በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቶስ ጉባኤውን ይመራል

ክርስቶስ ጉባኤውን ይመራል

ክርስቶስ ጉባኤውን ይመራል

“እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”—⁠ማቴዎስ 28:19, 20

1, 2. (ሀ) ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲያፈሩ ለተከታዮቹ ትእዛዝ በሰጠ ጊዜ ምን ቃል ገባላቸው? (ለ) ኢየሱስ የጥንት ክርስቲያን ጉባኤን በሚገባ የመራው እንዴት ነው?

 ከሞት የተነሳው መሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ ተገለጠና እንዲህ አላቸው:- “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”​—⁠ማቴዎስ 23:10 NW፤ 28:18-20

2 ኢየሱስ ተከታዮቹ ተጨማሪ ደቀ መዛሙርት በማፍራት ሕይወት አድን በሆነው ሥራ እንዲካፈሉ ኃላፊነት መስጠት ብቻ ሳይሆን ከእነርሱ ጋር እንደሚሆንም ቃል ገብቶላቸዋል። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው የጥንት ክርስቲያኖች ታሪክ ኢየሱስ ከአምላክ ያገኘውን ሥልጣን በመጠቀም በወቅቱ አዲስ የነበረውን ጉባኤ እንደመራ የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ይሰጣል። ተከታዮቹን ለማጠንከርና ትጋት የተሞላበት ሥራቸውን ለመምራት ቃል የገባላቸውን “ረዳት” ማለትም መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል። (ዮሐንስ 16:7 NW፤ ሥራ 2:4, 33፤ 13:2-4፤ 16:6-10) ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለመደገፍ በሥሩ የሚገኙትን መላእክት ተጠቅሟል። (ሥራ 5:19፤ 8:26፤ 10:3-8, 22፤ 12:7-11፤ 27:23, 24፤ 1 ጴጥሮስ 3:22) ከዚህም በላይ መሪያችን ብቃት ያላቸው ወንዶች የአስተዳደር አካል ሆነው እንዲያገለግሉ በማደራጀት ለጉባኤው አመራር ሰጥቷል።​—⁠ሥራ 1:20, 24-26፤ 6:1-6፤ 8:5, 14-17

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹ ጥያቄዎች ይብራራሉ?

3 እኛ ስለምንኖርበት ስለዚህ ‘ዓለም ፍጻሜስ’ ምን ለማለት ይቻላል? ኢየሱስ ክርስቶስ በጊዜያችን የክርስቲያን ጉባኤን እየመራ ያለው እንዴት ነው? ይህን አመራር እንደተቀበልን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

ጌታው ታማኝ ባሪያ አለው

4. (ሀ) “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆነው የሚሠሩት እነማን ናቸው? (ለ) ጌታው ለባሪያው ምን ኃላፊነት ሰጠው?

4 ኢየሱስ በሥልጣን ላይ መገኘቱን የሚጠቁመውን ምልክት አስመልክቶ ትንቢት በተናገረ ጊዜ እንዲህ አለ:- “እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፣ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል።” (ማቴዎስ 24:45-47) እዚህ ላይ የተጠቀሰው ‘ጌታ’ መሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን እርሱም “ታማኝና ልባም ባሪያ” ተብሎ የሚታወቀውን ምድር ላይ የሚገኙትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ያቀፈውን ቡድን ምድር ባለው ንብረቶቹ ሁሉ ላይ ሾሞታል።

5, 6. (ሀ) ሐዋርያው ዮሐንስ በተቀበለው ራእይ ውስጥ ‘ሰባቱ የወርቅ መቅረዞች’ እና ‘ሰባቱ ከዋክብት’ ምን ያመለክታሉ? (ለ) ‘ሰባቱ ከዋክብት’ በኢየሱስ ቀኝ እጅ ውስጥ መሆናቸው ምን ያመለክታል?

5 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ ታማኝና ልባም ባሪያ በቀጥታ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን ሥር እንደሆነ ይናገራል። ሐዋርያው ዮሐንስ ‘የጌታን ቀን’ በማስመልከት በተመለከተው ራእይ ውስጥ ‘ሰባት የወርቅ መቅረዞች እና በመቅረዞቹም መካከል በቀኝ እጁ ሰባት ከዋክብት የያዘ የሰው ልጅ የሚመስል’ ተመልክቷል። ኢየሱስ ራእዩን ለዮሐንስ ሲገልጽለት እንዲህ አለ:- “በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብትና የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ምሥጢር ይህ ነው፤ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መላእክት ናቸው፣ ሰባቱም መቅረዞች ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።”​—⁠ራእይ 1:1, 10-20

6 ‘ሰባቱ የወርቅ መቅረዞች’ በ1914 በጀመረው ‘የጌታ ቀን’ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም የእውነተኛ ክርስቲያን ጉባኤዎች ያመለክታሉ። ሆኖም ‘ሰባቱ ከዋክብት’ ምንድን ናቸው? በመጀመሪያ ደረጃ የሚያመለክቱት በአንደኛው መቶ ዘመን ለነበሩት ጉባኤዎች እንክብካቤ ያደርጉ የነበሩትን በመንፈስ የተወለዱትን ቅቡዓን የበላይ ተመልካቾች በሙሉ ነው። a የበላይ ተመልካቾቹ በኢየሱስ ቀኝ እጅ ውስጥ ማለትም በእርሱ ቁጥጥርና አመራር ሥር ነበሩ። አዎን፣ ክርስቶስ ኢየሱስ ከሰዎች የተውጣጣውን የባሪያ ክፍል መርቷል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ የቅቡዓን የበላይ ተመልካቾች ቁጥር በጣም ጥቂት ነው። ታዲያ የክርስቶስ አመራር በዓለም ዙሪያ ለሚገኙት ከ93, 000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በሙሉ የሚዳረሰው እንዴት ነው?

7. (ሀ) ኢየሱስ በመላው ምድር የሚገኙ ጉባኤዎችን ለመምራት የአስተዳደር አካሉን የሚጠቀመው እንዴት ነው? (ለ) ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ናቸው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

7 እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ በአሁኑም ጊዜ ከቅቡዓን የበላይ ተመልካቾች መካከል የተውጣጣ መላውን ታማኝና ልባም ባሪያ የሚወክል ብቃት ያላቸውን ወንዶች ያቀፈ አንድ አነስተኛ ቡድን የአስተዳደር አካል ሆኖ ያገለግላል። መሪያችን ይህን የአስተዳደር አካል በመጠቀም በመንፈስ ከተቀቡትም ሆነ ካልተቀቡት መካከል በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆነው እንዲያገለግሉ ብቃት ያላቸው ወንዶችን ይሾማል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ እንዲጠቀምበት ይሖዋ የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። (ሥራ 2:32, 33) በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ የበላይ ተመልካቾች በመንፈስ ቅዱስ አነሣሽነት በተጻፈው በአምላክ ቃል ውስጥ የሰፈሩትን ብቃቶች ማሟላት ይገባቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-7፤ ቲቶ 1:5-9፤ 2 ጴጥሮስ 1:20, 21) የድጋፍ ሐሳብ የሚቀርበው እንዲሁም ሹመቱ የሚጸድቀው ጸሎት ከተደረገ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ነው። በተጨማሪም የሚሾሙት ግለሰቦች የዚህን መንፈስ ፍሬ እንዳፈሩ በግልጽ ያሳያሉ። (ገላትያ 5:22, 23) እንግዲያው ጳውሎስ “ለራሳችሁና እግዚአብሔር ጠባቂ አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ” በማለት የሰጠው ምክር ለሁሉም ሽማግሌዎች፣ ለተቀቡትም ሆነ ላልተቀቡት በእኩል ደረጃ ይሠራል። (ሥራ 20:28 አ.መ.ት ) እነዚህ የተሾሙ ወንዶች ከአስተዳደር አካሉ መመሪያ ይቀበላሉ እንዲሁም በፈቃደኝነት ጉባኤውን ይጠብቃሉ። በዚህ መንገድ ክርስቶስ ከእኛ ጋር በመሆን ጉባኤውን በሚገባ ይመራል።

8. ኢየሱስ ተከታዮቹን ለመምራት መላእክትን የሚጠቀመው እንዴት ነው?

8 ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ያሉትን ተከታዮቹን ለመምራት መላእክትንም ጭምር ይጠቀማል። ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ በሚናገረው ምሳሌ መሠረት የመከሩ ሥራ የሚከናወነው ‘በዓለም መጨረሻ’ ነው። ጌታው የመከሩን ሥራ የሚያሠራው በእነማን ነው? “አጫጆችም መላእክት ናቸው” በማለት ክርስቶስ ተናግሯል። ጨምሮም እንዲህ አለ:- “የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፣ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ።” (ማቴዎስ 13:37-41) ከዚህም በላይ ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ እንዲያገኘው አንድ መልአክ እንደ መራው ሁሉ በዛሬውም ጊዜ ክርስቶስ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች በማገናኘት ረገድ የእውነተኛ ክርስቲያኖችን ሥራ ለመምራት መላእክቱን እንደሚጠቀም የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች አሉ።​—⁠ሥራ 8:26, 27፤ ራእይ 14:6

9. (ሀ) ክርስቶስ በዛሬው ጊዜ ያለውን የክርስቲያን ጉባኤ በምን አማካኝነት ይመራል? (ለ) ከክርስቶስ አመራር ጥቅም ማግኘት ከፈለግን የትኛውን ጥያቄ መመርመር ይኖርብናል?

9 ኢየሱስ ክርስቶስ በአስተዳደር አካል፣ በመንፈስ ቅዱስና በመላእክት አማካኝነት በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ደቀ መዛሙርቱ አመራር እንደሚሰጥ ማወቁ ምንኛ መንፈስን የሚያረጋጋ ነው! አንዳንድ የይሖዋ አምላኪዎች በስደት ወይም በሌላ ምክንያት ከአስተዳደር አካሉ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ለጊዜውም ቢሆን ቢቋረጥ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስና መላእክት በሚሰጡት ድጋፍ አማካኝነት አመራር መስጠቱን ይቀጥላል። ይሁን እንጂ ከእርሱ አመራር ጥቅም ማግኘት የምንችለው አመራሩን ስንቀበል ብቻ ነው። የክርስቶስን አመራር እንደተቀበልን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

“ታዘዙና ተገዙ”

10. በጉባኤ ውስጥ ለተሾሙት ሽማግሌዎች አክብሮት እንዳለን ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው?

10 መሪያችን አንዳንዶች “ወንጌልን ሰባኪዎች፣ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ” ለጉባኤው “ወንዶችን ስጦታ አድርጎ” [NW ] ሰጥቷል። (ኤፌሶን 4:8, 11, 12) ለእነርሱ ያለን አመለካከትና ድርጊታችን የክርስቶስን አመራር የተቀበልን መሆን አለመሆናችንን በግልጽ ያሳያል። ክርስቶስ ለሰጠን መንፈሳዊ ብቃት ላላቸው ወንዶች ‘አመስጋኝነታችንን’ ማሳየታችን የተገባ ነው። (ቆላስይስ 3:15) ልናከብራቸውም ይገባናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በመልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች . . . እጥፍ ክብር ይገባቸዋል” በማለት ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 5:17) በጉባኤ ውስጥ ላሉት ሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾች አመስጋኞች እንደሆንንና አክብሮት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ “ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ” በማለት መልሱን ይሰጣል። (ዕብራውያን 13:17) አዎን፣ ልንታዘዛቸውና ልንገዛላቸው ይገባናል።

11. ሽማግሌዎች እንዲኖሩ ለተደረገው ዝግጅት አክብሮት ማሳየት ስንጠመቅ ከገባነው ቃል ጋር ተስማምቶ የመኖር ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው?

11 መሪያችን ፍጹም ነው። ስጦታ አድርጎ የሰጠን ሰዎች ግን ፍጹማን አይደሉም። ስለዚህ አልፎ አልፎ ስህተት ሊሠሩ ይችላሉ። ሆኖም ክርስቶስ ላደረገው ዝግጅት ምንጊዜም ታማኝ ሆነን መገኘታችን አስፈላጊ ነው። እንዲያውም ራሳችንን ለአምላክ ወስነን ስንጠመቅ ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን እንኖራለን ስንል በጉባኤ ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ ሹመት አማካኝነት የሚገኝ ሥልጣን እንዳለ አምነን እንቀበላለን እንዲሁም ለዚህ ሥልጣን በፈቃደኝነት እንገዛለን ማለታችን ነው። “በመንፈስ ቅዱስ ስም” መጠመቃችን መንፈስ ቅዱስ ምን እንደሆነ እንደተገነዘብንና በይሖዋ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና አምነን እንደተቀበልን በሕዝብ ፊት ማሳወቃችን ነው። (ማቴዎስ 28:19) ይህ ዓይነቱ ጥምቀት ከመንፈሱ ጋር እንደምንተባበርና በክርስቶስ ተከታዮች ላይ እንዳይሠራ የሚያግድ ምንም ነገር እንደማናደርግ ያሳያል። ሽማግሌዎች የድጋፍ ሐሳብ ሲቀርብላቸውም ሆነ ሲሾሙ መንፈስ ቅዱስ ወሳኝ ሚና የሚጫወት እንደመሆኑ በጉባኤ ውስጥ ካለው የሽማግሌዎች ዝግጅት ጋር ሳንተባበር ብንቀር ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን የገባነውን ቃል በታማኝነት እየጠበቅን ነው ብለን ልንናገር እንችላለን?

12. ለሥልጣን አክብሮት አለማሳየትን በሚመለከት ይሁዳ ምን ምሳሌ ጠቅሶ ተናገረ? ከእነዚህስ ምን እንማራለን?

12 ቅዱሳን ጽሑፎች ታዛዥና ተገዥ መሆን ጥቅም እንደሚያስገኝ የሚያስተምሩ ምሳሌዎች ይዘዋል። በጉባኤ ውስጥ በተሾሙ ወንዶች ላይ የስድብ ቃል የተናገሩ ሰዎችን በማስመልከት ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ ሦስት የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎችን በመጥቀስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ወዮላቸው፣ በቃየል መንገድ ሄደዋልና ስለ ደመወዝም ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል።” (ይሁዳ 11) ቃየን የይሖዋን ፍቅራዊ ምክር ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ ሆነ ብሎ ሕይወት ወደ ማጥፋት የመራውን የጥላቻ መንገድ ተከትሏል። (ዘፍጥረት 4:4-8) በለዓም በተደጋጋሚ መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ሲል የአምላክን ሕዝብ ለመርገም ጥረት አድርጓል። (ዘኁልቊ 22:5-28, 32-34፤ ዘዳግም 23:5) ቆሬ በእስራኤል መካከል የተከበረ መብት ነበረው፤ ሆኖም በዚያ አልረካም። በምድር ላይ ካሉት ሁሉ እጅግ ትሑት በነበረው በአምላክ አገልጋይ በሙሴ ላይ ዓመፅ አስነሳ። (ዘኁልቊ 12:3፤ 16:1-3, 32, 33) ቃየን፣ በለዓምና ቆሬ ጥፋት ደርሶባቸዋል። እነዚህ ምሳሌዎች ይሖዋ በኃላፊነት ቦታ ያስቀመጣቸው ሰዎች የሚሰጡትን ምክር የመስማትንና እነርሱን የማክበርን አስፈላጊነት በግልጽ ያስተምሩናል!

13. ሽማግሌዎች እንዲኖሩ ለተደረገው ዝግጅት ራሳቸውን የሚያስገዙ ሰዎች የሚያገኙትን በረከት በተመለከተ ነቢዩ ኢሳይያስ ምን ትንቢት ተናግሯል?

13 መሪያችን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ካቋቋመው የበላይ ተመልካቾች ዝግጅት ጥቅም ማግኘት የማይፈልግ ማን አለ? ነቢዩ ኢሳይያስ ይህ ዝግጅት የሚያስገኘውን በረከት እንዲህ በማለት ገልጿል:- “እነሆ፣ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል፣ መሳፍንትም በፍርድ ይገዛሉ። ሰውም ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሀም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ ይሆናል።” (ኢሳይያስ 32:1, 2) እያንዳንዱ ሽማግሌ ጥበቃና ደህንነት የሚገኝበት እንዲህ ያለ “መጠጊያ” ሆኖ መገኘት ይጠበቅበታል። ለሥልጣን መገዛት አስቸጋሪ ቢሆንብን እንኳ አምላክ በጉባኤ ውስጥ ላቋቋመው ሥልጣን የምንታዘዝና የምንገዛ እንድንሆን በመጸለይ ያልተቋረጠ ጥረት እናድርግ።

ሽማግሌዎች ለክርስቶስ አመራር የሚገዙት እንዴት ነው?

14, 15. በጉባኤ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው የሚመሩ ወንዶች ለክርስቶስ አመራር የሚገዙ መሆናቸውን የሚያሳዩት እንዴት ነው?

14 ሁሉም ክርስቲያኖች በተለይ ደግሞ ሽማግሌዎች የክርስቶስን አመራር መከተል ይገባቸዋል። የበላይ ተመልካቾች ወይም ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ በተወሰነ መጠን ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። ይሁን እንጂ ‘የእምነት ባልደረቦቻቸውን’ ሕይወት ለመቆጣጠር በመሞከር ‘በእምነታቸው ላይ መሠልጠን’ አይፈልጉም። (2 ቆሮንቶስ 1:24 NW ) ሽማግሌዎች “የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። በእናንተስ እንዲህ አይደለም” በማለት ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት ይከተላሉ። (ማቴዎስ 20:25-27) ሽማግሌዎች ኃላፊነቶቻቸውን በሚወጡበት ጊዜ ሌሎችን ለማገልገል ከልባቸው ይጥራሉ።

15 ክርስቲያኖች “ዋኖቻችሁን [“ግንባር ቀደም ሆነው የሚመሯችሁን፣” NW ] አስቡ፣ የኑሮአቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው” የሚል ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። (ዕብራውያን 13:7) ክርስቲያኖች እንዲህ የሚያደርጉት ሽማግሌዎች መሪዎች ስለሆኑ አይደለም። ኢየሱስ “ሊቃችሁ [“መሪያችሁ፣” NW ] አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 23:10) ሽማግሌዎች እውነተኛውን መሪያችንን ክርስቶስን የሚመስሉ በመሆናቸው ክርስቲያኖች እንደ ምሳሌ አድርገው የሚከተሉት የእነርሱን እምነት ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:1) ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ካሉት ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ረገድ የክርስቶስ ዓይነት ባሕርይ ለማሳየት ጥረት የሚያደርጉባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመልከት።

16. ኢየሱስ ከፍተኛ ሥልጣን የተሰጠው ቢሆንም ተከታዮቹን የያዘው እንዴት ነው?

16 ኢየሱስ በማንኛውም ዘርፍ ፍጹማን ካልሆኑት የሰው ልጆች የሚበልጥና ተወዳዳሪ የሌለው ሥልጣን ከአባቱ ያገኘ ቢሆንም እንኳ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በነበረው ግንኙነት ረገድ ትሑት ነበር። እውቀቱ እንዲታይለት በማድረግ አድማጮቹን ለማስደነቅ አልሞከረም። ኢየሱስ ሰብዓዊ ፍላጎቶቻቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ለተከታዮቹ ኃዘኔታንና ርኅራኄን አሳይቷቸዋል። (ማቴዎስ 15:32፤ 26:40, 41፤ ማርቆስ 6:31) ደቀ መዛሙርቱን ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር ጠብቆባቸው አያውቅም፤ ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይም አልጫነባቸውም። (ዮሐንስ 16:12) ኢየሱስ ‘የዋህና ትሑት’ ነበር። ብዙዎች እረፍት የሚሰጥ ሆኖ ማግኘታቸው ምንም አያስደንቅም።​—⁠ማቴዎስ 11:28-30

17. ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ካሉት ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ረገድ የክርስቶስ ዓይነት ትሕትና ማንጸባረቅ ያለባቸው እንዴት ነው?

17 መሪ የሆነው ክርስቶስ የትሕትና ባሕርይ ካሳየ በጉባኤ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው የሚመሩን ደግሞ ይህን ባሕርይ የበለጠ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል! አዎን፣ የተሰጣቸውን ማንኛውም ዓይነት ሥልጣን ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንዳይጠቀሙበት ይጠነቀቃሉ። እንዲሁም በሌሎች ፊት አድናቆትን ለማትረፍ በማሰብ ‘በረቀቀ የንግግር ችሎታ አይመጡም።’ (1 ቆሮንቶስ 2:1, 2 አ.መ.ት ) ከዚያ ይልቅ የቅዱሳን ጽሑፎችን እውነት ሊገባ በሚችል ቀላል አነጋገርና በቅንነት ለመናገር ይጣጣራሉ። ከዚህም በተጨማሪ ሽማግሌዎች ከሌሎች በሚጠብቁት ነገር ረገድ ምክንያታዊ ለመሆንና ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች አሳቢ ለመሆን ይጥራሉ። (ፊልጵስዩስ 4:5 NW ) ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ የአቅም ገደብ እንዳለበት በመገንዘብ ከወንድሞቻቸው ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ይህን ግምት ውስጥ ያስገባሉ። (1 ጴጥሮስ 4:8) ትሑትና የዋህ የሆኑ ሽማግሌዎች በእርግጥም እረፍት የሚሰጡ አይደሉም? በእርግጥም ናቸው።

18. ኢየሱስ ልጆችን ከያዘበት መንገድ ሽማግሌዎች ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ?

18 ኢየሱስ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ሰዎች እንኳ ሳይቀር በቀላሉ ሊቀርቡት የሚችሉት ዓይነት ሰው ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ‘ሕፃናትን ወደ እርሱ ያመጡትን’ ሰዎች በገሠጿቸው ጊዜ ምን ብሎ እንደተናገረ ተመልከት። “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው” በማለት ተናግሯል። ከዚያም ልጆቹን “አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው።” (ማርቆስ 10:13-16) ኢየሱስ ሞቅ ያለ መንፈስ ያለውና ደግ ነበር። ሰዎች ኢየሱስን ከመፍራት ይልቅ በቀላሉ ወደ እርሱ ይሳቡ ነበር። ልጆች እንኳን ሳይቀሩ አጠገቡ ሲሆኑ ደስ ይላቸው ነበር። ሽማግሌዎችም በቀላሉ የሚቀረቡ ናቸው። እንዲሁም ሞቅ ያለ የመውደድ ስሜትና ደግነት በሚያሳዩበት ጊዜ ልጆችን ጨምሮ ሌሎች ከእነርሱ ጋር መሆን ያስደስታቸዋል።

19. ‘የክርስቶስን አሳብ’ መያዝ ማለት ምን ማለት ነው? ይህስ ምን ዓይነት ጥረት ማድረግን ይጠይቃል?

19 ሽማግሌዎች ክርስቶስ ኢየሱስን ይበልጥ ባወቁት መጠን የዚያኑ ያህል እርሱን ሊመስሉት ይችላሉ። ጳውሎስ “እንዲያስተምረው የጌታን [“የይሖዋን፣” NW ] ልብ ማን አውቆት ነው?” በማለት ጠይቋል። ከዚያም “እኛ ግን የክርስቶስ ልብ [“አሳብ፣” NW ] አለን” በማለት ጨምሮ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 2:16) የክርስቶስ ዓይነት አሳብ መያዝ ማለት አንድ ለየት ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመው ምን እንደሚያደርግ ማወቅ እንችል ዘንድ የእርሱን አስተሳሰብ መኮረጅና የባሕርዩን አጠቃ​ላይ ገጽታ መገንዘብ ማለት ነው። ስለ መሪያችን ይህን ያህል የተሟላ እውቀት ማግኘት ምን ማለት ሊሆን እንደሚችል ለአንድ አፍታ አስብ! አዎን፣ ይህ ለወንጌል ዘገባዎች ትኩረት መስጠትንና አእምሯችንን ስለ ኢየሱስ ሕይወትና ምሳሌ በሚናገር እውቀት አዘውትሮ መሙላትን ይጠይቃል። ሽማግሌዎች የክርስቶስን አመራር ለመከተል ይህን ያህል ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ያሉት እምነታቸውን ለመምሰል ይበልጥ ቀላል ይሆንላቸዋል። ሽማግሌዎቹም ሌሎች የመሪያችንን አርአያ በደስታ ሲከተሉ ማየት እርካታ ይሰጣቸዋል።

ለክርስቶስ አመራር መገዛታችሁን ቀጥሉ

20, 21. ቃል የተገባውን አዲስ ዓለም አሻግረን ስንመለከት ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል?

20 ሁላችንም ለክርስቶስ አመራር መገዛታችንን መቀጠላችን በጣም አስፈላጊ ነው። ወደዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ይበልጥ እየተቃረብን በሄድን መጠን ያለንበት ሁኔታ በ1473 ከዘአበ በሞዓብ ሜዳ ሰፍረው ከነበሩት እስራኤላውያን ጋር ሊወዳደር ይችላል። እስራኤላውያን የተስፋይቱ ምድር ደፍ ላይ ነበሩ። እንዲሁም አምላክ በነቢዩ ሙሴ አማካኝነት “አንተ [ኢያሱ] ከዚህ ሕዝብ ጋር እግዚአብሔር ለአባቶቻቸው እንዲሰጥ ወደ ማለላቸው ምድር ትገባለህ” በማለት ተናገረ። (ዘዳግም 31:7, 8) ኢያሱ መሪ ሆኖ ተሹሞ ነበር። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር መግባት ከፈለጉ ለኢያሱ አመራር መገዛት ነበረባቸው።

21 መጽሐፍ ቅዱስ “ሊቃችሁ [“መሪያችሁ፣” NW ] አንድ እርሱም ክርስቶስ ነው” በማለት ይነግረናል። ቃል ወደተገባው ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም መርቶ የሚያስገባን ክርስቶስ ብቻ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:13) ስለዚህ በሁሉም የኑሯችን ዘርፍ ለእርሱ አመራር ለመገዛት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a እዚህ ላይ የተጠቀሱት “ከዋክብት” ቃል በቃል መላእክትን አያመለክቱም። ኢየሱስ አንድን ሰብዓዊ ሰው በመጠቀም በዓይን ለማይታዩ መንፈሳዊ ፍጥረታት መልእክት እንደማያጽፍ የተረጋገጠ ነው። ስለዚህ ‘ከዋክብቱ’ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን የኢየሱስ መልእክተኛ እንደሆኑ ተደርገው የተቆጠሩትን ሰብዓዊ የበላይ ተመልካቾችን ወይም ሽማግሌዎችን የሚያመለክቱ መሆን አለባቸው። ቁጥራቸው ሰባት መሆኑ በአምላክ የተወሰነ ሙላትን ያመለክታል።

ታስታውሳለህ?

• ክርስቶስ የጥንቱን ጉባኤ የመራው እንዴት ነው?

• ክርስቶስ በዛሬው ጊዜ ጉባኤውን የሚመራው እንዴት ነው?

• በጉባኤ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው ለሚመሩን መገዛት ያለብን ለምንድን ነው?

• ሽማግሌዎች ክርስቶስ መሪያቸው እንደሆነ በምን መንገዶች ሊያሳዩ ይችላሉ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቶስ ጉባኤውን የሚመራ ከመሆኑም በላይ የበላይ ተመልካቾችን በቀኝ እጁ ይዟል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ግንባር ቀደም ሆነው ለሚመሯችሁ ታዘዙና ተገዙ”

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ሞቅ ያለ መንፈስ ያለውና በቀላሉ የሚቀረብ ነበር። ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንደ እርሱ ለመሆን ይጥራሉ