በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የብቸኝነትን ስሜት ማሸነፍ ትችላላችሁ

የብቸኝነትን ስሜት ማሸነፍ ትችላላችሁ

የብቸኝነትን ስሜት ማሸነፍ ትችላላችሁ

“ነፋሱ ብቸኝነት ባጠቃው ልብ ላይ ይነፍሳል፣ ብቸኝነት ያጠቃውም ልብ ይጠወልጋል።” አየርላንዳዊው ባለቅኔ ዊልያም በትለር ይትስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት እንደሚያመለክቱት የብቸኝነት ስሜት የልብ ስብራት ሊያስከትል ይችላል።

የብቸኝነት ስሜት የሚያስከትለው ሐዘን ፈጽሞ ደርሶብኝ አያውቅም ሊል የሚችል ማን አለ? ብቸኝነት እንዲሰማን የሚያደርጉን ብዙ ምክንያቶች አሉ። በተለይ ደግሞ ፈጽሞ ያላገቡ ወይም ባሎቻቸው የሞቱባቸው አሊያም የተፋቱ ሴቶች የሚሰማቸው ብቸኝነት ከሁሉ የከፋ ነው።

ለምሳሌ ያህል ፍራንሲስ የተባለች አንዲት ክርስቲያን ወጣት እንዲህ ትላለች:- “23 ዓመት ሲሞላኝ ሁሉም ጓደኞቼ አግብተው እኔ ብቻ ቀረሁ።” a ዓመታት እያለፉ ሲሄዱና የማግባት አጋጣሚው እየጠበበ ሲመጣ የብቸኝነት ስሜቱም የዚያኑ ያህል እየጨመረ ሊሄድ ይችላል። አሁን በ40ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ የምትገኘው ሳንድራ “ነጠላ ሆኜ የመኖር ዓላማ አልነበረኝም፣ አሁንም ቢሆን አጋጣሚው ከተገኘ ማግባት እፈልጋለሁ” ስትል ሳትሸሽግ ተናግራለች። በ50ዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኘው አንጀላ እንዲህ ትላለች:- “በነጠላነት የመኖር ፍላጎት አልነበረኝም፤ ሆኖም ነገሮች እንደዚህ ሆኑ። ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል በተመደብኩበት ቦታ የነበሩት ነጠላ ወንድሞች ቁጥር በጣም ጥቂት ነበር።”

ብዙ ክርስቲያን ሴቶች “በጌታ ብቻ” እንዲያገቡ ይሖዋ የሰጠውን ምክር በታማኝነት በመከተል ላለማግባት መወሰናቸው የሚያስመሰግን ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:39 NW ) አንዳንዶች ነጠላነትን በጸጋ ሲቀበሉት ሌሎች ግን ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ለማግባትና ልጆች ለመውለድ ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል። ሳንድራ እንዲህ ስትል ሳትሸሽግ ተናግራለች:- “የትዳር ጓደኛ ባለማግኘቴ የሚሰማኝ የባዶነት ስሜት አብሮኝ የሚኖር ነገር ሆኗል።”

በዕድሜ የገፉ ወላጆችን እንደመንከባከብ ያሉ ሌሎች ኃላፊነቶችም የብቸኝነትን ስሜት ሊያባብሱ ይችላሉ። “ስላላገባሁ ቤተሰቦቼ በዕድሜ የገፉ ወላጆቻችንን መንከባከብ ያለብኝ እኔ እንደሆንኩ አድርገው ያስባሉ” ትላለች ሳንድራ። “ምንም እንኳን ያለነው ስድስት ልጆች ብንሆንም ለ20 ዓመታት ይህንን ኃላፊነት ብቻዬን ተሸክሜያለሁ። የሚደግፈኝ የትዳር ጓደኛ ቢኖረኝ ኖሮ ሕይወት የበለጠ ቀላል ይሆንልኝ ነበር።”

ፍራንሲስ የብቸኝነት ስሜቷን የሚያባብስባትን ሌላ ምክንያት ስትጠቅስ እንዲህ ብላለች:- “አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ‘ለምን አላገባሽም?’ ብለው ፊት ለፊት ይጠይቁኛል። እንደዚህ ዓይነቱ ጥያቄ ነጠላ የሆንኩት በራሴ ጥፋት እንደሆነ እንዲሰማኝ ያደርገኛል። በተገኘሁባቸው የሠርግ ግብዣዎች ላይ ማለት ይቻላል ‘የአንቺስ ተራ መቼ ነው?’ የሚለው የምፈራው ጥያቄ ይቀርብልኛል። እኔም ‘መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ወንድሞች የማይፈልጉኝ ከሆነ ምናልባት አስፈላጊ የሆኑት ክርስቲያናዊ ባሕርያት የሉኝም ወይም አልማርክ ይሆናል’ ብዬ ማሰብ እጀምራለሁ።”

የብቸኝነትንና ራስን የማግለልን ስሜት ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው? ሌሎች ማድረግ የሚችሉት ነገር ካለ ምን ዓይነት እርዳታ ሊለግሱ ይችላሉ?

በይሖዋ ታመኑ

መዝሙራዊው “ትካዜህን [“ሸክምህን፣” NW ] በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 55:22) “ሸክም” የሚለው የዕብራይስጡ ቃል፣ ቃል በቃል ሲተረጎም “እጣ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ከሕይወት እጣ ፈንታችን ጋር በተያያዘ የሚገጥመንን ስጋትና ጭንቀት ያመለክታል። ይሖዋ ከማንም ይበልጥ ያሉብንን ሸክሞች የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ እነዚህን ለመቋቋም የሚያስችለንን ጥንካሬ ሊሰጠን ይችላል። አንጀላ በይሖዋ መታመንዋ የብቸኝነት ስሜቷን እንድታሸንፍ ረድቷታል። ያሳለፈችውን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት በማስታወስ እንዲህ ትላለች:- “አቅኚ ሆኜ ማገልገል ስጀምር እኔና የአገልግሎት ጓደኛዬ ቅርብ ከሚባለው ጉባኤ በጣም ርቀን ነበር የምንኖረው። ስለዚህም በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመንን ተማርን፤ ይህም በሕይወቴ ሁሉ ጠቅሞኛል። አሉታዊ ሐሳቦች ወደ አእምሮዬ ሲመጡብኝ ይሖዋን አነጋግረዋለሁ እሱም ይረዳኛል። መዝሙር 23 ታላቅ መጽናኛ ሆኖልኛል። አዘውትሬም አነብበዋለሁ።”

ሐዋርያው ጳውሎስ ከባድ ሸክም ነበረበት። ቢያንስ ሦስት ጊዜ ‘የሥጋ መውጊያው ከእርሱ እንዲለይ ጌታን ለምኗል።’ ጳውሎስ ተአምራዊ ዕርዳታ አላገኘም፤ ሆኖም ይገባናል የማንለው የአምላክ ደግነት ደግፎ እንደሚያቆመው ቃል ተገብቶለታል። (2 ቆሮንቶስ 12:7-9) ጳውሎስ ባለው ረክቶ የመኖርን ምሥጢር አውቋል። ከጊዜ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ማጣትን ዐውቃለሁ፤ ማግኘትንም ዐውቃለሁ። ብጠግብም ብራብም፣ ባገኝም ሆነ ባጣ በማንኛውም ሆነ በየትኛውም ሁኔታ ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር ተረድቻለሁ። ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን እችላለሁ።”​—⁠ፊልጵስዩስ 4:12, 13 አ.መ.ት

አንድ ሰው ተስፋ ሲቆርጥ ወይም ብቸኝነት ሲሰማው ከአምላክ ኃይል ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ሳንድራ ይህንን ምክር ተግባራዊ አደረገች። እንዲህ ትላለች:- “ነጠላ እንደመሆኔ መጠን አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈው ብቻዬን ነው። ይህም ወደ ይሖዋ ለመጸለይ ሰፊ አጋጣሚ ይሰጠኛል። ወደ እርሱ በጣም እንደቀረብኩ ስለሚሰማኝ ችግሮቼንና ደስታዬን በነፃነት እነግረዋለሁ።” ፍራንሲስም እንዲህ ትላለች:- “ለብቻ ሆኖ ከአሉታዊ ስሜቶች ጋር መታገል የማይገፋ ነው። ሆኖም ስሜቶቼን ግልጥልጥ አድርጌ ለይሖዋ መንገሬ በእጅጉ ይረዳኛል። ይሖዋ መንፈሳዊና ስሜታዊ ደህንነቴን ጉዳት ላይ ሊጥል የሚችል ማንኛውንም ነገር ዝም ብሎ እንደማይመለከት ጽኑ እምነት አለኝ።”​—⁠1 ጢሞቴዎስ 5:5

“አንዱ የሌላውን ከባድ ሸክም ይሸከም”

በክርስቲያናዊው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ስንኖር ሸክማችንን ለብቻችን መሸከም የለብንም። ሐዋርያው ጳውሎስ “አንዱ የሌላውን ከባድ ሸክም ይሸከም፤ በዚህም ሁኔታ የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ” ሲል አጥብቆ መክሯል። (ገላትያ 6:2 አ.መ.ት ) ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር ባለን ግንኙነት የብቸኝነትን ሸክም ሊያቀልልን የሚችል መጽናኛ የሚሆን “መልካም ቃል” እናገኛለን።​—⁠ምሳሌ 12:25

ቅዱሳን ጽሑፎች የእስራኤል መስፍን ስለነበረው ስለ ዮፍታሄ ልጅ የሚናገሩትንም እንመልከት። ዮፍታሄ ጠላት በነበረው በአሞን ጦር ላይ ድል ከመቀዳጀቱ ቀደም ብሎ ከቤተሰቡ መካከል እሱን ለመቀበል መጀመሪያ የሚወጣውን ሰው ለይሖዋ ለመስጠት ተሳለ። ልትቀበለው የወጣችው ሴት ልጁ ሆና ተገኘች። (መሳፍንት 11:30, 31, 34-36) ምንም እንኳን ይህ ሕይወቷን ሙሉ በነጠላነት እንድትኖርና ቤተሰብ የመመሥረት ፍላጎቷን መሥዋዕት እንድታደርግ የሚጠይቅባት ቢሆንም የዮፍታሔ ልጅ ለዚህ ስዕለት ራስዋን በፈቃደኝነት በማስገዛት በቀሪው ሕይወትዋ ሴሎ በሚገኘው መቅደስ አገልግላለች። የከፈለችው መሥዋዕትነት ከንቱ ሆኖ ቀርቶ ይሆን? በጭራሽ። “የእስራኤልም ሴቶች ልጆች በዓመት በዓመቱ እየሄዱ የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በዓመት አራት ቀን ሙሾ እንዲያወጡ [“እንዲያመሰግኑ፣” የ1879 እትም] በእስራኤል ዘንድ ልማድ ሆነ።” (መሳፍንት 11:40) አዎን፣ ምስጋና ተቀባዩን ያበረታታል። እንግዲያው የሚገባቸውን ከማመስገን ወደኋላ አንበል።

የኢየሱስንም ምሳሌ መመልከታችን ጠቃሚ ነው። የአይሁዳውያን ባህል ወንዶች ከሴቶች ጋር እንዲነጋገሩ የሚፈቅድ ባይሆንም እንኳ ኢየሱስ ከማርያምና ከማርታ ጋር ጊዜ አሳልፏል። እነዚህ ሴቶች መበለት ወይም ያላገቡ ሊሆኑ ይችላሉ። ኢየሱስ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ወዳጅነት በመመሥረት በመንፈሳዊ እንዲጠቀሙ ፈልጎ ነበር። (ሉቃስ 10:38-42) እኛም በማኅበራዊ ግብዣዎች ላይ ያላገቡ መንፈሳዊ እህቶቻችን እንዲገኙ በማድረግ እንዲሁም በስብከቱ ሥራ ከእነሱ ጋር ለመካፈል እቅድ በማውጣት የኢየሱስን ምሳሌ ልንከተል እንችላለን። (ሮሜ 12:13) እንደዚህ ያሉ ግብዣዎችን በደስታ ይቀበሉ ይሆን? አንዲት እህት “ወንድሞች እንደሚወዱኝና እንደሚያደንቁኝ አውቃለሁ። ሆኖም በግል ትኩረት ሰጥተው ሲያነጋግሩኝ ደስ ይለኛል” ብላለች።

“የራሳችን የምንለው ሰው ስለሌለን እንደምንወደድና የመንፈሳዊው ወንድሞችና እህቶች ቤተሰብ አካል እንደሆንን እንዲሰማን እንፈልጋለን” ትላለች ሳንድራ። ይሖዋ እንዲህ ላሉት ሰዎች እንደሚያስብ የታወቀ ነው፤ እኛም እንደሚፈለጉና እንደሚወደዱ እንዲሰማቸው ስናደርግ ከእርሱ ጋር ተባብረን እንሠራለን። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) እንዲህ ዓይነቱ አሳቢነት ሳይስተዋል አይቀርም ምክንያቱም “ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፣ በጎነቱንም [ይሖዋ አምላክ] መልሶ ይከፍለዋል።”​—⁠ምሳሌ 19:17

እያንዳንዱ የራሱን ሸክም ሊሸከም ይገባዋልና

ሌሎች የሚሰጡት እርዳታ የሚያበረታታ ሊሆን ቢችልም ‘እያንዳንዱ የራሱን ሸክም መሸከም ይገባዋል።’ (ገላትያ 6:5 አ.መ.ት ) የብቸኝነትን ሸክም በመሸከም ረገድ ጥንቃቄ ልናደርግባቸው የሚገቡን አንዳንድ አደጋዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል ስሜታችንን የምንደብቅ ከሆነ የብቸኝነት ስሜት ሊያሸንፈን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ የብቸኝነትን ስሜት በፍቅር ልናሸንፍ እንችላለን። (1 ቆሮንቶስ 13:7, 8) ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ደስታ ለማግኘት የሚያስችለው ከሁሉ የተሻለው መንገድ መስጠትና ማካፈል ነው። (ሥራ 20:35) አንዲት ታታሪ አቅኚ እህት እንዲህ ብላለች:- “ስለ ብቸኝነቴ የማስብበት ብዙ ጊዜ የለኝም። ጠቃሚ እንደሆንኩ ሲሰማኝና ራሴን በሥራ ሳስጠምድ ብቸኝነት አይሰማኝም።”

በብቸኝነት ስሜት ተገፋፍተን ጥበብ የጎደለው ግንኙነት እንዳንመሠርትም መጠንቀቅ አለብን። ለምሳሌ ያህል ለማግባት ያለን ፍላጎት የማያምን ሰው ማግባት የሚያስከትላቸውን ችግሮችና በተለይ ደግሞ በእንዲህ ዓይነቱ ቀንበር እንዳንጠመድ የተሰጠንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ችላ እንድንል ቢያደርገን ምንኛ አሳዛኝ ይሆናል! (2 ቆሮንቶስ 6:14) አንዲት ትዳርዋ የፈረሰባት ክርስቲያን እህት “ከነጠላነት እጅግ የከፋ አንድ ነገር አለ። እሱም ከማይሆን ሰው ጋር መጋባት ነው” ብላለች።

አንድ ችግር መፍትሔ ከሌለው ያለው ምርጫ ለጊዜውም ቢሆን በጽናት መቋቋም ነው። በአምላክ እርዳታ የብቸኝነትን ስሜት መቋቋም ይቻላል። ይሖዋን ማገልገላችንን ከቀጠልን አንድ ቀን ችግሮቻችን በሙሉ በተሻለ ሁኔታ መፍትሔ እንደሚያገኙ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።​—⁠መዝሙር 145:16

[የግርጌ ማስታወሻ]

a እዚህ ላይ የተጠቀሱት ሴቶች ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመስጠትና በማካፈል የብቸኝነትን ስሜት ማሸነፍ ይቻላ