በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፈቃደኝነት መንፈስ ለጊልያድ ያበቃል

የፈቃደኝነት መንፈስ ለጊልያድ ያበቃል

የፈቃደኝነት መንፈስ ለጊልያድ ያበቃል

ጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የተቋቋመው ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ወንዶችንና ሴቶችን ለሚስዮናዊነት አገልግሎት ለማሰልጠን ነው። ጊልያድ መግባት የሚችሉት እነማን ናቸው? የፈቃደኝነት መንፈስ ያላቸው ናቸው። (መዝሙር 110:​3 አ.መ.ት ) መስከረም 8, 2001 የ111ኛው ክፍል ተማሪዎች በተመረቁበት ዕለት የታየውም ይህ ነበር።

የዚህ ክፍል ተመራቂዎች ከሆኑት ተማሪዎች መካከል አንዳንዶቹ ቀደም ሲልም ይበልጥ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄደው ለማገልገል ሲሉ በፈቃደኝነት ቤተሰባቸውን፣ ወዳጆቻቸውንና የትውልድ አገራቸውን የተዉ ናቸው። እንዲህ በማድረግ ከዚህ በፊት በማያውቁት አካባቢ ተላምደው መኖር ይችሉ እንደሆነና እንዳልሆነ ራሳቸውን ፈትነዋል። ለምሳሌ ያህል ሪሼ እና ናታሊ ወደ ቦሊቪያ፣ ቴድ እና ሚሼል ወደ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ ዴቪድ እና ሞኒክ ደግሞ በእስያ ወደምትገኝ አንዲት አገር በመሄድ የአምላክን መንግሥት ምሥራች አሰራጭተዋል። ሌሎች ተማሪዎች ደግሞ ኒካራጓ፣ ኢኳዶር እና አልባኒያ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ክሪስቲ ትዳር ከመያዟ በፊት ሁለት ዓመት በኢኳዶር ለማሳለፍ ላወጣችው እቅድ እንዲረዳት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለች ስፓንኛ ተምራለች። ሌሎች ደግሞ በየትውልድ አገሮቻቸው በሚገኙ የውጪ አገር ቋንቋ ተናጋሪ በሆኑ ጉባኤዎች ላይ ይገኙ ነበር። ሳኦል እና ጵርስቅላ ደግሞ ወደ ትምህርት ቤቱ ከመጠራታቸው በፊት በጣም የሚከብዳቸውን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የፈቃደኝነት መንፈስ አሳይተዋል።

ሃያ ሳምንታት የፈጀው የሚስዮናዊነት ሥልጠና ወዲያው አልቆ ወዳጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት ጥበብ የሞላባቸውን ምክሮችና የመጨረሻ የማበረታቻ ቃላት የሚያዳምጡበት ዕለት ከተፍ አለ።

የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር ከጊልያድ ትምህርት ቤት ሰባተኛው ክፍል የተመረቀውና አሁን የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል ሆኖ የሚያገለግለው ቴዎዶር ጃራዝ ነበር። የመክፈቻ ንግግሩ የአምላክ ድርጅት በጊልያድ ተማሪዎችን በማሠልጠን የመንግሥቱን ምሥራች በመላው ምድር ላይ ለማዳረስ ካለው ዓላማ ዝንፍ እንዳላለ ጎላ አድርጎ የሚገልጽ ነበር። (ማርቆስ 13:​10) ጊልያድ ብቃቱ ያላቸው ተማሪዎች ይህን የስብከት ሥራ ቀደም ሲል ያከናውኑ ከነበረበት በተሻለ ሁኔታ እንዲያከናውኑ እንዲሁም የሰለጠኑ ሚስዮናውያን ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው የዓለም ክፍሎች ሄደው እንዲያገለግሉ ያስታጥቃቸዋል። ወንድም ጃራዝ ተመራቂዎቹ በተመደቡባቸው 19 አገሮች ውስጥ በማገልገል ላይ ካሉ ሚስዮናውያን ጋር መሥራት በሚጀምሩበት ጊዜ በጊልያድ ያገኙትን ሥልጠና በሚገባ እንዲጠቀሙበት አሳስቧቸዋል።

ተመራቂዎቹ ያገኙት ወቅታዊ ምክር

ቀጥሎ ተከታታይ ንግግሮች ቀረቡ። የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ዊልያም ቫን ዲ ዎል “ሚስዮናዊ ቅንዓት​—⁠የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት” በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበ። በማቴዎስ 28:​19, 20 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው ‘ደቀ መዛሙርት ስለማድረግ’ በሚናገረው ተልዕኮ ላይ በማተኮር “በቅንዓትና በጋለ መንፈስ ሚስዮናዊ አገልግሎቱን ያከናወነውን ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ ኮርጁ” በማለት ተማሪዎቹን አበረታታቸው። እጩ ሚስዮናውያኑ የሚስዮናዊነት ቅንዓታቸው እንዳይቀዘቅዝ ለመርዳት “ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ፕሮግራም አውጥታችሁ ያንን በጥብቅ ተከተሉ፣ ጥሩ የግል ጥናት ልማድ ይኑራችሁ፣ ከቲኦክራሲያዊው እንቅስቃሴ ጋር እኩል ተራመዱ፤ እንዲሁም እዚያ የተመደባችሁበት ምክንያት ምንጊዜም ትዝ ይበላችሁ” በማለት አበረታታቸው።

በወጣው ፕሮግራም መሠረት ቀጥሎ ንግግሩን ያቀረበው የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ጋይ ፒርስ ነበር። ወንድም ፒርስ “‘የማመዛዘን ችሎታችሁን’ ማዳበራችሁን አታቋርጡ” የሚል ጭብጥ ያለው ንግግር አቀረበ። (ሮሜ 12:​1 NW ) ተመራቂ ተማሪዎቹ የአምላክ ስጦታ የሆነውን የማሰብና የማመዛዘን ችሎታ እንዲጠቀሙበት በማበረታታት ተግባራዊ ምክሮች ሰጣቸው። “ይሖዋ በቃሉ በኩል በሚነግራችሁ ነገር ላይ ማሰላሰላችሁን አታቋርጡ። ይህ ጥበቃ ይሆንላችኋል” አላቸው። (ምሳሌ 2:​11) በተጨማሪም ወንድም ፒርስ ተማሪዎቹ ‘የማመዛዘን ችሎታቸው’ እንዳይገታ እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚል ግትር አመለካከት እንዳይኖራቸው አጥብቆ አሳሰባቸው። በእርግጥም እነዚህ ወቅታዊ ማሳሰቢያዎች ተመራቂዎቹ ሚስዮናዊ አገልግሎታቸውን ሲጀምሩ ይረዷቸዋል።

ቀጥሎ ሊቀ መንበሩ ከጊልያድ አስተማሪዎች መካከል አንዱ የሆነውን ሎውረንስ ቦወንን ያስተዋወቀ ሲሆን እርሱም “ሌላ ነገር ላለማወቅ ቁረጡ” በሚል ጭብጥ ንግግር አቀረበ። ወንድም ቦወን፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ካከናወነው ሚስዮናዊ ሥራ ጋር በተያያዘ ‘ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር እርሱም እንደ ተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳያውቅ ቆርጦ’ እንደነበር አመልክቷል። (1 ቆሮንቶስ 2:​2) ጳውሎስ በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ከፍተኛው ኃይል ማለትም መንፈስ ቅዱስ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተንጸባርቆ የሚገኘውን ተስፋ በተሰጠበት ዘር አማካኝነት የይሖዋ ሉዓላዊነት እንደሚረጋገጥ የሚገልጸውን መልእክት እንደሚደግፍ ያውቅ ነበር። (ዘፍጥረት 3:​15) አርባ ስምንቱ ተመራቂዎች እንደ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ እንዲሆኑና ‘የጤናማውን ቃል ምሳሌ’ አጥብቀው በመያዝ በሚስዮናዊነታቸው ስኬት እንዲያገኙ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 1:​13

በመክፈቻው ላይ ከቀረቡት ተከታታይ ንግግሮች መካከል የመጨረሻው “የአምላክ ስጦታ ለሆነው ልዩ መብታችሁ አድናቆት ይኑራችሁ” የሚል ጭብጥ ነበረው። የጊልያድ ትምህርት ቤት ሬጂስትራር የሆነው ዋላስ ሊቨረንስ ተመራቂዎቹ የአገልግሎት መብት ይገባናል የማንለው የአምላክ ደግነት መግለጫ እንጂ ለሥራቸው እንደ ወሮታ ሆኖ የሚከፈል እንዳልሆነ እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል። ወንድም ሊቨረንስ ሐዋርያው ጳውሎስን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ይሖዋ ጳውሎስን የአሕዛብ ሐዋርያ እንዲሆን የመረጠው በሠራው ሥራ አልነበረም። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ጳውሎስ ይህን ቦታ የማግኘት መብት እንዲኖረው የሚያደርግ ሥራ አከናውኗል ማለት ይሆን ነበር። ምርጫው በሥራ ዘመን ብልጫ ወይም በልምድ ላይ የተመካ አልነበረም። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ የሚመረጠው በርናባስ ይሆን ነበር። ምርጫው በግል ችሎታ ላይ የተመሠረተም አልነበረም። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ከጳውሎስ ይልቅ አጵሎስ አንደበተ ርቱዕ ነበር። ይህ መብት ይገባናል የማንለው የአምላክ ደግነት መግለጫ ነው።” (ኤፌሶን 3:​7, 8) ወንድም ሊቨረንስ ተመራቂዎቹ ከአምላክ ያገኙትን ስጦታ ወይም የአገልግሎት መብታቸውን ሌሎች የአምላክ ወዳጅ እንዲሆኑና ‘የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ የሆነውን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት’ እንዲያገኙ ለመርዳት እንዲጠቀሙበት አበረታታቸው።​—⁠ሮሜ 6:​23

ከዚያ ቀጥሎ ሌላው የጊልያድ አስተማሪ ማርክ ኑሜር “ዝግጅት ጥሩ ውጤት ያስገኛል” በሚል ጭብጥ ከአንዳንድ ተማሪዎች ጋር የተደረገውን አስደሳች ውይይት መራ። (ምሳሌ 21:​5) ከቀረቡት ተሞክሮዎች ለማየት እንደተቻለው አንድ አገልጋይ በተለይ ልቡን በማዘጋጀት ለአገልግሎት ጥሩ ዝግጅት ሲያደርግ ለሰዎች ከልብ ማሰብ ይጀምራል። ምን እንደሚናገር አይጠፋውም። ከዚህ ይልቅ እነርሱን በመንፈሳዊ የሚረዳቸውን ነገር ይናገራል እንዲሁም ያደርጋል። ወንድም ኑሜር በአፍሪካ በሚስዮናዊነት ያሳለፈውን የራሱን ተሞክሮ በመጥቀስ “የተሳካለት ሚስዮናዊ ለመሆን ቁልፉ ዝግጅት ነው” በማለት ተናገረ።

ሚስዮናዊ አገልግሎት​—⁠እርካታ የሚገኝበት የሥራ መስክ

ራልፍ ዎልስ እና ቻርለስ ዉዲ ለልዩ ሥልጠና ወደ ፓተርሰን የትምህርት ማዕከል ከመጡ ተሞክሮ ያላቸው አንዳንድ ሚስዮናውያን ጋር ቃለ ምልልስ አደረጉ። የቀረቡት ቃለ ምልልሶች ሰውን ማፍቀር በሚስዮናዊ አገልግሎት ደስታ እንደሚያስገኝ የሚያጎሉ ነበሩ። ተማሪዎች፣ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ሚስዮናዊ አገልግሎት እርካታ የሚገኝበት የሥራ መስክ የሆነው ለምን እንደሆነ ተሞክሮ ካካበቱ ሚስዮናውያን አንደበት መስማታቸው ስሜትን የሚያነቃቃ ሆኖላቸዋል።

የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ጆን ኢ ባር “ለይሖዋ አዲስ መዝሙር ዘምሩ” በሚል ርዕስ ዋናውን ንግግር አቀረበ። (ኢሳይያስ 42:​10) ወንድም ባር “አዲስ መዝሙር” የሚለው መግለጫ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዘጠኝ ጊዜ እንደሚገኝ ገለጸና “ለመሆኑ ይህ አዲስ መዝሙር ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ አነሳ። ከዚያም “በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው አዲስ መዝሙር የተዘመረው የይሖዋን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በተወሰደው እርምጃ አዳዲስ ውጤቶች በመገኘታቸው ነው” በማለት መልስ ሰጠ። ተማሪዎቹ በመሲሐዊው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራውን ድል አድራጊ የአምላክ መንግሥት ለማወደስ በሚዘመረው መዝሙር መካፈላቸውን እንዳያቋርጡ አበረታታቸው። ወንድም ባር ተማሪዎቹ በጊልያድ ያገኙት ሥልጠና የዚህን “አዲስ መዝሙር” የተለያየ ገጽታ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እንዲረዱ ያስቻላቸው መሆኑን ገለጸ። “ትምህርት ቤቱ በምትሄዱባቸው ቦታዎች ከሚገኙ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ጋር በመሆን የይሖዋን ውዳሴ አጣጥማችሁ ‘መዘመራችሁ’ አስፈላጊ መሆኑን አጉልቶላችኋል። በምድብ ቦታችሁ ምንጊዜም ከሌሎች ጋር አንድነት ይኑራችሁ።”

ተማሪዎቹ ዲፕሎማቸውን ከተቀበሉ በኋላ የተማሪዎቹ ተወካይ ተማሪዎቹ በጊልያድ ቆይታቸው ላገኙት ሥልጠና የተሰማቸውን ልባዊ አድናቆት የሚገልጽ ደብዳቤ አነበበ።

አንተስ ለአምላክ የምታቀርበውን አገልግሎት ማስፋትና ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ ትችላለህ? ከሆነ አንተም እነዚህ ተመራቂዎች የነበራቸው ዓይነት የፈቃደኝነት መንፈስ ይኑርህ። እነርሱን ሚስዮናዊ ለመሆን ያበቃቸው ይህ ነው። አንድ ሰው በፈቃደኝነት ስሜት ራሱን ለአምላክ አገልግሎት ሲያቀርብ ታላቅ ደስታ ማግኘቱ አይቀርም።​—⁠ኢሳይያስ 6:​8

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ስለ ተማሪዎቹ የቀረበ አኃዛዊ መረጃ

የተውጣጡባቸው አገሮች ብዛት:- 10

የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 19

የተማሪዎቹ ብዛት:- 48

አማካይ ዕድሜ:- 33.2

በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 16.8

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 12.6

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 111ኛ ክፍል ተመራቂዎች

ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ተራ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።

(1) ዮማንስ ሲ፣ ቶካሪ ኤ፣ ኑንየስ ኤስ፣ ፊሊፕስ ጄ፣ ዶውኪን ኤም፣ ሲልቬስትሪ ፒ። (2) ሞረን ኤን፣ ቢኔ ጄ፣ ሎፔዝ ኤም፣ ቮን ሃውት ኤም፣ ካንቱ ኤ፣ ሲልቫሺ ኤፍ። (3) ዊልያምስ ኤም፣ ኢቶ ኤም፣ ቫን ኮይሊ ኤስ፣ ለቨሪንግ ዲ፣ ፉዘል ኤፍ፣ ጋይስለ ኤስ (4) ዮማንስ ጄ፣ ሞውስ ኤም፣ ሆጂንስ ኤም፣ ደዲንግ ኤስ፣ ብሪሰንዮ ጄ፣ ፊሊፕስ ኤም። (5) ሎፔዝ ጄ፣ ኢቶ ቲ፣ ሶውመሩድ ኤስ፣ ኮውዛ ሲ፣ ፉዘል ጂ፣ ሞውስ ዲ። (6) ዊልያምስ ዲ፣ ደዲንግ አር፣ ጋይስለ ኤም፣ ሞረን አር፣ ቢኔ ኤስ፣ ካንቱ ኤል። (7) ዶውኪን ኤም፣ ሆጂንስ ቲ፣ ለቨሪንግ ኤም፣ ሲልቬስትሪ ኤስ፣ ቮን ሃውት ዲ፣ ብሪሰንዮ ኤ። (8) ቫን ኮይሊ ኤም፣ ኑንየስ ኤ፣ ኮውዛ ቢ፣ ሶውመሩድ ጄ፣ ቶካሪ ኤስ፣ ሲልቫሺ ፒ