በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንጽሕና ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

ንጽሕና ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

ንጽሕና ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

ብዙ ሰዎች ንጽሕና ለሚለው ቃል የሚሰጡት ፍቺ የተለያየ ነው። ለምሳሌ አንድ ትንሽ ልጅ እናቱ እጁንና ፊቱን እንዲታጠብ ስትነግረው ጣቶቹን ውኃ ማስነካቱና ከንፈሩን በውኃ ማበሱ ብቻ በቂ እንደሆነ ይሰማው ይሆናል። ይሁን እንጂ እናቱ የተሻለ ስለምታውቅ እየጮኸም ቢሆን ወደ ቧንቧው ትወስደውና እጁንና ፊቱን በሳሙና ሙልጭ አድርጋ ታጥበዋለች!

እርግጥ የንጽሕና አጠባበቅ ደንቦች ከቦታ ቦታ ይለያያሉ። በተጨማሪም ሰዎች እንደየአስተዳደጋቸው ስለ ንጽሕናም የተለያየ አመለካከት ይኖራቸዋል። ባለፉት ጊዜያት በብዙ አገሮች የሚገኙ ንጹሕና ሥርዓታማ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ጥሩ የንጽሕና ልማድ እንዲያዳብሩ ረድተዋቸዋል። በዛሬው ጊዜ ግን የአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ በጣም ከመቆሸሹ የተነሣ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ እንጂ የመጫወቻ አሊያም የሰውነት እንቅስቃሴ መሥሪያ ቦታ አይመስልም። ስለ መማሪያ ክፍሎችስ ምን ለማለት ይቻላል? አውስትራሊያ በሚገኝ አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በጽዳት ክፍል የምትሠራው ዳረን የሚከተለውን አስተውላለች:- “በአሁኑ ጊዜ በክፍል ውስጥ አስጸያፊ ቆሻሻዎች ተጥለው ማየታችን የተለመደ ሆኗል።” አንዳንድ ተማሪዎች “አንሳው” ወይም “አጽዳው” የሚለውን መመሪያ እንደ ቅጣት አድርገው ይወስዱታል። የዚህ መንስኤ ደግሞ አንዳንድ አስተማሪዎች ማጽዳትን እንደ መቅጫ አድርገው መጠቀማቸው ነው።

በሌላው በኩል ደግሞ በንግዱ ዓለምም ሆነ በሌላ በማንኛውም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አዋቂዎች በንጽሕና ረገድ ሁልጊዜ ጥሩ ምሳሌዎች ሆነው አይገኙም። ለምሳሌ ያህል አብዛኞቹ ሕዝብ የሚበዛባቸው ቦታዎች የቆሸሹና ለማየት የሚያስቀይሙ ናቸው። አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች አካባቢን ይበክላሉ። ይሁን እንጂ የብክለት መንስኤዎች ዝቃጭ የሚያወጡ ኢንዱስትሪዎችና የንግድ ተቋማት ሳይሆኑ ሰዎች ናቸው። ምናልባት ዓለም አቀፍ ችግር ለሆነው ለብክለትና ከዚህ ጋር ተያይዘው ለሚመጡት ችግሮች ዋነኛ መንስኤ ስግብግብነት ሊሆን ቢችልም ንጽሕናን ያለመጠበቅ ልማድ ለችግሩ ከፊል አስተዋጽኦ አድርጓል። የቀድሞው የአውስትራሊያ የጋራ ብልጽግና አባል አገራት ዋና ዲሬክተር “የኅብረተሰብ ጤና የተመካው ወንድ፣ ሴት ሕፃን ሳይል እያንዳንዱ ሰው ንጽሕናውን በመጠበቁ ነው” በማለት ይህንን ሐሳብ የሚያጠናክር አስተያየት ሰንዝረዋል።

ይሁን እንጂ ዛሬም ቢሆን አንዳንዶች ንጽሕና የግል ጉዳይ እንደሆነና ማንኛውንም ሰው ሊመለከተው እንደማይገባ ይሰማቸዋል። ነገሩ በእርግጥ እንደዚያ ነው?

የምንበላው ምግብ ከገበያ የገዛነውም ይሁን፣ በሆቴል አሊያም በወዳጃችን ቤት የምንመገበው ንጹሕ መሆን እንደሚገባው ጥርጥር የለውም። የምንበላውን ምግብ የሚያዘጋጁም ሆኑ የሚያቀርቡ ሰዎች በጣም ንጹሕ መሆን አለባቸው። የእነርሱም ሆነ የእኛ እጅ የቆሸሸ ከሆነ ብዙ በሽታዎችን ሊያስከትል ይችላል። ከማንኛውም ቦታ ይልቅ ንጹሕ ሊሆን ይገባል ብለን ስለምናስበው ሆስፒታልስ ምን ለማለት ይቻላል? ታካሚዎች ለኢንፌክሽን የሚጋለጡትና በዚህ ሳቢያ በዓመት እስከ 10 ቢልዮን ዶላር የሚወጣው እጃቸውን የማይታጠቡ አንዳንድ ዶክተሮችና ነርሶች በመኖራቸው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ዘ ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦቭ ሜድስን ሪፖርት አድርጓል። በንጽሕና አጠባበቅ ረገድ ግዴለሽ የሆነ ማንኛውም ሰው ጤንነታችንን አደጋ ላይ እንዳይጥልብን መጠንቀቃችን የተገባ ነው።

በተጨማሪም አንድ ሰው ሆን ብሎ አሊያም በግዴለሽነት የውኃ አቅርቦታችንን ቢበክልብን ይህ እንዲሁ በቀላሉ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። እንዲሁም የዕፅ ሱሰኞች ወይም ሌሎች ተጠቅመው የጣሉዋቸው መርፌዎች በየቦታው በሚታዩበት የባሕር ዳርቻ በባዶ እግር መንሸራሸሩስ ምን ያህል ያስተማምናል? ምናልባትም ንጽሕና በራሳችን ቤት ውስጥ ይተገበራል? የሚለውን ጥያቄ በግላችን መጠየቅ ይኖርብን ይሆናል።

ሱለን ሆይ ቼሲንግ ደርት በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ “በውኑ እንደ ድሮው ንጹሖች ነን?” በማለት ጠይቀዋል። ሲመልሱም “አይመስለኝም” ብለዋል። ለዚህ እንደ ዋነኛ መንስኤ አድርገው የጠቀሱት በማኅበራዊ እሴቶች ረገድ የተደረገውን ለውጥ ነው። ሰዎች በቤት የሚያሳልፉት ጊዜ እያነሰ በመምጣቱ ገንዘብ በመክፈል ቤታቸውን ሌላ ሰው እንዲያጸዳላቸው ያደርጋሉ። ከዚህም የተነሣ የአካባቢን ንጽሕና የመጠበቁ ጉዳይ ቸል እየተባለ መጥቷል። አንድ ግለሰብ “ራሴን እንጂ መታጠቢያ ቤቱን አላጸዳም” በማለት ተናግሯል። “ቤቴ ቢቆሽሽም እኔ ንጹሕ ነኝ።”

ይሁን እንጂ ንጽሕና ሲባል ከውጪ ንጹሕ ሆኖ መታየት ማለት ብቻ አይደለም። የጤናማ አኗኗር አጠቃላይ ገጽታን የሚያካትት ግብረገብ ነው። ሥነ ምግባራችንንና አምልኳችንን የሚያካትት የአእምሮና የልብ ሁኔታም ጭምር ነው። እስቲ ይህ የሆነበትን ምክንያት እንመልከት።