በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለፍቅርና ለመልካም ሥራ የሚያነቃቁ ስብሰባዎች

ለፍቅርና ለመልካም ሥራ የሚያነቃቁ ስብሰባዎች

“ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ”

ለፍቅርና ለመልካም ሥራ የሚያነቃቁ ስብሰባዎች

ከቶሮንቶ እስከ ቶኪዮ፣ ከሞስኮ እስከ ሞንቲቪዲዮ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችና ጓደኞቻቸው በየሳምንቱ ለበርካታ ጊዜያት ወደ አምልኮ ቦታዎቻቸው ይጎርፋሉ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ለረዥም ሰዓታት ሲሠሩ ውለው ድክም ያላቸው ትጉህ የቤተሰብ ኃላፊዎች፣ ትንንሽ ልጆቻቸውን አስከትለው የሚሄዱ ታታሪ ሚስቶችና እናቶች፣ ትምህርት ቤት ውለው የሚመጡ ጠንካራ ወጣቶች፣ በሕመምና በድካም ምክንያት ዝግ ብለው የሚራመዱ እርጅና የተጫጫናቸው አረጋውያን፣ ደፋር መበለቶችና ወላጆች የሌላቸው ልጆች እንዲሁም መጽናኛ የሚሹ የተጨነቁ ነፍሳት ይገኙበታል።

እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ጀት ከሚወነጨፉ የመንገደኛ ባቡሮች አንስቶ እስከ አህያ፣ ከተጨናነቁ የምድር ውስጥ መኪናዎች አንስቶ እስከ ጭነት መኪና ባሉት የተለያዩ መጓጓዣዎች ይጠቀማሉ። አንዳንዶች አዞ የተሞሉ ወንዞችን ማቋረጥ ሲኖርባቸው ሌሎች ደግሞ በትላልቅ ከተሞች ያለውን ትዕግሥት አስጨራሽ የተሽከርካሪ ጭንቅንቅ መታገሥ ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሁሉ ሰዎች ይህን ያህል ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉት ለምንድን ነው?

ዋነኛው ምክንያት በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና ተሳትፎ ማድረግ ለይሖዋ አምልኮ የሚቀርብበት አንዱ አስፈላጊ መንገድ በመሆኑ ነው። (ዕብራውያን 13:15) ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ በጻፈ ጊዜ ሌላም ተጨማሪ ምክንያት ጠቅሷል:- “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ . . . መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር [“እንበረታታ፣” አ.መ.ት] እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።” (ዕብራውያን 10:24, 25፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እዚህ ላይ ጳውሎስ “ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ” በማለት የዘመረውን የመዝሙራዊውን ዳዊት ስሜት አስተጋብቷል።​—⁠መዝሙር 122:1

ክርስቲያኖች በስብሰባዎቻቸው ላይ መገኘት የሚያስደስታቸው ለምንድን ነው? በስብሰባው ላይ የሚገኙት ሰዎች ተመልካቾች ብቻ ባለመሆናቸው ነው። ይልቁንም ስብሰባዎቹ እርስ በእርስ ለመተዋወቅ የሚያስችል አጋጣሚ ይሰጧቸዋል። በተለይ እነዚህ ስብሰባዎች ለመቀበል ብቻ ሳይሆን ለመስጠት እንዲሁም ፍቅር ለማሳየትና በመልካም ሥራ በመካፈል እርስ በእርስ ለመነቃቃት አጋጣሚ ይከፍታሉ። ይህም ስብሰባዎች የሚያንጹ ወቅቶች እንዲሆኑ ያስችላል። ከዚህም በላይ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ኢየሱስ “ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ” ሲል የገባውን ቃል የሚፈጽምበት አንደኛው መንገድ ነው።​—⁠ማቴዎስ 11:28

መጽናኛ የሚገኝበትና አሳቢነት የሚታይበት ቦታ

የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎቻቸውን እረፍት የሚገኝበት ቦታ አድርገው እንዲመለከቱ የሚያደርጋቸው በቂ ምክንያት አላቸው። አንደኛው ምክንያት “ታማኝና ልባም ባሪያ” በተገቢው ጊዜ የሚያዘጋጃቸው መንፈሳዊ ምግቦች በስብሰባዎች ላይ ይቀርባሉ። (ማቴዎስ 24:45) ስብሰባዎች የይሖዋ አገልጋዮች የሰለጠኑና ቀናተኛ የአምላክ ቃል አስተማሪዎች እንዲሆኑ በመርዳት ረገድም ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። በተጨማሪም አንድ ሰው አፍቃሪና አሳቢ እንዲሁም በአስቸጋሪ ጊዜያት ሌሎችን ለመርዳትና ለማጽናናት ዝግጁና ፈቃደኛ የሆኑ ተንከባካቢ ወዳጆች በመንግሥት አዳራሹ ማግኘት ይችላል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 7:5-7

ሴት ልጆቿ የአምስትና የስምንት ዓመት ዕድሜ በነበሩበት ወቅት ባሏን በሞት ያጣች ፊሊስ የተባለች አንዲት መበለት ያጋጠማት ይህ ነበር። ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የእሷንም ሆነ የልጆቿን መንፈስ በማደስ ረገድ የተጫወቱትን ሚና በማስመልከት ስትናገር እንዲህ ብላለች:- “የእምነት ባልደረቦቼ እቅፍ በማድረግ፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ በማካፈል ወይም እጄን ጠበቅ አድርገው በመጨበጥ ሁልጊዜም ፍቅራቸውንና አሳቢነታቸውን ስለሚገልጹልኝ ወደ መንግሥት አዳራሹ መሄድ የሚያጽናና ነው። ፈጽሞ ከዚያ መለየት አልፈልግም።”​—⁠1 ተሰሎንቄ 5:14

ማሪ ከባድ ቀዶ ሕክምና ከተደረገላት በኋላ ለመዳን ቢያንስ ስድስት ሳምንታት እንደሚወስድባት ሐኪሟ ነገራት። ማሪ እያገገመች በነበረችባቸው የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት በስብሰባዎች ላይ መገኘት አልቻለችም። ሐኪሟ እንደቀድሞው ደስተኛ እንዳልሆነች አስተዋለ። በስብሰባዎች ላይ እንደማትገኝ ሲረዳ እንድትሄድ አበረታታት። ማሪም እምነትዋን የማይጋራት ባለቤትዋ ለጤናዋ በማሰብ ወደ ስብሰባዎች እንድትሄድ እንደማይፈቅድላት ነገረችው። በዚህ ምክንያት ሐኪሙ ማበረታቻና የሚያንጽ ወዳጅነት ለማግኘት ወደ መንግሥት አዳራሽ እንድትሄድ “የሚያዝዝ” ወረቀት ሰጣት። ማሪ እንዲህ ስትል ትደመድማለች:- “የጉባኤ ስብሰባ ላይ በተገኘሁ በመጀመሪያው ቀን በጣም ተሻለኝ። መብላት ጀመርኩ፣ ሙሉውን ሌሊት ተኝቼ አደርኩ፣ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒት አሁንም አሁንም መውሰድ አላስፈለገኝም፤ ፊቴም በደስታ ፈካ!”​—⁠ምሳሌ 16:24

በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚታየው ፍቅር የሰፈነበት መንፈስ በሌሎች ዘንድ ሳይስተዋል አላለፈም። አንዲት የኮሌጅ ተማሪ በኢተኖሎጂ ትምህርቷ ለምታዘጋጀው የጥናት ጽሑፍ የይሖዋ ምሥክሮችን ቀርባ ለመመልከት መረጠች። በስብሰባዎች ላይ የተመለከተችውን ሁኔታ በጥናት ጽሑፏ ላይ እንዲህ ብላ ጽፋለች:- “የተደረገልኝ ሞቅ ያለ አቀባበል . . . በጣም የሚያስደንቅ ነበር። ወዳጃዊ መንፈስ የይሖዋ ምሥክሮች ተለይተው የሚታወቁበት ባሕርይ ሲሆን እኔም የተመለከትኩት ይህንን ትልቅ ግምት የሚሰጠው የስብሰባው ገጽታ ነው።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 14:25

በዚህ በመከራ በተሞላ ዓለም ውስጥ የክርስቲያን ጉባኤ በበረሃ ውስጥ እንዳለ መንፈሳዊ ገነት ነው። ሰላምና ፍቅር የሚገኝበት ቦታም ነው። አንተም በስብሰባዎች ላይ በመገኘት “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፣ እነሆ፣ መልካም ነው፣ እነሆም፣ ያማረ ነው” የሚሉትን የመዝሙራዊው ቃላት እውነተኝነት በዓይንህ መመልከት ትችላለህ።​—⁠መዝሙር 133:1

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለየት ያለ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ትኩረት መስጠት

መስማት የተሳናቸው ሰዎች ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ጥቅም ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው? የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎች እያቋቋሙ ነው። ባለፉት 13 ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 27 የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎችና 43 የምልክት ቋንቋ ቡድኖች ተቋቁመዋል። በአሁኑ ጊዜ ቢያንስ በ40 ሌሎች አገሮች ውስጥ 140 የሚያክሉ የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎች አሉ። ክርስቲያናዊ ጽሑፎች በ13 የምልክት ቋንቋዎች በቪዲዮ ተዘጋጅተዋል።

የክርስቲያን ጉባኤ መስማት የተሳናቸው ይሖዋን ማወደስ የሚችሉበት አጋጣሚ አዘጋጅቶላቸዋል። በፈረንሳይ የምትኖረውና ቀድሞ ካቶሊክ የነበረችው ኦዴል በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ትሰቃይና ራስዋን ለማጥፋት ታስብ ነበር። በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ ላገኘችው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ከልብ በመነጨ የአመስጋኝነት ስሜት “ጤንነቴ ተመልሶልኛል እንዲሁም ሕይወት አስደሳች ሆኖልኛል። ከሁሉ በላይ ደግሞ እውነትን አግኝቻለሁ። አሁን ሕይወት ትርጉም ያለው ሆኖልኛል” በማለት ትናገራለች።