በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዚህ ቀደም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ትመላለስ ነበርን?

ከዚህ ቀደም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ትመላለስ ነበርን?

ከዚህ ቀደም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ትመላለስ ነበርን?

ወጣቱ ልጅ በኃፍረትና በሐዘን ተውጦ ይታያል። የተቦጫጨቁትና የተዘባተሉት ልብሶቹ በአንድ ወቅት ምርጥ እንደነበሩ ያስታውቃሉ። የአሁኑ ይዞታቸው ግን ችግር ውስጥ መውደቁን ይናገራሉ። ሐሳቡ ከአድማስ ባሻገር ወደሚገኘው ትውልድ አገሩ ሲወስደው እስከ አሁን ያሳለፈው ብልሹ ሕይወትና ካልተሰጠኝ ሞቼ እገኛለሁ ብሎ ያለጊዜው የወሰደውን ውርስ ያባከነበት መንገድ ያንገበግበዋል። ሆዱን የሚሞረሙረው ረሃብ ችግሩን ይበልጥ ያባባሰበት ሲሆን ዘመዶቹም በጣም ናፍቀውታል። የሚገርመው በአባቱ ቤት ያሉ አገልጋዮች እንኳን ከእርሱ የተሻለ ኑሮ ይኖራሉ! ከእነርሱ እንደ አንዱ ቢሆን ምንኛ ደስ ባለው!

ይሁን እንጂ ወደ ቤት ቢመለስ አባትየው ምን ዓይነት አቀባበል ያደርግለት ይሆን? አባቱ በደግነት ያደረገለትን በሚያሳፍር መንገድ ካባከነ በኋላ አሁን እቤት ቢመለስ ሞቅ ባለ መንፈስ ይቀበለኛል ወይም እቤት እንድገባ ይፈቀድልኛል ብሎ እንደማይጠብቅ የታወቀ ነው። የሆነው ሆኖ ወደ ቤትህ መመለስ አለብህ የሚል ጥልቅ ስሜት አእምሮውንና ልቡን ገፋፋው።

ይህ ወጣት ልጅ አባቱ ለእርሱ ስለሚኖረው ስሜት የነበረው አመለካከት ምንኛ የተሳሳተ ነበር! ወደ ቀድሞ ቤቱ ሲቃረብ በዓይኑ ያየውን ነገር ማመን አቃተው! እንዲያውም “እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፣ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው።”​—⁠ሉቃስ 15:​20

አንተም እንደ አባካኙ ልጅ ቤትህን ጥለህ ሄደሃልን? ከአባትህ ከይሖዋና ከድርጅቱ ርቀህ ሄደሃልን? አሁንስ ‘ወደ ቤትህ መመለስ’ ትፈልጋለህ?

ብዙውን ጊዜ እንደታየው አንዳንዶች የይሖዋን ድርጅት ትተው የሄዱት ልክ እንደ ኮብላዩ ልጅ ነው ማለት አይደለም። ብዙዎቹ አንዲት ትንሽ ጀልባ እየተንሳፈፈችና እየዋለለች ቀስ በቀስ ከመሬት እንደምትርቅ ሁሉ እነርሱም ቀስ በቀስ እንዲያውም ሳይታወቅ ጠፍተዋል። አንዳንዶቹ የገጠማቸው የገንዘብ ችግር፣ የቤተሰብ ችግር፣ በሽታ ወይም በዓለም ውስጥ “ከፍ ያለ ደረጃ ላይ የመድረስ” ፍላጎት ጊዜያቸውን ከማጣበቡ የተነሳ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ጊዜ እንዲያጡ አድርጓቸዋል። ሌሎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች እንዲያደናቅፏቸው በመፍቀዳቸው ወይም የይሖዋ ድርጅት አንድን ቅዱስ ጽሑፋዊ ነጥብ አስመልክቶ የሰጠው ማብራሪያ ስላልተዋጠላቸው ድርጅቱን ጥለው ሄደዋል። ሌሎች ደግሞ የዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ እነርሱ በጠበቁት ጊዜ ሳይመጣ በመቅረቱ ምክንያት ተስፋ ቆርጠው በድርጅቱ ውስጥ መመላለሳቸውን አቁመዋል።

አንተም ከላይ ከተገለጹት በአንዱ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ምክንያቶች የተነሳ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ መመላለስህን አቁመህ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን አሁን መመለስ እንዳለብህ ማሰብ አይኖርብህም?​—⁠ማቴዎስ 18:​12-14

ተሰናክለህ ታውቃለህ?

የሰው ዘር ከፍጽምና ምን ያህል እንደራቀ ግምት ውስጥ ማስገባታችን የባሕርይ አለመጣጣም ሊያጋጥም እንደሚችል እንድንገነዘብ ሊያደርገን ይችላል። ይህ አንዳንዶች እንዲሰናከሉ አድርጓቸዋል። ሌሎች ደግሞ በጣም የሚያከብሩት አንድ ግለሰብ ድንገት የችኮላ እርምጃ በመውሰዱ ወይም ክርስቲያናዊ ያልሆነ ባሕርይ በማሳየቱ ወይም ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት ተሰናክለዋል።

አንተም እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞሃል? መሰናክል የሆነብህ ምንም ይሁን ምን መሰናክሉን ያስቀመጠው ይሖዋ እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። (ከገላትያ 5:​7, 8 ጋር አወዳድር።) ስለሆነም አንድ ግለሰብ በወሰደው እርምጃ የተነሳ ከእርሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት እንድናቋርጥ ሊያደርገን ይገባል? ከዚህ ይልቅ ከይሖዋ የተሰወረ ነገር እንደሌለና እኛንም በፍቅር እንደሚይዘን በመተማመን እርሱን በታማኝነት ማገልገላችንን መቀጠል አይኖርብንም?​—⁠ቆላስይስ 3:​23-25

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ አንዳንዶች በአንድ ወቅት መሰናክል የሆነባቸው ምክንያት አሁን እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ወይም ከናካቴው መወገዱን ይገነዘባሉ። ወይም ጉዳዩን ረጋ ብለው ሲያስቡት ጥፋተኞቹ እነርሱ ራሳቸው መሆናቸውን ተገንዝበውም ሊሆን ይችላል። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው የተሰጠው ምክር ወይም ተግሣጽ እንዲያዝንና እንዲሰናከል በሚያደርገው ጊዜ ይህ ሁኔታ ይከሰታል። ሆኖም ሁኔታውን መለስ ብሎ ሲያስበው እንዲህ ያለው ተግሣጽ በእውነተኛ ፍቅርና ለራሱ ጥቅም ሲባል እንደተሰጠው ይገነዘባል። (ዕብራውያን 12:​5-11) እንግዲያው ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረጉ ምንኛ የተገባ ነው! እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የላሉትን እጆች የሰለሉትንም ጒልበቶች አቅኑ፤ ያነከሰውም እንዲፈወስ እንጂ እንዳይናጋ፣ ለእግራችሁ ቅን መንገድ አድርጉ።”​—⁠ዕብራውያን 12:​12, 13

ለአንድ ትምህርት የተሰጠው ማብራሪያ አልተዋጠልህም?

የይሖዋን ድርጅት ትተህ የሄድከው በአንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ነጥቦች ረገድ ያለህ መረዳት የተለየ በመሆኑ ሊሆን ይችላል። በግብፅ ይደርስባቸው ከነበረው መከራ የዳኑት እስራኤላውያን ‘አምላክ ያደረገላቸውን ሥራ ፈጥነው በመርሳታቸው’ ‘በምክሩ ለመሄድ ሳይታገሡ’ እንደቀሩት ሁሉ አንተም ትክክል ነው ብለህ ያመንክበትን ሐሳብ ድርጅቱ ባለመቀበሉ ምክንያት ከድርጅቱ ጋር ያለኝን ግንኙነት ማቋረጥ አለብኝ የሚል የችኮላ እርምጃ ወስደህ ይሆናል። (መዝሙር 106:​13) ምናልባት ከዚያ ወዲህ ሐሳቡ በአምላክ መንፈስ መሪነት ተጨማሪ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምርምር ተደርጎ ትክክለኝነቱ ተረጋግጦ ወይም ተለውጦ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ የሚሰጠውን ምላሽ በመጠበቅ በድርጅቱ ውስጥ መቆየት የተሻለ አይሆንም ነበር?

ይሖዋ ከአንድ ድርጅት በላይ እንደማይጠቀም ማስታወሱ ጥሩ ነው። በዘመናችን “ታማኝና ልባም ባሪያ” “በጊዜው” መንፈሳዊ ምግብ በማሰራጨት ላይ ይገኛል። ይህ ባሪያ ‘ጌታው ሲመጣ እንዲህ ሲያደርግ ሊያገኘው’ እንደሚገባ ልብ በል። (ማቴዎስ 24:​45-47) ጌታ ቀደም ሲል እንደመጣ በዛሬው ጊዜ የተገነዘበው ማን ነው? ጌታው የሰጠውን ሥራ ለማከናወን ከላይ ታች የሚለው ማን ነው? በይሖዋ የክርስቲያን ምሥክሮች ድርጅት ውስጥ የሚመላለሱ ብቻ ናቸው!

ሌሎች ኢየሱስን ትተውት ሲሄዱ ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” ብሎት ነበር። ጴጥሮስ ኢየሱስ መሲህ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። ስለዚህ ብዙዎቹ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ የተናገራቸው አንዳንድ ቃላት አስደንጋጭ ሲሆኑባቸው ጴጥሮስ “የዘላለም ሕይወት ቃል” ምንጭ የሆነውን ኢየሱስን ትቶ መሄዱ ጥበብ እንዳልሆነ ተገንዝቧል። ማንኛውም ዓይነት ጥርጣሬ ወይም የተሳሳተ እውቀት በጊዜ ሂደት መስተካከሉ የማይቀር ነው። (ዮሐንስ 6:​51-68፤ ከሉቃስ 24:​27, 32 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ አገልጋዮቹን በሕይወት መንገድ ላይ እንዲጓዙ ያለማቋረጥ በሚመራቸው በዚህ ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።​—⁠ምሳሌ 4:​18

አሁኑኑ ተመለስ

ነቢዩ ኤርምያስ “መንገዳችንን እንመርምርና እንፈትን፣ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ” በማለት ተማጽኗል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:​40) ይሁን እንጂ አንዳንዶች ብመለስ ሌሎች የጉባኤው አባላት ጥሩ አቀባበል አያደርጉልኝ ይሆናል ብለው በመስጋት ከመመለስ ወደ ኋላ ይላሉ። ይሁን እንጂ አባካኙ ልጅ ወደ ቤት በተመለሰ ጊዜ ምን ዓይነት አቀባበል ተደረገለት? አባትየው “ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን . . . ይገባናል” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 15:​32) ፈቃዱን ለማድረግ ልባዊ ፍላጎት አድሮባቸው ‘ወደ ይሖዋ የሚመለሱትም’ በተመሳሳይ ሞቅ ያለ አቀባበል ይደረግላቸዋል።​—⁠ከሉቃስ 15:​7 ጋር አወዳድር።

ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ‘ወደ ቤት መመለስ’ አለብኝ ብለው በሚመጡበት ጊዜ የክርስቲያን ጉባኤ ዳር ቆሞ አይመለከታቸውም። ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው አባት ልጁ “ገና ሩቅ ሳለ” ሊቀበለው ሮጧል። በተመሳሳይም የይሖዋ ምሥክሮች በአንድ ወቅት በድርጅቱ ውስጥ ይመላለሱ የነበሩትን የመፈለግና እንዲመለሱ የመርዳት ግዴታ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል።

ይሁን እንጂ አንድ ግለሰብ ከይሖዋ ድርጅት ርቆ በቆየበት ጊዜ ውስጥ ከባድ ኃጢአት ፈጽሞ ቢሆንስ? ወይም ደግሞ አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት ከአምላክ ሕዝቦች መካከል ተወግዶ ከዚያ ወዲህ ክርስቲያናዊ ያልሆነ አኗኗር መከተሉን አቁሞ ቢሆንስ? ሽማግሌዎች እንዲህ ያለው ሰው ከይሖዋ ጋር መልሶ መታረቅ ይችል ዘንድ በደግነትና ፍቅራዊ በሆነ መንገድ እንዴት መርዳት እንደሚችሉ ያውቃሉ። ስለዚህ መመለስና ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ፍላጎቱን ለሽማግሌዎች ማሳወቅ ይኖርበታል። “ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር፤ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች።”​—⁠ኢሳይያስ 1:​18

የሰማዩ አባታችን ምንኛ ደግ፣ የሚቀረብና አፍቃሪ ነው! ምንኛ ታጋሽና ስለ እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ የሚያስብ ነው! በእርግጥም ከዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ጋር እንድንጠፋ አይፈልግም። (2 ጴጥሮስ 3:​9) የጥንት ሕዝቦቹን “ወደ እኔ ተመለሱ፣ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” በማለት የተማጸናቸው ይሖዋ ነው። ይህ ግብዣ አሁንም በማስተጋባት ላይ ይገኛል።​—⁠ሚልክያስ 3:​7

ጊዜው እያለቀ ስለሆነ እርምጃ ለመውሰድ አትዘግይ። ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ‘የአምላክን ሕግ የሚወድዱ ሰዎች የሚያገኙትን ሰላም’ በማግኘት መደሰትህን ቀጥል። መዝሙራዊው “ዕንቅፋትም የለባቸውም” ብሏል። (መዝሙር 119:​165) ለይሖዋ ሕግ የጠለቀ ፍቅር አለህ? ራስህን የወሰንክ የአምላክ አገልጋይ ከሆንክ ራስህን የወሰንከው ለዚሁ ነው። ከይሖዋ ጋር የነበረህን ዝምድና ከማደስ ጋር የሚወዳደር ምንም ነገር አዎን አንዳችም ነገር ሊኖር አይችልም። ጀርባህን አትስጠው። ጉዳዩን በጥንቃቄና በጸሎት አስብበት። የይሖዋ ሕዝቦች ያላቸው አንድነትና ሞቅ ያለ ወዳጅነት እንደቀረብህ ሆኖ የሚሰማህ ከሆነ ወደ ይሖዋ ድርጅት ለመመለስ እርምጃ የምትወስድበት ጊዜ አሁን ነው። ሳትዘገይ ይህንን አድርግ።