ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ
ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ
አውሮፓ በሚገኙ የአልፕስ ተራሮች አናት ላይ አልፓይን ሮዝ የሚባል ጠንካራ ቁጥቋጦ በቅሎ መመልከት ትችላለህ። አብዛኛውን ጊዜ ይህ ድንክ አልፓይን ሮዝ ከከፍታ ቦታ ከሚነፍሰው ኃይለኛ ነፋስ ለመሸሸግ ጥቅጥቅ ባለ ጥሻ ውስጥ ተፋፍጎ ያድጋል። ያለማቋረጥ የሚነፍሰው ነፋስ ሙቀቱን በመቀነስ፣ አየሩንና አፈሩን በማድረቅ እንዲሁም ሥሩን በመነቃቀል የተክሉን ሕልውና አደጋ ላይ ጥሎታል።
አልፓይን ሮዝ ብዙውን ጊዜ በተሰነጣጠቁ አለቶች መሃል በማደግ ከኃይለኛው ነፋስ ያመልጣል። እዚህ ቦታ ላይ ብዙ አፈር ባይኖርም ስንጥቁ ተክሉን ከነፋስ ይከላከልለታል እንዲሁም ውኃ እንዲቆጥብ ያስችለዋል። ይህ ተክል ለብዙ ወራት ከእይታ ተሰውሮ ይቆይና ልክ በጋ ሲጠባ ተራሮቹን በደማቅ ቀይ አበባ ያስውባቸዋል።
ነቢዩ ኢሳይያስ አምላክ ‘መሳፍንትን’ እንደሚሾምና እያንዳንዳቸውም “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ” ሆነው እንደሚያገለግሉ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 32:1, 2) እነዚህ መንፈሳዊ መሳፍንት ወይም የበላይ ተመልካቾች በንጉሡ በክርስቶስ ኢየሱስ አመራር ሥር በመሆን ውጥረት ወይም ጭንቀት በሚያጋጥምበት ጊዜ እንደማይነዋወጡ አለቶች ጽኑ ይሆናሉ። ችግር ለገጠማቸው አስተማማኝ ከለላ ይሆኑላቸዋል እንዲሁም ከአምላክ ቃል ያጠራቀሙትን መንፈሳዊ ውኃ እንዲጠብቁ ይረዷቸዋል።
እንደ ኃይለኛ ነፋስ ያለ ስደት፣ ተስፋ መቁረጥ አሊያም ሕመም አንድን ክርስቲያን ሊያንገላታውና እምነቱን ሊያዳክምበት ይችላል። ክርስቲያን ሽማግሌዎች በትኩረት በማዳመጥ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር፣ ማበረታቻና ተግባራዊ እርዳታ በመስጠት ከለላ ሊሆኑለት ይችላሉ። እንደ ንጉሣቸው እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ እነርሱም ‘የተጣሉትን’ ለመርዳት ይፈልጋሉ። (ማቴዎስ 9:36) በሐሰት ትምህርት ማዕበል ጉዳት የደረሰባቸውንም ለመርዳት ይፈልጋሉ። (ኤፌሶን 4:14) እንዲህ ያለው በተገቢው ጊዜ የሚሰጥ እርዳታ ጠቃሚ ሆኖ ሊገኝ ይችላል።
ሚርያም “አንዳንድ የቅርብ ጓደኞቼ እውነትን ትተው ሲሄዱና በዚሁ ወቅትም አባቴ አንጎሉ ውስጥ ደም ፈስሶት ሲሰቃይ ስመለከት ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ያዘኝ” በማለት ገልጻለች። “ጭንቀቴን ለመቋቋም ስል አንድ ዓለማዊ የወንድ ጓደኛ ያዝኩ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ የከንቱነት ስሜት አደረብኝ። ይሖዋ አይወደኝም ብዬ በማሰብ እውነትን ለመተው መወሰኔን ለጉባኤው ሽማግሌዎች ነገርኳቸው።
“በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ አንድ አፍቃሪ ሽማግሌ የዘወትር አቅኚ ሆኜ ያገለገልኩባቸውን ዓመታት እንዳስታውስ አደረገኝ። ታማኝነቴን ዘወትር ያደንቅ እንደነበረም ገለጸልኝ። ከዚያም ይሖዋ እንደሚወደኝ በማረጋገጥ ሽማግሌዎች የሚሰጡኝን እርዳታ በፈቃደኝነት እንድቀበል በደግነት ጠየቀኝ። በዚያ ወሳኝ ወቅት ላይ ሽማግሌዎቹ ያሳዩኝ ፍቅራዊ አሳቢነት በዙሪያዬ አንዣብቦ ከነበረው መንፈሳዊ ማዕበል ‘መሸሸጊያ’ ሆኖልኛል። አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከወንድ ጓደኛዬ ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቋረጥኩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በእውነት መንገድ ላይ መጓዜን ቀጥያለሁ።”
ሽማግሌዎች የእምነት ባልንጀሮቻቸው በተገቢው ጊዜ ባገኙት ጥበቃ ምክንያት በመንፈሳዊ ሲያብቡ ሲመለከቱ ድካማቸው ከንቱ እንዳልቀረ ይገነዘባሉ። እንዲሁም እነዚህ ‘መሸሸጊያ ቦታዎች’ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት የምናገኘውን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ጥበቃ ለቅምሻ የሚያሳዩ ናቸው።