በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዎልደንሳውያን—ከመናፍቅነት ወደ ፕሮቴስታንትነት

ዎልደንሳውያን—ከመናፍቅነት ወደ ፕሮቴስታንትነት

ዎልደንሳውያን—ከመናፍቅነት ወደ ፕሮቴስታንትነት

ዓመቱ 1545 ሲሆን ቦታው በደቡባዊ ፈረንሳይ የምትገኘውና የፕሮቮንስ ግዛት የሆነችው ውቧ ሉበሮ ናት። አንድ የጦር ሠራዊት በሃይማኖታዊ አክራሪነት መንፈስ የተቆሰቆሰውን አሰቃቂ የጥፋት ተልዕኮ ለማስፈጸም ተሰባስቧል። አንድ ሳምንት የፈጀ ደም መፋሰስ ተከሰተ።

መንደሮች የወደሙ ሲሆን ነዋሪዎቹም ለእስር አሊያም ለሞት ተዳርገዋል። አውሮፓን ከዳር እስከ ዳር ባናወጠው በዚህ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ወቅት ደም የጠማቸው ወታደሮች አሰቃቂና ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጊቶች ፈጽመዋል። በሴቶችና በሕፃናት ላይ የደረሰውን ይህ ነው የማይባል መከራና ስቃይ ሳይጨምር ወደ 2, 700 የሚጠጉ ወንዶች የተገደሉ ሲሆን 600 የሚያክሉት ደግሞ የጀልባ ቀዛፊዎች እንዲሆኑ ተደርገዋል። የፈረንሳዩ ንጉሥና የካቶሊኩ ሊቀ ጳጳስ ይህንን በዓይነቱ ልዩ የሆነ አሰቃቂ ዘመቻ የመራውን የጦር አዛዥ አሞግሰውታል።

የፕሮቴስታንት እምነት መስፋፋት ያሳሰበው የፈረንሳዩ ንጉሥ ፍራንሲስ አንደኛ በግዛቱ ውስጥ ስለሚገኙት መናፍቃን ማጣራት ሲጀምር ተሃድሶው ጀርመንን ለሁለት ከፍሏት ነበር። የፕሮቮንስ ባለሥልጣናት ምርመራ ሲያካሂዱ በጥቂት ግለሰብ መናፍቃን ፋንታ ጠቅላላው የመንደሩ ነዋሪ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚ ሆኖ አገኙት። እነዚህን መናፍቃን ለማጥፋት የወጣው አዋጅ የ1545ቱን የጅምላ ጭፍጨፋ አስከትሏል።

እነዚህ መናፍቃን እነማን ነበሩ? የሃይማኖታዊ አክራሪዎች ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ዒላማ የሆኑትስ ለምንድን ነው?

ከባለጠግነት ወደ ድህነት

በጅምላ ጭፍጨፋው የተገደሉት ሰዎች በ12ኛው መቶ ዘመን ወደ ሕልውና የመጣ የአንድ ሃይማኖታዊ ንቅናቄ አባላት ሲሆኑ ይህ ንቅናቄ በአብዛኛው የአውሮፓ ክፍል ተስፋፍቶ ነበር። የንቅናቄው መስፋፋትና ለብዙ ዓመታት በሕልውና መቆየት በሃይማኖታዊ ቅራኔ ዜና ታሪክ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ቦታ እንዲሰጠው አድርጓል። ይህ ንቅናቄ በ1170 አካባቢ እንቅስቃሴውን እንደጀመረ አብዛኞቹ ታሪክ ጸሐፊዎች ይስማማሉ። ሊዮን በተባለች አንዲት የፈረንሳይ ከተማ የሚኖር ቮዴ የተባለ አንድ ሀብታም ነጋዴ አምላክን ማስደሰት ስለሚችልበት መንገድ ለመማር ከፍተኛ ፍላጎት አደረበት። ኢየሱስ ያለውን ሁሉ ሸጦ ለድሆች እንዲያካፍል ለአንድ ባለጠጋ በሰጠው ምክር በመገፋፋት ሳይሆን አይቀርም ቮዴ ቤተሰቡ በቁሳዊ እንዳይቸገር የሚያስችለውን ዝግጅት ካደረገ በኋላ ቀሪ ሀብቱን ወንጌሉን ለመስበክ ተጠቅሞበታል። (ማቴዎስ 19:​16-22) ብዙም ሳይቆይ ዎልደንሳውያን በሚል ስያሜ የሚታወቁ ተከታዮች አፈራ። a

የቮዴ ሕይወት በዋነኛነት ያተኮረው በድህነት፣ በስብከትና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነበር። የቀሳውስቱን በድሎት ላይ የተመሠረተ አኗኗር በሚመለከት ብዙ ጊዜ ተቃውሞ ይነሳ ነበር። በአንድ ወቅት የቤተ ክርስቲያኗን ብልሹ ምግባርና ድርጊት ያወግዙ የነበሩ ተቃዋሚ የቤተ ክህነት ሰዎች ነበሩ። ሆኖም ቮዴ እንደ አብዛኞቹ ተከታዮቹ ሁሉ ተራ ሰው ነበር። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ በተራው ሕዝብ ቋንቋ እንዲተረጎም የፈለገበትን ምክንያት ያለጥርጥር ይጠቁማል። በላቲን ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት የሚችሉት ቀሳውስቱ ብቻ ስለነበሩ ቮዴ ወንጌሎችና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ለመጀመሪያ ጊዜ በምሥራቅ ፈረንሳይ መካከለኛ ግዛት በስፋት በሚነገረው የፍራንኮ ፕሮቬኒካል ቋንቋ እንዲተረጎሙ አስፈላጊውን ዝግጅት አደረገ። b የሊዮን ድሆች የኢየሱስን ትእዛዝ በመከተል በመንገድ ላይ መስበክ ጀመሩ። (ማቴዎስ 28:​19, 20) ታሪክ ጸሐፊው ጋብሪኤል ኦዲሲዮ እንደተናገሩት ዎልደንሳውያን ለሕዝብ በሚሰጡት ምስክርነት መጽናታቸው ቤተ ክርስቲያኒቷን በእጅጉ አሳስቧት ነበር።

ከካቶሊክነት ወደ መናፍቅነት

በወቅቱ መስበክ የሚችሉት ቄሶች ብቻ የነበሩ ሲሆን ቤተ ክርስቲያኗ ደግሞ የመስበክ ሥልጣን የመስጠት መብት እንዳላት አድርጋ ታስብ ነበር። ቀሳውስቱ ዎልደንሳውያንን አላዋቂዎችና ያልተማሩ አድርገው ይቆጥሯቸው ነበር። ሆኖም ቮዴ በ1179 ከሊቀ ጳጳስ አሌክሳንደር ሦስተኛ ኦፊሴላዊ የመስበክ ሥልጣን እንዲሰጠው ጠየቀ። ፈቃዱ የተሰጠው ቢሆንም ይህ ፈቃድ ሊጸና የሚችለው የአካባቢው ቀሳውስት ካጸደቁት ብቻ ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ማልኮልም ላምቤር ይህ “ከእምቢታ የማይተናነስ እሺታ” ነበር ብለዋል። በእርግጥም የሊዮኑ ሊቀ ጳጳስ ዣን ቤልመ ተራ ስብከትን በግልጽ አግደዋል። በዚህ ጊዜ ቮዴ ሥራ 5:​29ን በመጥቀስ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” የሚል ምላሽ ሰጠ። ቮዴ እገዳውን ባለማክበሩ በ1184 ከቤተ ክርስቲያኗ ተገለለ።

ምንም እንኳ ዎልደንሳውያን ከሐገረ ስብከቱም ሆነ ከከተማው ቢባረሩም የመጀመሪያው ድንጋጌ ጥብቅ ተፈጻሚነት እንዲኖረው አልተደረገም ነበር። አብዛኛው ተራ ሕዝብ የዎልደንሳውያኑን ቅንነትና የአኗኗር መንገድ ያደንቅ የነበረ ሲሆን ጳጳሳት እንኳ ሳይቀሩ ከእነርሱ ጋር መነጋገራቸውን ቀጥለው ነበር።

ኦን ካመሮ የተባሉ አንድ ታሪክ ጸሐፊ እንደገለጹት ከሆነ ዎልደንሳውያን ሰባኪዎች “ራሷን የሮማ ቤተ ክርስቲያንን አልተቃወሙም።” የእነርሱ ፍላጎት “መስበክና ማስተማር” ብቻ ነበር። ንቅናቄው ከመናፍቃን ጎራ የተመደበው ቀስ በቀስ ኃይሉን ያዳከሙት ተከታታይ ድንጋጌዎች ከወጡ በኋላ እንደሆነ ታሪክ ጸሐፊዎች ይናገራሉ። በ1215 ፎርዝ ላተራን ካውንስል ዎልደንሳውያንን ሲያወግዝ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጩኸት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ታዲያ ይህ ስብከታቸውን የነካው እንዴት ነው?

በድብቅ መንቀሳቀስ ጀመሩ

ቮዴ በ1217 የሞተ ሲሆን ስደት ተከታዮቹን በፈረንሳይ ወደሚገኙ ተራራማ ሸለቆዎች፣ ወደ ጀርመን፣ ወደ ሰሜናዊ ኢጣሊያ እንዲሁም ወደ መካከለኛውና ምሥራቅ አውሮፓ እንዲበተኑ አደረጋቸው። በተጨማሪም ስደቱ ዎልደንሳውያንን በገጠራማ አካባቢዎች እንዲሰፍሩ ያደረጋቸው ሲሆን ይህም በብዙ ቦታዎች የስብከት እንቅስቃሴያቸውን ገድቦባቸዋል።

በ1229 የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ ፈረንሳይ የሚገኙትን ካታራውያን ወይም አልበጀንሳውያንን ለማጥፋት ያካሄደችውን ዘመቻ አጠናቀቀች። c የእንዲህ ዓይነቱ ጥቃት ቀጣይ ሰለባዎች ዎልደንሳውያን ነበሩ። ብዙም ሳይቆይ ኢንኩዊዝሽኑ እያንዳንዱን የቤተ ክርስቲያኗን ተቃዋሚ ያላንዳች ርህራሄ መመንጠሩን ተያያዘው። ዎልደንሳውያን በጣም በመፍራታቸው በድብቅ መንቀሳቀስ ጀመሩ። በ1230 በሕዝብ ፊት መስበካቸውን አቆሙ። ኦዲሲዮ የሚከተለውን ብለዋል:- “ዎልደንሳውያኑ አዳዲስ በጎች መፈለጋቸውን አቁመው . . . ውጪያዊ ፈተናና ስደት የደረሰባቸው የእምነት አጋሮቻቸው ከእምነታቸው ተሰናክለው እንዳይወጡ መርዳቱን ተያያዙት።” አክለውም “ስብከት ከፍተኛ ቦታ ቢሰጠውም በተግባር ግን የተለየ ሁኔታ ሰፍኖ ነበር።”

እምነቶቻቸውና ልማዶቻቸው

ወንድ ሴት ሳይል ሁሉም በስብከት እንቅስቃሴ እንዲካፈል ከማድረግ ይልቅ ዎልደንሳውያን በ14ኛው መቶ ዘመን ሰባኪያንና አማኞች የሚል መደብ ፈጥረው ነበር። መስበክ የሚችሉት በቂ ሥልጠና ያገኙ ወንዶች ብቻ ነበሩ። እነዚህ ከቦታ ወደ ቦታ የሚዘዋወሩ አገልጋዮች ቆየት ብሎ ባርብ (አጎቶች) ተብለው መጠራት ጀመሩ።

ዎልደንሳውያን ቤተሰቦችን ቤታቸው ድረስ እየሄዱ የሚጎበኙት ባርቦች እምነታቸውን ለማስፋፋት ከመሞከር ይልቅ ንቅናቄው ሕልውናውን እንደያዘ ለማቆየት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ሁሉም ባርቦች ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ሲሆን ስድስት ዓመት ገደማ የሚፈጀው ሥልጠና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያተኮረ ነበር። በቋንቋቸው የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘታቸው ቃሉን አለችግር ለመንጎቻቸው ለማብራራት አስችሏቸዋል። ልጆቻቸውን ጨምሮ ዎልደንሳውያን ጥልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንደነበራቸውና አብዛኞቹን የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል መጥቀስ ይችሉ እንደነበር ተቃዋሚዎች እንኳ ሳይቀሩ ያምናሉ።

ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ የቀድሞዎቹ ዎልደንሳውያን ውሸት፣ መንጽሔ፣ የሙታን መታሰቢያ በዓላት፣ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥነ ሥርዓቶች እንዲሁም የማርያምንና “የቅዱሳንን” አምልኮ የመሳሰሉትን ነገሮች ይቃወሙ ነበር። በተጨማሪም በየዓመቱ የጌታ እራት ወይም የመጨረሻው እራት የሚባለውን በዓል ያከብሩ ነበር። ላምቤር እንዳሉት ከሆነ የአምልኮ ሥርዓታቸው ከአንድ “ተራ ሰው ሃይማኖት ጋር ይመሳሰላል።”

“ሁለት ዓይነት ኑሮ”

የዎልደንሳውያን ማኅበረሰብ እርስ በእርሱ የተሳሰረ ነበር። አባላቱ ጋብቻ የሚመሠርቱት በዚያው በንቅናቄው ውስጥ ካለ ሰው ጋር ሲሆን ይህም የኋላ ኋላ ዎልደንሳውያን የመጨረሻ ስሞች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። ይሁን እንጂ ዎልደንሳውያን ሕልውናቸውን ለማቆየት ባደረጉት ጥረት አመለካከታቸውን ለመደበቅ ሞክረዋል። ከሃይማኖታዊ እምነቶቻቸውና ልማዶቻቸው ጋር በተያያዘ አንዳንድ ጉዳዮችን ለመደበቅ መሞከራቸው ተቃዋሚዎቻቸው ፈጽሞ ከእውነታው የራቀ ክስ እንዲመሠርቱባቸው ሁኔታውን ምቹ አድርጎላቸዋል። ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት በሰይጣን አምልኮ ይካፈላሉ የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር። d

ዎልደንሳውያኑ እንደዚህ የመሳሰሉትን ክሶች ለማስተባበል የሞከሩበት አንደኛው መንገድ አቋማቸውን ማላላትና ታሪክ ጸሐፊው ካመሮ እንዳሉት ከካቶሊኮች ጋር “በመጠኑ ተስማምተው” አንዳንድ ነገሮችን መፈጸም ነበር። ብዙ ዎልደንሳውያን ለካቶሊክ ቄሶች ይናዘዙ፣ በቅዳሴ ሥርዓት ላይ ይገኙ፣ ጠበል ይረጩና ሌላው ቀርቶ ቤተ ክርስቲያን ሄደው ይሳለሙ ነበር። ላምቤር የሚከተለውን ብለዋል:- “ዎልደንሳውያን በአብዛኛው ካቶሊክ ጎረቤቶቻቸው የሚያደርጓቸውን ነገሮች ያደርጋሉ።” ኦዲሲዮ ዎልደንሳውያን “ሁለት ዓይነት ኑሮ” መኖር ጀምረው እንደነበረ በግልጽ ተናግረዋል። አክለውም “ከካቶሊኮች ጋር ያላቸውን አንጻራዊ ሰላም ለመጠበቅ ሲሉ እንደ ካቶሊኮች ይሆናሉ። በሌላው በኩል ደግሞ ማኅበረሰቡ ጨርሶ እንዳልጠፋ የሚያሳዩ አንዳንድ ሥነ ሥርዓቶችንና ልማዶችን ይከተላሉ።”

ከመናፍቅነት ወደ ፕሮቴስታንትነት

በ16ኛው መቶ ዘመን የተከናወነው ተሃድሶ የአውሮፓን ሃይማኖታዊ ገጽታ ሙሉ በሙሉ ለውጦታል። የሃይማኖታዊ አክራሪዎች ሰለባ የሆኑት ቡድኖች በራሳቸው አገር ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት መጣር አሊያም ይበልጥ የተሻለ ሁኔታ ወዳለባቸው አገሮች መሰደድ ነበረባቸው። ብዙ ሰዎች ሰፊ ተቀባይነትን ባገኙ ሃይማኖቶች ላይ ጥያቄ ማንሳት በመጀመራቸው መናፍቅ የሚለው ሐሳብም ቀስ በቀስ እየተረሳ መጣ።

በ1523 መጀመሪያ ላይ ታዋቂው የተሃድሶ አራማጅ ማርቲን ሉተር ዎልደንሳውያንን ጠቅሶ ነበር። በ1526 ከዎልደንሳውያን ባርቦች መካከል አንዱ በአውሮፓ የተደረጉትን ሃይማኖታዊ ለውጦች የሚያበስር ዜና ይዞ ወደ አልፕስ ተጓዘ። ይህም በፕሮቴስታንቱና በዎልደንሳውያኑ መካከል የሐሳብ ልውውጥ መድረክ እንዲከፈት አድርጓል። ፕሮቴስታንቶቹ የመጀመሪያውን የፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትም እንዲያዘጋጁ ዎልደንሳውያኑን አበረታቷቸው። በ1535 የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ቆየት ብሎ ኦሊቬታን በሚል ስያሜ ታወቀ። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ዎልደንሳውያን የፈረንሳይኛ ቋንቋ ችሎታ አልነበራቸውም።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የጫረችው የስደት እሳት ሲቀጣጠል ብዙ ዎልደንሳውያን የፕሮቴስታንት ስደተኞች እንዳደረጉት ሁሉ ደህንነት ለማግኘት በፈረንሳይ ደቡባዊ ግዛት ወደምትገኘው ፕሮቮንስ ተሰደዱ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ የስደተኞቹ ወሬ ባለ ሥልጣናቱ ጆሮ ደረሰ። የዎልደንሳውያንን አኗኗርና ሥነ ምግባር በተመለከተ ብዙ አዎንታዊ ሪፖርቶች ቢኖሩም አንዳንዶች የዎልደንሳውያንን ታማኝነት ከመጠራጠራቸውም በላይ የሥርዓታማ አኗኗር ጠር ናቸው በማለት ከሰሱአቸው። ይህም ሜሪንዶል የተባለው ዐዋጅ እንዲወጣ በር የከፈተ ሲሆን በመግቢያው ላይ የተጠቀሰውን አሰቃቂ ደም መፋሰስም አስከትሏል።

በካቶሊኮችና በዎልደንሳውያን መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ እየሻከረ ሲሄድ ዎልደንሳውያኑ ለሚሰነዘርባቸው ጥቃት ምላሽ ለመስጠትና ራሳቸውን ለመከላከል ሲሉ የጦር ኃይል መጠቀም ጀመሩ። ይህ ግጭት ከፕሮቴስታንቶች ጋር እንዲቀላቀሉ ያደረጋቸው ሲሆን በመጨረሻም ከእነርሱ ጋር ግንባር ፈጥረዋል።

ባለፉት መቶ ዓመታት የዎልደንሳውያን ቤተ ክርስቲያናት እንደ ኡራጓይና ዩናይትድ ስቴትስ ባሉ ከፈረንሳይ ርቀው በሚገኙ አገሮች ውስጥ ተቋቁመው ነበር። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ታሪክ ጸሐፊዎች “የዎልደንሳውያኑ እምነት” ወደ ፍጻሜው የመጣው በተሃድሶው ወቅት በፕሮቴስታንቶች “ሲዋጥ ነው” በማለት ከተናገሩት ከኦዲሲዮ ሐሳብ ጋር ይስማማሉ። እርግጥ የዎልደንሳውያን ንቅናቄ የቀድሞ ቅንዓቱን ያጣው ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ሲሆን ይህም ሊከሰት የቻለው አባላቱ ከፍርሃት የተነሳ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስብከታቸውንና ትምህርታቸውን በማቆማቸው ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ቮዴ ቫልዴ፣ ቫልዲሲየስ ወይም ዋልዶ በሚባሉት ስሞችም ይታወቃል። “ዎልደንሳውያን” የሚለው መጠሪያ የተገኘው ዋልዶ ከሚለው ስም ነው። ዎልደንሳውያን ወይም ዎልደንሶች የሊዮን ድሆች በመባልም ይታወቃሉ።

b በ1199 በሰሜናዊ ምሥራቅ ፈረንሳይ የምትገኘው የሜዝ ጳጳስ ግለሰቦች በቋንቋቸው የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብና በመወያየት ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ለሊቀ ጳጳሳቱ ኢኖሰንት ሦስተኛ አቤቱታ አቅርበዋል። ጳጳሱ ስለ ዎልደንሳውያን እየተናገሩ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም።

c “ካታራውያን ክርስቲያን ሰማዕታት ናቸውን?” በሚል ርዕስ በመስከረም 1, 1995 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 27-30 ላይ የወጣውን ተመልከት።

d በዎልደንሳውያኑ ላይ ያለማቋረጥ ይደርስ የነበረው ነቀፋ በመጨረሻ ቮደሪ (ቮዷ ከተባለው የፈረንሳይኛ ቃል የመጣ ነው) የሚለውን ስም አሰጥቷቸዋል። ቃሉ ተጠርጣሪ መናፍቃንን ወይም የሰይጣን አምላኪዎችን ለማመልከት ይሠራበታል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ዎልደንሳውያን የነበሩባቸው አካባቢዎች

ፈረንሳይ

ሊዮን

ፕሮቮንስ

ሉበሮ

ስትራስበርግ

ሚላን

ሮም

በርሊን

ፕራግ

ቬይና

[ሥዕል]

በ1535 የታተመው ኦሊቬታን የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲተረጎም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደረጉት ዎልደንሳውያን ነበሩ

[ምንጭ]

መጽሐፍ ቅዱስ:- © Cliché Bibliothèque nationale de France, Paris

[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቮዴ

በእድሜ የገፉ ሁለት ዎልደንሳውያን ሴቶች በእሳት ሲቃጠሉ

[ምንጭ]

ገጽ 20 እና 21:- © Landesbildstelle Baden, Karlsruhe