በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በተራራ ላይ ያለች ከተማ

በተራራ ላይ ያለች ከተማ

በተራራ ላይ ያለች ከተማ

ኢየሱስ ዝነኛ በሆነው የተራራ ስብከቱ ላይ ለደቀ መዛሙርቱ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም” ብሏቸው ነበር።​—⁠ማቴዎስ 5:14

ብዙዎቹ የይሁዳና የገሊላ ከተሞች ዝቅ ብሎ ከሚገኘው ሸለቋማ ቦታ ይልቅ በተራራዎች ላይ የተሠሩ ነበሩ። ከፍታ ቦታዎች የሚመረጡበት ዋነኛው ምክንያት ለደህንነት ሲባል ነው። ከወራሪ ጭፍሮች ሌላ አደጋ ጣዮችም የእስራኤላውያንን ሰፈሮች ያጠቁ ነበር። (2 ነገሥት 5:2፤ 24:2) ቆራጥ የሆኑ ነዋሪዎች ከአደጋ ለመከላከል ሲባል በረዥም ግንብ መታጠር ከሚያስፈልገው በዝቅተኛ ቦታ ላይ ከተሠራ ከተማ ይልቅ ችምችም ብለው በተራራ ጫፍ ላይ የተሠሩ ቤቶችን መጠበቅ ይበልጥ ቀላል ይሆንላቸዋል።

የአይሁዳውያን ቤቶች በአብዛኛው በኖራ የተለሰኑ ነበሩ። እነዚህ ነጭ የተቀቡና በተራራ ላይ ችምችም ብለው የተሠሩ በርካታ ቤቶች ከየትኛውም አቅጣጫ በቀላሉ ከርቀት ይታዩ ነበር። (ሥራ 23:3) ዓይን በሚያጥበረብረው የጳለስጢና ፀሐይ እነዚህ በከፍታ ቦታ ላይ የተሠሩ ከተሞች በባሕር ማማ ላይ እንደተተከለ መብራት ያበሩ ነበር። በዘመናችንም በሜዲትራንያን የሚገኙ ተመሳሳይ ከተሞች እንዲሁ ጎልተው ይታያሉ።

ኢየሱስ ይህን ትኩረት የሚስብ የገሊላና የይሁዳ የገጠር ከተሞች ገጽታ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ስለሚኖረው ድርሻ ለተከታዮቹ ለማስተማር ተጠቅሞበታል። “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 5:16) ምንም እንኳን ክርስቲያኖች መልካም ነገር የሚሠሩት በሌሎች ለመመስገን ብለው ባይሆንም የሚያሳዩት በጎ ጠባይ የሰዎችን ትኩረት መሳቡ አይቀርም።​—⁠ማቴዎስ 6:1

እንዲህ ዓይነቱ በጎ ጠባይ በተለይ በይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ጎልቶ ይታያል። በስፔይን የሚታተም አንድ ጋዜጣ በቅርብ ስለተደረገ የአውራጃ ስብሰባ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “በሌሎች ሃይማኖታዊ ቡድኖች ውስጥ ሰዎች ለሃይማኖታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ያላቸው ፍላጎት እየቀነሰ ቢሆንም በይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ዋጋማነቱን እንዲያጣ ስለማይፈልጉ የአምላክን ቃል በተግባር ያውሉታል።”

በሰሜናዊ ምዕራብ ስፔይን ምሥክሮቹ በተደጋጋሚ ጊዜያት የሚጠቀሙበት ስታዲየም ጠባቂ የሆነው ቶማስ የአምላክን ቃል ተግባራዊ ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር አብሮ መሆን ያስደስተው ነበር። በይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ወቅት ለመገኘት ሲል ጡረታ የሚወጣበትን ጊዜ በበርካታ ሳምንታት አራዘመው። ከስብሰባው በኋላ ትናንሽ ልጆችን ጨምሮ ብዙ ተሰብሳቢዎች ወደ እሱ ቀርበው ባለፉት ዓመታት ላሳየው የትብብር መንፈስ ሲያመሰግኑትና መልካም የጡረታ ጊዜ እንዲሆንለት እንደሚመኙ ሲነግሩት እንባውን አውጥቶ አለቀሰ። “በሕይወቴ ውስጥ ካጋጠሙኝ አስደሳች ሁኔታዎች አንዱ እናንተን ማወቄ ነው” ሲል ተናግሯል።

በተራራ ላይ የተሠራ ከተማ ከበስተጀርባው ካለው አድማስ አንጻር ጎልቶ ስለሚታይና በውስጡ ያሉ ነጫጭ ቤቶችም የፀሐይዋን ብርሃን ስለሚያንጸባርቁ የተመልካችን ትኩረት ይስባል። በተመሳሳይም እውነተኛ ክርስቲያኖች ከፍ ያሉትን የሐቀኝነት፣ የሥነ ምግባርና የርኅራኄ ቅዱስ ጽሑፋዊ መስፈርቶች ለመከተል ስለሚጥሩ ለየት ብለው ይታያሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ክርስቲያኖች በስብከት እንቅስቃሴያቸው አማካኝነት የእውነትን ብርሃን ያበራሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ምሕረት እንደ ተሰጠን መጠን ይህ አገልግሎት ስላለን አንታክትም። . . . እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን።” (2 ቆሮንቶስ 4:1, 2) የስብከት ሥራቸውን በሚያከናውኑባቸው ቦታዎች ሁሉ ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም ይሖዋ አገልግሎታቸውን ባርኮላቸው ስለነበረ በ60 እዘአ አካባቢ ጳውሎስ ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ” ተሰብኳል ብሎ ሊጽፍ ችሏል።​—⁠ቆላስይስ 1:23

ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ እንዳዘዘው ‘ብርሃናቸውን በሰው ፊት የማብራት’ ኃላፊነታቸውን በቁም ነገር ይመለከቱታል። በቃላቸውና በጽሑፎች አማካኝነት የመንግሥቱን ምሥራች በዓለም ዙሪያ በ235 አገሮች ያሰራጫሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ የእውነት ብርሃን የሚቻለውን ያህል ለብዙ ሰዎች እንዲዳረስ ለማድረግ ጽሑፎቻቸውን ወደ 370 በሚጠጉ ቋንቋዎች አዘጋጅተዋል።​—⁠ማቴዎስ 24:14፤ ራእይ 14:6, 7

በብዙ ቦታዎች ምሥክሮቹ የስብከቱ ሥራ ከታገደባቸው ወይም ታግዶባቸው ከነበሩ ቦታዎች የተሰደዱ ሰዎችን ቋንቋ በመማር ተፈታታኝ የሆነ ተግባር ያከናውናሉ። ለምሳሌ ያህል ከቻይናና ከሩስያ የመጡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ወደ አብዛኞቹ የሰሜን አሜሪካ ትላልቅ ከተሞች እየጎረፉ ነው። የአገሩ ተወላጅ የሆኑ ምሥክሮች ለአዲሶቹ ሰዎች መልካሙን የምሥራች ለማካፈል ሲሉ የቻይና፣ የሩስያና የሌሎች አገሮችን ቋንቋዎች ለመማር ጥረት አድርገዋል። እንዲያውም አዝመራው ‘ነጥቶ እያለ’ ምሥራቹን ለሌሎችም ለመስበክ እንዲቻል የመማሩን ሂደት የሚያፋጥኑ ኮርሶች በብዙ ቋንቋዎች እየተሰጡ ነው።​—⁠ዮሐንስ 4:35

ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ተንብዮ ነበር:- “በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፣ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፣ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ።” የይሖዋ ምሥክሮች በምግባራቸውና በአገልግሎታቸው በሁሉም ቦታ ያሉ ሰዎች ወደ “እግዚአብሔር ቤት ተራራ” እንዲመጡና ስለ አምላክ መንገዶች እንዲያውቁ እንዲሁም በአምላክ ጎዳና ላይ መጓዝ እንዲማሩ እየረዱ ነው። (ኢሳይያስ 2:2, 3) ይህ ሥራ የሚያስገኘው አስደሳች ውጤት ኢየሱስ እንደተናገረው በህብረት ሆነው “በሰማያት ያለውን አባታቸውን” ይሖዋ አምላክን ማስከበራቸው ነው።​—⁠ማቴዎስ 5:16፤ 1 ጴጥሮስ 2:12