በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መልካም ሥራዎች አምላክን ያስከብራሉ

መልካም ሥራዎች አምላክን ያስከብራሉ

መልካም ሥራዎች አምላክን ያስከብራሉ

እውነተኛ ክርስቲያኖች በመልካም አኗኗራቸውና ለሌሎች አርአያ በሚሆኑ ተግባሮቻቸው አምላክን ያስከብራሉ። (1 ጴጥሮስ 2:​12) በቅርብ ዓመታት ውስጥ በኢጣሊያ የተፈጸመው ነገር ይህንኑ የሚያስገነዝብ ነው።

መስከረም 1997 የማርሽንና የአምብሪያን የተለያዩ ግዛቶች የመታው ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ 90, 000 የሚያክሉ ቤቶችን አፈራርሷል። ወዲያው የይሖዋ ምሥክሮች በቡድን በቡድን ሆነው የእምነት አጋሮቻቸውንና ሌሎችን ለመርዳት ተንቀሳቅሰዋል። ተንቀሳቃሽ ቤቶች፣ መተኛ ከረጢቶች (sleeping bags)፣ ማብሰያ ምድጃዎች፣ ጀነሬተሮችና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳ ቁሶች ሁሉ ቀርበው ነበር። እርዳታ ለማበርከት የተደረገው ይህ ጥረት የሌሎችን ትኩረት ስቧል።

ኢል ቼንትሮ የተባለ አንድ ጋዜጣ የሚከተለውን ሪፖርት አድርጓል:- “የእርዳታ ቁሳ ቁሶች ጭነው ጉዳት ወደደረሰባቸው አካባቢዎች ለመምጣት የመጀመሪያ የነበሩት በሮሴቶ [በቴራሞ ግዛት] የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። . . . ለይሖዋ ታማኝ የሆኑት ለመጸለይ በየጊዜው የሚገናኙ ከመሆኑም በላይ እገሌ ከገሌ ብለው በእምነት አድልዎ ሳያደርጉ መከራ የደረሰባቸውን ሁሉ በመርዳት ተግባራዊ ነገር አከናውነዋል።”

የአደጋው ዋነኛ ሰለባ ከሆኑት ከተሞች መካከል አንዷ የሆነችው የኖቼራ አምብራ ከተማ ከንቲባ ለምሥክሮቹ የሚከተለውን ጽፈዋል:- “ለኖቼራ ሕዝብ ላደረጋችሁት እርዳታ በግል ልባዊ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ። ይህ የነዋሪዎቿም ስሜት እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ።” በተጨማሪም የአገሪቱ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኮንግሬጋትስዮኔ ክርስቲያና ዴ ቴስቲሞኒ ዲ ዤኦቫ (ለይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያን ጉባኤ) የበጎ አድራጎት ማረጋገጫ የምሥክር ወረቀት የሰጠ ሲሆን “በአምብራና በማርሽ ግዛቶች ከተከሰተው ድንገተኛ አደጋ ጋር በተያያዘ ለተከናወነው ትጋት የተሞላበት ሥራ ምሥክር እንዲሆን” አንድ ሜዳልያ ሸልሟል።

ጥቅምት 2000 ደግሞ ኃይለኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በኢጣሊያ ሰሜናዊ ክፍል የምትገኘውን የፒድሞንት ክልል አጥለቅልቆ ነበር። ወዲያው ምሥክሮቹ እርዳታ ለመስጠት የሚያስችላቸውን ዝግጅት አደረጉ። እነዚህ መልካም ሥራዎችም ቢሆኑ የሌሎችን ትኩረት ስበው ነበር። የፒድሞንት ክልል ምሥክሮቹ “የጎርፉ ሰለባ የሆኑትን የፒድሞንት ነዋሪዎች ለመታደግ ያከናወኑትን የላቀ ግምት የሚሰጠው የፈቃደኝነት አገልግሎት” በማስመልከት አንድ ጽሑፍ የተቀረጸበት ፍሬም ሸልሟቸዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቷቸዋል:- “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።” (ማቴዎስ 5:​16) የይሖዋ ምሥክሮች ጎረቤቶቻቸውን በመንፈሳዊና በሌሎች መንገዶች የሚጠቅሙ ‘መልካም ሥራዎች’ በማከናወን ራሳቸውን ሳይሆን አምላክን ለማስከበር በደስታ ይጥራሉ።