በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምንጊዜም ጥሩነት አሳዩ

ምንጊዜም ጥሩነት አሳዩ

ምንጊዜም ጥሩነት አሳዩ

“የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና [“በጥሩነትና፣” NW ] በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና።”​ኤፌሶን 5:​9

1. ዛሬ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከመዝሙር 31:​19 ጋር እንደሚስማሙ የሚያሳዩት እንዴት ነው?

 ማንኛውም ሰው ሊያደርገው ከሚችለው ሁሉ የላቀው ጥሩ ተግባር ለይሖዋ ክብር ማምጣት ነው። ዛሬ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክን ስለ ጥሩነቱ በማወደስ እርሱን እያስከበሩ ነው። ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች እንደ መሆናችን መጠን “በአንተ ለሚያምኑ በሰው ልጆች ፊት ያዘጋጀሃት ለሚፈሩህም የሰወርሃት፣ ቸርነትህ [“ጥሩነትህ፣” NW ] እንደ ምን በዛች!” ሲል ከዘመረው መዝሙራዊ ጋር ሙሉ በሙሉ እንስማማለን።​—⁠መዝሙር 31:​19

2, 3. ደቀ መዝሙር የማድረግ ሥራችን በጥሩ ምግባር ካልታገዘ ውጤቱ ምን ይሆናል?

2 ለይሖዋ ያለን አክብሮታዊ ፍርሃት ስለ ጥሩነቱ እንድናወድሰው ይገፋፋናል። እንዲሁም ‘እንድናመሰግነው፣ እንድንባርከውና የመንግሥቱንም ክብር እንድንናገር’ ያነሳሳናል። (መዝሙር 145:​10-13) በመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት የምንካፈልበትም ምክንያት ይኸው ነው። (ማቴዎስ 24:​14፤ 28:​19, 20) እርግጥ የስብከት ሥራችን በጥሩ ምግባር መታገዝ ይኖርበታል። አለዚያ ግን በይሖዋ ቅዱስ ስም ላይ ነቀፌታ ልናመጣ እንችላለን።

3 ብዙ ሰዎች አምላክን እንደሚያመልኩ ቢናገሩም አድራጎታቸው በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ ውስጥ ከሚገኘው መስፈርት ጋር አይጣጣምም። ጥሩ እንደሚያደርጉ እየተናገሩ በቃላቸው የማይገኙ አንዳንድ ሰዎችን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? . . . በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደ ተጻፈ።”​—⁠ሮሜ 2:21, 22, 24

4. ጥሩ ምግባራችን ምን ውጤት አለው?

4 በይሖዋ ስም ላይ ነቀፌታ ከማምጣት ይልቅ በጥሩ ምግባራችን ስሙን ለማስከበር እንጥራለን። ይህም ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ባሉት ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል። በመጀመሪያ ደረጃ የተቃዋሚዎችን አፍ ለማዘጋት ይረዳናል። (1 ጴጥሮስ 2:​15) ከሁሉ ይበልጥ ደግሞ ጥሩ ምግባራችን ሌሎች ሰዎች ወደ ድርጅቱ እንዲሳቡ እንዲሁም ለይሖዋ ክብር እንዲያመጡና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ በር ይከፍታል።​—⁠ሥራ 13:​48

5. አሁን ልንመረምራቸው የሚገቡ ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?

5 ፍጹማን ባለመሆናችን አምላክን ሊያስነቅፍና እውነትን የሚፈልጉትን ሊያሰናክል የሚችል ምግባር ከማሳየት መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው? በእርግጥ ጥሩነትን በማሳየት ረገድ ሊሳካልን የሚችለው እንዴት ነው?

የብርሃን ፍሬ

6. ‘ፍሬ የሌለው የጨለማ ሥራ’ ከተባሉት ነገሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ይሁንና ክርስቲያኖች ሊያሳዩት የሚገባው ፍሬ ምንድን ነው?

6 ራሳችንን የወሰንን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን “ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ” እንድንርቅ የሚረዳንን ነገር አግኝተናል። ከዚህ የጨለማ ሥራ መካከል ውሸት፣ ስርቆት፣ ስድብ፣ የብልግና ወሬ፣ ወራዳ ድርጊትና ጸያፍ ቀልድ እንዲሁም ስካር ይገኙበታል። (ኤፌሶን 4:25, 28, 31፤ 5:​3, 4, 11, 12, 18) ‘እንደ ብርሃን ልጆች እንመላለሳለን’ እንጂ ራሳችንን በእነዚህ ሥራዎች አናጠላልፍም። ሐዋርያው ጳውሎስ “የብርሃኑ ፍሬ በበጎነት [“በጥሩነት፣” NW ] እና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና” ሲል ተናግሯል። (ኤፌሶን 5:8, 9) እንግዲያው ጥሩነትን ማሳየታችንን መቀጠል የምንችለው በብርሃኑ በመመላለስ ነው። ይሁንና ይህ ምን ዓይነት ብርሃን ነው?

7. የጥሩነትን ፍሬ ማሳየታችንን ለመቀጠል ምን ማድረግ ይኖርብናል?

7 አለፍጽምና ቢኖርብንም በመንፈሳዊ ብርሃን ከተመላለስን ጥሩነትን ማሳየት እንችላለን። መዝሙራዊው “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴ ብርሃን ነው” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 119:​105) ‘በጥሩነት ሁሉ’ ‘የብርሃኑን ፍሬ’ ማሳየታችንን መቀጠል ከፈለግን በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኘውና በክርስቲያናዊ ጽሑፎች ላይ ከሚብራራው እንዲሁም አምልኮ በምናካሂድባቸው ስብሰባዎች ላይ ውይይት ከሚደረግበት መንፈሳዊ ብርሃን አዘውትረን መጠቀም ይኖርብናል። (ሉቃስ 12:​42፤ ሮሜ 15:​4፤ ዕብራውያን 10:​24, 25) እንዲሁም “የዓለም ብርሃን” እና ‘የይሖዋ የክብሩ ነጸብራቅ’ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የተወውን ምሳሌና ያስተማረውን ትምህርት በትኩረት ልንከታተል ይገባል።​—⁠ዮሐንስ 8:​12፤ ዕብራውያን 1:​1-3

የመንፈስ ፍሬ

8. ጥሩነት ማሳየት የምንችለው ለምንድን ነው?

8 መንፈሳዊ ብርሃን ጥሩነትን እንድናሳይ እንደሚረዳን ምንም ጥያቄ የለውም። በተጨማሪም ይህንን ባሕርይ ማሳየት የምንችለው በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል ስለምንመራ ነው። ጥሩነት ‘ከመንፈስ ፍሬ’ አንዱ ነው። (ገላትያ 5:​22, 23 NW ) ለይሖዋ ቅዱስ መንፈስ አመራር ከተገዛን መንፈሱ ግሩም የሆነውን የጥሩነት ፍሬ በውስጣችን ያፈራል።

9. በሉቃስ 11:​9-13 ላይ ከሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ጋር በሚስማማ መንገድ እርምጃ መውሰድ የምንችለው እንዴት ነው?

9 የመንፈስ ፍሬ የሆነውን ጥሩነት በማንጸባረቅ ይሖዋን ለማስደሰት ያለን ልባዊ ፍላጎት ከሚከተሉት የኢየሱስ ቃላት ጋር በሚስማማ መንገድ እርምጃ እንድንወስድ ሊያነሳሳን ይገባል:- “ለምኑ፣ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፣ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፣ ይከፍትላችሁማል። የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፣ የሚፈልግም ያገኛል፣ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል። አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ እንጀራ ቢለምነው፣ እርሱም ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ደግሞ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን? ወይስ እንቊላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? እንኪያስ እናንተ [ፍጽምና የጎደላችሁና አንጻራዊ በሆነ መንገድ] ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፣ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?” (ሉቃስ 11:9-13) እንግዲያው የይሖዋ መንፈስ ፍሬ የሆነውን ጥሩነትን ማንጸባረቃችንን ለመቀጠል የኢየሱስን ምክር በመከተል መንፈሱን ለማግኘት እንጸልይ።

‘ጥሩ የሆነውን ማድረጋችሁን ቀጥሉ’

10. በዘጸአት 34:​6, 7 NW ላይ የተጠቀሱት የይሖዋ ጥሩነት ገጽታዎች ምንድን ናቸው?

10 ከአምላክ ቃል በምናገኘው መንፈሳዊ ብርሃንና በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ‘ጥሩ የሆነውን ማድረጋችንን መቀጠል’ እንችላለን። (ሮሜ 13:​3 NW ) አዘውትረን መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና የይሖዋን ጥሩነት መምሰል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይበልጥ እየተማርን እንሄዳለን። ከዚህ በፊት የነበረው ርዕስ በዘጸአት 34:​6, 7 NW ላይ ተመዝግቦ በሚገኘውና ሙሴ በሰማው መግለጫ ላይ የተጠቀሱትን የአምላክ ጥሩነት አንዳንድ ገጽታዎች አብራርቷል። ጥቅሱ እንዲህ ይነበባል:- “ይሖዋ፣ ይሖዋ መሐሪ፣ ደግ፣ ለቁጣ የዘገየ፣ ፍቅራዊ ደግነቱና እውነቱ የበዛ፣ እስከ ሺህ ትውልድም ፍቅራዊ ደግነትን የሚጠብቅ፣ ስህተትና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፣ [በደለኛውን] ሳይቀጣ የማያልፍ . . . አምላክ ነው።” ይህንን የይሖዋ ጥሩነት መግለጫ በጥልቀት መመርመራችን ‘ጥሩ የሆነውን ማድረጋችንን እንድንቀጥል’ ይረዳናል።

11. ይሖዋ መሐሪ እንዲሁም ደግ መሆኑን ማወቃችን ሊነካን የሚገባው እንዴት ነው?

11 ይህ መለኮታዊ መግለጫ መሐሪ እንዲሁም ደግ በመሆን ይሖዋን የመኮረጁን አስፈላጊነት እንድናስተውል ይረዳናል። ኢየሱስ “የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፣ ይማራሉና” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:7፤ ሉቃስ 6:36) ይሖዋ ደግ መሆኑን በመገንዘብ የምንሰብክላቸውን ሰዎች ጨምሮ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ደግና ተወዳጅ ለመሆን እንጥራለን። ይህ ሐዋርያው ጳውሎስ ከሰጠው ከሚከተለው ምክር ጋር ይስማማል:- “ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፣ በጨው እንደ ተቀመመ፣ በጸጋ [“በደግነት፣” NW ] ይሁን።”​—⁠ቆላስይስ 4:5-6

12. (ሀ) አምላክ ለቁጣ የዘገየ በመሆኑ እኛ ሌሎችን እንዴት ልንይዝ ይገባናል? (ለ) የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?

12 አምላክ ለቁጣ የዘገየ በመሆኑ ‘ጥሩ የሆነውን እያደረግን ለመቀጠል’ ያለን ፍላጎት የእምነት ወንድሞቻችንን ጥቃቅን ስህተቶች በመታገስ በመልካም ባሕርያቸው ላይ እንድናተኩር ያነሳሳናል። (ማቴዎስ 7:​5፤ ያዕቆብ 1:​19) የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት በጣም ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ሳይቀር ታማኝ ፍቅር እንድናሳይ ያነሳሳናል። ይህ ደግሞ ተወዳጅ ባሕርይ እንደሆነ ግልጽ ነው።​—⁠ምሳሌ 19:​22 NW 

13. ይሖዋ ‘ባለ ብዙ እውነት’ መሆኑን ለማንጸባረቅ እንዴት መመላለስ ይገባናል?

13 ሰማያዊው አባታችን ‘ባለ ብዙ እውነት ’ ስለሆነ ‘በእውነት ቃል ራሳችንን የእግዚአብሔር አገልጋዮች አድርገን ለማቅረብ’ እንጥራለን። (2 ቆሮንቶስ 6:​3-7 አ.መ.ት ) ይሖዋ ከሚጠላቸው ሰባት ነገሮች መካከል “ሐሰተኛ ምላስ” እና “በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር” ይገኙበታል። (ምሳሌ 6:​16-19) በመሆኑም አምላክን ለማስደሰት ያለን ፍላጎት ‘ውሸትን አስወግደን እውነትን እንድንነጋገር’ ይገፋፋናል። (ኤፌሶን 4:​25) በዚህ በጣም ወሳኝ የሆነ መንገድ ጥሩነትን ከማሳየት ወደኋላ አንበል።

14. ይቅር ባይ መሆን የሚኖርብን ለምንድን ነው?

14 አምላክ ለሙሴ የሰጠው መግለጫ ይቅር ባይ እንድንሆንም ሊያንቀሳቅሰን ይገባል። ምክንያቱም ይሖዋ ራሱ ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው። (ማቴዎስ 6:​14, 15) እርግጥ ይሖዋ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችን ይቀጣል። በመሆኑም የጉባኤውን መንፈሳዊ ንጽሕና መጠበቅን በተመለከተም የእርሱን የጥሩነት የአቋም ደረጃ ማክበር ይኖርብናል።​—⁠ዘሌዋውያን 5:​1፤ 1 ቆሮንቶስ 5:​11, 12፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:​22

“በጥንቃቄ ተጠበቁ”

15, 16. በኤፌሶን 5:​15-19 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው የሐዋርያው ጳውሎስ ምክር ጥሩነትን ማሳየታችንን እንድንቀጥል የሚረዳን እንዴት ነው?

15 ዙሪያችንን የከበበን ክፋት እያለ የጥሩነትን ጎዳና ለመከተል ከፈለግን በአምላክ መንፈስ መሞላትና እንዴት እንደምንመላለስ አካሄዳችንን በጥንቃቄ መጠበቅ ይኖርብናል። በዚህ ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን የነበሩትን ክርስቲያኖች እንደሚከተለው ሲል አጥብቆ አሳስቧቸዋል:- “እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና፤ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ።” (ኤፌሶን 5:​15-19) ይህ ምክር በእነዚህ አስጨናቂ የመጨረሻ ቀናት ለምንኖረው ሰዎች በእርግጥ ተስማሚ ነው።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​1

16 ጥሩነትን ማሳየታችንን መቀጠል ከፈለግን አምላካዊ ጥበብ እንዳላቸው ሰዎች በጥንቃቄ መመላለስ ይኖርብናል። (ያዕቆብ 3:​17) ከከባድ ኃጢአቶች መራቅና መንፈስ ቅዱስ እንዲመራን በመፍቀድ በመንፈስ መሞላት ይኖርብናል። (ገላትያ 5:​19-25) በክርስቲያናዊ የጉባኤ፣ የወረዳና የልዩ እንዲሁም የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የሚሰጠውን መንፈሳዊ ትምህርት ሥራ ላይ በማዋል ጥሩ የሆነውን ማድረጋችንን ልንቀጥል እንችላለን። ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የተናገራቸው ቃላት ለአምልኮ አንድ ላይ በምንገናኝባቸው በአብዛኛዎቹ ስብሰባዎች ‘መንፈሳዊ መዝሙሮችን’ ከልባችን በመዘመር የምናገኘውን ጥቅም ያሳስቡናል። ብዙዎቹ መዝሙሮች እንደ ጥሩነት ባሉት መንፈሳዊ ባሕርያት ላይ ያተኮሩ ናቸው።

17. በከባድ ሕመም የተያዙ ክርስቲያኖች ያሉበት ሁኔታ በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው እንዳይገኙ የሚያግዳቸው ከሆነ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ሊሆኑ ይችላሉ?

17 ባለባቸው ከባድ ሕመም ምክንያት አዘውትረው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ስለማይችሉ የእምነት ወንድሞቻችንስ ምን ማለት ይቻላል? ሁልጊዜ በመንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው መካከል ተገኝተው ይሖዋን ማምለክ ባለመቻላቸው መንፈሳቸው ተሰብሮ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሁኔታቸውን እንደሚረዳላቸው፣ በእውነት ውስጥ እንደሚያቆያቸው፣ መንፈሱን እንደሚሰጣቸውና ጥሩ የሆነውን ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ እንደሚረዳቸው እርግጠኛ ሊሆኑ ይችላሉ።​—⁠ኢሳይያስ 57:​15

18. የጥሩነትን ጎዳና እንድንከተል ምን ሊረዳን ይችላል?

18 የጥሩነትን ጎዳና መከታተል ባልንጀሮቻችንን በጥበብ መምረጥንና ‘ጥሩ የሆነውን ከማይወዱ ሰዎች’ መራቅን ይጠይቃል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​2-5 NW ፤ 1 ቆሮንቶስ 15:​33) እንዲህ ያለውን ምክር መከተል ከመንፈሱ አመራር ተቃራኒ በመሄድ ‘የአምላክን መንፈስ ከማሳዘን’ ይጠብቀናል። (ኤፌሶን 4:​30) ከዚህም በላይ ጥሩነትን እንደሚወድዱና በይሖዋ መንፈስ እንደሚመሩ በሕይወታቸው ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር ቅርርብ መፍጠራችን ጥሩ የሆነውን እንድናደርግ ይረዳናል።​—⁠አሞጽ 5:​15፤ ሮሜ 8:​14፤ ገላትያ 5:​18

ጥሩነት ግሩም ውጤቶችን ያስገኛል

19-21. ጥሩነት ማሳየት ያለውን ውጤት የሚያንጸባርቁ ተሞክሮዎችን ተናገር።

19 በመንፈሳዊ ብርሃን መሄድ፣ ለአምላክ መንፈስ አመራር መታዘዝና አካሄዳችንን ጠብቀን መመላለስ ክፉ ከሆነው ነገር እንድንርቅና ‘ጥሩ የሆነውን ማድረጋችንን እንድንቀጥል’ ይረዳናል። ይህም ግሩም ውጤቶች ሊያስገኝ ይችላል። ለምሳሌ ያህል በደቡብ አፍሪካ የሚገኘውን አንድ የይሖዋ ምሥክር ሁኔታ ተመልከት። ዞንጌዚሌ ይባላል። አንድ ቀን ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት እየሄደ እያለ የሚያጠራቅማት አነስተኛ ገንዘብ ስንት እንደደረሰች ለማረጋገጥ ወደ ባንኩ ይገባል። አውቶማቲኩ ማሽን ያተመለት ደረሰኝ በስህተት 42, 000 ራንድ (6, 000 የአሜሪካ ዶላር) ትርፍ ያሳየዋል። አንድ የባንክ ጥበቃ ሠራተኛና ሌሎችም ሰዎች ገንዘቡን አውጥቶ በሌላ ባንክ በራሱ ስም እንዲያስቀምጠው አበረታቱት። ከዚህ ገንዘብ ሣንቲም እንኳ ሳያወጣ በመቅረቱ ያመሰገኑት አብረውት የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክር ባልና ሚስት ብቻ ነበሩ።

20 በሚቀጥለው የሥራ ቀን ዞንጌዚሌ የተፈጠረውን ስህተት ለባንኩ አሳወቀ። ከዚያም ጉዳዩ ሲጣራ የእርሱ የሒሳብ ቁጥር ከአንድ ሀብታም ነጋዴ ጋር ተመሳሳይ ስለነበረ ሰውዬው በስህተት በእርሱ የሒሳብ ቁጥር ገንዘባቸውን እንዳስቀመጡ ታወቀ። ዞንጌዚሌ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ አንድም ባለማጉደሉ በመገረም ነጋዴው “ሃይማኖትህ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። የይሖዋ ምሥክር መሆኑን ነገራቸው። የባንክ ቤቱ ሠራተኞችም “ሁሉም ሰው እንደ ይሖዋ ምሥክሮች ሐቀኛ ቢሆን እንዴት ጥሩ ነበር” ሲሉ ከልብ አመስግነውታል። በእርግጥም ሐቀኝነትና ጥሩነት ሌሎች ይሖዋን እንዲያከብሩ ያደርጋል።​—⁠ዕብራውያን 13:​18

21 የጥሩነት ድርጊት ጥሩ ውጤት እንዲያስገኝ የግድ ለየት ያለ መሆን አለበት ማለት አይደለም። ይህን የሚያረጋግጥ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ከሳሞአ ደሴቶች በአንዷ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኖ የሚያገለግል አንድ ወጣት በአካባቢው ወዳለ ሆስፒታል ይሄዳል። እዚያም ሰዎች ዶክተሩ ጋር ለመግባት ወረፋ እየጠበቁ ስለነበር ምሥክሩ ከእርሱ አጠገብ የነበሩ አንዲት አረጋዊ ሴት በጠና መታመማቸውን ያስተውላል። ስለዚህ ሴትዮዋ ቶሎ ዶክተሩ ጋር መግባት ይችሉ ዘንድ የእርሱን ተራ አሳልፎ ሰጣቸው። በሌላ አጋጣሚ ምሥክሩ እኚህን ሴት በገበያ ስፍራ ሲያገኛቸው እርሱንም ሆነ በሆስፒታል ያደረገላቸውን ጥሩ ተግባር በማስታወስ “በእርግጥ የይሖዋ ምሥክሮች ለጎረቤቶቻቸው ፍቅር እንዳላቸው አሁን ተረድቻለሁ” ሲሉ ተናግረዋል። ሴትዮዋ ቀደም ሲል የመንግሥቱን መልእክት ለመቀበል ፈቃደኛ ያልነበሩ ቢሆንም ምሥክሩ ያሳያቸው ጥሩነት መልካም ውጤት አምጥቷል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለው የአምላክን ቃል እውቀት መቅሰም ጀምረዋል።

22. ጥሩ ማድረጋችንን የምንቀጥልበት አንዱ አብይ መንገድ ምንድን ነው?

22 አንተም ጥሩነት ማሳየት የሚያስገኘውን ውጤት የሚጠቁሙ ተሞክሮዎችን መናገር እንደምትችል አያጠያይቅም። ‘ጥሩ ማድረጋችንን መቀጠል’ ከምንችልባቸው አብይ መንገዶች አንዱ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በማወጁ ሥራ ሳያሰልሱ መካፈል ነው። (ማቴዎስ 24:​14) በተለይ ምላሽ ለሚሰጡ ሰዎች ጥሩ ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ምሥራቹን ማድረስ መሆኑን በመገንዘብ በዚህ ውድ ሥራ በቅንዓት መካፈላችንን እንቀጥል። ከሁሉም በላይ ደግሞ አገልግሎታችንና ጥሩ ምግባራችን የጥሩነት አብነት የሆነውን ይሖዋን ያስከብራል።​—⁠ማቴዎስ 19:​16, 17

‘ጥሩ የሆነውን ማድረጋችሁን’ ቀጥሉ

23. ክርስቲያናዊ አገልግሎት ጥሩ ሥራ የሆነው ለምንድን ነው?

23 አገልግሎታችን ጥሩ ሥራ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። ለራሳችንም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱሱን መልእክት ለሚያዳምጡ መዳን የሚያስገኝ ሲሆን እነርሱም ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ እንዲሄዱ ይረዳቸዋል። (ማቴዎስ 7:​13, 14፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:​16) ውሳኔ ማድረግ ሲያስፈልገን ጥሩ ለማድረግ ያለን ፍላጎት እንደሚከተለው ብለን እንድንጠይቅ ያደርገን ይሆናል:- ‘ይህ ውሳኔ የመንግሥቱን ስብከት ሥራዬን የሚነካብኝ እንዴት ነው? በእርግጥ አሁን እያሰብኩት ያለው ጎዳና ያዋጣልን? ሌሎች “የዘላለሙን ወንጌል” እንዲቀበሉና ከይሖዋ ጋር እንዲቀራረቡ ለመርዳት ያስችለኛልን?’ (ራእይ 14:​6) የመንግሥቱን ጥቅም ለማራመድ የሚበጅ ውሳኔ ማድረግ ትልቅ ደስታ ያስገኛል።​—⁠ማቴዎስ 6:​33፤ ሥራ 20:​35

24, 25. በጉባኤ ውስጥ ጥሩ ነገር ማድረግ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? ጥሩነት ማሳየታችንን ከቀጠልንስ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

24 ጥሩነት ያለውን ጠቃሚ ውጤት ፈጽሞ አቅልለን አንመልከተው። የክርስቲያን ጉባኤን በመደገፍና የጉባኤውን ጥቅምና ደህንነት ለማስጠበቅ የቻልነውን ሁሉ በማድረግ ይህንን ባሕርይ ማሳየታችንን ልንቀጥል እንችላለን። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን ስንገኝና ተሳትፎ ስናደርግ ጥሩ ማድረጋችን ነው። መገኘታችን ራሱ የእምነት ወንድሞቻችንን የሚያበረታታቸው ሲሆን ጥሩ ዝግጅት አድርገን የምንሰጣቸው ሐሳቦች ደግሞ በመንፈሳዊ ይገነቧቸዋል። እንዲሁም ጥሪታችንን የመንግሥት አዳራሹን ለመጠገንና ለመንከባከብ ስናውል ጥሩ ተግባር መፈጸማችን ነው። (2 ነገሥት 22:​3-7፤ 2 ቆሮንቶስ 9:​6, 7) “እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም [“ጥሩ፣” NW ] እናድርግ።”​—⁠ገላትያ 6:10

25 ጥሩነት ለማሳየት የሚያስችል ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚያጋጥመን አስቀድመን ማወቅ አንችልም። አንድ አዲስ ሁኔታ ሲገጥመን የቅዱሳን ጽሑፎችን ብርሃን እንፈልግ፣ የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ ለማግኘት እንጸልይ እንዲሁም የእርሱን ጥሩና ፍጹም ፈቃድ እንፈጽም። (ሮሜ 2:​9, 10፤ 12:​2) ጥሩነትን ማሳየታችንን በቀጠልን መጠን ይሖዋ አብዝቶ እንደሚባርከን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ከሁሉ የላቀ ጥሩ ተግባር ማከናወን የምንችለው ምን ስናደርግ ነው?

• ጥሩነት ‘የብርሃን ፍሬ’ ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው?

• ጥሩነት ‘የመንፈስ ፍሬ’ ተብሎ የተጠራውስ ለምንድን ነው?

• ጥሩ ምግባር ማሳየታችን ምን ውጤት አለው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ ቃልና ቅዱስ መንፈሱ በጎነት እንድናሳይ ይረዱናል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥሩነትን ማሳየት ግሩም ውጤቶች አሉት