በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውን በሆነው አምላክ በይሖዋ ታመን

እውን በሆነው አምላክ በይሖዋ ታመን

እውን በሆነው አምላክ በይሖዋ ታመን

በምሽት በከዋክብት የተሞላ ጥርት ያለ ሰማይ ተመልክተህ ታውቃለህ? እነዚህ ሁሉ ከዋክብት እንዴት ሊገኙ ቻሉ?

ፀጥ ባለው ሌሊት በሰማይ ላይ ተረጭተው የሚታዩት ከዋክብት ለንጉሥ ዳዊት መልእክት ነበራቸው። ከዚህም የተነሣ “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል” ብሎ ለመጻፍ ተገፋፍቷል። (መዝሙር 19:​1) አዎን፣ ‘ክብር ውዳሴ ኃይል ሊቀበል’ የሚገባው ፍጥረት ሳይሆን ፈጣሪ ነው።​—⁠ራእይ 4:​10, 11፤ ሮሜ 1:​25

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሁሉን ያዘጋጀ እግዚአብሔር ነው’ በማለት ይናገራል። (ዕብራውያን 3:​4) በእርግጥም ‘ስሙ ይሖዋ የሆነው’ እውነተኛው አምላክ ‘በምድር ሁሉ ላይ ሉዓላዊ ነው።’ (መዝሙር 83:​18 NW ) ለዓይን እንደሚያደናግር እይታ እውን ያልሆነ ነገር አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊ አባቱን ይሖዋን አስመልክቶ ‘የላከኝ እውን ነው’ በማለት ተናግሯል።​—⁠ዮሐንስ 7:​28 NW 

ይሖዋ​—⁠ዓላማዎቹን የሚፈጽም አምላክ

ይሖዋ የሚለው የአምላክ ልዩ ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ብቻ ወደ 7, 000 ጊዜ ያህል ይገኛል። ይህ ስም ራሱ ይሖዋ እውን መሆኑን ያረጋግጣል። የአምላክ ስም ቃል በቃል ሲተረጎም “እንዲሆን ያደርጋል” ማለት ነው። ይህም ይሖዋ አምላክ ራሱን የዓላማዎቹ አስፈጻሚ አድርጎ እንደሚያቀርብ የሚጠቁም ነው። ሙሴ ስሙን በጠየቀው ጊዜ “መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ” በማለት ስሙ ያዘለውን ትርጉም ገልጿል። (ዘጸአት 3:​14) የሮዘርሃም ትርጉም ትንሽ ለየት ባለ አነጋገር “መሆን የምሻውን ሁሉ እሆናለሁ” ሲል አስቀምጦታል። የትኛውንም ዓይነት መሥዋዕትነት ቢጠይቅበትም ይሖዋ የጽድቅ ዓላማዎቹንና ተስፋዎቹን ለማስፈጸም ሲል መሆን የሚፈልገውን ወይም የሚሻውን ይሆናል። በዚህም ምክንያት ፈጣሪ፣ አባት፣ ሉዓላዊ ጌታ፣ እረኛ፣ የሠራዊት ጌታ፣ ጸሎት ሰሚ፣ ፈራጅ፣ ታላቅ አስተማሪ፣ ተቤዥ የሚሉትን የመሳሰሉ በርካታና አስደናቂ የማዕረግ ስሞች አሉት።​—⁠መሳፍንት 11:​27፤ መዝሙር 23:​1፤ 65:​2፤ 73:​28 NW ፤ 89:​26፤ ኢሳይያስ 8:​13፤ 30:​20 NW ፤ 40:​28፤ 41:​14

የሰው ልጆች ስለ እቅዳቸው ተፈጻሚነት እርግጠኛ መሆን ስለማይችሉ ይሖዋ የሚለው ስም የሚገባው እውነተኛው አምላክ ብቻ ነው። (ያዕቆብ 4:​13, 14) እንደሚከተለው ብሎ መናገር የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው:- “ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፣ ምድርን እንደሚያረካት፣ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፣ ዘርንም ለሚዘራ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፣ ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።”​—⁠ኢሳይያስ 55:​10, 11

ይሖዋ ዓላማዎቹ እንደሚፈጸሙ እርግጠኛ ከመሆኑ የተነሳ ለሰዎች እውን መስሎ የማይታየው ነገር እንኳ ለእርሱ እውን ነው። አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ከሞቱ ከብዙ ጊዜ በኋላ ኢየሱስ እነርሱን በመጥቀስ “ሁሉ ለእርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፣ [ይሖዋ] የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 20:​37, 38) ሦስቱ ታማኝ ዕብራውያን አባቶች ሞተዋል። ይሁን እንጂ አምላክ እነርሱን በትንሣኤ ለማስነሳት ያለው ዓላማ እንደሚፈጸም እርግጠኛ ከመሆኑ የተነሣ በእርሱ ፊት ሕያዋን እንደሆኑ ያህል ነው። የመጀመሪያውን ሰው ከአፈር ለፈጠረው ለይሖዋ እነዚህን ታማኝ የጥንት አገልጋዮች እንደገና ወደ ሕይወት ማምጣት ቀላል ነው።​—⁠ዘፍጥረት 2:​7

ሐዋርያው ጳውሎስ አምላክ ዓላማውን እንደሚፈጽም የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ ጠቅሷል። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አብርሃም ‘የብዙ አሕዛብ አባት’ ተብሎ ተጠርቷል። (ሮሜ 4:​16, 17) ይሖዋ ልጅ አልባ ለነበረው ለአብራም “የብዙ ሕዝብ አባት” የሚል ትርጉም ያለውን አብርሃም የሚል ስም ሰጥቶታል። ይሖዋ በእድሜ የገፋውን የአብርሃምንና እርጅና የተጫጫናትን የሣራን የመራባት ኃይል በተአምራዊ መንገድ በመመለስ የዚህ ስም ትርጉም ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል።​—⁠ዕብራውያን 11:​11, 12

ከፍተኛ ኃይልና ሥልጣን የተሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰዎች አመለካከት ላቅ ስላሉ እውነታዎች ተናግሯል። የቅርብ ወዳጁ አልዓዛር የሞተ ቢሆንም ለደቀ መዛሙርቱ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” በማለት ነገራቸው። (ዮሐንስ 11:​11) ኢየሱስ አንድን የሞተ ሰው እንዲያው እንቅልፍ እንደተኛ አድርጎ የገለጸው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ቢታንያ ተብላ ወደምትጠራው የአልዓዛር የትውልድ ከተማ ሲደርስ ወደ መቃብሩ ሄደና የመቃብሩን የድንጋይ መዝጊያ እንዲያነሱት አዘዘ። ጮክ ብሎ ከጸለየ በኋላ “አልዓዛር ሆይ፣ ወደ ውጭ ና” በማለት አዘዘ። “የሞተውም” መቃብሩ ላይ ዓይናቸውን የተከሉት ሰዎች እያዩት “እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፊቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበረ።” ከዚያም ኢየሱስ “ፍቱትና ይሂድ ተዉት አላቸው።” (ዮሐንስ 11:​43, 44) ኢየሱስ ለአራት ቀናት ሞቶ የነበረውን አልዓዛርን አስነሣው! ክርስቶስ ወዳጁ አልዓዛር እንደተኛ አድርጎ መናገሩ እውነታውን አዛብቶ አቅርቧል አያሰኘውም። ሞቶ የነበረው አልዓዛር በይሖዋና በኢየሱስ አመለካከት እንዲያው እንቅልፍ የወሰደው ያህል ነበር። አዎን፣ ኢየሱስና ሰማያዊ አባቱ ትኩረት የሚያደርጉት በእውነታዎች ላይ ነው።

ይሖዋ ተስፋዎቻችንን ይፈጽምልናል

አታላይ በሆኑ ጣዖታትና እውን በሆነው አምላክ መካከል ያለው ልዩነት ምንኛ ሰፊ ነው! ጣዖት አምላኪዎች አማልክቶቻቸው ከሰው በላይ የሆነ ኃይል አላቸው የሚል የተሳሳተ እምነት አላቸው። ይሁን እንጂ ለእነዚህ ጣዖታት የሚሰጠው አምልኮና ክብር የቱንም ያህል ከፍተኛ ቢሆን ይህ ተአምራዊ ችሎታዎችን አይለግሳቸውም። በሌላው በኩል ግን ይሖዋ አምላክ ለሞቱ የጥንት ታማኝ አገልጋዮቹ መልሶ ሕይወት መስጠት ስለሚችል ሕያው እንደሆኑ አድርጎ መናገር ይችላል። ይሖዋ “እውነተኛ አምላክ ነው።” በፍጹም ሕዝቡን አያታልልም።​—⁠ኤርምያስ 10:​10

ይሖዋ የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ በአእምሮው የያዛቸውን ሰዎች ከሞት እንደሚያስነሳቸው ወይም ወደ ሕይወት እንደሚመልሳቸው ማወቁ ምንኛ ያጽናናል! (ሥራ 24:​15) አዎን፣ ትንሣኤ የሞተው ግለሰብ የቀድሞ ስብዕናውን እንደተላበሰ ማስነሣትን ይጨምራል። የሞቱትን ሰዎች የቀድሞ ሕይወት ማስታወስና ስብዕናቸውን እንደተላበሱ ማስነሳት ገደብ የለሽ ጥበብና ኃይል ላለው ፈጣሪ ከባድ አይሆንም። (ኢዮብ 12:​13፤ ኢሳይያስ 40:​26) ይሖዋ ሁለንተናው ፍቅር ስለሆነ የሞቱት ሰዎች የቀድሞ ስብዕናቸውን እንደተላበሱ ገነት በሆነች ምድር ላይ እንዲነሱ ለማድረግ ፍጹም አእምሮውን ይጠቀማል።​—⁠1 ዮሐንስ 4:​8

የሰይጣን ዓለም ፍጻሜ እየተቃረበ ሲሄድ የወደፊቱ ጊዜ በእውነተኛው አምላክ ለሚታመኑ ሰዎች በእርግጥም ብሩህ ነው። (ምሳሌ 2:​21, 22፤ ዳንኤል 2:​44፤ 1 ዮሐንስ 5:​19) መዝሙራዊው የሚከተለውን ማረጋገጫ ሰጥቷል:- “ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” (መዝሙር 37:​10, 11) ወንጀልና ዓመፅ ጨርሶ አይኖሩም። ፍትህ ይሰፍናል። የኑሮ ውድነት ይወገዳል። (መዝሙር 37:​6፤ 72:​12, 13፤ ኢሳይያስ 65:​21-23) የማኅበራዊ፣ የዘር፣ የጎሳና የብሔር ልዩነቶች ያስከተሉት ጠባሳ ሙሉ በሙሉ ይሽራል። (ሥራ 10:​34, 35) ጦርነትና የጦር መሣሪያዎች ጨርሰው ይወገዳሉ። (መዝሙር 46:​9) “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም።” (ኢሳይያስ 33:​24) እያንዳንዱ ሰው ፍጹምና የተሟላ ጤንነት ይኖረዋል። (ራእይ 21:​3, 4) በቅርቡ ምድር ገነት እንደምትሆን የሚናገረው ተስፋ እውን ይሆናል። ይህ የይሖዋ ዓላማ ነው!

አዎን፣ በቅርቡ ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። ታዲያ ትምክህታችንን ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ ማድረግ ስንችል ለምን በዚህ ዓለም ጣዖታት እንታለላለን? የአምላክ ፈቃድ ‘ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:​3, 4) ጊዜያችንንና ጥሪታችንን ለዚህ የነገሮች ሥርዓት ማታለያዎችም ሆነ ለአማልክቱ ማደናገሪያዎች ከማዋል ይልቅ ስለ እውነተኛው አምላክ በሚናገረው እውቀት እንደግ እንዲሁም በሙሉ ልባችን በእርሱ እንታመን።​—⁠ምሳሌ 3:​1-6፤ ዮሐንስ 17:​3

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በይሖዋና በኢየሱስ አመለካከት አልዓዛር እንቅልፍ የተኛ ያክል ነበር

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቅርቡ ምድር ገነት ትሆናለች