በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንደ አቅማቸው ጠቢባን ናቸው

እንደ አቅማቸው ጠቢባን ናቸው

እንደ አቅማቸው ጠቢባን ናቸው

አንድ የናይጄርያ ምሳሌ “ወላጆች ጥበብ እንዳላቸው ሁሉ ልጆችም እንደ አቅማቸው ጠቢባን ናቸው” ይላል። ኤድወን የተባለ በናይጄርያ የሚኖር ክርስቲያን ሽማግሌ ይህ ምሳሌ እውነት መሆኑን ተገንዝቦአል።

አንድ ቀን ኤድወን እቤቱ ከጠረጴዛው ሥር የብረት ሣጥን ያገኛል።

ኤድወን “ይሄ የማን ነው?” ሲል ሦስቱን ልጆቹን ጠየቃቸው።

የስምንት ዓመቱ ኢማኑዌል “የኔ ነው” ብሎ መለሰ። አክሎም ይህ አናቱ ላይ ቀዳዳ ያለውና 12 ሴንቲ ሜትር በ12 ሴንቲ ሜትር የሆነ የዛገ የብረት ሣጥን ለዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ አስተዋጽኦ ማድረጊያ መሆኑን ፈጠን ብሎ ይነግረዋል። “ወደ መንግሥት አዳራሹ በየቀኑ ስለማልሄድ ለሻይ ከሚሰጠኝ ገንዘብ የሚተርፈኝን የማስቀምጥበት ሣጥን ለመሥራት ወሰንኩ” ሲል አስረዳው።

የኢማኑዌል አባት ዓመታዊውን የአውራጃ ስብሰባ ለመካፈል የሚያስችል ገንዘብ ለማጠራቀም ብሎ ያዘጋጀው ሣጥን ነበረው። ይሁን እንጂ ቤተሰቡ አጣዳፊ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው በሣጥኑ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ ተጠቅመውበት ነበር። ኢማኑዌል አስተዋጽኦ ያደረገው ገንዘብ ለሌላ ዓላማ እንዳይውል ማድረግ ስለፈለገ ገንዘቡን ሊያጠራቅምበት ያሰበውን አሮጌ ጣሳ ይዞ ወደ አንድ በያጅ ይሄድና አናቱን እንዲደፍንለት ይጠይቀዋል። በያጁ ጣሳው የተፈለገበትን ዓላማ ሲረዳ ከወዳደቀ ብረታ ብረት ለኢማኑዌል ሣጥን ሠራለት። የኢማኑዌል ወንድም የሆነው የአምስት ዓመቱ ማይክልም ተመሳሳይ ሣጥን እንደሚፈልግ ተናገረ።

ልጆቹ ባደረጉት ነገር የተደነቀው ኤድወን ሣጥኖቹን ለምን እንዳሠሩ ይጠይቃቸዋል። ማይክል “አስተዋጽኦ ማድረግ ስለምፈልግ ነው!” ሲል መለሰ።

ወላጆቻቸው ሳያውቁ ኢማኑዌል፣ ማይክልና ዘጠኝ ዓመት የሆናት እህታቸው ዩቼ ለሻይ ከሚሰጣቸው ገንዘብ ከፊሉን እያጠራቀሙ በሣጥኖቹ ውስጥ ያስቀምጡ ነበር። እንዴት እንደዚህ ሊያስቡ ቻሉ? ልጆቹ ገንዘብ በእጃቸው ለመያዝ የሚችሉበት እድሜ ላይ ሲደርሱ ወላጆቻቸው በመንግሥት አዳራሽ ባለው የአስተዋጽኦ ሣጥን ውስጥ ጥቂት ገንዘብ መክተት አስተምረዋቸው ስለነበር ነው። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ልጆቹ የተማሩትን በተግባር እያዋሉ ነበር።

ሣጥኖቹ ሲሞሉ ተከፈቱ። ያጠራቀሙት ገንዘብ 3.13 የአሜሪካ ዶላር ሆኖ ነበር። ይህ ገንዘብ የአንድ ሰው አማካይ የዓመት ገቢ ጥቂት መቶ ዶላሮች ብቻ በሆነበት አገር ውስጥ ትንሽ የሚባል አይደለም። በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ በ235 አገሮች እየተካሄደ ያለው የይሖዋ ምሥክሮች የስብከት እንቅስቃሴ የሚደገፈው በእንደዚህ ዓይነት በፈቃደኛነት በሚ​ደረጉ መዋጮዎች ነው።