በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሽማግሌዎች—ኃላፊነት እንዲሸከሙ ሌሎችን አሠልጥኑ

ሽማግሌዎች—ኃላፊነት እንዲሸከሙ ሌሎችን አሠልጥኑ

ሽማግሌዎች—ኃላፊነት እንዲሸከሙ ሌሎችን አሠልጥኑ

በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ በኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሊያገለግሉ የሚችሉ ወንዶችን የማግኘቱ ጉዳይ በጣም አጣዳፊ ነው። ይህ የሆነው በሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች የተነሳ ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋ ‘ታናሹን ብርቱ ሕዝብ’ ለማድረግ የገባውን ቃል በመፈጸም ላይ ነው። (ኢሳይያስ 60:​22) ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ አንድ ሚልዮን የሚያክሉ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ይገባናል በማንለው የአምላክ ደግነት ተጠቅመው የይሖዋ ምሥክሮች በመሆን ተጠምቀዋል። እነዚህ አዲሶች ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና እንዲያድጉ ለመርዳት ኃላፊነት የሚሸከሙ ወንዶች ያስፈልጋሉ።​—⁠ዕብራውያን 6:​1

በሁለተኛ ደረጃ፣ ለተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በጉባኤ ሽማግሌነት ያገለገሉ አንዳንድ ወንድሞች በዕድሜ መግፋት ወይም በጤና ችግሮች ምክንያት በጉባኤ ውስጥ ያለባቸውን የሥራ ጫና ለመቀነስ ተገድደዋል።

በሦስተኛ ደረጃ፣ በርካታ ቀናተኛ ክርስቲያን ሽማግሌዎች በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች፣ በአካባቢ ሕንፃ ሥራ ኮሚቴዎች ወይም በትልልቅ ስብሰባ አዳራሽ ኮሚቴዎች ውስጥ ገብተው በማገልገል ላይ ናቸው። አንዳንዴ ሚዛናቸውን ለመጠበቅ ቢያንስ የተወሰኑ የጉባኤ ኃላፊነቶቻቸውን መተው አስፈልጓቸዋል።

ብቃቱን የሚያሟሉ ወንዶችን የማግኘቱን አጣዳፊ ጉዳይ መወጣት የሚቻለው እንዴት ነው? ለዚህ መፍትሄው ሌሎችን ማሠልጠን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ‘ሌሎችን ሊያስተምሩ የሚችሉ የታመኑ ሰዎችን’ እንዲያሰለጥኑ ያበረታታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:​2) አንድ መዝገበ ቃላት “ማሠልጠን” የሚለውን ግሥ “ለቦታው እንዲመጥን፣ ብቃቱን እንዲያሟላ ወይም በቂ ችሎታ እንዲኖረው ማስተማር” የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። ሽማግሌዎች ብቃቱን የሚያሟሉ ሌሎች ወንዶችን እንዴት ማሠልጠን እንደሚችሉ እስቲ እንመልከት።

የይሖዋን ምሳሌ ኮርጁ

ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥም ለሥራው ‘የሚመጥን፣ ብቃቱን የሚያሟላ እንዲሁም በቂ ችሎታ ያለው’ ነበር። ደግሞም ይህ መሆኑ ምንም አያስደንቅም! ያሠለጠነው ይሖዋ አምላክ ራሱ ነበር። ይህ የሥልጠና ፕሮግራም ይህን ያህል ውጤታማ እንዲሆን ያደረጉት ነገሮች ምንድን ናቸው? በዮሐንስ 5:​20 ላይ እንደተመዘገበው ኢየሱስ “አብ [1] ወልድን ይወዳልና፣ [2] የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ [3] ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል” በማለት ሦስት ምክንያቶችን ጠቅሷል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እነዚህን ሦስት ምክንያቶች መመርመሩ ስለ ሥልጠና ጥልቅ ማስተዋል ያስገኛል።

ኢየሱስ በመጀመሪያ “አብ ወልድን ይወዳልና” ማለቱን ልብ በል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ከፍጥረት መባቻ አንስቶ በይሖዋና በልጁ መካከል የጠበቀ ወዳጅነት ነበር። ምሳሌ 8:​30 በዚህ ወዳጅነት ላይ ተጨማሪ ብርሃን ይፈነጥቃል:- “የዚያን ጊዜ እኔ [ኢየሱስ] በእርሱ [በይሖዋ አምላክ] ዘንድ ዋና ሠራተኛ ነበርሁ፤ ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፤ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ኢየሱስ ይሖዋ ‘ደስ ይሰኝበት’ እንደነበረ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አድሮበት አያውቅም። እንዲሁም ኢየሱስ ከአባቱ ጋር በመሥራቱ የተሰማውን ደስታ ከመናገር ወደኋላ አላለም። በክርስቲያን ሽማግሌዎችና እነርሱ በሚያሠለጥኗቸው ሰዎች መካከል ሞቅ ያለና ግልጽነት የሚታይበት ወዳጅነት መኖሩ ምንኛ መልካም ነው!

ኢየሱስ የጠቀሰው ሁለተኛው ምክንያት አብ ‘የሚያደርገውን ሁሉ የሚያሳየው’ መሆኑ ነው። እነዚህ ቃላት ጽንፈ ዓለሙ ሲፈጠር ኢየሱስ በይሖዋ ‘ዘንድ እንደነበረ’ የሚናገረውን የምሳሌ 8:​30 ሐሳብ የሚያጠናክሩ ናቸው። (ዘፍጥረት 1:​26) ሽማግሌዎች የጉባኤ አገልጋዮች ኃላፊነቶቻቸውን እንዴት በብቃት እንደሚወጡ በማሳየት ረገድ ከእነርሱ ጋር ተቀራርበው በመሥራት ይህን ግሩም ምሳሌ መኮረጅ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ቀጣይነት ያለው ሥልጠና የሚያስፈልጋቸው አዲስ የተሾሙ የጉባኤ አገልጋዮች ብቻ አይደሉም። ለብዙ ዓመታት የበላይ ተመልካች ለመሆን ሲጣጣሩ የቆዩ ሆኖም ያልተሾሙ ታማኝ ወንድሞችስ ሥልጠና አያስፈልጋቸውም? (1 ጢሞቴዎስ 3:​1) ሽማግሌዎች እንዲህ ያሉ ወንዶች በምን በኩል ማሻሻያ ማድረግ እንዳለባቸው እንዲያውቁ ለመርዳት ድክመታቸውን ለይተው በመጥቀስ ምክር ሊለግሷቸው ይገባል።

ለምሳሌ ያህል አንድ የጉባኤ አገልጋይ የተሰጠውን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ እምነት የሚጣልበት፣ ቀልጣፋና ጠንቃቃ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ጎበዝ አስተማሪ ሊሆን ይችላል። በጉባኤ ውስጥ በብዙ መልኩ ሥራውን በግሩም ሁኔታ የሚያከናውን ይሆናል። ይሁን እንጂ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ትንሽ የኃይለኝነት ባሕርይ እንደሚታይበት ላይታወቀው ይችላል። ሽማግሌዎች ‘ከጥበብ የሆነ የዋህነት’ ማንጸባረቅ ይጠበቅባቸዋል። (ያዕቆብ 3:​13) አንድ ሽማግሌ ችግሩን በግልጽ በማስቀመጥ፣ ተጨባጭ ምሳሌዎችን በመስጠትና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ የማሻሻያ ሐሳቦችን በመጠቆም የጉባኤ አገልጋዩን ቢያነጋግረው ደግነት አይሆንም? ሽማግሌው ‘ምክሩን በጨው እንደተቀመመ አድርጎ’ በጥንቃቄ የሚሰጥ ከሆነ ሐሳቡ ተቀባይነት ማግኘቱ አይቀርም። (ቆላስይስ 4:​6) እርግጥ ነው፣ የጉባኤ አገልጋዩ ግልጽ እንዲሁም የሚሰጠውን ማንኛውንም ምክር ተቀባይ በመሆን የሽማግሌውን ሥራ ይበልጥ አስደሳች ማድረግ ይችላል።​—⁠መዝሙር 141:​5

በአንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ ሽማግሌዎች ለጉባኤ አገልጋዮች ቀጣይነት ያለው ተግባራዊ ሥልጠና ይሰጣሉ። ለምሳሌ ያህል የታመሙ ወይም አረጋውያንን በሚጠይቁበት ጊዜ ብቃት ያላቸው የጉባኤ አገልጋዮችን ይዘው ይሄዳሉ። በዚህ መንገድ የጉባኤ አገልጋዮቹ በእረኝነቱ ሥራ ልምድ ያገኛሉ። እርግጥ ነው አንድ የጉባኤ አገልጋይ የራሱን መንፈሳዊ እድገት ለማፋጠን ብዙ ሊያደርገው የሚችለው ነገር አለ።​—⁠“የጉባኤ አገልጋዮች ሊያደርጉ የሚችሏቸው ነገሮች” የሚለውን ከዚህ በታች ያለ ሣጥን ተመልከት።

ኢየሱስ ያገኘውን ሥልጠና ውጤታማ እንዲሆን ያደረገው ሦስተኛው ምክንያት ይሖዋ የወደፊቱን እድገት በማሰብ ስላሠለጠነው ነው። ኢየሱስ ስለ አብ ሲናገር ለወልድ “ከዚህ የሚበልጥ ሥራ” ያሳየዋል ብሏል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ኢየሱስ ምድር ሳለ ያገኘው ተሞክሮ ወደፊት የሚረከበውን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስፈልጉትን ባሕርያት እንዲያዳብር አስችሎታል። (ዕብራውያን 4:​15፤ 5:​8, 9) ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ በቅርቡ አሁን ሞተው ያሉ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሙታንን የማስነሳትና የመፍረድ ከባድ ኃላፊነት ይረከባል!​—⁠ዮሐንስ 5:​21, 22

ሽማግሌዎች የጉባኤ አገልጋዮችን በሚያሠለጥኑበት ጊዜ ወደፊት የሚያስፈልጉበት አጋጣሚ ሊመጣ እንደሚችል ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል። የኃላፊነት ቦታዎችን የሚሸፍኑ በቂ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ኖረው ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም አንድ አዲስ ጉባኤ ቢቋቋም ያሉት ብቻቸውን በቂ ይሆናሉ? ከአንድ በላይ አዳዲስ ጉባኤዎች ቢቋቋሙስ? ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በዓለም ዙሪያ ከ6, 000 በላይ አዳዲስ ጉባኤዎች ነበሩ። ለእነዚህ አዳዲስ ጉባኤዎች በጣም ብዙ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች አስፈልገዋል!

ሽማግሌዎች፣ ከምታሠለጥኗቸው ወንዶች ጋር ሞቅ ያለ ወዳጅነት በመመሥረት የይሖዋን ምሳሌ ትኮርጃላችሁ? ሥራቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ ታሳዩአቸዋላችሁ? ወደፊት በጣም የሚያስፈልጉበት አጋጣሚ እንደሚኖርስ ከግምት ውስጥ ታስገባላችሁን? ይሖዋ ኢየሱስን በማሠልጠን የተወውን ምሳሌ መከተሉ ለብዙዎች የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል።

ኃላፊነት ለመስጠት አትስጉ

ከባድና ተደራራቢ ኃላፊነቶችን የተሸከሙ ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎች ለሌሎች ኃላፊነት ከመስጠት ወደኋላ ሊሉ ይችላሉ። ቀደም ሲል ለሌሎች ኃላፊነት ለመስጠት ሞክረው ውጤቱ አላስደሰታቸው ይሆናል። ስለዚህ ‘አንድ ሥራ በጥሩ ሁኔታ እንዲሠራ ከፈለግህ አንተው ራስህ መሥራት አለብህ’ የሚል አመለካከት ሊያዳብሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ተሞክሮ የሌላቸው ወንዶች ይበልጥ ተሞክሮ ካላቸው ወንዶች ሥልጠና እንዲያገኙ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከተገለጸው የአምላክ ፈቃድ ጋር ይስማማል?​—⁠2 ጢሞቴዎስ 2:​2

ሐዋርያው ጳውሎስ ከጉዞ ጓደኞቹ መካከል አንዱ የነበረው ዮሐንስ ማርቆስ ጵንፍልያ ላይ ትቶት ወደ ቤቱ በመመለሱ ተበሳጭቶ ነበር። (ሥራ 15:​38, 39) ይሁን እንጂ ጳውሎስ ይህ ሁኔታ ሌሎችን ማሠልጠኑን እንዲተው አላደረገውም። ጢሞቴዎስ የሚባል ሌላ ወጣት ወንድም መርጦ በሚስዮናዊ ሥራ አሠለጠነው። a (ሥራ 16:​1-3) ሚስዮናውያን ቤርያ ውስጥ ከባድ ተቃውሞ ስላጋጠማቸው ጳውሎስ አካባቢውን ለቅቆ መሄድ ግድ ሆነበት። ስለዚህ ጳውሎስ አዲሱን ጉባኤ የመምራቱን ኃላፊነት በዕድሜ ትልቅ ለሆነው ጎልማሳ ወንድም ለሲላስና ለጢሞቴዎስ ሰጥቶ ሄደ። (ሥራ 17:​13-15) ጢሞቴዎስ ከሲላስ ብዙ ስለመማሩ ምንም ጥርጥር የለውም። ከጊዜ በኋላ ጢሞቴዎስ ተጨማሪ ኃላፊነቶችን መሸከም የሚችልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ በዚያ የሚገኘውን ጉባኤ እንዲያበረታታ ጳውሎስ ወደ ተሰሎንቄ ላከው።​—⁠1 ተሰሎንቄ 3:​1-3

በጳውሎስና በጢሞቴዎስ መካከል የተመሠረተው ወዳጅነት ሞቅ ያለ ስሜት የሚንጸባረቅበት እንጂ ከአንገት በላይ አልነበረም። በመካከላቸው የጠበቀ ቅርርብ ነበር። ጳውሎስ ቆሮንቶስ ወደሚገኘው ጉባኤ ሲጽፍ ወደዚያ ሊልከው ያሰበውን ጢሞቴዎስን “የምወደውንና የታመነውን በጌታ ልጄ የሆነውን” በማለት ጠርቶታል። አክሎም “በክርስቶስ ኢየሱስ የሚሆነውን መንገዴን እርሱ [ጢሞቴዎስ] ያሳስባችኋል” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 4:​17) ጢሞቴዎስ የተሰጠውን ሥራ በብቃት በማከናወን ከጳውሎስ ላገኘው ሥልጠና በጎ ምላሽ አሳይቷል። ብዙ ወጣት ወንድሞች ጥሩ ችሎታ ያላቸው የጉባኤ አገልጋዮች፣ ሽማግሌዎች ሌላው ቀርቶ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሊሆኑ የቻሉት ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንዳደረገው ሁሉ ሽማግሌዎች ትኩረት ሰጥተው ስላሠለጠኗቸው ነው።

ሽማግሌዎች፣ ሌሎችን አሠልጥኑ!

ዛሬ በኢሳይያስ 60:​22 ላይ የሚገኘው ትንቢት በትክክል ፍጻሜውን እያገኘ ነው። ይሖዋ “ታናሹ[ን] ለብርቱ ሕዝብ” እያደረገው ነው። ይህ ሕዝብ ‘ብርቱ’ ሆኖ እንዲቀጥል በጥሩ ሁኔታ መደራጀት ይገባዋል። እናንተ ሽማግሌዎች፣ ብቃቱን ለሚያሟሉ ራሳቸውን የወሰኑ ወንዶች ተጨማሪ ሥልጠና መስጠት ስለምትችሉባቸው መንገዶች ለምን በቁም ነገር አታስቡም? እያንዳንዱ የጉባኤ አገልጋይ እድገት እንዲያደርግ ከተፈለገ ማሻሻል የሚኖርበትን ማንኛውንም ነገር ማወቅ እንዳለበት አትዘንጉ። እንዲሁም እናንተ የተጠመቃችሁ ወንድሞች እንድታሻሽሉ የሚነገራችሁን በሙሉ ትኩረት ሰጥታችሁ ሥሩበት። ችሎታችሁን፣ እውቀታችሁን እንዲሁም ልምዳችሁን ለማሻሻል አጋጣሚዎችን ሁሉ ተጠቀሙ። ይሖዋ ፍቅራዊ እርዳታ የሚሰጥበትን እንዲህ ያለውን ፕሮግራም እንደሚባርክ ምንም ጥርጥር የለውም።​—⁠ኢሳይያስ 61:​5

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ ከዮሐንስ ማርቆስ ጋር ሠርቷል።​—⁠ቆላስይስ 4:​10

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የጉባኤ አገልጋዮች ሊያደርጉ የሚችሏቸው ነገሮች

ሽማግሌዎች ለጉባኤ አገልጋዮች ሥልጠና መስጠት የሚገባቸው መሆኑ እንዳለ ሆኖ፤ የጉባኤ አገልጋዮች የራሳቸውን መንፈሳዊ እድገት ለማፋጠን ብዙ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር አለ።

—የጉባኤ አገልጋዮች የተሰጣቸውን ሥራ በማከናወን ረገድ ትጉዎችና እምነት የሚጣልባቸው መሆን ይገባቸዋል። እንዲሁም ጥሩ የጥናት ልማድ ማዳበር ይኖርባቸዋል። እድገታቸው በአብዛኛው በጥናትና የተማሩትን ተግባራዊ በማድረግ ላይ የተመካ ነው።

—አንድ የጉባኤ አገልጋይ በክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ንግግር ለማቅረብ ዝግጅት በሚያደርግበት ጊዜ ጥሩ ችሎታ ያለው ሽማግሌ ክፍሉን እንዴት እንደሚያቀርብ ሐሳብ እንዲሰጠው ለመጠየቅ ማመንታት አይገባውም።

—በተጨማሪም የጉባኤ አገልጋዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር በሚያቀርብበት ጊዜ እንዲከታተለውና ማድረግ ስለሚኖርበት መሻሻል ምክር እንዲሰጠው አንድን ሽማግሌ መጠየቅ ይችላል።

የጉባኤ አገልጋዮች ከሽማግሌዎች ምክር መጠየቅ፣ መቀበልና በሥራ ላይ ማዋል ይገባቸዋል። በዚህ መንገድ እድገታቸው “በሰው ሁሉ ዘንድ ግልጥ ሆኖ” ይታያል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​15 NW