በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጽኑ ልብ ይሖዋን ማገልገላችሁን ቀጥሉ

በጽኑ ልብ ይሖዋን ማገልገላችሁን ቀጥሉ

በጽኑ ልብ ይሖዋን ማገልገላችሁን ቀጥሉ

“እግዚአብሔር ሆይ፤ ልቤ ጽኑ ነው፤ ልቤ ጽኑ ነው።”​—⁠መዝሙር 57:​7 አ.መ.ት

1. የዳዊትን የመሰለ ጽኑ እምነት ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው?

 ራሳችንን ለእርሱ የወሰንን አገልጋዮቹ በመሆን እውነተኛውን ክርስትና የሙጥኝ ብለን መኖር እንችል ዘንድ ይሖዋ በክርስቲያናዊ እምነት እንድንጸና ሊያደርገን ይችላል። (ሮሜ 14:​4) በዚህም ምክንያት “እግዚአብሔር ሆይ፤ ልቤ ጽኑ ነው” በማለት ለመዘመር እንደተገፋፋው እንደ መዝሙራዊው ዳዊት እኛም ጽኑ እምነት ሊኖረን ይችላል። (መዝሙር 108:​1) ልባችን ጽኑ ከሆነ ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን የገባነውን ቃል ለመፈጸም እንገፋፋለን። መመሪያና ብርታት እንዲሰጠን ወደ እርሱ እየተመለከትን እኛም ‘የጌታ ሥራ ሁልጊዜ እንደበዛላቸው’ ጽኑ አቋም ጠባቂዎች የማንነቃነቅ ከጽኑ አቋማችንና ከእምነታችን ፍንክች የማንል መሆናችንን ማስመስከር እንችላለን።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​58

2, 3. አንደኛ ቆሮንቶስ 16:​13 ላይ ሠፍሮ የሚገኘው የጳውሎስ ማሳሰቢያ ትርጉም ምንድን ነው?

2 ሐዋርያው ጳውሎስ በጥንቷ ቆሮንቶስ ለሚኖሩ የኢየሱስ ተከታዮች “ነቅታችሁ ኑሩ፣ በእምነት ጸንታችሁ ቁሙ፣ እንደ ወንድ ሆናችሁ ወደፊት ግፉ፣ እየጎለበታችሁ ሂዱ” የሚል ጥብቅ ምክር ሰጥቷቸው ነበር። ይህ ማሳሰቢያው ዛሬ ላሉ ክርስቲያኖችም ይሠራል። (1 ቆሮንቶስ 16:​13 NW ) በግሪክኛ እነዚህ ትእዛዛት በአሁን ጊዜ ግሥ ስለተቀመጡ ቀጣይነት ያለውን ድርጊት ያመለክታሉ። ይህ ማሳሰቢያ ያዘለው ትርጉም ምንድን ነው?

3 ዲያብሎስን በመቃወምና ወደ አምላክ ተጠግቶ በመኖር በመንፈሳዊ ‘ነቅተን መኖር’ እንችላለን። (ያዕቆብ 4:​7, 8) በይሖዋ መታመናችን አንድነታችንን ጠብቀን እንድንኖርና ‘በክርስቲያናዊ እምነት ጸንተን እንድንቆም’ ያስችለናል። የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን አምላክን በድፍረት እያገለገልን በመካከላችን የሚገኙ ብዙ ሴቶችን ጨምሮ ሁላችንም ‘እንደ ወንድ ሆነን ወደፊት እንግፋ።’ (መዝሙር 68:​11 NW ) ፈቃዱን ለማድረግ የሚያስችለንን ብርታት እንዲሰጠን ያለማቋረጥ የሰማዩ አባታችንን በመመልከት ‘እየጎለበትን እንሄዳለን።’​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​13 አ.መ.ት

4. ክርስቲያን ለመሆን ከመጠመቃችን በፊት የወሰድናቸው እርምጃዎች የትኞቹ ናቸው?

4 ያለ ምንም ገደብ ራሳችንን ለይሖዋ ወስነን ይህን ውሳኔያችንን በውኃ ጥምቀት ስናሳይ እውነተኛውን እምነት መቀበላችንን የሚያረጋግጥ ነው። ይሁን እንጂ ከመጠመቃችን በፊት የወሰድናቸው እርምጃዎች ምንድን ናቸው? በመጀመሪያ ስለ አምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት አገኘን። (ዮሐንስ 17:​3) ይህ ደግሞ እምነት እንድናዳብርና ቀደም ሲል ለፈጸምነው ስህተት ከልብ ተጸጽተን ንስሐ እንድንገባ አነሳሳን። (ሥራ 3:​19፤ ዕብራውያን 11:​6) ከዚያም ሕይወታችንን ከአምላክ ፈቃድ ጋር ለማስማማት መጥፎ ድርጊቶችን መፈጸም አቆምንና ተለወጥን። (ሮሜ 12:​2፤ ኤፌሶን 4:​23, 24) ከዚያ ቀጥሎ ራሳችንን በሙሉ ልባችን ለይሖዋ መወሰናችንን በጸሎት ገለጽን። (ማቴዎስ 16:​24፤ 1 ጴጥሮስ 2:​21) አምላክ በጎ ሕሊና እንዲሰጠን ልመና በማቅረብ ራሳችንን ለእርሱ መወሰናችንን በጥምቀት አሳየን። (1 ጴጥሮስ 3:​21) ባደረግናቸው በእነዚህ እርምጃዎች ላይ ማሰላሰላችን ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን ለመኖር ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን እንድናስብበትና በጽኑ ልብ ይሖዋን ማገልገላችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።

ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት ጥረት ማድረግህን ቀጥል

5. ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀት መቅሰማችንን መቀጠል የሚገባን ለምንድን ነው?

5 ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን ለመኖር እምነት የሚገነባ የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀት ማግኘታችንን መቀጠል ይገባናል። የአምላክን እውነት መቅሰም በጀመርንበት ጊዜ እንመገብ በነበረው መንፈሳዊ ምግብ ምንኛ ተደስተን ነበር! (ማቴዎስ 24:​45-47) እነዚህ “ምግቦች” ግሩም ጣዕም ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ በመንፈሳዊ ጥሩ አድርገው ገንብተውናል። አሁን ራሳችንን የወሰንን የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ያገኘነውን ጽኑ ልብ ጠብቀን ማቆየት እንችል ዘንድ ገንቢ መንፈሳዊ ምግብ መመገባችንን መቀጠል አስፈላጊ ነው።

6. ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ልባዊ አድናቆት እንድታዳብር እርዳታ ያገኘኸው እንዴት ሊሆን ይችላል?

6 ተጨማሪ የቅዱሳን ጽሑፎችን እውቀት ለማግኘት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ሁኔታው አንድን የተቀበረ ሃብት ለማግኘት ከሚደረግ ከፍተኛ ጥረት ጋር የሚመሳሰል ነው። ሆኖም ‘የአምላክን እውቀት’ ማግኘት ምንኛ የሚክስ ነው! (ምሳሌ 2:​1-6) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስትጀምር አንድ የመንግሥቱ አስፋፊ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ ጥናት ጀምሮልህ ሊሆን ይችላል። እያንዳንዱን ምዕራፍ ለመሸፈን ረጅም ሰዓት ማጥናት ምናልባትም ከአንድ ጊዜ በላይ መገናኘት አስፈልጓችሁ ሊሆን ይችላል። ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የሠፈሩት ጥቅሶች መነበባቸውና መብራራታቸው ጠቅሞሃል። ለመረዳት አስቸጋሪ ሆኖ ላገኘሃቸው ነጥቦች ማብራሪያ ተሰጥቶሃል። መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናህ የነበረው ሰው ጥሩ አድርጎ ይዘጋጅ፣ የአምላክን መንፈስ ለማግኘት ይጸልይና ለእውነት ልባዊ አድናቆት እንዲያድርብህ ይረዳህ ነበር።

7. አንድ ሰው የአምላክን እውነት ለሌሎች ለማስተማር ብቁ የሚያደርገው ምንድን ነው?

7 ጳውሎስ “ቃሉን የሚማር ከሚያስተምረው ጋር መልካምን ነገር ሁሉ ይከፋፈል” በማለት እንደጻፈው ይህ ሁሉ ጥረት መደረጉ የተገባ ነው። (ገላትያ 6:​6) ግሪክኛው ጥቅስ የአምላክ ቃል ትምህርት ‘በሚማረው’ ሰው አእምሮና ልብ ውስጥ መተከሉን ያመለክታል። በዚህ መንገድ መማርህ አንተም በበኩልህ ሌሎችን ለማስተማር ብቁ እንድትሆን አስችሎሃል። (ሥራ 18:​25) ራስህን ለአምላክ ስትወስን የገባኸውን ቃል መፈጸም እንድትችል የአምላክን ቃል ያለማሰለስ በማጥናት መንፈሳዊ ጤንነትህንና ጽናትህን መጠበቅ ይገባሃል።​—⁠1 ጢሞቴ​ዎስ 4:​13፤ ቲቶ 1:​13,  14፤ 2:​2

ንስሐ የገባህና የተመለስክ መሆንህን አስታውስ

8. አምላካዊ ባሕርይን ጠብቆ መኖር የሚቻለው እንዴት ነው?

8 እውነትን ተምረህ፣ ንስሐ ገብተህ ከዚያም በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ባሳደርከው እምነት መሠረት አምላክ ይቅር እንዳለህ በተሰማህ ጊዜ አግኝተኸው የነበረውን የእፎይታ ስሜት ታስታውሳለህ? (መዝሙር 32:​1-5፤ ሮሜ 5:​8፤ 1 ጴጥሮስ 3:​18) መቼም ወደ ቀድሞ የኃጢአት ሕይወት መመለስ እንደማትፈልግ የታወቀ ነው። (2 ጴጥሮስ 2:​20-22) ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ ዘወትር ወደ ይሖዋ መጸለይህ አምላካዊ ባሕርይን እንድትጠብቅ፣ ራስህን ለአምላክ ስትወስን ከገባኸው ቃል ጋር ተስማምተህ እንድትኖርና ይሖዋን በታማኝነት ማገልገልህን እንድትቀጥል ይረዳሃል።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:​11, 12

9. ከኃጢአት ድርጊቶች በመመለስ በየትኛው መንገድ ላይ መጓዝ ይኖርብናል?

9 ከኃጢአት ድርጊቶች በመመለስ የተለወጥህ እንደመሆንህ ያገኘኸውን ጽኑ ልብ ጠብቀህ ለመኖር የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ሳታቋርጥ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። ሁኔታው ቀደም ሲል በተሳሳተ መንገድ ስትጓዝ ከቆየህ በኋላ እምነት የሚጣልበት ካርታ ተመልክተህ በትክክለኛው ጎዳና ላይ መጓዝ የመጀመር ያህል ነው። አሁንም መንገድ እንዳትስት ተጠንቀቅ። በአምላክ መመሪያ ላይ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ መጓዝህን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።​—⁠ኢሳይያስ 30:​20, 21፤ ማቴዎስ 7:​13, 14

ራስህን ለአምላክ የወሰንክና የተጠመቅህ መሆንህን ፈጽሞ አትርሳ

10. ራሳችንን ለአምላክ መወሰናችንን በሚመለከት የትኞቹን ነጥቦች መዘንጋት አይኖርብንም?

10 አምላክን ለዘላለም በታማኝነት ለማገልገል በጸሎት ራስህን ለይሖዋ የወሰንህ መሆንህን ፈጽሞ አትዘንጋ። (ይሁዳ 20, 21) ራስን ለአምላክ መወሰን ለአንድ ቅዱስ ዓላማ ራስን መለየትን ያመለክታል። (ዘሌዋውያን 15:​31፤ 22:​2) አምላክን ለማገልገል ያደረግኸው ውሳኔ ጊዜያዊ ስምምነት ወይም ለሰዎች የገባኸው ግዴታ አይደለም። ለአጽናፈ ዓለሙ የበ​ላይ ገዥ ለዘለቄታው የገባኸው ቃል ሲሆን ከገባኸው ቃል ጋር ተስማምተህ ለመኖርም ዕድሜ ልክ ለአምላክ ታማኝ መሆንን ይጠይቃል። አዎን፣ ‘ብንኖርም ብንሞትም የይሖዋ ነን።’ (ሮሜ 14:​7, 8) ደስታ ማግኘታችን ለፈቃዱ ራሳችንን በማስገዛታችንና በጽኑ ልብ እሱን ማገልገላችንን በመቀጠ​ላችን ላይ የተመካ ነው።

11. ጥምቀትህንና ጥምቀትህ ያዘለውን ትርጉም ማስታወስ የሚኖርብህ ለምንድን ነው?

11 አምላክን ለማገልገል ከልብ በመነጨ ስሜት ያደረግኸውን ውሳኔ በጥምቀት ያሳየህ መሆንህን ፈጽሞ አትርሳ። ውሳኔውን ያደረግከው አንተው ራስህ ስለሆንክ የተጠመቅከው ተገድደህ አይደለም። በቀሪው ሕይወትህ የአንተን ፈቃድ ከአምላክ ፈቃድ ጋር አስማምተህ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል? አምላክ በጎ ሕሊና እንዲሰጥህ ከጸለይህ በኋላ ለእርሱ ያደረግከውን ውሳኔ በመጠመቅ አሳየህ። ራስህን ለአምላክ ስትወስን የገባኸውን ቃል በመፈጸም ያገኘኸውን ይህን በጎ ሕሊና ጠብቅ፤ ይህም የይሖዋን የተትረፈረፈ በረከት ያስገኝልሃል።​—⁠ምሳሌ 10:​22

የአንተም ፈቃድ ድርሻ አለው

12, 13. የራሳችን ፈቃድ ራሳችንን ለአምላክ ከመወሰናችንና ከመጠመቃችን ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?

12 ራስን ለአምላክ መወሰንና መጠመቅ በመላው ምድር ለሚኖሩ በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ታላቅ በረከት አስገኝቶላቸዋል። ራሳችንን ለአምላክ የወሰንን መሆናችንን በውኃ ጥምቀት ስናሳይ ለቀድሞ አኗኗራችን ብንሞትም ለራሳችን ፈቃድ ግን ሞተናል ማለት አይደለም። ተገቢውን እውቀት ያገኘን አማኞች እንደመሆናችን መጠን ራሳችንን መወሰናችንን ለአምላክ በጸሎት ስንገልጽና ስንጠመቅ በእርግጥም የገዛ ራሳችንን ፈቃድ ማድረጋችን ነበር። ራስን ለአምላክ መወሰንና መጠመቅ የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለይቶ ማወቅንና ይህንንም ሆነ ብሎ መምረጥን የሚጠይቅ ነው። (ኤፌሶን 5:​17) በዚህ መንገድ፣ በገዛ ፈቃዱ የአናጢነት ሙያውን እርግፍ አድርጎ ትቶ የተጠመቀውንና የሰማያዊ አባቱን ፈቃድ ለመፈጸም ራሱን ሙሉ በሙሉ ያስጠመደውን የኢየሱስን ምሳሌ እንኮርጃለን።​—⁠መዝሙር 40:​7, 8፤ ዮሐንስ 6:​38-40

13 ይሖዋ አምላክ ልጁ ‘በመከራ ፍጹም’ እንዲሆን ዓላማው ነበር። ስለሆነም ኢየሱስ እንዲህ ያለውን መከራ በታማኝነት ለመወጣት የራሱን ፈቃድ መጠቀም ነበረበት። ይህንንም ዳር ለማድረስ “ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፣ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት።” (ዕብራውያን 2:​10, 18፤ 5:​7, 8) እኛም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አክብሮታዊ ፍርሃት ለአምላክ የምናሳይ ከሆነ ጸሎታችን ‘እንደሚሰማልን’ እና ራሳችንን የወሰንን ምሥክሮቹ እንደመሆናችን መጠን ይሖዋ እንደሚያጸናን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።​—⁠ኢሳይያስ 43:​10

ጽኑ ልብ ይዘህ መኖር ትችላለህ

14. መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ ያለብን ለምንድን ነው?

14 ጽኑ ልብ በመያዝ ራስህን ለአምላክ ስትወስን ከገባኸው ቃል ጋር ተስማምተህ ለመኖር ምን ሊረዳህ ይችላል? ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደውን የአምላክ ቃል እውቀት ማግኘት ትችል ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ አንብብ። “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንዲህ እንድናደርግ ያለማቋረጥ ያሳ​ስበናል። ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምቶ መኖር በአምላክ እውነት ውስጥ መጓዝን የሚጠይቅ በመሆኑ እንዲህ ያለው ምክር መሰጠቱ አስፈላጊ ነው። የይሖዋ ድርጅት ሆን ብሎ የሐሰት ትምህርቶችን የሚያስፋፋ ቢሆን ኖሮ የይሖዋ ምሥክሮችም ሆኑ እነርሱ የሚሰብኩላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡ ምክር አይሰጥም ነበር።

15. (ሀ) ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ምን ነገር ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል? (ለ) ሰብዓዊ ሥራ የአንድ ክርስቲያን ተቀዳሚ ሥራ አይደለም ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

15 ማንኛውንም ውሳኔ በምታደርግበት ጊዜ ራስህን ለይሖዋ ስትወስን የገባኸውን ቃል ለመፈጸም የምታደርገውን ጥረት እንዴት ሊነካብህ እንደሚችል ማጤን ይኖርብሃል። ይህ ከሰብዓዊ ሥራህ ጋር ሊያያዝ ይችላል። ሥራህ እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት የሚረዳህ እንዲሆን ጥረት ታደርጋለህ? በጥቅሉ ሲታይ አሠሪዎች ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖች እምነት የሚጣልባቸውና ውጤታማ ሠራተኞች መሆናቸውን ከመገንዘባቸው ባሻገር የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ውስጥ እውቅና የማግኘት ምኞት የተጠናወታቸው እንዳልሆኑና የተሻለ ክፍያ የሚያስገኝ ቦታ ለማግኘት ሲሉ ከሌሎች ጋር እንደማይፎካከሩ ያውቃሉ። ይህ የሆነበት ምክንያት የምሥክሮቹ ግብ ሃብት፣ ዝና፣ ክብር ወይም ሥልጣን ማሳደድ ስላልሆነ ነው። ራሳቸውን ለአምላክ ሲወስኑ ከገቡት ቃል ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ክርስቲያኖች ቅድሚያ የሚሰጡት መለኮታዊውን ፈቃድ ማድረግን ነው። ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት የሚሠሩት ሰብዓዊ ሥራ ሁለተኛ ቦታ የሚይዝ ነው። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ ተቀዳሚ ወይም ዋነኛ ሥራቸው ክርስቲያናዊ አገልግሎታቸው ነው። (ሥራ 18:​3, 4፤ 2 ተሰሎንቄ 3:​7, 8፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:​8) አንተስ በሕይወትህ ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ የምትሰጠው ለመንግሥቱ ጉዳዮች ነው?​—⁠ማቴዎስ 6:​25-33

16. ከልክ ያለፈ ጭንቀት ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን እንዳንኖር እንቅፋት ቢሆንብን ምን ማድረግ እንችላለን?

16 አንዳንዶች እውነትን ከማወቃቸው በፊት በተለያዩ ጭንቀቶች ተውጠው ሊሆን ይችላል። ሆኖም የመንግሥቱን ተስፋዎች ሲሰሙ ልባቸው በታላቅ ደስታ፣ ምስጋናና ለአምላክ ባላቸው ፍቅር ተሞላ! ከዚያን ጊዜ ወዲህ ያገኟቸውን የተለያዩ በረከቶች መለስ ብለው ማሰባቸው ራሳቸውን ለይሖዋ ሲወስኑ ከገቡት ቃል ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ በእጅጉ ሊረዳቸው ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ እሾህ ቡቃያው አድጎ በደንብ እንዳያፈራ እንደሚያደርገው ሁሉ በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚያጋጥሙ የተለመዱ ችግሮች የሚያስከትሉት ከልክ ያለፈ ጭንቀት ‘የአምላክን ቃል’ ቢያንቅብህስ? (ሉቃስ 8:​7, 11, 14፤ ማቴዎስ 13:​22፤ ማርቆስ 4:​18, 19) በአንተ ወይም በቤተሰብህ ላይ እንዲህ ያለ ነገር መታየት እንደጀመረ ካስተዋልክ ጭንቀትህን በይሖዋ ላይ በመጣል በፍቅርና በአድናቆት እያደግህ እንድትሄድ እንዲረዳህ ጸልይ። ሸክምህን በእርሱ ላይ የምትጥል ከሆነ በጽኑ ልብ እሱን በደስታ ማገልገልህን እንድትቀጥል ደግፎ ያቆምሃል እንዲሁም ብርታት ይሰጥሃል።​—⁠መዝሙር 55:​22፤ ፊልጵስዩስ 4:​6, 7፤ ራእይ 2:​4

17. የሚያጋጥሙንን ከባድ ፈተናዎች ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?

17 ራስህን ለአምላክ ስትወስን እንዳደረግኸው ሁሉ ዘወትር ወደ ይሖዋ አምላክ ሳታሰልስ ጸልይ። (መዝሙር 65:​2) ስህተት እንድትፈጽም ስትፈተን ወይም ከባድ ፈተና ሲያጋጥምህ አምላክ መመሪያ እንዲሰጥህና መመሪያውን መከተል እንድትችል እንዲረዳህ ለምነው። እምነት አስፈላጊ መሆኑን አትርሳ። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብም እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከእናንተ ግን ማንም [ፈተናን መቋቋም የሚያስችል] ጥበብ ቢጐድለው፣ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፣ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው።” (ያዕቆብ 1:​5-8) አንድ ፈተና ከአቅማችን በላይ እንደሆነ ከተሰማን “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፣ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል” የሚለውን ማረጋገጫ እናስታውስ።​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:​13

18. የተሰወረ ከባድ ኃጢአት ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን ለመኖር ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ቢያዳክምብን ምን ማድረግ እንችላለን?

18 በስውር የፈጸምከው ከባድ ኃጢአት ሕሊናህን ቢረብሽህና ራስህን ለአምላክ ስትወስን ከገባኸው ቃል ጋር ተስማምቶ ለመኖር ያደረግከውን ቁርጥ ውሳኔ ቢያዳክምብህስ? ንስሐ የምትገባ ከሆነ ይሖዋ ‘የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እንደማይንቅ’ ማወቅህ ሊያጽናናህ ይችላል። (መዝሙር 51:​17) የይሖዋን ምሳሌ የሚከተሉት አፍቃሪ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከሰማያዊው አባትህ ጋር የነበረህን ወዳጅነት እንደገና ለማደስ ያለህን ፍላጎት አቅልለው እንደማይመለከቱት አውቀህ እርዳታ እንዲሰጡህ ጠይቅ። (መዝሙር 103:​10-14፤ ያዕቆብ 5:​13-15) ከዚያም የምታገኘው መንፈሳዊ ጥንካሬና ጽኑ ልብ ለእግርህ ቀና መንገድ እንድታደርግና ራስህን ለአምላክ ስትወስን ከገባኸው ቃል ጋር ተስማምተህ እንድትኖር ያስችልሃል።​—⁠ዕብራውያን 12:​12, 13

በጽኑ ልብ ማገልገላችሁን ቀጥሉ

19, 20. ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን መኖራችንን መቀጠላችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

19 በዚህ አስጨናቂ ዘመን ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን መኖርና በጽኑ ልብ አምላክን ማገልገላችንን ለመቀጠል ብርቱ ትግል ማድረግ ይገባናል። ኢየሱስ “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:​13) “በመጨረሻው ቀን” እንደመኖራችን መጠን መጨረሻው በማንኛውም ጊዜ ሊመጣ ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) ከዚህም በላይ ማንኛችንም ብንሆን ነገን በሕይወት ስለመኖራችን በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። (ያዕቆብ 4:​13, 14) ስለዚህ ዛሬ ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን መኖራችን እጅግ አስፈላጊ ነው!

20 ሐዋርያው ጴጥሮስ በሁለተኛ መልእክቱ ላይ ይህን ጉዳይ ጎላ አድርጎ ገልጿል። አምላካዊ አክብሮት ያልነበራቸው ሰዎች በጥፋት ውኃ እንደጠፉ ሁሉ ምሳሌያዊው ምድር ወይም ክፉው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ “በይሖዋ ቀን” [NW ] ተጠራርጎ እንደሚጠፋ ገልጿል። ስለሆነም ጴጥሮስ “በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል?” በማለት ጠይቋል። እንዲሁም “ወዳጆች ሆይ፣ ይህን አስቀድማችሁ ስለምታውቁ፣ በዓመፀኞቹ [በሐሰት አስተማሪዎችና ለአምላክ አክብሮት በሌላቸው ሰዎች] ስሕተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ” በማለት በጥብቅ አሳስቧቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:​15-17) አንድ የተጠመቀ ክርስቲያን ከትክክለኛው ጎዳና ቢወጣና በጽኑ ልብ መኖር አቁሞ ሳለ ሕይወቱ ወይም ሕይወቷ ቢቀጭ ወይም ብትቀጭ ምንኛ የሚያሳዝን ይሆናል!

21, 22. የመዝሙር 57:​7 ቃላት በዳዊትና በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ እውነት መሆኑ የታየው እንዴት ነው?

21 የተጠመቅክበትን አስደሳች ዕለት መለስ ብለህ የምታስብና ቃልህና ድርጊትህ የአምላክን ልብ የሚያስደስት እንዲሆን የአምላክን እርዳታ የምትፈልግ ከሆነ ራስህን ለአምላክ ስትወስን ከገባኸው ቃል ጋር ተስማምተህ ለመኖር ያደረግኸው ውሳኔ ይበልጥ ይጠናከራል። (ምሳሌ 27:​11) ይሖዋ ሕዝቡን ፈጽሞ አይጥልም። እኛም ለእርሱ ታማኝ ሆነን መገኘት ይገባናል። (መዝሙር 94:​14) ጠላቶቹ የሸረቡበትን ደባ አክሽፎ ከእጃቸው በማዳን ለዳዊት ምሕረትና ርኅራኄ አሳይቶታል። ዳዊት አዳኙ ለሆነው አምላክ ያለው ፍቅር ጽኑና የማያወላውል መሆኑን በመናገር ለዚህ ያለውን አመስጋኝነት ገልጿል። “እግዚአብሔር ሆይ፤ ልቤ ጽኑ ነው፤ ልቤ ጽኑ ነው፤ እቀኛለሁ፤ አዜማለሁ” በማለት ከልብ በመነጨ ስሜት ዘምሯል።​—⁠መዝሙር 57:​7 አ.መ.ት

22 እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደ ዳዊት ሁሉ ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር ፈጽሞ አያላሉም። በጽኑ ልብ ይሖዋ አዳኛቸውና ጠባቂያቸው መሆኑን በመግለጽ የውዳሴ መዝሙር ለእርሱ ይዘምራሉ። ጽኑ ልብ ካለህ በአምላክ ላይ ትመካለህ፤ በእርሱ እርዳታም ራስህን ለአምላክ ስትወስን የገባኸውን ቃል መፈጸም ትችላለህ። አዎን፣ አንተም “ከክፉ ነገር አይፈራም፤ በእግዚአብሔር ለመታመን ልቡ የጸና ነው” በማለት መዝሙራዊው እንደተቀኘለት ‘ጻድቅ ሰው’ መሆን ትችላለህ። (መዝሙር 112:​6, 7) አምላክን በማመንና በእርሱ ላይ ሙሉ በሙሉ በመመካት ራስህን ለአምላክ ስትወስን ከገባኸው ቃል ጋር ተስማምተህ መኖርና በጽኑ ልብ ይሖዋን ማገልገልህን መቀጠል ትችላለህ።

ታስታውሳለህ?

• የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት መቅሰማችንን መቀጠል የሚገባን ለምንድን ነው?

• ንስሐ የገባንና የተለወጥን መሆናችንን መዘንጋት የማይገባን ለምንድን ነው?

• ራሳችንን ለአምላክ የወሰንንና የተጠመቅን መሆናችንን በማስታወስ የምንጠቀመው እንዴት ነው?

• ይሖዋን በጽኑ ልብ ማገልገላችንን እንድንቀጥል ምን ሊረዳን ይችላል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክን ቃል በየዕለቱ በማንበብ መንፈሳዊ ጤንነትህን ትጠብቃለህ?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያናዊውን አገልግሎት ዋነኛው ሥራችን ማድረጋችን ይሖዋን በጽኑ ልብ ማገልገላችንን እንድንቀጥል ይረዳናል