በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ወንጌላውያን ናቸው

ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ወንጌላውያን ናቸው

ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ወንጌላውያን ናቸው

“እግዚአብሔርን አመስግኑ ስሙንም ባርኩ፣ ዕለት ዕለትም ማዳኑን አውሩ።”​መዝሙር 96:​2

1. ሰዎች ሊሰሙት የሚገባ ምሥራች ምንድን ነው? የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ የመሰለውን ምሥራች በማዳረስ ረገድ በምሳሌነት የሚጠቀሱትስ እንዴት ነው?

 በየዕለቱ የተለያዩ ችግሮች በሚከሰቱበት ዓለም ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ ጦርነት፣ ወንጀል፣ ረሃብና ጭቆና እንደሚያከትም መናገሩን ማወቅ በእርግጥ የሚያጽናና ነው። (መዝሙር 46:​9፤ 72:​3, 7, 8, 12, 16) ታዲያ ይህ፣ ሁሉም ሰው ሊሰማው የሚገባ ምሥራች አይደለም? የይሖዋ ምሥክሮች እንደዚያ ይሰማቸዋል። በየትኛውም ሥፍራ የሚታወቁት “የመልካምን ወሬ የምስራች” በመስበክ ነው። (ኢሳይያስ 52:​7) እርግጥ ነው፣ ብዙ ምሥክሮች ምሥራቹን ለመናገር ባላቸው ቁርጠኝነት ስደት ደርሶባቸዋል። ይሁንና ይህን የሚያደርጉት ለሰዎች ጥቅም በማሰብ ነው። ደግሞም ምሥክሮቹ ያሳዩት ቅናትና ጽናት መልካም ስም አትርፎላቸዋል!

2. የይሖዋ ምሥክሮች በቅንዓት እንዲሰብኩ የሚያነሳሳቸው አንዱ ምክንያት ምንድን ነው?

2 በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያሳዩት ቅንዓት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ካሳዩት ቅንዓት አይለይም። እነሱን አስመልክቶ ሎሰርቫቶሬ ሮማኖ የተባለው የሮማ ካቶሊክ ጋዜጣ እንዲህ ሲል በትክክል ተናግሯል:- “የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ከተጠመቁበት ጊዜ አንስቶ ወንጌሉን የማዳረስ ግዴታ እንዳለባቸው ይሰማቸው ነበር። ባሮች ወንጌሉን በቃል ያስተላልፉ ነበር።” የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች በቅንዓት የሚሰብኩት ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ የሚያውጁት ምሥራች ከራሱ ከይሖዋ አምላክ የመጣ በመሆኑ ነው። በቅንዓት ለመስበክ የሚያነሳሳ ከዚህ የበለጠ ምክንያት ሊኖር ይችላል? ስብከታቸው “እግዚአብሔርን አመስግኑ ስሙንም ባርኩ፣ ዕለት ዕለትም ማዳኑን አውሩ” ለሚሉት የመዝሙራዊው ቃላት ምላሽ ነው።​—⁠መዝሙር 96:​2

3. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች በቅንዓት እንዲሰብኩ የሚያነሳሳቸው ሁለተኛ ምክንያት ምንድን ነው? (ለ) ‘[አምላክ] የሚሰጠው መዳን’ ምንን ያካትታል?

3 የመዝሙራዊው ቃላት የይሖዋ ምሥክሮች በቅንዓት የሚሰብኩበትን ሁለተኛ ምክንያት ያስታውሱናል። መልእክታቸው መዳንን የሚያስገኝ ነው። አንዳንድ ግለሰቦች የሰዎችን ሕይወት ለማሻሻል በሕክምና፣ በማኅበራዊ ኑሮ፣ በኢኮኖሚ ወይም በሌሎች መስኮች ተሰማርተው ይሠራሉ፤ ደግሞም ጥረታቸው የሚያስመሰግን ነው። ሆኖም አንድ ሰው ለሌላው ማድረግ የሚችለው ማንኛውም ነገር ቢሆን ‘[አምላክ] ከሚሰጠው መዳን’ ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ አይባልም። ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ታዛዥ ሰዎችን ከኃጢአት፣ ከበሽታና ከሞት ያድናል። በዚህ ዝግጅት የሚጠቀሙ ሰዎች ለዘላለም ይኖራሉ! (ዮሐንስ 3:​16, 36፤ ራእይ 21:​3, 4) ዛሬ ክርስቲያኖች “ክብሩን በሕዝቦች መካከል፣ ድንቅ ሥራውንም በሰዎች ሁሉ ፊት ተናገሩ። እግዚአብሔር ታላቅ ነውና፤ ውዳሴም የሚገባው ነው፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ ሊፈራ ይገባዋል” ለሚሉት ቃላት ምላሽ በመስጠት ከሚናገሩት ‘ድንቅ ሥራዎች’ መካከል ማዳኑ ይገኝበታል።​—⁠መዝሙር 96:​3, 4 አ.መ.ት

ጌታ የተወው ምሳሌ

4-6. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች በቅንዓት እንዲሰብኩ ያነሳሳቸው ሦስተኛ ምክንያት ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ቅንዓት ያሳየው እንዴት ነው?

4 የይሖዋ ምሥክሮች በቅንዓት እንዲሰብኩ የሚያነሳሳቸው ሦስተኛ ምክንያት አለ። የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ይከተላሉ። (1 ጴጥሮስ 2:​21) ፍጹም ሰው የሆነው ኢየሱስ ‘ለድሆች የምሥራች እንዲሰብክ’ የተሰጠውን ሥራ በሙሉ ልብ ተቀብሏል። (ኢሳይያስ 61:​1፤ ሉቃስ 4:​17-21) ከዚህ የተነሳ ወንጌላዊ ማለትም ምሥራች አብሳሪ ሆኗል። ‘የመንግሥቱን ወንጌል እየሰበከ’ በመላው ገሊላና ይሁዳ ዞሯል። (ማቴዎስ 4:​23) ደግሞም ብዙዎች ለምሥራቹ በጎ ምላሽ እንደሚሰጡ ስለተረዳ ደቀ መዛሙርቱን “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” ብሏቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 9:​37, 38

5 ኢየሱስ ከጸሎቱ ጋር በሚስማማ መንገድ ሌሎችም ወንጌላውያን እንዲሆኑ ሥልጠና ሰጥቷቸዋል። ከጊዜ በኋላ ሐዋርያቱ ራሳቸውን ችለው እንዲሰብኩ የላካቸው ሲሆን “ሄዳችሁም:- መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ” ብሏቸዋል። በወቅቱ የነበሩትን ማኅበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ መርሐ ግብሮች ቢነድፉ ይበልጥ ጠቃሚ ይሆን ነበር? ወይስ በጊዜው ተስፋፍቶ የሚገኘውን ሙስና ለመዋጋት ፖለቲካ ውስጥ መግባት ነበረባቸው? በጭራሽ። ከዚያ ይልቅ ኢየሱስ ተከታዮቹን “ሄዳችሁም . . . ስበኩ” ብሎ ሲነግራቸው ክርስቲያን ወንጌላውያን በሙሉ ሊከተሉት የሚገባውን መሥፈርት አስቀምጧል።​—⁠ማቴዎስ 10:​5-7

6 ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ቀረበች’ ብለው እንዲያውጁ ሌላ የደቀ መዛሙርት ቡድን ላከ። የወንጌላዊነት ጉዟቸውን ስኬታማነት ተመልሰው መጥተው ሪፖርት ሲያደርጉለት ኢየሱስ ከፍተኛ ደስታ ተሰማው። “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፣ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግናለሁ” ሲል ጸለየ። (ሉቃስ 10:​1, 8, 9, 21) ቀደም ሲል ዓሣ አጥማጆች፣ ገበሬዎችና በሌሎች መስኮች ተሠማርተው ጥረው ግረው ይኖሩ የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በብሔሩ ከነበሩት በጣም የተማሩ የሃይማኖት መሪዎች ጋር ሲነጻጸሩ እንደ ሕፃናት ነበሩ። ሆኖም ደቀ መዛሙርቱ ከሁሉ የላቀውን ምሥራች እንዲያውጁ ሥልጠና አግኝተዋል።

7. ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ተከታዮቹ በመጀመሪያ ምሥራቹን የሰበኩት ለእነማን ነበር?

7 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ተከታዮቹ የመዳንን ምሥራች ማወጃቸውን ቀጥለዋል። (ሥራ 2:​21, 38-40) በመጀመሪያ የሰበኩት ለእነማን ነበር? አምላክን ለማያውቁ አሕዛብ ነበርን? አይደለም። በመጀመሪያ የሰበኩት ከ1, 500 ለሚበልጡ ዓመታት ከይሖዋ ጋር ትውውቅ ለነበረው የእስራኤል ሕዝብ ነው። አስቀድሞም ይሖዋ በሚመለክበት አገር የመስበክ መብት ነበራቸው? አዎን፣ ነበራቸው። ኢየሱስ “በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” ሲል ነግሯቸው ነበር። (ሥራ 1:8) እንደ ሌላ ማንኛውም ብሔር ሁሉ የእስራኤል ብሔርም ምሥራቹን መስማት ያስፈልገው ነበር።

8. በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን የኢየሱስ ተከታዮች አርዓያ የሚከተሉት እንዴት ነው?

8 ዛሬም በተመሳሳይ የይሖዋ ምሥክሮች በመላው ምድር ይሰብካሉ። ዮሐንስ ከተመለከተው ‘በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ካለው’ መልአክ ጋር ይተባበራሉ። (ራእይ 14:6) በ2001፣ ብዙውን ጊዜ የክርስቲያን አገር እንደሆኑ ተደርገው የሚታዩትን አንዳንድ አገሮች ጨምሮ በ235 አገሮችና ክልሎች ውስጥ ሰብከዋል። የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሕዝበ ክርስትና ቀደም ሲል አብያተ ክርስቲያናት ባቋቋመችባቸው አገሮች ውስጥ መስበካቸው ስሕተት ነውን? አንዳንዶች ትክክል እንዳልሆነ ከመናገራቸውም በላይ እንዲህ ዓይነቱን የወንጌላዊነት ሥራ “በጎችን እንደ መዝረፍ” አድርገው ሊቆጥሩት ይችላሉ። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ በዘመኑ ለነበሩት ትሁት አይሁዳውያን ያሳየውን ስሜት አይዘነጉም። ምንም እንኳ አስቀድሞም የክህነት አገልግሎት ቢኖራቸውም ኢየሱስ ምሥራቹን ለእነሱ ከመናገር ወደኋላ አላለም። “እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።” (ማቴዎስ 9:36) የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ የማያውቁ ትሁት ሰዎች ሲያጋጥሟቸው የአንድ ሃይማኖት አባል ናቸው ስለተባለ ብቻ ምሥራቹን ከመስበክ መቆጠብ አለባቸው ማለት ነው? የኢየሱስ ሐዋርያትን ምሳሌ ስለምንከተል መልሳችን ከመስበክ ወደኋላ ማለት የለባቸውም የሚል ነው። እገሌ ከገሌ ሳይባል ምሥራቹ “ለአሕዛብ ሁሉ” መሰበክ አለበት።​—⁠ማርቆስ 13:​10

የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በሙሉ ወንጌላውያን ነበሩ

9. በመጀመሪያው መቶ ዘመን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከነበሩት በስብከቱ ሥራ የተካፈሉት እነማን ናቸው?

9 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በስብከቱ ሥራ የተካፈሉት እነማን ነበሩ? ሁሉም ክርስቲያኖች ወንጌላውያን እንደነበሩ ማስረጃዎቹ ያሳያሉ። ደራሲው ደብልዩ ኤስ ዊልያምስ እንዲህ ብለዋል:- “በጥቅሉ ማስረጃው እንደሚያሳየው በጥንቱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የታቀፉ ክርስቲያኖች በሙሉ . . . ወንጌሉን ሰብከዋል።” መጽሐፍ ቅዱስ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት የተፈጸመውን ነገር በተመለከተ እንዲህ ይላል:- “በሁሉም [ወንዶችም ሴቶችም] መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፣ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።” ወንጌላውያን ከሆኑት መካከል ወንዶችና ሴቶች፣ ወጣቶችና ሽማግሌዎች፣ ባሪያዎችና ነፃ ሰዎች ይገኙበታል። (ሥራ 1:​14፤ 2:​1, 4, 17, 18፤ ኢዩኤል 2:​28, 29፤ ገላትያ 3:​28) በርካታ ክርስቲያኖች በስደቱ የተነሳ ከኢየሩሳሌም ለመሸሽ ሲገደዱ ‘የተበተኑትም በሄዱበት ሁሉ የቃሉን ምሥራች ሰብከዋል።’ (ሥራ 8:4) የተሾሙ ጥቂት ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ “የተበተኑት” ሁሉ ወንጌሉን ሰብከዋል።

10. የአይሁድ ሥርዓት ከመደምሰሱ በፊት ፍጻሜ ያገኘው ድርብ ተልዕኮ ምን ነበር?

10 በእነዚያ የቀድሞዎቹ ዓመታት በሙሉ ሁኔታው ይህን የሚመስል ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናግሯል:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴዎስ 24:14) በእነዚህ ቃላት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ፍጻሜ መሠረት የሮማ ሠራዊት የአይሁድን ሃይማኖታዊና ፓለቲካዊ ሥርዓት ከመደምሰሱ በፊት ምሥራቹ በሰፊው ተሰብኮ ነበር። (ቆላስይስ 1:​23) በተጨማሪም የኢየሱስ ተከታዮች በሙሉ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል የሰጠውን ትእዛዝ ፈጽመዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች፣ እሺ ባይ ሰዎች ሲያጋጥሟቸው በኢየሱስ እንዲያምኑ ከነገሯቸው በኋላ አንዳንድ ዘመናዊ ሰባኪያን እንደሚያደርጉት ያለ መመሪያ አምላክን በራሳቸው መንገድ እንዲያገለግሉ አልተዉአቸውም። ከዚህ ይልቅ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ አስተምረዋቸዋል፣ በጉባኤ መልክ አደራጅተዋቸዋል፤ እንዲሁም እነሱም ምሥራቹን ሰብከው ደቀ መዛሙርት ማፍራት እንዲችሉ አሠልጥነዋቸዋል። (ሥራ 14:​21-23) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮችም ይህን አሠራር ይከተላሉ።

11. በዛሬው ጊዜ ለሰው ልጆች ከሁሉ የተሻለውን ምሥራች በማወጁ ሥራ የሚካፈሉት እነማን ናቸው?

11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጳውሎስ፣ በርናባስና ሌሎች የተዉትን ምሳሌ በመከተል በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ሚስዮናውያን ሆነው ወደ ባዕድ አገሮች ሄደዋል። በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ስላልገቡ ወይም በሌሎች ጉዳዮች ውስጥ ገብተው ምሥራቹን እንዲሰብኩ ከተሰጣቸው ተልዕኮ ስላልወጡ ያከናወኑት ሥራ በእርግጥ ጠቃሚ ነበር። ኢየሱስ “ሄዳችሁም . . . ስበኩ” ሲል ከሰጣቸው መመሪያ ንቅንቅ አላሉም። ሆኖም አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች በባዕድ አገር በሚስዮናዊነት በማገልገል ላይ አይደሉም። ብዙዎቹ መተዳደሪያ ለማግኘት ተቀጥረው ሰብዓዊ ሥራ የሚሠሩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ገና በትምህርት ዓለም ላይ ናቸው። አንዳንዶች የሚያሳድጓቸው ልጆች አሏቸው። ሆኖም ሁሉም ምሥክሮች የሰሙትን ምሥራች ለሌሎች ያካፍላሉ። ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች መጽሐፍ ቅዱስ “ቃሉን ስበክ፣ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና” ሲል የሰጠውን ምክር በደስታ ይፈጽማሉ። (2 ጢሞቴዎስ 4:​2) የይሖዋ ምሥክሮች እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ቀደምት ምሳሌዎቻቸው ሁሉ “ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም።” (ሥራ 5:​42) ለሰው ልጆች ከሁሉ የተሻለውን ምሥራች ያውጃሉ።

ሃይማኖት ማስለወጥ ወይስ ወንጌል መስበክ?

12. ፕሮሲሊቲዝም የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ትርጉሙ ምንድን ነው? ከቅርብ ጊዜ ወዲህስ ምን መልእክት የሚያስተላልፍ እየሆነ መጥቷል?

12 በግሪክኛ ቋንቋ “ሃይማኖቱን የለወጠ” የሚል ትርጉም ያለው ፕሮሲሊቶስ የተባለ ቃል አለ። “ፕሮሲሊቲዝም” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተገኘው ከዚህ ቃል ሲሆን መሠረታዊ ትርጉሙም “ሃይማኖትን ማስለወጥ” ማለት ነው። በአሁኑ ጊዜ አንዳንዶች፣ ሃይማኖትን ማስለወጥ ጉዳት እንዳለው ይናገራሉ። አልፎ ተርፎም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ያሳተመው አንድ ሰነድ “ሃይማኖትን ማስለወጥ ኃጢአት” እንደሆነ ይናገራል። ለምን? ካቶሊክ ዎርልድ ሪፖርት የተባለው መጽሔት እንዲህ ይላል:- “የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ በምታሰማው ምሬት የተነሳ ‘ፕሮሲሊቲዝም’ የሚለው ቃል ሃይማኖትን በኃይል ማስለወጥ የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ እየሆነ መጥቷል።”

13. ሃይማኖትን ማስለወጥ ጎጂ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎች ምንድን ናቸው?

13 የአንድን ሰው ሃይማኖት ማስለወጥ ጉዳት አለው? ሊኖረው ይችላል። ኢየሱስ ጻፎችና ፈሪሳውያን የሚያካሂዱት ሃይማኖትን የማስለወጥ ተግባር ሃይማኖታቸውን በለወጡት ሰዎች ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል ተናግሯል። (ማቴዎስ 23:​15) “ሃይማኖትን በኃይል ማስለወጥ” ትክክል አለመሆኑ ግልጽ ነው። ለምሳሌ ያህል ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ እንዳለው ከሆነ መቃባዊው ጆን ሂርካነስ ኤዶማውያንን በቁጥጥሩ ሥር ካዋለ በኋላ “እስከተገረዙና የአይሁዳውያንን ሕጎች ለመጠበቅ ፈቃደኛ እስከሆኑ ድረስ እዚያው በአገራቸው እንዲቀመጡ ፈቅዶላቸዋል።” ኤዶማውያን በአይሁዳውያን አገዛዝ ሥር ለመኖር ከመረጡ የአይሁዳውያንን ሃይማኖት መቀበል ነበረባቸው። በስምንተኛው መቶ ዘመን እዘአ ሻርለማኝ በሰሜናዊ አውሮፓ የሚኖሩትን አረማዊ ሳክሰኖች ከተቆጣጠረ በኋላ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ሃይማኖታቸውን በኃይል እንዳስለወጣቸው ታሪክ ጸሐፊዎች ይናገራሉ። a ይሁንና ሳክሰኖችና ኤዶማውያን ያደረጉት የሃይማኖት ለውጥ ምን ያህል ልባዊ ነበር? ለምሳሌ ያህል ሕፃኑን ኢየሱስን ለማስገደል ሙከራ ያደረገው ኤዶማዊው ንጉሥ ሄሮድስ በመለኮታዊ አነሳሽነት ለተጻፈው ለሙሴ ሕግ ምን ያህል ከልብ ይታዘዝ ነበር?​—⁠ማቴዎስ 2:​1-18

14. አንዳንድ የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንዲለውጡ ጫና የሚያሳድሩት እንዴት ነው?

14 በዛሬው ጊዜ ሃይማኖትን በኃይል የማስለወጥ ተግባር አለ? በአንዳንድ ሁኔታዎች አለ ማለት ያስደፍራል። አንዳንድ የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን ሃይማኖታቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች የውጭ አገር የነፃ ትምህርት ዕድል እንደሚሰጡ ይነገራል። ወይም አንድ የተራበ ስደተኛ የራሽን ምግብ ለማግኘት ቁጭ ብሎ ስብከት እንዲያዳምጥ ያደርጉ ይሆናል። በ1992 የኦርቶዶክስ ጳጳሳት ጉባኤ ያወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ከሆነ “ሃይማኖትን የማስለወጥ ተግባር አንዳንድ ጊዜ ቁሳዊ መደለያዎችን በመስጠት፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የተለያየ ዓይነት የኃይል ድርጊት በመጠቀም ይፈጸማል።”

15. የይሖዋ ምሥክሮች የሰዎችን ሃይማኖት በግድ ያስለውጣሉን? አብራራ።

15 ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንዲለውጡ ማስገደድ ትክክል አይደለም። የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንዲለውጡ በፍጹም አያስገድዱም። b በመሆኑም ፕሮሲሊታይዝ የሚለው ቃል በያዘው ዘመናዊ ትርጉም መሠረት የሰዎችን ሃይማኖት አያስለውጡም። ከዚህ ይልቅ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ምሥራቹን ለሰዎች ሁሉ ይሰብካሉ። ለምሥራቹ በፈቃደኝነት ምላሽ የሚሰጥ ማንኛውም ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት ተጨማሪ እውቀት እንዲያገኝ ግብዣ ይቀርብለታል። ፍላጎት ያሳዩ እንዲህ ዓይነት ሰዎች በትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ላይ በጥብቅ ተመሥርተው በአምላክና በዓላማዎቹ ላይ እምነት ማሳደር ይማራሉ። ከዚህም የተነሳ ለመዳን ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም ይጠራሉ። (ሮሜ 10:​13, 14, 17) ምሥራቹን መቀበል አለመቀበል የግል ምርጫቸው ነው። ማስገደድ የሚባል ነገር የለም። እንደዚህ ያለ ነገር ቢኖር ኖሮ ሃይማኖትን መለወጥ ትርጉም የለሽ ይሆን ነበር። አምልኮታችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ከልብ የመነጨ መሆን ይኖርበታል።​—⁠ዘዳግም 6:​4, 5፤ 10:​12

በዚህ ዘመን እየተካሄደ ያለው የወንጌላዊነት ሥራ

16. በዚህ ዘመን የይሖዋ ምሥክሮች የወንጌላዊነት ሥራ ምን እድገት አሳይቷል?

16 በዚህ ዘመን ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ማቴዎስ 24:​14 ታላቅ ፍጻሜውን እንዲያገኝ በሚያስችል ሁኔታ ምሥራቹን ሰብከዋል። በዚህ የወንጌላዊነት ሥራቸው የሚጠቀሙበት ዋነኛ መሣሪያ መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ነው። c በ1879 የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ እትም ሲወጣ የመጽሔቱ ስርጭት በአንድ ቋንቋ ወደ 6, 000 ገደማ ነበር። በ2001 ከ122 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ስርጭቱ በ141 ቋንቋዎች 23,042,000 ቅጂዎች ላይ ደርሷል። ከዚህ ጭማሪ ጋር ተያይዞ የይሖዋ ምሥክሮች የወንጌላዊነት እንቅስቃሴ እድገት ሲያሳይ ቆይቷል። በ19ኛው መቶ ዘመን በየዓመቱ ለወንጌላዊነቱ ሥራ ይውል የነበረውን በጥቂት ሺዎች የሚቆጠር ሰዓት በ2001 በስብከቱ ሥራ ላይ ከዋለው 1,169,082,225 ሰዓት ጋር አነጻጽር። በየወሩ በአማካይ የተመሩትን 4, 921, 702 በነፃ የተካሄዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ተመልከት። እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ድንቅ ሥራ ተከናውኗል! በሥራው የተሳተፉት 6,117,666 ገደማ የሚሆኑ ንቁ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ነበሩ።

17. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ምን ዓይነት የሐሰት አማልክት ይመለካሉ? (ለ) ማንኛውም ሰው ቋንቋው፣ ዜግነቱ ወይም ማኅበራዊ ደረጃው ምንም ዓይነት ይሁን ምን ማወቅ የሚኖርበት ነገር ምንድን ነው?

17 መዝሙራዊው እንዲህ ይላል:- “የሕዝብ አማልክት ሁሉ ጣዖታት ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።” (መዝሙር 96:5 አ.መ.ት) ከሃይማኖት በራቀው በዛሬው ዓለም ውስጥ ብሔራዊ ስሜት፣ ብሔራዊ አርማዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ቁሳዊ ነገሮች፣ አልፎ ተርፎም ሀብት የሚመለኩ ነገሮች ሆነዋል። (ማቴዎስ 6:​24፤ ኤፌሶን 5:​5፤ ቆላስይስ 3:​5) ሞሃንዳስ ኬ ጋንዲ በአንድ ወቅት እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “ዛሬ አውሮፓ የክርስቲያን አገር ተብላ የምትጠራው እንዲያው ለስሙ ብቻ . . . እንደሆነ በጽኑ አምናለሁ። አውሮፓ በእርግጥ የምታመልከው ገንዘብን [ሀብትን] ነው።” ምሥራቹ በማንኛውም ቦታ መሰበክ ያለበት መሆኑ ሐቅ ነው። እያንዳንዱ ሰው ቋንቋው፣ ዜግነቱ ወይም ማኅበራዊ ደረጃው ምንም ዓይነት ይሁን ምን ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ማወቅ ይኖርበታል። ሁሉም ሰው ለሚከተሉት የመዝሙራዊው ቃላት ምላሽ እንዲሰጥ እንመኛለን:- “ክብርንና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ፤ ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር አምጡ”! (መዝሙር 96:​7, 8) የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎች በአግባቡ ለይሖዋ ክብር ማምጣት እንዲችሉ ስለ እሱ እንዲማሩ ይረዷቸዋል። በጎ ምላሽ የሚሰጡት ደግሞ ከፍተኛ ጥቅም ያገኛሉ። ጥቅሞቹ ምንድን ናቸው? ይህ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ እንዳለው ከሆነ በተሃድሶ ዘመን ሕዝቡ አንድን ሃይማኖት በኃይል እንዲቀበል የሚደረግበትን ሁኔታ ለመግለጽ “የአገሪቱ ሃይማኖት የሚወሰነው በገዢው ነው” የሚል ትርጉም ያለው አንድ የላቲን መርሕ ነበር።

b የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የሃይማኖታዊ ነፃነት ኮሚሽን ኅዳር 16, 2000 ባደረገው ስብሰባ ላይ አንድ ተሳታፊ ሃይማኖትን በኃይል ለማስለወጥ በሚጥሩ ቡድኖችና የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት የስብከት እንቅስቃሴ መካከል ልዩነት መኖሩን ገልጸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ለሌሎች በሚሰብኩበት ጊዜ አንድ ሰው “ፍላጎት የለኝም” ብሎ በሩን ከዘጋ ከዚያ በላይ አልፈው እንደማይሄዱ ተጠቅሷል።

c የመጽሔቱ ሙሉ ስም የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ ነው።

ልታብራራ ትችላለህ?

• የይሖዋ ምሥክሮች ቀናተኛ ወንጌላውያን የሆኑት ለምንድን ነው?

• የይሖዋ ምሥክሮች ሕዝበ ክርስትና ቤተ ክርስቲያኖች ባቋቋመችባቸው አገሮች ሳይቀር የሚሰብኩት ለምንድን ነው?

• ቃሉ ዛሬ ካለው ትርጉም አንጻር የይሖዋ ምሥክሮች ፕሮሲሊታይዘርስ ሊባሉ የማይችሉት ለምንድን ነው?

• በዚህ ዘመን የይሖዋ ምሥክሮች የወንጌላዊነት ሥራ እድገት ያሳየው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ቀናተኛ ወንጌላዊ የነበረ ሲሆን ሌሎችም ይህንኑ ሥራ እንዲሠሩ አሠልጥኗቸዋል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው ጉባኤ የሚገኙ ሁሉ በወንጌላዊነቱ ሥራ ተካፍለዋል

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንዲለውጡ ማስገደድ ትክክል አይደለም