በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥቅም ማግኘት ትችላለህ

ከአምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥቅም ማግኘት ትችላለህ

ከአምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥቅም ማግኘት ትችላለህ

እንስሳት በደመ ነፍስ የሚመሩ መሆናቸውን እንደምታውቅ ጥርጥር የለውም። ብዙ ማሽኖች የተሠሩት መመሪያ እንዲቀበሉ ተደርጎ ነው። ይሁን እንጂ ሰዎች የተፈጠሩት በመሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲመሩ ተደርገው ነው። ይህን እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሁሉ ምንጭ የሆነው ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች በፈጠረበት ጊዜ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” በማለት ተናግሮ ነበር። ፈጣሪ መንፈስ ስለሆነ እንደ እኛ ያለ ሥጋዊ አካል የለውም። በመሆኑም ‘በምሳሌው’ ተፈጥረናል የምንለው ግሩም ባሕርያቱን በተወሰነ መጠን ማንጸባረቅ ስለምንችል ነው። ሰዎች ሕይወታቸውን በመሠረታዊ ሥርዓቶች ማለትም ትክክል ነው ብለው በሚያምኑበት ደንብ መሠረት የመምራት ችሎታ አላቸው። ይሖዋ ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል ብዙዎቹ በቃሉ ውስጥ እንዲሰፍሩ አድርጓል።​—⁠ዘፍጥረት 1:​26፤ ዮሐንስ 4:​24፤ 17:​17

ይሁን እንጂ አንድ ሰው ‘በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ መሠረታዊ ሥርዓቶች አሉ። ሁሉንም ማወቅ የምችል አይመስለኝም’ ይል ይሆናል። እውነት ነው። እስቲ የሚከተለውን ሐቅ ተመልከት:- ሁሉም አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጠቃሚ ቢሆኑም አንዳንዶቹ ከሌሎች ይበልጥ ክብደት ያላቸው ናቸው። ይህንን ኢየሱስ በሙሴ ሕግ ውስጥ ከሚገኙት ትእዛዛትና መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዳንዶቹ ከሌሎች እንደሚበልጡ ከጠቀሰበት ከማቴዎስ 22:​37-39 መገንዘብ ትችላለህ።

የበለጠ ክብደት የሚሰጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው? ቁልፍ የሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና በቀጥታ የሚነኩት ናቸው። በእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች የምንመራ ከሆነ በሥነ ምግባር ኮምፓሳችን ላይ ዋነኛውን ሚና የሚጫወተው ፈጣሪ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነቶች የሚነኩ መሠረታዊ ሥርዓቶችም አሉ። እነዚህንም ተግባራዊ ማድረጉ ምንም ዓይነት ስያሜ ይሰጠው እኔ ልቅደም የሚለውን መንፈስ እንድንቋቋም ይረዳናል።

እስቲ በመጀመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት የላቀ ቦታ ከሚሰጣቸው እውነቶች መካከል አንዱን እንመልከት። ይህ እውነት ምንድን ነው? እኛንስ የሚነካን እንዴት ነው?

“በምድር ሁሉ ላይም አንተ ብቻ ልዑል”

ቅዱሳን ጽሑፎች ይሖዋ ታላቁ ፈጣሪያችንና ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ እንደሆነ በግልጽ ይናገራሉ። የሚተካከለው ወይም የሚመሳሰለው ምንም ነገር የለም። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበ ቁልፍ እውነት ነው።​—⁠ዘፍጥረት 17:​1፤ መክብብ 12:​1

ከመዝሙር መጽሐፍ ጸሐፊዎች መካከል አንዱ ስለ ይሖዋ ሲናገር “በምድር ሁሉ ላይም አንተ ብቻ ልዑል” ነህ በማለት ገልጿል። የጥንቱ ንጉሥ ዳዊት “አቤቱ፣ መንግሥት የአንተ ነው፣ አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ” ብሏል። እንዲሁም ታዋቂው ነቢይ ኤርምያስ “አቤቱ፣ እንደ አንተ ያለ የለም፤ አንተ ታላቅ ነህ ስምህም በኃይል ታላቅ ነው” ብሎ ለመጻፍ ተገፋፍቷል።​—⁠መዝሙር 83:​18፤ 1 ዜና መዋዕል 29:​11፤ ኤርምያስ 10:​6

ስለ አምላክ የሚናገሩትን እነዚህን እውነቶች በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት ነው?

በሕይወታችን ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ መያዝ ያለበት ማን መሆኑ ግልጽ ነው። ፈጣሪያችንና ሕይወት ሰጪያችን መሆን አለበት። እንግዲያው በአንዳንዶች ላይ ጎልቶ የሚታየውን የሰዎችን ትኩረት ወደራስ የመሳብ ዝንባሌ እንዳያድርብን መታገሉ ተገቢ አይሆንም? “ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” የሚለው መመሪያ ጥበብ ያለበት መሠረታዊ ሥርዓት ነው። (1 ቆሮንቶስ 10:​31) በዚህ ረገድ ነቢዩ ዳንኤል ግሩም ምሳሌ ትቶልናል።

የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በአንድ ወቅት በተመለከተው ሕልም አንደተጨነቀና ፍቺውን ለማወቅ ጠይቆ እንደነበረ ታሪካዊው መዝገብ ያስረዳል። ሁሉም ሰው ግራ ሲጋባ ዳንኤል ግን ንጉሡ ማወቅ የፈለገውን ሁሉ በትክክል ነገረው። ዳንኤል ለዚህ ነገር እንዲመሰገን ፈልጎ ነበር? በጭራሽ። ክብሩን ‘በሰማይ ለሚኖረው ምሥጢር ለሚገልጥ አምላክ’ ሰጥቷል። ዳንኤል በመቀጠል “በዚህ ዓለም ካሉ ሰዎች ይልቅ በጥበብ ስለ በለጥሁ አይደለም” በማለት ተናግሯል። ዳንኤል በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ ሰው ነበር። በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ሦስት ጊዜ በአምላክ ዘንድ “እጅግ የተወደድህ” ተብሎ መጠራቱ ምንም አያስደንቅም።​—⁠ዳንኤል 2:​28, 30፤ 9:​23፤ 10:​11, 19

አንተም የዳንኤልን ምሳሌ ብትከተል ትጠቀማለህ። በአንደኛ ደረጃ ከዳንኤል የሚገኘው ትምህርት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ መያዝ ነው። ላከናወንከው ሥራ መከበር የሚገባው ማን ነው? ያለህበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ሉዓላዊ ጌታ ነው ከሚለው እጅግ አስፈላጊ ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር የሚስማማ ተግባር መፈጸም ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ በአምላክ ፊት ‘እጅግ እንድትወደድ’ ያደርግሃል።

አሁን ደግሞ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ መመሪያ ሊሆኑን የሚችሉ ሁለት ወሳኝ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንመልከት። ለራስ የተጋነነ አመለካከት መስጠት በእጅጉ በተስፋፋበት በዚህ ጊዜ ይህ የሕይወት ዘርፍ ይበልጥ ተፈታታኝ ነው።

“በትሕትና”

ራሳቸውን ማስቀደም የሚፈልጉ ሰዎች እምብዛም እርካታ አያገኙም። ብዙዎች ሁልጊዜ የተሻለ ሕይወት መኖርና ይህንንም አሁኑኑ ማግኘት ይፈልጋሉ። ለእነርሱ ልክን ማወቅ የድክመት ምልክት ነው። ትዕግሥት ሌሎች ሰዎች ብቻ ሊያሳዩት የሚገባ ባሕርይ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ለእነርሱ እውቅና የሚያስገኝላቸው ከሆነ ግን ሁሉም ነገር የተፈቀደ ነው። አንተም የእነርሱ ዓይነት ጠባይ ለማሳየት የሚያስችል አማራጭ እንዳለህ ሆኖ ይሰማሃል?

የአምላክ አገልጋዮች እንዲህ ያለው ባሕርይ በየዕለቱ ያጋጥማቸዋል። ይሁን እንጂ ሊጋባባቸው አይገባም። የጎለመሱ ክርስቲያኖች “እግዚአብሔር የሚያመሰግነው እንጂ ራሱን የሚያመሰግን እርሱ ተፈትኖ የሚወጣ አይደለምና” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት ይቀበላሉ።​—⁠2 ቆሮንቶስ 10:​17, 18

በፊልጵስዩስ 2:​3, 4 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ይጠቅማል። ይህ ጥቅስ ‘ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ እንዳታደርግ ከዚያ ይልቅ ባልንጀራህ ከራስህ ይልቅ እንደሚሻል በትሕትና እንድትቆጥር’ ያበረታታሃል። በዚህ መንገድ ‘ለራስህ የሚጠቅምህን ሳይሆን ለባልንጀራህ የሚጠቅመውን ትመለከታለህ።’

ከጥንቶቹ ዕብራውያን መሳፍንት አንዱ የሆነው ጌዴዎን ስለ ራሱ ጤናማ አመለካከትና ያልተጋነነ ግምት የነበረው ሰው ነው። የእስራኤል መሪ ለመሆን አልፈለገም። ይሁን እንጂ ጌዴዎን መሪ እንዲሆን በተመረጠ ጊዜ ለቦታው እንደሚበቃ ሆኖ አልተሰማውም። “ወገኔ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው፤ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ” በማለት መለሰ።​—⁠መሳፍንት 6:​12-16

ከዚህም በላይ ይሖዋ ጌዴዎንን ድል ካቀዳጀው በኋላ የኤፍሬም ሰዎች ሊጣሉት ፈለጉ። ጌዴዎን ምን ምላሽ ሰጠ? ያገኘው ድል ከሌሎች የበለጠ ሆኖ እንዲሰማው አድርጎት ይሆን? በጭራሽ። የለዘበ መልስ በመስጠት ሊደርስ ይችል የነበረውን አደጋ አስቀርቷል። “እናንተ ያደረጋችሁትን የሚመስል እኔ ምን ማድረግ እችል ኖሮአል?” ጌዴዎን ትሑት ሰው ነበር።​—⁠መሳፍንት 8:​1-3

እርግጥ ጌዴዎን ያጋጠመው ሁኔታ ከተከሰተ ረጅም ዘመናት አልፈዋል። ሆኖም ታሪኩን በመመርመር አሁንም ጥቅም ማግኘት ይቻላል። ጌዴዎን በዛሬው ጊዜ ተስፋፍቶ ከሚገኝ ዝንባሌ ፈጽሞ የተለየ ባሕርይ እንዳንጸባረቀና ከዚህም ባሕርይ ጋር ተስማምቶ በመኖሩ ጥቅም እንዳገኘ መመልከት ትችላለህ።

በራስ ላይ ትኩረት እንድናደርግ ግፊት የሚያደርገው ዝንባሌ ለራሳችን የሚኖረንን ግምት ሊያዛባው ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከፈጣሪና ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ያለንን ትክክለኛ ቦታ እንድናውቅ በማስተማር ይህን የተዛባ አስተሳሰብ ያስተካክሉልናል።

የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ ይህ ዓለም ከተጠናወተው መንፈስ መራቅ እንችላለን። ከእንግዲህ ወዲህ በስሜት ወይም በግል አስተሳሰብ አንመራም። ስለ ጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይበልጥ በተማርን መጠን እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ከሰጠው አካል ጋር ይበልጥ እንተዋወቃለን። አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ በምናነብበት ጊዜ ለአምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች የተለየ ትኩረት ለመስጠት ጥረት ብናደርግ በብዙ እንካሳለን።​—⁠ሣጥኑን ተመልከት።

ይሖዋ ሰዎችን የፈጠራቸው በደመ ነፍስ ከሚንቀሳቀሱ እንስሳት አስበልጦ ነው። የአምላክን ፈቃድ መከተል መለኮታዊ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ሥራ ላይ ማዋልንም ይጨምራል። በዚህ መንገድ አምላክ ወዳዘጋጀው አዲስ ሥርዓት የሚያመለክተው የሥነ ምግባር ኮምፓስ በትክክል መሥራቱን እንዲቀጥል ማድረግ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጽድቅ የሚኖርበት’ አዲስ ምድር አቀፍ ሥርዓት በቅርቡ እንደሚመጣ ማስረጃ ይሰጠናል።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:​13

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ጠቃሚ የሆኑ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች

በቤተሰብ ውስጥ፦

“እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:​24

“ፍቅር . . . የራሱንም አይፈልግም።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 13:​4, 5

“ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት።”​—⁠ኤፌሶን 5:​33

“ሚስቶች ሆይ፣ በጌታ እንደሚገባ ለባሎቻችሁ ተገዙ።”​—⁠ቆላስይስ 3:​18

“የወለደህን አባትህን ስማ፣ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት።”​—⁠ምሳሌ 23:​22

በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ ወይም በንግድ አካባቢ፦

“እግዚአብሔር የተጭበረበረ ሚዛንን ይጸየፋል፤ . . . ክፉ ሰው የሚያገኘው ትርፍ መቅኖ የለውም።”​—⁠ምሳሌ 11:​1, 18 አ.መ.ት

“የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፣ ነገር ግን በዚያ ፈንታ . . . መልካምን እየሠራ ይድከም።”​—⁠ኤፌሶን 4:​28

“ሊሠራ የማይወድ አይብላ።”​—⁠2 ተሰሎንቄ 3:​10

“ለጌታ እንደምታደርጉ፣ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት።”​—⁠ቆላስይስ 3:​23

“በነገር ሁሉ በመልካም [“በሐቀኝነት፣” NW ] እንድንኖር [ወደናል]።”​—⁠ዕብራውያን 13:​18

ለሀብት ሊኖር ስለሚገባው አመለካከት፦

“ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኩል ግን ሳይቀጣ አይቀርም።”​—⁠ምሳሌ 28:​20

“ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም።”​—⁠መክብብ 5:​10

ለራሳችን ስለምንሰጠው ግምት መመርመር፦

“የራስን ክብር መፈላለግ አያስከብርም።”​—⁠ምሳሌ 25:​27

“ሌላ ያመስግንህ እንጂ አፍህ አይደለም።”​—⁠ምሳሌ 27:​2

“ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ።”​—⁠ሮሜ 12:​3

“አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና።”​—⁠ገላትያ 6:​3

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳንኤል ለአምላክ የሚገባውን ክብር ሰጥቷል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ሌሎችን መያዝ አስደሳች ወዳጅነት ለመመሥረትና ደስተኛ ለመሆን ይረዳል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

U.S. Fish & Wildlife Service, Washington, D.C./Robert Bridges