በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ብቃት ያለው አመራር ማግኘት—ዓለም አቀፍ ችግር

ብቃት ያለው አመራር ማግኘት—ዓለም አቀፍ ችግር

ብቃት ያለው አመራር ማግኘት—ዓለም አቀፍ ችግር

ሰውዬው ደራሲና ገጣሚ ነበር። የወደፊቱ ጊዜ ለሁሉም ሰው ጥሩ ነገር እንደሚያመጣ ብሩህ ተስፋ ነበረው። ከ90 ዓመት ገደማ በፊት “አእምሮ ከፍርሃት የሚላቀቅበትንና ሰዎች አንገታቸውን ቀና አድርገው የሚሄዱበትን፣ እውቀት በነፃ የሚገኝበትን፣ ዓለም በብሔራዊ ድንበሮች የማትከፋፈልበትን፣ እውነት የሚነገርበትን [እና] ሰዎች ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ በሚሠሯቸው ነገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ወደ ፍጽምና መቅረብ የሚችሉበትን” ዓለም በዓይነ ህሊናው ተመልክቶ ነበር።

ከዚያም ደራሲው የአገሩም ሆነ የተቀረው የዓለም ሕዝብ አንድ ቀን ይህን በመሰለ ቦታ እንደሚኖሩ ያለውን ተስፋ ገለጸ። የኖቤል ተሸላሚ የሆነው ይህ ገጣሚ ዛሬ በሕይወት ቢኖር ኖሮ ከፍተኛ ሐዘን እንደሚሰማው ምንም አያጠራጥርም። ዓለም ከፍተኛ እድገትና መሻሻል ብታሳይም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተከፋፍላለች። እንዲሁም የሰው ልጅ የወደፊት ተስፋ በአጠቃላይ ጨልሟል።

አንድ ገበሬ በሚኖርበት አገር ውስጥ በተወሰኑ አንጃዎች መካከል በድንገት ግጭት ሊፈጠር የቻለው ለምን እንደሆነ ሲጠየቅ መንስኤ ይሆናል ብሎ ያሰበውን አንድ ምክንያት ጠቅሷል። “ብቃት ያላቸው መሪዎች በመጥፋታቸው ነው” ሲል ተናግሯል። የታሪክ ምሁር የሆኑት ጆናታን ግሎቨር ሂውማኒቲ​—⁠ኤ ሞራል ሂስትሪ ኦቭ ዘ ትዌንቲዝ ሴንቸሪ በተባለው መጽሐፋቸው “[በዚያው አገር] የተካሄደው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሳይታሰብ የፈነዳ የጎሳ ጥላቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሥልጣን ላይ መቆየት የፈለጉ ሰዎች ያቀነባበሩት ሴራ ነው” ሲሉ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።

በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ግዛቶች በነበሩ ሁለት ሪፑብሊኮች መካከል ጦርነት ሲፈነዳ አንዲት ጋዜጠኛ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ለበርካታ ዓመታት አንድ ላይ በደስታ እንዳልኖርን አሁን አንዳችን የሌላውን ልጅ መግደል ጀምረናል። ለመሆኑ እንዲህ የሆንነው ምን ነክቶን ነው?”

መግቢያው ላይ የተጠቀሰው ገጣሚ የትውልድ አገር የሆነችው ህንድ ከአውሮፓና ከአፍሪካ ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቃ ትገኛለች። ደራሲው ፕራናይ ጉብቴ “ህንድ አንድነቷ ሳይናጋ መኖር ትችል ይሆን?” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ንግግር ላይ ‘ወደ 70 በመቶ የሚጠጋው ብዙሃኑ የህንድ ሕዝብ ከ30 ዓመት በታች ያለ ቢሆንም አርአያ የሚሆኑት መሪዎች አላገኘም’ ብለዋል።

በአንዳንድ አገሮች መሪዎች በሙስና በመከሰሳቸው ምክንያት ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ ተገድደዋል። እንግዲያው ዓለም በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ የአመራር ቀውስ እንደደረሰበት በግልጽ ማየት ይቻላል። ከ2, 600 ዓመታት ገደማ በፊት የኖረ አንድ ነቢይ የተናገራቸው ቃላት እውነት መሆናቸውን ሁኔታዎች ይመሰክራሉ። ነቢዩ “የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” ሲል ተናግሯል።​—⁠ኤርምያስ 10:23

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ የሚታየው ችግር መፍትሔ ይኖረዋል? ሰብዓዊ ኅብረተሰብ በግጭት መከፋፈሉ ወደሚያቆምበት እና ከፍርሃት ወደሚላቀቅበት፣ እውነተኛ እውቀት በነፃና እንደ ልብ ወደሚገኝበት እንዲሁም ሰዎች ፍጹም ወደሚሆኑበት ዓለም የሰው ልጆችን ሊያስገባ የሚችለው ማን ነው?

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Fatmir Boshnjaku