጣም አስፈላጊ የሆኑ ብቃቶች በጠቀሰ ጊዜ ሰውዬው እነዚህን ብቃቶች ቀደም ሲልም ይፈጽማቸው እንደነበረ ገለጸ። ቢሆንም ገና ሊያደርገው የሚገባ ነገር እንዳለ ተገነዘበ። ኢየሱስም ሰውዬው ንቁ ደቀ መዝሙር ለመሆን የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በሆነ መንገድ በሕይወቱ ውስጥ በሥራ ላይ ለማዋል ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርግ ጠየቀው። ሰውዬው ግን ይህን ለማድረግ የተዘጋጀ አይመስልም ነበር። (ሉቃስ 18:18-23) ስለሆነም ዛሬ የኢየሱስን ትምህርቶች ለመማር የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በኢየሱስ ትምህርቶች እንደሚስማማ በመግለጽና ትምህርቶቹን አጥብቆ በመያዝ መካከል ልዩነት እንዳለ ማስታወስ ይኖርበታል። ውጥረትን ማቅለል የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው።

18. ከዚህ ጥናት ጋር የቀረበውን ሣጥን ጠቃሚ በሆነ መንገድ እንዴት ልትጠቀምበት እንደምትችል ግለጽ።

18 የኢየሱስን ትምህርቶች መመርመርና በሥራ ላይ ማዋል ትችል ዘንድ በመጀመሪያ ከዚህ ርዕስ ጋር በቀረበው ሣጥን ውስጥ የሚገኘውን አንደኛ ነጥብ ተመልከት። ማቴዎስ 5:​3-9ን ይጠቅሳል። ማናችንም ብንሆን በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ በሚገኙት ግሩም ምክሮች ላይ ረዘም ላለ ሰዓት ማሰላሰል እንደምንችል የታወቀ ነው። ሆኖም እንዲያው በጥቅሉ ስትመለከታቸው ባሕርይን በሚመለከት ምን ብለህ ልትደመድም ትችላለህ? ከልክ ያለፈ ውጥረት በሕይወትህ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በእርግጥ ማሸነፍ የምትፈልግ ከሆነ ምን ሊረዳህ ይችላል? ትኩረት ሰጥተህ በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ በማሰላሰል ያለህበትን ሁኔታ ማሻሻል የምትችለው እንዴት ነው? ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ተጨማሪ ትኩረት መስጠት ትችል ዘንድ በሕይወትህ ውስጥ ያን ያህል ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው የማይገቡ አንዳንድ ጉዳዮች ይኖሩ ይሆን? እንደዚያ ካደረግህ ደስታህ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ይጨምራል።

19. ተጨማሪ ማስተዋልና እውቀት ለማግኘት ምን ልታደርግ ትችላለህ?

19 አሁን ደግሞ ልትወስደው የሚገባ ሌላ ተጨማሪ እርምጃ እንመልከት። እነዚህን ጥቅሶች ከአንድ የአምላክ አገልጋይ ምናልባትም ከትዳር ጓደኛህ፣ ከቅርብ ዘመድህ ወይም ከጓደኛህ ጋር ለምን አትወያይባቸውም? (ምሳሌ 18:24፤ 20:5) ባለጠጋው አለቃ አስፈላጊ ስለሆነ አንድ ጉዳይ ሌላ ሰው ማለትም ኢየሱስን እንደጠየቀ ልብ በል። የተሰጠው ምላሽ ደስታውን ሊጨምርለትና ቀሪ ሕይወቱን ብሩህ ሊያደርግለት ይችል ነበር። እነዚህን ጥቅሶች የምታወያየው የእምነት ባልደረባህ ከኢየሱስ ጋር እንደማይተካከል እሙን ነው፤ ሆኖም በኢየሱስ ትምህርቶች ላይ የምታደርጉት ውይይት ሁለታችሁንም ይጠቅማችኋል። ለምን አሁኑኑ እንዲህ ማድረግ አትጀምርም።

20, 21. ስለ ኢየሱስ ትምህርቶች ለመማር ምን ዓይነት ፕሮግራም ልትከተል ትችላለህ? ያደረግኸውን እድገት መገምገም የምትችለውስ እንዴት ነው?

20 አሁንም “አንተን ለመርዳት የተዘጋጁ ትምህርቶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት። ትምህርቶቹ በየቀኑ ቢያንስ አንድ ጥቅስ መመርመር በሚያስችልህ መንገድ ተዘጋጅተዋል። በመጀመሪያ በተጠቀሱት ጥቅሶች ውስጥ ኢየሱስ የተናገረውን ልታነብ ትችላለህ። ከዚያም ስለ ቃላቱ አስብ። በሕይወትህ እንዴት በሥራ ላይ ልታውላቸው እንደምትችል አሰላስል። እየሠራህበት ያለኸው ነገር እንደሆነ ከተሰማህ ከዚህ መለኮታዊ ትምህርት ጋር ተስማምተህ ለመኖር ምን ተጨማሪ ነገር ልታደርግ እንደምትችል አሰላስል። በዚያው ዕለት ትምህርቱን በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት አድርግ። ትምህርቱን መረዳት ወይም እንዴት በሥራ ላይ እንደምታውለው ማወቅ ከተቸገርህ ሌላ አንድ ቀን ጨምር። ይሁን እንጂ በዚህ ትምህርት እስካልተሳካልህ ድረስ ወደ ሌላ ትምህርት ማለፍ እንደማትችል አድርገህ አታስብ። በሚቀጥለው ቀን ሌላ ትምህርት ልትመረምር ትችላለህ። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ አራቱን ወይም አምስቱን የኢየሱስ ትምህርቶች በሥራ ላይ በማዋል ረገድ ምን ያህል እንደተሳካልህ ልትከልስ ትችላለህ። በሁለተኛውም ሳምንት በየቀኑ እንዲሁ አድርግ። ያለፉትን አንዳንድ ትምህርቶች በሥራ ላይ ማዋል ብትቸገር ተስፋ አትቁረጥ። ሁሉም ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። (2 ዜና መዋዕል 6:36፤ መዝሙር 130:3፤ መክብብ 7:20፤ ያዕቆብ 3:8) ትምህርቶቹን በሦስተኛውም በአራተኛውም ሳምንት በሥራ ላይ ማዋልህን ቀጥል።

21 በአንድ ወር ወይም ከዚያ ብዙም በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ሠላሳ አንዱንም ነጥቦች ሸፍነህ ትጨርስ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ በመጨረሻ ምን ይሰማሃል? ውጥረትህ ቀለል እንደሚልልህና ይበልጥ ደስተኛ ልትሆን እንደምትችል አይሰማህም? ያደረግኸው መሻሻል አነስተኛ ቢሆንም እንኳ ያለብህ ውጥረት እንደሚቀንስ የታወቀ ነው፤ ሌላው ቢቀር ያለብህን ውጥረት በተሻለ መንገድ መቋቋም ትችላለህ። በዚሁ መቀጠል የሚያስችል ዘዴም ታገኛለህ። በዚህ ዝርዝር ውስጥ ያልተካተቱ ግሩም የሆኑ ሌሎች የኢየሱስ ትምህርቶች እንዳሉ አትዘንጋ። አንዳንዶቹን በመመርመር ለምን በሥራ ላይ ለማዋል አትሞክርም?​—⁠ፊልጵስዩስ 3:16

22. የኢየሱስን ትምህርቶች መከተል ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል? ይሁን እንጂ ልንመረምረው የሚገባን ሌላ ምን ተጨማሪ ገጽታ አለ?

22 የኢየሱስ ቀንበር ምንም ክብደት የሌለው ነው ባይባልም እንኳ ልዝብ እንደሆነ ልትመለከት ትችላለህ። ትምህርቱም ሆነ የእርሱ ደቀ መዝሙር መሆን ለመሸከም የሚከብድ አይደለም። የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ 60 ለሚያክሉ ዓመታት በራሱ ሕይወት ላይ ከተመለከተው ተሞክሮ በመነሳት “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም” በማለት ይህን ሐቅ መስክሯል። (1 ዮሐንስ 5:3) አንተም ተመሳሳይ የሆነ ትምክህት ሊያድርብህ ይችላል። የኢየሱስን ትምህርቶች ይበልጥ በሥራ ላይ እያዋልክ በሄድክ መጠን በአሁን ጊዜ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ሕይወታቸው በውጥረት እንዲሞላ ያደረጉት ነገሮች በአንተ ላይ ያን ያህል ጭንቀት የሚፈጥሩ እንደማይሆኑ የበለጠ ግልጽ እየሆነልህ ይሄዳል። ከፍተኛ እፎይታ እንዳመጣልህም መገንዘብ ትችላለህ። (መዝሙር 34:8) ሆኖም የኢየሱስን ልዝብ ቀንበር በሚመለከት ልትመረምረው የሚገባ ሌላ ገጽታም አለ። ኢየሱስ ‘የዋህና በልቡም ትሑት እንደሆነ’ ተናግሯል። ይህ የኢየሱስን ትምህርት ከመማራችንና የእርሱን ምሳሌ ከመከተላችን ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ይህን እንመረምራለን።​—⁠ማቴዎስ 11:29

መልስህ ምንድን ነው?

• ከውጥረት እፎይታ ለማግኘት ከፈለግን ወደ ኢየሱስ ዞር ማለት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

• ቀንበር ምንን ለማመልከት ያገለግል ነበር? ለምንስ?

• ኢየሱስ ቀንበሩን እንዲሸከሙ ሰዎችን የጋበዘው ለምን ነበር?

• መንፈሳዊ እረፍት ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የይሖዋ ምሥክሮች የ2002 የዓመት ጥቅስ “ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ” የሚለው ይሆናል።​—⁠ማቴዎስ 11:28

[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አንተን ለመርዳት የተዘጋጁ ትምህርቶች

ከማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7 ድረስ ምን ጠቃሚ ነገሮችን ልታገኝ ትችላለህ? እነዚህ ምዕራፎች ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ ገሊላ በሚገኝ በአንድ የተራራ ጥግ ያስተማራቸውን ትምህርቶች ይዘዋል። መጽሐፍ ቅዱስህን ከፍተህ ከዚህ በታች የሰፈሩትን ጥቅሶች እያነበብክ ከጥቅሶቹ ጎን የሰፈሩትን ጥያቄዎች ራስህን ጠይቅ።

1. 5:3-9 ያለኝን አጠቃላይ ዝንባሌ በተመለከተ ይህ ምን ይነግረኛል? ደስታዬን ለመጨመር ምን ማድረግ እችላለሁ? ለመንፈሳዊ ፍላጎቶቼ ተጨማሪ ትኩረት መስጠት የምችለው እንዴት ነው?

2. 5:25, 26 ብዙዎች የሚያንጸባርቁትን የጠበኝነት መንፈስ ከመከተል ይልቅ ምን ማድረጉ የተሻለ ነው?​—⁠ሉቃስ 12:58, 59

3. 5:27-30 የፆታ ቅዠትን በተመለከተ ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ጠበቅ አድርገው የሚገልጹት ምንድን ነው? እንዲህ ያለውን ስሜት ማስወገዴ ደስታና የአእምሮ ሰላም የሚጨምርልኝ እንዴት ነው?

4. 5:38-42 ዛሬ ባለው ኅብረተሰብ ውስጥ ጎልቶ የሚታየው የአትንኩኝ ባይነት ባሕርይ እንዳይጋባብኝ መጣር ያለብኝ ለምንድን ነው?

5. 5:43-48 ጠላቶች እንደሆኑ አድርጌ የማስባቸውን ሰዎች በቅርብ ለማወቅ ጥረት ባደርግ የምጠቀመው እንዴት ነው? ውጥረትን ለመቀነስ ወይም ለማጥፋት ይህ ምን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል?

6. 6:14, 15 አንዳንድ ጊዜ ይቅር ለማለት የሚከብደኝ ከሆነ ይህ የሚሆንበት ዋነኛው ምክንያት ምቀኝነት ወይም ጥላቻ በውስጤ ስላለ ይሆን? በዚህ ረገድ ለውጥ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

7. 6:16-18 ከውስጣዊው ይልቅ ለውጫዊ ማንነቴ የበለጠ ትኩረት የመስጠት ዝንባሌ አለኝ? ይበልጥ ሊያሳስበኝ የሚገባው የትኛው ነው?

8. 6:19-32 ለገንዘብና ለሃብት ከልክ በላይ የምጨነቅ ብሆን ምን ውጤት ሊያስከትልብኝ ይችላል? በዚህ ረገድ ሚዛኔን እንድጠብቅ የሚረዳኝ ስለምን ነገር ማሰብ ነው?

9. 7:1-5 ስህተት ከሚለቃቅሙ፣ ከሚነቅፉና ሌሎችን ከሚኮንኑ ሰዎች ጋር በምሆንበት ጊዜ ምን ይሰማኛል? እንደዚያ ዓይነት ሰው ከመሆን መራቅ ያለብኝ ለምንድን ነው?

10. 7:7-11 ልመና በማቀርብበት ጊዜ አምላክን አለማቋረጥ መጠየቁ አስፈላጊ ከሆነ በሌሎች የኑሮ ገጽታዎችስ ምን ለማለት ይቻላል?​—⁠ሉቃስ 11:5-13

11. 7:12 ምንም እንኳ ወርቃማውን ሕግ ባውቀውም ከሌሎች ጋር ባለኝ ግንኙነት ይህን ምክር ምን ያህል እሠራበታለሁ?

12. 7:24-27 ሕይወቴን በምመራበት መንገድ ረገድ ተጠያቂው ራሴ ብሆንም እንደ ኃይለኛ ዝናብ ላለ ችግርና እንደ ጎርፍ ላለ መከራ ራሴን በተሻለ መንገድ ማዘጋጀት የምችለው እንዴት ነው? ስለዚህ ጉዳይ አሁኑኑ ማሰብ ያለብኝ ለምንድን ነው?​—⁠ሉቃስ 6:​46-49

ልመረምር የምችላቸው ሌሎች ተጨማሪ ትምህርቶች:-

13. 8:2, 3 ኢየሱስ ብዙ ጊዜ እንዳደረገው ለተቸገሩ ርኅራኄ ማሳየት የምችለው እንዴት ነው?

14. 9:9-38 ምሕረት ማሳየት በሕይወቴ ውስጥ ምን ያህል ትልቅ ቦታ አለው? ይህን ባሕርይ ይበልጥ ማሳየት የምችለውስ እንዴት ነው?

15. 12:19 ለኢየሱስ ከተነገረው ትንቢት ትምህርት በመቅሰም ወደ ጠብ ከሚመራ ጭቅጭቅ ለመራቅ ጥረት አደርጋለሁ?

16. 12:20, 21 በቃልም ሆነ በድርጊት ሌሎችን ባለመስበር ምን ጥሩ ነገር ላደርግ እችላለሁ?

17. 12:34-37 አብዛኛውን ጊዜ የማወራው ስለ ምን ጉዳይ ነው? ብርቱካን ስጨምቅ የብርቱካን ጭማቂ እንደሚወጣ ሁሉ በውስጤ ማለትም በልቤ ውስጥ ስላለው ነገር ማሰብ የሚኖርብኝ ለምንድን ነው?​—⁠ማርቆስ 7:20-23

18. 15:4-6 ኢየሱስ ከሰጠው አስተያየት አረጋውያንን ስለመንከባከብ ምን ቁም ነገር እመለከታለሁ?

19. 19:13-15 ምን ለማድረግ ጊዜ መዋጀት ያስፈልገኛል?

20. 20:25-28 በሥልጣን አላግባብ መጠቀም ተገቢ ያልሆነው ለምንድን ነው? በዚህ ረገድ ኢየሱስን መምሰል የምችለው እንዴት ነው?

ማርቆስ ያሠፈራቸው ተጨማሪ ሐሳቦች:-

21. 4:24, 25 ሌሎችን የምይዝበት መንገድ ምን ውጤት ያስከትላል?

22. 9:50 የምናገረውና የማደርገው ሌሎችን የሚያስደስት ከሆነ ምን ውጤት ሊኖረው ይችላል?

በመጨረሻም ሉቃስ ካሰፈራቸው ዘገባዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ትምህርቶች:-

23. 8:11, 14 ጭንቀት፣ ባለ ጠግነትና ተድላ ሕይወቴን የሚቆጣጠሩት ከሆነ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል?

24. 9:1-6 ኢየሱስ የታመሙትን መፈወስ ይችል የነበረ ቢሆንም እንኳ በመጀመሪያ ምን ያደርግ ነበር?

25. 9:52-56 ቶሎ እበሳጫለሁ? የበቀለኝነትን ስሜት አስወግጄአለሁ?

26. 9:62 ስለ አምላክ መንግሥት የመናገር ኃላፊነቴን እንዴት መመልከት ይኖርብኛል?

27. 10:29-37 ለሌላው ግድ የሌለኝ ሳልሆን የሰው ችግር የሚሰማኝ መሆኔን ማሳየት የምችለው እንዴት ነው?

28. 11:33-36 ኑሮዬን ቀላል ለማድረግ ምን ለውጦችን ማድረግ እችላለሁ?

29. 12:15 በሕይወትና በንብረት መካከል ያለው ተዛምዶ ምንድን ነው?

30. 14:28-30 የማደርጋቸውን ውሳኔዎች ጊዜ ወስጄ የምመዝን ከሆነ ከምን ነገር ልርቅ እችላለሁ? ይህስ ምን ጥቅም አለው?

31. 16:10-12 የአቋም ጽናትን ጠብቆ መኖር ምን ጥቅሞች ሊያስገኝልኝ ይችላል?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኢየሱስ ቀንበር ሥር ሆነን የምናከናውነው ሕይወት አድን ሥራ እረፍት የሚሰጥ ነው