እውነት ለአንተ ምን ያህል ውድ ነው?
እውነት ለአንተ ምን ያህል ውድ ነው?
“እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት [“ነፃ፣” አ.መ.ት ] ያወጣችኋል።”—ዮሐንስ 8:32
1. ጲላጦስ “እውነት” የሚለውን ቃል የተጠቀመበት መንገድ ኢየሱስ ከተጠቀመበት መንገድ ፈጽሞ የሚለየው እንዴት ነው?
“እውነት ምንድን ነው?” ጲላጦስ ይህን ጥያቄ ሲያቀርብ ለእውነት ፍላጎት እንደሌለው የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ እየተናገረ ያለው ስለ አጠቃላይ እውነት ነበር። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 18:37, 38) ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው ስለ መለኮታዊ እውነት ነው።
ዓለም ለእውነት ያለው አመለካከት
2. ኢየሱስ እውነት ምን ያህል ውድ መሆኑን ሲገልጽ ምን ብሎ ተናግሯል?
2 ጳውሎስ ‘እምነት ለሁሉ አይሆንም’ ብሏል። (2 ተሰሎንቄ 3:1, 2) እውነትን በተመለከተም ተመሳሳይ ነገር መናገር ይቻላል። ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሲነገራቸው ሆን ብለው ችላ ይሉታል። ሆኖም ምንኛ ውድ ነው! ኢየሱስ “እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት [“ነፃ፣” አ.መ.ት ] ያወጣችኋል” ሲል ተናግሯል።—ዮሐንስ 8:32
3. አሳሳች ትምህርቶችን በተመለከተ የትኛውን ማስጠንቀቂያ መከተል አለብን?
3 ሐዋርያው ጳውሎስ እውነት በሰዎች ፍልስፍናና ወግ ውስጥ እንደማይገኝ ተናግሯል። (ቆላስይስ 2:8) በእርግጥም እነዚህ ትምህርቶች አታላይ ናቸው። የኤፌሶን ክርስቲያኖች እምነታቸውን በሰው ፍልስፍናና ወግ ላይ ካደረጉ በመንፈሳዊ ሕፃናት እንደሚሆኑና ‘እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኰል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እንደሚፍገመገሙ’ አስጠንቅቋቸዋል። (ኤፌሶን 4:14) በዛሬው ጊዜ ‘የሰዎች ማታለል’ መለኮታዊውን እውነት የሚቃወሙ ሰዎች በሚያዛምቱት ፕሮፓጋንዳ እየተሰራጨ ነው። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ “ፕሮፓጋንዳ” የሚለውን ቃል “የሌሎች ሰዎችን እምነት፣ አስተሳሰብ ወይም አድራጎት ለማስቀየር የሚደረግ ዘዴ የተሞላበት ጥረት” ሲል ይፈታዋል። እንዲህ ዓይነቱ ፕሮፓጋንዳ እውነቱን አጣምሞ በማቅረብ ውሸትን እንደ እውነት አድርጎ ያቀርባል። እንዲህ ዓይነት መሰሪ ግፊቶች እያሉ እውነትን ለማግኘት ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት መመርመር ይገባናል።
ክርስቲያኖችና ዓለም
4. እውነትን እነማን በቀላሉ ሊያገኙት ይችላሉ? እውነትን የተቀበሉ ሰዎች ምን ግዴታ አለባቸው?
4 ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን አስመልክቶ “በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። (ዮሐንስ 17:17) እነዚህ ሰዎች ለይሖዋ አገልግሎትና ስሙንና መንግሥቱን ለማሳወቅ ይቀደሳሉ ወይም ይለያሉ። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ 24:14) ሁሉም ሰው ያለው ባይሆንም እንኳ የይሖዋ እውነት ማንኛውም ሰው ዜግነቱ፣ ዘሩ ወይም ባሕሉ ምንም ይሁን ምን በነፃ ሊያገኘው ይችላል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ” ብሏል።—ሥራ 10:34, 35
5. ክርስቲያኖች አብዛኛውን ጊዜ የሚሰደዱት ለምንድን ነው?
5 ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች ያካፍላሉ፤ ሆኖም ሁሉም በደስታ አይቀበሏቸውም። ኢየሱስ “ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፣ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” ሲል አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 24:9) አየርላንዳዊው ቄስ ጆን አር ኮተር በዚህ ጥቅስ ላይ ሐሳብ ሲሰጡ በ1817 እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “[ክርስቲያኖች] በስብከታቸው አማካኝነት የሰው ልጆችን ሕይወት ለመለወጥ የሚያደርጉትን ጥረት ሰዎች በምስጋና ከመቀበል ይልቅ ክፋታቸውን ስለሚያጋልጥባቸው ደቀ መዛሙርቱን እንዲጠሉና እንዲያሳድዱ ያነሳሷቸዋል።” እንደዚህ ያሉት አሳዳጆች ‘ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር አይቀበሉም።’ በዚህም ምክንያት “በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ፣ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል።”—2 ተሰሎንቄ 2:9-12
6. አንድ ክርስቲያን የትኞቹን ምኞቶች ማዳበር የለበትም?
6 ሐዋርያው ዮሐንስ ጥላቻ በሞላበት በዚህ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖችን “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም እንጂ ከአባት [አይደለም]” ሲል አጥብቆ መክሯቸዋል። (1 ዮሐንስ 2:15, 16) ዮሐንስ “ሁሉ” የሚለውን ቃል መጠቀሙ ምንም ያስቀረው ነገር እንደሌለ ያሳያል። በዚህም ምክንያት ይህ ዓለም ለሚያቀርበው ከእውነት ሊያርቀን ለሚችል ለማንኛውም ነገር ምኞት ማዳበር አይገባንም። የዮሐንስን ምክር መከተላችን በሕይወታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። እንዴት?
7. የእውነት እውቀት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ለተግባር የሚያነሳሳቸው እንዴት ነው?
7 የይሖዋ ምሥክሮች ለሕይወት የሚያበቁ መለኮታዊ ብቃቶችን ለግለሰቦችና ለቡድኖች በማስተማር በ2001 ዓመት በዓለም ዙሪያ በየወሩ ከአራት ተኩል ሚልዮን በላይ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መርተዋል። በዚህም የተነሳ 263, 431 የሚያህሉ ሰዎች ተጠምቀዋል። እነዚህ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ያገኙትን የእውነት ብርሃን እንደ ውድ ሀብት አድርገው የሚቆጥሩት ከመሆኑም በላይ ክፉ ባልንጀሮችንና በዚህ ዓለም ላይ ተስፋፍቶ የሚገኘውን አምላክን የማያስከብር ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር እርግፍ አድርገው ትተዋል። ከተጠመቁበት ጊዜ አንስቶ ይሖዋ ለሁሉም ክርስቲያኖች ካወጣቸው የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተው መኖራቸውን ቀጥለዋል። (ኤፌሶን 5:5) እውነት ለአንተ ያን ያህል ውድ ነው?
ይሖዋ ይንከባከበናል
8. ይሖዋ እርሱን ለማገልገል ላደረግነው ውሳኔ ምላሽ የሚሰጠው እንዴት ነው? ‘አስቀድመን መንግሥቱን መፈለጋችን’ ጥበብ የሆነው ለምንድን ነው?
8 ፍጽምና የሚጎድለን ቢሆንም እንኳ ይሖዋ እርሱን ለማገልገል ያደረግነውን ውሳኔ በምሕረቱ በመቀበል በምሳሌያዊ አነጋገር ራሱን ዝቅ አድርጎ ወደ እርሱ ይስበናል። በዚህ መንገድ ከፍ ያሉ ግቦችና ምኞቶች እንዲኖሩን ያስተምረናል። (መዝሙር 113:6-8) በተመሳሳይም ይሖዋ ከእሱ ጋር የግል ዝምድና እንድንመሠርት የሚፈቅድልን ከመሆኑም በላይ ‘አስቀድመን መንግሥቱንና ጽድቁን የምንፈልግ’ ከሆነ እንደሚንከባከበን ቃል ገብቶልናል። ይህን የምናደርግና በመንፈሳዊ ራሳችንን የምንጠብቅ ከሆነ “ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” ሲል ቃል ገብቷል።—ማቴዎስ 6:33
9. “ታማኝና ልባም ባሪያ” ማን ነው? ይሖዋ በዚህ “ባሪያ” አማካኝነት የሚንከባከበን እንዴት ነው?
9 ኢየሱስ ክርስቶስ 12 ሐዋርያቱን ከመረጠ በኋላ ‘የአምላክ እስራኤል’ ተብሎ ለሚጠራው ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ መሠረት ጣለ። (ገላትያ 6:16፤ ራእይ 21:9, 14) ከጊዜ በኋላ “የእውነት ዓምድና መሠረት፣ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን [“ጉባኤ፣” NW ]” ተብሎ ተገልጿል። (1 ጢሞቴዎስ 3:15) ኢየሱስ የዚህን ጉባኤ አባላት “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንዲሁም “ታማኝና ልባም መጋቢ” በማለት ለይቶ ገልጿል። ይህ ታማኝ ባሪያ ለክርስቲያኖች “ምግባቸውን በጊዜው” የመስጠት ኃላፊነት እንዳለበት ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:3, 45-47፤ ሉቃስ 12:42) ሥጋዊ ምግብ ካልተመገብን በረሃብ እንደምንሞት ሁሉ መንፈሳዊ ምግብ ካልተመገብንም በመንፈሳዊ ተዳክመን እንሞታለን። በመሆኑም ‘የታማኝና ልባም ባሪያ’ መኖር ይሖዋ እንደሚንከባከበን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። በዚህ “ባሪያ” አማካኝነት ለሚቀርብልን ውድ መንፈሳዊ ምግብ አድናቆት እንዳለን ሁልጊዜ የምናሳይ እንሁን።—ማቴዎስ 5:3
10. በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘታችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
10 መንፈሳዊ ምግብ መመገብ የግል ጥናት ማድረግን ይጠይቃል። በተጨማሪም ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር መቀራረብንና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትን ያጠቃልላል። ከስድስት ወር እንዲያውም ከስድስት ሳምንት በፊት የተመገብከውን ምግብ በትክክል ታስታውሳለህ? አታስታውስ ይሆናል። ይሁን እንጂ የተመገብከው ምግብ ምንም ዓይነት ይሁን በሕይወት ለመቆየት የሚያስፈልግህን ነገር አሟልቶልሃል። ከዚያን ጊዜ በኋላም ተመሳሳይ ምግብ ተመግበህ ይሆናል። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ የሚቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በስብሰባዎች ላይ የሰማናቸውን ነገሮች አንድ በአንድ በዝርዝር አናስታውስ ይሆናል። እንዲሁም ተመሳሳይ ትምህርት ከአንድ ጊዜ በላይ ቀርቦም ሊሆን ይችላል። ሆኖም ለደኅንነታችን እጅግ ጠቃሚ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ነው። ስብሰባዎቻችን በተገቢው ሰዓት የተዘጋጀ ገንቢ መንፈሳዊ ማዕድ ሁልጊዜ ያቀርቡልናል።
11. በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ምን ግዴታዎች አሉብን?
11 በተጨማሪም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ኃላፊነት ያስከትልብናል። ክርስቲያኖች እርስ በርስ እንዲበረታቱና በጉባኤ ያሉ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን “ለፍቅርና ለመልካም ሥራ” እንዲያነቃቁ ተመክረዋል። ለሁሉም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መዘጋጀት፣ በሁሉም ላይ መገኘትና ተሳትፎ ማድረግ የራሳችንን እምነት የሚያጠናክርልን ከመሆኑም በላይ ሌሎችን የሚያበረታታ ነው። (ዕብራውያን 10:23-25) ምግብ እየመረጡ እንደሚመገቡት ሕፃናት አንዳንዶች መንፈሳዊ ምግብ እንዲመገቡ ተደጋጋሚ ማበረታቻ ማግኘት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። (ኤፌሶን 4:12, 13) እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና ማደግ ይችሉ ዘንድ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እንዲህ ዓይነት ማበረታቻ መስጠቱ ፍቅራዊ መግለጫ ነው። ጳውሎስ ጎልማሳ ክርስቲያኖችን በተመለከተ “ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው” ሲል ጽፏል።—ዕብራውያን 5:14
የራሳችንን መንፈሳዊነት መንከባከብ
12. በእውነት ለመቀጠል ኃላፊነቱ በዋነኛነት የሚወድቀው በማን ላይ ነው? አብራራ።
12 የትዳር ጓደኛችን ወይም ወላጆቻችን በእውነት መንገድ እንድንጓዝ ሊያበረታቱን ይችላሉ። በተመሳሳይም በሥራቸው የምንገኝ የመንጋው ክፍል እንደመሆናችን መጠን የጉባኤ ሽማግሌዎች እረኝነት ሊያደርጉልን ይችላሉ። (ሥራ 20:28) ሆኖም በእውነት ላይ በተመሠረተው የሕይወት መንገድ መጓዛችንን መቀጠል ከፈለግን ኃላፊነቱ በዋነኛነት የሚወድቀው በማን ላይ ነው? ኃላፊነቱ የሚወድቀው በእያንዳንዳችን ላይ ነው። በደህናውም ሆነ በአስቸጋሪ ጊዜያት ይህ እውነታ አይለወጥም። ቀጥሎ የቀረበውን ሁኔታ ተመልከት።
13, 14. ስለ አንዲት ግልገል በቀረበው ተሞክሮ ላይ እንደታየው አስፈላጊ የሆነ መንፈሳዊ እርዳታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
13 በስኮትላንድ፣ የተወሰኑ በጎች ለግጦሽ ተሰማርተው ሳለ አንዲት ግልገል ከመንጋው ተነጥላ ወደ ገደል አፋፍ ሄደችና ወደቀች። ከጉዳት የተረፈች ቢሆንም እንኳ በጣም ተደናግጣ ስለነበር ከገደሉ ለመውጣት ያደረገችው ጥረት ሁሉ ሳይሳካላት ቀረ። ከዚህም የተነሳ አምርራ መጮኽ ጀመረች። እናትየው ጩኸቷን ሰምታ እረኛው መጥቶ ግልገሏን ከጉድጓዱ እስኪያወጣት ድረስ እርሷም መጮኽ ጀመረች።
14 የሁኔታዎቹን ቅደም ተከተል ልብ በሉ። ግልገሏ እርዳታ ለማግኘት ጮኸች፣ እናትየዋም አብራ መጮኽ ጀመረች ከዚያም ንቁ የሆነው እረኛ ግልገሏን ለማዳን አፋጣኝ እርምጃ ወሰደ። አንዲት ትንሽ ግልገልና እናቷ አደጋ መፈጠሩን አውቀው ወዲያውኑ ለእርዳታ ከጮኹ እኛስ በመንፈሳዊ መሰናክል ሲያጋጥመን ወይም ከሰይጣን ዓለም ያልተጠበቀ አደጋ ሲደቀንብን ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ አይገባንም? (ያዕቆብ 5:14, 15፤ 1 ጴጥሮስ 5:8) እኛም በተለይ በዕድሜ ለጋ በመሆናችን ወይም ወደ እውነት የመጣነው በቅርቡ በመሆኑ ምክንያት ተሞክሮ የሚጎድለን ከሆነ እርዳታ መጠየቅ ይኖርብናል።
መለኮታዊ መመሪያ መከተል ደስታ ያስገኛል
15. አንዲት ሴትዮ ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር መሰብሰብ ሲጀምሩ ምን ስሜት አደረባቸው?
15 መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ያለውን ጠቀሜታና ይህም የእውነትን አምላክ ለሚያገለግሉ ሰዎች የሚያስገኝላቸውን የአእምሮ ሰላም ተመልከት። ዕድሜያቸውን በሙሉ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን አባል የነበሩ አንዲት የ70 ዓመት ወይዘሮ ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን አወቁና በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ለሚቀርቡ ልብ ለሚነኩ ጸሎቶች አብረው “አሜን” ማለት ጀመሩ። በከፍተኛ ስሜት ተውጠው እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “አምላክ በጣም ሩቅ ከመሆኑ የተነሳ ማንም ሰው ሊቀርበው እንደማይችል አድርጋችሁ ከማቅረብ ይልቅ ልክ እንደ ቅርብ ወዳጅ እዚሁ በመካከላችን እንዳለ እንዲሰማን ታደርጋላችሁ። ይህ ለእኔ አዲስ ነገር ነው።” እኚህ ፍላጎት ያሳዩ ሴት እውነትን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰሙ ያደረባቸውን ስሜት ፈጽሞ እንደማይረሱት እርግጠኞች ነን። እኛም በተመሳሳይ እውነትን ለመጀመሪያ ጊዜ ስንሰማ ምን ያህል እንደ ውድ አድርገን እንደተመለከትነው ፈጽሞ አንዘንጋ።
16. (ሀ) ገንዘብን ማግኘት የሕይወታችን ዋነኛ ግብ ብናደርግ ምን ሊደርስብን ይችላል? (ለ) እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
16 ብዙዎች ብዙ ገንዘብ ቢኖራቸው ይበልጥ ደስተኞች እንደሚሆኑ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ገንዘብን ማግኘት የሕይወታችን ዋነኛ ግብ ካደረግን “ከፍተኛ የአእምሮ ሥቃይ” ሊደርስብን ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:10፣ ፊሊፕስ) ምን ያህል ሰዎች ሎተሪ እንደሚገዙ፣ በቁማር ገንዘብ እንደሚያጠፉ ወይም ሀብት የማግኘት ቅዥት ውስጥ ገብተው በአክሲዮን ገበያ ጥሪታቸውን እንደሚያፈስሱ አስብ። የተመኙትን የሚያገኙት በጣም ጥቂቶች ናቸው። እነዚህም ቢሆኑ አብዛኛውን ጊዜ በቅጽበት ያገኙት ሀብት ደስታ እንደማያስገኝላቸው ይገነዘባሉ። ከዚህ ይልቅ ዘላቂ ደስታ የሚገኘው በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ አመራርና በመላእክቱ እርዳታ ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ሆኖ የይሖዋን ፈቃድ በመፈጸም ነው። (መዝሙር 1:1-3፤ 84:4, 5፤ 89:15) ይህን በምናደርግበት ጊዜ ያልጠበቅናቸውን በረከቶች ልናገኝ እንችላለን። በሕይወትህ ውስጥ እንደዚህ ያሉ በረከቶችን ማግኘት በሚያስችል መጠን እውነትን እንደ ውድ ሀብት አድርገህ ትመለከተዋለህ?
17. ጴጥሮስ በቆዳ ፋቂው በስምዖን ቤት ማረፉ የሐዋርያውን አስተሳሰብ በተመለከተ ምን ይገልጣል?
17 ሐዋርያው ጴጥሮስ ያጋጠመውን ተሞክሮ ተመልከት። በ36 እዘአ ወደ ሰሮና ሚስዮናዊ ጉዞ አደረገ። በልዳ በቆየበት ጊዜ ኤንያ የተባለ አንድ ሽባ ሰው ፈወሰና የወደብ ከተማ ወደሆነችው ወደ ኢዮጴ አቀና። እዚያም ዶርቃን ከሞት አስነሣት። ሥራ 9:43 “በኢዮጴም ስምዖን ከሚሉት ከአንድ ቊርበት ፋቂ ጋር አያሌ ቀን ኖረ” ይላል። ጴጥሮስ እዚያች ከተማ የሚኖሩ ሰዎችን እስካገለገለ ድረስ ለሕዝቡ የጥላቻ ስሜት እንዳልነበረው ይህ አጭር ዘገባ ያሳያል። እንዴት? የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ፍሬደሪክ ደብልዩ ፋራር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “[የሙሴ] የቃል ሕግ የሙጥኝ ብሎ የሚከተል ማንኛውም ሰው በአንድ ቁርበት ፋቂ ቤት ለመኖር ፈቃደኛ አይሆንም። ይህ ሙያ በየቀኑ ከቆዳና ከተለያዩ እንስሳት በድን ጋር የግድ የሚያገናኝ በመሆኑና ለሥራው የሚያስፈልጉት ጥሬ ዕቃዎች ዓይነት ሕጉን በጥብቅ በሚከተሉ ሰዎች ዓይን ሥራውን ርኩስና አስጸያፊ ያደርገዋል።” “በባሕር አጠገብ” የሚገኘው የስምዖን ቤት ሥራውን የሚያከናውንበት ቤት አጠገብ የሚገኝ ባይሆን እንኳ ስምዖን ‘እንደ ጸያፍ ተደርጎ በሚታይ ሥራ የተሠማራ ሲሆን ይህም በሙያው የተሠማሩ ሁሉ ለራሳቸው አክብሮት እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ነበር’ ሲሉ ፋራር ተናግረዋል።—ሥራ 10:6
18, 19. (ሀ) ጴጥሮስ በተመለከተው ራእይ ግራ የተጋባው ለምንድን ነው? (ለ) ጴጥሮስ ምን ያልጠበቀው በረከት አገኘ?
18 ቀና አመለካከት የነበረው ጴጥሮስ የስምዖንን መስተንግዶ የተቀበለ ከመሆኑም በላይ እዚያው እያለ ጴጥሮስ ያልተጠበቀ መለኮታዊ መመሪያ ደረሰው። በአይሁዶች ሕግ መሠረት የረከሱ እንስሳትን እንዲበላ የሚያዝዝ ራእይ ተመለከተ። ጴጥሮስ “አንዳች ርኩስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅም” በማለት ተቃወመ። ሆኖም “እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው” ተብሎ ሦስት ጊዜ ተነገረው። “ጴጥሮስም ስላየው ራእይ:- ምን ይሆን? ብሎ በልቡ” ያመነታበትን ምክንያት ለመረዳት አያዳግትም።—ሥራ 10:5-17፤ 11:7-10
19 ጴጥሮስ 50 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በቂሣርያ የሚኖር ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ አሕዛብ ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ ራእይ መመልከቱን አያውቅም ነበር። የይሖዋ መልአክ ቆርኔሌዎስ ቆዳ ፋቂው ስምዖን ቤት ሰዎችን ልኮ ጴጥሮስን እንዲያስጠራው ነገረው። ቆርኔሌዎስ ወደ ስምዖን ቤት የላካቸው አገልጋዮች ከጴጥሮስ ጋር ወደ ቂሣርያ ተመለሱ። እዚያም ለቆርኔሌዎስ፣ ለዘመዶቹና ለቅርብ ወዳጆቹ ሰበከላቸው። በውጤቱም ካልተገረዙ አሕዛብ መካከል መንፈስ ቅዱስ ለመቀበልና የመንግሥቱ ወራሽ ለመሆን የመጀመሪያዎቹ አማኞች ለመሆን በቁ። ወንዶቹ ያልተገረዙ ቢሆኑም እንኳ የጴጥሮስን ስብከት ያዳመጡ ሁሉ ተጠምቀዋል። ይህ ክንውን በአይሁዳውያን አመለካከት ርኩስ ተደርገው ይታዩ የነበሩ አሕዛብ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት እንዲሆኑ መንገድ ከፈተ። (ሥራ 10:1-48፤ 11:18) ጴጥሮስ እንዲህ ላለው ታላቅ መብት ሊበቃ የቻለው እውነትን እንደ ውድ ነገር አድርጎ በመመልከቱና ይህም እውነት ከይሖዋ የመጣውን መመሪያ እንዲከተልና በእምነት እንዲመላለስ ስላስቻለው ነው!
20. እውነት በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ እንዲይዝ ካደረግን ምን ዓይነት መለኮታዊ ድጋፍ እናገኛለን?
20 ጳውሎስ ‘“እውነትን በፍቅር እየተናገርን፣ ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ በነገር ሁሉ እናድጋለን፤ እርሱም ክርስቶስ ነው” በማለት አጥብቆ መክሯል። (ኤፌሶን 4:15 አ.መ.ት፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አዎን፣ እውነት በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ እንዲይዝ ካደረግንና ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት አካሄዳችንን እንዲመራልን ከፈቀድን በአሁኑ ጊዜም እንኳ ሳይቀር ወደር የማይገኝለት ደስታ ያስገኝልናል። በተጨማሪም ቅዱሳን መላእክት በወንጌላዊነት ሥራችን የሚሰጡንን ድጋፍ አስታውስ። (ራእይ 14:6, 7፤ 22:6) ይሖዋ እንድናከናውነው ለሰጠን ተልዕኮ እንዲህ ዓይነት ድጋፍ በማግኘታችን ምንኛ ታድለናል! ጽኑ አቋማችንን መጠበቃችን የእውነት አምላክ የሆነው ይሖዋን ለዘላለም እንድናወድሰው ያስችለናል። ታዲያ ከዚህ የሚበልጥ ውድ ነገር ሊኖር ይችላል?—ዮሐንስ 17:3
ምን ተምረናል?
• ብዙዎች እውነትን የማይቀበሉት ለምንድን ነው?
• ክርስቲያኖች በሰይጣን ዓለም ለሚገኙ ነገሮች ሊኖራቸው የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው?
• ለስብሰባዎች ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው? ለምንስ?
• መንፈሳዊነታችንን ለመንከባከብ ምን ኃላፊነት አለብን?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ታላቁ ባሕር
ቂሣሪያ
የሰሮና ሜዳ
ኢዮጴ
ልዳ
ኢየሩሳሌም
[ሥዕል]
ጴጥሮስ መለኮታዊ መመሪያ በመከተል ያልተጠበቁ በረከቶችን አግኝቷል
[ምንጭ]
ካርታ:- Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ለእውነት መስክሯል
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንደ ሥጋዊ ምግብ ሁሉ መንፈሳዊ ምግብም ለደኅንነታችን በጣም አስፈላጊ ነው