በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የክርስቶስ አመራር ለአንተ እውን ነውን?

የክርስቶስ አመራር ለአንተ እውን ነውን?

የክርስቶስ አመራር ለአንተ እውን ነውን?

“መሪ ተብላችሁም አትጠሩ፣ መሪያችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና።”​ማቴዎስ 23:10 NW

1. የእውነተኛ ክርስቲያኖች መሪ ማን ብቻ ነው?

 ዕለቱ ማክሰኞ ኒሳን 11 ነው። ከሦስት ቀናት በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ ይገደላል። በቤተ መቅደስ ሲገኝ ይህ የመጨረሻው ጊዜ ነው። በዚህ ዕለት ኢየሱስ እዚያ ለተሰበሰበው ሕዝብና ለደቀ መዛሙርቱ አስፈላጊ የሆነ አንድ ትምህርት ሰጠ። እንዲህ አለ:- “መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ። አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም:- አባት ብላችሁ አትጥሩ። ሊቃችሁ [“መሪያችሁ፣” NW ] አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና:- ሊቃውንት [“መሪዎች፣” NW ] ተብላችሁ አትጠሩ።” (ማቴዎስ 23:8-10) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የእውነተኛ ክርስቲያኖች መሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

2, 3. ይሖዋን ማዳመጣችንና እርሱ የሾመውን መሪ መቀበላችን በሕይወታችን ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

2 የኢየሱስን አመራር መቀበላችን በሕይወታችን ላይ እንዴት ያለ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል! ይሖዋ አምላክ የዚህን መሪ መምጣት አስመልክቶ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት የሚከተለውን ተንብዮአል:- “እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፣ ወደ ውኃ ኑ፣ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፤ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። . . . አድምጡኝ፣ በረከትንም ብሉ፣ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው። . . . እነሆ፣ ለአሕዛብ ምስክር፣ ለወገኖችም አለቃና [“መሪና፣” የ1980 ትርጉም ] አዛዥ እንዲሆን ሰጥቼዋለሁ።”​—⁠ኢሳይያስ 55:1-4

3 ኢሳይያስ ይሖዋን ስናዳምጥና እርሱ የሾመልንን መሪና አዛዥ ስንከተል የግል ሕይወታችን እንዴት እንደሚነካ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ለማሳየት እንደ ውኃ፣ ወተትና ወይን ጠጅ ያሉ የተለመዱ ፈሳሾችን ተጠቅሟል። ይህን ማድረጋችን እርካታ ያስገኝልናል። ሞቃታማ በሆነ ቀን አንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ውኃ የመጠጣት ያህል ነው። ለእውነትና ለጽድቅ የነበረንን ጥም ይቆርጥልናል። ለሕፃናት ጥንካሬና እድገት ወተት አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ ‘የቃሉ ወተትም’ ብርታት ይሰጠናል እንዲሁም ከአምላክ ጋር ባለን ዝምድና ረገድ በመንፈሳዊ እንድናድግ ይረዳናል። (1 ጴጥሮስ 2:1-3) የወይን ጠጅስ ቢሆን በግብዣ ወቅት ደስታ እንደሚሰጥ ማን ሊክድ ይችላል? በተመሳሳይም እውነተኛውን አምላክ ማምለክና እርሱ የሾመውን አለቃ ፈለግ መከተል ‘ፍጹም ደስታ’ ያስገኛል። (ዘዳግም 16:15) ስለዚህ ወጣትም ሆንን በዕድሜ የገፋን፣ ወንድም ሆንን ሴት ሁላችንም የክርስቶስ አመራር እውን እንደሆነልን ማሳየታችን እጅግ አስፈላጊ ነው። ታዲያ መሲሑ መሪያችን እንደሆነ በዕለታዊ ሕይወታችን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

ወጣቶች​—⁠‘በጥበብ ማደጋችሁን’ ቀጥሉ

4. (ሀ) ኢየሱስ በ12 ዓመቱ በማለፍ በዓል ላይ ለመገኘት ኢየሩሳሌም ሄዶ ሳለ ምን ነገር ተከሰተ? (ለ) ኢየሱስ ገና የ12 ዓመት ልጅ እያለ ምን ያህል እውቀት ነበረው?

4 መሪያችን ለወጣቶች የተወውን ምሳሌ ተመልከት። ስለ ኢየሱስ የልጅነት ጊዜ ብዙም የምናውቀው ነገር ባይኖርም እንኳ በአንድ ወቅት የተከሰተው ሁኔታ ጥሩ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ነው። ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ ወላጆቹ የማለፍን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ዓመታዊ ጉዞ ባደረጉበት ጊዜ ይዘውት ሄዱ። በዚህ ወቅት በአንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት ተስቦ በመቅረቱ ቤተሰቡ ሳያውቁ ትተውት ሄዱ። ከሦስት ቀናት በኋላ በሁኔታው የተደናገጡት ወላጆቹ ዮሴፍ እና ማርያም “በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውም ሲጠይቃቸውም” በቤተ መቅደስ አገኙት። ከዚህም በላይ “የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ተገረሙ።” እስቲ አስበው፣ ኢየሱስ ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳለ የሚያመራምሩና መንፈሳዊ የሆኑ ጥያቄዎች መጠየቅ ብቻ ሳይሆን አስገራሚ መልሶች ይሰጥ ነበር! ወላጃዊ ሥልጠና አግኝቶ እንደነበር ምንም አያጠራጥርም!​—⁠ሉቃስ 2:41-50

5. ወጣቶች ለቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያላቸውን አመለካከት መመርመር የሚችሉት እንዴት ነው?

5 ምናልባት አንተም ወጣት ልትሆን ትችላለህ። ወላጆችህ ለአምላክ ያደሩ አገልጋዮች ከሆኑ ዘወትር የሚደረግ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንደሚኖራችሁ የታወቀ ነው። ለቤተሰብ ጥናቱ ያለህ አመለካከት ምንድን ነው? እንደሚከተሉት ያሉትን ጥያቄዎች ለምን አታስብባቸውም:- ‘ቤተሰቦቼ ያወጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም ከልቤ እደግፋለሁ? ፕሮግራሙን የሚያደናቅፍ ምንም ነገር ከማድረግ በመቆጠብ ከዝግጅቱ ጋር እተባበራለሁ?’ (ፊልጵስዩስ 3:16) ‘በጥናቱ ላይ በንቃት እካፈላለሁ? ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ከሚጠናው ትምህርት ጋር የተያያዘ ጥያቄ እጠይቃለሁ? በተግባራዊነቱ ላይ ሐሳብ እሰጣለሁ? በመንፈሳዊ እድገት በማድረግ እንደ “ጎለመሱ ሰዎች ጠንካራ ምግብ” የመመገብ ፍላጎት እያዳበርኩ ነው?’​—⁠ዕብራውያን 5:13, 14

6, 7. መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ለማንበብ ፕሮግራም ማውጣት ወጣቶችን ሊጠቅም የሚችለው እንዴት ነው?

6 መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ለማንበብ የሚያስችል ፕሮግራም ማውጣትም አስፈላጊ ነው። መዝሙራዊው እንዲህ በማለት ዘምሯል:- “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፣ . . . ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፣ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል።” (መዝሙር 1:1, 2) በሙሴ እግር የተተካው ኢያሱ ‘ሕጉን በቀንና በሌሊት ያነብብ’ ነበር። ይህም በጥበብ እንዲያከናውንና አምላክ የሰጠውን ሥራ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲፈጽም አስችሎታል። (ኢያሱ 1:8) መሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 4:4) ሥጋዊ ምግብ በየዕለቱ መመገብ የሚያስፈልገን ከሆነ መንፈሳዊ ምግብ አዘውትረን መመገባችን ደግሞ ይበልጥ አስፈላጊ ነው!

7 የአሥራ ሦስት ዓመቷ ኒኮል ለመንፈሳዊ ፍላጎቷ ንቁ በመሆን መጽሐፍ ቅዱስ በየዕለቱ ማንበብ ጀመረች። a አሁን 16 ዓመቷ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ጊዜ ከዳር እስከ ዳር አንብባ ጨርሳ ለሁለተኛ ጊዜ አጋምሳዋለች። የምትጠቀመው ዘዴ ቀላል ነው። “በቀን ቢያንስ አንድ ምዕራፍ ለማንበብ ወሰንኩ” በማለት ትናገራለች። በየዕለቱ የምታደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የረዳት እንዴት ነው? እንዲህ በማለት ትመልሳለች:- “በአሁኑ ጊዜ የትም ብትሄዱ መጥፎ ተጽዕኖዎች ያጋጥሟችኋል። እምነቴን የሚፈታተኑ ተጽዕኖዎች በትምህርት ቤትና በሌሎች ቦታዎች በየዕለቱ ያጋጥሙኛል። በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤ እነዚህን ተጽዕኖዎች ለመቋቋም የሚያስችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዛትንና መሠረታዊ ሥርዓቶችን ወዲያውኑ እንዳስታውስ ይረዳኛል። ይህም ወደ ይሖዋ እና ወደ ኢየሱስ ይበልጥ እንደቀረብኩ ሆኖ እንዲሰማኝ ያደርገኛል።”

8. ኢየሱስ በምኩራቦች ምን የማድረግ ልማድ ነበረው? ወጣቶች እንዴት ሊመስሉት ይችላሉ?

8 ኢየሱስ ቅዱሳን ጽሑፎች በሚነበቡበት ምኩራብ ተገኝቶ የማዳመጥና የመሳተፍ ልማድ ነበረው። (ሉቃስ 4:16፤ ሥራ 15:21) ወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስ በሚነበብባቸውና በሚጠናባቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው በመገኘት ይህን ምሳሌ ቢከተሉ ምንኛ ይጠቀማሉ! የ14 ዓመቱ ሪቻርድ ለእነዚህ ስብሰባዎች ያለውን አድናቆት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ከስብሰባዎች ከፍተኛ ጥቅም አገኛለሁ። ጥሩና መጥፎ የሚባሉት ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ፣ ጥሩ የሚባለው ሥነ ምግባርና መጥፎ የሚባለው ሥነ ምግባር የትኛው እንደሆነ፣ የክርስቶስ ዓይነት ባሕርያት የሚባሉት የትኞቹ እንደሆኑ የማያቋርጥ ማሳሰቢያ አገኛለሁ። ትምህርት ለማግኘት የግድ በመከራ ውስጥ ማለፍ አያስፈልገኝም።” አዎን፣ “የይሖዋ ማሳሰቢያ እምነት የሚጣልበት ነው፣ ተሞክሮ የሌላቸውን ጠቢባን ያደርጋል።” (መዝሙር 19:7 NW ) ኒኮልም ምንም ሳታሰልስ በየሳምንቱ በሚደረጉት በአምስቱም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ትገኛለች። ለእነዚህ ስብሰባዎች ለመዘጋጀት ከሁለት እስከ ሦስት የሚደርስ ሰዓት ትመድባለች።​—⁠ኤፌሶን 5:15, 16

9. ወጣቶች ‘በጥበብ ማደግ’ የሚችሉት እንዴት ነው?

9 የወጣትነት ዕድሜ ‘ብቸኛውን እውነተኛ አምላክና እርሱ የላከውን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማወቅ’ አመቺ ጊዜ ነው። (ዮሐንስ 17:3) የቀልድ መጽሐፍ በማንበብ፣ ቴሌቪዥን በመመልከት፣ የቪዲዮ ጨዋታዎችን በመጫወት ወይም ኢንተርኔት በመቃኘት ጊዜያቸውን የሚያጠፉ ወጣቶችን ታውቅ ይሆናል። መሪያችን የተወልን ፍጹም ምሳሌ እያለልህ እነርሱን የምትመስልበት ምን ምክንያት አለህ? ልጅ በነበረበት ጊዜ ስለ ይሖዋ መማር ያስደስተው ነበር። ይህስ ምን ውጤት አስገኘለት? ኢየሱስ ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍቅር ስለነበረው “በጥበብ . . . ያድግ ነበር።” (ሉቃስ 2:52) አንተም ማደግ ትችላለህ።

“አንዳችሁ ለአንዳችሁ ተገዙ”

10. የቤተሰብ ሕይወት ሰላምና ደስታ የሚገኝበት እንዲሆን ምን ሊረዳ ይችላል?

10 ቤት ሰላምና እርካታ የሚገኝበት ቦታ ወይም ግጭትና ጠብ የሚካሄድበት ጦር ሜዳ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 21:19፤ 26:21) የክርስቶስን አመራር መቀበላችን በቤተሰብ ውስጥ ሰላምና ደስታ እንዲሰፍን ያደርጋል። እንዲያውም ኢየሱስ የተወው ምሳሌ በቤተሰብ ውስጥ ለሚኖረው ዝምድና ሞዴል ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ቅዱሳን ጽሑፎች እንዲህ ይላሉ:- “ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ [“አንዳችሁ ለአንዳችሁ ተገዙ፣” አ.መ.ት ]። ሚስቶች ሆይ፣ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና። . . . ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ።” (ኤፌሶን 5:21-25) ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላስይስ ጉባኤ “ልጆች ሆይ፣ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ” በማለት ጽፏል።​—⁠ቆላስይስ 3:18-20

11. አንድ ባል የክርስቶስ አመራር እውን እንደሆነለት ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው?

11 ይህን ምክር መከተል ማለት ባል ቤተሰቡን ይመራል፣ ሚስቱ በታማኝነት ትደግፈዋለች እንዲሁም ልጆች ወላጆቻቸውን ይታዘዛሉ ማለት ነው። ያም ሆኖ የወንድ ራስነት ደስታ የሚያመጣው ተገቢ በሆነ መንገድ ሲሠራበት ብቻ ነው። አንድ ጥበበኛ የሆነ ባል የእርሱ ራስና መሪ የሆነውን የክርስቶስ ኢየሱስን ምሳሌ በመኮረጅ የራስነት ሥልጣንን እንዴት መጠቀም እንደሚገባ መማር አለበት። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ “ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን” የተሰጠ ቢሆንም እንኳ ወደ ምድር የመጣው “ሊያገለግል . . . እንጂ እንዲያገለግሉት” አይደለም። (ኤፌሶን 1:22፤ ማቴዎስ 20:28) በተመሳሳይም አንድ ክርስቲያን ባል የራስነት ሥልጣኑን የሚጠቀምበት የራሱን ጥቅም ብቻ ለማሟላት ሳይሆን የሚስቱንና የልጆቹን ማለትም የመላውን ቤተሰብ ፍላጎት ለማሟላት ነው። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5) ራሱ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ያንጸባረቀውን አምላካዊ ባሕርያት ለመኮረጅ ይጥራል። እንደ ኢየሱስ የዋህና ትሑት ነው። (ማቴዎስ 11:28-30) ስህተት በሚሠራበት ጊዜ “ይቅርታ” ወይም “አንቺ ትክክል ነሽ” ብሎ ለመናገር አይከብደውም። ግሩም ምሳሌነቱ ሚስቱ “ረዳት፣” “ማሟያ” እና “አጋር [አ.መ.ት ]” እንድትሆነው እንዲሁም እንዲህ ካለው ሰው ለመማርና ከእርሱ ጋር ሆና ለመሥራት እንዲቀላት ይረዳታል።​—⁠ዘፍጥረት 2:20 NW፤ ሚልክያስ 2:14

12. አንዲት ሚስት ለራስነት ሥልጣን የወጣውን መሠረታዊ ሥርዓት እንድታከብር የሚረዳት ምንድን ነው?

12 ሚስትም በበኩሏ ለባሏ መገዛት ይኖርባታል። ይሁን እንጂ በዓለም መንፈስ ከተሸነፈች ለራስነት ሥልጣን መሠረታዊ ሥርዓት ያላት አመለካከት ሊሸረሸርና ለወንድ መገዛት የሚለው ሐሳብ የማይዋጥ ሆኖ ልታገኘው ትችላለች። ቅዱሳን ጽሑፎች ወንድ ጨቋኝ መሆን እንዳለበት አይናገሩም። ሆኖም ሚስቶች ለባሎቻቸው መገዛት እንዳለባቸው ይናገራሉ። (ኤፌሶን 5:24) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በቤተሰብ ውስጥ ኃላፊነት መሸከም ያለበት ባል ወይም አባት እንደሆነ ይናገራል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ቤተሰብ ሰላማዊና ሥርዓታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያበረክታል።​—⁠ፊልጵስዩስ 2:5

13. ተገዥነትን በተመለከተ ኢየሱስ ለልጆች ምን ምሳሌ ትቷል?

13 ልጆች ለወላጆቻቸው መታዘዝ ይኖርባቸዋል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ ይሆናል። የ12 ዓመቱ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ለሦስት ቀናት በቆየበት ጊዜ ከተከሰተው ሁኔታ በኋላ “ከእነርሱም [ከወላጆቹ] ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፣ ይታዘዝላቸውም ነበር።” (ሉቃስ 2:51) ልጆች ለወላጆቻቸው የሚገዙ መሆናቸው በቤተሰብ ውስጥ ሰላምና ስምምነት እንዲሰፍን አስተዋጽዖ ያበረክታል። ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ለክርስቶስ አመራር ተገዥ በሚሆኑበት ጊዜ ቤተሰቡ ደስተኛ ይሆናል።

14, 15. በቤት ውስጥ ተፈታታኝ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ ችግሩን ለመወጣት ምን ሊረዳን ይችላል? ምሳሌ ስጥ።

14 በቤት ውስጥ ተፈታታኝ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜም እንኳ መፍትሔ ለማግኘት ቁልፉ የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅና መመሪያውን መቀበል ነው። ለምሳሌ ያህል የ35 ዓመቱ ጄሪ እና በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ልጅ ያላት ላና በተጋቡ ጊዜ ሁለቱም ያልጠበቁት አንድ ችግር ተፈጠረ። ጄሪ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “ጥሩ ራስ ሆኜ ለመገኘት ሌሎች ቤተሰቦች ስኬታማ እንዲሆኑ የረዷቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋል እንዳለብኝ አውቅ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ በማውልበት ጊዜ ከፍተኛ ጥበብና ማስተዋል መጠቀም እንዳለብኝ ተረዳሁ።” የእንጀራ ልጁ በእርሷና በእናቷ መካከል እንደገባ ጋሬጣ ሆኖ ታያት። በዚህም የተነሳ በጣም ጠላችው። ጄሪ ይህ አመለካከቷ በምትናገረውና በምታደርገው ነገር ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ለመረዳት አስተዋይ መሆን አስፈልጎት ነበር። ታዲያ ሁኔታውን ያስተካከለው እንዴት ነው? ጄሪ እንዲህ በማለት ይመልሳል:- “ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ እኔ ከእንጀራ ልጄ ጋር ጥሩ ዝምድና በመመሥረቱ ላይ ብቻ እንዳተኩርና ምክርና ተግሣጽ የመስጠቱ የወላጅነት ኃላፊነት የላና እንዲሆን በጋራ ተስማማን። እንዲህ ማድረጋችን ከጊዜ በኋላ ጥሩ ውጤት አስገኘ።”

15 በቤት ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ የቤተሰቡ አባላት በሚናገሩት ቃልና በሚፈጽሙት ድርጊት ላይ ተጽዕኖ ያደረገው ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ አስተዋይ መሆን ይኖርብናል። በተጨማሪም አምላካዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተገቢ በሆነ መንገድ ሥራ ላይ ለማዋል ጠቢብ መሆን ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ደም ይፈስሳት የነበረችው ሴት ለምን እንደነካችው በሚገባ ተገንዝቧል። በዚህም የተነሳ በጥበብና በርኅራኄ ይዟታል። (ዘሌዋውያን 15:25-27፤ ማርቆስ 5:30-34) ጥበብና ማስተዋል የመሪያችን ዓይነተኛ ባሕርያት ናቸው። (ምሳሌ 8:12) እኛም እንደ እርሱ ብናደርግ ደስተኞች እንሆናለን።

‘መንግሥቱን ፈልጉ’

16. በሕይወታችን ውስጥ ማስቀደም ያለብን ነገር ምንድን ነው? ኢየሱስ ይህንን ምሳሌ በመሆን ያሳየው እንዴት ነው?

16 ኢየሱስ የእርሱን አመራር የሚቀበሉ ሁሉ በሕይወታቸው ውስጥ ምን ማስቀደም እንዳለባቸው በግልጽ ተናግሯል። “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:33) በተጨማሪም ራሱ ምሳሌ በመሆን ይህን ማድረግ የምንችልበትን መንገድ አሳይቶናል። ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ለ40 ቀናት በመጾም፣ በማሰላሰልና በመጸለይ ያሳለፈው ጊዜ ሊገባደድ ተቃርቦ ሳለ አንድ ፈተና ገጠመው። ሰይጣን ዲያብሎስ ‘በዓለም መንግሥታት ሁሉ’ ላይ እንዲገዛ ግብዣ አቀረበለት። ኢየሱስ፣ ዲያብሎስ ያቀረበለትን ግብዣ ተቀብሎ ቢሆን ኖሮ ምን ዓይነት ሕይወት ሊኖረው ይችል እንደነበረ ገምት! ሆኖም ክርስቶስ ትኩረቱ ያረፈው የአባቱን ፈቃድ በማድረጉ ላይ ነበር። በተጨማሪም በሰይጣን ዓለም ውስጥ የሚገኘው እንዲህ ያለው ሕይወት ለዘለቄታው እንደማይቀጥል ያውቅ ነበር። ሰይጣን ያቀረበለትን ግብዣ ወዲያው ውድቅ በማድረግ “ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል” በማለት ተናገረ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር።” (ማቴዎስ 4:2, 8-10, 17) ክርስቶስ በቀሪው ምድራዊ የሕይወት ዘመኑ ሁሉ የአምላክ መንግሥት የሙሉ ጊዜ አዋጅ ነጋሪ ሆኖ ሠርቷል።

17. የመንግሥቱን ጉዳዮች በሕይወታችን ውስጥ እንዳስቀደምን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

17 እኛም መሪያችን የተወልንን ምሳሌ መከተልና የሰይጣን ዓለም ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራን የሕይወታችን ዋነኛ ግብ አድርገን እንድንከታተል የሚያቀርብልንን ማባበያ መቃወም ይኖርብናል። (ማርቆስ 1:17-21) የመንግሥቱን ጉዳዮች በሁለተኛ ደረጃ አስቀምጠን በዓለማዊ ጉዳዮች በእጅጉ ብንጠላለፍ ምንኛ ሞኝነት ነው! ኢየሱስ የመንግሥቱን ስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በአደራ ሰጥቶናል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) አዎን፣ የቤተሰብ ወይም ሌሎች ኃላፊነቶች ይኖሩብን ይሆናል። ሆኖም እንድንሰብክና እንድናስተምር የተሰጠንን ክርስቲያናዊ ኃላፊነት ለመፈጸም ምሽቶችን ጨምሮ ቅዳሜና እሁድን ለመጠቀም አንጓጓምን? በ2001 የአገልግሎት ዓመት 780, 000 የሚያህሉ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ወይም አቅኚዎች ሆነው ማገልገል መቻላቸው ምንኛ የሚያበረታታ ነው!

18. በአገልግሎት ደስታ እንድናገኝ የሚረዳን ምንድን ነው?

18 የወንጌል ዘገባዎች ኢየሱስ ከአንጀቱ የሚራራና የተግባር ሰው እንደሆነ አድርገው ይገልጹታል። አብረውት የነበሩት ሰዎች በመንፈሳዊ መራባቸውን በተመለከተ ጊዜ አዘነላቸውና የእርዳታ እጁን ዘረጋላቸው። (ማርቆስ 6:31-34) ለሌሎች ባለን ፍቅር ተገፋፍተንና እነርሱን ለመርዳት በቅን ፍላጎት ተነሳስተን በአገልግሎት ስንካፈል አገልግሎታችን የሚያስደስት ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለውን ፍላጎት እንዴት ማዳበር እንችላለን? “በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለሁ” ይላል ጄይሰን የተባለ አንድ ወጣት፣ “አገልግሎት እምብዛም አያስደስተኝም ነበር።” ለዚህ ሥራ ፍቅር እንዲያዳብር የረዳው ምንድን ነው? ጄይሰን እንዲህ በማለት ይመልሳል:- “ሁልጊዜ ቅዳሜ ጠዋት የቤተሰባችን ፕሮግራም አገልግሎት ነበር። ይህ እኔን በጣም ጠቅሞኛል። ምክንያቱም በአገልግሎት ይበልጥ በተካፈልኩ መጠን አገልግሎቱ የሚያስገኛቸውን መልካም ነገሮች ይበልጥ እየተመለከትኩና ይበልጥ ደስታ እያገኘሁበት መጣሁ።” እኛም በአገልግሎት ዘወትር በትጋት መካፈል ይገባናል።

19. የክርስቶስን አመራር በተመለከተ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት?

19 የክርስቶስን አመራር መቀበል በእርግጥም መንፈስን የሚያነቃቃና የሚክስ ነው። የክርስቶስን አመራር ከተቀበልን የወጣትነት ዕድሜ በእውቀትና በጥበብ የምናድግበት ወቅት ይሆናል። የቤተሰብ ኑሮ ሰላምና ደስታ የሰፈነበት፣ አገልግሎትም ደስታና እርካታ የሚገኝበት ይሆናል። እንግዲያው በተቻለን መጠን የዕለት ተዕለት ሕይወታችንም ሆነ የምናደርጋቸው ውሳኔዎች የክርስቶስ አመራር እውን እንደሆነልን የሚያሳዩ እንዲሆኑ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (ቆላስይስ 3:23, 24) ይሁንና ኢየሱስ ክርስቶስ በሌላ አቅጣጫም ማለትም በክርስቲያን ጉባኤም አመራር ይሰጣል። የሚቀጥለው ርዕስ ከዚህ ዝግጅት እንዴት መጠቀም እንደምንችል ያብራራልናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።

ታስታውሳለህ?

• አምላክ የሾመልንን መሪ መከተላችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

• ወጣቶች የኢየሱስን አመራር መከተል እንደሚፈልጉ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

• ቤተሰቦች ለክርስቶስ አመራር ራሳቸውን ማስገዛታቸው በቤተሰብ ሕይወታቸው ውስጥ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

• በአገልግሎት የምናደርገው ተሳትፎ የክርስቶስ አመራር እውን እንደሆነልን ሊያሳይ የሚችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የወጣትነት ዕድሜ አምላክንና የተሾመውን መሪያችንን ለማወቅ አመቺ ጊዜ ነው

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለክርስቶስ አመራር ተገዥ መሆን በቤተሰብ ውስጥ ደስታ ያሰፍናል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ መንግሥቱን አስቀድሟል። አንተስ?