በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምሥራቹ የሚያስገኛቸው በረከቶች

ምሥራቹ የሚያስገኛቸው በረከቶች

ምሥራቹ የሚያስገኛቸው በረከቶች

“ለድሆች [“ለየዋሆች፣” NW ] የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፣ . . . የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽናና ዘንድ።”ኢሳይያስ 61:​1, 2

1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ማንነቱን በተመለከተ ምን ብሏል? እንደዚያ የሆነውስ በምን መንገድ ነው? (ለ) ኢየሱስ ያወጀው ምሥራች ምን በረከቶች አስገኝቷል?

 ኢየሱስ በአገልግሎቱ መጀመሪያ በአንድ የሰንበት ቀን ናዝሬት በሚገኝ ምኩራብ ውስጥ ነበር። ዘገባው እንደሚገልጸው “የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፣ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ:- የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፣ . . . ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና . . . ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ።” ኢየሱስ ተጨማሪ የትንቢቱን ክፍል ማንበቡን ቀጠለ። ከዚያም ተቀምጦ “ይህ በጆሮአችሁ የሰማችሁት የመጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” (አ.መ.ት ) አላቸው።​—⁠ሉቃስ 4:​16-21

2 በዚህ መንገድ ኢየሱስ ትንቢት የተነገረለት ወንጌላዊ፣ ምሥራች አብሳሪና የመጽናኛ ምንጭ እሱ መሆኑን አሳወቀ። (ማቴዎስ 4:​23) ኢየሱስ የተናገረው መልእክት በእርግጥም ምሥራች ነው! ለአድማጮቹ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ሲል ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 8:​12) በተጨማሪም “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 8:​31, 32) አዎን፣ ኢየሱስ “የዘላለም ሕይወት ቃል” ነበረው። (ዮሐንስ 6:​68, 69) ብርሃን፣ ሕይወትና ነፃነት በእርግጥ እንደ ውድ ሀብት የሚታዩ በረከቶች ናቸው!

3. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን ምሥራች ሰብከዋል?

3 በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የጀመረውን የወንጌላዊነት ሥራ ቀጥለዋል። ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ ለእስራኤላውያንም ሆነ ለአሕዛብ ሰብከዋል። (ማቴዎስ 24:​14፤ ሥራ 15:​7፤ ሮሜ 1:​16) ወንጌሉን የተቀበሉ ሰዎች ይሖዋ አምላክን ማወቅ ችለዋል። ከሃይማኖታዊ ባርነት ተላቅቀው ጌታቸው ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማይ ለዘላለም የመግዛት ተስፋ ያላቸው የአዲሱ መንፈሳዊ ብሔር ክፍል ማለትም ‘የእግዚአብሔር እስራኤል’ አባላት ሆነዋል። (ገላትያ 5:​1፤ 6:​16፤ ኤፌሶን 3:​5-7፤ ቆላስይስ 1:​4, 5፤ ራእይ 22:​5) በእርግጥም እነዚህ ውድ በረከቶች ናቸው!

ወንጌላዊነት በዛሬው ጊዜ

4. ምሥራቹን የመስበኩ ተልእኮ በዛሬው ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?

4 በዛሬው ጊዜ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የ“ሌሎች በጎች” ክፍል በሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” እየታገዙ በመጀመሪያ ለኢየሱስ ተሰጥቶት የነበረውን ትንቢታዊ ተልእኮ በመፈጸም ላይ ናቸው። (ራእይ 7:​9፤ ዮሐንስ 10:​16) በመሆኑም ምሥራቹ ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ መጠን በመሰበክ ላይ ይገኛል። በ235 አገሮችና ክልሎች የይሖዋ ምሥክሮች ‘ለድሆች የምሥራችን ለመስበክ፣ ልባቸው የተሰበረውን ለመጠገን፣ ለተማረኩትም ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን ለመናገር፣ የተወደደችውን የእግዚአብሔርን ዓመት አምላካቸውም የሚበቀልበትን ቀን ለመናገር፣ የሚያለቅሱትንም ሁሉ ለማጽናናት’ ጥረት አድርገዋል። (ኢሳይያስ 61:​1, 2) በመሆኑም ክርስቲያናዊው የወንጌላዊነት ሥራ ለብዙዎች በረከት እንዲሁም ‘በመከራ ሁሉ ላሉት’ እውነተኛ መጽናናት እያስገኘ ነው።​—⁠2 ቆሮንቶስ 1:​3, 4

5. ምሥራቹን በመስበክ ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች ከሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት የሚለዩት እንዴት ነው?

5 እርግጥ ነው የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት የተለያዩ የወንጌላዊነት ዘዴዎችን እንደሚጠቀሙ ይታወቃል። አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ሃይማኖታቸውን የሚቀበሉ ሰዎች ለማፍራት ወደ ሌሎች አገሮች ሚስዮናውያን ይልካሉ። ለምሳሌ ያህል ዚ ኦርቶዶክስ ክርስቺያን ሚሽን ሴንተር ማጋዚን የኦርቶዶክስ ሚስዮናውያን በአፍሪካ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው በማዳጋስካር፣ በታንዛኒያና በዚምባብዌ እያደረጉ ስላሉት እንቅስቃሴ ዘግቧል። ይሁን እንጂ በሌሎቹ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት እንደሚታየው ሁሉ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም አብዛኞቹ ምዕመናን በወንጌላዊነቱ ሥራ አይሳተፉም። በአንጻሩ ደግሞ ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ በወንጌላዊነቱ ሥራ ለመሳተፍ ጥረት ያደርጋሉ። ምሥራቹን ማወጅ እውነተኛ እምነት እንዳላቸው የሚያሳይ ማስረጃ እንደሆነ ይገነዘባሉ። ጳውሎስ “ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና” ሲል ተናግሯል። ለተግባር የማያነሳሳ እምነት የሞተ ነው ሊባል ይችላል።​—⁠ሮሜ 10:​10፤ ያዕቆብ 2:​17

ዘላለማዊ በረከቶች የሚያስገኝ ምሥራች

6. በዛሬው ጊዜ እየተሰበከ ያለው ምሥራች ምንድን ነው?

6 የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰብኩት ምሥራች አቻ የለውም። ኢየሱስ የሰው ልጆች ወደ አምላክ መቅረብ የሚችሉበትን መንገድ ለመክፈት፣ የኃጢአት ይቅርታ ለማስገኘትና የዘላለም ሕይወት ተስፋ ለመዘርጋት ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ መክፈሉን መልእክቱን ለሚቀበሉ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ እየገለጡ ያሳያሉ። (ዮሐንስ 3:​16፤ 2 ቆሮንቶስ 5:​18, 19) የአምላክ መንግሥት በተቀባው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር በሰማይ መቋቋሙንና በቅርቡ ከምድር ላይ ክፋትን አስወግዶ ምድር ተመልሳ ገነት እንድትሆን ሥራውን በበላይነት እንደሚቆጣጠር ያውጃሉ። (ራእይ 11:​15፤ 21:​3, 4) በኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት የሰው ዘር ለምሥራቹ ምላሽ መስጠት የሚችልበት ‘የተወደደው የእግዚአብሔር ዓመት’ አሁን መሆኑን ለጎረቤቶቻቸው ያሳውቃሉ። በተጨማሪም ይሖዋ ከአካሄዳቸው የማይመለሱ ክፉ አድራጊዎችን በማጥፋት ‘አምላካችን የሚበቀልበት ቀን’ በቅርቡ እንደሚመጣ ያስጠነቅቃሉ።​—⁠መዝሙር 37:​9-11

7. የይሖዋ ምሥክሮች አንድነት እንዳላቸው የሚያሳየው ተሞክሮ የትኛው ነው? ይህን የመሰለ አንድነት ሊያገኙ የቻሉትስ እንዴት ነው?

7 በመከራና በእልቂት በተሞላ ዓለም ውስጥ ዘላለማዊ በረከት የሚያስገኘው ምሥራች ይህ ብቻ ነው። ምሥራቹን የሚቀበሉ ሰዎች በብሔር፣ በጎሳ ወይም በኢኮኖሚ ልዩነቶች የማይከፋፈለውና አንድነት ያለው ዓለም አቀፍ የክርስቲያኖች ወንድማማች ማኅበር ክፍል ይሆናሉ። ‘ፍጹም የአንድነት ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ለብሰዋል።’ (ቆላስይስ 3:​14 NW ፤ ዮሐንስ 15:​12) ይህ ሁኔታ ባለፈው ዓመት በአንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ ታይቷል። አንድ ቀን ማለዳ ዋና ከተማዋ በተኩስ እሩምታ ተናወጠች። የመንግሥት ግልበጣ ለማድረግ እየተሞከረ ነበር። ሁኔታው መልኩን ቀይሮ ወደ ጎሳ ግጭት ሲለወጥ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ የሌላ ጎሳ አባላት የሆኑ የእምነት ጓደኞቻቸውን በማስጠለላቸው ከባድ ውግዘት ደረሰባቸው። ቤተሰቡ “እኛ ቤት የመጡት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው” ሲል መልስ ሰጠ። እነሱ ትኩረት ያደረጉት በጎሳ ልዩነት ላይ ሳይሆን ለተቸገሩት መጽናኛ እንዲሰጡ በሚያነሳሳቸው በክርስቲያናዊው ፍቅር ላይ ነበር። የይሖዋ ምሥክር ያልሆነች አንዲት ዘመዳቸው “የሌሎች ሃይማኖቶች አባላት የእምነት ጓደኞቻቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል። እንዲህ ያላደረጉት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው” ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች። በእርስ በርስ ግጭት ከሚታመሱ አገሮች ሪፖርት የተደረጉ በርካታ ተመሳሳይ ክስተቶች የይሖዋ ምሥክሮች በእርግጥ “ለመላው የወንድማማቾች ማኅበር ፍቅር” እንዳላቸው ያሳያሉ።​—⁠1 ጴጥሮስ 2:​17 NW

ምሥራቹ ሰዎችን ይለውጣል

8, 9. (ሀ) ምሥራቹን የተቀበሉ ሰዎች ምን ዓይነት ለውጥ ያደርጋሉ? (ለ) ምሥራቹ ያለውን ኃይል የሚያሳዩት የትኞቹ ተሞክሮዎች ናቸው?

8 ጳውሎስ “የአሁንና የሚመጣው ሕይወት” ሲል የገለጸው ጉዳይ ከምሥራቹ ጋር ዝምድና አለው። (1 ጢሞቴዎስ 4:​8) ምሥራቹ ስለ ወደፊቱ ጊዜ እርግጠኛ የሆነ ብሩህ ተስፋ መፈንጠቅ ብቻ ሳይሆን ‘የአሁኑ ሕይወታችንም’ እንዲሻሻል ያደርጋል። የይሖዋ ምሥክሮች በግለሰብ ደረጃ ሕይወታቸውን ከአምላክ ፈቃድ ጋር ለማስማማት በአምላክ ቃል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ይመራሉ። (መዝሙር 119:​101) እንደ ጽድቅና ታማኝነት የመሳሰሉትን ባሕርያት ሲያፈሩ ስብዕናቸው ጭምር ይታደሳል።​—⁠ኤፌሶን 4:​24

9 ቁጣውን የመቆጣጠር ችግር የነበረበትን የፍራንኮን ምሳሌ ተመልከት። አንድ ነገር እሱ ባሰበው መንገድ ሳይሆን ከቀረ በቁጣ ገንፍሎ ዕቃ ይሰባብራል። ሚስቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ታጠና ስለነበረ ክርስቲያናዊ ምሳሌነታቸው ውሎ አድሮ ፍራንኮ ለውጥ ማድረግ እንዳለበት እንዲገነዘብ አስቻለው። ከእነሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ አጠና፤ በመጨረሻም የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች የሆኑትን ሰላምንና ራስ መግዛትን ማፍራት ቻለ። (ገላትያ 5:​22, 23) ፍራንኮ በ2001 የአገልግሎት ዓመት በቤልጂየም ከተጠመቁት 492 ሰዎች መካከል አንዱ ነው። የአሌሃንድሮንም ሁኔታ ተመልከት። ይህ ወጣት የአደገኛ ዕፅ ሱሰኛ ከመሆኑ የተነሳ ሱሱን ማርካት የሚችልበትን ገንዘብ ለማግኘት በቆሻሻ መጣያ ቦታ የሚያገኛቸውን ዕቃዎች እየሸጠ ይኖር ነበር። አሌሃንድሮ 22 ዓመት ሲሆነው የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና ግብዣ ያቀረቡለት ሲሆን እሱም ግብዣውን ተቀበለ። በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ። በሕይወቱ ላይ ፈጣን ለውጥ በማድረጉ ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በወንጌላዊነቱ ሥራ መሳተፍ የቻለ ሲሆን ባለፈው ዓመት በፓናማ ከነበሩት 10, 115 ወንጌላውያን መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል።

ምሥራቹ ለየዋሆች በረከት ያመጣል

10. ምሥራቹን የሚቀበሉት እነማን ናቸው? አመለካከታቸው የሚቀየረውስ እንዴት ነው?

10 ኢሳይያስ ምሥራቹ የዋህ ለሆኑት እንደሚሰበክ ተንብዮ ነበር። የዋሆች የተባሉት እነማን ናቸው? በሥራ መጽሐፍ ላይ “ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ” ተብለው የተገለጹት ሰዎች ናቸው። (ሥራ 13:​48) በየትኛውም የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የእውነትን መልእክት የሚቀበሉ ትሑት ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ዓለም ሊያስገኝ ከሚችለው ከማንኛውም ነገር እጅግ የላቀ በረከት እንደሚያስገኝ ተገንዝበዋል። (1 ዮሐንስ 2:​15-17) ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች በወንጌላዊነት ሥራቸው የሰዎችን ልብ መንካት የሚችሉት እንዴት ነው?

11. ጳውሎስ እንዳለው ከሆነ ምሥራቹ መሰበክ ያለበት እንዴት ነው?

11 ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “እኔም፣ ወንድሞች ሆይ፣ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም። በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደ ተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቈርጬ ነበርና” ሲል የጻፈውን የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ እስቲ ተመልከት። (1 ቆሮንቶስ 2:​1, 2) ጳውሎስ ባለው እውቀት አድማጮቹን ለማስደመም አልሞከረም። ዛሬ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግበው ከሚገኙት መለኮታዊ ማረጋገጫ ካላቸው እውነቶች በስተቀር ሌላ ነገር አላስተማረም። በተጨማሪም ጳውሎስ አብሮት ወንጌላዊ ለሆነው ለጢሞቴዎስ “በጥድፊያ ስሜት ቃሉን ስበክ” ሲል የሰጠውን ማበረታቻም ልብ በል። (2 ጢሞቴዎስ 4:​2 NW ) ጢሞቴዎስ “ቃሉን” ማለትም የአምላክን መልእክት መስበክ ነበረበት። እንዲሁም ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፣ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ” ሲል ጽፎለታል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 2:15

12. በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የጳውሎስን ቃልና ምሳሌ የሚከተሉት እንዴት ነው?

12 የይሖዋ ምሥክሮች የጳውሎስን ምሳሌ እንዲሁም ለጢሞቴዎስ የጻፈለትን ምክር ይከተላሉ። የአምላክ ቃል ኃይል እንዳለው የሚገነዘቡ ከመሆኑም በላይ ከቃሉ ተስማሚ የሆኑ ተስፋና ማጽናኛ የያዙ ቃላትን ለጎረቤቶቻቸው በመጥቀስ በጥሩ ሁኔታ ይጠቀሙበታል። (መዝሙር 119:​52፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17፤ ዕብራውያን 4:​12) እርግጥ ነው፣ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በትርፍ ጊዜያቸው ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማግኘት እንዲችሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎቻቸው በሚገባ ይጠቀማሉ። ሆኖም ምንጊዜም ለሰዎች ከቅዱስ ጽሑፉ ጠቅሰው ማሳየት ይፈልጋሉ። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል የትሑት ሰዎችን ልብ ሊያነሳሳ እንደሚችል ያውቃሉ። በዚህ መንገድ በቅዱስ ጽሑፉ መጠቀማቸው የራሳቸውንም እምነት ያጠናክርላቸዋል።

‘የሚያለቅሱትን ሁሉ አጽናኑ’

13. በ2001፣ የሚያለቅሱትን ማጽናናት የሚጠይቅ ምን ሁኔታ ተከስቶ ነበር?

13 እንደ ሌሎቹ ዓመታት ሁሉ 2001ም እልቂት ያልተለየው ሲሆን በዚያም ሳቢያ ብዙ ሰዎች ማጽናኛ አስፈልጓቸው ነበር። ባለፈው መስከረም በዩናይትድ ስቴትስ፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የዓለም የንግድ ማዕከልና ዋሽንግተን ዲ ሲ አቅራቢያ ፔንታጎን ላይ የደረሰው የአሸባሪዎች ጥቃት ለዚህ ጉልህ ማስረጃ ይሆናል። እነዚህ ጥቃቶች ለመላ አገሪቱ አስደንጋጭ ክስተቶች ነበሩ! እንዲህ ዓይነት ክስተቶች ሲያጋጥሙ የይሖዋ ምሥክሮች ‘የሚያለቅሱትን ሁሉ የማጽናናት’ ተልዕኳቸውን ለመወጣት ይጥራሉ። ይህን የሚያደርጉበትን መንገድ የሚያሳዩ ጥቂት ተሞክሮዎች ቀርበዋል።

14, 15. የይሖዋ ምሥክሮች በሁለት የተለያዩ አጋጣሚዎች ላይ የሚያለቅሱትን ለማጽናናት ቅዱሳን ጽሑፎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም የቻሉት እንዴት ነው?

14 የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ የሆነች አንዲት ምሥክር የእግረኛ መንገድ ላይ ቆማ ወዳለች አንዲት ሴት ቀርባ በቅርቡ ስለተፈጸመው የአሸባሪዎች ጥቃት ምን እንደተሰማት ስትጠይቃት ሴትዮዋ ማልቀስ ጀመረች። ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማትና እርዳታ ማድረግ የምትችልበት መንገድ ቢኖር እንደምትደሰት ተናገረች። ምሥክሯ አምላክ ለሁላችንም ከልብ እንደሚያስብ ከነገረቻት በኋላ ኢሳይያስ 61:​1, 2ን አነበበችላት። ሴትዮዋ እነዚህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ቃላት አሳማኝ ስለሆኑላት ሰው ሁሉ በሐዘን እንደተደቆሰ ተናገረች። ትራክት የወሰደች ከመሆኑም በላይ ምሥክሯ ቤቷ መጥታ እንድታነጋግራት ጠየቀች።

15 በወንጌላዊነቱ ሥራ ተሰማርተው የነበሩ ሁለት ምሥክሮች ግቢው ውስጥ ሲሠራ የነበረ አንድ ሰው አገኙ። በቅርቡ በዓለም የንግድ ማዕከል ላይ የደረሰውን አሳዛኝ ክስተት በተመለከተ ከቅዱሳን ጽሑፎች የሚያጽናኑ ቃላት ለማሳየት ሐሳብ አቀረቡለት። ፈቃደኛነቱን ሲገልጽላቸው “መጽናናታችን . . . በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና” የሚሉት ቃላት የሚገኙበትን 2 ቆሮንቶስ 1:​3-7ን አነበቡለት። ሰውዬው ጎረቤቶቹ የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎችን የሚያጽናና ሐሳብ እያካፈሉ መሆናቸውን ያደነቀ ከመሆኑም በላይ “ይህን የሚደነቅ ሥራችሁን አምላክ ይባርከው” አላቸው።

16, 17. መጽሐፍ ቅዱስ በአሰቃቂ አደጋዎች ያዘኑ ወይም የተረበሹ ሰዎችን ሊያጽናና እንደሚችል የትኞቹ ሁለት ተሞክሮዎች ያሳያሉ?

16 ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ላይ የነበረ አንድ ምሥክር ከዚህ በፊት ፍላጎት አሳይታ የነበረችን የአንዲት ሴት ልጅ አግኝቶ ባነጋገረው ጊዜ በቅርቡ ከደረሰው አሳዛኝ አደጋ በኋላ የጎረቤቶቹ ሁኔታ ስላሳሰበው እንዴት እንደሆኑ ለመጠየቅ እንደመጣ ገለጸ። ምሥክሩ ጊዜውን ሠውቶ ጎረቤቶቹ እንዴት እንደሆኑ ለመጠየቅ መምጣቱ ሰውዬውን አስገረመው። ሰውዬው በአደጋው ወቅት በዓለም የንግድ ማዕከል አቅራቢያ ሲሠራ እንደነበረና ሁኔታውን በሙሉ እንደተመለከተ ተናገረ። ሰውዬው አምላክ በሰዎች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምን እንደሆነ ሲጠይቀው ምሥክሩ “የጻድቃን መድኃኒታቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ በመከራቸውም ጊዜ መጠጊያቸው እርሱ ነው” የሚለውን መዝሙር 37:​39ን ጨምሮ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ጥቅሶችን አነበበለት። ሰውዬው ምሥክሩና ቤተሰቡ እንዴት እንደሆኑ በደግነት ከጠየቀው በኋላ ተመልሶ እንዲመጣ ጋበዘው እንዲሁም መጥቶ ስላነጋገረው የተሰማውን ልባዊ አድናቆት ገለጸ።

17 የአሸባሪዎች ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ባሉት ቀናት ከይሖዋ ምሥክሮች ማጽናኛ ካገኙት በሺዎች የሚቆጠሩ የሚያለቅሱ ሰዎች አንዷ ምሥክሮቹ ጎረቤቶቻቸውን እየጠየቁ በነበረበት ወቅት ያገኟት ሴት ነች። በደረሰው እልቂት በጣም የተረበሸች ሲሆን ምሥክሮቹ “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፤ ስማቸው በፊቱ ክቡር ነው” የሚለውን መዝሙር 72:​12-14ን በሚያነቡበት ጊዜ በጥሞና አዳመጠች። እነዚህ ቃላት በእጅጉ አጽናኗት! ሴትዮዋ ምሥክሮቹ ጥቅሱን በድጋሚ እንዲያነቡላት የጠየቀች ከመሆኑም በላይ ውይይቱን ለመቀጠል ወደ ቤት እንዲገቡ ጋበዘቻቸው። ከዚህ ውይይት በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ።

18. አንድ ምሥክር ሌሎችን ወክሎ እንዲጸልይ የቀረበለትን ግብዣ በመጠቀም ሰዎችን የረዳው እንዴት ነው?

18 አንድ የይሖዋ ምሥክር የሚሠራበት ምግብ ቤት የሚገኘው ከዚህ ቀደም ለመንግሥቱ ምሥራች ያን ያህል ፍላጎት የማያሳዩ ባለጸጎች በሚኖሩበት ሠፈር ውስጥ ነው። ከዚህ የአሸባሪዎች ጥቃት በኋላ ነዋሪዎቹ በጣም ተረብሸው ነበር። ከጥቃቱ በኋላ በነበረው አርብ ቀን ምሽት የምግብ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ሁሉም ሰው ወደ ውጪ ወጥቶ ሻማ እንዲይዝና ለጥቃቱ ሰለባዎች የሕሊና ጸሎት እንዲያቀርብ ሐሳብ አቀረበች። ምሥክሩ ስሜታቸውን ላለመጉዳት ሲል ወደ ውጭ ወጥቶ የእግረኛ መንገዱ ላይ ጸጥ ብሎ ቆመ። ሥራ አስኪያጅዋ፣ ይህ ሰው የይሖዋ ምሥክር አገልጋይ መሆኑን ታውቅ ስለነበር የሕሊና ጸሎት አቅርበው እንዳበቁ ወንድም ሁሉንም ወክሎ እንዲጸልይ ጠየቀችው። ምሥክሩ በሐሳቡ ተስማማ። ባቀረበው ጸሎት ላይ ብዙዎች ሐዘን እንደደረሰባቸው ሆኖም ሐዘንተኞቹ ተስፋ ቢስ መሆን እንደሌለባቸው ጠቀሰ። እንዲህ ዓይነት በጣም አሰቃቂ ድርጊቶች ስለሚቀሩበት ጊዜ ከጠቀሰ በኋላ ሁሉም ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ በሚገኝ ትክክለኛ እውቀት አማካኝነት የመጽናናት ምንጭ ወደሆነው አምላክ መቅረብ እንዲችል ጸለየ። “አሜን” ካሉ በኋላ ሥራ አስኪያጅዋ ወደ ምሥክሩ ቀርባ አቅፋ ያመሰገነችው ሲሆን እስከ ዛሬ ድረስ እንዲህ ዓይነት ጸሎት ሰምታ እንደማታውቅ ገለጸችለት። ከምግብ ቤቱ ውጪ የነበሩ ከ60 በላይ የሚሆኑ ሰዎችም ምስጋናቸውን ገለጹለት።

በኅብረተሰቡ ላይ ያሳደረው በጎ ተጽዕኖ

19. አንዳንዶች የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃ የሚከተሉ መሆናቸውን እንደሚያስተውሉ የትኛው ተሞክሮ ያሳያል?

19 በተለይ በእነዚህ ቀናት የይሖዋ ምሥክሮች በሚሰብኩበት ኅብረተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የእነሱ መኖር እንደጠቀማቸው ብዙዎች ተናግረዋል። ደግሞስ ሰላምን፣ ሐቀኝነትንና ንጹህ ሥነ ምግባርን የሚያራምዱ ሰዎች እንዴት በጎ ተጽዕኖ አያሳድሩም? በአንድ የማዕከላዊ እስያ አገር የይሖዋ ምሥክሮች ከቀድሞው የብሔራዊ ደኅንነት ድርጅት በጡረታ ከተገለሉ አንድ መኮንን ጋር ተገናኙ። በአንድ ወቅት በተለያዩ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ላይ ጥናት እንዲያካሂዱ ተመድበው እንደነበር ተናገሩ። በይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖት ላይ ጥናት ሲያካሂዱ በሐቀኝነታቸውና በመልካም ምግባራቸው እንደተደነቁ ገልጸዋል። ጽኑ እምነታቸውና ትምህርታቸው በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ መሆኑ አድናቆት አሳድሮባቸው ነበር። እኚህ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፈቃደኛ ሆነዋል።

20. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች ያለፈው ዓመት እንቅስቃሴ ሪፖርት ምን ያሳያል? (ለ) ገና በጣም ብዙ የሚሠራ ሥራ እንዳለ የሚጠቁመው ምንድን ነው? የወንጌላዊነት መብታችንንስ እንዴት እንመለከተዋለን?

20 በሺዎች ከሚቆጠሩ ተሞክሮዎች መካከል እዚህ ርዕስ ላይ የቀረቡት ጥቂት ተሞክሮዎች የይሖዋ ምሥክሮች በ2001 የአገልግሎት ዓመት ብዙ እንደሠሩ በግልጽ ያሳያሉ። a በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን አነጋግረዋል፣ ሐዘን የደረሰባቸውን ብዙዎችን አጽናንተዋል እንዲሁም የወንጌላዊነት ሥራቸው መልካም ፍሬ አፍርቷል። ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን በጥምቀት ያሳዩ 263, 431 ሰዎች ነበሩ። በዓለም አቀፍ ደረጃ የወንጌላውያን ቁጥር 1.7 በመቶ ጨምሯል። እንዲሁም በዓመታዊው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ 15,374,986 ሰዎች መገኘታቸው ገና በጣም ብዙ የሚሠራ ሥራ እንዳለ ይጠቁማል። (1 ቆሮንቶስ 11:​23-26) ለምሥራቹ ምላሽ የሚሰጡ የዋሆችን መፈለጋችንን እንቀጥል። እንዲሁም የተወደደው የይሖዋ ዓመት እስኪያበቃ ድረስ “ልባቸው የተሰበረውን” ማጽናናታችንን እንቀጥል። ምንኛ አርኪ የሆነ ሥራ አለን! በእርግጥም ሁላችንም “በእግዚአብሔር እጅግ ደስ ይለኛል፣ ነፍሴም በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች” የሚሉትን የኢሳይያስ ቃላት እናስተጋባለን። (ኢሳይያስ 61:​10) አምላክ “ጌታ እግዚአብሔር ጽድቅንና ምስጋናን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ያበቅላል” የሚሉት ትንቢታዊ ቃላት ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ሲያደርግ በእኛ መጠቀሙን እንዲቀጥል ምኞታችን ነው።​—⁠ኢሳይያስ 61:11

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ከገጽ 19 እስከ 22 ላይ ያለው ሰንጠረዥ የይሖዋ ምሥክሮችን የ2001 የአገልግሎት ዓመት እንቅስቃሴ ሪፖርት ይዟል።

ታስታውሳለህን?

• የዋህ የሆኑ ሰዎች ኢየሱስ በሰበከው ወንጌል የተጠቀሙት እንዴት ነው?

• በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላከናወኑት የወንጌላዊነት ሥራ ምላሽ የሰጡ ሰዎች ምን በረከቶች አግኝተዋል?

• በዛሬው ጊዜ ተቀባይ የሆኑ ሰዎች በምሥራቹ የተባረኩት እንዴት ነው?

• የወንጌላዊነት መብታችንን እንዴት እንመለከተዋለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[ከገጽ 19-22 የሚገኝ ሰንጠረዥ]

የ2001 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ሪፖርት

(መጽሔቱን ተመልከት)

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች ወንጌሉን የመስበክ ኃላፊነታቸውን ምንጊዜም አይዘነጉም

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለምሥራቹ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ዓለም አቀፍ አንድነት ያለው የወንድማማች ማኅበር ክፍል ይሆናሉ