ከዚህ ዓለም ፍጻሜ በሕይወት መትረፍ የምትችለው እንዴት ነው?
ከዚህ ዓለም ፍጻሜ በሕይወት መትረፍ የምትችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ “የመዓት ቀን፣ የመከራና የጭንቀት ቀን፣ የመፍረስና የመጥፋት ቀን፣ የጨለማና የጭጋግ ቀን፣ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን” በማለት ይጠራዋል። (ሶፎንያስ 1:15) በጉጉት የምትጠብቀው እንዲህ ያለ ቀን እንዳልሆነ የታወቀ ነው! ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያን ባልንጀሮቹ:- ‘የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቁና እያስቸኰሉ’ እንዲኖሩ መክሯቸዋል። “ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።”—2 ጴጥሮስ 3:11-13
እዚህ ላይ ጴጥሮስ ግዑዝ የሆኑት ሰማያትና ምድር እንደሚጠፉ መናገሩ አልነበረም። ጴጥሮስ “ሰማያት” እና “ምድር” የሚሉትን ቃላት እዚህ ላይ የተጠቀመው በምሳሌያዊ መንገድ ሲሆን ይህም ዛሬ ያለውን ብልሹ ሰብዓዊ መስተዳድርና ለአምላክ አክብሮት የሌለውን ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ለማመልከት ነው። “የእግዚአብሔር ቀን” ቃል በቃል ምድርን አያጠፋትም። ከዚያ ይልቅ ‘ኃጢአተኞችዋን ከእርስዋ ዘንድ ያጠፋል።’ (ኢሳይያስ 13:9) በመሆኑም ዛሬ ባለው ክፉ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ውስጥ በሚፈጸመው ‘ርኩሰት ሁሉ ለሚያለቅሱና ለሚተክዙ ሰዎች’ የይሖዋ ቀን የመዳን ቀን ይሆንላቸዋል።—ሕዝቅኤል 9:4
ታዲያ አንድ ሰው “[ከ]ታላቁና [ከ]ሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን” መዳን የሚችለው እንዴት ነው? ከነቢያቶቹ ለአንዱ የተገለጠው “የእግዚአብሔር ቃል” ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል:- “እንዲህም ይሆናል፤ የእግዚአብሔርን [“የይሖዋን፣” NW ] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።” (ኢዩኤል 1:1፤ 2:31, 32) የይሖዋን ስም መጥራት ምን ትርጉም እንዳለው ሊያሳውቁህ ፈቃደኞች ናቸው።