በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ብቃት ያለው አመራር ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?

ብቃት ያለው አመራር ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?

ብቃት ያለው አመራር ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ ቤት በአንድ ሰው ተዘጋጅቶአልና፣ ሁሉን ያዘጋጀ ግን እግዚአብሔር ነው” ይላል። (ዕብራውያን 3:4፤ ራእይ 4:11) እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ‘ፍጥረታችንን ያውቃል።’ (መዝሙር 103:​14) ያሉብንን የአቅም ገደቦችና የሚያስፈልጉንን ነገሮች በተመለከተ የተሟላ እውቀት አለው። ደግሞም አፍቃሪ አምላክ ስለሆነ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ማሟላት ይፈልጋል። (መዝሙር 145:​16፤ 1 ዮሐንስ 4:​8) ብቃት ያለው አመራር ለማግኘት ያለን ፍላጎትም ከዚህ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም።

ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል እንዲህ ብሏል፦ “እነሆ፣ ለአሕዛብ ምስክር፣ ለወገኖችም አለቃና [“መሪና፣” የ1980 ትርጉም] አዛዥ እንዲሆን ሰጥቼዋለሁ።” (ኢሳይያስ 55:4) በዛሬው ጊዜ ላለው የአመራር ቀውስ መፍትሔው ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ የተሾመውን የዚህን መሪ ማንነት ማወቅንና የእሱን አመራር መቀበልን ያጠቃልላል። ታዲያ ይህ በትንቢት የተነገረው መሪና አዛዥ ማን ነው? መሪ ለመሆን እንደሚበቃ የሚያሳዩ ምን ማስረጃዎች አሉት? የሚመራን ወዴት ነው? ከእሱ አመራር ለመጠቀም ምን ማድረግ አለብን?

ተስፋ የተሰጠበት መሪ መጣ

ከ2, 500 ዓመታት ገደማ በፊት መልአኩ ገብርኤል ለነቢዩ ዳንኤል ተገልጦለት እንዲህ አለው፦ “ስለዚህ እወቅ አስተውልም፤ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው [“መሪው፣” NW ] እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፤ እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች።”​—⁠ዳንኤል 9:25

በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ይሖዋ የመረጠው መሪ የሚመጣበትን ጊዜ መልአኩ ለዳንኤል ለይቶ አሳውቆታል። ‘መሪው መሢሕ’ ኢየሩሳሌም እንድትጠገን ትእዛዝ ከወጣበት ከ455 ከዘአበ አንስቶ 69 ሳምንታት ወይም 483 ዓመታት ካለፉ በኋላ በዓመታቱ ማብቂያ ላይ ይገለጣል። a (ነህምያ 2:​1-8) ይህ ዘመን ሲያበቃ ምን ተፈጸመ? ወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ እንዲህ ይላል፦ “ጢባርዮስ ቄሣርም በነገሠ በአሥራ አምስተኛይቱ ዓመት፣ ጴንጤናዊው ጲላጦስም በይሁዳ ሲገዛ፣ ሄሮድስም በገሊላ የአራተኛው ክፍል ገዥ ሆነው ሳሉ [29 እዘአ]፣ . . . የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ። . . . ለኃጢአት ስርየት የንስሐን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለችው አገር ሁሉ መጣ።” በዚህ ጊዜ ‘ሕዝቡ [መሪውን መሢሕ] ሲጠብቁ ነበር።’ (ሉቃስ 3:1-3, 15) ብዙዎች ወደ ዮሐንስ ቢመጡም እንኳ ሲጠበቅ የነበረው መሪ እሱ አልነበረም።

ከዚያም በ29 እዘአ ጥቅምት ገደማ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሊጠመቅ ወደ ዮሐንስ መጣ። ዮሐንስ እንዲህ ሲል መስክሯል፦ “መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ። እኔም አላውቀውም ነበር፣ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፦ መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ።” (ዮሐንስ 1:32-34) ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት የተቀባ መሪ ማለትም መሢሕ ወይም ክርስቶስ ሆነ።

አዎን፣ አስቀድሞ ተስፋ የተሰጠበት ‘ለወገኖችም መሪና አዛዥ’ የሚሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ታወቀ። ከዚህም በላይ እንደ መሪ መጠን ያሉትን ባሕርያት ስንመረምር አመራሩ በዚህ ዘመን ከአንድ ብቁ መሪ ከሚጠበቁት ብቃቶች እጅግ የላቀ መሆኑን በቀላሉ መገንዘብ እንችላለን።

መሢሑ​—⁠ብቃት ያለው መሪ

አንድ ብቃት ያለው መሪ በሥሩ ያሉ ሰዎች ችግሮችን ስኬታማ በሆነ መንገድ መፍታት የሚችሉበት የግል ጥንካሬና ችሎታ እንዲኖራቸው ግልጽ መመሪያና እርዳታ ይሰጣቸዋል። ‘ይህ በ21ኛው መቶ ዘመን የሚገኝ ስኬታማ የሆነ መሪ ሊያሟላው የሚገባ አስፈላጊ ብቃት ነው’ ሲል ትዌንቲ ፈርስት ሴንቸሪ ሊደርሺፕ:- ዳያሎግስ ዊዝ 100 ቶፕ ሊደርስ የተባለው መጽሐፍ ገልጿል። ኢየሱስ አድማጮቹ በየዕለቱ የሚያጋጥሟቸውን ሁኔታዎች መወጣት እንዲችሉ በሚገባ አስታጥቋቸዋል! እስቲ እጅግ ዝነኛ የሆነውን ንግግሩን ማለትም የተራራ ስብከቱን ተመልከት። ከማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7 ድረስ የተመዘገቡት ቃላት ተግባራዊ በሆኑ ምክሮች የተሞሉ ናቸው።

ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ አለመግባባቶችን መፍታት የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ የሰጠውን ምክር ተመልከት። “እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፣ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፣ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፣ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፣ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ” ብሏል። (ማቴዎስ 5:23, 24) የሙሴ ሕግ በሚያዝዘው መሠረት በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ መሠዊያ ላይ መባ እንደ ማቅረብ የመሳሰሉ ሃይማኖታዊ ተግባሮችን ከማከናወንም በፊት ቅድሚያውን ወስዶ ከሌሎች ጋር ሰላም መፍጠር ያስፈልግ ነበር። ይህ ካልሆነ ግን የአምልኮ ሥራዎች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አይኖራቸውም። ኢየሱስ የሰጠው ምክር ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ተግባራዊ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ተግባራዊ ነው።

ኢየሱስ አድማጮቹ ከሥነ ምግባር ብልግና ወጥመድ እንዲርቁም ረድቷቸዋል። “አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል” ሲል ጥብቅ ምክር ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 5:27, 28) ምንኛ ተገቢ ማስጠንቀቂያ ነው! ስለ ምንዝር በማውጠንጠን ምንዝር ወደ መፈጸም የሚመራ ጎዳና መከተል ለምን እንጀምራለን? ኢየሱስ ከልብ ምንዝርና ዝሙት እንደሚወጡ ተናግሯል። (ማቴዎስ 15:​18, 19) ልባችንን መጠበቃችን ጥበብ ነው።​—⁠ምሳሌ 4:​23

ከዚህ በተጨማሪ የተራራው ስብከት ጠላትን ስለመውደድ፣ ልግስና ስለማሳየት፣ ለቁሳዊና መንፈሳዊ ነገሮች ሊኖረን ስለሚገባው ተገቢ አመለካከት እና ስለ መሳሰሉት ጉዳዮች በጣም ግሩም ምክር ይዟል። (ማቴዎስ 5:​43-47፤ 6:​1-4, 19-21, 24-34) ኢየሱስ አድማጮቹን ምን ብለው እንደሚጸልዩ በማስተማር የአምላክን እርዳታ እንዴት መጠየቅ እንደሚችሉም ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:​9-13) መሪው መሢሕ ተከታዮቹ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሱትን ችግሮች መወጣት እንዲችሉ ያበረታቸዋል እንዲሁም ያዘጋጃቸዋል።

ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ስድስት ጊዜ ያህል ንግግሩን “እንደ ተባለ ሰምታችኋል” በሚሉት ቃላት ካስተዋወቀ በኋላ “እኔ ግን እላችኋለሁ” በማለት ከዚያ የተለየ ሐሳብ አቅርቧል። (ማቴዎስ 5:​21, 22, 27, 28, 31-34, 38, 39, 43, 44) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው አድማጮቹ በቃል በሚነገረው የፈሪሳውያን ወግ መሠረት በሆነ መንገድ የመመላለስ ልማድ ነበራቸው። አሁን ግን ኢየሱስ የተለየ መንገድ ያሳያቸው ሲሆን ይህም የሙሴን ሕግ ትክክለኛ መንፈስ ያንጸባርቃል። በመሆኑም ኢየሱስ ለውጥ እያስተዋወቀ የነበረ ከመሆኑም በላይ ይህንም ያደረገው ተከታዮቹ ለመቀበል በሚቀልላቸው መንገድ ነው። አዎን፣ ኢየሱስ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ በመንፈሳዊም ሆነ በሥነ ምግባራዊ ሁኔታ አስገራሚ ለውጦች እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል። ይህ የአንድ ብቃት ያለው መሪ ምልክት ነው።

አንድ የአስተዳደር መማሪያ መጽሐፍ እንዲህ ዓይነት ለውጥ ማምጣት ምን ያህል አዳጋች መሆኑን ጠቅሷል። መጽሐፉ እንዲህ ይላል፦ “የለውጡ አራማጅ [መሪ] የማኅበራዊ ሠራተኛ አሳቢነት፣ የሥነ ልቦና ጠበብት ማስተዋል፣ የማራቶን ሯጭ ብርታት፣ የውሻ ጽናት፣ የባሕታዊ በራስ የመተማመን መንፈስና የቅዱሳን ትዕግሥት ሊኖረው ይገባል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ ባሕርያት ኖረውትም እንኳ ለስኬታማነቱ ምንም ዋስትና የለም።”

“ሊደርሺፕ፦ ዱ ትሬይትስ ማተር?” በሚል ርዕስ የወጣ አንድ ጽሑፍ “መሪዎች ከተከታዮቻቸው ማየት የሚፈልጉትን ባሕርይ እነሱ ራሳቸው ማሳየት አለባቸው” ብሏል። በእርግጥም አንድ ብቃት ያለው መሪ የሚናገረውን በተግባር ያውላል። ይህ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በሚገባ ታይቷል! አዎን፣ ተከታዮቹን ትሕትና እንዲያሳዩ ማስተማር ብቻ ሳይሆን እግራቸውን በማጠብ ተግባራዊ ምሳሌም ትቶላቸዋል። (ዮሐንስ 13:​5-15) የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንዲሰብኩ ደቀ መዛሙርቱን መላክ ብቻ ሳይሆን ራሱም በዚህ ሥራ ላይ በሙሉ ኃይሉ ተካፍሏል። (ማቴዎስ 4:​18-25፤ ሉቃስ 8:​1-3፤ 9:​1-6፤ 10:​1-24፤ ዮሐንስ 10:​40-42) ከዚህም ሌላ ኢየሱስ ለአመራር ምላሽ በመስጠት ረገድ ምሳሌ ትቷል። “አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም” በማለት ስለራሱ ተናግሯል።​—⁠ዮሐንስ 5:​19

ከላይ የተመለከትነው ኢየሱስ የተናገረውና ያደረገው ነገር ብቃት ያለው መሪ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። እንዲያውም ኢየሱስ ፍጹም ስለሆነ ጥሩ አመራርን በተመለከተ ሰዎች ካወጧቸው መሥፈርቶች ሁሉ የላቀ ደረጃ አለው። ሞቶ ከተነሳ በኋላ የማይጠፋ ሕይወት ስላገኘ ለዘላለም ይኖራል። (1 ጴጥሮስ 3:​18፤ ራእይ 1:​13-18) እነዚህን ብቃቶች ሊያሟላ የሚችል የትኛው ሰብዓዊ መሪ ነው?

ምን ማድረግ አለብን?

መሪው መሢሕ በሥልጣን ላይ ያለ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች በረከቶች ያዘንብላቸዋል። ይህን በተመለከተ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚከተለውን ተስፋ ይሰጣሉ፦ “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች።” (ኢሳይያስ 11:9) “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” (መዝሙር 37:11) “ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።” (ሚክያስ 4:4) “እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።”​—⁠ራእይ 21:3, 4

በዛሬው ጊዜ ዓለም የአመራር ቀውስ ደርሶበታል። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ገር የሆኑ ሰዎችን ሰላም ወደሰፈነበት አዲስ ዓለም እየመራቸው ነው። በዚያ ታዛዥ የሰው ልጆች በይሖዋ አምልኮ አንድ ይሆናሉ እንዲሁም ወደ ፍጽምና እየቀረቡ ይሄዳሉ። ጊዜ ወስደን ስለ እውነተኛው አምላክና እሱ ስለ ሾመው መሪ ለማወቅ መጣራችንና ከቀሰምነው እውቀት ጋር ተስማምተን መኖራችን እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው!​—⁠ዮሐንስ 17:​3

ለአንድ ሰው ያለንን አድናቆት መግለጽ ከምንችልባቸው ከሁሉ የተሻሉ መንገዶች አንዱ እሱን መምሰል ነው። ታዲያ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተነሳውን ከሁሉ የላቀውን መሪ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስን ለመ​ምሰል መጣር አይገባንም? ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የእሱን አመራር መቀበል በሕይወታችን ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? እነዚህና ሌሎች ጥያቄዎች ቀጥሎ ባሉት ሁለት ርዕሶች ላይ ይብራራሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳንኤል አምላክ የመረጠው መሪ የሚመጣበትን ጊዜ ተንብዮአል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢየሱስ ትምህርቶች ሰዎች በሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መወጣት እንዲችሉ አስታጥቀዋቸዋል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ታዛዥ የሰው ልጆችን ሰላም ወደ ሰፈነበት አዲስ ዓለም ይመራቸዋል