በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሬሳ የማድረቅ ልማድ ለክርስቲያኖች ተገቢ ነውን?

ሬሳ የማድረቅ ልማድ ለክርስቲያኖች ተገቢ ነውን?

ሬሳ የማድረቅ ልማድ ለክርስቲያኖች ተገቢ ነውን?

ታማኙ ፓትርያርክ ያዕቆብ በሕይወቱ ፍጻሜ ላይ “በኬጢያዊ በኤፍሮን እርሻ ላይ ባለችው ዋሻ ከአባቶቼ ጋር ቅበሩኝ፤ እርስዋም በከነዓን ምድር በመምሬ ፊት ያለች . . . ዋሻ ናት” የሚል ጥያቄ አቀረበ። ​—⁠ዘፍጥረት 49:​29-31

ዮሴፍ በወቅቱ በግብፅ ውስጥ በሰፊው ይሠራበት የነበረውን ልማድ በመከተል አባቱ የጠየቀውን ፈጽሟል። ዮሴፍ “አገልጋዮቹ የሆኑትን መድኀኒት ቀማሚዎች የአባቱን ሬሳ መልካም መዓዛ ባለው ሽቶ እያሹ እንዲያደርቁት” አዘዘ። በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ 50 ውስጥ ተመዝግቦ በሚገኘው ዘገባ መሠረት መድኃኒት ቀማሚዎቹ በተለመደው 40 ቀን ውስጥ ሬሳውን አደረቁ። የያዕቆብ ሬሳ እንዲደርቅ መደረጉ በዝግታ የሚጓዙት እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው የቤተሰቡ አባላትና የግብፅ መኳንንቶች 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ተጉዘው የያዕቆብን አስከሬን ኬብሮን ለመቅበር አስችሏቸዋል።​—⁠ዘፍጥረት 50:​1-14 የ1980 ትርጉም

በመድኃኒት እንዲደርቅ የተደረገውን የያዕቆብ አስከሬን አንድ ቀን ማግኘት ይቻል ይሆን? አስከሬኑን የማግኘቱ አጋጣሚ እጅግ የመነመነ ነው። የእስራኤል ምድር ውኃ የሞላበት አካባቢ የነበረ መሆኑ ሰው ሠራሽ ቅርሶችን የማግኘቱን አጋጣሚ ውስን አድርጎታል። (ዘጸአት 3:​8) ከብረት ወይም ከድንጋይ የተሠሩ ጥንታዊ ዕቃዎችን በብዛት ማግኘት ቢቻልም እንደ ልብስ፣ ቆዳና የደረቀ አስከሬንን የመሰሉ በቀላሉ ሊበሰብሱ የሚችሉ አብዛኞቹ ነገሮች እርጥበቱንና ተለዋዋጭ የተፈጥሮ ክስተቶችን መቋቋም አይችሉም።

ሬሳ ማድረቅ ምንድን ነው? ዓላማውስ ምን ነበር? ሬሳ ማድረቅ ለክርስቲያኖች ተገቢ ነውን?

ልምዱ የጀመረው የት ነበር?

ሬሳ ማድረቅ የሰውን ወይም የእንስሳን በድን ሳይበሰብስ የማቆያ ዘዴ ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። ሬሳ የማድረቅ ልማድ ግብፅ ውስጥ የጀመረ ቢሆንም በጥንት አሦራውያን፣ ፋርሳውያንና እስኩቴሶችም ዘንድ የተለመደ እንደነበረ የታሪክ ተመራማሪዎች ይስማማሉ። ሬሳ ስለማድረቅ ዘዴ ለማወቅ እንዲሁም በዚያ ላይ ምርምር ለማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ሐሳቡ የመነጨው በበረሃ አሸዋ ውስጥ ተቀብረው የቆዩ አስከሬኖች ምንም ሳይፈራርሱ ከተገኙ በኋላ ሳይሆን አይቀርም። እንዲህ ባለ አካባቢ የተቀበረ አካል እርጥበትና አየር ስለማያገኘው የመበስበስ አጋጣሚው አነስተኛ ይሆናል። አንዳንዶች ሬሳ የማድረቅ ልማድ የጀመረው ናትሮን (ሶዲየም ካርቦኔት) በተባለ አልካሊ ውስጥ ያልበሰበሱ በድን አካላት ከተገኙ በኋላ እንደሆነ ለማስረዳት ይሞክራሉ። ይህ አልካሊ ደግሞ በግብፅና በአካባቢው በብዛት ይገኛል።

ሬሳ እንዲደርቅ የሚደረግበት ዓላማ ከሞት በኋላ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የሚከሰተውን አስከሬኑ እንዲበሰብስ የሚያደርገውን የባክቴሪያዎች እንቅስቃሴ እንዲገታ ለማድረግ ነው። ይህን ሒደት ማቋረጥ ከተቻለ አስከሬኑ መበስበሱን ያቆማል ወይም ቢያንስ ፍጥነቱ በእጅጉ ይቀንሳል። ሬሳ እንዲደርቅ የሚደረገው በሦስት ምክንያቶች የተነሳ ነው፦ አስከሬኑን ልክ በሕይወት እንዳለ ለማስመሰል፣ እንዳይበሰብስ ለመከላከል እንዲሁም በአውዳሚ ነፍሳት እንዳይበላሽ ለማድረግ ነው።

የጥንቶቹ ግብፃውያን በአብዛኛው ሙታናቸውን የሚያደርቁት በሃይማኖታዊ ምክንያቶች የተነሳ ነው። ከሞት በኋላ ሕይወት አለ የሚለው እምነታቸው ከግዑዙ ዓለም ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዳይቋረጥ ካላቸው ፍላጎት ጋር የተያያዘ ነበር። በድን አካላቸው ለዘላለም ጥቅም ላይ እንደሚውልና በመጨረሻም መልሶ ሕይወት እንደሚያገኝ ያምኑ ነበር። ሬሳ ማድረቅ የተለመደ የመሆኑን ያህል እንዴት ያደርቁ እንደነበር የሚገልጽ አንድም የታሪክ መዝገብ እስከ አሁን ድረስ አልተገኘም። ከሁሉ የተሻለው የታሪክ መዝገብ በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የኖረው ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ሄሮዶቱስ ያሰፈረው ዘገባ ነው። ይሁን እንጂ ሄሮዶቱስ ያሰፈረውን መመሪያ ተከትሎ ተመሳሳይ ውጤት ለማግኘት የተደረገው ሙከራ ጥሩ ውጤት እንዳላስገኘ ተገልጿል።

ለክርስቲያኖች ተገቢ ነውን?

የያዕቆብን አስከሬን በመድኃኒት ያደረቁት ሰዎች ከእርሱ ጋር የሚመሳሰል ሃይማኖታዊ እምነት ያላቸው ሰዎች አልነበሩም። ሆኖም ዮሴፍ የአባቱን አስከሬን ለመድኃኒት ቀማሚዎች ሲሰጥ በወቅቱ ግብፅ ውስጥ ሬሳ በሚደርቅበት ጊዜ ይደረግ የነበረው ዓይነት የጸሎትና ሌላ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት እንዲደረግ ጠይቋል ብሎ ማሰቡ ፈጽሞ የማይመስል ነው። ያዕቆብም ሆነ ዮሴፍ የእምነት ሰዎች ነበሩ። (ዕብራውያን 11:​21, 22) ምንም እንኳን ይሖዋ የያዕቆብ አስከሬን ሳይፈርስ እንዲቆይ ያዘዘ ባይሆንም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ድርጊቱ እንደተወገዘ የሚያሳይ ምንም ሐሳብ የለም። የያዕቆብ ሬሳ እንዲደርቅ መደረጉ ለእስራኤል ሕዝብም ሆነ ለክርስቲያን ጉባኤ ምሳሌ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። እንዲያውም በአምላክ ቃል ውስጥ ይህን በሚመለከት የተሰጠ ግልጽ የሆነ መመሪያ የለም። የዮሴፍ አስከሬን እዚያው ግብፅ ውስጥ እንዲደርቅ መደረጉን ከሚገልጸው ታሪክ በኋላ ስለዚህ ድርጊት የሚናገር ሌላ ተጨማሪ ሐሳብ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አይገኝም።​—⁠ዘፍጥረት 50:​26 አ.መ.ት

በጳለስጢና ምድር በመቃብሮች ውስጥ የሚገኙት የበሰበሱ አስከሬኖች ዕብራውያን ለአጭር ጊዜ ካልሆነ በስተቀር ሬሳ የማድረቅ ልማድ እንዳልነበራቸው ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል የአልዓዛር አስከሬን እንዲደርቅ አልተደረገም። በጨርቅ ተገንዞ የነበረ ቢሆንም እንኳ መቃብሩ የተገጠመበት ድንጋይ ሊነሳ ሲል ሁኔታው ያሳሰባቸው ሰዎች ነበሩ። አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን አልፎት ስለነበር መቃብሩ ሲከፈት ሊሸት እንደሚችል እህቱ እርግጠኛ ነበረች።​—⁠ዮሐንስ 11:​38-44

የኢየሱስ ክርስቶስ አስከሬን እንዲደርቅ ተደርጎ ነበር? የወንጌል ዘገባዎች ይህን ሐሳብ አይደግፉም። በዚያ ዘመን አይሁዳውያን ሬሳ ከመቅበራቸው በፊት በቅመማ ቅመምና በሽቱ አሽተው የማዘጋጀት ልማድ ነበራቸው። ለምሳሌ ያህል ኒቆዲሞስ የኢየሱስን አስከሬን ለማዘጋጀት ብዙ መጠን ያለው ቅመም አምጥቶ ነበር። (ዮሐንስ 19:​38-42) ይህ ሁሉ ቅመም ለምን አስፈለገ? ለኢየሱስ የነበረው ልባዊ ፍቅርና አክብሮት እንዲህ ያለ ደግነት እንዲያሳይ ስላነሳሳው ሊሆን ይችላል። ይህ ሁሉ ቅመም የመጣው አስከሬኑን ለማድረቅ ታስቦ ነው ብለን መደምደም አይኖርብንም።

አንድ ክርስቲያን ሬሳ የማድረቅን ልማድ መቃወም ይኖርበታልን? እንደ እውነቱ ከሆነ ሬሳ እንዲደርቅ የሚደረገው መምጣቱ የማይቀረውን ሂደት ለማዘግየት ነው። ከአፈር ተሠርተናል፤ በምንሞትበት ጊዜ ወደ አፈር እንመለሳለን። (ዘፍጥረት 3:​19) ሆኖም አንድ ሰው ከሞተ በኋላ እስኪቀበር ድረስ ምን ያህል ጊዜ ሊቆይ ይችላል? የቤተሰቡ አባላትና ወዳጆች ከሩቅ ቦታ የሚመጡ ከሆነና ሬሳውን ማየት የሚፈልጉ ከሆነ አስከሬኑ በተወሰነ ደረጃ መድረቅ ይኖርበታል።

ስለዚህ በአካባቢው ሬሳ እንዲደርቅ የሚያዝዝ ደንብ ቢኖር ወይም የቤተሰብ አባላት እንዲህ እንዲደረግ የሚፈልጉ ቢሆን ከቅዱስ ጽሑፉ አንጻር ሊያሳስብ የሚገባ ነገር የለም። ‘ሙታን አንዳች አያውቁም።’ (መክብብ 9:​5) በአምላክ መታሰቢያ ውስጥ የሚገኙ ከሆነ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ ከሞት ይነሳሉ።​—⁠ኢዮብ 14:​13-15፤ ሥራ 24:​15፤ 2 ጴጥሮስ 3:​13

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሬሳ የማድረቅ ዘዴ​—⁠ጥንትና ዛሬ

በጥንቷ ግብፅ አስከሬን የሚደርቅበት መንገድ እንደ ቤተሰቡ ደረጃ ይለያያል። አንድ ባለጸጋ ቤተሰብ የሚከተለውን ዓይነት የማድረቂያ ዘዴ ይመርጥ ይሆናል፦

አንጎሉ ከብረት በተሠራ መሣሪያ አማካኝነት በአፍንጫው በኩል እንዲወጣ ይደረጋል። ከዚያም የራስ ቅሉ ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጁ የተለያዩ መድኃኒቶች አማካኝነት በደንብ ይታሻል። ቀጥሎ ከልቡና ከኩላሊቱ በስተቀር የውስጥ ብልቶችን በሙሉ የማውጣቱ ሥራ ይቀጥላል። ሆድ ዕቃውን ለማውጣት እንዲቻል ሆዱን መቅደድ የግድ አስፈላጊ ይሆናል፤ ሆኖም ይህ ድርጊት እንደ ኃጢአት ይታይ ነበር። ግብፃውያን ሬሳ አድራቂዎች ይህን አወዛጋቢ ፈተና ለማለፍ የመቅደዱን ሥራ የሚያከናውን ቆራጭ የሚባል ሰው ያዘጋጃሉ። ይህ ሥራ እርግማንና በድንጋይ መወገርን የሚያስከትል ወንጀል በመሆኑ ሥራውን እንደ ጨረሰ በፍጥነት ሮጦ ያመልጣል።

ሆድ ዕቃው ከወጣ በኋላ ሙልጭ ተደርጎ ይታጠባል። ታሪክ ጸሐፊው ሄሮዶቱስ “ሆድ ዕቃውን ንጹሕ ሆኖ በተፈጨ ከርቤ፣ ብርጉድ እንዲሁም ዕጣንን ሳይጨምር በማንኛውም ዓይነት ቅመማ ቅመም ይሞሉትና መልሰው ይሰፉታል” በማለት ጽፏል።

ቀጥሎ በድን አካሉ በናትሮን ውስጥ ለ70 ቀናት ዘፍዝፎ በማስቀመጥ ውስጡ ያለው ፈሳሽ ተመጥጦ እንዲወጣ ይደረጋል። ከዚያ በኋላ አስከሬኑ ይታጠብና በጥንቃቄ በጨርቅ ይገነዛል። ከዚያም ጨርቁ በሙጫ ወይም እንደ ሙጫ በሚያገለግል አንድ ዓይነት በማጣበቂያ ይቀባል፤ ከዚያ የተገነዘው አስከሬን (mummy) በሰው ቅርጽ በተሠራ ውብ በሆነ የእንጨት ሣጥን ውስጥ ይቀመጣል።

በዛሬው ጊዜ ሬሳ የማድረቅ ሥራ በጥቂት ሰዓት ውስጥ ሊከናወን ይችላል። በአብዛኛው ሬሳ እንዲደርቅ የሚደረገው ትክክለኛ መጠን ያለው የማድረቂያ ፈሳሽ በደም መልስና በደም ቅዳ ቧንቧዎች እንዲሁም በሆድ ዕቃና በደረት ውስጥ በመጨመር ነው። ባለፉት በርካታ ዓመታት የተለያዩ ፈሳሽ መድኃኒቶች ተዘጋጅተው ጥቅም ላይ ውለዋል። ይሁን እንጂ ከዋጋውና ከሚያስከትለው አደጋ አንጻር አብዛኛውን ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውለው ፎርማልዲሃይድ የተባለው የሬሳ ማድረቂያ ፈሳሽ ነው።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የንጉሥ ቱታንክሃመን ከወርቅ የተሠራ የሬሳ ሣጥን