በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ከሚወድዳቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነህን?

አምላክ ከሚወድዳቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነህን?

አምላክ ከሚወድዳቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነህን?

“ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል።”​ዮሐንስ 14:21

 ይሖዋ ሰብዓዊ ፍጥረታቱን ይወድዳቸዋል። እንዲያውም “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ” የሰውን ዘር ዓለም ይወድዳል። (ዮሐንስ 3:16) የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል የሚከበርበት ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ እውነተኛ ክርስቲያኖች ይሖዋ ‘ስላሳየን ፍቅርና ለኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን ስለ መላኩ’ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ሊያስቡ ይገባል።​—⁠1 ዮሐንስ 4:10

2 ኢየሱስና 12 ሐዋርያቱ ኒሳን 14, 33 እዘአ ምሽት ላይ እስራኤላውያን ከግብፅ ነፃ የወጡበትን የፋሲካን በዓል ለማክበር ኢየሩሳሌም በሚገኝ በአንድ ደርብ ተሰብሰቡ። (ማቴዎስ 26:17-20) ይህን የአይሁዳውያንን በዓል አክብረው ከጨረሱ በኋላ ኢየሱስ የአስቆሮቱ ይሁዳን አሰናበተና ክርስቲያኖች የሚያከብሩትን የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ እራት አቋቋመ። a ኢየሱስ ሥጋውንና ደሙን ለማመልከት ያልቦካ ቂጣና ቀይ ወይን እንደ ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም ከተቀሩት ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ይህን እራት ተቋደሰ። የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ የወንጌል ጸሐፊዎች ማለትም ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ እንዲሁም በዓሉን “የጌታ እራት” በማለት የሰየመው ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ በዓሉን እንዴት እንዳከበረ የሚገልጽ ዝርዝር መግለጫ ሰጥተዋል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 11:20፤ ማቴዎስ 26:26-28፤ ማርቆስ 14:22-25፤ ሉቃስ 22:19, 20

3 ሐዋርያው ዮሐንስ ቂጣና ወይን ስለመዞሩ ምንም የገለጸው ነገር አለመኖሩ ትኩረት የሚስብ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ምናልባት የወንጌል ዘገባውን በጻፈበት ጊዜ (በ98 እዘአ አካባቢ) የበዓሉ አከባበር ሥርዓት በጥንት ክርስቲያኖች ዘንድ በደንብ ይታወቅ ስለነበረ ሊሆን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 11:23-26) ይሁን እንጂ ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ በዓል ከማቋቋሙ ትንሽ ቀደም ብሎና ካቋቋመ በኋላ ወዲያው ስላከናወናቸውና ስለተናገራቸው ነገሮች በመንፈስ አነሳሽነት ጠቃሚ መረጃ ያሠፈረልን ዮሐንስ ብቻ ነው። እነዚህ ስሜት ቀስቃሽ ዝርዝር ዘገባዎች በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ከአምስት ያላነሱ ምዕራፎችን ይዘዋል። አምላክ ምን ዓይነት ሰዎችን እንደሚወድ የማያሻማ ማብራሪያ ይሰጣሉ። እስቲ ከዮሐንስ 13 እስከ 17 ያሉትን ምዕራፎች እንመርምር።

ምሳሌ ከሚሆነው የኢየሱስ ፍቅር ተማሩ

4 ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጠውን የመሰነባበቻ ምክር በያዙት በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ዋነኛው ጭብጥ ፍቅር ነው። እንዲያውም በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ “ፍቅር” የሚለው ቃል በተለያዩ መንገዶች 31 ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። ኢየሱስ ለአባቱና ለደቀ መዛሙርቱ ያለውን ፍቅር የእነዚህን ምዕራፎች ያህል ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ ሌላ ምዕራፍ የለም። ኢየሱስ ለይሖዋ ፍቅር እንዳለው የሚገልጹ ሐሳቦችን ከሌሎቹ ወንጌሎች ማንበብ ቢቻልም ኢየሱስ ‘አብን እወደዋለሁ’ በማለት በግልጽ መናገሩን የዘገበው ዮሐንስ ብቻ ነው። (ዮሐንስ 14:31) በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ይሖዋ እንደሚወድደውና የሚወድደውም ለምን እንደሆነ ምክንያቱን ተናግሯል። እንዲህ አለ:- “አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፣ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ።” (ዮሐንስ 15:9, 10) አዎን፣ ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ታዛዥ ስለሆነ ይሖዋ ይወድደዋል። ለሁሉም የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ይህ እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ነው!

5 ኢየሱስ ለተከታዮቹ ያለው ጥልቅ ፍቅር ከሐዋርያቱ ጋር ስላደረገው የመጨረሻ ስብሰባ በሚተርከው በዮሐንስ ዘገባ መክፈቻ ላይ ጎላ ብሎ ሰፍሯል። ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይተርካል:- “ከፋሲካ በዓል በፊት፣ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፣ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው።” (ዮሐንስ 13:1) በዚያ የማይረሳ ምሽት ኢየሱስ በፍቅር ሌሎችን ማገልገልን በሚመለከት ምንጊዜም የማይረሱት ትምህርት ሰጣቸው። እግራቸውን አጠበ። ይህ እያንዳንዳቸው በፈቃደኝነት መንፈስ ተነሳስተው ለኢየሱስም ሆነ ለወንድሞቻቸው ሊያደርጉት የሚገባ ተግባር ነበር። ሆኖም አንዳቸውም አላደረጉትም። ኢየሱስ ይህን ትሕትና የሚጠይቅ ተግባር ካከናወነ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው:- “እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና።” (ዮሐንስ 13:14, 15) እውነተኛ ክርስቲያኖች በፈቃደኝነትና በደስተኝነት መንፈስ ተነሳስተው ወንድሞቻቸውን ማገልገል ይገባቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 20:26, 27፤ ዮሐንስ 13:17

አዲሱን ትእዛዝ መከተል

6 የአስቆሮቱ ይሁዳ ከመካከላቸው ተለይቶ እንደወጣ የሚገልጸውን ዘገባ የምናገኘው ዮሐንስ በኒሳን 14 ምሽት በደርብ ውስጥ ስለተከናወነው ነገር ባሰፈረው ዘገባ ውስጥ ብቻ ነው። (ዮሐንስ 13:21-30) የወንጌል ዘገባዎችን በማነጻጸር መገንዘብ እንደሚቻለው ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ ያቋቋመው ይህ ከሃዲ ከወጣ በኋላ ነው። ከዚያም የመሰነባበቻ ምክርና መመሪያዎችን በመስጠት ለታማኝ ሐዋርያቱ ረዘም ያለ ንግግር አደረገ። በመታሰቢያው በዓል ላይ ለመገኘት በምንዘጋጅበት ጊዜ ኢየሱስ በበዓሉ ላይ ስለተናገራቸው ነገሮች አጥብቀን ልናስብ ይገባል። በተለይ ይህን የምናደርገው አምላክ ከሚወድዳቸው ሰዎች መካከል መሆን ስለምንፈልግ ነው።

7 ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ በዓል ካቋቋመ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው የመጀመሪያ መመሪያ አዲስ ነበር። እንዲህ አለ:- “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፣ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐንስ 13:34, 35) ይህንን ትእዛዝ አዲስ የሚያሰኘው ምንድን ነው? በዚያው ምሽት ትንሽ ቆየት ብሎ ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ አድርጎታል:- “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት። ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።” (ዮሐንስ 15:12, 13) የሙሴ ሕግ እስራኤላውያን ‘ባልንጀራቸውን እንደ ራሳቸው አድርገው እንዲወድዱ’ ያዝዝ ነበር። (ዘሌዋውያን 19:18) ሆኖም የኢየሱስ ትእዛዝ ከዚያ አልፎ የሚሄድ ነበር። ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን ለወንድሞቻቸው መሥዋዕት አድርገው ለማቅረብ ፈቃደኞች እስከ መሆን ድረስ ክርስቶስ እንደወደዳቸው እርስ በርሳቸው መዋደድ ነበረባቸው።

8 የመታሰቢያ በዓል ሰሞን እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለይቶ የሚያሳውቀው ይህ ምልክት ማለትም የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር በእርግጥ ያለን መሆናችንንና አለመሆናችንን ለማረጋገጥ በግለሰብም ሆነ በጉባኤ ደረጃ ራሳችንን የምንመረምርበት ተስማሚ ጊዜ ነው። እንዲህ ያለው የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር ወንድሞቻችንን አሳልፎ ከመስጠት ይልቅ ሕይወታችንን ለእነርሱ አሳልፎ መስጠትን የሚጠይቅ ነው፤ ደግሞም የጠየቀባቸው ጊዜያት አሉ። ሆኖም ብዙውን ጊዜ ወንድሞቻችንንና ሌሎች ሰዎችን ለመርዳትና ለማገልገል ስንል የግል ጥቅማችንን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆንን የሚጠይቅ ነው። በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። (2 ቆሮንቶስ 12:15፤ ፊልጵስዩስ 2:17) የይሖዋ ምሥክሮች ወንድሞቻቸውንና ጎረቤቶቻቸውን ለመርዳትና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች ለመንገር በሚያሳዩት የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ በዓለም ዙሪያ የታወቁ ናቸው። b​—⁠ገላትያ 6:10

ከፍ ተደርጎ ሊታይ የሚገባው ዝምድና

9 የይሖዋንና የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር ከማግኘት የበለጠ ውድ ነገር የለም። ይሁን እንጂ ከእነርሱ ይህን ፍቅር ለማግኘትና እንዳገኘነውም እንዲሰማን አንድ ነገር ማድረግ ይገባናል። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ባሳለፈው በዚያች የመጨረሻ ምሽት እንዲህ አለ:- “ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ።” (ዮሐንስ 14:21) ከአምላክና ከልጁ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ከፍ አድርገን ስለምንመለከተው የሚያዙንን ሁሉ በደስታ እንፈጽማለን። ይህም የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር እንድናሳይ የሚያዘውን አዲስ ትእዛዝና ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ‘ለሕዝብ እንድንሰብክና የተሟላ ምሥክርነት እንድንሰጥ’ እንዲሁም ምሥራቹን የተቀበሉትን “ደቀ መዛሙርት” እንድናደርግ የሰጠውን ትእዛዝ መፈጸምንም ይጨምራል።​—⁠ሥራ 10:42፤ ማቴዎስ 28:19, 20

10 በዚያን ዕለት ሌሊት ኢየሱስ ታማኙ ሐዋርያ ይሁዳ (ታዴዎስ) ላቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ እንዲህ አለ:- “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን።” (ዮሐንስ 14:22, 23) በሰማይ ከክርስቶስ ጋር እንዲገዙ የተጠሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምድር እያሉም እንኳ ከይሖዋ እና ከልጁ ጋር ልዩ የሆነ የቀረበ ዝምድና አላቸው። (ዮሐንስ 15:15፤ 16:27፤ 17:22፤ ዕብራውያን 3:1፤ 1 ዮሐንስ 3:2, 24) ታዛዥ የሆኑት በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑት ጓደኞቻቸውም ‘አንድ እረኛ’ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ እና አምላካቸው ከሆነው ከይሖዋ ጋር ውድ የሆነ ዝምድና አላቸው።​—⁠ዮሐንስ 10:16፤ መዝሙር 15:1-5፤ 25:14

‘የዓለም ክፍል አይደላችሁም’

11 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ከታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ባደረገው በዚህ የመጨረሻ ስብሰባ ላይ አንድ ሰው በአምላክ ዘንድ ሲወደድ በዓለም ጥላቻ እንደሚያተርፍ በመግለጽ ትኩረት የሚስብ ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው። እንዲህ አለ:- “ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። ባርያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ።”​—⁠ዮሐንስ 15:18-20

12 ኢየሱስ ይህን ማስጠንቀቂያ የሰጠው እነዚህ 11 ሐዋርያትም ሆኑ ከእነርሱ በኋላ የሚመጡት ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ዓለም ጠላን ብለው ተስፋ እንዳይቆርጡና እጅ እንዳይሰጡ በማሰብ ነው። በተጨማሪም እንዲህ አለ:- “እንዳትሰናከሉ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። ከምኵራባቸው ያወጡአችኋል፤ ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል። ይህንም የሚያደርጉባችሁ አብንና እኔን ስላላወቁ ነው።” (ዮሐንስ 16:1-3) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደገለጸው እዚህ ላይ “መሰናከል” ተብሎ የተተረጎመው ግስ አገባብ “አንድ ሰው ሊያምነውና ሊታዘዘው በሚገባው አንድ አካል ላይ እንዲጠራጠር እንዲሁም እንዲከዳ ማድረግ” የሚል ትርጉም አለው። የመታሰቢያውን በዓል የምናከብርበት ዕለት እየተቃረበ ሲመጣ ሁላችንም ጥንትም ሆነ ዛሬ የታመኑ ሰዎች የተከተሉትን የሕይወት ጎዳና ማሰላሰልና በመከራ ጊዜ ያሳዩትን የጽናት ምሳሌ መኮረጅ ይኖርብናል። የሚደርስብህ ተቃውሞ ወይም ስደት ይሖዋንና ኢየሱስን ትተህ እንድትሄድ እንዲያደርግህ አትፍቀድ። ከዚያ ይልቅ በእነርሱ ላይ ለመታመንና እነርሱን ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።

13 ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ከሚገኘው ከዚያ ደርብ ወጥቶ ከመሄዱ በፊት ባቀረበው የመደምደሚያ ጸሎት ለአባቱ እንዲህ አለ:- “እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው። ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም በእውነትህ ቀድሳቸው።” (ዮሐንስ 17:14-16) ይሖዋ የሚወድዳቸውን እንደሚጠብቅና ከዓለም ተለይተው ለመኖር ጥረት ሲያደርጉ ብርታት እንደሚሰጣቸው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።​—⁠ኢሳይያስ 40:29-31

በአባት ፍቅርና በልጅ ፍቅር መኖር

14 ኢየሱስ ኒሳን 14 ምሽት ከታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ባደረገው ውይይት ራሱን ‘እውነተኛ የወይን ግንድ’ እንደሆነ አድርጎ ሲገልጽ ታማኝ ሳይሆኑ የቀሩትን እስራኤላውያን ደግሞ ‘የተበላሸ ወይን’ እንደሆኑ አድርጎ ገልጿል። “እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው” በማለት ተናገረ። (ዮሐንስ 15:1) ኤርምያስ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ይሖዋ ለከዳተኛ ሕዝቡ “እኔ የተመረጠች ወይን . . . አድርጌ ተክዬሽ ነበር፤ አንቺ ግን ክፉ የእንግዳ ወይን ግንድ ሆነሽ እንዴት ተለወጥሽብኝ?” በማለት የተናገራቸውን ቃላት መዝግቧል። (ኤርምያስ 2:21) እንዲሁም ነቢዩ ሆሴዕ “እስራኤል ፍሬው የተበላሸ ወይን ነው፤ ለራሱ ብዙ ፍሬ አፈራ። . . . ልባቸው ግብዝ ሆነ” በማለት ጽፏል።​—⁠ሆሴዕ 10:1, 2 NW

15 እስራኤል የእውነተኛውን አምልኮ ፍሬ ከማፍራት ይልቅ ከሃዲ ሆነችና የራሷን ፍሬ ማፍራት ጀመረች። ኢየሱስ ከታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ከመገናኘቱ ከሦስት ቀናት ቀደም ብሎ ግብዝ የነበሩትን አይሁዳውያን መሪዎች “እላችኋለሁ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 21:43) ይህ አዲስ ብሔር 144, 000 ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ያቀፈውና ‘የእውነተኛው ወይን ግንድ’ የኢየሱስ ክርስቶስ ‘ቅርንጫፍ’ እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸው ‘የአምላክ እስራኤል’ ነው።​—⁠ገላትያ 6:16፤ ዮሐንስ 15:5፤ ራእይ 14:1, 3

16 ኢየሱስ በዚያ ደርብ ውስጥ አብረውት ለነበሩት 11 ሐዋርያት እንዲህ አላቸው:- “ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግድዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፣ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም።” (ዮሐንስ 15:2, 4) ዘመናዊው የይሖዋ ሕዝቦች ታሪክ እንደሚያሳየው የቅቡዓን ክርስቲያኖች ታማኝ ቀሪዎች ራሳቸው ከሆነው ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ተስማምተው ኖረዋል። (ኤፌሶን 5:23) የተወሰደውን የማንጻትና የማጥራት እርምጃ ተቀብለዋል። (ሚልክያስ 3:2, 3) ከ1919 አንስቶ በመጀመሪያ ሌሎች ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ከዚያም ከ1935 ጀምሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣውን “እጅግ ብዙ ሰዎች” የሆኑትን ጓደኞቻቸውን በመሰብሰብ የመንግሥቱን ፍሬ በብዛት አፍርተዋል።​—⁠ራእይ 7:9፤ ኢሳይያስ 60:4, 8-11

17 ኢየሱስ ቀጥሎ የተናገራቸው ቃላት ለቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆነ ለጓደኞቻቸው በሙሉ ይሠራሉ:- “ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል። አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፣ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ።”​—⁠ዮሐንስ 15:8-10

18 ሁላችንም በአምላክ ፍቅር ውስጥ መኖር እንፈልጋለን። ይህም ፍሬ የምናፈራ ክርስቲያኖች እንድንሆን ያንቀሳቅሰናል። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ በመስበክ ይህንን እናደርጋለን። (ማቴዎስ 24:14) እንዲሁም በግል ሕይወታችን “የመንፈስ ፍሬ” ለማንጸባረቅ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። (ገላትያ 5:22, 23) በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ መገኘት ይህን ለማድረግ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ የሚያጠነክርልን ከመሆኑም በላይ አምላክና ክርስቶስ ለእኛ ያላቸውን ታላቅ ፍቅር እንድናስታውስ ይረዳናል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 5:14, 15

19 ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ካቋቋመ በኋላ አባቱ ለታማኝ አገልጋዮቹ ‘ረዳት የሆነውን መንፈስ ቅዱስ’ እንደሚልክላቸው ቃል ገባላቸው። (ዮሐንስ 14:26 NW ) ቅቡዓንና ሌሎች በጎች በይሖዋ ፍቅር ውስጥ እንዲኖሩ ይህ መንፈስ የሚረዳቸው እንዴት እንደሆነ በሚቀጥለው ርዕስ እንመረምራለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በመጽሐፍ ቅዱስ አቆጣጠር መሠረት በ2002 ኒሳን 14 የሚጀምረው ሐሙስ፣ መጋቢት 28 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ነው። በዚህ ዕለት ምሽት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት ለማሰብ ይሰበሰባሉ።

b የይሖዋ ምሥክሮች —⁠የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች (እንግሊዝኛ) የተባለውን የይሖዋ ምሥክሮች ያሳተሙትን መጽሐፍ ምዕራፍ 19 እና 32ን ተመልከት።

የክለሳ ጥያቄዎች

• በፍቅር ተነሳስቶ ማገልገልን በሚመለከት ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ተግባራዊ የሆነ ትምህርት ሰጣቸው?

• የመታሰቢያው በዓል ሰሞን ራስን ለመመርመር ተስማሚ ጊዜ የሚሆነው በምን ረገድ ነው?

• ኢየሱስ ዓለም ጥላቻና ስደት እንደሚያደርስብን በሰጠው ማስጠንቀቂያ መደናቀፍ የማይኖርብን ለምንድን ነው?

• ‘እውነተኛው የወይን ግንድ’ ማን ነው? ‘ቅርንጫፎቹ’ እነማን ናቸው? ምንስ ይጠበቅባቸዋል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

1, 2. (ሀ) ይሖዋ ለሰው ዘር ፍቅር እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ኒሳን 14, 33 እዘአ ምሽት ምን አቋቋመ?

3. ኢየሱስ በደርብ ውስጥ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ስላሳለፋቸው የመጨረሻ ሰዓታት የሚገልጸው የዮሐንስ ዘገባ ከሌሎቹ የሚለየው አስፈላጊ በሆኑ በምን መንገዶች ነው?

4. (ሀ) ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ባቋቋመበት ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ያደረገውን ስብሰባ ዋና ጭብጥ ዮሐንስ ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ኢየሱስን እንዲወድደው ያደረገው አንዱ ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?

5. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ፍቅር እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

6, 7. (ሀ) የመታሰቢያውን በዓል መቋቋም በማስመልከት ዮሐንስ ምን አስፈላጊ የሆነ ዝርዝር ዘገባ አስፍሯል? (ለ) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው አዲስ ትእዛዝ ምንድን ነው? አዲስ ያሰኘውስ ምንድን ነው?

8. (ሀ) የራሱን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር ምን ማድረግን ይጨምራል? (ለ) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር የሚያሳዩት እንዴት ነው?

9. ከአምላክና ከልጁ ጋር የመሠረትነውን ውድ ዝምድና ጠብቀን ለማቆየት ስለምንፈልግ ምን ለማድረግ ደስተኞች ነን?

10. ቅቡዓንና ‘ሌሎች በጎች’ ምን ውድ ዝምድና አግኝተዋል?

11. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ትኩረት የሚስብ ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው?

12. (ሀ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ዓለም እንደሚጠላቸው ያስጠነቀቃቸው ለምንድን ነው? (ለ) የመታሰቢያው በዓል እየተቃረበ ሲመጣ ሁላችንም ስለ ምን ነገር ማሰባችን ጥሩ ይሆናል?

13. ኢየሱስ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ተከታዮቹን በተመለከተ ምን ብሎ ለመነ?

14, 15. (ሀ) ‘ከተበላሸው ወይን’ ጋር በማነጻጸር ኢየሱስ ራሱን ከምን ጋር አመሳስሏል? (ለ) ‘የእውነተኛው ወይን ግንድ’ ‘ቅርንጫፎች’ እነማን ናቸው?

16. ኢየሱስ አሥራ አንዱን ታማኝ ሐዋርያት ምን እንዲያደርጉ አጥብቆ አሳስቧቸዋል? በዚህ የመጨረሻ ዘመን ስላሉት ታማኝ ቀሪዎችስ ምን ለማለት ይቻላል?

17, 18. (ሀ) ቅቡዓንም ሆኑ ሌሎች በጎች በይሖዋ ፍቅር ውስጥ መኖራቸውን እንዲቀጥሉ የትኞቹ ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ይረዷቸዋል? (ለ) በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘትስ የሚረዳን እንዴት ነው?

19. በሚቀጥለው ርዕስ ረዳት ስለሆነ ምን ነገር እንመለከታለን?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ሌሎችን በፍቅር ስለማገልገል ለሐዋርያቱ የማይረሳ ትምህርት ሰጥቷቸዋል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር እንዲያሳዩ የሰጣቸውን ትእዛዝ ያከብራሉ