በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዘመናዊ ሰማዕታት በስዊድን ምሥክርነት እየሰጡ ነው

ዘመናዊ ሰማዕታት በስዊድን ምሥክርነት እየሰጡ ነው

የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት

ዘመናዊ ሰማዕታት በስዊድን ምሥክርነት እየሰጡ ነው

“ማርተር” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “ምሥክር” ተብሎ ከተተረጎመው ማርቲር ከተሰኘው የግሪክኛ ቃል የተገኘ ሲሆን “በሞቱ ምሥክርነት የሚሰጥ” ማለት ነው። በአንደኛው መቶ ዘመን የነበሩ ብዙ ክርስቲያኖች ለእምነታቸው ሲሉ በመሞት ስለ ይሖዋ ምሥክርነት ሰጥተዋል።

በተመሳሳይ በ20ኛው መቶ ዘመን በሺዎች የሚቆጠሩ ምሥክሮች ፖለቲካንና ብሔራዊ ስሜትን በተመለከቱ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኝነታቸውን በመጠበቃቸው በሂትለር ታማኝ ደጋፊዎች ተገድለዋል። እነዚህ ዘመናዊ ሰማዕታትም ጠንካራ ምሥክርነት ይሰጣሉ። በቅርቡ በስዊድን የተፈጸመው ይኸው ነው።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያበቃበት 50ኛ ዓመት ሲከበር የስዊድን መንግሥት እልቂቱን በማስመልከት አገር አቀፍ የትምህርት ዘመቻ ለማካሄድ ዝግጅት ጀምሮ ነበር። ፕሮጀክቱ ሕያው ታሪክ ተብሎ ተሰየመ። የይሖዋ ምሥክሮችም የደረሰባቸውን በመናገር በፕሮጀክቱ እንዲካፈሉ ተጋብዘው ነበር።

ምሥክሮቹ፣ የተረሱት የእልቂቱ ሰለባዎች የሚል ርዕስ ያለው ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት ምላሽ ሰጥተዋል። ኤግዚቢሽኑ የተከፈተው በስትሬንኔስ በሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ውስጥ ነበር። ከእልቂቱ በሕይወት የተረፉ ምሥክሮች ተሞክሮአቸውን ለመናገር በኤግዚቢሽኑ ላይ የተገኙ ሲሆን በመጀመሪያው ዕለት ብቻ ከ8, 400 የሚበልጡ ጎብኚዎች መጥተው ነበር! በ1999 መገባደጃ ላይ ኤግዚቢሽኑ በመላው ስዊድን ከ100 በሚበልጡ ሙዝየሞችና የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ቀርቦ ወደ 150, 000 የሚጠጉ ሰዎች ተመልክተውታል። ከጎብኚዎቹ መካከል ብዙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከመገኘታቸውም በላይ ስለተመለከቱት ነገር አዎንታዊ አስተያየት ሰንዝረዋል።

ከዚህ ቀደም በስዊድን ካለው የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የዚህን ያህል በስፋት ለሕዝብ የታየና አዎንታዊ በሆነ መንገድ የተዘገበለት አንድም ክንውን አልነበረም። ብዙዎቹ ጎብኚዎች “እልቂቱ በተፈጸመበት ወቅት ስለደረሰባችሁ ሁኔታ ካሁን በፊት ለምን አልነገራችሁንም?” ሲሉ ጠይቀዋል።

አንድ ጉባኤ ኤግዚቢሽኑ በአካባቢያቸው ከታየ በኋላ በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ረገድ 30 በመቶ ጭማሪ እንዳገኘ ሪፖርት አድርጓል! አንድ ምሥክር አብሮት የሚሠራውን ሰው ኤግዚቢሽኑን እንዲያይ ይጋብዘዋል። ሰውየው ግብዣውን በደስታ ተቀበለና ከአንድ ጓደኛው ጋር መጣ። ኤግዚቢሽኑን ከተመለከቱ በኋላ ጓደኛው ሰዎች እምነታቸውን እንደካዱ የሚናገር ሰነድ ፈርመው ነፃ ከመውጣት ይልቅ እስከ ሞት ድረስ እንዲጸኑ የሚያደርግ ጠንካራ እምነት ሊኖራቸው መቻሉ ፈጽሞ ሊገባት እንዳልቻለ ተናገረች። ይህም ቀጣይ ውይይት እንዲደረግ በር በመክፈቱ ከሴትዮዋ ጋር የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ።

እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን መሰሎቻቸው ሁሉ እነዚህ የ20ኛው መቶ ዘመን ታማኝ ሰማዕታትም ይሖዋ የማይናወጥ እምነትና ታማኝነት ልናሳየው የሚገባው ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑን በድፍረት መስክረዋል።​—⁠ራእይ 4:11

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Camp prisoner: Państwowe Muzeum Oświęcim-Brzezinka, courtesy of the USHMM Photo Archives