በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የሥጋ መውጊያን’ መቋቋም

‘የሥጋ መውጊያን’ መቋቋም

‘የሥጋ መውጊያን’ መቋቋም

“ይገባኛል የማትለው ደግነቴ ይበቃሃል።”2 ቆሮንቶስ 12:9 NW

1, 2. (ሀ) ፈተናዎችና ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ ግራ መጋባት የማይኖርብን ለምንድን ነው? (ለ) በፈተና ወቅት ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

 “በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:​12) ለምን? ምክንያቱም ሰይጣን ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ብቻ ነው የሚል ክስ ያነሳ ሲሆን ይህንንም ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ “ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ” በማለት ታማኝ ሐዋርያቱን አስጠንቅቋቸው ነበር። (ሉቃስ 22:31) ሰይጣን ሥቃይ በሚያስከትሉ ችግሮች እኛን እንዲፈትን አምላክ እንደፈቀደለት ኢየሱስ ያውቅ ነበር። ይህ ማለት ግን የሚደርሱብን መከራዎች በሙሉ በቀጥታ ሰይጣን ወይም አጋንንቱ የሚያመጧቸው ናቸው ማለት አይደለም። (መክብብ 9:​11) ሆኖም ሰይጣን የተቻለውን ሁሉ በመጣር ጽኑ አቋማችንን እንድናላላ ለማድረግ ይሞክራል።

2 ፈተና ሲያጋጥመን ግራ መጋባት እንደሌለብን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ምንም ዓይነት ፈተና ቢገጥመን አዲስ ወይም እንግዳ ነገር ሊሆንብን አይገባም። (1 ጴጥሮስ 4:12) እንዲያውም “በዓለም ያሉት ወንድሞቻች[ን] ያን መከራ በሙሉ” ይቀበላሉ። (1 ጴጥሮስ 5:9) በዛሬ ጊዜ ሰይጣን በእያንዳንዱ የአምላክ አገልጋይ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። ዲያብሎስ እንደ መውጊያ ባሉ በርካታ ችግሮች ስንሠቃይ ማየት ያስደስተዋል። በእኛ ላይ ተጨማሪ ‘የሥጋ መውጊያ’ ለማምጣት ወይም ያለብንን ለማባባስ በእርሱ ቁጥጥር ሥር ያለውን የነገሮች ሥርዓት መሣሪያ አድርጎ ይጠቀማል። (2 ቆሮንቶስ 12:7) የሆነ ሆኖ ሰይጣን የሚሰነዝረው ጥቃት ጽኑ አቋማችንን እንድናላላ ሊያደርገን አይገባም። ይሖዋ ፈተናዎችን በጽናት መቋቋም እንችል ዘንድ ‘መውጫውን’ እንደሚያዘጋጅ ሁሉ እንደ ሥጋ መውጊያ ያሉ ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜም እንዲሁ ተመሳሳይ ዝግጅት ያደርግልናል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:13

መውጊያን መቋቋም የሚቻልበት መንገድ

3. ጳውሎስ የሥጋውን መውጊያ እንዲያስወግድለት ይሖዋን በጠየቀ ጊዜ ምን ምላሽ ሰጠው?

3 ሐዋርያው ጳውሎስ የገጠመውን የሥጋ መውጊያ እንዲያስወግድለት አምላክን ለምኖት ነበር። “ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ።” ይሖዋስ ለጳውሎስ ልመና ምን ምላሽ ሰጠ? “ይገባኛል የማትለው ደግነቴ ይበቃሃል፤ ኃይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ነውና።” (2 ቆሮንቶስ 12:8, 9 NW ) አምላክ የሰጠውን መልስ እንመርምርና በእኛ ላይ ያለውን ማንኛውንም እንደ መውጊያ ያለ ችግር እንድንቋቋም የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

4. ጳውሎስ ይገባኛል በማይለው የይሖዋ ደግነት የተጠቀመው በምን መንገዶች ነው?

4 ጳውሎስ በክርስቶስ አማካኝነት ያገኘውን ይገባኛል የማይለውን ደግነት እንዲያደንቅ አምላክ እንዳበረታታው አስተውል። በእርግጥም ጳውሎስ በብዙ መንገዶች በእጅጉ ተባርኳል። ቀደም ሲል የኢየሱስን ተከታዮች በጭፍን ይቃወም የነበረ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ በፍቅሩ ተገፋፍቶ ደቀ መዝሙር የመሆን መብት ሰጥቶታል። (ሥራ 7:58፤ 8:3፤ 9:1-4) ከዚያም ይሖዋ አስደሳች የሆኑ በርካታ ኃላፊነቶችንና መብቶችን በደግነት ሰጥቶታል። ከዚህ ምን ትምህርት ልናገኝ እንደምንችል ግልጽ ነው። በጣም አስከፊ የሚባሉ ችግሮች እያሉብን እንኳ አመስጋኝ ልንሆንባቸው የሚገቡ ብዙ በረከቶች አሉን። የሚደርሱብን ፈተናዎች ይህ ነው የማይባለውን የይሖዋን በጎነት እንድንረሳ እንዲያደርጉን ፈጽሞ አንፍቀድ።​—⁠መዝሙር 31:19

5, 6. (ሀ) ይሖዋ መለኮታዊ ኃይል ‘በድካም ፍጹም እንደሚሆን’ ለጳውሎስ ያስተማረው እንዴት ነው? (ለ) የጳውሎስ ምሳሌ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ያረጋገጠው እንዴት ነው?

5 ይገባናል የማንለውን የይሖዋን ደግነት ማግኘቱ ብቻ በቂ እንደሆነ የሚያሳይ ሌላም ነገር አለ። አምላክ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች እንድንወጣ ለመርዳት የሚሰጠን ኃይል ታላቅ ነው። (ኤፌሶን 3:20) ይሖዋ መለኮታዊ ኃይሉ ‘በድካም ፍጹም እንደሚሆን’ ለጳውሎስ አስተምሮታል። እንዴት? ጳውሎስ የገጠመውን ፈተና መቋቋም ይችል ዘንድ በፍቅር ተነሳስቶ ብርታት ሰጥቶታል። በምላሹም ጳውሎስ ያሳየው ጽናትና በይሖዋ ላይ ያሳደረው ፍጹም ትምክህት የአምላክ ኃይል በዚህ ደካማና ኃጢአተኛ በሆነ ሰው ላይ ድል እንደተቀዳጀ ሁሉም ክርስቲያኖች እንዲገነዘቡ የሚያደርግ ነበር። ይህ ሁኔታ ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት ሲመቻቸውና ከችግር ነፃ በሚሆኑበት ጊዜ ብቻ ነው በማለት በተናገረው በዲያብሎስ ላይ የሚያስከትለውን ውጤት ተመልከት። ጳውሎስ ያሳየው ጽኑ አቋም ይህ ስም አጥፊ የኃፍረት ማቅ እንዲከናነብ አድርጎታል!

6 ቀደም ሲል ጳውሎስ አምላክን ከሚቃወመው ከሰይጣን ጎን የተሰለፈ፣ ቀንደኛ የክርስቲያኖች አሳዳጅና ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው ቤተሰቦች በመወለዱ ምክንያት የተንደላቀቀ ኑሮ የነበረው ቀናተኛ ፈሪሳዊ ነበር። አሁን ግን ጳውሎስ ‘ከሐዋርያት ሁሉ የሚያንስ’ የይሖዋና የክርስቶስ አገልጋይ ሆነ። (1 ቆሮንቶስ 15:9) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበረው የክርስቲያን የአስተዳደር አካል ሥልጣን በትህትና ይገዛ ነበር። የሥጋ መውጊያ የነበረበት ቢሆንም እንኳ በታማኝነት ጸንቷል። ጳውሎስ የደረሰበት ፈተና ቅንዓቱን አላቀዘቀዘበትም። ይህም ሰይጣንን የሚያበሳጭ ነበር። ጳውሎስ በክርስቶስ ሰማያዊ መንግሥት ተካፋይ የመሆን ተስፋውን ፈጽሞ ከአእምሮው አላጠፋም። (2 ጢሞቴዎስ 2:12፤ 4:18) የትኛውም መውጊያ ምንም ያህል የሚያሠቃይ ቢሆን ቅንዓቱን ሊያጠፋበት አልቻለም። የእኛም ቅንዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የሚሄድ ይሁን! ይሖዋ በመከራችን ሁሉ ደግፎ በማቆም ሰይጣን ውሸታም መሆኑ ይረጋገጥ ዘንድ የበኩላችንን ድርሻ እንድናበረክት መብት በመስጠት ያከብረናል።​—⁠ምሳሌ 27:11

የይሖዋ ዝግጅቶች ወሳኝ ናቸው

7, 8. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ኃይል የሚሰጠው በምን አማካኝነት ነው? (ለ) በሥጋችን ላይ የሚደርስብንን መውጊያ ለመቋቋም በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ማጥናት እጅግ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

7 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ በመንፈስ ቅዱሱ፣ በቃሉና በክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበራችን አማካኝነት ታማኝ ክርስቲያኖችን ያበረታቸዋል። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ እኛም በጸሎት አማካኝነት ሸክማችንን በይሖዋ ላይ ልንጥል እንችላለን። (መዝሙር 55:22) ይሖዋ የደረሰብንን ፈተና ባያስወግድልን እንኳ በጣም ከባድ የሆኑትን ፈተናዎች ሳይቀር ተቋቁመን ለመኖር የሚያስችል ጥበብ ሊሰጠን ይችላል። እንዲሁም መጽናት እንድንችል “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” በመስጠት ሊያጠናክረን ይችላል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:7 NW

8 ይህን እርዳታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? በውስጡ የሰፈሩትን እውነተኛ ማጽናኛዎች ማግኘት እንድንችል የአምላክን ቃል በትጋት ማጥናት አለብን። (መዝሙር 94:19) የአምላክ አገልጋዮች መለኮታዊ እርዳታ ለማግኘት ያቀረቧቸውን ልብ የሚነኩ ልመናዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናነባለን። የሚያጽናኑ ቃላትን ያዘለው የይሖዋ ምላሽ ልናሰላስልበት የሚገባ ነገር ነው። ‘የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ ስላይደለ’ የአምላክን ቃል ማጥናታችን ጥንካሬ ይሰጠናል። ሰውነታችንን ለመገንባትና ጥንካሬ ለማግኘት በየቀኑ ሥጋዊ ምግብ መመገብ እንዳለብን ሁሉ የአምላክንም ቃል አዘውትረን መመገብ ይገባናል። እንዲህ እያደረግን ነው? እንዲህ የምናደርግ ከሆነ የምናገኘው ‘ከወትሮው የበለጠ ኃይል’ የሚደርስብንን ማንኛውንም ዓይነት ምሳሌያዊ መውጊያ በጽናት እንድንቋቋም ይረዳናል።

9. ሽማግሌዎች ካሉባቸው ችግሮች ጋር የሚታገሉትን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

9 ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንደ ‘ነፋስ’ ካለ መከራ “መሸሸጊያ” እንደ ‘ዐውሎ ነፋስ’ ካሉ ችግሮች ደግሞ “መጠጊያ” ሊሆኑልን ይችላሉ። ይህን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መግለጫ አሟልተው ለመገኘት የሚፈልጉ ሽማግሌዎች ሥቃይ ለደረሰባቸው ሰዎች በትክክለኛ ቃላት እንዴት መልስ መስጠት እንደሚችሉ ያውቁ ዘንድ ይሖዋ “የተማሩትን ምላስ” እንዲሰጣቸው በትሕትናና ከልብ በመነጨ ስሜት ይጠይቁታል። ሽማግሌዎች የሚናገሯቸው ቃላት በሕይወታችን ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ መንፈሳችንን ቀዝቀዝ እንደሚያደርግና እንደሚያድስ ካፊያ ሊሆኑልን ይችላሉ። ሽማግሌዎች ‘የተጨነቁትን ነፍሳት በማጽናናት’ በገጠማቸው የሥጋ መውጊያ ምክንያት የደከሙ ወይም የተከዙ መንፈሳዊ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ይደግፏቸዋል።​—⁠ኢሳይያስ 32:2፤ 50:4 NW፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14 NW

10, 11. የአምላክ አገልጋዮች በከባድ ፈተና ውስጥ የሚገኙትን ማበረታታት የሚችሉት እንዴት ነው?

10 ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ይሖዋ አንድ ያደረገው የክርስቲያን ቤተሰብ ክፍል ናቸው። አዎን፣ “እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን” እንዲሁም “እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል።” (ሮሜ 12:5፤ 1 ዮሐንስ 4:11) ይህን ግዴታ መፈጸም የምንችለው እንዴት ነው? 1 ጴጥሮስ 3:​8 እንደሚናገረው ‘የሌላው መከራ ለእኛ እንደሚሆን አድርገን በማየት፣ የወንድማማች ፍቅር በማሳየትና’ በእምነት ለሚዛመዱን ሁሉ ‘ርኅራኄ’ በማሳየት እንዲህ ማድረግ እንችላለን። ወጣትም ሆኑ በዕድሜ የገፉ ከባድ የሥጋ መውጊያ ያለባቸውን ሁላችንም የተለየ አሳቢነት ልናሳያቸው እንችላለን። እንዴት?

11 ለሚደርስባቸው ሥቃይ የሐዘኔታ ስሜት ልናሳያቸው ይገባል። ርኅራኄ የጎደለን፣ ችግራቸው የማይሰማን ወይም ግድ የለሾች ከሆንን ሳይታወቀን ሥቃያቸውን ልናባብስባቸው እንችላለን። የሚደርስባቸውን ፈተና ማወቃችን የምንናገረውን ቃል፣ የምንናገርበትን መንገድና ድርጊታችንን በተመለከተ ጠንቃቆች እንድንሆን ሊገፋፋን ይገባል። አዎንታዊ አመለካከት የምንይዝና ማበረታቻ የምንሰጣቸው ከሆነ የገጠማቸው መውጊያ ምንም ይሁን ምን የሚሰማቸው ሥቃይ ቀለል እንዲልላቸው ሊረዳቸው ይችላል። በዚህ መንገድ የብርታት ምንጭ ልንሆናቸው እንችላለን።​—⁠ቆላስይስ 4:11 NW

አንዳንዶች በተሳካ ሁኔታ መቋቋም የቻሉት እንዴት ነው?

12-14. (ሀ) አንዲት ክርስቲያን የደረሰባትን የካንሰር በሽታ ለመቋቋም ምን አደረገች? (ለ) የዚህች ሴት መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች ድጋፍና ማበረታቻ የሰጧት እንዴት ነው?

12 ወደዚህ የመጨረሻ ዘመን ፍጻሜ እየተቃረብን በሄድን መጠን ‘የምጡ ጣር’ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው። (ማቴዎስ 24:8) በዚህም የተነሳ በምድር ላይ በሚኖር በማንኛውም ሰው ላይ በተለይ ደግሞ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ በሚጣጣሩት ታማኝ አገልጋዮች ላይ የተለያዩ ፈተናዎች ሊደርሱ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሰማራችን የአንዲት ክርስቲያን ሁኔታ ተመልከት። በተደረገላት የሕክምና ምርመራ ካንሰር እንዳለባት በመታወቁ የምራቅና የሊንፍ ዕጢዎቿን በቀዶ ሕክምና ማስወጣት ነበረባት። ይህ በሽታ እንዳለባት እርሷና ባለቤቷ እንዳወቁ ወዲያውኑ ወደ ይሖዋ ረዥም የልመና ጸሎት አቀረቡ። ከጊዜ በኋላ እንደተናገረችው ሁለቱም ከፍተኛ ሰላም አገኙ። እንዲህም ሆኖ በርካታ ውጣ ውረዶችን በተለይ ደግሞ ከተደረገላት ሕክምና ጋር በተያያዘ የደረሰባትን የጎንዮሽ ጉዳት በጽናት ተቋቁማለች።

13 ይህች እህት የደረሰባትን ሁኔታ ለመቋቋም ስለ ካንሰር የቻለችውን ያህል ብዙ እውቀት ለመቅሰም ጥረት አደረገች። ሐኪሞቿን አማከረች። በመጠበቂያ ግንብ፣ንቁ! እና በሌሎች ክርስቲያናዊ ጽሑፎች ላይ አንዳንዶች ይህ በሽታ በስሜታቸው ላይ ያስከተለውን ጉዳት እንዴት እንደተቋቋሙ የሚገልጹ የሕይወት ታሪኮችን አገኘች። እንዲሁም በመከራ ጊዜ ይሖዋ ሕዝቡን ደግፎ ለማቆም ያለውን ችሎታ የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችንና ሌሎች ጠቃሚ መረጃዎችን አነበበች።

14 የተስፋ መቁረጥ ስሜትን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል የሚገልጽ አንድ ጽሑፍ “መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል” የሚሉትን ጥበብ የሞላባቸውን ቃላት ጠቅሷል። (ምሳሌ 18:1) ከዚያም ጽሑፉ “ራስን የማግለል ዝንባሌ አስወግድ” የሚል ምክር ይለግሳል። a እህት እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ብዙዎች እንደሚጸልዩልኝ ነግረውኛል። ሌሎች ደግሞ ስልክ ደውለውልኛል። ሁለት ሽማግሌዎች አዘውትረው ስልክ እየደወሉ ጠይቀውኛል። አበቦችና በርካታ ካርዶች ደርሰውኛል። እንዲያውም አንዳንዶች ምግብ አዘጋጅተውልኛል። እንዲሁም ብዙዎች በፈቃደኝነት ራሳቸውን በማቅረብ ሐኪም ቤት አመላልሰውኛል።”

15-17. (ሀ) አንዲት ክርስቲያን በደረሱባት አደጋዎች ምክንያት የገጠማትን ችግር የተቋቋመችው እንዴት ነው? (ለ) በጉባኤ ውስጥ ያሉት ምን ዓይነት ድጋፍ ሰጡ?

15 በኒው ሜክሲኮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ይሖዋን ለረዥም ዓመት ያገለገለች አንዲት እህት ሁለት ጊዜ የመኪና አደጋ ደረሰባት። አደጋው በአንገቷና በትከሻዋ ላይ ጉዳት ያደረሰባት ሲሆን ይህም ከ25 ለሚበልጡ ዓመታት ስትታገለው የኖረችውን የአርትራይተስ በሽታዋን አባባሰባት። እንዲህ ትላለች፦ “ጭንቅላቴን ቀና ለማድረግና ከሁለት ኪሎ ያለፈ ዕቃ ለመያዝ እቸገር ነበር። ሆኖም ለይሖዋ ያቀረብኩት ልባዊ ጸሎትና በመጠበቂያ ግንብ ላይ ያጠናናቸው ጽሑፎች ደግፈው አቁመውኛል። ከእነዚህ ጽሑፎች በአንዱ ላይ ሚክያስ 6:​8ን በማስመልከት የተሰጠው ማብራሪያ ልክን አውቆ ከአምላክ ጋር መሄድ ማለት የአቅም ገደብን ማወቅ ማለት እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ ይዞ ነበር። ይህም ካለብኝ የአቅም ገደብ አንጻር የምፈልገውን ያህል በአገልግሎት መካፈል ባልችልም ተስፋ መቁረጥ እንደማይገባኝ እንድገነዘብ ረድቶኛል። ትልቁ ነገር ከንጹሕ ልብ በመነጨ ስሜት እርሱን ማገልገል ነው።”

16 ጨምራም እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ሽማግሌዎች በስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና በመስክ አገልግሎት ለመሰማራት የማደርገውን ጥረት ሳያደንቁ ያለፉበት ጊዜ የለም። ልጆች እቅፍ አድርገው ሰላም ይሉኛል። አቅኚ ሆነው የሚያገለግሉት በትዕግሥት የሚይዙኝ ሲሆን ፕሮግራማቸውን እንደ ጤንነቴ ሁኔታ ያስተካክሉልኛል። የአየሩ ጠባይ መጥፎ በሚሆንበት ጊዜ በደግነት ወደ ተመላልሶ መጠየቅ ይወስዱኛል ወይም ጥናት ይጋብዙኛል። የጽሑፍ ቦርሳ መያዝ ስለማልችል ለስብከት በምወጣበት ጊዜ ሌሎች አስፋፊዎች ጽሑፎቼን በራሳቸው ቦርሳ ይይዙልኛል።”

17 እነዚህ ሁለት እህቶች እንደ መውጊያ የሚያሠቃያቸውን ሕመም እንዲቋቋሙ የጉባኤ ሽማግሌዎችና የእምነት ባልደረቦቻቸው እንዴት እንደረዷቸው ልብ በል። በመንፈሳዊ፣ በአካላዊና በስሜታዊ ሁኔታ የሚያስፈልጋቸውን ለማሟላት ተግባራዊ የሆነ ድጋፍ በደግነት ሰጥተዋቸዋል። ይህ ሁኔታ አንተም ችግር ላለባቸው ወንድሞችና እህቶች ተመሳሳይ እገዛ እንድታደርግ አያበረታታህም? ወጣቶችም ብትሆኑ ከሥጋቸው መውጊያ ጋር እየታገሉ ያሉ በጉባኤያችሁ የሚገኙ ወንድሞችንና እህቶችን ልትረዱ ትችላላችሁ።​—⁠ምሳሌ 20:​29

18. በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ ከሚወጡት የሕይወት ታሪኮች ምን ማበረታቻ ማግኘት እንችላለን?

18 በሕይወታቸው ውስጥ የገጠሟቸውን ችግሮች ተቋቁመው ያሸነፉና በመቋቋም ላይ የሚገኙ የበርካታ ምሥክሮች የሕይወት ታሪኮችና ተሞክሮዎች በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ ወጥተዋል። እንደዚህ ያሉትን ርዕሶች አዘውትረህ በምታነብበት ጊዜ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ መንፈሳዊ ወንድሞችህና እህቶችህ የኢኮኖሚ ችግሮችን፣ በተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣትንና ጦርነት የሚያስከትላቸውን አደገኛ ሁኔታዎች እንደተቋቋሙ ትመለከታለህ። ሌሎች ደግሞ አካልን በሚያሽመደምድ በሽታ ተይዘዋል። ብዙዎች፣ ጤናማ ሰዎች አቅልለው የሚመለከቷቸውን ተራ የሆኑ ተግባሮች መሥራት አይችሉም። ያለባቸው ሕመም በተለይ ደግሞ የሚፈልጉትን ያህል በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል ሲሳናቸው ከባድ ፈተና ይሆንባቸዋል። ወጣትም ሆኑ በዕድሜ የገፉ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ለሚሰጧቸው እርዳታና ድጋፍ ከልብ አመስጋኞች ናቸው!

ጽናት ደስታ ያስገኛል

19. ጳውሎስ እንደ መውጊያ ያለ ፈተናና ድካም እያለበት ደስተኛ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው?

19 ጳውሎስ አምላክ እንዴት እንዳበረታው በማየቱ በጣም ተደስቷል። እንዲህ በማለት ተናገረ፦ “የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።” (2 ቆሮንቶስ 12:9, 10) ጳውሎስ ከራሱ የግል ተሞክሮ በመነሳት እንዲህ ብሎ በልበ ሙሉነት ሊናገር ችሏል፦ “ይህን ስል ስለ ጒድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጒደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ [“በእርሱ፣” አ.መ.ት ] ሁሉን እችላለሁ።”​—⁠ፊልጵስዩስ 4:11-13

20, 21. (ሀ) ‘በማይታዩት ነገሮች’ ላይ በማሰላሰል ደስታ ልናገኝ የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ገነት በምትሆነው ምድር ውስጥ ለማየት ተስፋ የምታደርጋቸው አንዳንዶቹ ‘የማይታዩ ነገሮች’ ምንድን ናቸው?

20 ስለዚህ በሥጋችን ላይ ያለውን ማንኛውንም ዓይነት ምሳሌያዊ መውጊያ በጽናት በመቋቋም የይሖዋ ኃይል በእኛ ድካም ፍጹም እንደሚሆን ሌሎች እንዲመለከቱ በማድረግ ከፍተኛ ደስታ ልናገኝ እንችላለን። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “አንታክትም፣ . . . የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። የማይታየውን . . . [ብ]ንመለከት፣ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ . . . የማይታየው . . . የዘላለም ነው።”​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:16-18

21 በዛሬ ጊዜ የሚኖሩ አብዛኞቹ የይሖዋ ሕዝቦች አምላክ ገነት በሚያደርጋት ምድር ላይ ለመኖርና ቃል የገባቸውን በረከቶች ለማግኘት በጉጉት ይጠባበቃሉ። በዛሬው ጊዜ እነዚህ በረከቶች ‘እንደማይታዩ’ አድርገን እናስብ ይሆናል። ይሁን አንጂ እነዚህን በረከቶች በዓይናችን የምናይበትና ለዘላለም የምንደሰትበት ጊዜ በፍጥነት እየቀረበ ነው። ከእነዚህ በረከቶች መካከል አንዱ እንደ መውጊያ ያለ ማንኛውም ዓይነት ችግር ሳይደርስብን የምንኖር መሆናችን ነው! የአምላክ ልጅ ‘የዲያብሎስን ሥራ በማፍረስ’ ‘በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት ይሽራል።’​—⁠1 ዮሐንስ 3:8፤ ዕብራውያን 2:14

22. ምን ዓይነት ትምክህትና ቁርጠኝነት ሊኖረን ይገባል?

22 ስለዚህ በዛሬው ጊዜ የሚያሠቃየን ምንም ዓይነት የሥጋ መውጊያ ይኑርብን መታገላችንን እንቀጥል። እንደ ጳውሎስ እኛም ኃይልን አትረፍርፎ ከሚሰጠው ከይሖዋ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ጥንካሬ እናገኛለን። ገነት በሆነች ምድር ላይ በምንኖርበት ጊዜ በርካታ ድንቅ ነገሮች ያደረገልንን አምላካችንን ይሖዋን በየቀኑ እንባርካለን።​—⁠መዝሙር 103:2 አ.መ.ት

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በግንቦት 2000 የንቁ! እትም ላይ የወጣውን “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት፦ የተስፋ መቁረጥን ስሜት መቋቋም የሚቻልበት መንገድ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ዲያብሎስ እውነተኛ ክርስቲያኖች ያላቸውን ጽኑ አቋም ለማበላሸት የሚጥረው ለምንድን ነው? ይህንንስ የሚያደርገው እንዴት ነው?

• የይሖዋ ኃይል ‘በድካም ፍጹም የሚሆነው’ እንዴት ነው?

• ሽማግሌዎችና ሌሎች በችግር የሚሠቃዩትን ማበረታታት የሚችሉት እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ የሥጋውን መውጊያ እንዲያስወግድለት አምላክን ሦስት ጊዜ በጸሎት ጠይቆ ነበር