የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ በመያዝ ማገልገል
የሕይወት ታሪክ
የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ በመያዝ ማገልገል
ዶን ሬንዴል እንደተናገረው
እናቴ በ1927 ስትሞት ገና የአምስት ዓመት ልጅ ነበርኩ። ሆኖም የነበራት እምነት በሕይወቴ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
እናቴ ወታደር የነበረውን አባቴን ስታገባ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን አጥባቂ ተከታይ ነበረች። ይህ የሆነው ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በፊት ነው። አንደኛው የዓለም ጦርነት በ1914 ከፈነዳ በኋላ እናቴ የቤተ ክርስቲያኗ ቄስ የመስበኪያ ሰገነቱን የወታደር መመልመያ መድረክ ማድረጉን ተቃወመች። የቄሱ መልስ ምን ነበር? “ወደ ቤት ሂጂ፤ እንዲህ ያለ ጥያቄ እያነሳሽ ራስሽን አታስጨንቂ!” ይህ መልስ እናቴን አላረካትም።
ጦርነቱ ተፋፍሞ በቀጠለበት በ1917 እናቴ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለውን ፊልም ለማየት ሄደች። እውነትን እንዳገኘች ስላመነች ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር (በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ይበልጥ ለመቀራረብ ስትል ቤተ ክርስቲያን መሄዷን ወዲያው አቆመች። በእንግሊዝ ግዛት ሱመርሴት ውስጥ እኛ ለምንኖርባት መንደር ለዌስት ኮከር በጣም ቅርብ በሆነችው በዮቪል ከተማ በሚደረግ የጉባኤ ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመረች።
እናቴ ብዙም ሳትቆይ አዲሱን እምነቷን ለሦስቱም እህቶቿ አካፈለቻቸው። እናቴና እህቷ ሚሊ በዙሪያችን ባለው ሰፊ ገጠራማ ክልል ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት የተባሉ መጽሐፎችን ለማሰራጨት በብስክሌት እንዴት ይጠቀሙ እንደነበር በዮቪል ጉባኤ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ወንድሞችና እህቶች አጫውተውኛል። የሚያሳዝነው ግን እናቴ በወቅቱ መድኃኒት ባልተገኘለት በሳንባ ነቀርሳ በሽታ ከመሞቷ በፊት ለ18 ወራት የአልጋ ቁራኛ ሆነች።
የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ በተግባር ሲገለጽ
በወቅቱ ከእኛ ጋር ትኖር የነበረችው አክስታችን ሚሊ እናቴ በታመመች ጊዜ ታስታምማትና እኔንና የሰባት ዓመት እህቴን ጆአንን ትንከባከብ ነበር። እናቴ ስትሞት አክስቴ ሚሊ እኛን ማሳደግ እንደምትፈልግ ወዲያውኑ ገለጸች። አባቴ ሸክሙን እንደሚያቀልለት ስለተሰማው አክስቴ ሚሊ ከእኛ ጋር እንድትኖር ሳያንገራግር ፈቀደ።
አክስታችንን እንወዳት ስለነበረ ከእኛ ጋር በመኖሯ ደስ አለን። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ውሳኔ ያደረገችው ለምንድን ነው? አባታችን ለሃይማኖት ግድ የለሽ ስለነበረ እኔንና ጆአንን ፈጽሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንደማያስጠናን ስለተገነዘበች እናታችን በጣለችው መሠረት ላይ የመገንባት ኃላፊነት እንዳለባት ተሰምቷት መሆኑን ከብዙ ዓመታት በኋላ ነግራናለች።
የኋላ ኋላ አክስታችን ሚሊ በራስዋ ሕይወት ላይም ሌላ ከባድ ውሳኔ አድርጋ እንደነበረ ተረዳን። እኛን በጥሩ ሁኔታ ለማሳደግ ስትል ሳታገባ ኖራለች! እንዴት ያለ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ነው! እኔና ጆአን እርስዋን ከልብ እንድናመሰግን የሚያደርጉን ብዙ ምክንያቶች አሉን። አክስታችን ሚሊ ያስተማረችንና የተወችልን ግሩም ምሳሌነት በውስጣችን ተተክሏል።
የውሳኔ ጊዜ
እኔና ጆአን በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የመንደር ትምህርት ቤት ገባን። አክስታችን ሚሊ የምንከተለውን ሃይማኖታዊ ትምህርት በተመለከተ ያላትን ጽኑ አቋም ለዲሬክተሯ አስረዳቻት። ሌሎች ተማሪዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ እኛ ወደ ቤታችን እንሄዳለን፤ እንዲሁም ቄሱ ሃይማኖታዊ ትምህርት ለመስጠት ትምህርት ቤት ሲመጡ እኛ ለብቻችን እንቀመጥና በቃላችን የምናጠናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ይሰጠን ነበር። እነዚያ ጥቅሶች እንዳይረሱ ሆነው በአእምሮዬ ላይ ስለተቀረጹ የኋላ ኋላ በጣም ጠቅመውኛል።
አሥራ አራት ዓመት ሲሆነኝ በአካባቢው በሚገኝ አይብ ማምረቻ ፋብሪካ ውስጥ የአራት ዓመት ሥልጠና ለመውሰድ ትምህርቴን አቋረጥኩ። ፒያኖ መጫወት ከመማሬም በተጨማሪ ትርፍ ጊዜዬን በሙዚቃና በዳንስ ማሳለፍ ጀመርኩ። በልቤ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ቢኖርም ለተግባር ግን አላንቀሳቀሰኝም ነበር። ከዚያም በ1940 መጋቢት ወር ላይ አንድ ቀን አንዲት አረጋዊ ምሥክር 110 ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ በሚገኘው በስዊንደን በሚደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ እንድገኝ አብሬያት እንድሄድ ጋበዘችኝ። ብሪታንያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግለው አልበርት ዲ ሽሮደር የሕዝብ ንግግሩን አቀረበ። ይህ ስብሰባ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ለውጥ እንዳደርግ አነሳሳኝ።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተፋፍሞ ቀጥሏል። ሕይወቴን መጠቀም የሚኖርብኝ እንዴት ነው? በዮቪል ወደሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ለመሄድ ወሰንኩ። በስብሰባ ላይ በተገኘሁበት በመጀመሪያው ዕለት የመንገድ ላይ ምሥክርነትን በተመለከተ ንግግር ተሰጠ። የነበረኝ እውቀት ውስን ቢሆንም ፈቃደኛ ሆኜ በዚህ ሥራ ተካፈልኩ። እንዲህ ሳደርግ ያዩኝ ብዙ ጓደኞቼ በጣም ከመገረማቸው የተነሳ እያፌዙብኝ ያልፉ ነበር!
ሰኔ 1940 በብሪስትል ከተማ ተጠመቅኩ። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኜ በዘወትር አቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እህቴም ራስዋን ለአምላክ ወስና በመጠመቋ ከፍተኛ ደስታ ተሰማኝ!
በጦርነት ወቅት በአቅኚነት ማገልገል
ጦርነቱ ከጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ ለውትድርና የመጥሪያ ወረቀት ደረሰኝ። በሕሊና ምክንያት እንደማልዋጋ ዮቪል ውስጥ ተመዝግቤ ስለነበር ብሪስቶል በሚገኝ ችሎት ፊት መቅረብ ነበረብኝ። ከጆን ዊን ጋር በሲንደርፎርድ፣ በግላስተርሻየር በኋላም ዌልስ ውስጥ በሃቨርፎርድዌስት እና በካርማርተን አብሬ አገለገልኩ። a ከጊዜ በኋላ በካርማርተን በዋለው ችሎት የ25 ፓውንድ (ይህ በወቅቱ ከፍተኛ ገንዘብ ነበር) የገንዘብ ቅጣት ጨምሮ በስዋንዜ እስር ቤት የሦስት ወር እስር ተፈረደብኝ። የኋላ ኋላም ይህን የገንዘብ መቀጫ ለመክፈል ባለመቻሌ ለሁለተኛ ጊዜ የሦስት ወር እስር ተፈረደብኝ።
ለሦስተኛ ጊዜ ችሎት ፊት ስቀርብ “ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የቄሣርን ለቄሣር’ እንደሚል አታውቅም?” የሚል ጥያቄ ቀረበልኝ። “አዎን፣ እንደዚያ እንደሚል አውቃለሁ። ሆኖም የጥቅሱን የመጨረሻ ቃላት ብናገር ደስ ይለኛል:- ‘የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ’ ይላል። እኔም እያደረግኩ ያለሁት ይህንኑ ነው” የሚል መልስ ሰጠሁ። (ማቴዎስ 22:21) ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ከወታደራዊ አገልግሎት ግዴታ ነጻ መሆኔን የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰኝ።
በ1945 መግቢያ ላይ ለንደን በሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ ውስጥ እንዳገለግል ተጋበዝኩ። በቀጣዩ ክረምት ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ አደረጃጀት በበላይነት ይመራ የነበረው ናታን ኤች ኖር እና የእርሱ ጸሐፊ ሚልተን ጂ ሄንሽል ለንደን መጡ። በስምንተኛው የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ለሚስዮናዊ ሥልጠና ስምንት ወጣት ወንድሞች የተጋበዙ ሲሆን ከእነርሱ መካከል እኔም እገኝበት ነበር።
ሚስዮናዊ ምድቦች
ግንቦት 23, 1946 በጦርነቱ ወቅት በተሠራ ሊበርቲ በተባለ መርከብ ተሳፍረን ፋውል ከሚገኘው አነስተኛ የኮርኒሽ ወደብ ጉዞ ጀመርን። የወደቡ ኃላፊ ካፒቴን ኮሊንስ የይሖዋ ምሥክር ስለነበር ወደቡን ለቅቀን ስንሄድ ፊሽካ ነፋ። የእንግሊዙ የባሕር ጠረፍ ከእይታችን እየጠፋ ሲሄድ ሁላችንም ሆዳችንን ባር ባር አለው። አትላንቲክን በችግር ብናቋርጥም ከ13 ቀናት ጉዞ በኋላ በሰላም ዩናይትድ ስቴትስ ደረስን።
ከነሐሴ 4 እስከ 11, 1946 ለስምንት ቀናት በክሌቭላንድ ኦሃዮ በተደረገው ግላድ ኔሽንስ ቴኦክራቲክ አሴምብሊ በተባለ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ መገኘታችን የማይረሳ ትዝታ ጥሎብናል። በስብሰባው ላይ ከ32 አገሮች የመጡት 302 እንግዶችን ጨምሮ 80, 000 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር። በዚያ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ንቁ! b የተባለ መጽሔትና መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት የሚረዳ “አምላክ እውነተኛ ይሁን” የተባለ መጽሐፍ መውጣቱ በደስታ ለተዋጠው ተሰብሳቢ ተነገረ።
በ1947 ከጊልያድ ትምህርት ቤት ከተመረቅን በኋላ እኔና ቢል ኮፕሰን ግብፅ ተመደብን። ሆኖም ወደ ግብፅ ከመሄዳችን በፊት ብሩክሊን ቤቴል ውስጥ በሪቻርድ አብራሃምሰን አማካኝነት ስለ ቢሮ ውስጥ አሠራር ጥሩ ሥልጠና ተሰጠኝ። እስክንድርያ ደርሰን ብዙም ሳንቆይ ከመካከለኛው ምሥራቅ የአኗኗር ዘይቤ ጋር ተላመድኩ። ሆኖም አረብኛ መልመዱ በጣም ፈታኝ ሆኖብኝ ነበር። ስለሆነም በአራት ቋንቋዎች የተዘጋጁ የመመስከሪያ ካርዶችን መጠቀም ነበረብኝ።
ቢል ኮፕሰን እዚያ ሰባት ዓመት ሲቆይ እኔ ግን ቪዛዬ ሊታደስልኝ ስላልቻለ ከአንድ ዓመት በኋላ አገሪቱን ለቅቆ መውጣት ግድ ሆነብኝ። በሚስዮናዊ አገልግሎት ያሳለፍኩት ይህ የአንድ ዓመት ጊዜ እጅግ ፍሬያማ ነበር። በየሳምንቱ ከ20 የሚበልጡ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን የመምራት ልዩ መብት አግኝቼ የነበረ ሲሆን በዚያን ወቅት እውነትን ከተማሩት መካከል አንዳንዶቹ አሁንም ድረስ ይሖዋን በማወደስ ላይ ይገኛሉ። ከግብፅ በኋላ ቆጵሮስ ተመደብኩ።
ቆጵሮስ እና እስራኤል
በመጀመሪያ ግሪክኛ መማር የጀመርኩ ሲሆን ከዚያም የአካባቢውን የአነጋገር ዘይቤ አጠናሁ። ጥቂት ቆይቶ አንቶኒ ሲዴሪስ ግሪክ እንዲያገለግል ሲመደብ እኔ ቆጵሮስ የሚገኘውን ሥራ በበላይነት እንድከታተል ተሾምኩ። በዚያን ጊዜ እስራኤል በቆጵሮስ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ትገኝ ስለነበር ከሌሎች ወንድሞች ጋር በመሆን እዚያ የሚገኙ ጥቂት ወንድሞችን የመጎብኘት አጋጣሚ አግኝቻለሁ።
ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እስራኤል በሄድኩበት ወቅት ሃይፋ ውስጥ ባለ አንድ ምግብ ቤት 50 ወይም 60 ተሰብሳቢዎች የተገኙበት ስብሰባ አድርገን ነበር። ተሰብሳቢውን እንደየብሔሩ በማስቀመጥ የስብሰባውን ፕሮግራም በስድስት የተለያዩ ቋንቋዎች አቀረብን! በሌላ ወቅት ደግሞ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ፊልም ኢየሩሳሌም ውስጥ ካሳየሁ በኋላ የሕዝብ ንግግር አቀረብኩ። በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚዘጋጅ አንድ ጋዜጣ ይህን ንግግር በሚመለከት የአድናቆት አስተያየት ሰንዝሯል።
በዚያን ወቅት ቆጵሮስ ውስጥ 100 የሚያክሉ ምሥክሮች የነበሩ ሲሆን እነርሱም ለእምነታቸው ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር። የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት ሕዝባዊ ዓመፅ በማስነሳት የልዩና የወረዳ ስብሰባዎችን ያስተጓጉልብን የነበረ ሲሆን በገጠራማ ክልሎች ውስጥ ስንመሠክር በድንጋይ መወገር ለእኔ አዲስ ተሞክሮ ነበር። ፈጥኖ እንዴት ማምለጥ እንደሚቻል መልመድ ነበረብኝ! እንዲህ ያለ ከባድ ተቃውሞ ቢኖርም በደሴቲቱ ላይ እንዲሠሩ የተመደቡ ተጨማሪ ሚስዮናውያንን ማግኘት እምነት የሚያጠነክር ነበር። ቶም እና ማሪ ጎልደን እንዲሁም ለንደን ተወልዶ ያደገው ቆጵሮሳዊው ኒና ኮንስታንቲ ወደ ሊማሶል ተመድበው ሲሄዱ ዴኒስ እና ማቪስ ማቴዎስ ከጆአን ሃሌይ እና በሪል ሄይዉድ ጋር እኔ ባለሁበት በፋማጉስታ ተመደቡ። በዚያው ጊዜ ቢል ኮፕሰንም ቆጵሮስ እንዲያገለግል ሲመደብ ከጊዜ በኋላ በርት እና በርይል ቬይሲ ከእርሱ ጋር እንዲያገለግሉ ተመደቡ።
ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር መላመድ
በ1957 መጨረሻ ላይ ታመምኩና በሚስዮናዊ አገልግሎቴ መቀጠል ተሳነኝ። ሁኔታው ቢያሳዝነኝም ጤንነቴ እንዲመለስልኝ ወደ እንግሊዝ ለመመለስ ወሰንኩ። እዚያም እስከ 1960 ድረስ በአቅኚነት አገለገልኩ። እህቴና ባለቤትዋ በደግነት እቤታቸው አሳረፉኝ። ሆኖም ሁኔታዎች ተለወጡ። ጆአን ከጊዜ ወደ ጊዜ ኑሮ እየከበዳት መጣ። ከእኔ ተለይታ በኖረችበት 17 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ባለቤትዋንና ሴት ልጅዋን ከመንከባከብ በተጨማሪ አረጋዊ የሆኑትንና እምብዛም ጤና ያልነበራቸውን አባታችንንና አክስታችንን ሚሊን በፍቅር ስትጦር ቆይታለች። አክስቴ ያሳየችውን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ ምሳሌ የመኮረጅ አስፈላጊነት በግልጽ የታየው በዚህ ጊዜ ሲሆን አክስቴም ሆነች አባቴ እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ ከእህቴ ጋር አብሬ ቆየሁ።
እንግሊዝ ውስጥ ኑሮ መሥርቶ መኖር በጣም ቀላል ቢሆንም ከጥቂት ቆይታ በኋላ ወደ ምድቤ ተመልሼ መሄድ እንዳለብኝ ተሰማኝ። ደግሞስ የይሖዋ ድርጅት እኔን ለማሠልጠን ከፍተኛ ገንዘብ አውጥቶ የለ? ስለዚህ በ1972 በአቅኚነት ለማገልገል በራሴ ወጪ ተመልሼ ወደ ቆጵሮስ ሄድኩ።
በቀጣዩ ዓመት ለሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ዝግጅት ለማድረግ ናታን ኤች ኖር መጥቶ ነበር። መመለሴን ሲረዳ ለመላው ደሴት የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንድሾም የቀረበውን ሐሳብ አጸደቀው። በዚህ ውድ መብት ለአራት ዓመታት አገልግያለሁ። ይሁን እንጂ ሥራው አብዛኛውን ጊዜ ግሪክኛ እንድናገር የሚያስገድድ በመሆኑ ተፈታታኝ ነበር።
የመከራ ጊዜ
ፖል አንድሩ ከሚባል ግሪክኛ ተናጋሪ ቆጵሮሳዊ ምሥክር ጋር በምሥራቅ ኪሬኒያ ሰሜናዊ የባሕር ዳርቻ በምትገኝ ካራኮሚ በምትባል መንደር አንድ ቤት መኖር ጀመርን። የቆጵሮስ ቅርንጫፍ ቢሮ ከኪሬኒያ ተራራዎች በስተደቡብ ኒቆሲያ ውስጥ ይገኝ ነበር። ሐምሌ 1974 መጀመሪያ ላይ ፕሬዚዳንት ማካሪዮስን ከሥልጣን ለማስወገድ የመንግሥት ግልበጣ ሲደረግ ኒቆሲያ ውስጥ ስለነበርኩ ቤተ መንግሥቱ በእሳት ሲጋይ ተመልክቻለሁ። ሁከቱ ጋብ ሲል ለወረዳ ስብሰባ ዝግጅት ለማድረግ ወደ ኪሬኒያ ፈጥኜ ተመለስኩ። ከሁለት ቀናት በኋላ በወደቡ ላይ የመጀመሪያው ቦንብ ሲፈነዳ ሰማሁ፤ ከዚያም ሰማዩ ከቱርክ ወታደሮችን በሚያመላልሱ ሄሊኮፕተሮች ተሞላ።
የብሪታንያ ተወላጅ ስለሆንኩ የቱርክ ወታደሮች ከኒቆሲያ ወጣ ብሎ ወደሚገኝ ቦታ ወሰዱኝ። እዚያም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ቃሌን ከተቀበሉ በኋላ ከቅርንጫፍ ቢሮው ጋር ግንኙነት አደረጉ። ከዚያም ውስብስብ የስልክና የኤሌክትሪክ ሽቦዎች ያሉበትን ቦታ አቋርጬ ሰው ዝር ወደማይልባቸው አካባቢዎች ሄድኩ። ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለኝ የሐሳብ ግንኙነት መስመር ባለመቋረጡ ምንኛ ደስተኛ ነበርኩ! ጸሎቴ በሕይወቴ ውስጥ እጅግ አስጨናቂ የነበረውን ይህን አስፈሪ ሁኔታ እንዳልፍ ረድቶኛል።
ንብረቴን ሁሉ ያጣሁ ቢሆንም በቅርንጫፍ ቢሮው ላይ ምንም ጉዳት አለመድረሱ አስደስቶኛል። አለመረጋጋቱ የቆየው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነበር። በጥቂት ቀናት ውስጥ ጣልቃ ገቡ ጦር የደሴቲቱን አንድ ሦስተኛ ደቡባዊ ክፍል በቁጥጥሩ ሥር አደረገ። እኛም ቤቴልን ለቀን ወደ ሊማዞል ለመሄድ ተገደድን። በሁከቱ ምክንያት ከተነኩት 300 ወንድሞች መካከል አብዛኞቹ ቤታቸውን ያጡ ሲሆን እነርሱን ለመርዳት ታስቦ በተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ መሥራት በመቻሌ ተደስቻለሁ።
ተጨማሪ የምድብ ለውጦች
በጥር 1981 የአስተዳደር አካሉ ወደ ግሪክ ተዛውሬ አቴንስ ከሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ ጋር እንድቀላቀል ጠየቀኝ። ሆኖም በዓመቱ መጨረሻ ላይ እንደገና ወደ ቆጵሮስ ተመልሼ የቅርንጫፍ ኮሚቴው አስተባባሪ ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ። ከለንደን ተልከው የመጡ እንድሪያስ ኮንቶዮርጊስ እና ማሮ የሚባሉ ቆጵሮሳውያን ባልና ሚስት “የብርታት ምንጭ” ሆነውልኝ ነበር።—ቆላስይስ 4:11 NW
በ1984 በቴዎዶር ጃራዝ በተደረገልን የዞን የበላይ ተመልካች ጉብኝት መደምደሚያ ላይ “ወንድም ጃራዝ ጉብኝቱን ሲጨርስ አብረኸው ወደ ግሪክ እንድትሄድ እንፈልጋለን” የሚል አጭር መልእክት የሰፈረበት ደብዳቤ ከአስተዳደር አካሉ ደረሰኝ። ለዚህ የተሰጠ ምክንያት አልነበረም። ሆኖም ግሪክ ከደረስን በኋላ በዚያች አገር ውስጥ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አስተባባሪ ሆኜ መሾሜን የሚገልጽ ከአስተዳደር አካሉ የተላከ ሌላ ደብዳቤ ለቅርንጫፍ ቢሮው ኮሚቴ ተነበበ።
በወቅቱ ክህደት ተከስቶ ነበር። እንዲሁም ሃይማኖትን የማስለወጥ ሕገ ወጥ ድርጊት ፈጽማችኋል የሚሉ ብዙ ክሶች ይነሱብን ነበር። በየዕለቱ የይሖዋ ሕዝቦች እየተያዙ ችሎት ፊት ይቀርባሉ። በወቅቱ የነበረውን ፈተና ተቋቁመው ፍጹም አቋማቸውን ከጠበቁ ወንድሞችና እህቶች ጋር መተዋወቅ ምንኛ ታላቅ መብት ነው! አንዳንዶቹ ጉዳያቸው በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የታየ ሲሆን በግሪክ ለሚደረገው የስብከት c
ሥራ ጥሩ ውጤት ያስገኙ ውሳኔዎችም ተሰጥተዋል።ግሪክ ውስጥ ባገለገልኩበት ወቅት በአቴንስ፣ በተሰሎንቄ እንዲሁም በሮድ እና በቀርጤስ ደሴቶች ላይ በተደረጉ የማይረሱ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ችያለሁ። እነዚያ አራት ዓመታት አስደሳችና ፍሬያማ ነበሩ። ሆኖም በ1988 ወደ ቆጵሮስ እንድመለስ የሚያደርግ ሌላ ለውጥ ይጠብቀኝ ነበር።
ወደ ቆጵሮስ ከዚያም እንደገና ወደ ግሪክ
ከቆጵሮስ በተለየሁባቸው ጊዜያት ወንድሞች ከኒቆሲያ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ወጣ ብሎ በሚገኝ ኔሱ በሚባል አካባቢ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ አግኝተው ስለነበር ብሩክሊን ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የመጣው ካሪ ባርበር የውሰና ንግግሩን አቀረበ። አሁን የደሴቲቱ ሁኔታ ይበልጥ እየተረጋጋ በመምጣቱ በመመለሴ ተደሰትኩ። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ አንዳንድ ለውጦች ተከሰቱ።
የአስተዳደር አካሉ ከአቴንስ በስተሰሜን ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ራቅ ብሎ በሚገኝ ቦታ ላይ አዲስ የቤቴል ቤት ለመገንባት የቀረበውን ፕላን አጸደቀው። እንግሊዝኛም ሆነ ግሪክኛ መናገር እችል ስለነበር በ1990 አዲሱ የሕንፃ ግንባታ ሥራ በሚካሄድበት ቦታ ላይ የሚሠሩ ዓለም ዓቀፍ ሠራተኞችን ላቀፈው ቤተሰብ በአስተርጓሚነት እንድሠራ ተጋበዝኩ። የግንባታ ሠራተኞችን ካቀፈው ቤተሰብ ጋር በፈቃደኝነት ለመሥራት የሚመጡ በመቶ የሚቆጠሩ የግሪክ ወንድሞችንና እህቶችን ለመቀበል በበጋ ወራት ሁልጊዜ ጠዋት በአሥራ ሁለት ሰዓት በግንባታው ቦታ ስደርስ ይሰማኝ የነበረው ደስታ አሁን ድረስ ይታወሰኛል! ደስታቸውና ቅንዓታቸው ምንጊዜም ከአእምሮዬ አይጠፋም።
የግሪክ ኦርቶዶክስ ቀሳውስትና ደጋፊዎቻቸው ወደ ግንባታው ቦታ ለመግባትና ሥራችንን ለማስተጓጎል ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም ይሖዋ ጸሎታችንን ሰምቶ ጥበቃ አድርጎልናል። አዲሱ የቤቴል ቤት ለአምላክ አገልግሎት እስከሚወሰንበት እስከ ሚያዝያ 13, 1991 ድረስ እዚያው ቆየሁ።
ውድ እህቴን መርዳት
በቀጣዩ ዓመት ለእረፍት ወደ እንግሊዝ ተመልሼ ሄድኩና ከእህቴና ከባለቤትዋ ጋር ቆየሁ። የሚያሳዝነው ግን እዚያው እያለሁ የእህቴ ባል ሁለት ጊዜ የልብ ድካም አጋጠመውና ለህልፈተ ሕይወት ዳረገው። ጆአን በሚስዮናዊ አገልግሎት በቆየሁባቸው ጊዜያት ያልተቆጠበ ድጋፍ ስታደርግልኝ ቆይታለች። የማበረታቻ ደብዳቤ ሳትጽፍልኝ የቀረችበት አንድም ሳምንት የለም ለማለት እችላለሁ። ለማንኛውም ሚስዮናዊ ቢሆን እንዲህ ያለው ግንኙነት ምንኛ በረከት ነው! አሁን እሷ ራሷ ጤና ያጣች መበለት በመሆኗ እርዳታ የሚያስፈልጋት ሆነች። ምን ማድረግ ይኖርብኛል?
የጆአን ሴት ልጅ ቴልማ እና ባለቤትዋም ቢሆኑ በጉባኤያቸው የምትገኝ በጠና የታመመች ታማኝ መበለት የሆነችውን የአጎቴን ልጅ እየረዱ ነበር። ስለዚህ ከብዙ ጸሎት በኋላ ጆአንን ለመርዳት ስል እዚያው መቆየት እንዳለብኝ ወሰንኩ። ራስን ከሁኔታዎች ጋር ማስማማት እንዲህ የዋዛ አልነበረም። ሆኖም በዮቪል ከሚገኙ ሁለት ጉባኤዎች መካከል በአንዱ ማለትም በፔን ሚል ሽማግሌ ሆኜ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ።
ሚስዮናዊ ሆኜ አብሬያቸው ስሠራ ከነበሩ ወንድሞች ጋር ዘወትር በስልክና በደብዳቤ የምንገናኝ ሲሆን ለዚህም በጣም አመስጋኝ ነኝ። ወደ ግሪክ ወይም ወደ ቆጵሮስ መመለስ እንደምፈልግ ብናገር የአውሮፕላን ትኬት ወዲያው እንደሚደርሰኝ አውቃለሁ። ሆኖም አሁን የ80 ዓመት አዛውንት በመሆኔ ዓይኔም ሆነ ጤንነቴ እንደቀድሞው አይደለም። እንደበፊቱ የልቤን ማድረግ አለመቻሌ የሚያሳዝነኝ ቢሆንም በቤቴል አገልግሎት ያሳለፍኳቸው ዓመታት በአሁኑ ጊዜ ጠቃሚ ሆነው ያገኘኋቸውን በርካታ ልማዶች እንዳዳብር ረድተውኛል። ለምሳሌ ያህል ሁልጊዜ ከቁርስ በፊት የዕለቱን ጥቅስ አነብባለሁ። ለሚስዮናዊ አገልግሎት ስኬታማነት ቁልፍ የሆኑትን ከሰዎች ጋር የመግባባትና ሌሎችን የማፍቀር ባሕርያት ማዳበር ችያለሁ።
ይሖዋን በማወደስ ያሳለፍኳቸውን 60 የሚያክሉ አስደሳች ዓመታት ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስባቸው የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ታላቅ ጥበቃና ከሁሉ የተሻለ ትምህርት የሚገኝበት መሆኑን እረዳለሁ። እኔም፣ “በመከራዬ ቀን መጠጊያዬና አምባዬ ሆነኸኛል” በማለት ዳዊት ለይሖዋ የተናገራቸውን ቃላት በሙሉ ልቤ ማስተጋባት እችላለሁ።—መዝሙር 59:16
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የጆን ዊን የሕይወት ታሪክ “ልቤ በምስጋና ተሞልቷል” በሚል ርዕስ መስከረም 1, 1997 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 25-8 ላይ ወጥቷል።
b ቀደም ሲል መጽናኛ ተብሎ ይታወቅ ነበር።
c የታኅሣሥ 1, 1998 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 20-1 እና የመስከረም 1, 1993 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 27-31 እንዲሁም የጥር 8, 1998 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 21-2 እና የመጋቢት 22, 1997 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 14-5 ተመልከት።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ግሪክ
አቴንስ
ቆጵሮስ
ኒቆሲያ
ኪሬኒያ
ፋማጉስታ
ሊማዞል
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እናቴ በ1915
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እኔና (ከግራ አራተኛ) ሌሎች የጊልያድ ስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች በ1946 በብሩክሊን ቤቴል ጣሪያ ላይ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እንግሊዝ ከተመለስኩ በኋላ ከአክስቴ ከሚሊ ጋር