በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የማያምን ባል ያላት አንዲት ክርስቲያን ሚስት ባለቤቷ በሃይማኖታዊ በዓሎች የሚካፈል ቢሆን ለአምላክ ያላትን ታማኝነት ሳታጓድል ለባልዋ መገዛት የምትችለው እንዴት ነው?

እንዲህ ማድረግ ጥበብና ብልሃት ይጠይቅባታል። ሆኖም ሁለቱን ግዴታዎቿን በሚዛናዊነት ለመወጣት መጣሯ ስህተት የለበትም። ኢየሱስ “እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” በማለት ከዚህ ጋር በሚመሳሰል ጉዳይ ላይ ምክር ሰጥቷል። (ማቴዎስ 22:​21) እርግጥ ነው፣ ይህን ሲል ክርስቲያኖች ከጊዜ በኋላ እንዲገዙላቸው ለተነገራቸው ለመንግሥት ባለ ሥልጣናት ያለባቸውን ግዴታ ማመልከቱ ነበር። (ሮሜ 13:​1) ሆኖም ምክሩ አንዲት ሚስት ባልዋ የማያምን ቢሆንም እንኳ ለአምላክ ያለባትን ግዴታ ሳታጓድል ለባልዋ ማሳየት የሚገባትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ተገዥነት እንድትወጣም ሊያስተምር ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ የአንድ ክርስቲያን ቀዳሚ ግዴታ በማንኛውም ጊዜ ሁሉን ቻይ ለሆነው አምላክ ታማኝነትን ማሳየት መሆኑን በጥብቅ እንደሚናገር ማንኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ የሚስማማበት ጉዳይ ነው። (ሥራ 5:​29) ያም ሆኖ አንድ እውነተኛ አምላኪ ከፍ ያሉትን የአምላክ ሕጎች ሳይጥስ በእርሱ ላይ ሥልጣን ያለውን የማያምን ሰው ጥያቄ ወይም ፍላጎት ማሟላት የሚችልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ።

በዳንኤል ምዕራፍ 3 ውስጥ ከሚገኘው ስለ ሦስቱ ዕብራውያን ከሚናገረው ታሪክ ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣን የነበረው ናቡከደነፆር እነርሱም ሆኑ ሌሎች ሰዎች በዱራ ሜዳ እንዲገኙ አዋጅ አስነገረ። እነዚህ ሦስት ዕብራውያን የሐሰት አምልኮ ለማካሄድ መታቀዱን በመገንዘብ እንደ ምርጫቸው ቢሆን ኖሮ በቦታው ባይገኙ ደስ ባላቸው ነበረ። ዳንኤል እንዲቀር ያደረገው በቂ ምክንያት የነበረው ሊሆን ቢችልም እነዚህ ሦስቱ ግን ለመቅረት የሚያስችል ምንም ምክንያት አልነበራቸውም። a ስለዚህ በዚያ ቦታ እንዲገኙ የወጣውን መመሪያ ለማክበር፣ ሆኖም በማንኛውም ዓይነት የተሳሳተ ድርጊት ላለመካፈል ወሰኑ። ደግሞም አልተካፈሉም።​—⁠ዳንኤል 3:​1-18

በተመሳሳይም በበዓል ሰሞን አንድ የማያምን ባል ክርስቲያን የሆነችው ሚስቱ ባታደርግ የምትመርጠውን ነገር እንድታደርግለት ሊጠይቃት ወይም ሊያዛት ይችላል። አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት:- እርሱና ሌሎች ሰዎች ዓመት በዓል በሚያከብሩበት ዕለት የሚመገቡት አንድ ዓይነት ምግብ እንድታዘጋጅለት ይነግራታል። ወይም በበዓሉ ዕለት ለግብዣ ወይም እንዲሁ ለጥየቃ (ሚስቱን ጨምሮ) ቤተሰቡን ይዞ ዘመዶቹ ቤት መሄድ ይፈልግ ይሆናል። ወይም ደግሞ በዓሉ ከመድረሱ በፊት ሚስቱ ገበያ ስትወጣ በዚያው ለበዓሉ የሚያስፈልግ ምግብ፣ የስጦታ ዕቃዎችን ወይም ስጦታ መጠቅለያ ወረቀትና ከስጦታዎቹ ጋር አብሮ የሚሰጠው ካርዶች እንድትገዛለት ይነግራት ይሆናል።

አንዲት ክርስቲያን ሚስት በሐሰት ሃይማኖታዊ ድርጊቶች ላለመካፈል ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርባታል። ሆኖም ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉ ጥያቄዎች ቢቀርቡላትስ? የቤተሰቡ ራስ እሱ ነው። የአምላክ ቃል ደግሞ “ሚስቶች ሆይ፣ በጌታ እንደሚገባ ለባሎቻችሁ ተገዙ” ይላል። (ቆላስይስ 3:​18) እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማት ለአምላክ ያላትን ታማኝነት ሳታጓድል ከአንዲት ሚስት የሚጠበቀውን ተገዥነት ማሳየት ትችላለች? ለይሖዋ ልትሰጠው የሚገባትን የላቀ ታዛዥነት ሳታጓድል ለባልዋ እንዴት መታዘዝ እንደምትችል መወሰን ይኖርባታል።

ባለቤትዋ በሌሎች ጊዜያት አንድ የሚወደውን ወይም ብዙውን ጊዜ በአንድ ወቅት መመገብ የለመደውን ምግብ እንድትሠራለት ይጠይቃት ይሆናል። ለእርሱ ያላትን ፍቅርና የራስነት ሥልጣኑን እንደምታከብር ማሳየት ትፈልጋለች። ሆኖም ያንን ምግብ ለበዓሉ ቀን እንድታዘጋጅለት ቢጠይቃት ትታዘዘዋለች? አንዳንድ ክርስቲያን ሚስቶች ምግብ የማብሰል ሥራ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው እንደሆነ አድርገው በመቁጠር በጥሩ ሕሊና የተባሉትን ያከናውኑ ይሆናል። ባለቤቷ ሁኔታውን ከበዓል ጋር ቢያያይዘውም እንኳ የትኛዋም ታማኝ ክርስቲያን እንደዚያ አድርጋ እንደማታያይዘው የታወቀ ነው። በተመሳሳይም በየወሩ ወይም በየዓመቱ በተለያዩ ጊዜያት ዘመዶቹን ለመጠየቅ በሚሄድበት ጊዜ አብራው እንድትሆን ይጠይቃት ይሆናል። ዕለቱ ዓመት በዓል ቢሆንም እንኳ አብራው ትሄዳለች ማለት ነው? ወይም ገበያ በምትወጣበት ጊዜ በዚያው እንድትገዛለት የጠየቃትን ዕቃ ምን ሊያደርግበት እንዳሰበ ለማወቅ መጨነቅ ሳያስፈልጋት የጠየቃትን እቃ ለመግዛት ፈቃደኛ ትሆናለች?

እርግጥ ነው አንዲት ክርስቲያን ሚስት የምታደርገው ነገር በሌሎች ላይ ስለሚያሳድረው ተጽእኖ ማሰብ ይኖርባታል። (ፊልጵስዩስ 2:​4) ልክ ሦስቱ ዕብራውያን ወደ ዱራ ሜዳ ሲጓዙ ሌሎች እንዳያዩአቸው ለማድረግ ጥረት አድርገው ሊሆን እንደሚችል ሁሉ እሷም በዓሉን እንደምታከብር የሚያስመስል ነገር ከማድረግ ለመቆጠብ ጥረት ታደርጋለች። ስለሆነም ባለቤትዋ ስሜቷን ለመጠበቅ ካለው ፍላጎት የተነሳ ከዓመት በዓል ጋር የተያያዙ አንዳንድ ሥራዎችን እሱ ራሱ በማከናወን የምትወደውንና የምታከብረውን ሚስቱን ማሳረፍ ይችል እንደሆነ በዘዴ ልታግባባው ትችላለች። ሚስቱ በሐሰት ሃይማኖታዊ ድርጊቶች ለመካፈል ፈቃደኛ ባትሆን በሁለቱም ላይ ሊከተል የሚችለው አሳፋሪ ውጤት ከወዲሁ ይታየው ይሆናል። አዎን፣ በረጋ መንፈስ አስቀድሞ መነጋገር ሰላማዊ መፍትሔ ሊያስገኝ ይችላል።​—⁠ምሳሌ 22:​3

ለማጠቃለል ያህል አንዲት ታማኝ ክርስቲያን ሚስት እውነታዎቹን አገናዝባ ምን ማድረግ እንዳለባት መወሰን ይገባታል። ሦስቱ ዕብራውያን እንዳደረጉት ለአምላክ ታዛዥ መሆን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። (1 ቆሮንቶስ 10:​31) ሆኖም ይህን በአእምሮ በመያዝ እያንዳንዱ ክርስቲያን በቤተሰቡ ወይም በኅብረተሰቡ ውስጥ ሥልጣን ያለው ግለሰብ የሚሰጠውን ትእዛዝ ለመወጣት አቋሙን ሳያላላ ምን ነገር ማድረግ እንደሚችል መወሰን ይኖርበታል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በነሐሴ 1, 2001 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባብያን ጥያቄዎች” ተመልከት።