የጥንቱ ዓለም የጠፋው ለምንድን ነው?
የጥንቱ ዓለም የጠፋው ለምንድን ነው?
ዓለም አቀፉ የጥፋት ውኃ የተፈጥሮ አደጋ አልነበረም። ከአምላክ የመጣ ፍርድ ነበር። ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም በአብዛኛው ሰሚ ጆሮ ተነፍጎት ነበር። ለምን? ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል:- “በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፣ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፣ [ሰዎች] ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደነበሩ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ [አላወቁም።]”—ማቴዎስ 24:38, 39፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
በሥልጣኔ የመጠቀ ኅብረተሰብ
ከጥፋት ውኃው በፊት የነበረው ኅብረተሰብ በአንዳንድ መንገዶች ዛሬ እኛ የሌሉን አጋጣሚዎች ነበሩት። ለምሳሌ ያህል መላው የሰው ዘር አንድ ቋንቋ ይናገር ነበር። (ዘፍጥረት 11:1) ይህም የተለያየ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች የተቀናጀ ጥረት ለሚጠይቀው ሥነ ጥበባዊና ሳይንሳዊ ግኝት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጎ መሆን አለበት። በተጨማሪም ብዙ ሰዎች ረዥም ዘመን መኖር መቻላቸው የእውቀት ክምችታቸውን እንዲያሳድጉ ረድቷቸው መሆን አለበት።
አንዳንዶች በወቅቱ የሰው ዘር እድሜ የሚባለውን ያክል ረዥም እንዳልነበረና በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ውስጥ የተጠቀሱት ዓመታት ወራት ብቻ እንደሆኑ ይናገራሉ። ይህ ትክክል ነው? እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መላልኤል የሚናገረውን ተመልከት:- “መላልኤልም መቶ ስድሳ አምስት [“ስድሳ አምስት፣” አ.መ.ት ] ዓመት ኖረ፣ ያሬድንም ወለደ . . . መላልኤልም የኖረበት ዘመን ሁሉ ስምንት መቶ ዘጠና አምስት ዓመት ሆነ፤ ሞተም።” (ዘፍጥረት 5:15-17) አንድ ዓመት አንድ ወር ከሆነ መላልኤል ልጅ የወለደው ገና በአምስት ዓመቱ ነው ማለት ነው! ይህ ደግሞ በፍጹም ሊሆን አይችልም። በዚያን ጊዜ የነበሩት ሰዎች ለፍጽምና የቀረቡ በመሆናቸው የመጀመሪያው ሰው አዳም የነበረው ዓይነት ጥንካሬ ነበራቸው። በዚህም ምክንያት ለብዙ መቶ ዓመታት ኖረዋል። ታዲያ ምን አከናወኑ?
የጥፋት ውኃ ከመምጣቱ ብዙ ዓመታት ቀደም ብሎ የምድር ሕዝብ ቁጥር በጣም ከመጨመሩ የተነሣ የአዳም ልጅ ቃየን ሄኖሕ የተባለችውን ከተማ ቆረቆረ። (ዘፍጥረት 4:17) ከጥፋት ውኃው በፊት በነበሩት ዓመታት የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ተቋቁመው ነበር። ‘ናስና ብረትን’ በማቅለጥ የተለያዩ መሣሪያዎች ይሠሩ ነበር። (ዘፍጥረት 4:22) እነዚህ መሣሪያዎች ለግንባታ፣ ለአናጺነት ሙያ፣ ለልብስ ስፌትና ለእርሻ ሥራዎች እንደሚውሉ ምንም ጥርጥር የለውም። እነዚህ ሁሉ የሥራ መስኮች የተጠቀሱት ስለ መጀመሪያዎቹ የምድር ነዋሪዎች በሚገልጹት ዘገባዎች ውስጥ ነው።
ይህ ዓይነቱ የእውቀት ክምችት ተከታዩ ትውልድ በሥነ ብረታ ብረት፣ ዘር በማልማት ጥናት፣ በከብት እርባታ እንዲሁም በሥነ ጽሑፍና በሥነ ጥበብ የሙያ መስኮች ችሎታውን እንዲያዳብር ረድቶት መሆን አለበት። ለምሳሌ ያህል ዩባል “በገናንና መለከትን ለሚይዙ አባት ነበረ።” (ዘፍጥረት 4:21) ሥልጣኔ ተስፋፍቶ ነበር። ሆኖም በድንገት ሁሉም ነገር እንዳልነበረ ሆነ። ምን ተፈጠረ?
ችግሩ ምን ነበር?
ከጥፋት ውኃ በፊት የኖረው ትውልድ ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎች የነበሩት ቢሆንም ጅምሩ ግን መጥፎ ነበር። የሁሉም አባት የነበረው አዳም በአምላክ ላይ ዓምፆአል። የመጀመሪያዋን ከተማ የቆረቆረው ቃየን የገዛ ወንድሙን ገድሏል። ክፋት በፍጥነት መዛመቱ ምንም አያስደንቅም! አዳም ለልጆቹ ያወረሰው ብልሹ ቅርስ ያስከተለው መዘዝ እያደር እየከፋ የሚሄድ ነበር።—ሮሜ 5:12
ይሖዋ ሁኔታው በዚህ መልኩ የሚቀጥለው ለተጨማሪ 120 ዓመት ብቻ እንደሆነ ሲወስን ሁኔታዎቹ የሚደመደሙበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ግልጽ ሆኖ ነበር። (ዘፍጥረት 6:3) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- ‘የሰው ክፋት በምድር ላይ በዛ፣ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ ሆነ። ምድርም ግፍን ተሞላች።’—ዘፍጥረት 6:5, 11
ከጊዜ በኋላ አምላክ የጥፋት ውኃ በማምጣት መላውን ሥጋ ለባሽ እንደሚያጠፋ ለኖኅ በግልጽ ነገረው። (ዘፍጥረት 6:13, 17) ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” የነበረ ቢሆንም ሰዎች በዙሪያቸው ያለው ዓለም ድንገት ይጠፋል ብሎ ማሰብ ከብዷቸው ሊሆን እንደሚችል ምንም አያጠራጥርም። (2 ጴጥሮስ 2:5) ማስጠንቀቂያውን የሰሙትና ከጥፋቱ በሕይወት የተረፉት ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። (1 ጴጥሮስ 3:20) ይህ ዛሬ ለምንኖረው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ለእኛ የሚያስተላልፈው መልእክት ምንድን ነው?
የምንኖረው ከኖኅ ዘመን ጋር በሚመሳሰል ጊዜ ውስጥ ነው። በየቀኑ አሰቃቂ ስለሆኑ የሽብርተኝነት ድርጊቶች፣ የዘር ማጥፋት ዘመቻዎች፣ ስውር ዓላማ ያላቸው መሣሪያ የታጠቁ ግለሰቦች ስለሚያደርሱት የጅምላ ጭፍጨፋና አስደንጋጭ በሆነ መጠን እየጨመረ ስለመጣው የቤት ውስጥ ዓመፅ የሚገልጹ ዜናዎች እንሰማለን። ምድር እንደገና በዓመፅ ተሞልታለች። ጥንት እንደተደረገው ሁሉ ዛሬም ዓለም ስለሚመጣባት ፍርድ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷታል። ኢየሱስ ራሱ በአምላክ የተሾመ ፈራጅ ሆኖ እንደሚመጣና እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ሰዎችን እንደሚለያያቸው ተናግሯል። ኢየሱስ ብቃቱን አሟልተው ያልተገኙ “ወደ ዘላለም ቅጣት . . . ይሄዳሉ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 25:31-33, 46) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው በዚህ ጊዜ ብቸኛውን እውነተኛ አምላክ የሚያመልኩ በሚልዮን የሚቆጠሩ እጅግ ብዙ ሰዎች ከጥፋቱ ይተርፋሉ። እነዚህ ሰዎች ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መጠን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት አግኝተው በመጪው ዓለም ውስጥ በደስታ ይኖራሉ።—ሚክያስ 4:3, 4፤ ራእይ 7:9-17
ብዙዎች ይህንን በመሳሰሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦችና ስለ ፍርድ እርምጃ በሚገልጹ ማስጠንቀቂያዎች ያፌዛሉ። የፍርድ እርምጃው እነዚህ ሐሳቦች እውነት መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው። ሆኖም ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደገለጸው እነዚህ ዘባቾች እውነታውን ለመቀበል አይፈልጉም። እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች . . . [ይመጣሉ።] . . . እነርሱም:- የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? . . . ሰማያት ከጥንት ጀምረው ምድርም በእግዚአብሔር ቃል ከውኃ ተጋጥማ በውኃ መካከል እንደ ነበሩ ወደው አያስተውሉምና፤ በዚህም ምክንያት ያን ጊዜ የነበረ 2 ጴጥሮስ 3:3-7
ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤ አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል።”—በዛሬው ጊዜ የኢየሱስን ትንቢታዊ መመሪያ በመታዘዝ ስለመጪው የፍርድ ቀን የሚገልጸው ማስጠንቀቂያና ይህንን ተከትሎ ስለሚሰፍነው ሰላም የሚናገረው ምሥራች በዓለም ዙሪያ በቅንዓት በመሰበክ ላይ ነው። (ማቴዎስ 24:14) ይህ ማስጠንቀቂያ በቀላሉ ሊታይ አይገባውም። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የተናገረውን ይፈጽማል።
መጪው ዓለም
ከፊታችን ከሚጠብቀን ታላቅ ለውጥ አንጻር የሰው ዘር የወደፊት ዕጣ ምን ይሆናል? ኢየሱስ በዝነኛው የተራራ ስብከቱ መግቢያ ላይ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና” በማለት ቃል ገብቷል። ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ “ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው ወደ አምላክ እንዲጸልዩ አስተማራቸው። (ማቴዎስ 5:5፤ 6:10) አዎን፣ ኢየሱስ ራሱ ታማኝ የሰው ዘሮች በዚህችው ምድር ላይ አስደናቂ የወደፊት ጊዜ እንደሚጠብቃቸው አስተምሯል። ሁኔታውን ደግሞ “ዳግመኛ ልደት” ሲል ጠርቶታል።—ማቴዎስ 19:28
ስለዚህ ስለ መጪው ጊዜ ስታሰላስል ዘባቾች የአምላክን ማስጠንቀቂያ እንድትጠራጠር እንዲያደርጉህ አትፍቀድ። በዙሪያችን ያለው ዓለም ተደላድሎ የቆመ የሚመስል ሲሆን ረዥም ዘመንም አስቆጥሯል። ሆኖም ትምክህታችንን በእርሱ ላይ መጣል የለብንም። የሰው ዘር ዓለም ተፈርዶበታል። ስለዚህ ሐዋርያው ጴጥሮስ በደብዳቤው መደምደሚያ ላይ ከገለጸው ሐሳብ ማበረታቻ አግኝ:-
“ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፣ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? . . . ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፣ . . . በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ።” (2 ጴጥሮስ 3:11, 12, 14, 18) በኖኅ ዘመን ከደረሰው ሁኔታ ተማር። ወደ አምላክ ቅረብ። በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት እደግ። ለአምላክ የማደርን ባሕርይ አዳብር። ከዚህ ዓለም ፍጻሜ በሕይወት ተርፈው ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ከመረጡት በሚልዮን ከሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ተባበር።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከጥፋት ውኃው በፊት የብረታ ብረት ሥራ ይታወቅ ነበር
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከፊታችን አስደናቂ ጊዜ ይጠብቀናል