ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት በባይዛንቲየም
ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት በባይዛንቲየም
የክርስትና መሥራች በተከታዮቹና ከአምላክ በራቀው የሰው ዘር መካከል ሊኖር የሚገባውን ልዩነት በተመለከተ ግልጽ ሐሳብ ሰጥቷል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል” በማለት ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 15:19) የዘመኑ የፖለቲካ ሥልጣን ወኪል ለነበረው ለጲላጦስ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም” ብሎታል።—ዮሐንስ 18:36
ክርስቲያኖች “እስከ ምድር ዳር” እንዲሰብኩ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ለመፈጸም በዓለማዊ ጉዳዮች ከመጠላለፍ መቆጠብ ነበረባቸው። (ሥራ 1:8) ኢየሱስ እንዳደረገው ሁሉ የቀድሞ ክርስቲያኖችም በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ አልገቡም። (ዮሐንስ 6:15) ታማኝ ክርስቲያኖች የፖለቲካ ሥልጣንም ሆነ የአስተዳደር ቦታዎችን እንዳልያዙ ማየት ይቻላል። ይሁን እንጂ ሁኔታው እንዲሁ አልቀጠለም።
“የዓለም ክፍል”
ሐዋርያት ሞተው ካለቁ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የሃይማኖት መሪዎች ለራሳቸውና ለዓለም ሊኖራቸው የሚገባውን አመለካከት በገዛ ፈቃዳቸው መለወጥ ጀመሩ። ዓለም ውስጥ የሚገኝ ብቻ ሳይሆን የዓለም ክፍል የሆነ “መንግሥት” በዓይነ ሕሊናቸው መመልከት ጀመሩ። ባይዛንቲየምን (የአሁኗን ኢስታቡል) ዋና ከተማዋ ባደረገችው በባይዛንታይን ማለትም በምሥራቃዊ የሮማ ግዛት ሃይማኖትና ፖለቲካ ምን ያህል እርስ በርስ ተሳስረው እንደነበረ መመልከቱ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
ማዕከሉን ባይዛንቲየም ያደረገው የባይዛንታይን ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖት ትልቅ ሚና በሚጫወትበት ኅብረተሰብ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ነበረው። ፓናዮቴስ ክሪስቱ የተባሉ አንድ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ “የባይዛንታይን ሰዎች ምድራዊ ግዛታቸውን የአምላክ መንግሥት አምሳል እንደሆነ አድርገው ያስቡ ነበር” በማለት ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ንጉሠ ነገሥቱ ሁልጊዜ ከዚህ ሐሳብ ጋር ይስማማል ማለት አልነበረም። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ጊዜ በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል ከፍተኛ ግጭት ይፈጠር ነበር። ዚ ኦክስፎርድ ዲክሽነሪ ኦቭ ባይዛንቲየም እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል:- “የቁስጥንጥንያ [ወይም የባይዛንቲየም] ጳጳሳት ኃይለኛ ለሆነ መሪ ጸጥ ለጥ ብሎ ከመገዛት አንስቶ . . . ከንጉሠ ነገሥቱ ጎን እስከመቆምና . . . የንጉሠ ነገሥቱን ፈቃድ በጽኑ እስከመቃወም የሚደርሱ የተለያዩ ባሕርያትን አንጸባርቀዋል።”
የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ዋና ሹም የሆነው የቁስጥንጥንያው ፓትርያርክ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበረው ሰው ሲሆን የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ቋሚ ጠበቃ እንዲሆን በማሰብ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ዘውድ የጫነው እርሱ ነበር።
በተጨማሪም ጠቅላላውን የቤተ ክርስቲያን ንብረት በመቆጣጠሩ በጣም ሃብታም ነበር። ኃይሉ ስፍር ቁጥር በሌላቸው መነኮሳት ላይ ከነበረው ሥልጣንና በምእመናኑ ላይ ማሳደር ከቻለው ተጽእኖ የመነጨ ነበር።ፓትርያርኩ አብዛኛውን ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱን መቃወም የሚያስችል ሥልጣን የነበረው ሲሆን ትገለላለህ ብሎ በማስፈራራትም ሆነ ከዙፋኑ ሊወርድ የሚችልባቸውን ሌሎች መንገዶች በመጠቀም የገዛ ፈቃዱን በአምላክ ስም ለማስፈጸም ይጥር ነበር።
ከዋና ከተማው ውጪ ያለው የሲቪል አስተዳደር ቀስ በቀስ እየተዳከመ ሲመጣ ጳጳሳቱ በየከተሞቻቸው ያላቸው ተሰሚነት እየጨመረ የሄደ ሲሆን በእነርሱ እገዛ ከተመረጡት አገረ ገዢዎች ያላነሰ ሥልጣን ለማግኘት በቅተዋል። ጳጳሳቱ ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከት ጉዳይ ኖረም አልኖረ ፍርድን ጨምሮ የተለያዩ ዓለማዊ ጉዳዮችን ይከታተሉ ነበር። ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረገው በየግዛታቸው ለሚገኘው ጳጳስ የሚገዙ በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ቄሶችና መነኮሳት መኖራቸው ነው።
ፖለቲካና ሲሞናዊነት
ከላይ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው ሃይማኖትና ፖለቲካ ፈጽሞ የማይነጣጠሉ ነገሮች ሆነዋል። ከዚህም በላይ የቄሶቹ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርም ሆነ የሚያከናውኑት ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ መብዛት በጣም ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ ነበር። ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው አብዛኞቹ ቄሶች የተንደላቀቀ ኑሮ ነበራቸው። ቤተ ክርስቲያኗ ሥልጣንና ሃብት እያገኘች ስትሄድ ሐዋርያዊ ድህነትና ቅድስና ጨርሰው ጠፉ። አንዳንድ ቄሶችና ጳጳሳት ሹመቱን በገንዘብ ይገዙ ነበር። ሲሞናዊነት ከትንሹ አንስቶ እስከ ትልቁ የሥልጣን ተዋረድ ድረስ የተለመደ ሆኖ ነበር። በሃብታም የምክር ቤት አባላት የሚደገፉ ቄሶች በንጉሠ ነገሥቱ ፊት መቀመጫ ለማግኘት ይፎካከሩ ነበር።
ከፍተኛ ሥልጣን ባላቸው የሃይማኖት መሪዎች ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ጉቦም በመሣሪያነት አገልግሏል። ንግሥት ዞኢ (ከ978 ገደማ-1050 እዘአ) ባሏን ሳልሳዊ ሮማነስን አስገድላ ፍቅረኛዋንና የወደፊቱን ንጉሠ ነገሥት ሚካኤል አራተኛን ለማግባት ፈለገች። ስለዚህ ባሏ እንደሞተ ወዲያው ፓትርያርክ አሌክሰስን ወደ ቤተ መንግሥት አስጠራችው። ፓትርያርኩም ሮማነስ እንደሞተና የሠርግ ሥነ ሥርዓት ማከናወን እንደሚጠበቅበት ተነገረው። በዚያ ምሽት ቤተ ክርስቲያኑ የስቅለትን በዓል የሚያከብር መሆኑ ሁኔታውን ምቹ ባያደርግለትም ንግሥቲቱ የሰጠችውን ጠቀም ያለ ጉርሻ በመቀበል ፍላጎቷን አሟልቶላታል።
ለንጉሠ ነገሥቱ መገዛት
በባይዛንታይን የግዛት ዘመን ንጉሠ ነገሥቱ የቁስጥንጥንያን ፓትርያርክ በመምረጥ ረገድ የተሰጠውን የመሾም ሥልጣን አልፎ አልፎ ይጠቀምበት ነበር። በእነዚህ ጊዜያት ከንጉሠ ነገሥቱ ፈቃድ ውጪ ማንኛውም ሰው ፓትርያርክ መሆንም ሆነ በሥልጣኑ ላይ መቆየት አይችልም ነበር።
ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አንድሮኒከስ (1260-1332) ፓትርያርኮችን ዘጠኝ ጊዜ መለወጥ አስፈልጎታል። እንዲህ ያደርግ የነበረበት ዋነኛ ዓላማ በተፈለገው አቅጣጫ ሊነዳ የሚችልን ሰው በቦታው ላይ ማስቀመጥ ነው። እንዲያውም አንድ ፓትርያርክ ለንጉሠ ነገሥቱ በጻፈው ደብዳቤ “ንጉሠ ነገሥቱ የቱንም ያህል ሕገ ወጥ የሆነ ጥያቄ ቢጠይቅ የጠየቀውን ሁሉ ለማሟላትና እርሱን የሚያሳዝነውን ማንኛውንም ነገር ከመፈጸም ለመቆጠብ” ቃል ገብቶ እንደነበረ ዘ ባይዛንታይንስ የተባለው መጽሐፍ ገልጿል። ነገሥታቱ ሁለት ጊዜ የቤተሰቡን አልጋ ወራሽ ፓትርያርክ አድርገው በመሾም ፈቃዳቸውን ለማስፈጸም ሞክረዋል። ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ሮማነስ ቲዮፊላክት የተባለ ገና የ16 ዓመት ልጁን ፓትርያርክ አድርጎ ሾሞታል።
ልዑሉ በፓትርያርኩ ካልተደሰተ አስገድዶ ከሥልጣኑ ሊያወርደው አሊያም ለሲኖዶሱ መመሪያ በመስጠት ከሥልጣኑ እንዲወገድ ሊያደርገው ይችላል። ባይዛንታይን የተባለው መጽሐፍ እንደሚከተለው ይላል:- “የባይዛንታይን ታሪክ እንደሚያሳየው በጳጳሳት አመራረጥ ረገድ ንጉሠ ነገሥቱና ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት የላቀ ሚና ተጫውተዋል።”
ንጉሠ ነገሥቱ ፓትርያርኩን ከጎኑ አስቀምጦ ቤተ ክርስቲያኑ የሚያካሂደውን ስብሰባ በሊቀ መንበርነት ይመራ ነበር። በተጨማሪም የጦፉ ክርክሮችን ያካሂድና እምነትን መሠረት ያደረጉ ጽሑፎች ያዘጋጅ ነበር። እንዲሁም ከጳጳሳትና ከመናፍቃን ጋር የሚከራከር ሲሆን ከእርሱ ጋር ያልተስማሙትን በእንጨት ላይ እንዲሰቀሉ ያደርግ ነበር። ንጉሠ ነገሥቱ በምክር ቤቱ ተቀባይነት ያገኙ ቀኖናዎችን ያጸድቅና በሥራ እንዲተገበሩ ያደርግ ነበር። ተቃዋሚዎች ካሉ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ዓመፅ አካሂደዋል በሚል ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንና የአምላክ ጠላቶችም ናቸው በሚል ይከስሳቸው ነበር። አንድ የስድስተኛው መቶ ዘመን ፓትርያርክ “በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ከንጉሠ ነገሥቱ ፈቃድና ትእዛዝ ውጪ ምንም ነገር መደረግ የለበትም” በማለት
ተናግሯል። በቤተ መንግሥቱ ዙሪያ የነበሩት ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ላዩን ብቻ ጠንካራ መስለው የሚታዩ፣ በተነዱበት አቅጣጫ የሚሄዱ፣ ለማንኛውም የብልጠት ማባበያ ወይም ድርድር እጃቸውን የሚሰጡ ሰዎች በመሆናቸው በጥቅሉ ሲታይ ከዋናቸው የተሻለ የተቃውሞ ድምፅ አላሰሙም።ለምሳሌ ያህል ፓትርያርኩ ኢግናትየስ (ከ799 ገደማ-878 እዘአ) ባርዳስ የተባለውን ጠቅላይ ሚኒስትር ቁርባን እንዳይወስድ በከለከለው ጊዜ ባርዳስ ሁኔታውን አሜን ብሎ አልተቀበለም። አድማና ክሕደት ፈጽሞብኛል በሚል ኢግናትየስን ከከሰሰው በኋላ እንዲታሠርና ከሥልጣኑ እንዲወገድ አድርጓል። ከዚያም በእርሱ ምትክ በስድስት ቀን ውስጥ ሁሉንም የቤተ ክርስቲያን የሥልጣን እርከኖች ለመውጣትና በመጨረሻም ፓትርያርክ ለመሆን የበቃውን ፎሼስ የተባለ ተራ ሰው እንዲመረጥ አደረገ። ፎሼስ ለዚህ ሥልጣን የሚበቃ ሰው ነበር? ፎሼስ “የሥልጣን ጥም የተጠናወተው፣ ትዕቢት የወጠረውና ከፍተኛ የፖለቲካ ችሎታ የነበረው” ሰው እንደሆነ ይነገርለታል።
የቤተ ክርስቲያን ቀኖና ለፖለቲካዊ ሽፋን ሲውል
በኦርቶዶክሶችና በመናፍቃን መካከል ይካሄድ የነበረው ክርክር አብዛኛውን ጊዜ ፖለቲካዊውን ተቃውሞ ይሸፍነው ነበር። በተጨማሪም በአብዛኞቹ ነገሥታት ላይ ተጽእኖ አሳድሮ የነበረው አዳዲስ መሠረተ ትምህርቶችን የማስተዋወቅ ፍላጎት ሳይሆን ፖለቲካዊ ውጥኖችን የማሳካት ምኞት ነበር። ጠቅለል ባለ አነጋገር ንጉሠ ነገሥቱ የቤተ ክርስቲያን ድንጋጌዎችን የማስፈጸምና ቤተ ክርስቲያኑን ለፈቃዱ የማስገዛት ሥልጣን ነበረው።
ለምሳሌ ያህል ንጉሠ ነገሥት ሄራኩለስ (575-641 እዘአ) ሊፈራርስ በተቃረበ ግዛቱ ውስጥ የክርስቶስን መለኮትነት አስመልክቶ የተፈጠረውን መከፋፈል ለማስቀረት ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ነበር። ስምምነት ለመፍጠር በማሰብ ሞኖቴሊትዝም የተባለ አዲስ መሠረተ ትምህርት አስተዋወቀ። a ከዚያም የደቡባዊ ግዛቶቹን ታማኝነት ለማረጋገጥ እንዲረዳው እርሱ የደገፈውን መሠረተ ትምህርት የተቀበለ የፌሲሱ ቂሮስ የሚባል አንድ አዲስ ፓትርያርክ በእስክንድርያ ሾመ። ንጉሠ ነገሥቱ ቂሮስን ፓትርያርክ ብቻ ሳይሆን የመላው ግብጽ አገረ ገዢም አደረገው። ቂሮስ ትንሽ ተቃውሞ ቢደርስበትም የአብዛኞቹን የግብጽ አብያተ ክርስቲያናት ድጋፍ አግኝቷል።
መራራ ውጤት
እነዚህ ድርጊቶች ኢየሱስ “ከዓለም አይደሉም” በማለት ስለ ተከታዮቹ ያቀረበውን ጸሎት ቃላትና መንፈስ እንዴት ሊያንጸባርቁ ይችላሉ?—ዮሐንስ 17:14-16
በባይዛንታይን የግዛት ዘመን የነበሩትም ሆኑ የኋለኞቹ ክርስቲያን ነን ባይ የሃይማኖት መሪዎች ከዓለም ፖለቲካና የጦር ኃይል ጋር ከነበራቸው ትስስር የተነሳ መራራ ውጤት አጭደዋል። ታዲያ ይህ አጭር ታሪካዊ ቅኝት ምን ያስተምርሃል? የባይዛንታይን ቤተ ክርስቲያን መሪዎች የአምላክንና የኢየሱስ ክርስቶስን ሞገስ አግኝተዋል?—ያዕቆብ 4:4
እውነተኛ ክርስትና እነዚህን ከመሰሉት የሥልጣን ጥም የተጠናወታቸው ሃይማኖታዊ መሪዎችም ሆነ ከፖለቲካዊ ውሽሞቻቸው አንዳችም ያገኘው ጥቅም የለም። እንዲህ ያለው የረከሰ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ትስስር ሰዎች ኢየሱስ ያስተማረውን ንጹሕ ሃይማኖት በተሳሳተ መንገድ እንዲረዱት አድርጓል። እንግዲያው ከታሪክ በመማር “የዓለም ክፍል” አንሁን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ሞኖቴሊትዝም ማለት ክርስቶስ አምላክም ሰውም ነው። ይሁንና ፈቃዱ አንድ ነው።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
“በሰማያት መካከል እንደሚንጎራደድ አምላክ”
በፓትርያርክ ሚካኤል ሴሉላሪየስ (ከ1000 ገደማ-1059) ዘመን የተፈጸሙት ክንውኖች በወቅቱ ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል በመንግሥት ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ትገባ እንደነበረና ለዚህም በዋነኛነት አስተዋጽኦ ያደረገው የሥልጣን ምኞት እንደሆነ የሚያሳይ ዓይነተኛ ማስረጃ ነው። ሴሉላሪየስ ፓትሪያርክ ከሆነም በኋላ ሌላ ተጨማሪ ነገር ፈለገ። “ትዕቢተኛ፣ ኩሩና ግትር” የሚል ስም ያተረፈ ሲሆን “በሰማያት መካከል እንደሚንጎራደድ አምላክ” ተደርጎ ተገልጿል።
ሴሉላሪየስ ራሱን በራሱ ለማሳደግ ካለው ምኞት የተነሣ በ1054 ሮም ከሚገኘው ሊቀ ጳጳስ ጋር በመሻረክ አንድ ክፍፍል ጠነሰሰ። ከዚያም ንጉሠ ነገሥቱ ክፍፍሉን እንዲቀበል አስገደደው። ባገኘው ድል የተደሰተው ሴሉላሪየስ ሚካኤል አራተኛን ንጉሠ ነገሥት ካደረገ በኋላ ሥልጣኑን እንዲያጠናክር ረዳው። ከአንድ ዓመት በኋላ ሴሉላሪየስ ይህንኑ ንጉሠ ነገሥት አስገድዶ ከሥልጣኑ ካስወረደው በኋላ በምትኩ ይስሐቅ ካምኒነስ (ከ1005 ገደማ-1061) የተባለ ሰው አስቀመጠ።
በፓትርያርኩና በንጉሠ ነገሥቱ መካከል ያለው ግጭት እየተካረረ በመሄዱ የሕዝብ ድጋፍ እንዳለው እርግጠኛ የነበረው ሴሉላሪየስ ማስፈራራት፣ ማስገደድና ዓመፅን እንደ መሣሪያ አድርጎ መጠቀም ጀመረ። አንድ በዘመኑ የነበሩ ታሪክ ጸሐፊ እንደገለጹት “‘ከፍ አድርጌህ ነበር። አንተ ጅል። አሁን ግን አጠፋሃለሁ’ የሚሉትን የስድብ ቃላት በመጠቀም የንጉሠ ነገሥቱን ውድቀት አስቀድሞ” ተናግሮ ነበር። ሆኖም ሴሉላሪየስ ይስሐቅ ኮምኒነስን አስይዞ ካሳሰረው በኋላ ከአገር በማስወጣት ወደ ኢምብሮስ እንዲላክ አድርጓል።
እነዚህ ምሳሌዎች የቁስጥንጥንያው ፓትርያርክ ምን ያህል ችግር ይፈጥርና የንጉሠ ነገሥቱን ሥልጣን ይዳፈር እንደነበረ ያሳያሉ። ንጉሠ ነገሥቱ አብዛኛውን ጊዜ የእርሱንም ሆነ የጦር ኃይሉን ትእዛዝ የሚጥሱ ፖለቲከኞችን መቋቋም ነበረበት።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የባይዛንታይን ግዛት ጠቅላላ ስፋት
ራቬና
ሮም
መቄዶንያ
ቁስጥንጥንያ
ጥቁር ባሕር
ኒቂያ
ኤፌሶን
አንጾኪያ
ኢየሩሳሌም
እስክንድርያ
ሜዲትራንያን ባሕር
[ምንጭ]
ካርታ:- Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.
[በገጽ 10, 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኮምኒነስ
ሳልሳዊ ሮማነስ (በስተግራ)
ሚካኤል አራተኛ
ንግሥት ዞኢ
ቀዳማዊ ሮማነስ (በስተግራ)
[ምንጭ]
ኮምኒነስ፣ ሳልሳዊ ሮማነስና ሚካኤል አራተኛ:- Courtesy Classical Numismatic Group, Inc.; ንግሥት ዞኢ:- Hagia Sophia; ቀዳማዊ ሮማነስ:- Photo courtesy Harlan J. Berk, Ltd.
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፖይተስ
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሄራክለስና ልጁ
[ምንጭ]
ሄራክለስና ልጁ:- Photo courtesy Harlan J. Berk, Ltd.; all design elements, pages 8-12: From the book L’Art Byzantin III Ravenne Et Pompose