በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተለያየ አመለካከት ያዳበሩ ወንድማማቾች

የተለያየ አመለካከት ያዳበሩ ወንድማማቾች

የተለያየ አመለካከት ያዳበሩ ወንድማማቾች

ወላጆች የሚያደርጉት ውሳኔ በልጆቻቸው ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ምንም ጥርጥር የለውም። በዔድን የአትክልት ቦታ የሆነው ነገር ይህንን ሃቅ የሚያረጋግጥልን ሲሆን ዛሬም ያለው ሁኔታ ከዚያ የተለየ አይደለም። አዳምና ሔዋን የተከተሉት የዓመፅ መንገድ መላውን የሰው ዘር በእጅጉ ነክቷል። (ዘፍጥረት 2:​15, 16፤ 3:​1-6፤ ሮሜ 5:​12) ሆኖም እያንዳንዳችን ከፈለግን ከፈጣሪያችን ጋር ጥሩ ወዳጅነት የመመሥረት አጋጣሚው አለን። በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ወንድማማቾች የሆኑት የቃየንና የአቤል ታሪክ ለዚህ ግሩም ምሳሌ ነው።

አዳምና ሔዋን ከዔድን ከተባረሩ በኋላ አምላክ እንዳነጋገራቸው የሚገልጽ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አናገኝም። ያም ሆኖ ግን ይሖዋ ወንዶች ልጆቻቸውን ገሸሽ አላደረጋቸውም። ቃየንና አቤል ስለተከሰተው ሁኔታ ከወላጆቻቸው ተምረው ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። “ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል” ሰይፍ መቀመጡን ማየት ይችሉ ነበር። (ዘፍጥረት 3:​24) በተጨማሪም እነዚህ ወንዶች አምላክ በሰው ልጅ ላይ ስለሚደርሰው ድካምና ጭንቅ የተናገረው ቃል ሲፈጸም አይተዋል።​—⁠ዘፍጥረት 3:​16, 19

ቃየንና አቤል “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ” በማለት ይሖዋ ለእባቡ ስለተናገረው ቃል አውቀው መሆን አለበት። (ዘፍጥረት 3:​15) ቃየንና አቤል ስለ ይሖዋ የሚያውቁት ነገር ከእርሱ ጋር ተቀባይነት ያለው ዝምድና እንዲመሠርቱ የሚያስችላቸው ነበር።

ቃየንና አቤል ይሖዋ በተናገረው ትንቢትና አፍቃሪ ረዳት በመሆን በሚያንጸባርቃቸው ባሕርያቱ ላይ ማሰላሰላቸው መለኮታዊ ሞገስ የማግኘት ፍላጎት እንዲያድርባቸው ሳይገፋፋቸው አልቀረም። ይሁን እንጂ ይህን ፍላጎት እስከ ምን ድረስ ያሳድጉት ይሆን? በተፈጥሮ ላገኙት አምላክን የማምለክ ፍላጎት ታዝዘው በእርሱ እንዲያምኑ የሚያደርግ መንፈሳዊነት ያዳብሩ ይሆን?​—⁠ማቴዎስ 5:​3 NW

ወንድማማቾቹ መሥዋዕት አቀረቡ

ከጊዜ በኋላ ቃየንና አቤል ለአምላክ መሥዋዕት አቀረቡ። ቃየን ከምድር ፍሬ መሥዋዕት ሲያቀርብ አቤል ደግሞ ከመንጋው መካከል በኩራቱን አቀረበ። (ዘፍጥረት 4:​3, 4) አዳም ሦስተኛ ልጁን ሴትን ሲወልድ 130 ዓመቱ ስለነበር እነዚህ ሰዎች 100 ዓመት ሆኗቸው ሊሆን ይችላል።​—⁠ዘፍጥረት 4:​25፤ 5:​3 አ.መ.ት

መሥዋዕት ማቅረባቸው ቃየንና አቤል ኃጢአተኛ መሆናቸውን ተገንዝበው የአምላክን ሞገስ ለማግኘት መፈለጋቸውን የሚያሳይ ነበር። ይሖዋ እባቡንና የሴቲቱን ዘር አስመልክቶ የሰጠውን ተስፋ በመጠኑም ቢሆን አስበውበት መሆን አለበት። ቃየንና አቤል ከይሖዋ ጋር ተቀባይነት ያለው ዝምድና ለመመሥረት ምን ያህል ጊዜ እንዳዋሉና ምን ያህል ጥረት እንዳደረጉ አልተገለጸም። ይሁን እንጂ አምላክ ሁለቱ ሰዎች ላቀረቡት መሥዋዕት የሰጠው ምላሽ የሁለቱንም ውስጣዊ አስተሳሰብ በግልጽ አሳይቷል።

አንዳንድ ምሁራን ሔዋን ቃየንን ስትወልድ “ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ” ብላ መናገሯ የእባቡን ራስ የሚቀጠቅጠው “ዘር” ቃየን እንደሆነ አድርጋ ታስብ እንደነበር ያሳያል የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። (ዘፍጥረት 4:​1) ቃየንም እንደዚያ አስቦ ከነበረ ፈጽሞ ተሳስቷል። በሌላ በኩል ደግሞ አቤል መሥዋዕቱን ያቀረበው በእምነት ነበር። ስለሆነም “አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ።”​—⁠ዕብራውያን 11:​4

በእነዚህ ወንድማማቾች መካከል የነበረው ልዩነት አቤል መንፈሳዊ ማስተዋል ሲኖረው ቃየን ግን የሌለው መሆኑ ብቻ አልነበረም። የአመለካከት ልዩነትም ነበራቸው። በዚህ ምክንያት “እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም።” ቃየን ስለሚያቀርበው መሥዋዕት በቁም ነገር ያሰበ አይመስልም። እንዲሁ ለይስሙላ የቀረበ መሥዋዕት ነበር። ሆኖም አምላክ ከአንገት በላይ የቀረበ የይስሙላ አምልኮ አያስደስተውም። ቃየን ልቡ ክፉ የነበረ ሲሆን ይሖዋም የውስጥ ዝንባሌው የተሳሳተ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። ቃየን ያቀረበው መሥዋዕት ተቀባይነት ሲያጣ የሰጠው ምላሽ ውስጣዊ ማንነቱን በግልጽ አሳይቷል። ቃየን የተሳሳተ አመለካከቱን ማስተካከል ሲገባው “እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ።” (ዘፍጥረት 4:​5) የሰጠው ምላሽ ክፉ ሐሳቡንና ዝንባሌውን የሚያጋልጥ ነበር።

የተሰጠው ማስጠንቀቂያና ያሳየው ስሜት

አምላክ የቃየን ዝንባሌ ስለገባው “ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፣ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት” በማለት ምክር ለገሰው።​—⁠ዘፍጥረት 4:​6, 7

እኛም ከዚህ የምናገኘው ትምህርት አለ። ኃጢአት እኛን ለመዋጥ በር ላይ አድብታ ትጠብቀናለች። ሆኖም አምላክ ነጻ ምርጫ ስለሰጠን ትክክል የሆነውን ለማድረግ መምረጥ እንችላለን። ይሖዋ ቃየን ‘መልካም እንዲያደርግ’ ከመምከር ውጪ ሐሳቡን እንዲለውጥ አላስገደደውም። ቃየን የራሱን መንገድ መርጧል።

በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ዘገባ ቀጥሎ “ቃየንም ወንድሙን አቤልን:- ና ወደ ሜዳ እንሂድ አለው። በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፣ ገደለውም” ይላል። (ዘፍጥረት 4:​8) ስለሆነም ቃየን እምቢተኛና ጨካኝ ነፍሰ ገዳይ ሆነ። ሌላው ቀርቶ ይሖዋ “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” ብሎ በጠየቀው ጊዜ ስለ ድርጊቱ ቅንጣት ታክል ጸጸት አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ ቃየን በደንታ ቢስነትና በማን አለብኝነት መንፈስ “አላውቅም፤ የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?” የሚል መልስ ሰጠ። (ዘፍጥረት 4:​9) ይህ ዓይን ያወጣ ቅጥፈትና ክህደት የቃየንን ጨካኝነት የሚያጋልጥ ነበር።

ይሖዋ ቃየንን በመርገም ከዔድን አካባቢ አባረረው። ቀደም ሲል ለምድር የተነገረው እርግማን ቃየን በተረገመ ጊዜ በተጠናከረ ሁኔታ የተደገመ ሲሆን ምድርን ባረሰ ጊዜ ፍሬዋን አትሰጠውም። በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ይሆናል። ቃየን ስለተበየነበት ፍርድ ክብደት ያሰማው ቅሬታ የወንድሙን ደም ለመበቀል ብለው እንደሚገድሉት ካደረበት ጭንቀት የመነጨ እንጂ ከልብ ንስሐ መግባቱን የሚያሳይ አይደለም። ይሖዋ ለቃየን “ምልክት” አደረገለት። ይህ ምልክት ቃየንን በበቀል ስሜት ተነሳስተው እንዳይገድሉት ታስቦ የተነገረ ሌሎች የሚያውቁትና የሚጠብቁት ድንጋጌ እንደሚሆን ይታመናል።​—⁠ዘፍጥረት 4:​10-15

ከዚያ በኋላ ቃየን “ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፤ ከዔድንም ወደ ምሥራቅ በኖድ ምድር ተቀመጠ።” (ዘፍጥረት 4:​16) ከእህቶቹ ካልሆነም ከወንድሙ ወይም ከእህቶቹ ልጆች መካከል አንዷን አግብቶ በበኩር ልጁ ስም ሄኖሕ ብሎ የሰየማትን ከተማ ቆረቆረ። በቃየን የትውልድ መሥመር የተወለደው ላሜሕ አምላካዊ ፍርሃት እንደሌለው እንደ ቃየን ዓመፀኛ ነበር። ይሁን እንጂ የቃየን የትውልድ መስመር በኖኅ የጥፋት ውኃ ተጠራርጎ ጠፍቷል።​—⁠ዘፍጥረት 4:​17-24

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት

ስለ ቃየንና አቤል ከሚናገረው ዘገባ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ሐዋርያው ዮሐንስ “ከክፉው እንደ ነበረ ወንድሙንም እንደ ገደለ እንደ ቃየል” እንዳይሆኑ ከዚህ ይልቅ እርስ በእርሳቸው እንዲዋደዱ ክርስቲያኖችን በጥብቅ አሳስቧቸዋል። ቃየን “የገዛ ሥራው ክፉ፣ የወንድሙም ሥራ ጽድቅ” ነበረ። በተጨማሪም ዮሐንስ “ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፣ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ” በማለት ተናግሯል። አዎን፣ ክርስቲያን ወንድሞቻችንን የምንይዝበት መንገድ ከአምላክ ጋር ያለንን ግንኙነት እንዲሁም የወደፊት ተስፋችንን ይነካል። የእምነት ወንድማችንን እየጠላን የአምላክን ሞገስ ማግኘት አንችልም።​—⁠1 ዮሐንስ 3:​11-15፤ 4:​20

ቃየንና አቤል ተመሳሳይ አስተዳደግ የነበራቸው ቢሆንም ቃየን በአምላክ ላይ እምነት አልነበረውም። እንዲያውም የመጀመሪያው ‘ነፍሰ ገዳይና የሐሰት አባት’ የሆነውን የዲያብሎስን መንፈስ አንጸባርቋል። (ዮሐንስ 8:​44) ቃየን የተከተለው መንገድ እያንዳንዳችን ምርጫ የማድረግ ነጻነት እንዳለን፣ ኃጢአትን የመረጡ ሰዎች ራሳቸውን ከአምላክ እንደሚለዩና ይሖዋ ንስሐ በማይገቡት ላይ የቅጣት ፍርዱን እንደሚያስፈጽም ያሳያል።

በሌላ በኩል አቤል በይሖዋ ላይ እምነት ነበረው። በእርግጥም “አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፣ በዚህም፣ እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር፣ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት።” ምንም እንኳ አቤል የተናገረው አንድም ቃል በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተመዝግቦ ባይገኝም በምሳሌነት ሊጠቀስ በሚችለው እምነቱ አማካኝነት “እስከ አሁን ይናገራል።”​—⁠ዕብራውያን 11:​4

አቤል ጽኑ አቋም ካሳዩት በርካታ ሰዎች መካከል የመጀመሪያው ነው። ‘ከምድር ወደ ይሖዋ የጮኸው’ ደሙ በከንቱ ፈስሶ አልቀረም። (ዘፍጥረት 4:​10፤ ሉቃስ 11:​48-51) እኛም እንደ አቤል ያለ እምነት የምናሳይ ከሆነ ከይሖዋ ጋር ውድና ዘላቂ ዝምድና መመሥረት እንችላለን።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ገበሬውና እረኛው

ምድርን ማረስና እንስሳትን መንከባከብ አምላክ በመጀመሪያ ለአዳም ከሰጠው ኃላፊነት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። (ዘፍጥረት 1:​28፤ 2:​15፤ 3:​23) ልጁ ቃየን ገበሬ ሲሆን አቤል ደግሞ እረኛ ሆነ። (ዘፍጥረት 4:​2) ይሁን እንጂ እስከ ጥፋት ውኃ ድረስ የሰው ዘር ለምግብነት ይጠቀም የነበረው ፍራፍሬና አትክልቶችን ብቻ ሆኖ ሳለ በግ ማርባት ለምን አስፈለገ?​—⁠ዘፍጥረት 1:​29፤ 9:​3, 4

በጎች በደንብ እንዲራቡ የሰው እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል። የአቤል ሥራ የሰው ልጅ እነዚህን የቤት እንስሳት ከሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ አንስቶ ያረባ እንደነበረ ምሥክር ያረጋግጣል። ቅዱሳን ጽሑፎች ከጥፋት ውኃ በፊት የኖሩ ሰዎች የእንስሳትን ወተት እንደ ምግብነት ይጠቀሙበት ነበር ወይስ አልነበረም በሚለው ጉዳይ ላይ ምንም የሚሰጡት ፍንጭ የለም። ሆኖም አትክልት ብቻ የሚመገቡ ሰዎችም እንኳ የበግን ሱፍ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። እንዲሁም አንድ በግ ሲሞት ሌጦው ጠቃሚ ለሆነ አገልግሎት ይውላል። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ለማልበስ “የቁርበትን ልብስ” ተጠቅሟል።​—⁠ዘፍ​ጥረት 3:​21

ያም ሆነ ይህ ቃየንና አቤል መጀመሪያ ላይ እርስ በርስ ይረዳዱ ነበር ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው። ለሌሎች የቤተሰቡ አባላት ለልብስነትና ለምግብነት የሚውሉ ነገሮች ያመርቱ ነበር።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቃየን “የገዛ ሥራው ክፉ፣ የወንድሙም ሥራ ጽድቅ ” ነበር