በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የእውነትን መንፈስ’ ተቀብላችኋልን?

‘የእውነትን መንፈስ’ ተቀብላችኋልን?

‘የእውነትን መንፈስ’ ተቀብላችኋልን?

“እርሱም [አብ ] ከእናንተ ጋር ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ [“ረዳት፣” NW ] ይሰጣችኋል።”ዮሐንስ 14:16, 17 አ.መ.ት

1. ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በደርብ ላይ በነበረባቸው የመጨረሻ ሰዓታት ምን አስፈላጊ የሆነ ነገር ነገራቸው?

 “ጌታ ሆይ ወዴት ትሄዳለህ?” ኢየሱስ ኢየሩሳሌም በሚገኘው ደርብ አብሯቸው በነበረበት ወቅት ሐዋርያቱ ካቀረቡለት ጥያቄ መካከል አንደኛው ይህ ነበር። (ዮሐንስ 13:36) ስብሰባው እየተካሄደ ሳለ ኢየሱስ ከእነርሱ ተለይቶ ወደ አባቱ የሚመለስበት ጊዜ መቃረቡን ነገራቸው። (ዮሐንስ 14:28፤ 16:28) ከአሁን በኋላ በአካል አብሯቸው ሆኖ አያስተምራቸውም እንዲሁም ለጥያቄያቸው መልስ አይሰጣቸውም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ [“ረዳት፣” NW ] ይሰጣችኋል” የሚል ማረጋገጫ ሰጣቸው።​—⁠ዮሐንስ 14:16, 17 አ.መ.ት

2. ኢየሱስ ከሄደ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ምን እንደሚልክ ቃል ገባ?

2 ኢየሱስ የዚህን ረዳት ማንነት የገለጸ ከመሆኑም በላይ ደቀ መዛሙርቱን እንዴት አድርጎ እንደሚረዳቸው አብራርቷል። እንዲህ አላቸው:- “ከእናንተም ጋር ስለ ነበርሁ በመጀመሪያ ይህን አልነገርኋችሁም። አሁን ግን ወደ ላከኝ እሄዳለሁ . . . እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ [“ረዳቱ፣” NW ] ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። . . . የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል።”​—⁠ዮሐንስ 16:4, 5, 7, 13

3. (ሀ) ለጥንት ክርስቲያኖች ‘የእውነት መንፈስ’ የተላከላቸው መቼ ነው? (ለ) መንፈሱ በምን አስፈላጊ መስክ “ረዳት” ሆኖላቸዋል?

3 ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዳረጋገጠው ይህ የተስፋ ቃል በ33 እዘአ በዋለው በጰንጠቆስጤ ዕለት ፍጻሜውን አግኝቷል። “ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው።” (ሥራ 2:32, 33) ቆየት ብለን እንደምንመለከተው በጰንጠቆስጤ ዕለት የፈሰሰው መንፈስ ቅዱስ ለጥንት ክርስቲያኖች በርካታ ተግባራት አከናውኖላቸዋል። ሆኖም ኢየሱስ ‘የእውነት መንፈስ’ ‘እርሱ የነገራቸውን ሁሉ እንደሚያስታውሳቸው’ ቃል ገብቶላቸው ነበር። (ዮሐንስ 14:26) የኢየሱስን አገልግሎትና ትምህርቶች ሌላው ቀርቶ የተናገራቸውን ቃላት ሁሉ እንዲያስታውሱና በጽሑፍ እንዲያሰፍሩ ያስችላቸዋል። በተለይ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ በዕድሜ ገፍቶ የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ የወንጌል ዘገባውን መጻፍ በጀመረበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በእጅጉ ረድቶታል። ይህ ዘገባ ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ ባቋቋመበት ዕለት የተናገረውን ውድ ምክርም ጨምሮ ይዟል።​—⁠ዮሐንስ ምዕራፍ 13-17

4. ‘የእውነት መንፈስ’ የጥንት ቅቡዓን ክርስቲያኖችን የረዳቸው እንዴት ነው?

4 በተጨማሪም ኢየሱስ መንፈሱ ‘ሁሉን እንደሚያስተምራቸው’ እና ‘ወደ እውነት ሁሉ እንደሚመራቸው’ ለጥንት ደቀ መዛሙርቱ ቃል ገብቶላቸዋል። መንፈሱ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን ጥልቅ ነገሮች እንዲያስተውሉና በአሳብ፣ በእውቀትና በዓላማ ያላቸውን አንድነት እንዲጠብቁ ይረዳቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 2:10፤ ኤፌሶን 4:3) መንፈስ ቅዱስ እነዚህን የጥንት ክርስቲያኖች በቡድን ደረጃ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆነው እንዲሠሩ በማድረግ ለእያንዳንዱ ቅቡዕ ክርስቲያን ‘በጊዜው መንፈሳዊ ምግብ’ እንዲያቀርቡ ኃይል ሰጥቷቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 24:45

መንፈሱ ይመሠክራል

5. (ሀ) ኢየሱስ ኒሳን 14, 33 እዘአ ምሽት ለደቀ መዛሙርቱ ምን ተስፋ ፈነጠቀላቸው? (ለ) ኢየሱስ የሰጠውን የተስፋ ቃል በመፈጸም ረገድ መንፈስ ቅዱስ ምን ሚና ይጫወታል?

5 ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ እንደሚወስዳቸውና ከእርሱና ከአባቱ ጋር በሰማይ እንደሚኖሩ ኒሳን 14, 33 እዘአ ምሽት ለደቀ መዛሙርቱ ፍንጭ ሰጥቷቸዋል። እንዲህ አላቸው:- “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፣ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።” (ዮሐንስ 13:36፤ 14:2, 3) ከእርሱም ጋር አብረው በመንግሥቱ ይገዛሉ። (ሉቃስ 22:28-30) ይህን ሰማያዊ ተስፋ እንዲያገኙ የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች ሆነው ‘ከመንፈስ መወለድና’ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ንጉሥና ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ መቀባት ነበረባቸው።​—⁠ዮሐንስ 3:5-8፤ 2 ቆሮንቶስ 1:21, 22፤ ቲቶ 3:5-7፤ 1 ጴጥሮስ 1:3, 4፤ ራእይ 20:6

6. (ሀ) ሰማያዊው ጥሪ የጀመረው መቼ ነው? ይህን ጥሪ ያገኙትስ ስንት ናቸው? (ለ) የተጠሩት ወደ ምን ውስጥ ይጠመቃሉ?

6 ይህ ‘ሰማያዊ ጥሪ’ በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት የጀመረ ሲሆን በዋነኛነት በ1930ዎቹ አጋማሽ የተጠናቀቀ ይመስላል። (ዕብራውያን 3:1) የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት እንዲሆኑ ‘ከሰዎች የተዋጁትና’ በመንፈስ ቅዱስ የታተሙት ሰዎች ቁጥር 144, 000 ነው። (ራእይ 7:4፤ 14:1-4) በመንፈሳዊው የክርስቶስ አካል ውስጥ፣ በጉባኤው ውስጥና በሞቱ ውስጥ የተጠመቁት እነዚህ ናቸው። (ሮሜ 6:3፤ 1 ቆሮንቶስ 12:12, 13, 27፤ ኤፌሶን 1:22, 23) በውኃ ከተጠመቁና በመንፈስ ቅዱስ ከተቀቡ በኋላ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ የአቋም ጽናታቸውን ጠብቀው መሥዋዕትነት የሚጠይቅ ጎዳና መከተል ይጀምራሉ።​—⁠ሮሜ 6:4, 5

7. በመታሰቢያው በዓል ወቅት ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን የመካፈል መብት ያላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ የሆኑት ለምንድን ነው?

7 እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መንፈሳዊ እስራኤላውያን እንደመሆናቸው መጠን በይሖዋ እና ‘በአምላክ እስራኤል’ መካከል የተገባው የአዲሱ ቃል ኪዳን ክፍል ናቸው። (ገላትያ 6:16፤ ኤርምያስ 31:31-34) አዲሱ ቃል ኪዳን የጸደቀው በፈሰሰው የክርስቶስ ደም ነው። ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ በዓል ሲያቋቁም ይህን ጠቅሶ ተናግሯል። ሉቃስ እንዲህ በማለት ዘግቧል:- “እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ ቆርሶም ሰጣቸውና:- ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ:- ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው።” (ሉቃስ 22:19, 20) የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል በሚከበርበት ጊዜ ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን የመካፈል መብት ያላቸው ቀሪዎቹ ወይም ገና ምድር ላይ ያሉት የ144, 000 አባላት ናቸው።

8. ቅቡዓን ሰማያዊ ጥሪ እንደተቀበሉ እንዴት ያውቃሉ?

8 ቅቡዓን ለሰማያዊ ሕይወት የተጠሩ መሆናቸውን የሚያውቁት እንዴት ነው? መንፈስ ቅዱስ ፈጽሞ የማያሻማ ምሥክርነት ይሰጣቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለእነዚህ ሰዎች እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። . . . የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፣ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።” (ሮሜ 8:14-17) መንፈሱ የሚሰጠው ምሥክርነት ፈጽሞ የማያሻማ በመሆኑ ሰማያዊ ጥሪ ለማግኘታቸው ትንሽም ቢሆን ጥርጣሬ የሚሰማቸው ሰዎች ለሰማያዊ ሕይወት እንዳልተጠሩ በትክክል ሊደመድሙ ይችላሉ። ስለዚህም በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚዞረው ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን ከመካፈል ይታቀባሉ።

መንፈሱና ሌሎች በጎች

9. በወንጌሎችና በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት ሁለት የተለያዩ ቡድኖች ምንድን ናቸው?

9 ኢየሱስ የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት እንዲሆኑ የተጠሩት ክርስቲያኖች ቁጥር ውስን እንደሆነ ስለሚያውቅ “ታናሹ መንጋ” በማለት ጠርቷቸዋል። እነዚህ ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን “በረት” እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ሲሆን ቁጥራቸው ያልተወሰነው ኢየሱስ እንደሚሰበስባቸው የተናገረላቸው “ሌሎች በጎች” ግን ወደዚህ ቃል ኪዳን አይገቡም። (ሉቃስ 12:32፤ ዮሐንስ 10:16) በመጨረሻው ዘመን የሚሰበሰቡት የሌሎች በጎች አባላት ‘እጅግ ብዙ ሰዎች’ በመሆን ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ‘ታላቁን መከራ’ በሕይወት ያልፋሉ። ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ መገባደጃ ላይ የተመለከተው ራእይ በእነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎችና በ144, 000 የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት መካከል ልዩነት እንዳለ ያሳያል። (ራእይ 7:4, 9, 14) ሌሎች በጎችስ መንፈስ ቅዱስ ይቀበላሉ? ከሆነ ይህ ሕይወታቸውን የሚነካው እንዴት ነው?

10. ሌሎች በጎች “በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” የሚጠመቁት እንዴት ነው?

10 መንፈስ ቅዱስ በሌሎች በጎች ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን የሚያሳዩት “በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” በመጠመቅ ነው። (ማቴዎስ 28:19) የይሖዋን ሉዓላዊነት ይቀበላሉ፣ እንደ ንጉሣቸውና አዳኛቸው አድርገው በመመልከት ለክርስቶስ ይገዛሉ እንዲሁም የአምላክ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል በሕይወታቸው ላይ እንዲሠራ ይፈቅዳሉ። በየዕለቱ በሕይወታቸው ውስጥ እንደ “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት” ያሉትን ‘የመንፈስ ፍሬዎች’ ለማፍራት ጥረት ያደርጋሉ።​—⁠ገላትያ 5:22, 23

11, 12. (ሀ) ቅቡዓን ልዩ በሆነ መንገድ የተቀደሱት እንዴት ነው? (ለ) ሌሎች በጎች የተቀደሱትና ቅዱሳን የሆኑት በምን መንገድ ነው?

11 ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች በጎች የአምላክ ቃልና መንፈስ ቅዱሱ እንዲያነጿቸውና እንዲቀድሷቸው መፍቀድ ይኖርባቸዋል። ቅቡዓን የክርስቶስ ሙሽራ በመሆን እንደ ጻድቅና ቅዱስ ስለተቆጠሩ ልዩ በሆነ መንገድ ተቀድሰዋል። (ዮሐንስ 17:17፤ 1 ቆሮንቶስ 6:11፤ ኤፌሶን 5:23-27) ነቢዩ ዳንኤል “የሰው ልጅ” ተብሎ በተጠራው በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት መንግሥት የተቀበሉ ‘የልዑል ቅዱሳን’ እንደሆኑ አድርጎ ገልጿቸዋል። (ዳንኤል 7:13, 14, 18, 27) ቀደም ሲል ይሖዋ በሙሴና በአሮን አማካኝነት ለእስራኤል ብሔር እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር:- “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና፤ ሰውነታችሁን ቀድሱ፣ ቅዱሳንም ሁኑ፣ እኔ ቅዱስ ነኝና።”​—⁠ዘሌዋውያን 11:44

12 “መቀደስ” የሚለው ቃል “ቅዱስ ማድረግ፣ መለየት፣ ለይሖዋ አምላክ አገልግሎት ለይቶ ማስቀመጥ፣ ቅዱስ፣ የተቀደሰ ወይም የጠራ መሆን” የሚል መሠረታዊ ትርጉም አለው። በ1938 የወጣ አንድ መጠበቂያ ግንብ ኢዮናዳቦች ወይም ሌሎች በጎች “የተለዩ መሆን [ራስን ለአምላክ መወሰን] እና ቅድስና የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል ከሚሆንና በምድር ላይ ከሚኖር ከእያንዳንዱ ሰው የሚጠበቅ እንደሆነ ማወቅ ይኖርባቸዋል” ሲል ገልጾ ነበር። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ እንደሚገኘው በራእይ የታዩት እጅግ ብዙ ሰዎች ‘ልብሳቸውን አጥበው በበጉ ደም እንዳነጹና’ ‘ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ቅዱስ አገልግሎት’ ለይሖዋ እንደሚያቀርቡ ተነግሮላቸዋል። (ራእይ 7:9, 14, 15) ሌሎች በጎች መንፈስ ቅዱስ በሚሰጣቸው እርዳታ እየታገዙ ይሖዋ ለቅድስና ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው ለመኖር የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ።​—⁠2 ቆሮንቶስ 7:1

ለክርስቶስ ወንድሞች መልካም ማድረግ

13, 14. (ሀ) ኢየሱስ ስለ በጎችና ፍየሎች በተናገረው ምሳሌ መሠረት የበጎቹ መዳን የተመካው በምን ላይ ነው? (ለ) በዚህ የፍጻሜ ዘመን ሌሎች በጎች ለክርስቶስ ወንድሞች መልካም ያደረጉት እንዴት ነው?

13 ኢየሱስ ስለ ‘ዓለም መጨረሻ’ በተናገረው ትንቢት ውስጥ በማካተት ስለ በጎችና ፍየሎች በተናገረው ምሳሌ ውስጥ በሌሎች በጎችና በታናሹ መንጋ መካከል የተቀራረበ ዝምድና እንዳለ ጎላ አድርጎ ገልጿል። በዚህ ምሳሌ ላይ ክርስቶስ የሌሎች በጎች መዳን “ወንድሞቼ” ብሎ ለጠራቸው ቅቡዓን በሚያደርጉት መልካም ነገር በእጅጉ የተመካ መሆኑን በግልጽ አመልክቷል። እንዲህ አለ:- “ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል:- እናንተ የአባቴ ብሩካን፣ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። . . . እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት።”​—⁠ማቴዎስ 24:3፤ 25:31-34, 40

14 “ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት” የሚለው አገላለጽ የሰይጣን ዓለም እንደ መጻተኛ ለሚመለከታቸውና አልፎ ተርፎም አንዳንዶቹን እስር ቤት ለጣላቸው በመንፈስ ለተወለዱት የክርስቶስ ወንድሞች የተደረገውን በፍቅር ላይ የተመሠረተ ድጋፍ ያመለክታል። ምግብና ልብስ እንዲሁም ሕክምና ያጡበት ጊዜ ነበር። (ማቴዎስ 25:35, 36አዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ከ1914 ጀምሮ በዚህ የፍጻሜ ዘመን ውስጥ በርካታ ቅቡዓን እንዲህ ያለ ሁኔታ ገጥሟቸዋል። ዘመናዊው የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ እንደሚመሠክረው ታማኝ ጓደኞቻቸው የሆኑት ሌሎች በጎች በመንፈሱ እየተመሩ ለቅቡዓኑ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

15, 16. (ሀ) ሌሎች በጎች በምድር ላይ የሚገኙትን የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች እየረዷቸው ያሉት በተለይ በየትኛው እንቅስቃሴ ነው? (ለ) ቅቡዓን ለሌሎች በጎች ያላቸውን አድናቆት የሚገልጹት እንዴት ነው?

15 በተለይ በዚህ የፍጻሜ ዘመን ምድር ላይ ያሉት የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች ‘ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህን የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ እንዲሰብኩ’ አምላክ የሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከሌሎች በጎች ያልተቋረጠ ድጋፍ አግኝተዋል። (ማቴዎስ 24:14፤ ዮሐንስ 14:12) ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በምድር ላይ ያሉት ቅቡዓን ቁጥር እየተመናመነ ሲሄድ የሌሎች በጎች ቁጥር ግን አድጎ ቃል በቃል በሚልዮኖች የሚቆጠር ሆኗል። ከእነዚህ መካከል በሺህ የሚቆጠሩት በአቅኚነትና በሚስዮናዊነት የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ሆነው በማገልገል የመንግሥቱን ምሥራች “እስከ ምድር ዳርም ድረስ” እያዳረሱ ነው። (ሥራ 1:8) ሌሎችም አቅማቸው የፈቀደላቸውን ያህል በምሥክርነቱ ሥራ ይካፈላሉ እንዲሁም ይህን አስፈላጊ ሥራ በገንዘባቸው ይደግፋሉ።

16 የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች እነዚህ የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት ጓደኞቻቸው ለሚሰጧቸው የታማኝነት ድጋፍ ምንኛ አመስጋኞች ናቸው! በ1986 የባሪያው ክፍል ባወጣው ‘የሰላሙ መስፍን’ ሲገዛ በምድር ዙሪያ የሚገኝ ዋስትና ያለው ሕይወት በተባለው መጽሐፍ ላይ ስሜታቸው በጥሩ ሁኔታ ተገልጿል። እንዲህ ይላል:- “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ ኢየሱስ ‘የመጨረሻውን ዘመን’ አስመልክቶ የተናገረውን ትንቢት በአብዛኛው እየፈጸሙ ያሉት ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑት ‘እጅግ ብዙ ሰዎች’ ናቸው። . . . ‘እጅግ ብዙ ሰዎች’ [ኢየሱስ] በማቴዎስ 24:​14 ላይ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ ለሚያበረክቱት የላቀ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ምስጋና ሊሰጣቸው ይገባል!”

‘ያለ እኛ ፍጹማን አይሆኑም’

17. በምድር ላይ ትንሣኤ የሚያገኙት ጥንት የነበሩ የታመኑ ሰዎች ‘ያለ [ቅቡዓን] ፍጹማን የማይሆኑት’ በምን መንገድ ነው?

17 ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱን ከቅቡዓኑ አንዱ እንደሆነ አድርጎ በመጥቀስ ከክርስቶስ ዘመን በፊት ስለኖሩት የታመኑ ወንዶችና ሴቶች ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፣ ያለ እኛ [ቅቡዓን] ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና።” (ዕብራውያን 11:35, 39, 40) በመጪው ሺህ ዓመት ክርስቶስና 144, 000 ቅቡዓን ወንድሞቹ በሰማይ ንጉሥና ካህናት ሆነው በመሥራት የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚያስገኘውን ጥቅም በምድር ለሚኖሩ ሁሉ ያዳርሳሉ። በዚህ መንገድ ሌሎች በጎች በአካልና በአእምሮ ‘ፍጹማን ይሆናሉ።’​—⁠ራእይ 22:1, 2

18. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ማረጋገጫ ሌሎች በጎች ምን እንዲገነዘቡ ሊረዳቸው ይገባል? (ለ) ሌሎች በጎች “የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ” የሚጠባበቁት በምን ተስፋ ነው?

18 ይህ ሁሉ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች በክርስቶስና በቅቡዓን ወንድሞቹ እንዲሁም በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ በሚኖራቸው ድርሻ ላይ ትኩረት የሚያደርጉት ለምን እንደሆነ ሌሎች በጎች እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል። ስለዚህ ሌሎች በጎች ‘የእግዚአብሔር ልጆች’ በአርማጌዶንና በሺህ ዓመቱ የግዛት ዘመን ‘የሚገለጡበትን’ ጊዜ እየተጠባበቁ በሚቻላቸው መንገድ ሁሉ ለተቀባው ባሪያ የሚያበረክቱትን እርዳታ እንደ ልዩ መብት አድርገው ይመለከቱታል። ‘ከጥፋት ባርነት ነፃ የሚወጡበትንና ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት የሚደርሱበትን’ ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ ይችላሉ።​—⁠ሮሜ 8:19-21

በመታሰቢያው በዓል ላይ በሚኖረው መንፈስ አንድ መሆን

19. “የእውነት መንፈስ” ለቅቡዓንና ለጓደኞቻቸው ምን አድርጎላቸዋል? በተለይ መጋቢት 28 ምሽት ላይ አንድ የሚሆኑት እንዴት ነው?

19 ኢየሱስ በኒሳን 14, 33 እዘአ ምሽት ባቀረበው የመደምደሚያ ጸሎት ላይ እንዲህ አለ:- “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፣ . . . አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፣ አንተ፣ አባት ሆይ፣ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፣ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ።” (ዮሐንስ 17:20, 21) አምላክ በፍቅሩ ተገፋፍቶ ቅቡዓንና በዓለም የሚኖሩ ታዛዥ የሰው ዘሮች መዳንን ያገኙ ዘንድ ሕይወቱን እንዲሰጥ ልጁን ላከ። (1 ዮሐንስ 2:2) “የእውነት መንፈስ” የክርስቶስን ወንድሞችና ጓደኞቻቸውን አንድ አድርጓቸዋል። መጋቢት 28 ምሽት፣ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ለማክበርና ይሖዋ በውድ ልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ያደረገላቸውን ሁሉ ለማስታወስ ሁለቱም ቡድኖች አንድ ላይ ይሰበሰባሉ። ሁለቱም ቡድኖች በዚህ በጣም አስፈላጊ በሆነ ወቅት ላይ መገኘታቸው አንድነታቸውን የሚያጠነክርላቸውና የአምላክን ፈቃድ ማድረጋቸውን ለመቀጠል ያደረጉትን ቁርጥ ውሳኔ የሚያድስላቸው እንዲሆንና አምላክ ከሚወድዳቸው ሰዎች መካከል መገኘታቸው የሚያስደስታቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዲሆንላቸው እንመኛለን።

ለክለሳ ያህል

• የጥንት ክርስቲያኖች ‘የእውነትን መንፈስ’ የተቀበሉት መቼ ነው? “ረዳት” ሆኖ ያገኙትስ በምን መንገድ ነው?

• ቅቡዓን ሰማያዊ ጥሪ እንዳላቸው የሚያውቁት እንዴት ነው?

• የአምላክ መንፈስ በሌሎች በጎች ላይ የሚሠራው በምን መንገዶች ነው?

• ሌሎች በጎች ለክርስቶስ ወንድሞች መልካም ያደረጉት እንዴት ነው? ያለ ቅቡዓን “ፍጹማን” የማይሆኑትስ ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት “የእውነት መንፈስ” በደቀ መዛሙርቱ ላይ ፈስሷል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ የሰጠውን የስብከት ተልእኮ በመፈጸም ረገድ ድጋፋቸውን በመለገስ ሌሎች በጎች ለክርስቶስ ወንድሞች መልካም አድርገዋል