በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

ዘመዳሞች በሆኑ ሰዎች መካከል የሚፈጸምን ጋብቻ በተመለከተ በሙሴ ሕግ የተጣለው ገደብ ዛሬ በክርስቲያኖች ላይ የሚሠራው እስከ ምን ድረስ ነው?

ይሖዋ ለእስራኤል ብሔር የሰጠው ሕግ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶችንና ደንቦችን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያዎች አይሰጥም። ይሁን እንጂ በተወሰኑ የጋብቻ ዝምድናዎች ረገድ አንዳንድ ገደቦች አስቀምጧል። ለምሳሌ በዘሌዋውያን 18:​6-20 ላይ ‘ከቅርብ የሥጋ ዘመድ’ ጋር መመሥረት የሌለባቸው ዝምድናዎች በዝርዝር ተቀምጠው እናገኛለን። ይኸው ምንባብ በየትኞቹ የሥጋ ዘመዳሞች መካከል የጾታ ግንኙነት ሊፈጸም እንደማይገባ አንድ በአንድ ይዘረዝራል። እርግጥ ነው፣ ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግም ሆነ በድንጋጌዎቹ ሥር አይደሉም። (ኤፌሶን 2:​14, 15፤ ቆላስይስ 2:​14) ሆኖም ክርስቲያኖች የትዳር ጓደኛ ሲመርጡ ይህንን ጉዳይ ችላ ይሉታል ማለት አይደለም። ይህ የሆነበትን አንዳንድ ምክንያቶች እንመልከት።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸመውን ጋብቻ የሚከለክሉ ሰብዓዊ ሕጎች አሉ። ክርስቲያኖች ደግሞ የሚኖሩበትን አገር ሕግ የመታዘዝ ግዴታ አለባቸው። (ማቴዎስ 22:​21፤ ሮሜ 13:​1) እርግጥ እንዲህ ያሉት ሕጎች ከአገር አገር ይለያያሉ። በዚህ መስክ የሚወጡት አብዛኞቹ ዘመናዊ ሕጎች የዘር ውርስን በዋነኛነት መሠረት ያደረጉ ናቸው። በቅርብ የሥጋ ዘመዳሞች መካከል የሚመሠረተው ጋብቻ የሚወለደውን ልጅ ለአካል ጉዳተኝነትና ለበሽታ ሊያጋልጠው እንደሚችል የታወቀ ነው። በዚህ ምክንያትና ‘በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣናት የሚገዙ’ በመሆናቸው የተነሣ ወደ ትዳር ዓለም ለመግባት የሚያስቡ ክርስቲያኖች የሚኖሩበት አገር ጋብቻን አስመልክቶ ያወጣውን ሕግ ይታዘዛሉ።

በሌላው በኩል ደግሞ አንድ ሰው በሚኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት ያላቸውና የሌላቸው ነገሮች ይኖራሉ። ሁሉም ባሕል ማለት ይቻላል፣ በቅርብ የሥጋ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸመውን ጋብቻ እንደ አስነዋሪ ድርጊት በመቁጠር ድርጊቱን የሚያወግዝ ደንብና ሥርዓት አለው። የሚወገዘው የዝምድና ዓይነት እንደ ባሕሉ ሊለያይ ቢችልም ዚ ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ እንደዘገበው “በጥቅሉ ሲታይ በሁለት ሰዎች መካከል ያለው ጀነቲካዊ ዝምድና ይበልጥ ቅርብ በሆነ መጠን በመካከላቸው የሚፈጸመውን የፆታ ግንኙነት የሚከለክለው ወይም የሚያወግዘው ደንብም የዚያኑ ያህል ይጠነክራል።” ስለዚህ ክርስቲያኖች በመካከላቸው ያለው የሥጋ ዝምድና ጋብቻ የሚያስከለክል በማይሆንበት ጊዜም እንኳ በክርስቲያን ጉባኤውም ሆነ በአምላክ ስም ላይ ነቀፋ ላለማምጣት ሲሉ ሕጋዊ መሠረት ያላቸውን የማኅበረሰብ ደንቦች ወደ ጎን ገሸሽ ከማድረግ ይቆጠባሉ።​—⁠2 ቆሮንቶስ 6:​3

ሌላው ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ ደግሞ ከአምላክ ያገኘነው ሕሊና ነው። ሁሉም ሰዎች ትክክልና ስህተት፣ ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር የመለየት ችሎታ ይዘው ተወልደዋል። (ሮሜ 2:​15) ሕሊናቸው በመጥፎ ተግባራት ካልደነዘዘና ካልተበላሸ በቀር የቱ ተገቢና ተቀባይነት ያለው የቱ ደግሞ ከተፈጥሮ ውጪና አስጸያፊ እንደሆነ ይነግራቸዋል። ይሖዋ ለእስራኤላውያን በቅርብ የሥጋ ዘመዳሞች መካከል የሚመሠረተውን ጋብቻ የሚከለክል ሕግ በሰጣቸው ጊዜ ይህንን እውነታ በተዘዋዋሪ መንገድ ጠቅሷል። እንዲህ የሚል እናነብባለን:- “እንደ ተቀመጣችሁባት እንደ ግብፅ ምድር ሥራ አትሥሩ፤ እኔም ወደ እርስዋ እንደማገባችሁ እንደ ከነዓን ምድር ሥራ አትሥሩ፤ በሥርዓታቸውም አትሂዱ።” (ዘሌዋውያን 18:​3) ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ ሕሊናቸውን ከፍ አድርገው ስለሚመለከቱት ትክክልና ስህተት የሆነውን በመለየት ረገድ ሰዎች ያላቸው የተዛባ አስተሳሰብ ተጽእኖ እንዲያሳድርባቸው አይፈቅዱም።​—⁠ኤፌሶን 4:​17-19

ታዲያ ምን ብለን መደምደም እንችላለን? ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባይሆኑም እንደ አባትና ሴት ልጅ፣ እናትና ወንድ ልጅ እንዲሁም ወንድምና እህት ባሉ የቅርብ የሥጋ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸመው ጋብቻ በክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ዘንድ ፈጽሞ የተወገዘ እንደሆነ ሕሊናቸው በግልጽ ይነግራቸዋል። a የሥጋ ዝምድናው የራቀ ቢሆንም ክርስቲያኖች ለሕጋዊ ጋብቻ መሠረት ሆነው የሚያገለግሉ ሕጎችንና ሥርዓቶችን እንዲሁም ማኅበራዊም ሆነ ባሕላዊ ተቀባይነት ያላቸው ደንቦችን ግምት ውስጥ ያስገባሉ። “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር . . . ይሁን” ከሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ ጋር መስማማት እንችል ዘንድ እነዚህ ነገሮች በጥንቃቄ ሊጤኑ ይገባቸዋል።​—⁠ዕብራውያን 13:​4

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት በመጋቢት 15, 1978 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 25-6 ላይ የሚገኘውን “በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸም ጋብቻ​—⁠ክርስቲያኖች እንዴት ሊመለከቱት ይገባል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።