በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጠመቅ ለምን አስፈለገ?

መጠመቅ ለምን አስፈለገ?

መጠመቅ ለምን አስፈለገ?

“ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . እያጠመቃችኋቸው . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”​—⁠ማቴዎስ 28:​19, 20

1, 2. (ሀ) አንዳንድ ጥምቀቶች የተከናወኑት እንዴት ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ነበር? (ለ) ጥምቀትን በሚመለከት ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?

 የፍራንካውያን ንጉሥ ሻርለማኝ ድል አድርጎ የያዛቸውን ሳክሰናውያንን ከ775-77 እዘአ በጅምላ እንዲጠመቁ አስገድዷቸው ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ጆን ሎርድ “ወደ ስመ ክርስትና እንዲለወጡ አስገደዳቸው” በማለት ጽፏል። በተመሳሳይም የሩሲያው ገዥ ቀዳማዊ ቭላድሚር የግሪክ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የሆነችን አንዲት ልዕልት በ987 እዘአ ካገባ በኋላ ዜጎቹ “ክርስቲያን” መሆን እንዳለባቸው ውሳኔ በማሳለፍ አስፈላጊ ከሆነ ሰይፍ ተጠቅመው ሕዝቡን በጅምላ እንዲያጠምቋቸው የሚያዝ ድንጋጌ አውጥቶ ነበር!

2 እንዲህ ያሉት ጥምቀቶች ተገቢ ናቸውን? እውነተኛ ትርጉምስ አላቸውን? ማንኛውም ሰው መጠመቅ ይችላል?

ጥምቀት​—⁠እንዴት?

3, 4. ውኃ መርጨት ወይም ራስ ላይ ማፍሰስ ትክክለኛ ክርስቲያናዊ ጥምቀት ያልሆነው ለምንድን ነው?

3 ሻርለማኝ እና ቀዳማዊ ቭላድሚር ሰዎች እንዲጠመቁ ሲያስገድዱ እነዚህ መሪዎች ከአምላክ ቃል ጋር የሚቃረን ተግባር መፈጸማቸው ነበር። እንዲያውም ውኃ በመርጨት፣ ራስ ላይ ውኃ በማፍሰስ ሌላው ቀርቶ የቅዱሳን ጽሑፎችን እውቀት ሳያገኙ ሰዎችን ውኃ ውስጥ በማጥለቅ ማጥመቅ አንዳች ፋይዳ የለውም።

4 የናዝሬቱ ኢየሱስ በ29 እዘአ ወደ መጥምቁ ዮሐንስ በሄደ ጊዜ ምን እንደተከናወነ ልብ በል። ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ሰዎችን ያጠምቅ ነበር። ሰዎቹ ለመጠመቅ ወደ እርሱ የሚመጡት በራሳቸው ፈቃድ ተነሳስተው ነበር። ዮሐንስ ሰዎቹን ያጠምቅ የነበረው በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ እንዲቆሙ አድርጎ ከወንዙ ውኃ እየጨለፈ ራሳቸው ላይ በማፍሰስ ወይም እላያቸው ላይ ውኃውን በመርጨት ነበርን? ዮሐንስ ኢየሱስን ያጠመቀው እንዴት ነበር? ማቴዎስ እንደዘገበው ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ “ወዲያው ከውኃ ወጣ።” (ማቴዎስ 3:​16) በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ እንዲጠልቅ በመደረጉ በውኃው ሙሉ በሙሉ ተሸፍኖ ነበር። በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስ ለአምላክ ያደረው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ የተጠመቀበትን ሁኔታ ሲዘግብ “ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ” ይላል። ከዚያም “ከውኃውም ከወጡ በኋላ . . . ” በማለት ይቀጥላል። ስለሆነም የኢየሱስም ሆነ የደቀ መዛሙርቱ ጥምቀት ውኃ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ጠልቆ መውጣትን የሚጠይቅ ነበር።​—⁠ሥራ 8:​38, 39

5. የጥንት ክርስቲያኖች ሰዎችን ያጠምቁ የነበረው እንዴት ነው?

5 “ማጥመቅ፣” “ጥምቀት” ወዘተ ተብለው የተተረጎሙት ግሪክኛ ቃላት ውኃ ውስጥ ማጥለቅን፣ መንከርን ወይም ደግሞ መዝፈቅን ያመለክታሉ። ስሚዝስ ባይብል ዲክሽነሪ “ጥምቀት የሚለው ቃል ተገቢውና ቀጥተኛ ትርጉሙ ማጥለቅ የሚል ነው” በማለት ይናገራል። ስለሆነም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “አጥላቂው ዮሐንስ” እና “ነካሪው ዮሐንስ” በማለት ተርጉመዋል። (ማቴዎስ 3:​1 ሮተርሃም፣ ዲያግሎት ኢንተርሊኒየር) በኦውግስተስ ኔአንደር የተዘጋጀው ሂስቶሪ ኦቭ ዘ ክሪስቺያን ሪሊጅን ኤንድ ቸርች ዱሪንግ ዘ ስሪ ፈርስት ሴንቸሪስ የተባለው ጽሑፍ “ጥምቀት መጀመሪያ ይከናወን የነበረው በማጥለቅ ነበር” ይላል። ስመ ጥር የፈረንሳይ የጽሑፍ ሥራ የሆነው ላሩስ ዱ ቨንቲዬም ሲዬክል (1928 ፓሪስ) “የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ውኃ በሚገኝበት ቦታ ሁሉ ውኃ ውስጥ እየጠለቁ ይጠመቁ ነበር” በማለት አስተያየት ሰጥቷል። እንዲሁም ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ “በጥንት ቤተ ክርስቲያን ጥምቀት ይከናወን የነበረው በማጥለቅ እንደነበር ምንም ጥያቄ የለውም” በማለት ገልጿል። (1967 ጥራዝ 2 ገጽ 56) ስለሆነም ዛሬ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን የሚደረገው ጥምቀት ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በማጥለቅ የሚከናወን በፈቃደኝነት የሚወሰድ እርምጃ ነው።

ለጥምቀት የሚያበቃ አዲስ ምክንያት

6, 7. (ሀ) ዮሐንስ ያጠምቅ የነበረበት ዓላማ ምን ነበር? (ለ) የኢየሱስ ተከታዮች ያከናወኑት ጥምቀት ምን አዲስ ገጽታ ነበረው?

6 ዮሐንስ ያጠምቅበት የነበረው ዓላማ የኢየሱስ ተከታዮች ያከናውኑት ከነበረው ጥምቀት የተለየ ነበር። (ዮሐንስ 4:​1, 2) ዮሐንስ ሰዎችን ያጠመቀው በሕጉ ላይ ከፈጸሙት ኃጢአት ንስሐ መግባታቸውን በሕዝብ ፊት ለማሳየት ነበር። a (ሉቃስ 3:​3) ይሁን እንጂ የኢየሱስ ተከታዮች ያከናወኑት ጥምቀት ከዚህ የተለየ ምክንያት ነበረው። በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ሐዋርያው ጴጥሮስ “ንስሐ ግቡ፣ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ” በማለት አድማጮቹን አሳስቧቸው ነበር። (ሥራ 2:​37-41) ጴጥሮስ ይናገር የነበረው ለአይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት ለተለወጡ ሰዎች ቢሆንም እንኳ በሕጉ ላይ ከተፈጸመው ኃጢአት ንስሐ መግባትን ለማሳየት ስለሚከናወን ጥምቀት መናገሩ ወይም በኢየሱስ ስም መጠመቅ ኃጢአትን አጥቦ እንደሚያስወግድ መግለጹም አልነበረም።​—⁠ሥራ 2:​10

7 በዚህ ወቅት ጴጥሮስ ‘ከመንግሥቱ መክፈቻዎች’ መካከል አንዱን ተጠቅሟል። ለምን ዓላማ? አድማጮቹ ወደ አምላክ መንግሥት የመግባት አጋጣሚ የተከፈተላቸው መሆኑን የሚገልጸውን እውቀት ለመግለጥ ተጠቅሞበታል። (ማቴዎስ 16:​19) አይሁዳውያን ኢየሱስን እንደ መሲሕ አድርገው ለመቀበል አሻፈረን ብለው ስለነበር ንስሐ መግባታቸውና በእርሱ ላይ እምነት ማዳበራቸው የአምላክን ምሕረት ለመጠየቅ ብሎም ለማግኘት የሚያበቃ አዲስና ወሳኝ ምክንያት ነበር። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በውኃ በመጠመቅ እንዲህ ያለው እምነት እንዳላቸው በሕዝብ ፊት ማሳየት ይችሉ ነበር። በዚህ መንገድ በክርስቶስ አማካኝነት በግለሰብ ደረጃ ለአምላክ ያደረጉትን ውሳኔ በሕዝብ ፊት ያሳያሉ። ዛሬም የአምላክን ሞገስ ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ተመሳሳይ እምነት ማዳበር፣ ለይሖዋ አምላክ ራሳቸውን መወሰንና ለልዑሉ አምላክ ያለምንም ገደብ ራሳቸውን መወሰናቸውን ለማሳየት ክርስቲያናዊውን ጥምቀት መቀበል ይገባቸዋል።

ትክክለኛ እውቀት የግድ አስፈላጊ ነው

8. ማንኛውም ሰው ለክርስቲያናዊ ጥምቀት ብቁ የማይሆነው ለም​ንድን ነው?

8 ማንኛውም ሰው ለክርስቲያናዊ ጥምቀት ብቁ አይሆንም። ኢየሱስ ተከታዮቹን “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት አዝዟቸዋል። (ማቴዎስ 28:​19, 20) ሰዎች ከመጠመቃቸው በፊት ‘ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያዘዛቸውን ነገሮች በሙሉ እንዲጠብቁ መማር’ ይገባቸዋል። ስለሆነም በአምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ እምነት የሌላቸው ሰዎች እንዲጠመቁ ማስገደድ ዋጋ ቢስ ከመሆኑም በላይ ኢየሱስ ለእውነተኛ ተከታዮቹ ከሰጣቸው ተልዕኮ ጋር የሚቃረን ነው።​—⁠ዕብራውያን 11:​6

9. ‘በአብ ስም’ መጠመቅ ሲባል ምን ማለት ነው?

9 ‘በአብ ስም’ መጠመቅ ሲባል ምን ማለት ነው? የጥምቀት እጩው የሰማዩ አባታችን ያለውን ቦታና ሥልጣን አውቆ ይቀበላል ማለት ነው። በዚህም የተነሳ ይሖዋ አምላክ ፈጣሪያችን፣ ‘በምድር ሁሉ ላይ ልዑል’ እንዲሁም የአጽናፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ መሆኑ ይታወቃል ማለት ነው።​—⁠መዝሙር 83:​18፤ ኢሳይያስ 40:​28፤ ሥራ 4:​24

10. ‘በወልድ ስም’ መጠመቅ ሲባል ምን ማለት ነው?

10 ‘በወልድ ስም’ መጠመቅ ሲባል ኢየሱስ የአምላክ አንድያ ልጅ እንደሆነ አውቆ ቦታውንና ሥልጣኑን መቀበል ማለት ነው። (1 ዮሐንስ 4:​9) ለመጠመቅ ብቁ የሚሆኑ ሰዎች አምላክ “ለብዙዎች ቤዛ” አድርጎ የሰጠው ኢየሱስ መሆኑን መቀበል ይኖርባቸዋል። (ማቴዎስ 20:​28፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:​5, 6) በተጨማሪም የጥምቀት እጩዎች አምላክ ለልጁ የሰጠውን “ከፍ” ያለ ቦታ አውቀው መቀበል ይገባቸዋል።​—⁠ፊልጵስዩስ 2:​8-11፤ ራእይ 19:​16

11. “በመንፈስ ቅዱስ ስም” መጠመቅ ምን ያመለክታል?

11 “በመንፈስ ቅዱስ ስም” የመጠመቅ ትርጉም ምንድን ነው? ይህ የጥምቀት ዕጩዎች መንፈስ ቅዱስ ይሖዋ ዓላማውን ለማስፈጸም በተለያዩ መንገዶች የሚጠቀምበት አንቀሳቃሽ ኃይሉ መሆኑን ይቀበላሉ ማለት ነው። (ዘፍጥረት 1:​2፤ 2 ሳሙኤል 23:​1, 2፤ 2 ጴጥሮስ 1:​21) ለመጠመቅ ብቃቱን የሚያሟሉ ዕጩዎች መንፈስ ቅዱስ “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር” እንዲያስተውሉ፣ የመንግሥቱን የስብከት ሥራ እንዲያከናውኑ እንዲሁም እንደ “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት” ያሉትን የመንፈስ ፍሬዎች እንዲያንጸባርቁ እንደሚረዳቸው ያውቃሉ።​—⁠1 ቆሮንቶስ 2:​10፤ ገላትያ 5:​22, 23፤ ኢዩኤል 2:​28, 29

ንስሐ የመግባትና የመለወጥ አስፈላጊነት

12. ክርስቲያናዊ ጥምቀት ንስሐ ከመግባት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?

12 ጥምቀት ንስሐ ከመግባት ጋር የሚዛመድ በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው እርምጃ ነው። ይህ አባባል ፍጹም ሰው የነበረውን የኢየሱስን ጥምቀት አይጨምርም። ንስሐ ስንገባ በሠራነው ወይም ሳናደርግ በቀረነው ነገር ከልብ እንጸጸታለን ወይም እናዝናለን። አምላክን ለማስደሰት የፈለጉ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን በክርስቶስ ላይ ለሠሩት ኃጢአት ንስሐ መግባት ነበረባቸው። (ሥራ 3:​11-19) በቆሮንቶስ ይኖሩ የነበሩ ከአሕዛብ የመጡ አንዳንድ አማኞች ከዝሙት፣ ከጣዖት አምልኮ፣ ከስርቆትና ከሌሎች ከባድ ኃጢአቶች ንስሐ ገብተዋል። ንስሐ በመግባታቸው ምክንያት በኢየሱስ ደም ‘ታጥበዋል’፤ ለአምላክ አገልግሎት ‘ተቀድሰዋል’ ወይም ተለይተዋል፤ እንዲሁም በክርስቶስ ስምና በአምላክ መንፈስ “ጸድቀዋል።” (1 ቆሮንቶስ 6:​9-11) ንስሐ መግባት በጎ ሕሊና ለማግኘትና ኃጢአት ከሚያሳድረው የጥፋተኝነት ስሜት ከአምላክ ዘንድ እፎይታ የሚያስገኝ ጠቃሚ እርምጃ ነው።​—⁠1 ጴጥሮስ 3:​21

13. በጥምቀት ረገድ መለወጥ ምን ማድረግን ይጨምራል?

13 ተጠምቀን የይሖዋ ምሥክር ከመሆናችን በፊት ለውጥ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። መለወጥ ክርስቶስ ኢየሱስን ለመከተል ከሙሉ ልብ የመነጨ ውሳኔ ያደረገ ሰው በፈቃደኝነት የሚወስደው እርምጃ ነው። እንዲህ ያለ እርምጃ የሚወስዱ ግለሰቦች ቀድሞ ይከተሉት የነበረውን የተሳሳተ ጎዳና በመተው በአምላክ ፊት ትክክል የሆነውን ለማድረግ ይወስናሉ። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ መለወጥን ለማመልከት የገቡት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ግሦች ጀርባን መስጠት፣ ዞር ማለት የሚል ትርጉም አላቸው። ይህ እርምጃ ከተሳሳተ ጎዳና ወደ አምላክ መዞርን ያመለክታል። (1 ነገሥት 8:​33, 34) መለወጥ “ለንስሐ የሚገባ ነገር” ማድረግን ይጠይቃል። (ሥራ 26:​20) በሐሰት አምልኮ መካፈልን መተው፣ ከአምላክ ትእዛዛት ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስና ለይሖዋ ብቻ የተወሰነ አምልኮ ማቅረብን ይጠይቃል። (ዘዳግም 30:​2, 8-10፤ 1 ሳሙኤል 7:​3) መለወጥ በአስተሳሰባችን፣ በዓላማችን እንዲሁም በባሕርያችን ላይ ለውጥ እንድናሳይ ያደርገናል። (ሕዝቅኤል 18:​31) አምላካዊ ያልሆኑ ባሕርያትን በአዲሱ ሰው ስንተካ ‘ተመልሰናል’ ለማለት እንችላለን።​—⁠ሥራ 3:​19፤ ኤፌሶን 4:​20-24፤ ቆላስይስ 3:​5-14

በሙሉ ነፍስ ራስን ለአምላክ መወሰን ያስፈልጋል

14. የኢየሱስ ተከታዮች ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸው ምን ያመለክታል?

14 የኢየሱስ ተከታዮች ከመጠመቃቸው በፊት በሙሉ ነፍስ ራሳቸውን ለአምላክ መወሰን ይገባቸዋል። ራስን ለአምላክ መወሰን ለአንድ ቅዱስ ዓላማ ራስን መለየትን ያመለክታል። ይህ እርምጃ በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ ለዘላለም እርሱን ብቻ ለማምለክ ያደረግነውን ውሳኔ ለይሖዋ በጸሎት መግለጽ ይኖርብናል። (ዘዳግም 5:​9, 10) እርግጥ ነው፣ ራሳችንን የምንወስነው ለአምላክ ለራሱ እንጂ ለአንድ ሥራ ወይም ለሰው አይደለም።

15. የጥምቀት እጩዎች የሚጠመቁት ለምንድን ነው?

15 በክርስቶስ በኩል ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ሕይወታችንን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሠፍሮ ከሚገኘው መለኮታዊ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመጠቀም ቁርጥ ውሳኔ ማድረጋችንን የሚያሳይ ነው። የጥምቀት እጩዎች ይህን ውሳኔያቸውን ለማሳየት ልክ ኢየሱስ ራሱን ለአምላክ ማቅረቡን ለማሳየት በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ እንደተጠመቀ ሁሉ እነርሱም በውኃ ይጠመቃሉ። (ማቴዎስ 3:​13) ኢየሱስ በዚህ ከፍተኛ ግምት በሚሰጠው ወቅት ላይ መጸለዩ ትኩረት የሚስብ ነው።​—⁠ሉቃስ 3:​21, 22

16. ሰዎች ሲጠመቁ በምናይበት ጊዜ ደስታችንን በተገቢው መንገድ መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው?

16 የኢየሱስ ጥምቀት አስደሳች ወቅት ቢሆንም አክብሮት የሚሰጠው ክንውን ነበር። ዛሬ የሚከናወነው ክርስቲያናዊ ጥምቀትም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው። ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሰዎች በሚጠመቁበት ጊዜ ደስታችንን አክብሮት በሚንጸባረቅበት ጭብጨባና ሞቅ ባለ ምስጋና መግለጽ እንችል ይሆናል። ሆኖም ይህ የእምነት መግለጫ ካለው ቅድስና አንጻር ደስታችንን በእልልታ፣ በፉጨትና ይህን በመሳሰሉ መንገዶች ከመግለጽ እንቆጠባለን። ደስታችንን መግለጽ የሚኖርብን አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ መሆን አለበት።

17, 18. ግለሰቦች ለመጠመቅ ብቁ መሆን አለመሆናቸውን ለመወሰን የሚረዳው ምንድን ነው?

17 የይሖዋ ምሥክሮች ሕፃናትን በመርጨት ወይም ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀት የሌላቸውን ሰዎች አስገድደው በጅምላ እንደሚያጠምቁ ሰዎች ማንንም ሰው አስገድደው አያጠምቁም። እንዲያውም ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃት የማያሟሉ ሰዎች እንዲጠመቁ አይፈቅዱም። ሌላው ይቅርና አንድ ሰው ያልተጠመቀ የምሥራቹ ሰባኪ ከመሆኑ በፊት ክርስቲያን ሽማግሌዎች ግለሰቡ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በትክክል የተረዳ፣ ከትምህርቶቹ ጋር በሚስማማ መንገድ የሚመላለስ መሆኑንና “ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንዱ ለመሆን በእርግጥ ትፈልጋለህ?” ለሚለው ጥያቄ አዎንታዊ መልስ መስጠቱን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ።

18 በአብዛኛው በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ በማድረግ ላይ ያሉ ሰዎች መጠመቅ እንደሚፈልጉ በሚገልጹበት ጊዜ ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ አማኞች መሆናቸውንና ለመጠመቅ የሚያበቃቸውን መለኮታዊ መስፈርት ያሟሉ እንደሆነ ለማረጋገጥ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከግለሰቦቹ ጋር ውይይት ያደርጋሉ። (ሥራ 4:​4፤ 18:​8) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለተመሠረቱ ከ100 ለሚበልጡ ጥያቄዎች በግል የሚሰጡት መልስ ሽማግሌዎች ተጠያቂዎቹ ለጥምቀት የሚያበቁትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ያሟሉ እንደሆኑና እንዳልሆኑ ለመወሰን ያስችላቸዋል። አንዳንዶች ብቃቱን ስለማያሟሉ ለክርስቲያናዊ ጥምቀት ብቁ ሳይሆኑ ይቀራሉ።

ወደኋላ እንድትል የሚያደርግህ ነገር ይኖር ይሆን?

19. ከዮሐንስ 6:​44 አንጻር ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙት እነማን ናቸው?

19 ተገድደው በጅምላ የተጠመቁ ብዙ ሰዎች ሲሞቱ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ተነግሯቸው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ፈለጉን የሚከተሉ ሰዎችን በማስመልከት “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 6:​44) ይሖዋ በሰማያዊው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙትን 144, 000 ሰዎች ወደ ክርስቶስ ስቧቸዋል። ሰዎችን በማስገደድ የሚፈጸመው ጥምቀት አንድን ሰው አምላክ ላዘጋጀው ለዚህ ክብራማ ዝግጅት ፈጽሞ ሊያበቃው አይችልም።​—⁠ሮሜ 8:​14-17፤ 2 ተሰሎንቄ 2:​13፤ ራእይ 14:​1

20. እስከ አሁን ያልተጠመቁ አንዳንድ ሰዎች ምን ነገር ሊረዳቸው ይችላል?

20 “ከታላቁ መከራ” በሕይወት አልፈው በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ እጅግ ብዙ ሰዎች በተለይ ከ1930ዎቹ አጋማሽ አንስቶ ከኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ጋር ተቀላቅለዋል። (ራእይ 7:​9, 14፤ ዮሐንስ 10:​16) ሕይወታቸውን ከአምላክ ቃል ጋር ያስማሙና ‘በፍጹም ልባቸው፣ ነፍሳቸው፣ ኃይላቸውና አሳባቸው’ እሱን የሚወድዱ በመሆናቸው ለጥምቀት ብቁ ይሆናሉ። (ሉቃስ 10:​25-28) ምንም እንኳን አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ‘አምላክን በመንፈስና በእውነት እንደሚያመልኩ’ ቢገነዘቡም እንደ ኢየሱስ በመጠመቅ ለአምላክ ልባዊ ፍቅር እንዳላቸውና ሙሉ በሙሉ ለእርሱ ያደሩ እንደሆኑ የሚያሳይ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ ይላሉ። (ዮሐንስ 4:​23, 24፤ ዘዳግም 4:​24፤ ማርቆስ 1:​9-11) ይህን አስፈላጊ እርምጃ በቀጥታ በመጥቀስ ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረብ ከአምላክ ቃል ጋር ሙሉ በሙሉ ተስማምቶ ለመኖር የሚያስችል ኃይልና ድፍረት እንዲያገኙና ያለምንም ገደብ ራሳቸውን ለይሖዋ አምላክ ወስነው እንዲጠመቁ ሊረዳቸው ይችላል።

21, 22. አንዳንዶች ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው ከመጠመቅ ወደኋላ የሚሉባቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

21 አንዳንዶች በዓለም ጉዳዮች ወይም ሃብት በማሳደድ ከልክ በላይ ከመጠላለፋቸው የተነሳ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ጊዜ ያጣሉ፤ ይህም ራሳቸውን ለአምላክ ከመወሰንና ከመጠመቅ ወደኋላ እንዲሉ ያደርጋቸዋል። (ማቴዎስ 13:​22፤ 1 ዮሐንስ 2:​15-17) አመለካከታቸውንና ግባቸውን ቢለውጡ ኖሮ ምንኛ ደስተኛ ይሆኑ ነበር! ወደ ይሖዋ መቅረባቸው በመንፈሳዊ ያበለጽጋቸዋል፣ ከጭንቀት እፎይ እንዲሉ ይረዳቸዋል እንዲሁም የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ሰላምና እርካታ ያስገኝላቸዋል።​—⁠መዝሙር 16:​11፤ 40:​8፤ ምሳሌ 10:​22፤ ፊልጵስዩስ 4:​6, 7

22 ሌሎች ደግሞ ይሖዋን እንደሚወዱ ይናገራሉ ሆኖም በአምላክ ፊት ከተጠያቂነት ነፃ የሚያደርጋቸው ስለሚመስላቸው ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው አይጠመቁም። ይሁን እንጂ ሁላችንም ለአምላክ መልስ እንሰጣለን። የይሖዋን ቃል መስማት ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ ኃላፊነት አለብን። (ሕዝቅኤል 33:​7-9፤ ሮሜ 14:​12) ‘የተመረጠ ሕዝብ’ የነበሩት የጥንት እስራኤላውያን ራሱን ለይሖዋ በወሰነ ብሔር ውስጥ በመወለዳቸው ምክንያት እርሱ በሰጠው መመሪያ መሠረት በታማኝነት የማገልገል ግዴታ ተጥሎባቸው ነበር። (ዘዳግም 7:​6, 11) ዛሬ እንዲህ በመሰለ ብሔር ውስጥ የተወለደ የለም። ሆኖም ትክክለኛ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን ካገኘን በእምነት እርምጃ መውሰድ ያስፈልገናል።

23, 24. ግለሰቦች ምንን በመፍራት ከመጠመቅ ወደኋላ ማለት አይኖርባቸውም?

23 አንዳንዶች በቂ እውቀት የለኝም የሚለው ፍርሃት ከመጠመቅ ወደኋላ እንዲሉ ያደርጋቸው ይሆናል። ሆኖም ‘እውነተኛው አምላክ ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ ማግኘት’ ስለማይችል ሁላችንም መማር የሚኖርብን ገና ብዙ ነገር አለ። (መክብብ 3:​11) ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ እንደ ምሳሌ አድርገን እንመልከት። ወደ ይሁዲነት የተለወጠ እንደመሆኑ መጠን ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች የተወሰነ እውቀት ነበረው፤ ሆኖም የአምላክን ዓላማ በሚመለከት ለሚነሱ ጥያቄዎች በሙሉ መልስ መስጠት ይችላል ማለት አልነበረም። ይሁን እንጂ ይህ ጃንደረባ ይሖዋ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት የመዳን ዝግጅት እንዳደረገ ከተረዳ በኋላ ወዲያውኑ በውኃ ተጠመቀ።​—⁠ሥራ 8:​26-38

24 ሌሎች ደግሞ ቃላችንን ጠብቀን መኖር አንችል ይሆናል በሚል ፍርሃት ራሳቸውን ለአምላክ ሳይወስኑ ይቀራሉ። የ17 ዓመቷ ሞኒክ “እስከ ዛሬ ድረስ ሳልጠመቅ የቆየሁት ራሴን ስወስን ከምገባው ቃል ጋር ተስማምቼ መኖር ቢያቅተኝስ የሚል ፍርሃት ይዞኝ ነው” ብላለች። ይሁን እንጂ በሙሉ ልባችን በይሖዋ ከታመንን ‘መንገዳችንን ያቀናልናል።’ ራሳችንን ለእርሱ የወሰንን ታማኝ አገልጋዮቹ እንደመሆናችን መጠን ‘በእውነት መሄዳችንን’ እንድንቀጥል ይረዳናል።​—⁠ምሳሌ 3:​5, 6፤ 3 ዮሐንስ 4

25. የትኛውን ጥያቄ መመርመር ይኖርብናል?

25 ለይሖዋ ባላቸው የማያወላውል እምነትና ልባዊ ፍቅር ተነሳስተው በየዓመቱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው ይጠመቃሉ። ራሳቸውን የወሰኑ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ለእርሱ ታማኝ ሆነው መኖር እንደሚፈልጉ የታወቀ ነው። ሆኖም የምንኖረው በመጨረሻው ቀን ውስጥ በመሆኑ ልዩ ልዩ የእምነት ፈተናዎች ያጋጥሙናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5) ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን ለመኖር ምን ማድረግ እንችላለን? ይህ በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ የምንመረምረው ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኢየሱስ ኃጢአት ስላልነበረበት የተጠመቀው ንስሐ መግባቱን ለማሳየት አልነበረም። የእርሱ ጥምቀት የአባቱን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን ለአምላክ ማቅረቡን የሚያሳይ ነበር።​—⁠ዕብራውያን 7:​26፤ 10:​5-10

ታስታውሳለህ?

• ክርስቲያናዊ ጥምቀት የሚከናወነው እንዴት ነው?

• አንድ ሰው ለጥምቀት ብቁ እንዲሆን ምን ዓይነት እውቀት ሊኖረው ይገባል?

• እውነተኛ ክርስቲያኖች ከመጠመቃቸው በፊት የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ይኖርባቸዋል?

• አንዳንዶች ለመጠመቅ ወደኋላ የሚሉት ለምንድን ነው? እንዴትስ እርዳታ ሊያገኙ ይችላሉ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” መጠመቅ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?